የሰው ልጅ ታሪክ ሲጠና ካንድ መሠረታዊ ጉዳይ ላይ ያርፋል። የሚፈልገውን ለማግኘትና ራሱን ከችግሮች ለመከላከል ከተፈጥሮና ከራሱ ጋር ታግሎአል። በትግሉም ስኬቶችን አስመዝግቦአል፤ ላጋጠሙት ውድቀቶችም ዋጋ ከፍሎአል። ትምህርትና ዕውቀት የሚቀሰሙት ከትምህርት ተቋማት ብቻ አይደለም። ስኬቶችም ሆኑ ውድቀቶች ትምህርት ቤቶች ናቸው። መማር ለሚችል አዕምሮ ሁሉም ነገርና ቦታ መማሪያ ነው። ከደረሱትና ከሚደርሱት አደጋዎች፤ ካጋጠሙና ከሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች፤ ከሚኖርባቸው ተፈጥሮአዊና ሰዋዊ፤ ማሕበራዊና ታሪካዊ፤ አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ክስተቶች ልምድንና ዕውቀትን ማፍለቅ የሰው ልጅ ልዩ ስጦታ ነው።
ሰው በፍፁም የማይፈቅዳቸው ግን ደግሞ የማይቀር ዕጣ-ፋንታ የሚሆኑበት በርካታ ነገሮች አሉ። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እ. ኤ. አ ከታሕሳስ 2019 ዓ. ም. መጨረሻ አካባቢ ውሃን ከተባለችው የቻይና ከተማ ተነስቶ እስከ ሚያዝያ ወር 2020 መጨረሻ ድረስ በዓለም ላይ ተሰራጭቶ ከ250 ሺህ ሕዝብ በላይ ለሕልፈተ-ሕይወት ዳረገ። የቫይረሱ ሌላ ስም ኮቪድ – 19 (Covid -19) ነው። ለበሽታው የተሰጠው ይህ አጭር ስም ሲተነተን “የ2019 የኮሮና ቫይረስ በሽታ” ማለት ነው። ወረርሽኝ ካንዱ ወደ ሌላው የሚተላለፍ፤ ሠፊ አካባቢን በመሸፈን ብዙ ሰዎችን ለሕመምና ለሞት የሚዳርግ ነው። ካንድ ቦታ በመነሳት ሠፊ አካባቢን ከመሸፈን አልፎ አገርን፤ ክፍለ-አህጉርን፤ አህጉርንና አህጉራትን በማጠቃለል ዓለምን ሊያዳርስ ችሎአል።
ከሁሃን ከተማ የተነሳው ኮሮና ቫይረስ ከአራት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ዓለምን ተቆጣጠራት። በአጭር ጊዜ ውስጥ ከምሥረቁ የዓለም ጫፍ ወደ ምዕራቡ፤ ከሰሜኑ የዓለም ጫፍ ወደ ደቡቡ ጫፍ አዳርሶ ቀይ ወይም ጥቁር፤ ነጭ ወይም ቢጫ፤ ሀብታም ወይም ደሃ፤ ልጅ ወይም አዋቂ፤ ወንድ ወይም ሴት ሳይል በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ገደለ፤ ሚሊዮኖችን በሕመም አሰቃየ፤ ግዙፍ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አደረሰ። ይህ ቀውሳዊ ጉዞው አሁንም ቀጥሎአል። ለመሆኑ የሚቆም ነው ? የሚቆም ከሆነስ መቸ ነው ማብቂያው ? ሰውስ እስከዚያ ድረስ እንዴት ነው የሚቆየው? ለመሆኑ መድኃኒት ወይም ክትባት ባጭር ጊዜ ይገኝለት ይሆን ? ካልተገኘስ ?
በርካታ አገሮች ውድ ዜጎቻቸውን በወረርሽኙ ተነጥቀዋል። በተለይ በልፅገዋል፤ ሰልጥነዋል የሚባሉ እንደነ አሜሪካ፤ ጣሊያን፤ እስፔንና ሌሎች የአውሮፓ፤ የኤስያ፤ የሰሜንና የደቡብ አሜሪካ አገሮች ሳይቀር በወረርሽኙ ክፉኛ ተመትተዋል። በአፍሪካ የለየለት ባይሆንም እስካሁን ድረስ ያለው ጉዳት መጠነኛ ነው ማለት ይቻላል። እንደነ ቻይና፤ ደቡብ ኮሪያ፤ ቬትናም ያሉ አገሮች #አልፈነዋል$ በማለት ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው ለመመለስ አንዳንድ መንደርደሪያ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው። ይሁን እንጂ አሁንም እጅግ የሚያሳስቡ ነገሮች አሉ። አንደኛ #አልፈነዋል$ ማለት አይመለስብንም ማለት አይደለም። የመተላለፊያ መንገዱ በሚገባ መዘጋቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ሁለተኛ ቫይረሱ ዓለም እስካሁን ያወቀለትን ባሕርይ ሊቀይር ይችላል። ሦስተኛ ከየትኛውም አህጉር ወረርሽኙን ለመቋቋም ዝቅተኛ አቅም ያላት አፍሪካ ዕጣ-ፋንታ ገና ያልየለት ነው። በብዙ ምክንያቶች የአፍሪካ አገሮችና መሪዎች ዛሬ እጅግ መሯሯጥ አለባቸው – አህጉሩንና ሕዝቡዋን ከዚህ ክፉ ወረርሽኝ ለማስጣል።
የሰው ልጅና ወረርሽኝ
ዓለም በወረርሽኝ በሽታ ስትወረር ይህ የመጀመሪያ አይደለም። ብዙ ጊዜ የተለያዩ መንስኤ በነበራቸው ወረርሽኞች ተመትታለች። ከብዙ በጥቂቱ እንጥቀሳቸው። እ.ኤ.አ በ 165 ዓ. ም 5 ሚሊዮን፤ ከ 541-542 ዓ. ም 25 ሚሊዮን፤ ከ 1346-1353 ዓ. ም
ከ75 -200 ሚሊዮን፤ በ 1852 ዓ. ም 1 ሚሊዮን፤ ከ 1889-1890 ዓ. ም. ከ 1 ሚሊዮን ያላነሱ ሕዝቦችን የፈጁ የተለያዩ ወረርሽኞች በዓለም ላይ ተከስተዋል። በ20ኛው ምዕተ-ዓመት ውስጥ ደግሞ ከ 1910-1911 ዓ. ም ከ 800 ሺህ በላይ፤ በ 1918 ዓ. ም ከ20-50 ሚሊዮን፤ ከ 1956-1958 ዓ. ም. ከ2 ሚሊዮን፤ በ 1968 ዓ. ም ከ 1 ሚሊዮን፤ ከ 2005-2012 ዓ. ም. ከ 36 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የፈጁ የኮሌራ፤ የኢንፍሉዌንዛና የኤች አይ ቪ ኤይድስ ወረርሽኞች ዓለምን አሽመድምደዋል። አንዳንዶቹ ወረርሽኞች ለአጭር ጊዜ ብቻ የነበሩ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ረዘም ላለ ጊዜ የቆዩ ናቸው። አሁን ደግሞ የኮሮና ቫይረስ ዓለማችንን እያሽመደመዳት ነው። ይህ የጊዜያችን ወረርሽኝ ምን ያህል ጊዜ እንደሚኖርና ምን ያህል ጉዳት እንደሚያደርስ መተንበይ ያስቸግራል።
ለመሆኑ ኮሮና ቫይረስ ምንድነው? ከየት መጣ? መንስኤው ምንድነው – ተፈጥሮ ነው ወይስ ሰው? ቫይረሱ ምን ጉዳት ያደርሳል? መቸና እንዴት ይቆማል? ይህ ጽሑፍ ስለተነሱት ጉዳዮች ሳይንሳዊ ትንተና የማድረግ አቅም የለውም። ትኩረቱ ኮሮና ቫይረስ በዓለም ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት መነሻ በማድረግ ሰው በዓለም ላይ ስላለው ቦታ አጭርና አጠቃላይ ዳሰሳ ማድረግና ይኸው ሰው ስለ ዓለም ያለውን ግንዛቤ ማስፋትና ማዳበር እንዳለበት መጠቆም ነው። ዳሰሳው ምክንያታዊ መረጃንና ምልከታን መሠረት በማድረግ ስለተነሱት ጥያቄዎች ፍልስፍናዊ ቅኝት ያደርጋል።
የዓለም ውስብስብነትና የሰው ልጅ አረዳድ
የሰው ልጅ የዓለምን ውስብስብነትና የራሱን አቅም የሚረዳበት መንገድ መፈተሽ አለበት። እኛ ሰዎች በቀሰምነው ዕውቀትና በቀመርናቸው ንድፈ-ሐሳቦች፤ በፈጠርናቸው ቴክኖሎጂዎችና ባበለፀግናቸው ጥበቦች ተኩራርተናል። በእርግጥ በሠራናቸው መልካም ነገሮች፤ ባስመዘገብናቸው ስኬቶችና በተቀዳጀናቸው ድሎች በአግባቡ መኩራራት ክፋት የለውም። ዓለምን እንደፈለግናትና እንደተመኘናት ልናደርጋት እንችላለን የሚል እምነት በውስጣችን ማሳደራችን ግን ስሕተት ነው። የሰው ልጅ ብዙ መልካም ለውጦችን ሠርቶአል። በሚሰራቸው መልካም ለውጦች ውስጥ መልካም ያልሆኑ ነገሮች ላለመኖራቸው ግን ማረጋገጫ የለውም። ራሱን ለማሻሻል የሚፈጥራቸው ነገሮች መልሰው እንዳይጥሉት ማሰብ አለበት። ስለምንኖርባት ዓለም የምናውቃቸው ነገሮች አሉ። የማናውቃቸውም ነገሮች አሉ። ከምናውቃቸው በላይ የማናውቃቸው እጅግ ብዙ ናቸው። ለወደፊትም በዕውቀት የምንደርስባቸው የመኖራቸውን ያህል መቸውም ቢሆን የማንደርስባቸው ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ።
በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በምናደርገው እንቅስቀሴ ከተፈጥሮ ሕጎች ጋር የሚያላትሙንን ነገሮች ልንፈጥር እንችላለን። ፈጥረናልም። አሁን ዓለምን እያሽመደመደ ያለው የኮሮና ቫይረስ የተፈጥሮ ሕግ ወይም የሰው ልጅ ሥራ ውጤት ስለመሆኑ በውል የታወቀ ነገር የለም። ሟርት አይሁንብን እንጂ ለወደፊቱም አደገኝነቱ ከኮሮና ቫይረስ የባሰ ወረርሽኝ የሰውን ልጅ ሊጎበኝ ይችላል። ለዚች ዓለም እያደረግን ያለው አያያዝ በእጅጉ አሳሳቢ ነው። ሰው ዓለምን በወረራ አልያዛትም። ተፈጥሮ አምጣ የወለደችው እናቱ እንጂ በወረራ የያዛት የጠላት አገር አይደለችም። ልጅ ለእናቱ የሚሳሳላትን ያህል ለዓለምም ሊሳሳላት ይገባል። እርሱ ግን ለመኖርና ለማደግ ሲል አንዱን አንስቶ ሌላውን ይጥላል፤ አንዱን ጥሎ ሌላውን ያነሳል። ለሚጠቅመው የዓለም ክፍል የተወሰነ ጥበቃ ያደርጋል፤ ለተቀሩት ግን ተገቢውን ትኩረት አያደርግም። ስለመኖሩም ሆነ ስላለመኖሩ ብዙ የሚጨነቅ አይመስልም። እዚህ ጋ የተፈጠረው መናጋት እዚያ ጋ ያለውን ሥርዓት ያቃውሳል። በዚህ ምክንያት የዚች ዓለም ጠባይ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያሳስብ እየሆነ ነው።
ሁለት ነገሮች መዘንጋት የለባቸውም። ዛሬ የማይጠቅምን ነገር ነገ ሊጠቅመን የሚችል መሆኑን ማሰብ ጠቃሚ ነው። ሰውን ባይጠቅም የተፈጥሮ ሥነ-ምህዳርንና ሚዛንን በመጠበቅ ረገድ ጠቀሜታ አለው። አይጠቅምም የሚባል ነገር በተፈጥሮ ሥርዓት ውስጥ የለም። እያንዳንዱ ነገር በተፈጥሮ ሥርዓት ውስጥ የራሱ ዋጋና ትርጉም አለው። ዓለም የተቀናጀ ሥርዓት አላት። ገደብ የሌለው የሰው ልጅ ጣልቃ-ገብነት ይህን ሥርዓት በመረበሽ ችግር እያስከተለ ነው። “አደማኋት፤ አቆሰልኳት፤ ችግር ፈጠርኩባት” ሳይል በሚችለው ጉልበት ክንዱን ሲያሳርፍባት ቆይቶአል። በዚህ ድርጊቱ ግዙፍ በደል ፈጽሞባታል። እርሷም በበኩሏ አጸፋውን በዓይነት እየመለሰች ነው። ይህ አሁን መላ-ምት ሳይሆን በተጨባጭ እየሆነ ያለ ነገር ነው። ስለዚህ የሰው ልጅ የኮቪድ – 19 ወረርሽኝ ትክክለኛ መንስኤ በዓለማችን ላይ የሚያደርሰው ጉዳት አለመሆኑን ማረጋገጥ አለበት።
ብዙ ጊዜ ሰው ማሕበራዊ እንስሳ ነው እንላለን። ኮሮና ቫይረስ ይህን ሃቅ በይበልጥና በተጨባጭ እንድንረዳው ረድቶናል። እንደ ሰው ማንም ራሱን ችሎ መኖር አይችልም። በየቀኑ ለሌሎች ሰጥተን ለራሳችን የምንቀበለው ነገር አለን። እኔ ለራሴ ወይም ለጋራ ጉዳይ ስል ሌሎችን እፈልጋለሁ። ሌሎችም እንዲሁ ይፈልጉኛል። ማሕበራዊ ሕይወታችን ለኮሮና ቫይረስ በፍጥነት መሰራጨት ምቹ ሆኖአል። በቀን ውስጥ የምናደርገው ንክኪ እጅግ በጣም ብዙ ነው። ንክኪ ደግሞ ሰንሰለት ይሰራል። በዚህ ምክንያት ከአንድ ግለሰብ የተገኘ ቫይረስ የመተላለፊያ መንገዱ ካልተዘጋ ለሁሉም የዓለማችን ሕዝብ መድረስ ይችላል።
የሰው ልጅ ግንኙነት የሚንቀሳቀሰው በተግባቦት ነው። ተግባቦት የምንፈጥረው በአንደበታችን በማሰብ፤ በአፋችን በመናገር፤ በአፍንጫችን በማሽተት፤ በጆሮአችን በመስማትና በእጃችን በመንካት ነው። የኮሮና ቫይረስ ካንዱ ወደ ሌላው የሚተላለፈው ለተግባቦት በምናደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ ነው። ስለዚህ ተፈጥሮአችን የሆነው ማሕበራዊ ሕይወት ለኮሮና ቫይረስ ስርጭት ምቹ ነው። ወረርሽኑ መድኃኒትና ክትባት ያልተገኘለት በመሆኑ አደገኛ ነው። በእርግጥ አንድ መልካም ነገር – የመተላለፊያ መንገዱ ቶሎ መታወቁ ዓለምን ከሞላ ጎደል ታድጓታል። የሚያደርሰውን አደጋ ለመከላከል፤ ለመቀነስና ለማቆም የሚያስችል አንድ ብቸኛ ነገር ለጊዜው የሚተላለፍለትን መንገድ ማቋረጥ ነው። ይህ የመከላከያ መንገድ በእጃችን ላይ መሆኑ እንደ ዕድል መወሰድ አለበት።
በቅድመ-ኮሮና ቫይረስ ግለሰቦች፤ አገሮችና መንግሥታት የተለያየ ቁመና ነበራቸው። አንዳንዶቹ በተለያዩ ነገሮች ጠንካሮችና ታላላቆች፤ ሌሎቹ ደግሞ ደካሞችና ትናንሾች ነበሩ። ዛሬ በኮሮና ፊት ሁሉም እኩል ደካሞች ሆነዋል። ለሰዎች ሁሉ “ጌታ ነኝ” ይል የነበረው በሚገርም ሁኔታ ወርዶ ከሁሉም ሰው እኩል የኮሮና ቫይረስ ሰለባ ሆኖአል። ስለዚህ ዛሬ በኮቪድ – 19 ፊት ጠንካራ ወይም ጎበዝ የሚባል ግለሰብ፤ አገር ወይም መንግሥት የለም። ለምዕተ-ዓመታት የተገነባው ኢኮኖሚና መሣሪያ፤ ጉልበትና ዕውቀት፤ ባሕልና እሴት ባንድ የቫይረስ ዓይነት ተሸመደመደ። በኮሮና የማይሞከርና የማይደፈር አገርና መንግሥት፤ ግለሰብና ሕዝብ ባለመኖሩ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ እኩል ደካሞች ሆነዋል። ግን ደግሞ ባንድ ላይ መቆም ከቻሉ ጠንካሮች ይሆናሉ። መደማመጥና መናበብ፤ መረዳዳትና መተጋገዝ ካለ የቫይረሱን ጉልበት መስበር የሚችል ዓለም አቀፋዊ አቅም መፍጠር ይቻላል። የሰውን ልጅ ለቫይረሱ ጥቃት ያመቻቹትን ነገሮች፤ ድርጊቶች፤ አሠራሮችና አኗኗሮች፤ አስተሳሰቦችና እምነቶች ለጊዜውም ቢሆን ከተወ በቫይረሱ ላይ ድል መቀዳጀት ይችላል።
ከደረሰው ጉዳት የሚገኝ ትምህርት
- በተፈጥሮ ሕግ ፊት ሰው አሁንም ደካማ መሆኑን መረዳት አለበት። በሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤት በእጅጉ ተማምነን ቆይተናል። የአቶሚክና የኑክለር ቦምብ ባለቤቶች ነን ብለን ተኩራርተናል።
ጠፈርን እያሰስን ነው ብለን ፎክረናል። ነገር ግን እውቀትና ጥበብ፤ መለኮታዊም ሆነ መንፈሳዊ ኃይል የሌለው አንድ በዓይን የማይታይ ረቂቅ ነገር የብዙ ድል ባለቤት የሆነውን ሰው ዋጋ አሳጣ። አቶሚክና ኑክሌር ቦምብ የሰውን ሕይወትና ኑሮ ያጠፋሉ። ኮሮና ቫይረስን ግን አይሞክሩም። ለጊዜው ኮሮና ቫይረስን የሚዳኙት ከሳይንስ ጋር በመሆን ግብረገብና ዲስፕሊን፤ እምነትና መንፈሳዊ እሴት ናቸው። ለሌላ ማሰብ ለራስ ማሰብ፤ ለራስ ማሰብ ለሌላ ማሰብ መሆኑ በተጨባጭ የተገለፀበት ጊዜ ቢኖር አሁን ነው።
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ፊት ያንድ አላዋቂ ወይም ቸልተኛ ሰው ድርጊት ለዓለማችን ጦስ መሆን ይችላል። እያንዳንዱ ሰው አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ድርሻ ወሳኝ ነው። ግለሰብ ራሱን ከቫይረሱ ሲከላከል ራሱን ብቻ ሳይሆን አገርንና ዓለምን ይታደጋል። ሳይንስና ቴክኖሎጂ ብቻቸውን ይህችን ዓለም ከኮሮና ቫይረስ ማዳን አይችሉም። እያንዳንዱ ሰው በዓለም ላይ ላለው ሰው ሁሉ የግብረገብ ኃላፊነት ወይም ግዴታ አለበት። በእኔ ምክንያት ማንም ሰው መጎዳት የለበትም የሚል ቁርጠኛ እምነትና ውሳኔ በውሰጡ ሊኖረው ይገባል። “በቫይረሱ ብያዝ ባልያዝ የራሴ ጉዳይ ነው” የሚባልበት ጊዜ አይደለም። ያንድ ሰው ሚናና ውሳኔ ለዓለም ወሳኝ የሆነበት ጊዜ ስለሆነ።
- ኮሮና የሰውን አቅም ለክቶአል። የሰው ጥንካሬ ትንሽ፤ ድክመቱ ግን ግዙፍ መሆኑን አሳይቶአል። በማናውቃቸውና ባልተመራመርንባቸው ነገሮች ፊት ደካሞች ነን። በሳይንስና ቴክኖሎጂ ጉልበት የደረስንባቸው የዓለማችን ምስጥሮች ትንሽ ናቸው፤ ያልደረስንባቸው ግን በጣም ብዙ ናቸው። ይሁን እንጂ በሳይንስ ዕውቀትና በቴክኖሎጂ ክህሎት ብዙ ጥቅሞችን መፍጠርና ችግሮችን መመከት እንችላለን የሚል እምነት በውስጣችን ፈጥረናል። በሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ የጣልነው ግዙፍ ተስፋ ለግብረገብና ለሥነ-ምግባር፤ ለሃይማኖትና መሰል መንፈሳዊ ሕይወት የሚገባቸውን ዋጋ እንድንነፍግ አድርጎናል። እንዲሁም ፋይዳ ያላቸው የሌሎች ነገሮችን ዋጋ አሳንሶአል። ይሁን እንጂ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፤ ጥበብና ዕውቀት ያልደረሱባቸው ቦታዎቻና ያልመለሱአቸው ጥያቄዎች ብዙ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ደረጃ በደረጃ የሚመለሱ ይኖራሉ፤ ከነጭራሹ የማይመለሱም ይኖራሉ። ስለዚህ ኮሮና ቫይረስ እኛ ዋጋ ያሳጣናቸውን ነገሮች (እንደ ሃይማኖት፤ ግብረገብ፤ ሥነ-ምግባር ወዘተ) እንደገና እንድናስባቸው አድርጎናል።
- ያንድ ሰው ሕይወት መኖር ወይም አለመኖር በሌላ ሰው ሕይወትና ደህንነት ጋር የተያያዘ ነው። መሬት ላይ ያለው እውነት ይኸ ሆኖ እያለ ድንበሩን የማያውቅ ወይም ከልክ ያለፈ ራስ-ወዳድነት ዓለምን አፍኖአታል። ይህ ራስ-ወዳድነት ከግለሰብ አንስቶ ዓለም እስከ መምራት የደረሱ መንግሥታትን ሁሉ መቆጣጠር ችሎአል። በዓለም ላይ እዚህም፤ እዚም ያሉ ጦርነቶች፤ አመፆች፤ ሁከቶች፤ ስደቶች፤ ክፋቶችና ጥፋቶች ዋና ምክንያት አንዱ ራስ-ወዳድነት ነው። ከልክ ያለፈ ራስ-ወዳድነት ድንበሩን አያውቅም፤ ቀይ መስመርን አይረዳም፤ የራሱን ጥቅም እንጂ የሌላውን ሞት አያይም። የሚከለክለው ነገር ቢኖር ውጫዊ ኃይል እንጂ ውስጣዊ ሕሊና አይደለም።
ሕሊና አቅም ባጣበት ሁኔታ ውስጥ የግል ነፃነትና ራስ ወዳድነት የግብረገብ መርህዎችንና ገደቦችን እንደልብ ይጥሳሉ። ሰው ጠንካራ ህሊና ካለው ገደቡን ያውቃል፤ ድንበሩን አይሻገርም:: ህሊናው ደካማ ከሆነ ግን በስሜት ቁጥጥር ሥር ይወድቃል። የዓለም ሕዝብ ሕሊና በተለያዩ ምክንያቶች በእጅጉ ላልቶአል። ይህ ደግሞ ዓለማችንና ሕዝብዋን ለበርካታ መከራዎች እንዳጋለጣቸው ሁሉ ለኮሮና ቫይረስ ጥቃትም አመቻችቶአቸዋል። ይህ በእጅጉ ያሳስባል። ዛሬ ስላለው ብቻ ሳይሆን ነገ ስለሚፈጠረውም አጥብቀን ማሰብ አለብን። ሰው የወጣችው ጀንበር ሳትጠልቅ የተቀናጀ መላ መምታት አለበት።
ይቀጥላል
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30/2012 ጠና ደዎ(ፒ.ኤች.ዲ)