የኖቭል ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ከቀላል እስከ ከባድ የመተንፈሻ አካል ሕመም የሚያስከትል የቫይረስ ዝርያ ነው። በበሽታው የተያዙ ሰዎች ትኩሳት፣ ሳል፣ የትንፋሽ መቆራረጥና የመተንፈስ ችግር ምልክቶች ይታይባቸዋል። በዓለም ጤና ድርጅት አገላለጽ፣ ኮሮና ቫይረስ የተለያዩ የቫይረስ ዓይነቶችን የያዘ የቫይረስ ቤተሰብ ነው።
ይህ ቫይረስ በሰዎችና በእንስሳት ላይ በሽታን ያስከትላል። በሰዎች ላይ የሚከሰተው ኮሮና ቫይረስ የመተንፈሻ አካላትን በመጉዳት ከተራ ጉንፋን እስከ ከፍተኛ የመተንፈሻ አካል ችግር የሚያደርስ ነው። ሽታው በጠናባቸው ታማሚዎች ላይ ደግሞ እንደ ሳንባ ምች (ኒሞኒያ)፣ ከባድ የመተንፈሻ አካላት ሕመም የሚያሳይ ሲሆን፣ የኩላሊት ሥራ ማቆምና ሞትን ሊያስከትል የሚችል በሽታ ነው።
በመግቢያዬ የተጠቀምኩት ሐሳብ ለሁላችሁም አዲስ እንዳልሆነ ይታወቃል። ይሁንና ማወቅና አውቆ መተግበር ለየቅል ናቸውና በብዞቻችን ዘንድ እየተስተዋለ ያለው መዘናጋት አሳሳቢ በመሆኑ መደጋገሙ ይበልጥ ትኩረት ይሰጠው ዘንድ ነው። በአሁኑ ወቅት በሽታውን አቅልሎ ከማየት ባሻገር ‹ብንያዝ በፍጥነት እናገግማለን› የሚል አጉል ሀሳብ ውስጥ ገብተንም እንገኛለን..። በየቀኑ ከበሽታው ያገገመው ሰው እየጨመረ ሲመጣ ህዝቡ ወደ ተለመደው እንቅስቃሴው ገብቷል ማለትም ይቻላል።
እረ ጎበዝ! ተያይዘን ልናልቅ እኮ ነው!! በኮሮና ምክንያት እረፍት ላይ ያለው ጥቂት የማይባል ሰው የጎረቤቱን በር እያንኳኳ ያለፈውን ነገር በማንሳት አተካሮ መግጠም ሁሉ ይዟል እየተባለም ነው። ኮሮናው ይለፍ እንጂ ልክ አስገብሃለው፤ አስገባሻለሁ እየተባባለም መሆኑ እየተነገረ ነው። እይይ…..መቼም ሰው አዕምሮ ሲያርፍ በቃ ነገር ያስባል……ውይ ስራ መዋል ለካ ከብዙ ነገር ይቆጥባል…ማለት ነው።
ኮሮና ወደ አገራችን ከገባ ጀምሮ ከበሽታው ይልቅ የሰው ጭቅጭቅ በርትቷል….ለምን ቢባል አኗኗራችን በጣም የተጠጋጋ ስለሆነና ማህበራዊ መስተጋብሮቻችን ይሉኝታን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ነው..። በአዲስ አበባ ይሁን በክልል ከተሞች ተመሳሳይነት ያለው አኗኗር ዘይቤ አለ። የምንጣላበትም..የምንዋደድበትም ሆነ የምንቀራረብበት ሁኔታ ተመሳሳይነት አለው..።
አብዛኛው ሰው አንድ ቦታ መቀመጥ ስለማይችል እየተዘዋወረ መዋልን …አማራጭ አድርጎታል..፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ ከውጭ መጥተው በለይቶ ማቆያ ውስጥ ያሉት ላይ ይብሳል…። በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲቀመጡ ሲደረግ ከህብረተሰቡ ጋር እንዳይቀላቀሉ ታስቦ ቢሆንም ‹‹አንድ ቦታ መቀመጥ አልወድም›› በሚል ገንዘብ እየከፈሉ ተዟዙሮ መመለስን ስራ አድርገውታል።
አንዳንድ ክልል ላይ ለይቶ ማቆያ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ከነጭራሹ እዛው እንደማይቀመጡ እየተነገረ ይገኛል። ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያታቸው የቦታው አለመመቸት፣ ምግብና መዝናኛ በበቂ ሁኔታ አለመሟላትና አንድ ቦታ ለመቀመጥ መሰልቸት ይጠቀሳሉ። በአዲስ አበባ ደግሞ የተዘጋጀው ለይቶ ማቆያ በዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ በመሆኑ ከውጭ የመጡ ሰዎች አንድ ቦታ ተሰብስበው በማውራት፣ ፎቶ በመነሳትና ተጠጋግቶ በመቀመጥ ጊዜያቸውን እንደሚሳልፉ ሲታይ የኮሮና ጥንቃቄ እንደተረሳ ማስተዋል ያስችላል።
መቼም በአለም ላይ የተለያዩ ወረርሽኞች ተከስተው እንደነበር የሚታወስ ነው..። ከዚህ ውስጥ ታድያ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ይጠቀሳል። በወቅቱ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ስርጭት ለመግታት በመገናኛ ብዙኃን በኩል ድራማዎች፣ የግንዛቤ ስራዎችና መልዕክቶች በብዛት ይተላለፉ ነበር…..። በተጨማሪም በየአካባቢው የፀረ ኤድስና ስነ ተዋልዶ ክበቦች ተቋቁመውም እስከቀበሌ ድረስ ትምህርት እንዲሰጥና በበሽታው የተያዙ ሰዎችን የማስታመም ስራ ይከናወን እንደነበር ይታወሳል….። ነገር ግን ስለ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በሽታ ግንዛቤ እንሰጣለን የሚሉት ሰዎች ከበሽታው ማምለጥ አልቻሉም ነበር….። ምክንያቱን ለናንተ ልተወው…።
ወደ ተነሳሁበት ልመልሳችሁና በኮሮና ቫይረስ መከሰት ምክንያት የመንግስት መስሪያ ቤቶችና ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል…። በሚያስደንቅ ሁኔታ ግን ህዝቡ እንደበፊቱ ምንም እንዳልተፈጠረ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል..። ተማሪዎችም በእረፍት ጊዜያቸው እንደሚደርጉት በመዝናናት ላይ ይገኛሉ። በትራንስፖርትና በሌሎች ቦታዎች የሚደረጉ ግርግሮች እንደቀጠሉ ናቸው..። መንግስትም የሚሰጠውን ማሳሰቢያ አጠናክሮ ቢቀጥልም….በሽታው እየተስፋፋ ይገኛል..።
እኔ የሚገርመኝ ግን የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ ገባ ከተባለበት ቀን ጀምሮ ለሁለት ሳምንት ህብረተሰቡ ቤቱ ተከትቶ….በየመንገዱ የእጅ መታጠቢ ቦታዎች ተዘጋጅተው……የግንዛቤ ስራዎች በበጎ ፈቃደኞች ይሰጥ ነበር..።አሁን የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ሲጨምር ሁሉም ነገር እርግፍ ተደርጎ የተተወው ለምን ይሆን? ህብረተሰቡስ ስለ ቫይረሱ አደገኝነት እየሰማ ከመጠንቀቅ ይልቅ ወደ ድሮ ልማዱ የተመለሰውስ ምን ተማምኖ ነው?…መልሱን እያንዳንዳችን በልባችን እንመልሰው..።
ሌላው ደግሞ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እጅን ቶሎቶሎ መታጠብ የሚመከር በመሆኑ የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በተቻለው አቅም ውሃ ለማዳረስ እንደሚጥር ተናግሮ ነበር…። ተናግሮም አልቆመም የቫይረሱ ስርጭት በተሰማበት ወቅት በቦቴና…..በፈረቃ ውሃ ሲያሰራጭ ቆይቷል…። ነገር ግን የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ውሃውን ይዞ ጠፍቷል..። ታዲያ እንዴት ከበሽታው እንድን ይሆን?
ህዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ እንዲደረግ የሚመከረውን ማስክ አጠቃቀም ብናስተውል በጣም ያስገርማል…፤ አንዳንዱ አገጩ ስር፣ አንዳንዱ ግንባሩ ላይ፣ አንዳንዱ አውልቆ እግሩ ላይ ምን አለፋችሁ ማስኩን ለምን እንዳደረገ የማያውቅም ሰው እንዳለ መታዘብ ይቻላል..። የማስክ ነገር ከተነሳ በየመንገዱ የተጣለ ማስክ አንስተው አጥበው የሚሸጡ እንዳሉ ስንቶቻችን ታዝበን ይሆን? ልብ ልንል ይገባል…። መተዛዘን እንደው ዘንድሮ ጠፍቷል…፤ ብቻ ፈጣሪ ካልጠበቀን መጨረሻችን እንደ ሌሎች አገር መሆኑ አይቀርም…። አጉል ድፍረት ግን ከሞት ጋር ያላትማልና ከመሞት መሰንበትን መርጠን የጤና ባለሙያውና መንግስት የሚሉንን እንተግብር። ቸር ሰንብቱ…፤ ርቀታችሁን ጠብቁ…፤ ቶሎ ቶሎ ታጠቡ…። በተለይ ደግሞ ፀሎት ማድረግ አትርሱ..።
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2012
መርድ ክፍሉ