ያነሰ እንዲሁም የበዛ ፍርሃት እና ጭንቀት ጤናማ ያለመሆናቸውን ያህል የተመጣጠነ ፍርሃት እና ጭንቀት ለጤናማ ኑሮ አስፈላጊ እንደሆኑ ይታመናል። ለምሳሌ በድቅድቅ ጭለማ ብቻችንን ወደ ቤታችን በሚወስደን ጠባብ መንገድ እየተጓዝን ነው እንበል…ከዛም ሁለት መላምቶችን እናስቀምጥ። አንደኛው ምንም ፍርሃት የማይኖርን ቢሆን እና ከኋላችን አንድ ሌባ ቢከተለን፥ ማድረግ ያለብንን ጥንቃቄ ሳናደርግ በቀላሉ ሊያጠቃን ይችላል። ሁለተኛው መላምት ደግሞ የበዛ ፍርሃት ውስጥ ብንገባ እና ምን ማድረግ እንዳለብን ግራ ስለምንጋባና ሰውነታችንም ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ስለሚገባ እንደልባችን መሮጥም፣ መከላከልም ሊያቅተን ስለሚችል ወይም በተጋነነ መልኩ አጸፋ ልንስጥ ስለምንችል ሌባው ከፍ ያለ ጉዳት ሊያደርስብን ወይም ልናደርስበት እንችላለን።
ከላይ ካሉት በተጨማሪ ብዙ ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉ። እስቲ ለደቂቃ ስለ በዛ ፍርሃት/ጭንቀት እና ያነሰ ፍርሃት/ጭንቀት እናስብ፤ ምን ጉዳት አላቸው? መጠነኛ ፍርሃትስ ምን ገንቢ ጥቅም አለው?
ጭንቀት እና ፍርሃት መደበኛ እና ጤናማ ከሆኑ ስሜቶች ጋር ይመደባሉ። ነገር ግን ጭንቀት ስንል በውስጡ አሉታዊ ስሜት የተቀላቀለበት፤ ስለ-መጪው ወይም ወደ ፊት ስለሚሆነው መስጋት ነው /Future oriented/። ፍርሃት ደግሞ በተመሳሳይ አሉታዊ ስሜት ያለበት ሆኖ ከጭንቀት የሚለየው ስጋቱ ስለ-አሁን ወይም አሁን ስላለንበት ሁኔታ በመሆኑ ነው /Present orient¬ed/። የሁለቱ ትስስርም እንዲህ ሊታይ ይችላል፦ ስለ ነገው የሚሰጋ ሰው ዛሬውን ያሳምራል። በሌላ ገፅ ዛሬውን የሚሰጋ ዛሬ ላይ ቆሞ ዛሬን ያሳምራል፤ ከነገም ጭንቀት ራሱንም ሌሎችንም ያተርፋል።
ሃሳቡን ስንሰበስበው በመጠነኛ ጭንቀት ተጠቅመን በቀዳሚነት ነጋችን እንዳያምር ከሚያደርጉ ተግባራት እንቆጠባለን፤ ወደፊት እንዳይፈጠር ከሚያሰጋን ነገር ዛሬ ላይ እንከለከላለን። ስለ ነገ የሚያሰጋን ምንድን ነው? ወደፊት የምግብ አቅርቦት እጥረት ሊገጥም ይችላል የሚል ነው? ታዲያ ይህ ስጋት ያለበት ሰው አሁን ላይ ለተወሰነ ጊዜ ከሚያስፈልገው በላይ ግዢ አይፈፅምም፤ ምክንያቱም እሱም ሌሎቹም በርካታ ግዢ በፈፀሙ ቁጥር ስለ ወደፊት ያለው ስጋቱ/ጭንቀቱ እውን ይሆናል። እንዴት? ካላችሁ…ሁሉም ከመጠን በላይ ግዢ ከፈፀመ ራሳችን በራሳችን ገበያ ላይ ያለውን የምግብ ነክ ነገሮች እናራቁታለን። ወደፊትም ያከማቸነው ቢያልቅና ለዳግም ግዢ ብንወጣ ያራቆትነውን ገበያ እናገኘዋለን፤ ይሄ የበዛ ጭንቀት ውጤት ነው፤ ሌሎችንም ራሳችንንም አንጠቅምም። በተቃራኒውም ምንም ጭንቀት የማይኖረን ከሆነ። ለነገ የሚያስፈልገንን ባለማድረጋችን ነገ ላይ ስንደርስ ግራ እንጋባለን፤ እንዲህ ባደርግ ኖሮ እያልን ራሳችንን እንወቅስ ይሆናል።
እንዲሁም መጠነኛ ፍርሃት ተጠቅመን ዛሬያችንን ከስጋት ነፃ ማድረግ ወይም ስለ ዛሬ ያለንን ስጋት መቀነስ እንችላለን። ታዲያ አካላዊ ምላሹን በመጠኑ እንዳስ። ሰውነታችን በተፈጥሮው አደጋ ውስጥ እንደሆንን ሲረዳ ቅፅበታዊ የነርቭ ሥርዓት /Autonomic Nervous Sys¬tem/ በሁለት አይነት መልኩ ምላሾችን እንዲሰጥ ያደርጋል። እነዚህም ስሜታዊ /Sympathetic Devision/ እና ስሜታዊ ያልሆኑ /Parasympathetic Division/ ናቸው። በስሜታዊነት ውስጥ፦ መታገል ወይም ማምለጥ እንደ አማራጭ ይወሰዳሉ፤ ቀጥሎም ሰውነታችን በመነሳሳት በርካታ ሃይል ይጠቀማል፣ የልብ ምት ይጨምራል። በአጠቃላይ ሰውነታችን ለመጋፈጥ የሚረዳውን ጉልበት ይሰበስባል፤ በዛም ሃይል ተጠቅሞ ወይ ይጋፈጣል ወይ ያመልጣል። ስሜታዊ ያልሆነው ሥርዓት በተቃራኒው ሰውነታችንን በመጠበቅ ላይ ይጠመዳል፤ በዚህም የተነሳ የስውነታችንን ውስጣዊ ሁኔታ ያረጋጋል፤ እንዲሁም ሃይልን ያምቃል ወይም ይሰበስባል።
ስለዚህ የሚሰጡንን የጥንቃቄ እርምጃዎች ፍርሃት አልባ ሁነን ችላ የምንል ከሆነ ማደረግ ያለብንን ሳናደርግ እንቀራለን። ነገር ግን በመጠነኛ ፍርሃት ውስጥ ሆኖ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማከናወን ራስንም ሌሎችንም ከከፋ ጉዳት ያድናል። ወረርሽኙ ግን ባንፈራውም ከጥንቃቄ ጉድለት፤ ከመጠን ባለፈ መልኩ ብንፈራውም ከመጠን ያለፈ ጥንቃቄ ስለምናደርግ ወዳልተፈለገ ፍርሃት፣ ጭንቀት፣ የበዛ ሃሳብ እና ተደጋጋሚ ደርጊት እናመራለን፤ ሁለቱም ጤናማ አይደሉም እና መጠነኛ ፍርሃት ላይ እንቁም፤ ፍርሃታችን ጤናችንን ይግዛልን፤ ጭንቀታችንም ነጋችንን ያሳምርልን።
በመጨረሻም ከፍተኛ ፍርሃት እና ጭንቀት ውስጥ ላሉ ጥቂት እንበልና ስለ-ወሸባ የምንጨዋወት ይሆናል። ነገሮች/ሁኔታዎች እንደዚህ ብቻ መሆን አለባቸው ብሎ አለማሰብ እና የከፋም የተሻለም ነገር ሊገጥመን እንደሚችል ማወቅ፤ በተመሳሳይ ሰዓትም ለተሻለው ዛሬ እና ነገ መጣር ቀዳሚዎቹ ፍርሃትን እና ጭንቀትን ማመጣጠኛ ስልቶች ናቸው። ሌላው የከፋ ፍርሃትን ለመቀነስ ፍርሃትን ከሚያባብሱ ነገሮች መራቅ። በቀን ውስጥ በተወሰነ ሰዓት ከመንግሥት አካላት እና የዓለም ጤና ድርጅት የሚሰጡ መረጃዎችን ብቻ መከታተል፤ ለምሳሌ በቀን አንዴ ወይም ሁለቴ። እንዲሁም ራስን በሌሎች ሥራዎች ላይ መጥመድ መልካም ሲሆን ምን ምን የሚለውን በቀጣይ በቤት ውስጥ መቀመጡ ያለውን ትሩፋቶች ስናወጋ እመለስበታለሁ።
የወሸባው ጊዜ እና የቤት ውስጥ ቆይታችን ምን ይመስላል? ምንስ ይምሰል?
እውቁ የሥነ-አዕምሮ ሐኪም ቪክቶር ፍራንክል (ዶ/ር) በናዚ ማጎሪያ ሰፈር/ካምፕ ውስጥ ያሳለፈውን የሦስት ዓመት ጊዜ “እርቃኑን የቀረ ህይወት” ሲለው ያለ ምክንያት አልነበረም። ከቤተሰቡ ውስጥ ከእህቱ በስተቀር አባቱን፣ እናቱን፣ ወንድሙን እና ባለቤቱን በማጎሩያ ሰፈሮቹ ውስጥ በሞት አጥቱዋቸው ነበር። በእዛ አሰቃቂ፥ በየደቂቃው፣ በየሰዓቱ፣ በየቀኑ…ሞት አፍንጫው ሥር ተቀምጦ “መጣው” በሚልበት ህይወት ውስጥ ሆኖ ፍራንክል (ዶ/ር) ታላቁን የህይወት ትምህርት ተገነዘበ። እርቃን በቀረ ህይወት ውስጥ የብርሃን ጮራ እንዴት እንደሚፈነጥቅ ‹‹ሎጎ የንግግር ህክምናን›› በማስተዋወቅ የበርካቶች ህይወት ላይ በጎ ተጽዕኖ ለመፍጠር ችሉዋል።
ፍራንክል እደሚለን “ሰዎች በህይወታቸው ሊኖራቸው የሚገባው መርህ ፍቃደ-ሃይል ወይም ፍቃደ-ደስታን መፈለግ ሳይሆን ፍቃደ-ትርጉምን መፈለግ ነው”። ፍቃደ-ትርጉም መፈለግ ስንል ‹‹በህይወታችን ላይ ትልቁን ቦታ እንዲይዝ ፍቃድ ልንሰጠው የሚገባው፥ ለህይወት የሰጠነው ትርጉም ነው›› የሚል አንድምታን ይይዛል። ስለዚህም ሰዎች ምንም እንኳን በአሰቃቂው የናዚ ማጎሪያ ሰፈር ቢገኙም፤ እዛ ውስጥ ላላቸው የእርቃን ኑሮ የሚሰጡት ትርጉም አሰቃቂውን ጊዜ ለማለፍም ሆነ ላለማለፍ ትልቅ ሚና አለው የሚል አንዳች ንድፈ-ሐሳብ እናገኛለን።
አሁን የናዚ ወጀብ የለም፤ አሁን እፊታችን የቆመው፣ ፍርሃታችንን ያበዛው ወይም መዳፈራችንን ያበዛው CO¬VID-19 ነው። አሁን እፊታችን የቆመው የወሸባ ጊዜ ነው፤ ለራሳችን፣ ለቤተሰባችን፣ ለሀገራችን እና ሲልቅም ለዓለማችን ስንል በቤታችን/በተወሰነ ቦታ የመቀመጥ ግዴታ። ታዲያ ከፍራንክል ተምረን ወደ ውሽባ የገባን ሁላ፤ ለውሽባው የምንሰጠውን ትርጉም በጎ በሆነ መልኩ ከቀየርነው ይህን ወጀብ አልፈን እንደ ቻይናዋ ግዛት የብርሃኑዋን ጮራ የማናይበት ምንም ምክንያት የለም። በርግጥ ወሸባ ታሞ ለህክምና በአንድ ቦታ ላይ መቀመጥን ቢያመለክትም፤ ሳንያዝም መ-ወሸብ አንዱ የቅድመ-መከላከል ህክምና ስልት ነውና ሃሳቡን መቀበል መልካም ነው። የወሸባ ፍቺ የተጣቀሰው ‹‹የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ የካቲት 1993›› ካሳተመው የአማረኛ መዝገበ ቃላት ነው። በመጨረሻም ጥቂት ሙያዊ ‹‹ሥነ-ልቦናዊ›› ሃሳቦችን እንካቹ ልበል።
በመጀመሪያ ነገሮች ምንም ያህል የከፉ ቢሆኑም፤ ነገሮችን የምንረዳበትን መንገድ በመቀየር በጎ ልናደርጋቸው ይቻለናል። ለምሳሌ አንድ ሰው ውሻ ብሎ ቢናገረን፤ አንድም ልክስክስ አለኝ ብለን መናደድ እንችላለን፤ ሁለትም ታማኝ ተባልኩ ብለን መደሰት እንችላለን፤ ባዩ የፈለገውን አስቦ ቢለንም እኛ የምንሰጠው ትርጉም በአዕምሮአችን ላይ ትልቁን ቦታ ይይዛል። ስለዚህ መወሸቡ ጉዳት እንዳለው ሁላ፣ ወጀቡ ንፋስ እንዳለው ሁላ ጥቅም እንዳለውም በማሰብ፤ በጨለማው በኩል ብርሃኑን እንይ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30/2012
ኖኅ ውብሸት
(ሳይክ-ኢን-አክሽን ክለብ፤ ሳይኮሎጂ ት/ቤት፣አ.አ.ዩ