አውሎ ነፋስ ፣ አውሎ ምድር ፣ አውሎ ባህር ፣ አውሎ ዝናብ ፣ አውሎ ደመና ፣ አውሎ ሰማይ ፣ አውሎ ጨረቃ ፣ አውሎ ከዋክብት ፣ አውሎ ገጠር ፣ አውሎ ከተማ … አውሎ አዲስ አበባ።
የአውሎ አይነቶቹን በ1985 ዓ.ም መስከረም ወር ከታተመው እፎይታ መጽሔት ተውሼ ነው። ወሰን ይሄይስ “አውሎ አዲሳባ” በሚል ርዕስ የጻፉት መጣጥፍ መግቢያ ላይ ይገኛሉ። ጸሐፊው አስር አውሎዎችን ደርድረው ደጅ ከጠኑ በኋላ የአዲስ አበባን ስም የሚጠሩት ለወቀሳ ነው። በቅድሚያ ስንኝ ቋጥረው እያዋዙ እንዲህ ይንደረደራሉ።
እስኪ ይሁና !
የስምሽ ምልኪ ቢቀና ቢያቀና
ያለጥርጣሬ እምነት የለምና
እውነት የለምና !
በቸርችል ጎዳና በአብዮት ጎዳና
ውስጡን በመርካቶ ወዲያ በቀበና።
በስድስት መስመር ግጥም ካሟሟቁ በኋላ ግለው እሳት መትፋት ይጀም ራሉ።
“አዲሳባ የጉንዳ ጉንድ መንደር ናትኮ። ምን የሌለ ጉድ አለ ? መንገዱ ቆሻሻ – ቤቱ ውሽልሽል ደሳሳ ! ለማኝ ተለማኙ ኮሳሳ! ምላስ ብቻ ! ሳቅ ብቻ! … ደሞ የስሟ ማማር! የነጋዴው እቃ ትርኪ ምርኪው መብዛቱ። ጨው ቢሏቸው ውድ ፣ ስኳር ውድ ፣ ዳቦ ውድ ፣ እንጨት ውድ ፣ ውሃ ውድ ፣ እና ውድ ብቻ ! ከቆሎ አቅም የሚሸጠው ከሳንቲም ቁጥር አይበልጥም። የአስር ሳንቲም አስር ፍሬ ፣ የሃምሳ ሳንቲም ሃምሳ ፍሬ። ችጋር ጠሪ!” እያሉ።
እንደ ጋሉ ሌሎች ብሶቶችን ያክላሉ። ከዚያ በግጥም አሟሙቀዋልና ምሬታቸውን ጨምቀው የተስፋ ገመድ ላይ እያሰጡ ፣ በግጥም ያቀዘቅዛሉ። እንዲህ እያሉ ፡-
«ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ
አገርም እንደ ሰው ይናፍቃል ወይ»
ብለው ያደነቁሽ ይበቃሻል ወይ ?
ወይስ ላክልልሽ እኔም በድርሻዬ
ማጠንተ ዲያቢሎስ ኩነኔዬ ብዬ
የሳጥናኤል እሳት ነበልባሌ ብዬ
ገለባዬ ብዬ።
አንችም ትኖሪያለሽ እኔም አለሁልሽ
ገለሽ ባትጨርሺኝ ሞቼ ባላልቅልሽ
እጅሽ ለኛም ገብቶ እስከምታዘብሽ።
እንግዲህ የወሰን ይሄይስ ጽሑፍ እንደሚነግረን ከ27 ዓመታት በፊትም የአዲስ አበባ ኗሪዎች ከፍ ያለ ምሬት ውስጥ ነበሩ። ኧረ እንዲያውም የአዲስ አበባ ችግር ከተቆረቆረችበት ዘመን የሚጀምር ነው።
መጋቢት 12 ቀን 2001 ዓ.ም የታተመው አዲስ ነገር ጋዜጣ የጋዜጠኞች ቡድን በማዋቀር ሰፋ ያለ ጊዜ ወስዶ ጥናት በማድረግ የአዲስ አበባ ከተማን ችግሮች በዝርዝር የሚያሳይ ልዩ እትም አስነብቦ ነበር። ጋዜጣው “The Fate of Addis Ababa” በሚል ንዑስ ርዕስ ስር የከተማዋ ችግሮች ከምን እንደመነጩ ሲገልጽ “ከተማዋ ከተቆረቆረች ጊዜ ጀምሮ ያለ ፕላን ከመመራቷ ፣ በተለያዩ ጊዜያት ከገጠማት ደካማ አመራርና አስተዳደር እንዲሁም ከአገሪቱ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት ጋር የተያያዙ ናቸው። ይሁኑና በኢህአዴግ የ18 አመታት አመራር አዲስ አበባ ብዙዎቹ ችግሮቿ ሲባባሱባት እንጂ ሲቀረፉላት አልታየም።” ይላል።
ከሁለት አመታት ወዲህ በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የጋዜጣው ድምዳሜ ትክክል ነበር የሚያሰኙ ናቸው። አዲስ አበባ አዲስ መንገድ ላይ ትገኛለች። የለገሀር የተቀናጀ መንደር ፣ የአድዋ ማዕከል ፣ የአዲስ አበባ ወንዞች ዳርቻ ልማት ፣ ግዙፍ የመኪና ማቆሚያዎች ፣ የትልቅ ቤተ-መፃሕፍት ፣ የሳር ቤት ቄራ ጎተራ መንገድ ፣ የሸገር ዳቦና የዳቦ ዱቄት ፋብሪካ ፣ የመስቀል አደባባይ ማዘጋጃ ቤት የአረንጓዴ ስፍራ መልሶ ማልማት ፣ የተለያዩ ፓርኮች ፣ ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት አካል የሆነው የእንጦጦ ፕሮጀክት እና ሌሎችም ግንባታዎች እየተቀላጠፉባት ነው።
አዲስ አበቤዎችም ከተማቸው በተያያዘችው መንገድ ደስ መሰኘታቸውን እየገለጹ ነው። ታዲያ ሁሉም አይደሉም ፤ አንዳንዶች አይናቸው ቀልቷል። ከቦሌ አየር ማረፊያ እስከ ቤተ መንግስት ያለው መንገድ በአበቦችና በምሽት መብራቶች ሲያሸበርቅ ጉልበታቸው ሽብርክ ያለባቸው አሉ። መስቀል አደባባይ ተቆፍሮ ከስር ከሁለት ሺ በላይ መኪናዎች ማቆሚያ እንዲሆን ተደርጎ እየተሰራ ነው ሲባሉ “ጉድ ተሰራን” ብለው ሙሾ ያወረዱም አሉ። ከታላቁ ቤተመንግስት እድሳት ጋር በተያያዘም የፒኮክ ንትርክ ውስጥ የተነከሩ ነገር አንኳሪዎች ብዙ ናቸው። ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶቹን እንደ ምርጫ ቅስቀሳ በመቁጠር ጨርቃቸውን የጣሉ “ፓለቲከኞች” ም ታይተዋል።
በከተማዋ ላይ የሚካሄዱ የልማት እንቅስቃሴዎችን ከስር ከስር እየተከታተሉ አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ የሚነዙ ነዝናዞች ደንዝዘዋል። አዲስ አበቤ በመተርተር ሳይሆን በመመተር ማመን ጀምሯል። አውርቶ አዳሪዎች “መጥፊያህ ነው” የሚሉት ነገር መዳኛው ሲሆን እያየ ነው። አዲስ አበባ በምግብ ራሷን እንድትችል ለማድረግ የከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ሲቋቋም የተካሄደው አፍራሽ ዘመቻ የከሸፈው በአዲስ አበቤዎች ንቃት ነው።
በ2006 ዓ.ም መጋቢት ወር የታተመው አዲስ ጉዳይ መጽሔት የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን ጨምሮ የከተማዋን ፓርክና መናፈሻ በማዘጋጀት ጉልህ ተሳትፎ የነበራቸውን ኢንጂነር ጌታቸው ማህተመ ስላሴን እንግዳው አድርጎ ነበር። ኢንጂነሩ የአዲስ አበባን ከተማ የምግብ ውድነት ችግር በምን መፍታት ይቻላል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ እንዲህ አሉ “በከተማ ህዝቡ በምግብ ውድነት ከሚደርስበት ችግር ለማዳን በመጣር ፈንታ ለም የሆኑ እና ማዳበሪያ የማይፈልጉ መሬቶች ለሕንጻ ግንባታ እየተሰጡ ነው። ይሄ በተለይ የግብርና ሙያተኞችን ይመለከታል። ባለስልጣናቱ ባያውቁት እንኳን የግብርና ሙያተኞቹ መሟገት ሲገባቸው ዝም ማለታቸው ተጠያቂ ከመሆን አያድናቸውም።” የኢንጂነሩ ምላሽ የአዲስ አበባ አዲስ መንገድ አዋጭ መሆኑን ያመላክታል።
በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ የተስፋ ብርሃን ቢፈነጥቅም ፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አሁንም በአንገብጋቢ ችግሮች እየተንገበገቡ ነው። የመኖሪያ ቤት ችግር፣ የኑሮ ውድነት፣ ስራ አጥነት ፣ የውሃና መብራት መቆራረጥና የትራንስፖርት ችግር ቀጣይ ስራን የሚጠይቁ ጉልበት ፈታኝ አቀበቶች ናቸው። እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ አሊያም ለመቀነስ የከተማዋ አስተዳደር ብዙ ርቀት መጓዝ ቢጠበቅበትም ባለፉት ሁለት አመታት የታዩት የልማት እንቅስቃሴዎች የከተማዋ ነዋሪዎች ተስፋ እንዲሰንቁ አድርገዋል።
ፕሮፌስር መስፍን ወልደማሪያም “አዲስ አበባ የመሬት ቅርጫ” በሚል ርዕስ በ2006 ዓ.ም ሚያዝያ ወር በታተመው ፋክት መጽሔት ላይ ያወጡትን ጽሑፍ ሲቋጩ “የቅሚያና የዝርፊያ ጊዜ እንዳለ ሁሉ የፍትህና የማስተካከያ ጊዜ አለ። ደሃዎችን ለሚያደኸዩ ጊዜ እንዳለ ሁሉ ዘራፊዎችን ሙልጭ ለሚያወጣ ጊዜ አለ። ሰለሞን ለሁሉም ጊዜ አለ ብሏልና።” ብለዋል። ፕሮፌሰሩ እንዳሉት አዲስ አበባ የምትካስበት የፍትህ ዘመን እየመጣ ይሆን ?
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2012
የትናየት ፈሩ