ከአዲስ አበባ ደቡብ ምስራቅ በአምስት መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ የሐረሪ ክልል ዋና ከተማ ናት። ከተማዋ ለዘመናት በከፍተኛ የንግድ ማዕከልነትም ትታወቃለች። ከመሀል አገር፣ ከአፍሪካ ቀንድና ከአረብ አገራት ጋር እንዲሁም ከቀሪው አለም ጋር በንግድ የተሳሰረች እንደነበረችም በታሪክ በስፋት ይነገራል። ከዚህም በላይ ሀረር መስካሪዋ የበዛ የፍቅር አገር ነች።
የሀረር ህዝብ ታሪኩ፣ ባህሉና ማንነቱ ከከተማዋ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ሐረሪዎች ማንነታቸውን ሊያስተዋውቁባቸው የሚችሉ የበርካታ ቅርስ ባለቤት ናቸው። ካሏቸው ቅርሶች መካከል የከተማዋ ልዩ ምልክት የሆነው የጀጎል ግንብ አንዱና ቀዳሚው ነው። ይህ በቅርስነቱ ለዘመናት የሚታወቀው የጀጎል ግንብ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ዝርዝር ውስጥ ተካቷል።
በጀጉል ግንብ ውስጥ በርካታ መስጂዶች ይገኛሉ። የመድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያንም በጀጎል ግምብ መገኘቱ የዩኔስኮ ቀልብ በመሳብ ከተማዋ የመቻቻልና የሰላም ተምሳሌት ተብላ በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንድታገኝ አድርጓታል። የጀጉል መንገዶች ከጁምአ ዕለት ድምቀት በተጨማሪ በዕለተ 27 የኦሮቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ ምዕመናን ለከተማዋ ልዩ ድምቀት ይሰጧታል።
አንድ ምዕተ ዓመት የተሻገረው ይህ ቤተ ክርስቲያን ንጉሰ ነገስቱ አጼ ምኒልክ ኢትዮጵያን በሚመሩበት ወቅት ራስ መኮንን የሐረርጌ ገዢ በነበሩበት ዘመን የታነጸ ሲሆን፣ ያሰሩትም ራስ መኮንን እንደሆኑ ይነገራል። በጀጎል ግንብ ቅጥር ግቢ ውስጥ ወዲህ ሂጃብ የለበሱ፤ ወዲያ ደግሞ ነጠላ አጣፍተው ጧፍ የያዙ መንገደኞች በጋራ ይንቀሳቀሱበታል።
የጀጎል ግንብ የሐረሪ ህዝብ የኪነ ህንፃ ችሎታውን የሚያስመሰክር የታሪክና የጥበብ መዘክር ነው። የተገነባው በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከአህመድ ግራኝ ጦርነት በኋላ በአሚር ኑር አማካኝነት ነው። ግንቡ የተገነባበት ዋና ምክንያት የሐረርን ከተማ ከወራሪዎች ለመከላከል ሲባል ነው። በጥንት ጊዜም የአካባቢው ነዋሪዎች ለንግድ ወደ ጀጎል ሲገቡ በሙሉ የያዙትን የጦር መሳሪያ በየበሩ ላሉት ጥበቃ ሰራተኞች ሰጥተው ይገቡ እንደነበር፣ ጀምበር ስትጠልቅ ሁሉም እንዲወጡ ተደርጎ ሁሉም በሮች ተቆልፈው ቁልፎቹ ለአሚሩ ይሰጡ እንደነበርም የታሪክ ማህደራት ይናገራሉ።
ግንቡ አጠቃላይ ርዝመቱ 3 ሺ 342 ሜትር ሲሆን፣ ከፍታው ደግሞ አራት ነጥብ አምስት ሜትር ነው። የግንቡ ውፍረት ደግሞ ከ40 እስከ 50 ኢንች የሚደርስ ሲሆን፣ ያረፈበት የቦታ ስፋት እንዲሁ 48 ሄክታር መሬት ላይ ነው። በግንቡ ውስጥ የሚገኙ መስጂዶች ብዛት 82 እንደሆኑ ይነገራል። በግንቡ ውስጥ ከ2ሺ በላይ ጥንታዊና ባህላዊ ቤቶች ይገኛሉ። ግንቡ አምስት በሮች አሉት። ሁሉም የየራሳቸው መጠሪያ ስም አላቸው፣ ሸዋ፣ ቡዳ፣ ሰንጋ፣ ኤረር እና ፈላና በር በመባል ይታወቃሉ። እነዚህ ስሞች በአካባቢውም ደግሞ ተጨማሪ የሆነ የየራሳቸው መጠሪያ አላቸው፣ አስዲን፣ በድሮ፣ ሱቁጣጥ፣ አርጎ እና አሱሚ በር ይባላሉ። ጽሑፉን ያጠናከርነው ከሕብረ ኢትዮጵያ መፅሐፍ እና ከሌሎችም መረጃዎች ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2012
አስቴር ኤልያስ