የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ባለሥልጣን ትንበያ እንደሚያመለክተው፤ በ2013 በጀት ዓመት በኢትዮጵያ የከተማ ህዝብ ዓመታዊ ዕድገት ምጣኔ 3 ነጥብ 7 ከመቶ ሲሆን፣ የከተሜነት ደረጃው ደግሞ በ2013 ዓ.ም 22 ነጥብ 0 በመቶ እንደሚሆን ይጠበቃል። ይህ ቁጥር ከ10 ዓመት በኋላ ማለትም በ2022 ዓ.ም 28 በመቶ ወይም 35 ሚሊዮን ህዝብ እንደሚደርስ ያሳያል። ይህ ማለት በቀጣይ 10 ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጨማሪ 12 ሚሊዮን በዓመት በአማካይ የ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የከተማ ህዝብ ጭማሪ እንዲሚኖር ይገመታል።
የከተማ ልማትና ቤት ሚኒስቴር በጥር 2008 ዓ.ም ባስጠናው አገራዊ የከተማ ልማት ልዩ ጥናት ትንበያ ሪፖርት መሠረት የአገሪቱ የከተማ ዕድገት ምጣኔ ከ5 በመቶ በላይ እንደሆነ ነው። የከተሜነት ደረጃውም በ2012 እስከ 25 በመቶ የሚደርስና በ2022 ዓመት እስከ 35 ከመቶ ድርሻ እንደሚኖረውም ያሳያል።
ኢትዮጵያ እንደ አገር በቀጣይ በከተሜነት ደረጃ ልትደርስበት ስላሰበችው ከፍታና ስለምታከናውነው እንቅስቃሴ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ እና…..አስተባባሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ወልደሚካኤልን ባነጋገርናቸው ወቅት እንዳስረዱት፤ ሚኒስቴሩ ባዘጋጀው የ10 ዓመት መሪ እቅድ ውስጥ ፈጣን ከተሜነት የመቀጠል ተስፋና ስጋት በኢትዮጵያ የሚል ጽንሰ ሐሳብ ተካቶበታል።
ይህ መሪ እቅድ እንደሚያመለክተውም፤ ከተሞች ለአገራዊ ዕደገት ትልቅ ሚና አንዳላቸው ነው። እ.ኤ.አ በ2015 የተካሄደው የኢትዮጵያ ከተሞች ጥናት ከተሞች በወቅቱ 18 በመቶ ያልበለጠ ህዝብ ይዘው የኢኮኖሚ ድርሻቸው ግን ከ38 በመቶ እንደሆነ ያሳያል። ይህ ሚናቸው እያደገ እንደሚቀጥል አገራት መካካለኛ ገቢ ሲደርሱ የከተሞች ድርሻ ከ60 በመቶ በላይ እንደሚደርስ በጥናት የተደገፈ ነው። ከዚህ የተነሳም የከተሜነት ጉዳይ በቀጣይ በፈጣን ሁኔታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል፤ የከተሞች በአገር ኢኮኖሚ የሚኖራቸው ድርሻ እያደገ ይሄዳል። ይህንን እውነታ በአግባቡ በመገንዘብ በቂ ዝግጅት ማድረግ የቀጣይ ዕቅዳው ዝግጅት መነሻ ይሆናል።
በተመሳሳይ ሁኔታ እ.ኤ.አ የ2015 አለም ባንክ የከተሜነት ሁኔታ ግምገማ ጥናት እንደሚያመለከተው፤ በ2012 ከነበረው 22 ነጥብ 2 በመቶ የከተማ ህዝብ ምጣኔ በዕቅድ ዘመኑ መጀመሪያ ማለትም በ2013 የከተማ ህዝብ 24 ነጥብ 04 በመቶ እንደሚደርስ ያሳያል። ከዚህ ጥናት መረዳት የሚቻለው በየዓመቱ የ1 ነጥብ 25 ሚሊዮን የከተማ ህዝብ ዕድገት ጭማሬ እንደሚኖር ነው። ከዚሁ ዕድገት ውስጥ 36 በመቶ የሚሆነው ከገጠር ወደ ከተማ በሚደረግ ፍልሰት የሚመጣ ሲሆን፣ 36 በመቶ በተፈጥሮአዊ ዕድገት፣ 9 በመቶ የገጠር ማዕከላት ወደ ከተማነት ደረጃ ሲያድጉ ከሚፈጠር ለውጥ፣ 3 በመቶ በከተማ መስፋፋት እንዲሁም 16 በመቶ አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶችን ተከትሎ የሚኖር የህዝብ ዕድገት እንደሆነ ማሳየቱን አቶ ተስፋዬ ይጠቅሳሉ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የከተማ ህዝብ ቁጥር ዕድገትና ምክንያቱ በዕቅዱ ተከታታይ ዘመናት እየጠነከረ እንደሚቀጥል መሪ እቅዱ እንደሚያመላክት የሚናገሩት አቶ ተስፋዬ፣ በ2022 በጀት ዓመትም አጠቃላይ የከተማ ህዝብ ብዛት ወደ 34 በመቶ ከአጠቃላይ ህዝብ ድርሻ እንደሚኖረው፤ ይህ የህዝብ ቁጥር ከሚቀድመው ዓመት የሚኖረው የህዝብ ቁጥር ለውጥም በ1 ነጥብ 76 ሚሊዮን ከፍ እንደሚልም ያመላከተ መሆኑን ይገልጻሉ። በዓመቱ ከተፈጠረው የህዝብ ቁጥር ጭማሪ ውስጥ 46 በመቶ የሚሆነው ከከተማ ወደ ገጠር በሚደረግ ፍልሰት የሚመጣ ተጨማሪ ጫና ሲሆን፣ 34 በመቶ በተፈጥሮአዊ ዕድገት፣ 6 በመቶ የገጠር ማዕከላት ወደ ከተማነት ሲጠቃለሉ የሚመጣ ለውጥ፣ 3 በመቶ በከተማ መስፋፋት የሚፈጠር እንዲሁም 11 በመቶ አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶችን ተከትሎ የሚኖር የህዝብ ዕድገት ጭማሬ እንደሆነም የሚያሳይ መሆኑን ያመለክታሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ የከተማ ህዝብ ቁጥር እንደሚያድግ ከሚያደርገውና ከፍተኛውንም ድርሻ የሚያዘው በአማካይ 45 በመቶ ከገጠር ወደ ከተማ በሚደረግ ፍልሰት ነው። ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ተፈጥሮአዊ መሰረታዊ ምክንያቶች አሉት፤ነገር ግን ጥናቶች እንደሚያመለከቱት፤ አገሪቱ በ2050 ዓ.ም 85 በመቶ የህዝብ ዕድገትና ከፍተኛ የውስጥ ፍልሰት እንደሚኖር ነው። ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ ከመሬት አጠቃቀምና ከአካባቢያዊ ሁኔታ ጋር በተገናኘ ከምርትና ምርታማነት መቀነስ ጋር የተያያዘ ችግር ስለሚሆን በአካባቢ ጥበቃና መካከለኛና አነስተኛ ከተሞች እርስ በርሳቸውና ከአካባቢያቸው በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ልማት ተሳስረውና መስተጋብር በመፍጠር ባላቸው የመልማት አቅም ልክ ማሳደግ ላይ ትኩረት በማድረግ መስራት ያስፈልጋል።
‹‹የትኛውንም ትንበያ ብንወስድ አሁን ያለው የአገራችን የከተሜነት ደረጃ ከአፍሪካ አማካይ 40 በመቶ፣ ከአለም 57 በመቶ ያነሰ ነው፤ በዕድገት ምጣኔ ደረጃ ግን ከአፍሪካ አማካይ 3 ነጥብ 1 በመቶ፣ ከዓለም 2 ነጥብ 7 በመቶ ደረጃ ላይ ይገኛል ይህም በጣም ከፍተኛ የሚባል ነው። አሁን ካለው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ከባቢያዊ ዕድገት ክፍተት በተጨማሪ ለሚኖረው የህዝብ ቁጥር መጨመር ጫና መልስ መስጠት የሚችል የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የመኖሪያ ቤትና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የመሠረተ ልማትና አገልግሎቶች በዓይነትም በመጠንም ማሳደግ እንደሚገባን የሚያሳይ ነው›› ብለዋል።
መካከለኛና አነስተኛ ከተሞች ከከፍተኛ ከተሞችና ከልማት ቀጣና ጋር ማስተሳሰር የሚያስፈልግ መሆኑን የሚጠቅሱት አቶ ተስፋዬ፣ ‹‹አሁን በአገራችን ባለው የአከታተም ሥርዓት የአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ከተማ በመሆን የኢንዱስትሪ ልማት ሞተር ሆና መቀጠሏ ስለማይቀር በዙሪያዋ ከሚገኘው የኦሮሚያ ልዩ ዞን ጋር መስተጋብር የፈጠረ የተቀናጀ ልማት መፍጠር እጅግ አስፈላጊ ይሆናል ›› ይላሉ። በአገራዊ የአከታተም ሥርዓት ከአዲስ አበባ ቀጥሎ የወደፊት ኢትዮጵያ የእድገት ሞተር የሚሆኑት ዋና ዋና ከተሞች በዙሪያቸው ከሚገኙ ከተሞችና የገጠር ማዕከላት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ከባቢያዊ ትስስር መፍጠር እንዳላቸው፤ የመልማት አቅማቸው እንዲያድጉ ማድረግ የሚጠበቅ እንደሆነ ያስረዳሉ።
እንደ እርሳቸው አባባል፤ እነዚህ ከተሞች የኢንዱስትሪ፣ የአገልግሎትና የገበያ ማዕከል በመሆን የግብርና ልማቱን በማፋጠን የራሳቸውንና የአካባቢያቸውን ልማት በማሳደግ ረገድ ተልዕኮ የሚወስዱ ናቸው። በመሆኑም ከተሞቹ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት ይችሉ ዘንድ ለልማት መሠረታዊና አስቻይ አገልግሎቶች በተለይ የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ሊሟሉላቸው ይገባል። የልማት ማዕከላት የሚሆኑ ስፍራዎችን በተመለከተ በአገር አቀፍ ደረጃ ፟የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፟ ኢንዱስትሪ ልማት ጨምሮ ለስኳር፣ ለማዳበሪያ፣ ለፖታሽ ማምረቻ፣ ለዩኒቨርስቲና ለመሳሰሉት ክላስተርነት የተለዩት ቦታዎች ይህን ተግባርና ኃላፊነት በየአካባቢያቸው እንደሚፈጽሙ ይጠበቃል። በቀጣይም ለማዕድን፣ ለቱሪስት መዳረሻ፣ ለተፈጥሮ ሀብት ልማት ወዘተ የሚከለለው ሥፍራ የአካባቢው የዕድገት ማዕከል እንደሚሆን ይታሰባል።
ስለዚህ ከከፍተኛ ከተሞችና ከልማት ቀጣና ጋር ተሳስረው የሚፈጠሩ ማዕከላት እንዲሁም በቀጣይ ትኩረት የተሠጣቸው ዘርፎችን ለማሳደግ በማዕከልነት ሚና ያላቸው ከተሞች አስፈላጊው ፕላን፣ መሰረተ ልማትና አገልግሎቶች ተሟልቶላቸው እንዲለሙ ማድረግ አንዱ መነሻ ተደርጎ እንደሚወሰድ አማካሪው ይናገራሉ። ይህ በመሠረታዊነት ከገጠር ወደ ከተማ ወይም ከከተማ ወደ ከተማ ለስራና መሠረታዊ አገልግሎት ፍለጋ የሚደረገውን ፍልሰት የሚቀንስበትና የተረጋጋ ሕይወት በመፍጠር በኩልም ድርሻው ከፍተኛ መሆኑን ይናገራሉ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2012
አስቴር ኤልያስ