ከግብፅ ካይሮ ተነስቶ ደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን የሚደርሰውና ከ10 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍነው የትራንስ አፍሪካን አውራ ጎዳና ፕሮጀክት አካል ነው። ከሞጆ ሃዋሳ ከሚዘልቀው የፍጥነት መንገድ ጋርም ይገናኛል። በልዩ ልዩ ውጣ ውረዶች በመፈተኑም ለዓመታት ሊዘገይ ችሏል። የሃዋሳ – ጭኮ የመንገድ ፕሮጀክት።
በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የደቡብ ሪጅን የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ማኔጅመንት ዳይሬክተር ኢንጂነር ደጀኔ ጉቱ እንደሚገልፁት፤ የመንገድ ፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ በሚያዚያ ወር 2013 የተጀመረ ነው። በአጠቃላይ 66 ኪሎ ሜትር የሚረዝምና በአስፓልት ኮንክሪት ደረጃ የሚሰራ ነው።
የመንገድ ፕሮጀክቱን ኤስ.ኢ.ደብሊው ኢንፍራስትራክቸር /SEW infrastructure/ የተሰኘው የህንድ ተቋራጭ እ.ኤ.አ እስከ ሚያዝያ 2016 ድረስ በሶስት ዓመታት ውስጥ አጠናቆ እንዲያስረክብ ተሰጥቶታል። እስከዚሁ ጊዜ ድረስም ተቋራጩ ሰላሳ ከመቶ ያህሉን የመንገድ ፕሮጀክቱን ግንባታ ስራ አከናውኗል። ከስልሳ ስደስት ኪሎ ሜትሩም 22 ኪሎ ሜትር ያህሉን አስፓልት የማልበስ ስራ ሰርቷል።
ይሁን እንጂ ተቋራጩ የመንገዱን ፕሮጀክት የሰራባቸው ቦታዎች ላይ የጥራት ችግሮች በመታየታቸውና የአፈፃፀም ድክመት የነበረ በመሆኑ የኮንትራት ስምምነት ህጉን በመከተልና ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር በመነጋገር ውሉ እንዲቋረጥ ተደርጓል። ውሉ ከተቋረጠ በኋላም አዲስ ጨረታ በማውጣት ሲኖሃይድሮ ኮርፖሬሽን / sino haydro corporation/ የተሰኘ የቻይና ኩባንያ ፕሮጀክቱን እንዲቀጥል ተደርጓል። የማማከር ስራውን ደግሞ ኤ.አይ.ሲ ፕሮጌቲ /AIC progeti/ የተሰኘ የጣልያን አማካሪ ድርጅት ሲሰራ ቆይቷል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ የፕሮጀክቱን ውል ለማቋረጥ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር ሲደረጉ የነበሩ ንግግሮችና የጨረታ ሂደቶች ጊዜ በመፍጀታቸው አዲሱ ስራ ተቋራጭ ፕሮጀክቱን እ.ኤ.አ በጥር ወር 2017 ካቆመበት ለማስጀመር ተገዷል። ይኸው ስራ ተቋራጭ ቀሪውን 44 ኪሎ ሜትር መንገድ ለሁለት ዓመታት ሲያከናውን ቆይቶ እ.ኤ.አ በታህሣሥ ወር 2019 በማጠናቀቅ ለትራፊክ ክፍት እንዲሆን አድርጓል። ከጥቃቅን የማስተካከያ ስራዎች ውጪም መንገዱ ተጠናቆ በቅርቡ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ የመንገድ ፕሮጀክቱ በኮንትራት ስምምነቱ መሰረት በተያዘለት ጊዜ ሊጠናቀቅ አልቻለም። ለዚህም ቀደም ሲል ፕሮጀክቱን ይዞ የነበረው ተቋራጭ የስራ አፈፃፀም ደካማ መሆንና የጥራት ችግር ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል። በዚህም ምክንያት ፕሮጀክቱ ለዓመታት ዘግይቷል። በዚሁ የመንገድ ፕሮጀክት መዘግየት ምክንያትም መንገዱ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች ላይ የሚገኘው ህብረተሰብም ለተደጋጋሚ ችግሮች ሲጋለጥ ቆይቷል። የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንም እያከናወናቸው ካሉ ፕሮጀክቶች ውስጥ ዋጋ የከፈለበትና በበርካታ ውጣውረዶች ውስጥ ያለፈበት የመንገድ ፕሮጀከት ይኸው የሃዋሳ ጭኮ የመንገድ ፕሮጀክት ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ በሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም በሲዳማ ዞን በተነሳው ረበሻ ምክንያት መንገዱ ሁለት መቶ አስራ አምስት ቦታዎች ላይ ተቆፋፍሯል። የውሃ ፍሳሽ ማስወገጃው ላይም ጉዳት ደርሷል። ይህንኑ የተጎዳ መንገድ መልሶ ለማስተካከልም ተጨማሪ ጊዜ ወስዷል፤ አምስት ሚሊዮን የሚሆን ገንዘብም ወጪ ተደርጓል። ይህም ለመንገዱ መዘገየት ሌላኛው ውጣውረድ ሆኖ ይጠቀሳል። በጭኮ ከተማ ያጋጠመው የውሃ መውረጃ (ድሪኔጅ) ችግርም የዚሁ የመንገድ ፕሮጀክት ውጣውረድ አካል ነበር።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ የመንገድ ፕሮጀክቱ የተለያዩ ስፋቶችን የያዘ ሲሆን፣ በሃዋሳ ከተማ ውስጥ የሚያልፈው አንዱ ጎን በአንድ ጊዜ ሶስት ተሽከርካሪዎችን የሚያሳልፍ ነው። 8 ኪሎ ሜትር ያህሉ 29 ነጥብ 5 ስፋት፣ በወረዳ ከተሞች ውስጥ ማለትም በቱላ፣ አፖስቶና ጭኮ የሚያልፈው 19 ሜትር ስፋት እንዲሁም በቀበሌ ከተሞች ውስጥ የሚያልፈው ደግሞ 12 ሜትር እንዲሁም በገጠር ከተሞች ውስጥ የሚያልፈው 10 ሜትር ስፋት ይዟል።
የመንገድ ፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ በጥር ወር 2020 ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ሆኗል። ፕሮጀክቱ የተከናወነው በአፍሪካ የልማት ባንክ የገንዘብ ድጋፍና በመንግስት በጀት ሲሆን፣ በአጠቃላይ 965 ሚሊዮን ብር ፈጅቷል። ቀደም ሲል መንገዱ ከመገንባቱ በፊት የአካባቢው ማህበረሰብ በመንገድ እጦት ሲቸገር ቆቷል። በተለይ ማህበረሰቡ ከሃዋሳ ከተማ ጭኮ ለመደረስ ከሁለት አስከ ሶስት ሰዓት ያህል ይፈጅበት ነበር። ይሁንና መንገዱ ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ጭኮ ከተማ ለመድረስ የሚደረገውን ጉዞ ከሰላሳ እና አርባ ደቂቃ በታች ዝቅ አድርጎታል። በዚህም ህበረተሰቡ በከተሞቹ መካከል የሚያደርገውን ምልልስ ከፍ እንዲል አድርጎታል።
በሌላ በኩል ደግሞ በአካባቢው ላይ ሰፊ የቡና አትክልትና ፍራፍሬ ምርት የሚካሄድበት በመሆኑ እነዚህን ምርቶች በይርጋለም እየተገነባ ወዳለው የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለማጓጓዝ እና ከዛም ከፓርኩ ተቀነባብሮ የሚወጣውን ይህንኑ ምርት ወደ አዲስ አበባ እና ሌሎችም አካባቢዎች ለገበያ ለማቅረብ መንገዱ ትልቅ አድል ይፈጥራል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2012
አስናቀ ፀጋዬ