የወፎችና የሰው ልጆች ቁርኝት እስከምን ድረስ ነው? ለመሆኑ ከመደበኛ ቋንቋ ያልተቆጠረው ‹‹ወፍ የለም›› የሚለው ንግግር አንድምታስ ምን ይሆን? አስበውት ያውቃሉ? ባለሙያዎቹ የሚያነሱት አስገራሚው ጉዳይ ወፍ በሌለበት የሰው ልጅም አለመኖሩ ነው።ለወፎች መኖሪያነት ምቹ የሆነ አካባቢ ለሰው ልጆችም ምቹ እንደሆነ ያስረዳሉ።በሽታን በመከላከል ወይም ደግሞ በሽታ ሊያመጡ የሚችሉትን ሁኔታዎች በማጽዳትና ነፍሳቶችን በመመገብ ጭምር ለሰዎች ጤና ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ።እነዚህን የተፈጥሮ ሂደቶች በጥናት በማስደገፍና ከሰው ልጆች የጥፋት ጫና እንዲላቀቁ በማድረግ ማጎልበት ላይ ቢሰራ መከላከል ላይ ለተመሰረተው የጤና ፖሊሲያችን መስፈንጠሪያ ‹‹ስፕሪንግ ቦርድ›› አይሆኑም ትላላችሁ?
በዓለም ከ10 ሺህ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ከ870 በላይ የወፍ ዝርያዎች መኖራቸውን ባለሙያዎች ይናገራሉ።ወፎች ለሰው ልጆች ተከፍሎ የማያልቅ ባለውለታዎች ስለመሆናቸው በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች በሰፊው የምናነሳ ይሆናል። በዛሬው ማህደረ ጤና አምዳችን ለሰው ልጆች ጤና በከፍተኛ ደረጃ እክል በመፍጠር በመሪነት ለሚገዳደረው የእብድ ውሻ በሽታም ሆነ ለሌሎች በሽታዎች ቅድመ መከላከል ተግባር ፍቱን መድሃኒት ስለሆኑት የወፍ ዝርያዎች በምርምር ሥራዎች ላይ ተመርኩዘን እናነሳለን።
አቶ አልዓዛር ዳካሩፍ ይባላሉ።በወፎች ምርምርና ክብካቤ ላይ ለ13 ዓመታት ሰርተዋል።በጆፌ(ጥንብ አንሳ )አሞራዎች ላይ ምርምር ማድረግ ከጀመሩ ደግሞ ሰባት ዓመታት ተቆጥረዋል፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል ስርጭት አላቸው? የአኗኗር ባህሪያቸው ምን ይመስላል? ለሰው ልጆች ያላቸው ፋይዳና የተጋረጡባቸው ፈተናዎች ምንድን ናቸው በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርገናል፡፡
አቶ አልዓዛር እንደሚሉት፣ ጆፌ (ጥንብ አንሳ) አሞራዎች ለሰው ልጆች ጤና በእጅጉ አስፈላጊ ናቸው።በየአካባቢው
የሚሞቱ እንስሳትን በአንድ አፍታ ፈጥነው በማስወገድ የሚወዳደራቸው የለም።ጥንብ አንሳ አሞራዎች ባህሪያቸው ከሌሎች የአሞራ ዝርያዎች ይለያሉ።የአካል አገነባብ ሂደታቸውን ከአንገታቸው ጀምሮ እስከ ጭንቅላታቸው ድረስ ያላቸው በጣም ደቂቅ የሆነ ላባ ነው።ይህ መሆኑ በሞተው እንስሳት ሆድ ዕቃ ውስጥ ገብተው በልተው ሲወጡ ደምና ሌሎች ባክቴሪያዎች ይዘው እንዳይመለሱ ይረዷቸዋል።ሌላ ቆሻሻን ይዘው አይመለሱም፤ከበሽታ ጽዱ ናቸው።ጥንብ አንሳ(ጆፌ) አሞራዎች ዝርያቸው በጣም የተለያዩ ናቸው።በዚህ የተነሳም አንዳንዶቹ ለስላሳ ስጋ ይበላሉ፤ ሌሎቹ ቆዳና ጅማት ይመገባሉ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ አጥንት የሚበሉ አሉ፡፡
በዓለም ላይ ከሚገኙት 23 የጥንብ አንሳ (ጆፌ) አሞራ ዝርያዎች ስድስቱ በሰሜን አሜሪካና በደቡብ አሜሪካ ይገኛሉ።በአውሮፓ፣ በአፍሪካና በኤዥያ ደግሞ አስራ ስድስት የጆፌ(ጥንብ አንሳ) አሞራ ዝርያዎች ይገኛሉ።በአፍሪካ አስራ አንድ ዝርያዎች ይገኛሉ።ከእነዚህ ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ
የሚገኙት ስምንት ዝርያዎች ናቸው።እነዚህ ዝርያዎች የራሳቸው ሳይንሳዊ መጠሪያዎች ያሏቸው ሲሆን ለስላሳ ስጋ፣ ቆዳና ጅማት እንዲሁም አጥንት የሚመገቡ ናቸው።በአንጀታቸው ውስጥ ‹‹ፒኤች›› መጠኑ አንድ የሆነ አደገኛ አሲድ በመኖሩ አጥንት እምሽክ አድርገው ማድቀቅ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
ጥንብ አንሳ አሞራዎች በሽታን የሚያስተላልፉ አይደሉም።ይልቁንም እንደ ‹‹ራቢስ›› የተሰኘውን የውሻ በሽታን በእጅጉ የሚከላከሉ ናቸው።እስከ 37 ዓመታት ዕድሜ ሲኖራቸው በእርጅና፣ በአደጋ እና በመርዝ ሊሞቱ የሚችሉ ሲሆን በደስታ በሽታም ሆነ በሌሎች በርካታ ዓይነት የእንስሳት በሽታዎች አይሞቱም።በየትኛውም በሽታ ታሞ የሞተ እንስሳት ሥጋ ቢመገቡም በእነሱ ውስጥ በሽታው በፍጹም ሊቆይ አይችልም።ከፍተኛ የሆነ አሲድ በሆዳቸው (በአንጀታቸው) ውስጥ በመኖሩ ባክቴሪያውም ሆነ ደቂቅ ሕዋሱ ያንን ተቋቁሞ ሊኖር አለያም ወደ ሌሎች እንስሳት ሊተላለፍ አይችልም።
በሕንድ አገር ከ2019 እስከ 2020ዎቹ መጀመሪያ ድረስ የተካሄዱ ጥናቶችን አጣቅሰው እንደሚሉት፣ ሕንድ በርካታ የጆፌ(ጥንብ አንሳ) ዝርያዎች አላቸው።ከእነሱ ውስጥ ‹‹ጅፕስ›› የተሰኙት ሦስት ዝርያዎች ቁጥራቸው በጣም ቀነሰ።ቁጥራቸው ለምን ቀነሰ በሚል የሞቱበት ምክንያት ሲጠና ኩላሊታቸውን ከጥቅም ውጪ የሚያደርግ ኬሚካል ተገኘ።ኬሚካሉም ‹‹ዳይክሎፌናክ›› ይባላል።ይህ ኬሚካል በሕንድ አገር ከብቶችን ለማከም የሚጠቀሙበት ነው።የሚሞቱትን ከብቶች ሲበሉ አሞራዎችም መሞት ጀመሩ።የአሞራዎቹ ቁጥር እየሞቱ ሲቀንስ የሚሞቱ ከብቶችን የሚበላ ባለመኖሩ ለውሾች ሁኔታው ምቹ አጋጣሚን ፈጠረላቸው።ውሾች በሰፊው መመገብ ጀመሩ።በዚህ የተነሳ ቁጥራቸው በእጅጉ እየጨመረ መጣ።
በእነዚህ አስር ያልበለጡ ዓመታት አምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ውሾች በመንገድ ላይ ተገኙ።እነዚህ ውሾች 38 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሰዎችን ነከሱ።በእብድ ውሻ በሽታ ተለከፉ።47 ሺህ 300 ሰዎች ደግሞ ለሞት ተዳረጉ።እነዚህን ውሾች ለማስወገድ እና ሰዎችን ለማከም 34 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ አድርጓል የሕንድ መንግሥት፡፡
በዚህ ምክንያት ከብቶች ሲታከሙበት የነበረው መድሃኒቱ እንዲታገድ ሆነ፤ ሌላ መድሃኒት ለከብቶች ማከሚያ እንዲውል ተደረገ።በተመሳሳይም በሌላ ጥናት መረጋገጥ እንደቻለው አንድ ጆፌ(ጥንብ አንሳ) አሞራ ልክ እንደ አንድ ሰው በጽዳት አገልግሎት በማዘጋጃ ቤት ተቀጥራ ብትሰራ ኖሮ በዓመት 11 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ዋጋ የሚያወጣ ጽዳት እንደምታጸዳ መረጋገጡን ተናግረዋል።በማህበር የሚበሉ ናቸው፤ ሃምሳ ቢሆኑ አስቡት? ስለዚህ ጠቀሜታቸው እስከዚህ ድረስ ከፍተኛ ነው። በኢትዮጵያ በየከተሞች የሚርመሰመሱት የውሻ መንጋዎች አደገኛ መዘዝ እንደሚያስከትሉ ያስረዳሉ፡፡
ይሄ ነባራዊ ሐቅ በኢትዮጵያ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በመላው አገሪቱ ለማረጋገጥ እ.ኤ.አ ከ2013 ጀምረው ከቤኒሻንጉል ክልል በስተቀር በሌሎች ክልሎች ዋና ዋና ከተሞች በሚገኙ ቄራዎች በአካል ተገኝተው ማረጋገጥ የቻሉትን ሀቅ አቶ አልዓዛር ሲገልጹ፣ የጆፌ(ጥንብ አንሳ) አሞራዎች በኢትዮጵያ ውስጥ አሁንም ቁጥራቸው ጥሩ ነው።ነገር ግን በአጠቃላይ ጥንብ አንሳዎች በሳይንስ ለአደጋ የተጋለጡ፣ ሊጠፉ የተቃረቡ የሚል ስም አላቸው።በኢትዮጵያ ማህበረሰቡ እነዚህ አሞራዎች ምንም ዓይነት በሽታ እንደማያመጡና የውሾች ቁጥር እንዳይጨምር በማድረግ በውሻ በሽታ ሊሞትና ሊታመም የሚችልን የማህበረሰብ ክፍል የሚታደጉ ናቸው።ቆሻሻን ያለአንዳች መዝረክረክ ጽድት አድርገው የሚያስወገዱ ናቸው።ለሥነምህዳር ጤናማነትም የራሳቸው በጎ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል።በአጠቃላይ ተላላፊ በሽታዎችን የሚከላከሉ ሲሆኑ ከመከላከል የጤና ፖሊሲው ጋር የሚጣጣሙና ወጪ የማያስወጡ በመሆናቸው በሰፊው በጥናት ተደግፎ ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30/2012
ሙሐመድ ሁሴን