‹‹ከምንም በላይ ምን ጊዜም ቢሆን ህግ መከበር አለበት›› የሚል ፅኑ እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ። ‹‹ህግ በመከበሩ የሚታጣ ነገር ካለም ቢታጣ አያስከፋም›› ብለውም ያስባሉ፤ አሁን አሁን ግን በህግ አክባሪነታቸው ቤት ማግኘት አለመቻላቸውን ሲያስተውሉ መፀፀት መጀመራቸውን አልሸሸጉም – በአዲስ አበባ ሽሮሜዳ አካባቢ ተወልደው ያደጉት አቶ ጌታቸው መኮንን።
በኢትዮጵያ ማተሚያ ኮርፖሬሽን በ1976 ዓ.ም ተቀጥረው ስራ የጀመሩት አቶ ጌታቸው፣ ከ36 ዓመታት በላይ በመንግስት ሰራተኝነት አገልግለዋል። ኮርፖሬሽኑ ሲፈርስ በተቋሙ ስር ይተዳደር ወደነበረው የካቲት የወረቀት ሥራዎች ድርጅት ተዘዋውረው ሲሰሩ ቆይተዋል። ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ በመንግስት ሰራተኛነት ቢያገለግሉም ቤት መስራትና እንደእኩዮቻቸው የመንግስት ሰራተኞች በቤታቸው በመኖር ዘመናቸውን ማጣጣም አልቻሉም።
በእርግጥ እርሳቸው ገና ሥራ እንደያዙ በ1976 ዓ.ም ‹‹በማህበር ቤት ለመስራት ተደራጁ›› ቢባልም በደመወዝ ስኬል ስለነበር በወቅቱ ማሟላት ባለመቻላቸው ዕድሉ ያመለጣቸው መሆኑን ይገልፃሉ። ኢህአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላም በ1985 ዓ.ም አካባቢ ለቤት መስሪያ 105 ካሬ ሜትር ቦታ ሲሰጥ ‹‹4 ሺህ ብር ተቀማጭ ያስፈልጋል›› በመባሉና እርሳቸው ተቀማጭ ገንዘብ ስላልነበራቸው እንዲሁም ደመወዛቸውም አነስተኛ ስለነበር በድጋሚ ዕድሉ እንዳመለጣቸው ይጠቅሳሉ።
እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎች ሰዎች ምንም እንኳ እነዚህ ህጋዊ ዕድሎች ቢያመልጧቸውም፤ የቅርብ ጓደኞቻቸውን ጨምሮ የተለያዩ ሰዎች በየጊዜው እርሳቸው ተከራይተው በሚኖሩበት የአሁኑ የካ ክፍለ ከተማ 01 ቀበሌ ፈረንሳይ አካባቢ ጫካ የነበረውን ሜዳና ተራራ ሳይቀር እየተመነጠሩ የመሬት ወረራ እያደረጉ ቤት መገንባታቸውን ያወሳሉ፤ እርሳቸው ግን ህገወጥነትን ተቃውመው በመታገላቸው በዛው አካባቢ ለ40 ዓመታት በግለሰብ ቤት ተከራይነት ለመኖር ተገደዋል።
ብዙዎች ‹‹የቤት ባለቤት ለመሆን ‹በህግ ተጠያቂ እሆናለሁ› የሚል ፍራቻን አስወግደህ፤ ደፍረህ አንዱን መሬት አጥረህ ቤት ስራ።›› የሚል ተደጋጋሚ ምክር ቢሰጧቸውም፤ እርሳቸው ግን ድርጊቱን የሚፈፅሙ ግለሰቦችን በመቃወም እርሳቸውም በህገወጥ መንገድ መሬት ሳይከልሉ እና ቤት ሳይሰሩ መኖራቸውን ነው የሚናገሩት።
‹‹ዓይኔ እያየ በቅርብ የማውቃቸው ሰዎች የጨረቃ ቤት ሲሰሩ፤ መንግስት ባለበት አገር ትክክል አይደለም በሚል እቃወም ነበር›› የሚሉት አቶ ጌታቸው፣ ቀዳሚ የመሬት ወራሪዎቹ ብዙ ባለመጎዳታቸው የመንግስት ሰራተኛ ሆነው የቆጠቡትን ገንዘብ በህገወጥ ግንባታ ላይ አውለው የገነቡት ፈርሶ ኪሳራ እንደማይገጥማቸው ቢገምቱም በዋናነትም የህግ አክባሪነት ፅኑ እምነታቸው እና ህሊናቸው እንደጓደኞቻቸው ህግ ለመጣስ አልፈቀደም፤ በመሆኑም በህገወጥ መንገድ መሬት ወረው ቤት በመገንባት ዘመናቸውን የቤት ባለቤት ሆነው ማሳለፍ አለመቻላቸውን ይገልፃሉ።
ወንደላጤነትን በኪራይ ቤት ያሳለፉት አቶ ጌታቸው፣ የትዳር ህይወታቸውንም ያሳለፉት በኪራይ ቤት ነው። ከአንዱ ቤት ወደ ሌላው ቤት በተከራይነት እየተንከራተቱ አንድ ወንድ እና አንድ ሴት ልጅ ወልደዋል። በተደጋጋሚ የቀበሌ ቤት ለማግኘት ሲያቀርቡ የነበረው ጥያቄ እንደርሳቸው ገለፃ፤ ሹመኛ፣ የፖለቲካ ሰው ወይም ከአመራሮች ጋር የተለየ ግንኙነት ያላቸው ባለመሆኑ ምላሽ አጥተዋል። አማራጫቸው የግለሰብ ቤትን መከራየት ብቻ ሆኖ አሁንም ድረስ ቀጥሏል።
በ1997 ዓ.ም መሬት መስጠት የማይቻል በመሆኑ ቤት ለማግኘት ‹‹የጋራ መኖሪያ ቤት ለማግኘት ተመዝገቡ›› በተባለው መሰረት ደመወዛቸውን ታሳቢ አድርገው ባለሁለት መኝታ ተመዝግበዋል። በጊዜው ምንም እንኳ ባለትዳር ቢሆኑም ባለቤታቸው ‹‹ሁለት ዕድል እንዲኖረን ልመዝገብ›› ሲሉ እርሳቸው ግን ‹‹አይቻልም፤ ለአንድ ቤተሰብ አንድ ቤት ነው። ባልና ሚስት ለየብቻ መመዝገብ የማይቻል በመሆኑ የወጣውን ህግ እናክብር። በሌላ በኩል ህግ በመጣሳችን ‹ሁለታችሁም ለምን ተመዘገባችሁ› በሚል የባሰ ዕድሉን እናጣለን›› በማለት እርሳቸው ብቻ መመዝገባቸውን ያስታውሳሉ።
ቅድሚያ ቤት ያጡት ተቀማጭ ገንዘብ ባለመኖሩ መሆኑ ያስቆጫቸው አቶ ጌታቸው፣ በ2005 ዓ.ም በዳግም ምዝገባ ሲካሄድ የቀደመ የባለ ሁለት መኝታ ምዝገባ በባለ ሶስት መኝታ እንዲለወጥ ቢጠይቁም፤ ‹‹ከባለ ሶስት መኝታ ወደ ባለ ሁለት መኝታ ማለትም ከላይ ወደ ታች እንጂ ከታች ወደ ላይ መቀየር አይቻልም›› ተባሉ። ያንኑ ባለ ሁለት መኝታ ቤት ለማግኘት በየወሩ መከፈል አለበት ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ሳይታክቱ ያላቸውን በመቆጠብ ‹‹ቅድሚያ ይሰጠኝ ይሆናል›› በሚል ገንዘብ ቢያስቀምጡም ከ15 ዓመት በፊት ተመዝግበው ዛሬም ድረስ ቤት እንዳላስገኘላቸው ይገልፃሉ።
‹‹በመሬት ወረራ አልሳተፍም›› በሚል ያከበሩት ህግ በባልም በሚስትም ስም ለጋራ መኖሪያ ቤት አልመዘገብም በማለት መድገማቸው እንዲሁ ዋጋ እያስከፈላቸው መሆኑን ይገልፃሉ። ህግ ሳያከብሩ ባል እና ሚስት ለየብቻ የተመዘገቡ አንዱ ቢያጣ ሌላው እያገኘ የቤት ባለቤት ሲሆኑ ማየታቸውን ይናገራሉ። አሁን አንዳንዶች ሚስት ለብቻ ባል ለብቻ ቤት እንዳላቸው እያዩ ነው። እርሳቸውና ቤተሰባቸው ግን እንኳን ሁለትና ሶስት ቤት ቀርቶ የአንድ ቤት ባለቤትነት ብርቅ ሆኖባቸው ዛሬም ድረስ ህይወታቸውን እየገፉ ይገኛሉ።
‹‹የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ ወጥቶላቸው አሁንም ድረስ የቀበሌ ቤት ውስጥ ያሉ አሉ›› የሚሉት አቶ ጌታቸው፣ እርሳቸው ግን እስከአሁን 4 ሺህ 500 ብር የቤት ኪራይ እየከፈሉ እንደሚኖሩ ይገልፃሉ። ስለተከራይነት ህይወታቸው ሲገልፁ፤ በ1996 ዓ.ም ትዳር የመሰረቱ ሲሆን፣ ትዳር ከመያዛቸው በፊትም ሆነ በኋላ ‹‹የምኖረው ተሳቅቄ የአከራይ ፊት አይቼ ነው›› በማለት ይናገራሉ።
አቶ ጌታቸው፣ ከአስር በላይ የግለሰብ ቤቶችን እንደተከራዩ ይገልፃሉ። ያከራዩዋቸው ሰዎች አንዳንዴ የቤት ኪራይ የሚጨምሩ መሆኑን በማስታወስ፤ በተለይ በገቡ በሶስት ወራቸው የቤት ኪራይ የተጨመረባቸው በመሆኑ መክፈል አቅቷቸው መጨነቃቸውን ያስታውሳሉ። ዕቃ ማጓጓዝ የሚያስወጣው ወጪና የዕቃው መንገላታት እጅግ አማርሯቸው ዕቃዎቻቸውን እስከመሸጥ መድረሳቸውን በማስታወስ፤‹‹ዕቃ አልገዛም በማለቴ ከባለቤቴ ጋር የምጋጭበት ሁኔታ አለ›› በማለት ይናገራሉ። ዕቃ ያለመግዛት ምክንያታቸው መቼ ከሚኖሩበት ቤት እንደሚለቁ ወደ ፊት ምን ዓይነት ቤት እንደሚኖራቸው ስለማያውቁ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
‹‹ልጆቼ የማጥኛ ቦታ የላቸውም፤ ወላጆቻቸው ተከራይ በመሆናቸው ደስተኞች አይደሉም። ነፃነት አይሰማቸውም›› የሚሉት አቶ ጌታቸው፤ የ16 ዓመት እና የ20 ዓመት ልጆቻቸው ነፃነት ሳይሰማቸው ማደጋቸውን ይናገራሉ። የኤሌክትሪክ ምድጃ መጠቀም፣ በፈለጉት ጊዜ ውሃ መቅዳትም ብርቅ መሆኑን ገልፀው፤ እንግዳ መጥቶ መጸዳጃ ቤት ሲገባ እንኳ እንደሚሳቀቁና ይህም አይነት ኑሮ እጅግ እያማረራቸው መሆኑን ይናገራሉ።
ቤተሰቡ ሳይቸገር ውሃ እንዲጠቀም፣ እንደፈለጉ ልብስ ለማፅዳትም ሆነ ገላ ለመታጠብ አከራዮች ሳይቀሩ የሚጠቀሙበትን የውሃ ቆጣሪ ክፍያ ‹‹እኔ እከፍላለሁ›› ቢሉም፤ አከራዮች ፈቃደኛ እንደማይሆኑ ይገልፃሉ። ሌሊት መብራት ለማብራት ቢፈልጉ እንደማያበሩ፤ ቴሌቪዥን ከፍተው እንደማያዩና ለፍሪጅ እንኳ እንደሚሳቀቁ፤ የልብስ ካውያ ፍፁም መጠቀም የማይቻል መሆኑን በማስታወስ፤ እንደሰው ለመኖር አዳግቷቸው መቆየታቸውን ይገልፃሉ።
አሁን በ24 ካሬ ሜትር ቤት ውስጥ እንደሚኖሩ በማስታወስ፤ በዚህ በወረርሽኝ ወቅት ቤተሰቡን አራርቆ ለማስተኛትም ሆነ ተራርቆ ለመቀመጥ የማያመች መሆኑን ያመለክታሉ። ያም ቢሆን አቶ ጌታቸው ‹‹እጅግ ብማረርም ዛሬም ተስፋ አልቆርጥም፤ በተለይ የጋራ መኖሪያ ቤት አገኛለሁ ብዬ በተስፋ ብቻ እኖራለሁ›› ብለውናል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2012
ምህረት ሞገስ