የዘንድሮ የትንሳዔ በዓል የኮሮና ወረርሽኝን አስረስቶ ሰንብቷል። የአዲስ አበባ ገበያዎች ሙሉ ነበሩ። ግርግሩም እንደወትሮው ድምቀት አልተለየውም። የበዓል እርዱ ከሞላ ጎደል በነበረበት ቀጥሎ የተከናወነ ነበር። የትራንስፖርቱ አገልግሎቱ፣ መንገዱ፣ መጠጥ ቤቱ… እንዲሁ በሕዝበ ሠራዊት እንደተሞላ ከርሟል። ቤተዘመድ “እንኳን አደረሰህ” መባባሉ ከወትሮው ጋር ሲነጻጸር ላላ የማለት ነገር ቢኖርም ጨርሶ አካላዊ ርቀትን በጠበቀ መልክ የተከናወነ እንዳልነበር ታዝበናል። በጥቅሉ የአፍሪካ መዲና፣ የዲፕሎማቶች መናኸሪያ በምንላት አዲስ አበባ ያለው መዘናጋት ያስደነግጣል። ገጠሩም ላይ እንዲሁ።
ሰሞኑን የተከሰተ ነው። በአማራ ክልል በምስራቅ ጎጃም ዞን በእነብሴ ሳር ምድር ወረዳ ቀበሌ 06 እንደወትሮው ሁሉ አንድ ሰርግ እየተካሄደ ነበር። ደስታውን ወደ ሐዘን የለወጠ መጥፎ ክስተት በድንገት ተሰማ። ለደስታ መግለጫ የተነገተ መሳሪያ ባርቆ ሙሽራው ተመታ፤ ሕይወቱም አለፈ። ሠርግን ያህል ደስታና ፈንጠዚያ በቅጽበት ክስተት ወደ ሐዘን ተቀየረ። ይኸ ሁሉ የተከሰተው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሠረት ሠርግ ማከናወን በይፋ ተከልክሎ ባለበት ሁኔታ ነበር። ከገጠር እስከ ከተማ ነገረ ሥራችን ሕግና ሥርዓት የማይገዛው መሆኑ ይኸ አብነት ጥሩ ማሳያ ነው።
እስከ እሁድ ሚያዝያ 25 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ብቻ በጠቅላላው በኢትዮጵያ በኮሮና የተያዘው ወገን ቁጥር 135 ነበር። ከሳምንት በኋላ ከትላንት በስቲያ ሰኞ ዕለት ቁጥሩ ወደ 250 ከፍ ብሏል። በሰባት ቀናት ልዩነት ብቻ 115 አዳዲስ የኮሮና ቫይረስ ሕሙማን መመዝገቡ ብቻውን ያለፈውን ሳምንት የተለየ ያደርገዋል።
እናም እንደ አገር የመመርመር አቅም እያደገ ወደ ህብረተሰቡ ውስጥ ሰፋ ያለ ምርመራ ማድረግ ሲቻል ደግሞ ከዚህም በላቀ ሁኔታ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል መረጃው ፍንጭ ይሰጣል።
ይኸ ብቻም አይደለም፤ እስከ ሐሙስ ሚያዝያ 29 ቀን ድረስ በኮሮና ቫይረስ ከተያዙት ከ187 ሰዎች መካከል ወደ 70 የሚጠጉት በለይቶ ማቆያ ውስጥ ያልነበሩ መሆናቸው የጤና ሚኒስቴር በተለያዩ ቀናት የተሰጡ መረጃዎች ያሳያሉ። የሐሙስ ዕለቱ ሪፖርት እንደሚያሳየው የኮሮና ስርጭት በሐዲያ፣ በከምባታ፣ በቦረና እና በአዲስ አበባ የታየ ሲሆን ቀደም ሲል በድሬደዋ፣ በባህርዳር ከተሞችና በመሳሰሉት መታየቱ ክልላዊ ስርጭቱም የዋዛ እንዳልሆነ ጠቋሚ ነው። ይኸ መረጃ ሁለት ትልልቅ ነገሮች ቁልጭ አድርጎ አሳይቶናል። አንዱ ቫይረሱ የውጪ አገር የጉዞ ታሪክ የሌላቸውን ሰዎች ላይ በስፋት እየታየ መምጣቱ ነው። ሌላው ደግሞ የቫይረሱ ስርጭት ክልሎችንም እያዳረሰ መምጣቱን መጠቆሙ ነው። በአጭሩ የኮሮና ቫይረስ በህብረተሰቡ ውስጥ ዘልቆ መግባቱን መረጃው ጮኾ ይናገራል። እናም እንዲህ አይነቱ መረጃ የሚያሳየው መዘናጋታችንን ነው። በጥቅሉ መረጃው ቆም ብለን እንድናስብ፣ ለራሳችን ለቤተሰባችን የምናደርገውን ጥንቃቄ እንድንፈትሽ፣ ችግር ካለም እንድናርም የሚወተውት ነው።
እርግጥ ነው፤ ብዙዎች በኢትዮጵያ የተያዘው ሰው ቁጥር አነስተኛ መሆኑ፣ ከተያዙትም አብዛኛው (በጸሐፊው ግምት 98 በመቶ) ማገገም መቻላቸው ለመዘናጋቱ ተጨማሪ አስተዋጽኦ ስለማድረጉ ብዙዎች ሲናገሩ ይደመጣል።
ከኤካ ኮተቤ የህክምና ባለሙያዎች እና አጋሮቻቸው ተልኮ ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨ መልዕክት እንዲህ ይላል።
“ …ኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆ/ል ከጅማሮ ተነስቶ ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። በመጀመሪያዎቹ 5ዐ ቀናት ውስጥ በርካታ ታካሚዎችን ተቀብሎ ያስተናገደ ሲሆን ወደ 66 የሚሆኑ ታካሚዎቻችን ከበሽታው አገግመው መውጣት የቻሉ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ 6 የሚሆኑ ታካሚዎቻችን በጽኑ ሕሙማን ክፍል ታክመው የሶስቱ ሕይወታቸው ቢያልፍም የጽኑ ሕሙማን ክፍል የሞት መጠን ወደ 5ዐ በመቶ ዝቅ ያለበት ሁኔታ ደግሞ ትልቅ ተስፋ የሚያሳይ ነው። አጠቃላይ እንደ አገር የቫይረሱ የሞት መጠን 2 ነጥብ 5 በመቶ መሆኑ ይታወቃል።”
የኢትዮጵያ የጤና ሚኒስቴር በያዝነው ሚያዝያ ወር መጨረሻ 250 ሺ ኢትዮጵያውያን በኮቪድ-19 ይጠቃሉ ሲል ገልጾ ነበር። እስካሁን ያለው ቁጥር ግን ከ187 በላይ ነው። ጎረቤት አገር ኬንያም በተመሳሳይ 10 ሺ ሰዎች በቫይረሱ ይጠቃሉ ብላ የተገኘው ቁጥር ከ300 አላለፈም። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽንም በአህጉሪቱ 150 ሺ ሰዎች ገምቶ የነበረ ሲሆን ይኸው ቁጥር አንድ ሶስተኛውን አልደረሰም። እነዚህ ሁኔታዎች በተለይ በኢትዮጵያ የሰዎችን አመለካከት ወደ መቀየር እያደገ መምጣቱ ያስፈራል። “ፈጣሪ ይጠብቀናል፣ ኢትዮጵያን ፈጣሪ ይወዳታል…” የሚሉ አዘናጊ ሀሳቦች፣ ምክሮች፣ ስብከቶች… በስፋት በህብረተሰቡ ውስጥ እየተንሸራሸሩ መምጣት የኋላ ኋላ ከባድ ዋጋ እንዳያስከፍል ያሰጋል።
በተለይ አዲሱን የጤና ሚኒስቴር ቅድመ መላ ምት ላደመጠ ሥጋቱ ጣራ ቢነካ ላያስገርም ይችላል። “በኢትዮጵያ ከፍተኛ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር እና የከፋ ጉዳት ሊደርስ የሚችለው በመጪው ሰኔ መጨረሻና ሐምሌ ወራት መጀመርያ ላይ ነው” የሚለው ማስጠንቀቂያ ጆሮ የሚያጮኸ ነው።
መግለጫው ቀጥሎ “መንግስት የኮሮና መከላከያ እርምጃዎችን ባይወስድ ኖሮ ከ27 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በኮሮና ቫይረስ ይጠቁ እንደነበርም ተገልጿል። ጤና ሚኒስቴር ወረርሽኙ ሊያደርስ የሚችለው የከፋ ውጤት ገና አላለ ፍነውም፤ እንደ ኮሮና ወረርሽኝ አንድ ሀገር ገብቶ የሚብስበት ጊዜ ገና የሚመጣ ነውና መዘናጋት አደገኛ ነው” ብሏል።
የጤና ሚኒስቴር መረጃው አያይዞም አንድ ወረርሽኝ የስርጭት ጣርያው ላይ ለመድረስ በአማካይ አስር ሳምንት ወይንም 3 ወር ይፈልጋል፤ እኛ አንድ ወር ከሁለት ሳምንታችን ስለሆነ አስከፊው ነገር ገና ከፊታችን ነው ተብሏል።
በታሪክ የተከሰቱ ወረርሽኞችም ለምሳሌ የህዳር በሽታ የዝናብና የብርድ ወቅት መውጣትን ተከትሎ ነው የስርጭታቸው ከፍታ ላይ የደረሱት ያሉ ሲሆን፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዝናብ ቀደም ብሎ ሚያዝያ፣ ግንቦት ላይ እየጀመረ ስለሆነ የሰኔ የመጨረሻ ሳምንትና የሐምሌ የመጀመሪያ ሳምንት ሊከፋ እንደሚችል የጤና ሚኒስቴር ማስጠንቀቁ ተሰምቷል።
ዋናው ነገር፤ ከመንግሥት ወይንም ከጤና ሚኒስቴር የሚወጡ መረጃዎችን እንመን። የሚሰጡ ሙያዊ ምክሮችንም አንስማ፣ እንተባበር። ይህ ካላየሁ አላምንም አይነት አስተሳሰቦች መታገልም ያስፈልጋል። ሰው ከጥንቃቄ ጋር በየእምነቱ መጸለይ የመንፈስ ዋጋን ከፍ ያደርጋል።
ከኮቪድ 19 ጋር ተያይዞ የመዘናጋት ሁኔታ የኤች ኤይቪን የቅርብ ጊዜ ታሪክ አስታውሶኛል። ያኔ ኤች አይ ቪ/ኤድስ በአስፈሪነቱ ተጋንኖ በሚነገርባቸው ጊዜያት እንዲሁ አናምንም ያሉ ብዙ ኢትዮጵያውን ነበሩ። የአንዳንዶች መታበይ “ኤድስ ራስዋ ቀሚስ ለብሳ ብትመጣ አልለቃትም” እስከማለት የዘለቀ ነበር። በኋላ ምን ሆነ? ኤች አይ ቪ/ኤድስ ቀስ እያለ የዘመድ፣ የጎረቤት፣ የጓደኛ፣ የቤተሰብ አባል በሮችን ማንኳኳት ጀመረ። ብዙ ሰዎች የልብ የሚሉትን ወዳጅ ማጣት ሲጀምሩ ከባድ ድንጋጤ ላይ ወድቀዋል። እናም የማስታወስ ችሎታ ማነስ (ሾርት ሚሞሪ) ነገር ሆኖ ያ ነገር ዛሬ ተረስቷል። ብዙዎች ዛሬም በመዘናጋት ውስጥ እንደልብ መሆን መቀጠላቸው ያሳስባል፣ እንደአገርም ያስፈራል።
ያው ድሆች ነን። ሐብታሞቹ እንደታላቋ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ፣ ስፔን፣ ጣሊያን የዜጎቻቸውን አስከሬን እንኳን በወጉ፣ በክብር መሸኘት በማይችሉበት ሁኔታ ሲመቱ አይተናል። በታላቋ ኒውዮርክ ከተማ በወረርሽኙ የሚሞቱ ሰዎች አስከሬን የሚቆይበት ማቀዝቀዣ ጠፍቶ በከተማ ውስጥ ለሥጋ እና ለአትክልት ፍራፍሬ ማመላለሻ የሚጠቅሙ ፍሪጅ ያላቸው ተሽከርካሪዎች ሁሉ ተለቅመው ለአስከሬን ማቆያነት ሲውሉ ታዝበን ከልብ አዝነናል።ይኸም በቂ ስላልነበር የሰዎች አስከሬን በየሆስፒታሉ ኮሪደር እስከመታየትም ተደርሷል። ይህ ክስተት የቱን ያህል ቅስምን እንደሚሰብር የታዘበ ያውቀዋል። ይህ መዓት፣ ይህ የፈጣሪ ቁጣ በእኛም አገር ተከስቶ ካላየሁ አላምንም ማለት ከጤነኛ አእምሮ አይጠበቅም።
ኮሮናን እጅግ አደገኛ የሚያደርገው ሰዎችን በበሽታው መግደሉ ብቻ አይደለም፡ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ አገራት የሚገኙ ሰዎችን ከበሽታው ቀጥተኛ ጥቃት በተጨማሪ በረሀብ እና በድህነት ሊገድልና ሊያሰቃይ የሚችልበት ዕድል ሰፊ የመሆኑ ነገር ነው። በአጠቃላይ የዚህ ወረርሽኝ ተፅዕኖ በቀጣይ ለሦስት ወራት ይቆያል የሚል የቢሆን መነሻ ብንይዝ፣ በመቀጠር ሥራ ከሚያስገኙ መስኮች ውስጥ ከ705 ሺ ሥራዎች የመጥፋት አደጋ ላይ ይወድቃሉ። በተጨማሪም ሦስት ሚሊዮን ራስ አገዝ ሥራዎችም አደጋ ውስጥ እንደሚገቡ ዶ/ር ፍፁም አሰፋ በሚኒስትር ማዕረግ የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር በቅርብ ለመገናኛ ብዙሃን መናገራቸውን የምናስታውሰው ነው።
የመዘናጋት አደጋ የገጠማቸው ዘርፎች ሪፖርታቸውን ከወዲሁ እየሰማን ነው። ከእነዚህ መካከል ባለኮከብ ሆቴሎች ይገኙበታል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ በአዲስ አበባ ካሉ ትልልቅ ሆቴሎች 87 በመቶዎቹ ሥራቸውን በከፊል እና ሙሉ በሙሉ ዘግተዋል ተብሏል። አብዛኛዎቹ የአዲስ አበባ የሆቴል ደንበኞች የውጭ አገር ዜጎች ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የዓለም አቀፍ ጉዞዎች ሲታገዱ አዲስ ደንበኛ መምጣት አቁሟል፤ ያሉትም ከቫይረሱ ስርጭት ማስፋፋት ጋር ተያይዞ ወደ አገራቸው መመለሳቸው ለዘርፉ መሽመድመድ ሌላ ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል።
እናም የኮሮናን ሁለንተናዊ ጉዳት ለማሳጠር “ጥንቃቄ ይቅደም” የሚለው የባለሙያዎች ምክር የምንተገብርበት በእጃችን ያለው ቀን እነሆ ዛሬ ነው። እናም ዛሬን በአግባቡ እንጠቀምበት!
እንደመቋጫ
ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ የዘንድሮውን የትንሳኤ በዓል አስመልክተው ያስተላለፉት መልዕከት መዘናጋታችን ላይ የሒስ ልምጭ ያሳረፈ ነው። በአጭሩ እንዲህ ይላል። “…በማንኛውም ጊዜ ጠንቃቃና ዝግጁ ሆኖ መገኘት የጠቢብነት መገለጫ ነው። የምናውቀውንና የምናምነውን መተግበር ሲያቅተን ለምን? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል። በከፍታ የሚኖር እኛነታችንን ከልዕልና ወደ ዝቅታ የሚገፋብንን አጋጣሚ በሌሊት ጨለማ እንደሚመጣ ውስጥ አዋቂ ሌባ መቁጠር ነው።
በጨለማ ውስጥ አድብቶ ሀብታችንን ሊቀማ የሚመጣን ውስጥ አዋቂ ሌባ ጠመንጃ ታጥቀን አንመልሰውም። ጩቤ ታጥቆ መጠበቅም ቢሆን ብዙም ከጉዳት አያድነንም። በጨለማ ከሚመጣ ውስጥ አዋቂ ሌባ በሚገባ መከላከል የምንችለው በአዕምሯዊ ብርሃን ነው። …. ወደ ላይ ወደ ዕውቀትና ምግባር ከፍታ እንሂድ። በብርሃንም መንገድ እንመላለስ።..” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
አሁን አሁን የሕብረተሰቡ መዘናጋት በአንድ በኩል አንዳንድ ፖለቲከኞች በሌላ በኩል የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በመግታት ረገድ እየተጫወቱ ያሉት ሚና በአሳሳቢነቱ ይነሳል። ህብረተሰቡ ጋር ከመዘናጋትና ከግንዛቤ እጦት እንዲሁም የዕለት ጉርስ ከማሳደድ ድህነት ጋር በጥብቅ የተቆራኙ ችግሮች ይታያሉ። በሌላ በኩል አንዳንድ ፖለቲከኞች ከኮሮና ቫይረስ አሳሳቢ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተያይዞ መጪው የምርጫ ጊዜ እንዲሸጋገር ፓርላማው የሰጠው ውሳኔ ከሕዝብ ጤና በላይ እየረበሻቸው ነው። በዚህም ምክንያት በየጊዜው በመንግስት የሚሰጥ መረጃን ጭምር “የተጋነነ ነው፣ ሐሰት ነው” በሚል ውዥንብር በመንዛት ህብረተሰቡ ይበልጥ እንዲዘናጋ የሚሰሩ ኃላፊነት የጎደላቸው ፖለቲከኞች እያየን መሆኑ በእጅጉ ያሳስባል። ምርጫ የሚካሄደው፣ የመንግሥት ሥልጣን የሚኖረው የአገርና የሕዝብ ደህንነት ሲረጋገጥ መሆኑን እነዚህ ፖለቲኮኞች ተረድተው መጀመሪያ የሕዝብ ጤና ጥበቃ የጋራ አጀንዳ ላይ ከመንግሥት ጎን ሆነው በመስራት ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡና ሕዝባዊ አጋርነታቸውን በተግባር ሊያረጋግጡ ይገባል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2012
ፍሬው አበበ