በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ መከሰቱ በይፋ ከተገለፀ ጀምሮ በሽታው እንዳይስፋፋ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው:: ከዚህም ጎን ለጎን ለበሽታው ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉ ሰዎችን በለይቶ ማቆያ እንዲቀመጡ በማድረግና ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸውን በመመርመር በየቀኑ ህብረተሰቡ እንዲያውቀው እየተደረገ ነው::
ከዚህ ጥረት ጎን ለጎንም የጤና ባለሙያዎች በአንድ ላይ ተሰባስበው ቫይረሱ በህብረተሰቡ ውስጥ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት የመገመት እንዲሁም በምን መልኩ መቆጣጠር እንደሚቻልና በተለይም በሽታውን በመከላከል የተያዙትንም በማከም ከፍተኛ ሃላፊነት የተጣለባቸውን የጤና ባለሙያዎች ደህንነት እንዲጠበቅ በማድረግና ህብረተሰቡም ትክክለኛ መረጃን አግኝቶ ከቫይረሱ ራሱን መጠበቅ እንዲችል ብሔራዊ አማካሪ ምክር ቤት ተቋቁሞ እየሠራ ይገኛል::
የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በአገር አቀፍ ደረጃ በበርካታ የጤና ባለሙያዎች ሕብረት የተቋቋመው አማካሪ ምክር ቤት ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ተግባር ይግዛው የዛሬ የተጠየቅ አምድ እንግዳችን ናቸው::
አዲስ ዘመን ፦ አማካሪ ምክር ቤቱ በዋናነት እየሠራቸው ያሉት ሥራዎች ምንድን ናቸው?
ዶክተር ተግባር፦ የዓለም ጤና ድርጅት ኮሮና ወረርሽኝ ነው ብሎ ካወጀና ቫይረሱ ብዙ የዓለም አገራትን እያጠቃ መሆኑ ከተገለፀ ጊዜ ጀምሮ የሙያ ማህበራት ከጤና ሚኒስቴር ጋር መተባበር ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሁሉም ድርሻ እንደሚያስፈልግ መግባባት ላይ በመደረሱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሙያ ማህበራት ጋር ለመሥራት እንዲችል አማካሪ ምክር ቤት አቋቁሟል:: ምክር ቤቱ ብዙ የህክምና ሙያ ማህበራትን ያቀፈ በመሆኑ እኛም በሙያችን ምን ልንሠራ እንችላለን? በሚለው ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ አንዱና የመጀመሪያው ሥራ የሆነው በሽታው ለዓለማችንም ይሁን ለአገራችን የጤና ሥርዓት አዲስ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ስለ በሽታው ባለሙያውን ማስተማርና ማዘጋጀት ነበር:: በዓለም ጤና ድርጅት የተዘጋጀውን የማሰልጠኛ ማንዋል በማየትና ወደ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በመመለስ አሰልጣኞች በማዘጋጀት መጀመሪያ አዲስ አበባ ላይ 600 ለሚሆኑ አዲስ ለተቀጠሩ ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠትም ይፋዊ ሥራውን ጀምሯል::
በሌላ በኩልም በፌዴራል ደረጃ ያሉ ትልልቅ ሆስፒታሎችን ጨምሮ በክልል ያሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ባለሙያዎችን የአሰልጣኞች ስልጠና የመስጠት ሥራው በመከናወን ላይ ነው::
ቫይረሱ ከሰው ወደሰው የሚተላለፍ በመሆኑ ህብረተሰቡን ስለ በሽታውና መደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ ማስተማር ያስፈልጋል፤ መንግሥት ደግሞ ሳይንሳዊ የሆኑና በምርምር የተደገፉ የቅድመ ጥንቃቄ ርምጃዎች መውሰድ አለበት በሚል ለመንግሥትም ምክረ ሃሳብ የመስጠት ሥራም እየተሠራ ነው::
በተለይም አማካሪ ምክር ቤቱ ጤና ሚኒስቴርን በተደራጀ መልኩ እንዲደግፍ በሰባት ቡድን የማደራጀት ሥራ ተከናውኗል::
አዲስ ዘመን፦ የሰባቱ ቡድኖች አስፈላጊነት ምንድን ነው ?
ዶክተር ተግባር፦ ሰባት የሆነው ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮችን ለመሸፈን ነው:: ለምሳሌ ህብረተሰቡ ስለ ወረርሽኙ ተገቢውን እውቀት እንዲያገኝ ማስተማር እራሱን፣ አካባቢውንና ወገኑን እንዲጠብቅ ማንቀሳቀስ የሚል ቡድን አለ፤ ጤና ተቋሞቻችን ታመው የሚመጡ ሰዎችን በቂ የህክምና አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ማዘጋጀት ለዚህም የሚሆኑ መመሪያዎችን ማሟላት ስለሚያስፈልግ ይህንን የሚሠራ ሁለተኛ ቡድን፤ አሰሳ ቅኝትና በሽታው ካለባቸው ሰዎች ጋር የተገናኙ ሰዎችን ማፈላለግ የሚሠራ ቡድን፤ ከታካሚ ወደ ባለሙያ ወይንም ደግሞ ከባለሙያም ወደ ሌላ ባለሙያ ቫይረሱ እንዳይተላለፍ መከተል ያለብን መንገዶች ምንድን ናቸው የሚለውን የሚለይና የሚያማክር ቡድን፤ ወረርሽኝ ሲሆን ከወትሮ በተለየ ማለትም ልክ እንደ ጦርነት በመሣሪያ በግብዓት በመድሃኒትና በሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን የሚሠራውስ
በጣም የተቀናጀ መሆን ስላለበት ይህንን የሚያግዝ ቡድን፤ የሚሠሩ ሥራዎች ሁሉ በመረጃ ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችንና ጥናቶችን በማየት ለእኛ አገር የሚጠቅሙ ልምዶችን መውሰድ በአገር ውስጥ በመንግሥትና በሌሎች አካላት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ምንዓይነት ከፍተት እንዳለባቸው መለየት የሚያስችልና መረጃ የሚያጠናቅር ቡድኖችን ያቀፉ ናቸው::
የሰባቱ ቡድኖች ዝርዝር ሥራና ዓላማ ኢትዮጵያ ውስጥ ወረርሽኙን ተከትሎ የሚሠራው ሥራ በሳይንስና በምርምር ላይ መሠረት ያደረገ እንዲሆን ማገዝ ነው:: ዓለም አቀፍ ጠንካራ ተሞክሮዎችን እያመጡ ለመንግሥት የፖሊሲ ምክረ ሃሳብ ማቅረብ ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ጠንካራና ደካማ ጎን በመለየት መሻሻል የሚገባቸውን በማየት አሁንም ለመንግሥት ምክረ ሃሳብ መስጠት ነው:: ሌላውና ዋናው ሥራ ጤና ሚኒስቴር የሚፈልጋቸውን መመሪያዎች ማዘጋጀት፤ የተዘጋጁትንም የመገምገምና ወቅታዊነታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ጉድለታቸውን በመሙላት ማገዝ ነው ::
አዲስ ዘመን፦ አማካሪ ምክር ቤቱ እየሠራ ባለው ሥራ ውጤታማ ነው ?
ዶክተር ተግባር፦ እንደዚህ ዓይነት ወረርሽኝ ሲመጣ ሰዎች ቤታቸው ቁጭ በሉ ሲባሉ የሚፈጠር መረበሽ፣ ቤተክርስቲያንና መስጊድ መሄድ አለመቻል፣ እንደ ልብ ደስታም ሆነ ሀዘንን ሰብሰብ ብሎ ማክበር አለመቻል፣ ለጤና ችግሮች መጋለጥ፣ ጭንቀት፣ ፍርሃትና ድንጋጤ ያመጣልና ከዚህ አንፃር ይህንን የሚደግፍ የሥነ ልቦናና የሥነ አዕምሮ ድጋፍ አማካሪ ምክር ቤት አለ:: ለምሳሌ ይህ ቡድን የሠራውን ብናይ ወደ 8335 የስልክ ጥሪ ለሚያደርጉ ሰዎች የመጀመሪያ ደረጃ የሥነ ልቦና ዕርዳታ ለማድረግ የሚያስችል መመሪያ ማዘጋጀት ተችሏል::
በዓለም ላይ እንደምናየው ወረርሽኙ ህዝቡን ብቻ ሳይሆን የጤና ባለሙያዎችንም በከፍተኛ ሁኔታ እያጠቃና ለህልፈተ ህይወት እየዳረጋቸው ነው፤ ሆኖም ከሞት ውጭም ቢሆን ሥራው በአካልም በአዕምሮም በጣም ጫና የሚፈጥርና አስፈሪ ነገር ስለሆነ በበሽታው መያዝ ብቻ ሳይሆን ለጭንቀትና ለድብርት ይጋለጣሉ፤ ስለዚህ ባለሙያዎች አገልግሎት ሲሰጡ ራሳቸውን እንዲጠብቁ የሚያስችል መመሪያ (ማንዋል) ተዘጋጅቷል::
የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) በአገር ውስጥ እጥረት አለ፤ ለማህበረሰቡም እየመከረን ያለነው በአገር ውስጥ የሚሠሩ አልያም በቤት ውስጥ የሚዘጋጁትን እንዲጠቀም ነው፤ ሆኖም እዚህም ላይ አሠራሩ ሊያሟላቸው የሚገቡ ደረጃዎች አሉና እነዚህ ምንድን ናቸው ? የሚለውን አማካሪ ምክር ቤቱ አዘጋጅቶ ለጤና ሚኒስቴር ሰጥቷል::
ለኢኖቬሽን ሚኒስቴርና ለህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለሙያዎች እራሳቸውን ለመጠበቅ የሚጠቀሙበትን መሣሪያዎች ምን ዓይነት ቅድመ ሁኔታ (ስታንዳርድ) ሊኖረው ይገባል? የሚለውን በሳይንሳዊ መረጃ አጣምሮ አዘጋጅቶ አቅርቧል::
በሽታው አዲስ እንደመሆኑ መጠን የጤና ተቋማት በቫይረሱ የሚጠረጠርን ሰው በምን አይነት አግባብ ነው የምንቀበለው? ምን ዓይነት ህክምናና እንክብካቤን ነው ማግኘት ያለባቸው? የሚሉትን መመሪያዎች አዘጋጅተናል የነበሩትንም በመገምገምና በማሻሻል ላይ ነን ::
አዲስ ዘመን፦ አማካሪ ምክር ቤቱ ጥሩ ድጋፎችን እያደረገ፤ ምክረ ሐሳቦችንም እየለገሰ ነው፤ ነገር ግን አሁን ያለንበት የመመርመር አቅም ውስን ይመስላልና በዚህስ ረገድ ምክረ ሐሳቦችን ለመስጠት ሞከራችሁ?
ዶክተር ተግባር፦ ብዙ ሰው እየመረመርንና በሚፈለገው ደረጃ እየሄድን አይደለንም:: በየቀኑ የምንመረምረውን የሰው ቁጥር ከፍ ማድረግ ይገባል:: ብዙ ቁጥር ያለው ሰው መመርመር አለብን በሚል ብቻ ያለችውን የመመርመሪያ ግብዓት ለመጣው ሁሉ መጠቀም የለብንም፤ ቅድሚያ ሊሰጣቸውና ለቫይረሱ ከፍተኛ ተጋላጭነው ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ትኩረት መስጠት ይገባል:: ይህንን ማድረግ ካልቻልን በትክክል መድረስ ያለብን ሰው ዘንድ ላንደርስ እንችላለን::
ለቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ የሆኑት እነማን ናቸው? ቁጥሩን ከፍ ለማድረግ ምን ዓይነት ሰትራተጂ መከተል ያስፈልጋል? የሚለውን አማካሪ ምክር ቤቱ አዘጋጅቶ ለጤና ሚኒስቴር አስረክቧል:: ሌላው ወረርሽኙን በመተንበይ በኩል ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ስንት ሰው ሊያጠቃ ይችላል? በከተማ፣ በገጠር፣ በአገር አቀፍ፣ እንዲሁም በክልል ደረጃ ፤ እንደገናም ደግሞ ምን ዓይነት እርምጃዎች ቢወሰዱ የወረርሽኙን ሥርጭት መከላከል ይቻላል፤ ውጤቱስ ምን ይመስላል? የሚለውን ሠርተን ከጤና ሚኒስቴር ጋር እየተወያየን ነው::
በአሁኑ ወቅት አሜሪካን አገር ካለ ተመሳሳይ አማካሪ ምክር ቤት ጋር ተቀናጅተን እየሠራ በመሆኑ ባለሙያዎቻችን የሚያምኑትና በፈለጉት ጊዜ የሚያገኙት የመረጃ ምንጭ እንዲኖራቸው የኢትዮጵያ የህክምና ማህበር ድረ ገጽ ለዚህ አገልግሎት ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል:: በዚህም ስለ ቫይረሱ ሳይንሳዊ የሆኑ፣ የተመረጡና የተመጠኑ አዳዲስ መረጃዎችን እንዲያገኙ ሥራዎች ተጀምረዋል::
አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ ካላት የህዝብ ቁጥር አንፃር በአሁኑ ወቅት እየመረመረች ያለው መጠን አላነሰም?
ዶክተር ተግባር፦ ከጀመርንበት ጊዜ አንፃር ስናየው ቁጥሩ እየጨመረ መጥቷል፤ ካለን የህዝብ ቁጥር፣ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ካሉበት ደረጃና ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ከሚያስችለው አንፃር ስናየው እየመረመርን ያለነው የሰው ቁጥር ዝቅተኛ ነው::
ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ ወደ 200 ሺህ የሚጠጋ ሰው መርምራለች፤ የህዝብ ቁጥሯ ግን 59 ሚሊየን ነው:: ጋና በተመሳሳይ የህዝብ ቁጥሯ 30 ሚሊየን ቢሆንም የመረመረችው ወደ 100 ሺህ የሚጠጋ ሰው ነው:: ከዚህ አንፃር እየመረመርን ያለው መጠን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም:: በእኛ የህዝብ ቁጥር ደረጃ በቀን ቢያንስ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች መመርመር አለብን:: የበሽታው ሥርጭት ብዙ ወይም ትንሽ ነው ማለት የሚቻለው ብዙ ሰው ከተመረመረ በኋላ ነው:: እስከ አሁን የመረመርነው 17 ሺህ ገደማ ነው ካለን የህዝብ ቁጥር አንፃር ስናየው ኢትዮጵያ ውስጥ በቂ የላብራቶሪ ምርመራ እየተደረገ አይደለም፤ ለጤና ሚኒስቴርም ለህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም በተደጋጋሚ እያሳሰብን ነው:: በተቻለ መጠን የምንመረምረውን ቁጥር ማሳደግ አለብን በአጭር ጊዜ ውስጥ በቀን አምስት ሺህ፤ ቀጥሎ አስር ሺህ ማድረስ የግድ ነው ብለን መክረናል::
በነገራችን ላይ አቅማችን የተለያየ ቢሆንም ያደጉት አገራት በቀን በርካታ ሰው ይመረምራሉ፤ ለምሳሌ እንግሊዝ በቀን 70 ሺህ ሰው ትመረምራለች:: በጥቂት ቀናት ውስጥ በቀን 100 ሺህ ሰው ለመመርመር ጥረት እያደረጉ ነው፤ ይህንን ደግሞ ከህዝብ ብዛት አንፃር ካሰብነው የእኛን ያህል አይደሉም:: ስለዚህ ላብራቶሪ ምርመራው ወደኋላ ቀርቷል::
መልካሙ ነገር የበሽታው ሥርጭት ሲጀምር አዲስ አበባ ላይ እንኳን ምርመራ አልነበረም፤ አሁን በበርካታ የክልል ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ላይ በማስጀመር ቁጥሩም ከ20 በላይ ደርሷል፤ በቅርቡም 30 እንደሚደርሱ መረጃው አለኝ::
ይህም ቢሆን ግን ሁሉም እየመረመሩ አይደለም:: ለምንድን ነው የማይመረምሩት? ለሚለው የተለያየ ምክንያት ማቅረብ ይቻል ይሆናል፤ ማናልባትም የሰው ሃይልና የግብዓት እጥረት ደግሞ ተጠቃሽ ነው:: ግን እነዚህ ምክንያቶች ለእኔ ትልቅ አይደሉም:: ይልቁንም መንግሥት ቶሎ ችግሮቹ ተቀርፈው ምርመራው እንዲጀመር መደረግ አለበት::
አዲስ ዘመን፦ ስለዚህ አለመመርመራችንም ሊሆን ይችላል በየቀኑ የምንሰማው የተጠቂዎችን ቁጥር ዝቅተኛ ያደረገው ማለት ነው?
ዶክተር ተግባር ፦ ሳንመረምር የተጠቂው ቁጥር ትንሽ ነው ማለት አይቻልም:: በስፋት ብዙ ቁጥር ያለውን ሰው ከመረመርን በኋላ የምናገኘው ውጤት ትንሽ ከሆነ መልካም ነው፤ የሠራነው ሥራ ውጤታማ ሆኗል ወይም እድለኛ ሆነን ብዙ ሰው አልተጠቃብንም ልንል እንችላለን:: ሳንመረምር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የተጠቂው ሰው ቁጥር ትንሽ ነው ማለት አንችልም:: ሌላው ደግሞ በላብራቶሪዎቻችንን ጥራትም እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል፤ ለምሳሌ መቶ ሰው መርምረን የተገኘው ውጤት ልክ መሆኑ የሚረጋገጥበት ሥርዓት ከሌለ ላብራቶሪው የነገረንን ብቻ መውሰድ ግዴታ ይሆናል:: በመሆኑም ከላብራቶሪ ጥራት ጋር ተያይዞ ያለው ነገርም ሊታይ ይገባል::
አዲስ ዘመን፦ ምርመራ ሊደረግበት የሚችል አካባቢንና የሚመረመሩትን የመለየት ሁኔታስ እንዴት እየታየ ነው?
ዶክተር ተግባር፦ ማንን እየመረመርን ነው የሚለው ነገር መታየት ያለበት ነው፤ በበሽታው የመጋለጥ ዕድል ያላቸው ሰዎች በህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተዘጋጀ ፕሮቶኮል ቢኖርም እሱንም መፈተሽ ያስፈልጋል፤ በትክክል ለበሽታው የተጋለጡ አካላትን ሁሉ እየመረመርን ነውን? ምርመራ እየተደረገበት ያለው ቦታና ምናልባትም በሽታው የተሰራጨበት አካባቢ ይለያይ ይሆን? የሚለውን መመልከትም ያስፈልጋል::
አዲስ ዘመን፦ ይህንን ወረርሽኝ ለመቆጣጣር ለኢትዮጵያ አዋጭ የሆነው መንገድ የትኛው ነው ይላሉ?
ዶክተር ተግባር፦ በየትኛውም አገር ቢሆን ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ወሳኝ ከሚባሉ ነገሮች መካከል ግንባር ቀደሙ ምርመራ ነው:: ወረርሽኙ ከሰው ወደሰው የሚዛመት እንደመሆኑ በሽታው ያለባቸውን ሰዎች መመርመርና በፍጥነት መለየት ካልቻልን በሽታው መዛመቱን ይቀጥላል:: በመሆኑም በበቂ ቁጥርና በስፋት እንዲሁም ጥራት ባለው የላብራቶሪ ሥርዓት ብዙ ሰው መመርመር ያስፈልጋል:: ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ በስፋት እየተሠራ አይደለም::
ሌላው የበሽታው አንዱ መተላለፊያ መቀራረብ በመሆኑ ሰዎች እርቀታቸውን እንዲጠብቁ ማድረግ ያስፈልጋል:: ይህም ቢሆን ግን አሁን እንደሚታየው ርቀትን መጠበቅ ህብረተሰቡም በሚፈለገው መንገድ ተግባራዊ ያላደረገው፤ መንግሥትም በተገቢው ሁኔታ ሊቆጣጠረው ያልቻለው ነገር ነው:: ስለዚህ ሰዎች የህልውና ጉዳይ ካልሆነባቸው በስተቀር ከቤት ባይወጡ፤ ግዴታ መውጣት ሲያስፈልግ ደግሞ ከሰዎች ራቅ ማለት፣ እጅን በሣሙናና በውሃ መታጠብ፤ ሰዎች በሚበዙባቸው ቦታዎች ላይ መሄድ አስገዳጅ ሲሆንና ሰዎች ትራንስፖርት ሲጠቀሙ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛን ቢያደርጉ መልካም ነው::
የጤና ተቋሞቻችንን በአግባቡ ማዘጋጀት ሌላው ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው:: ይህንን ስል ወሳኙ ነገር ባለሙያዎች ከታካሚ ጋር ሲገናኙ ራሳቸውን ለመጠበቅ የሚያስችሏቸውን ግብዓቶች ማዘጋጀት፤ ለሚታመሙ ሰዎች ደግሞ አስፈላጊውን የህክምና ዕርዳታ መስጠት ነው:: እዚህ ላይ በተለይም ለኮሮና ታማሚዎች ወሳኙ የመተንፈሻ መሣሪያ (ኦክስጅን) ነውና ይህንን ሁሉም ጤና ተቋሞቻችን በበቂ ሁኔታ እንዲኖራቸው ማድረግና ማረጋገጥ ያስፈልጋል:: አምስት በመቶ ያህሉ ደግሞ የፅኑ ህሙማን ታካሚዎች ሊሆኑ ስለሚችሉ በመስኩ የሰለጠነ ባለሙያ እንዲሁም ሜካኒካል የእስትንፋስ መርጃ (ቬንቲሌተር) ማሟላት ይገባል::
ለምሳሌ ኢኮኖሚያዊ ጫናው ከባድ ነው እንጂ በሽታው እንደገባ ሰሞን መንግሥት ከወሰዳቸው ጠንካራ እርምጃዎች መካከል ትምህርት ቤት መዝጋት፣ የጉዞ እንቅስቃሴን መገደብ የመሳሰሉት ጥሩ ነበሩ፤ በተለይም የጉዞ እንቅስቃሴው በሽታው ወደ ገጠሩ ገብቶ አደገኛ ሁኔታን እንዳይፈጥር በመረጃ ላይ የተመሰረተ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል::
አዲስ ዘመን፦ ወረርሽኙ በአገራቸን ሁለተኛና ሦስተኛ ዙር የመከሰት ዕድል ይኖረው ይሆን?
ዶክተር ተግባር፦ የእኛ ሥጋት እኮ አሁንም የወረርሽኙ መጠን ምን ያህል እንደሆነ አለማወቃችን ነው:: ባላወቅነው መጠን ደግሞ ተቆጣጥረነዋል አልተቆጣጠርነውም ማለት ያስቸግራል:: ስለዚህ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሰው መርምረን በየቀኑ የሚገኝ ቁጥር እያነሰ ከሄደ ተቆጣጥረነዋል ማለት እንችላለን::
መጀመሪያ እንደፈራነው አይደለም እንኳን ብንል በየቀኑ አዳዲስ ሰዎች እየተገኙ ነው፤ ይህ ደግሞ ከተማ ላይ ብቻ ሳይሆን በገጠርም ነው:: ለዚህ ማሳያው ደግሞ በአማራ፣ ሶማሌ፣ ኦሮሚያ፣ አፋር እንዲሁም አዲስ አበባ እየታየ ነው:: ይህ የሚያሳየው ደግሞ ግማሽ በሚሆነው የአገሪቱ ክፍል ላይ መድረሱን ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ ጎረቤት አገር ሶማሊያ በከፍተኛ ሁኔታ ሰዎች በቫይረሱ እየተጠቁ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከውጭ የመምጣት ዕድል አለው፤ አገር ውስጥም እየተሰራጨ ሊሆን ይችላል፤ በበቂ ሁኔታ ግን እየመረመርን ስላልሆነ ይህንን እርግጠኛ መሆን አንችልም::
ይህንን መቆጣጠር እስካልቻልንና ወረርሽኙ ክትባት እስካልተገኘለት ድረስ፤ እንዲሁም ክትባቱ ራሱ ተገኝቶና ተመርቶ ወደእኛ አገር እስኪመጣ ምናልባት ዓመት ሊወስድ ይችላል፤ ስለዚህ ካልተቆጣጠርነውና ካላወቅነው አሁን ያለው ሁኔታ ዝም ያለ ቢመስለን ከዛሬ መቶ ዓመት በፊት የህዳር በሽታ ተብሎ እንደተከሰተው ይሆናል:: ያኔ የህዳር በሽታ መጀመሪያ የተከሰተው ሚያዝያ ወር አካባቢ ነበር ከዚያ በኋላ ግን በከፍተኛ ሁኔታ ብዙ ሰው ያጠቃብንና የጨረሰው ህዳርና ታህሳስ ላይ ነው፤ ስለዚህ ይህ ወረርሽኝ የአንድና የሁለት ወር አይደለም፤ የሚገባው ጥንቃቄ ካልተደረገ ከአራትም ይሁን ከአምስት ወራት በኋላ እንደገና ገንፍሎ ብዙ ሰው የሚያጠቃበት ዕድል ሊኖር ይችላል::
አዲስ ዘመን፦ የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር የሚጠበቅበትን ተግባር እንዴት እየተወጣ ነው?
ዶክተር ተግባር፦ ማህበሩ ሁሌም ለጤና ሚኒስቴር መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎችና መደረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች ምክረ ሃሳብን እየሰጠን ነው:: ለምሳሌ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሳይወጣ በፊት ለጥንቃቄ የሚሆኑ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እየማከርን ነበር፤ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁም በዚያ መሠረት የተወሰደ ነው:: አሁን ደግሞ ባለው የቫይረሱ የሥርጭት መጠንና ዓለም አቀፍ ምርምሮችን በመከተል መንግሥት ሊወስዳቸው የሚገባቸውን እርምጃዎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኗቸውን ግምት ውስጥ አስገብተን ለመተግብር ያለውን ምቹ ሁኔታ አመዛዝነን እስከ አሁን የተሰጡትን ምክረ ሃሳቦች እንገመግማቸውና የቱ መቀጠል አለበት? ምንስ ቢጨመር ይሻላል? የሚለውን እንደ አዲስ ለመስጠት ውይይቶች እያደረግን ነው::
ይህንን ስንጨርስ እንደ አዲስ ምክረ ሃሳቦችን እናቀርባለን:: ስለዚህ የእኛ ሥራ አንዴ ሃሳብ ሰጥቶ መተው ብቻ ሳይሆን አዳዲስ መረጃዎችን በመንተራስ ነባራዊ ሁኔታውን በማገናዘብ እየከለስን ከጤና ሚኒስቴር ጋር እየሠራን ነው::
አዲስ ዘመን፦ ስለ ቫይረሱ በባለሙያዎች በኩል የሚነገሩ ምክሮች የተለያዩ ይሆናሉ፤ ይህ ምናልባትም የበሽታው ባህርይ አለመታወቅ ያሳደረው ተጽዕኖ ሊሆን ይችላል፤ ግን ደግሞ ህብረተሰቡ ከማን ነው መረጃዎችን መቀበል ያለበት ይላሉ?
ዶክተር ተግባር ፦ ይህ ጉዳይ እኛንም እንደ አማካሪ ምክር ቤት የሚያሳስበን ነው:: አንዳንዴ ሰዎች በቅንነት መረጃ ይሰጣሉ፤ ግን ደግሞ የተሳሳተ የሚሆንበትን ሁኔታ እንመለከታለን:: እኛ አሁን የምንመክረውና ሰዎች እርግጠኛ ሆነው እንደ መረጃ ምንጭ መከተል አለባቸው የምንለው የጤና ሚኒስቴር፣ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና በሙያ ማህበራት የተመሰረተው የአማካሪ ምክር ቤት የሚያወጣቸውን መረጃዎች ነው:: ስለዚህ ሰዎች በቫይረሱ ዙሪያ ጥያቄ ሲኖራቸው ከላይ ከተጠቀሱት የመረጃ ምንጮች በአንዱ በኩል መረጃን ለማግኘት መሞከር አለባቸው:: ይህ ካልሆነ ወይም ከሌላ ወገን የሚያገኙትን መረጃ ማረጋገጥ ካልቻሉ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል::
ይህንን ችግር ለመፍታትና ህብረተሰቡንም ለማስተማር አማካሪ ምክር ቤቱ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በመገናኛ ብዙሃን የሚለቀቁ መረጃዎች ወቅታዊ ትክክለኛና ተአማኒ እንዲሆኑ ጥረት እያደረገ ነው:: አንዳንድ ጊዜ ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች በመገናኛ ብዙሃን ቀርበው ስለ ቫይረሱም ሆነ ሌላ መረጃ ሲሰጡ እናያለን፤ ይህ ህብረተሰቡን በጣም የሚያምታታ በመሆኑ ሰዎች በተለይም ስለ ቫይረሱ ያላቸውን ጥያቄ በተመለከተ መረጃዎችን ከሦስቱ አካላት አንዱን በመጠየቅ የተጠናቀረ መረጃን ማግኘት ይችላሉ::
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ
ዶክተር ተግባር፦ እኔም በጣም አመሰግናለሁ::
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2012
እፀገነት አክሊሉ