ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚነግሩንና የሃይማኖት አባቶች እንደሚያስተምሩን የሰው ልጅ የተፈጠረው በፈጣሪ መልክና አምሳል ነው።የተፈጠረበትም ዋና ዓላማ ምድርን፣ ከምድር በላይና በታች ያሉትን ፍጥረታት እንዲንከባከብ፣ እንዲገዛና በበረከቶቹ ትሩፋቶችም ደስ ብሎት እንዲኖር ነበር።ፍጥረተ አዳም ወሔዋን (አደምና ሐዋ) ከገነት (ጀነት) እስከ ውድቀት የተጓዙባቸው የሕይወታቸው ምዕራፎች ግን የፈጣሪን መስመርና ጎዳና በመከተል ሳይሆን በተቃራኒው የተደረገ የአመጽ ጉዞ እንደሆነ የሃይማኖት ትምህርቶች ብቻ ሳይሆኑ እውነታው ራሱ አፍ አውጥቶ እየመሰከረ እንዳለ የምናስተውለው ሐቅ ነው፡፡
የሰው ልጅ በራስ ወዳድነት የጋራ የሆነችውን ዓለም “የግሌ ብቻ ካልሆነች” በሚል መስገብገብ ወንድም ወንድሙን፣ አንዱ ሕዝብ በሌላኛው ሕዝብ ላይ ሰይፍ እየመዘዘና ዘገር እየነቀነቀ “ባፍቅሮተ ነፍስ” እንዳበደና እንደተፋለመ እነሆ ዘመን በዘመን ላይ ጠብቶ ከዛሬዋ የእኛ ጀንበር ላይ አድርሶናል፡፡
አምላክ በመልኩና በምሳሌው የሰው ልጆችን ሁሉ መፍጠሩ ብቻ ሳይሆን “ይሄው ፈጣሪ ዓለምን በጥበቡ ካለመኖር ወደ መኖር ካመጣ በኋላ፤ የሰው ልጅ ደግሞ በእውቀቱ ወይንም በጦር ኃይሉ ሀገራትን በመልኩና በምሳሌው ሸንሽኖ መከፋፈሉ” በታሪክና በጥንታዊ በሳል ብሂሎችም ሳይቀር ሲነገርና ሲተረት ኖሯል።እናስ የሰው ልጅ በወሰን ችካል ሸንሽኖ፣ በወንዝ በውቂያኖስ ከልሎ፣ በአባት ወይንም በእናት እየመሰለ “የእኔ” የሚለውና “የዕትብቱ መቀበሪያ” እንደሆነ በማወጅና ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብ “በመልኬና በአምሳሌ የፈጠርኩት” እያለ የሚያንቆለጳጵሰውና የሚዘምርለት የሀገሩ መልክና ምሳሌ እንደምን ይገለጻል?
እንደ ሀረግ የተወሳሰበው የእነዚህ ጥያቄዎች ጓዝ ጉዝጓዝ ተስቦም ሆነ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም።ባዕዳን እንዲህ ዓይነት ውል አልባ ጥያቄዎች ጫፍና መዳረሻ እንደሌላቸው የሚገልጹት “vicious circle” እያሉ ነው።ብሂሉ “ውሃ ቢወቅጡት እምቦጭ” ከሚለው የሀገራችን አባባል ጋር ይስማማ አይስማማ እርግጠኛ አይደለሁም።ለማንኛውም በባለ ብዙ ዓይን ከሚመሰለው “የማር እንጀራ ጥያቄዎች” ውስጥ ሰፈፉን እያንገዋለልን ወለላ ማሩን ለማጣጣም የሌሎችን ጉዳይ ለጊዜው ወደ ጎን ገፍተን የራሳችንን ሀገር ጉዳይ እየፈተሽን ጥቂት ሃሳብ በመፈነጣጠቅ “እህ!” እንባባል፡፡
ሀገር የትናንቱ፣ የዛሬውና የነገው ትውልድ የማይገሠሥ “ሉዓላዊ ሀብቱ” ነች።እንደ ታላቁ የሀገራችን ደራሲ እንደ ከበደ ሚካኤል አገላለጽ “በመወለድ እትብት፣ በመሞት አካል ከአፈሩ ጋር ስለሚዋሃድ የሀገር አፈር ሕዝቡ በላዩ የሚኖርበት ማለት ነው።ሀገር ማለት አያት ቅድመ አያት የተወለዱበት፣ አድገውም በጀግንነት ከውጭ ጠላት እየተከላከሉ ለሕዝቡና ለመንግሥት የሚጠቅም ሥራ ሠርተው ዕድሜያቸው ሲደርስም ልጆቻቸውን ተክተው የተቀበሩበት ጉድጓድ ማለት ነው።በመወለድ ዕትብት፣ በመሞት አካል ከአፈሩ ጋር ስለሚዋሃድ የሀገሩ አፈር ሕዝቡ በላዩ የሚኖርበት ማለት ነው።ሀገር አባት፣ እናት፣ ዘመድ፣ ምግብ፣ ጌጥና ሀብት በመሆኑ ድህነትና ጥቃት በመጣ ቁጥር እስከ ሞት ድረስ እንዲሠራበት ከአያት ከቅድመ አያትና ከአባቶች በጥብቅ አደራ የተሰጠ ገንዘብ ነው፡፡”
አባባሉ ግሩም የሚሰኝ ብቻ ሳይሆን ጥልቅ ፍልስፍና ያዘለ ጭምር ነው።ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) በመጋቢት 2010 ዓ.ም ባደረጉት የበዓለ ሲመት ንግግራቸው ውስጥ የጠቃቀሷቸውን አንዳንድ ሃሳቦች ስንመለከት በደራሲ ከበደ ሚካኤል ፍልስፍና ሳይማረኩ እንዳልቀሩ እገምታለሁ።ለንፅፅር እንዲያግዝ ከረጂሙ ንግግራቸው ውስጥ ጥቂት ሃሳቦችን አስታውሳለሁ፡፡
“አማራው በካራማራ ለሀገሩ ሉዓላዊነት ተሰውቶ የካራማራ አፈር ሆኖ ቀርቷል።ትግራዋይ በመተማ ከሀገሬ በፊት አንገቴን ውሰዱ ብሎ የመተማ አፈር ሆኗል።ኦሮሞው በአድዋ ተራሮች ላይ ስለ ሀገሩ ደረቱን ሰጥቶ የሀገሩን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ከአድዋ አፈር ተቀላቅሏል።ሱማሌው፣ ሲዳማው፣ ቤንሻንጉሉ፣ ወላይታው፣ ጋምቤላው፣ ጉራጌው፣ አፋሩ፣ ስልጤው፣ ከምባታው፣ ሐዲያው እና ሌሎችም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሁሉ በባድመ ከሀገሬ በፊት እኔን ብለው እንደወደቁ ከባድመ አፈር ጋር ተዋህደዋል።አንድ ኢትዮጵያዊ አባት እንዳሉት እኛ ስንኖር ሰዎች፣ ስናልፍ አፈር፣ ስናልፍ ሀገር እንሆናለን።የየትኛውም ኢትዮጵያዊ ክቡር ሥጋና ደም በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ አፈር ሆኖ ታገኙታላችሁ።ኢትዮጵያዊያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ፤ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናልን፡፡”
የሀገርን ጥልቅ ትርጉም ከዚህ የበለጠ ሊያብራሩልን የሚችሉ ሌሎች ተጨማሪ ማመሳከሪያዎችን መፈለግ ጉንጭ አልፋነት እንዳይሆን እሰጋለሁ። የሀገር ምጡቅ ብያኔ በዚህን መሰሉ ጥቅል ሃሳብ መገለጡ የሚያስማማን ከሆነ የተንደረደርንበት የጽሑፋችን ርዕስም ምላሽ የሚያገኝ ይመስለኛል።ለካንስ የሀገር ምሳሌዋና መልኳ በድናቸው ከአፈር ተቀላቅሎ “ኢትዮጵያን የሠሩ ኢትዮጵያዊያን” እና በመስዋዕትነት በተከበረው የኢትዮጵያ አፈር ላይ የቆመው የዛሬው ኢትዮጵያዊ ትውልድ ናቸውና! በክቡራን ሰማዕታት “ኢትዮጵያዊያን አፈር ላይ” የቆመ ባለ አደራ ኢትዮጵያዊ ክቡር ትውልድ ይሏል እንዲህ ነው፡፡
ፈጣሪ ሰውን ከምድር አፈር አበጅቶ በአፍንጫው የሕይወትን እስትንፋስ እፍ እንዳለበት እኛ የዛሬዎቹ ኢትዮጵያዊያን በክብርና በሉዓላዊነት ተከብረን እንድንኖር “እፍ የተባለብንን የነፃነት እስትንፋስ” ያወረሱን በኖሩበት ዘመን ኢትዮጵያዊ፣ ከሞቱ በኋላ ደግሞ ኢትዮጵያን ራሷን የሆኑ እናቶቻችንና አባቶቻችን ናቸው። ዘላለማዊ ክብር የኢትዮጵያዊነትን መልክና ምሳሌ ኢትዮጵያዊ አፈር ሆነው ለሠሩ ጀግኖች ይሁንልን።“አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” እንደሚለው መለኮታዊ ቃል “ኢትዮጵያዊ ሆነን ኖረን ስናልፍ የኢትዮጵያ አፈር እንዳንሆን” የምንፈተንባቸውና የምንመዘንባቸው ዘመን ወለድ ተግዳሮቶች በርክተው ማየት እንደምን ልብን እንደሚሰብር ለማስረዳት አካባቢያችንን ግራና ቀኝ ማማተር ብቻ ይበቃል፡፡
ካለፈው የታሪካችን ምስክርነት፣ ከዛሬው የውሎ አምሽቶ ኑሯችን እንደምንረዳው ህሊናቸውን ከእውነት ጨፍነው፣ ጆሯቸውን በርካሽ ጥቅሞች ደፍነው “ኢትዮጵያዊ ሆነው ኖረው፤ ኢትዮጵያን ሆነው ለማለፍ ያልታደሉ ወይንም አፍረው ያሳፈሩን” በርካታ ፀረ ኢትዮጵያ እስትንፋስ የነበራቸውና ዛሬም ያሉ “ዜጎች!?” እንደነበሩ ብቻ ሳይሆን እንዳሉም ሊዘነጋ አይገባም፡፡
በታሪካችን ውስጥ አንዳንድ ሆድ አደር ባንዳዎች ከወራሪ ጠላት ጋር ወግነው በወገናቸው ላይ አፈሙዝ ያዞሩ እንደነበር በታሪክ መዛግብት ላይ ጥቋቁር ታሪካቸው ተመዝግቦ ሠፍሯል።ነበር ታሪካችን ብቻ ሳይሆን በዛሬም ጀንበር ቢሆን ዙሪያ ገባውንና የፖለቲካ ምህዳሩን በአስተውሎት ስንመረምር “በኮትቻ አፈር የሚመሰል” ተግባር እየፈጸሙ ያሉ ጥቂት ያይደሉ ግለሰቦች እንዳሉ ማስተዋሉ አይገድም፡፡
ነፍሰ ሄር ጥላሁን ገሠሠ “ዘንድሮ” የሚል አንድ ዜማ ነበረው።ይህ ዘመን ተሻጋሪ መልዕክት ያለው ዜማ በኪነ ጥበባት ካዝና ውስጥ ታሽጎ ብቻ የተቀመጠ ሳይሆን ዛሬንም ሆነ ነገን የመሄስ አቅሙ ከፍ ያለ ነው።ድምጻዊው የተጫወታቸውን የዜማ ግጥሞች በግለ ታሪክ መጽሐፉ (የኢትዮጵያ የሙዚቃ ንጉሥ፤ ጥላሁን ገሠሠ፤ ከ1933-2001 ዓ.ም) ውስጥ የዕውቀቴን ያህል ለመተንተን እድል አግኝቼ ስለነበር ብዙዎቹን ግጥሞቹን አልዘነጋኋቸውም።በመሆኑም ከነበርነቱ ይልቅ ዛሬነቱ ይበልጥ ትርጉም እንደሚሰጥ ስለማምን “ከዘንድሮ” የዜማ ግጥሙ ውስጥ ጥቂት ስንኞች ተውሼ ልጥቀስ፤
“ዘንድሮ፣ ዘንድሮ፣ ዘንድሮ፣ ዘንድሮ፣
የስንቱ ተወርቶ የስንቱ ተነግሮ፡፡
ብዙ ዓመት በድብቅ ሲጓዝ ከረመና፣
ዘንድሮ ላይ ሲደርስ ሸክሙ አጋደለና፤
ተዝረክርኮ ወድቆ በግልጽ ብናየው፣
የዘንድሮን ነገር ዘንድሮ አወቅነው፡፡”
ዜመኛው እውነቱን ነበር።የሀገራችንን ጉዳይ በተመለከተ የዘንድሮ ጀንበር ብዙ ጉድ አሳይቶናል። አንዳንዱ ደፋር “ስመ አክቲቪስትና ፖለቲከኛ” ለዓመታት ሲያጠራቅም የኖረው “የአመጽ እቁብ” ዘንድሮ ዕጣው ወጥቶለት በተሳከረው የፖለቲካ ፍልስፍናው ርዕዮት የሀገርን መልክና አምሳል “በራሱ ምሳሌነት ለመጠፍጠፍ” ሲሞክር እያስተዋልን ነው።የራሱ መልክ የኢትዮጵያ መልክ እንዲሆን መፈለጉ ብቻ ሳይሆን ምሳሌውም አምሳላችን እንዲሆን በእጅጉ እየጣረ ቀን ከሌት ሲማስን እያስተዋልን ነው።
በአደባባይና በግላጭ “የሀገሪቱ መልክና ምሳሌ” እኔና የእኔ የሆኑት ብቻ ነው እያለ በአደባባይ ሲፎክር እያደመጥንና እየታዘብን ዝምታን ስንመርጥ በአሜንታ የፀደቀለት የሚስለውም ብዙ ነው።አንዳንዱ እያልን የምንገልጸው ፊትአውራሪ በመልኩና በአምሳሉ የቀረጻቸውን “ምሳሌዎቹን” እየመራ ያለው እንዲያስቡና እንዲጠይቁ አድርጎ አይደለም።የዚህን “ምስለ ዜጋ” የአመራር ዘይቤ የማመሳስለው “ሆያ ሰለሜ!” በመባል ከሚታወቀው ከዝነኛው የደቡቡ የሀገራችን ክፍል (ሐዲያ) ባህላዊ ሙዚቃ ጋር ነው።“ሆያ ሰለሜን” ተወዳጅና ዝነኛ ያደረገው የግጥሙ ይዘትና ዜማው ብቻ ሳይሆን የአቀንቃኞቹ እንቅስቃሴ ጭምር ነው።“ሆያ ሰለሜ!” በርከት ያሉ ሰዎች በሰልፍ እየተንቀሳቀሱ የሚያቀነቅኑት ዜማ ነው።ሰልፈኞቹ አንዳቸው በአንዳቸው ትከሻ ላይ እጃቸውን አሳርፈው ከሰልፉ ዝንፍ ሳይሉ የመሪ አቀንቃኙን ግጥምና ዜማ እየተቀበሉ ምላሽ ይሰጣሉ።
መሪ አቅንቃኙ ጅራፍ በእጁ ይዞ ከኋላው የተሰለፉትን አጃቢዎች በዓይነ ቁራኛ እየተከታተለ ከመስመር እንዳይወጡ በያዘው ጅራፍ ሾጥ እያደረገ “ያግዳቸዋል”።ድንገት ከመስመሩ ዝንፍ ያለ አጃቢ በጅራፉ ክፉኛ ስለሚዠለጥ ከሰልፉ ላለመውጣት ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋል።ልክ እንደዛሬዎቹ “ባለ ጅራፍ ገራፊ ፖለቲከኞችና ተገራፊ ሰልፈኞቻቸው” መሆኑ ነው፡፡
ሀገርን በራሳቸው መልክና አምሳል ለመቅረጽ ቀን ከሌት የሚጥሩት እነዚህን መሰል ፖለቲከኞች “የዲሞክሲ ተብዬው” ውጤቶች መሆናቸውን በማስታወስ በዛሬ ሳምንቱ ጽሑፌ ውስጥ “ላም እሳት ወለደች፤ እንዳትልሰው ፈጃት አንዳትተወው ልጅ ሆነባት” በሚል ብሂል ጥቂት ቁዘማ ማድረጌ አይዘነጋም፡፡
በራሳቸው መልክና አምሳል ሀገራቸውን ካልጠፈጠፍን በማለት ከሚራኮቱ ሀገራት ትምህርት ለመውሰድ እንኳ ልባቸውን የደፈኑት እነዚህን መሰል “የዘንድሮ ፖለቲከኞች” ምን እየሰሩና እያወጁ እንደሆነ የምንሰማውና የምናስተውለው ብዙ ነው፡፡
ዜመኛው እንዳቀነቀነው ብዙ ዘመን በድብቅ ሲመከርበትና ሲሰራበት የኖረው ሤራ ዘንድሮ ነፍስ ዘርቶ የጦርነት ነጋሪት ሲጎሰምለት አያየን ነው።ከሜዳ ተነስቶ “ደሞ ገለሌ ፉከራ!” ለጊዜው “ጥቅሜን አስቀሩብኝ በሚል ፀፀት” የገዛ ስሜትን ያሟሙቅ ካልሆነ በስተቀር ሕዝብን ሆ! አሰኝቶ ለጦርነት የሚማግድ ታክቲክ ያለመሆኑን የተረዱት አይመስልም፡፡
የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ “እኔ ብቻ” በሚል መሪ ፍልስፍና መለወሱን እያስተዋልን ነው።አንዳንዱ ፖለቲከኛ ነኝ ባይ የዘመናችን ጉድ ፈጣሪ ከአዳም የጎን አጥንት ወስዶ ሔዋንን በፈጠረበት አካሄድ ከእርሱ የፖለቲካ ጎድን ላይ አጥንት ተወስዶ “አዲስቷ ኢትዮጵያ እንድትፈጠርለት” ሲቃዥ እየተመለከትን ነው።አንዳንዱም በወላዋይ ምላሱ ላይ ከሚያመነጨው አማላይ የወሬ ጅረት “ተስፋ” ቀድተን እንድንጠጣ ሲወሸክት እያስተዋልን ነው።አንዳንዱም የእባብ እንቁላል መታቀፉን እያወቅን የርግብ ጫጩት እንደሚፈለፈል ሊያሞኘን ይሞክራል።አንዳንዱም “የእኔ ሕይወት የተመሠረተው በፖለቲካ ስም ከሚገኝ ፍርፋሪ ስለሆነ” በዕለት እንጀራዬ ላይ አትምጡብኝ እያለ በግላጭ የአዞ እንባ ሲያነባ እየታዘብን ነው።ዘንድሮ ብዙ አንዳንዶችን አሳይቶናል።
ቀደም ባሉት ዘመናት ለኢትዮጵያ ሬዲዮ ፈርጥ ከነበሩት ዝነኛ ጋዜጠኞች መካከል በአባት ስም ሞክሼነት የሚመሳሰሉት አበራ ማሞና ጥሩነህ ማሞ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።ዛሬ ሁለቱም በአጸደ ሥጋ ተለይተውናል።እነዚህ ሁለት “አንደበተ ማር” ተደማጭ ጋዜጠኞች እሁድ ከሰዓት በኋላ የሚተላለፍ የዘፈን ምርጫ ፕሮግራም ነበራቸው።በሺህ የሚቆጠሩ የወቅቱ ዜጎች ብሶታቸውን፣ ፍቅራቸውን፣ ሀዘናቸውን ወይም ትዝብታቸውን ይገልጽልናል ብለው የሚያስቧቸውን ዘፈኖች ለእነዚህ “ዘፈን መራጮች” እያስተላለፉ ይዘፈንላቸው ነበር።በአንድ ወቅት ከመራጩ ቁጥር መብዛት የተነሳ ስም ዝርዝሩን እንኳ መጥራት ከተሳናቸው ዜማዎች ውስጥ የሚከተለው የጥላሁን ገሠሠ ዜማ ትዝ ይለኛል።ለዘንድሮ ግራ ገብ ፖለቲከኞች ይጠቅም ከሆነና ወደ ህሊናቸው ይመልሳቸውና ንስሃ ያስገባቸው ከሆነ ያንን የጥንቱን ዜማ ዘንድሮ እንደተመረጠላቸው እንዲያስቡ እነሆ ብያቸዋለሁ፡
“የእውነትን መንገድ ተሳስቼ፣
ተቀጣሁ በውሸት ተመርቼ፡፡
እውነት ማሪኝ እላለሁ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡
. . .
በቃኝ አይለምደኝም ዳግመኛ፣
እኔ በውሸት ተቀጣሁ ክፉኛ፣
ከስታ ብትታይ እውነት መንምና
ለእውነት ያለህ ብዬ ልጩኽ፣
አትጥለኝም ጨክና፡፡
ሰላም ይሁን!!
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2012
በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ)