ትኩረቴ በሀገሬ “የዴሞክራሲ አጫዋቾችና ተጫዎቾች ነን” ባዮች ላይ ያተኮረ ነው።የርዕሰ ጉዳዬን ሃሳብ ያጎለበትኩትም ካነበብኳቸው በርካታ መጻሕፍት እና በውሎ አምሽቶ ከቃረምኳቸው ትዝብቶቼ በመቀነጫጨብ ይሆናል።“ቀነጫጭቤ” ያልኩት እንደ ልብ ሃሳቤን በምልዓት ለመዘርገፍ የጋዜጣው አምድ የአርብ ጥበት ስለወሰነኝ ነው።“አርብ” የሚወክለው ዕለት ጁምዓን ሳይሆን በጠቢባኑ የሀገሬ ሸማኔዎች ቋንቋ “የሸማን ስፋትና ጥበት” የሚገልጸውን ብርቱ ቃል ነው፡፡
ርዕሴ ብቻ ሳይሆን ብዕሬም ሃሳቡን ለማስፈር የሞከረው በቁጣ ጫን ጫን እየተነፈሰ ነው።“ምን የሚያስቆጣ ነገር ተገኝቶ?” ብሎ ለሚሞግት አንባቢ “የሀገሬን ፖለቲካና የዴሞክራሲ ጉዳይ በተመለከተ ምን የማያናድድና የማያስቆጣ ነገር ይኖርና!” መልሴ ነው።ስለ እውነትና ስለ ሐቅ እንነጋገር ከተባለ የሰው ልጅ በሙሉ በአግባቡና በወጉ ከቁጡነት ባህርይ ነጻ መሆን እንደማይችል ሕይወት ራሷ የምታኖረን እየተቆጣችና እያደበነችን ስለመሆኑ ለመረዳት አይከብድም።በሥነ ቃላችን ውስጥም ቢሆን፤
“እረ ምረር ምረር ምረር እንደ ቅል፣
ስላልኮመጠጠ ስላልመረረ ነው
ዱባ እሚቀቀል፡፡”
የሚል ብሂል መኖሩን መጥቀስ ይቻላል።ቅዱሱ መጽሐፍም እኮ “ተቆጡ፤ ነገር ግን በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ እንዳይጠልቅ” በማለት የመለኮታዊ ቃል ማረጋገጫ ሰጥቶናል።ስለዚህም ጥቂት የብርሃን ወገግታ እያሳየን ያለው ሀገራዊ የትሩፋት ጀንበር “በእነ እንደ ልቡ” እኩይ ቅስቀሳ እንዳይዳምን ስለምሰጋ ነፃ ሃሳቤን ድምጸቱ መረር ቢልም ለሚመለከታቸው ሁሉ በብዕሬ ውክልና “ይድረስ!” ብል ክፋት ያለው አይመስለኝም።
የግል እምነቴን በተመለከተ የሀገሬ ዴሞክራሲና የፖለቲካ ምህዳር የሚያስታውሰኝ “ላም እሳት ወለደች፤ እንዳትልሰው ፈጃት፤ እንዳትተወው ልጇ ሆነባት” የሚለውን ነባር ብሂል ነው።የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝቦች ተመሳሳይ ይዘት ያለው ብሂላቸውን ያዋቀሩት እንደ እኛ በረጅም ብሂል ሳይሆን በሁለት ቃላት ጥምረት ነው፤ “necessary evel” በማለት፡፡
“አንቅረን እንዳንተፋው እዳ የሆነብን፤ አላምጠን እንዳንውጠው የሚለበልበን” የሀገራችን የፖለቲካ ጉዳይ ከጊዜ ወደ ጊዜ የፍም ረመጥ እየሆነ እንደሚሄድ እያስተዋልን ነው።ይሰክናል ብለን ተስፋ ስናደርግ በምላሳቸው ላይ “ፖለቲከኛ” የሚል ታርጋ በለጠፉ “ሳይሞቅ ፈላዎች” እስከ መቼ እየተናጥን እንደምንኖርም ግራ ተጋብተናል፡፡
ቢሆንልንማ “የእሳት ጥጃ” በወለደች ምስኪንና የዋህ ላም የመሰልናቸው የፖለቲካና የዴሞክራሲ ጽንሰ ሃሳቦች ከመዛግብተ ቃላቶቻችን ውስጥ ቢሻሩ በግሌ ደስታውን አልችለውም።ለምን ቢሉ “ዴሞክራሲ” የሚለው ጽንሰ ሃሳብ በየሥርዓተ መንግሥታቱ “ጽንሱ እየጨነገፈ” ስናስተውል ብንኖርም ዛሬም ድረስ “የደንቆሮ ለቅሶ መልሶ መላልሶ” እንዲሉ “የሰርክ ጸሎታችን ሆኖ” በነጋ በጠባ የመቃተቻ ምክንያት እንደሆነን “የዴሞክራሲ ጠበቆች” ነን ባዮቹ “የጠብ ዕቃዎች” ይጠፋቸዋል ለማለት ያዳግታል፡፡
ከቀደምት ዘመናት ጀምሮ የሀገራችን የመንግሥታት ሥርዓቶች “በወርቅ ቀለም” የተጻፈ ሕገ መንግሥታችን እያሉ ሲያስጨበጭቡን የኖሩት “ቢከፍቱት ተልባ” በሆኑ ቃላት የታጨቀ ሰነድ እያቆሙልን ነው።ለምሳሌ፤ ከ1923-1948 ዓ.ም “በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የቆመው ሕገ መንግሥት እና ከ1949-1966 ለ17 ዓመታት ሀገሬ የተገዛችበት የሁለተኛው ዘመን የንጉሡ ሕገ መንግሥት ሕዝቡን ጠፍንገው የገዙት እኩልነትንና ሰብዓዊነትን እየሰበኩ ነበር።የሚገርመው ነገር በእነዚህ ሁለት ሕገ መንግሥታት ውስጥ ለማጣፈጫነት የተነሰነሱት የዴሞክራሲ መገለጫ ቅመሞች ዛሬም ድረስ ልዩነት ሳይኖራቸው እንደተመሳሰሉ ዘልቀዋል፡፡
ለአብነት ያህልም በ1923 ዓ.ም ሰነድ ላይ ሕጉ ለምን እንደቆመ በተሰጠው “ያዋጅ ቃል” ውስጥ የሚከተለው
ወርቃማ አባባል ደመቅ ተደርጎ ተጽፏል፤ “እኛ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ የተቀበልነውን አደራ፣ እኛም ሠርተን ጠብቀን ተከታያችንም በሕግ እንዲቀበለንና በደንብ እንዲሠራ፣ ለሀገራችንም በመልካም አስተዳደር በሕግ የሚጠበቅበትን ደንብ ከማቆም በቀር ሌላ የምንመልሰው ወሮታ ስለሌለን ለኢትዮጵያ ልማት፣ ለመንግሥታችን ጽናት፣ ለምንወደው ሕዝባችን ጥቅምና ሀብት ሆኖ ደስ እንዲያሰኝ ተስፋ ስላደረግን አሳባችንን ገልጸንና አስረድተን የመንግሥት ሕግ እንዲቆም ቆረጥን፡፡” (ዝክረ ነገሥት ገጽ 766)፡፡
ተከታያችን ተብሎ “17 ዓመታት እንዲገዛ” ክፉ ትንቢት የተነገረለት ወታደራዊው ፀረ ዘውድ የደርግ መንግሥትም ባቆመው “ወርቃማ” ሕገ መንግሥት መግቢያ ላይ ለሀገራችንም አልፎ ለዓለም ሁሉ እንደሚተርፍ ያወጀበት ሕገ መንግሥት መግቢያ ይዘት እንዲህ ይላል፤ “ለዓለም ሰላም፣ ለፍትሕ፣ ለዴሞክራሲና ለማኅበራዊ እድገት ተገቢ አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚያስችለውን የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ የሚመሠረትበትን ይህን የአገሪቱ የበላይ ሕግ የሆነውን ሕገ መንግሥት በጥር 24 ቀን 1979 ባደረግነው ውሳኔ ሕዝብ አጽድቀናል፡፡” (የኢሕዲሪ ሕገ መንግሥት መስከረም 1/1980)፡፡
“ከወርቃማነት” ከፍ ያለውና ከ”አልማዝም” የላቀ ዋጋ እንዳለው ሲወደስና ሲዘከርለት የኖረው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም በሰነዱ ቀዳሚ መግቢያ ላይ ያሰፈረው ሃሳብ እንዲህ ይነበባል፤ “በትግላችን በከፈልነው መስዋዕትነት የተገኘውን ዴሞክራሲና ሰላም ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ፤ ይህ ሕገ መንግሥት ከዚህ በላይ ለገለጽናቸው ዓላማዎችና እምነቶች [የግለሰብና የብሔር/ብሔረሰብ መሠረታዊ መብቶች መከበራቸው፣ የፆታ እኩልነት መረጋገጡ፣ ባሕሎችና ሃይማኖቶች ካላንዳች ልዩነት እንዲራመዱ የማድረጉ ኃላፊነት ጽኑ እምነታችን በመሆኑ] ማሰሪያ እንዲሆነን እንዲወክሉን መርጠን በላክናቸው ተወካዮቻችን አማካይነት በሕገ መንግሥት ጉባዔ ዛሬ ኅዳር 29 ቀን 1987 አጽድቀነዋል፡፡” (በስራ ላይ ያለው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መግቢያ)፡፡
በሦስቱም የአገዛዝ ሥርዓቶች የተደነገጉት ሕገ መንግሥታት ሕዝቡን ሲያማልሉት የኖሩት “ከሰማይ በምትታለብ ላም” የተስፋ ወተት እየጋቱት ነበር።ሕዝቡም ከ“ወርቃማዎቹ ሕገ መንግሥታት” አንዳች ጠብ የሚል ትሩፋት ባለማግኘቱ “ላም አለኝ በሰማይ፤ ወተቷንም አላይ” እያለ በመተረት ዳቦ ብርቁ፣ ራስን ለማሸነፍ ድኩም ሆኖ “በቆይ ብቻ ጸጸት” ሊኖር ግድ ሆኗል፡፡
ከአሁን በፊት ያስነበብኩት አንድ ጽሑፍ “ኦ ዴሞክራሲ! በስምህ ስንት ግፍ ተሠራ!” የሚል ርዕስ እንደነበረው ቋሚ አንባቢያን የሚያስታውሱት ይመስ ለኛል። በዴሞክራሲ ስም ሲቀጠቀጥ የኖረ ሕዝብ ከእኛ ሌላ ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም።“ሀገሬን ርቧታል!” የራባት “እህል” ብቻ አይደለም።እንደ አቀን ቃኙ ድምጻዊ፤
“እህልማ ሞልቷል ሆዴ መች ጎደለ፣
ፍቅራችን ብቻ ነው ያልተደላደለ፡፡”
እያልን ለማንጎራጎር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት ግፉዓን ርሃብተኛ ወገኖቻችን በትዝብት እየሸነቆጡ ቢያሳቅቁንም ቢያንስ “የዴሞክራሲ ጠበቆች (የጠብ ዕቃዎች)” ነን የሚሉት የጥቂቶች መሶብ ከመትረፍረፍ ሊጎድል ያለመቻሉ ግን እውነት ነው፡፡
በዘመናት ውስጥ ለውጥ ፈላጊ ትንታጎች መፈክር አንግበው “አትነሳም ወይ!” እያሉ የጮሁለት ዴሞክራሲ፣ እልፍ አእላፍ ወገኖቻችን የተዋደቁለት ዴሞክራሲ፣ በትረ ሥልጣን የጨበጡ መሪዎች ሁሉ የመሃላቸው ኪዳን ያደረጉት ዴሞክራሲ፣ ብዙ ጥራዞች የተጻፉለት ዴሞክራሲ፣ ለብዙዎቹ የቀን ቅዠት የሌት ህልም የሆነባቸው ዴሞክራሲ ዛሬም ከጮርቃ ፍሬነት ደረጃ ከፍ ብሎ ልናጣጥመው አልታደልንም፡፡
ቢሆንልንማ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በበርሃ ውስጥ እየተጓዘ እያለ እርቧቸው ወደ አንዲት በለስ ፍሬ ለማግኘት ሲቀርቡ ቅጠል ብቻ ሆና እንዳገኟትና ረግመዋት እንደደረቀችው የበለስ ዛፍ እኛም ፍሬ አልባውን ዴሞክራሲ በጋራ ድምጽ ረግመን ብናደርቀው ሳይሻል ባልቀረ ነበር።ለምን ቢሉ የተረፈን
ስም ብቻ ነዋ! “የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ . . .” የሚል፡፡
ብዙ ሰዎች “ኦ ዴሞክራሲ! በስምህ ስንት ግፍ ተሠራ!” የሚለውን ጽሑፌን አንብበው “ዴሞክራሲ በራሱ ምን ችግር አለው? ችግሩ የዴሞክራሲ ጠበቃ (የጠብ ዕቃ) ነን የሚሉት ፖለቲከኞች አይደሉም ወይ? ትኩረትህንስ እነሱ ላይ ማድረጉ አይሻልም ወይ?” እያሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች አዥጎድጉደውልኛል፡፡
የግል አቋሜ አሮጌው የጥንታዊያኑ የግሪክ ፈላስፎች የዴሞክራሲ አቁማዳ የዛሬውን አዲስ “የወይን ጠጅ ትውልድ” ሃሳብ ስለመሸከሙ ያጠራጥረኛል።በተለይም በሀገራችን “የዴሞክራሲ ጥብቅና ፈቃድ” አለን የሚሉት “በመወለድ የአባቶቻቸው ልጆች፤ በአስተሳሰብ የእነ አርስቶትል ቅድመ አያቶች” የሆኑትና የጡረታቸውን ገደብ ጥሰው አደባባዩን ያጨናነቁት ፖለቲከኞቻችን በስመ ዴሞክራሲ ሲያናክሱን እያስተዋልን እንደምን “ዴሞክራሲ ሆይ ሺህ ዓመት ንገሥ!” እያልን ኮፍያችንን ለክብሩ እናነሳለን?
“ዴሞክራት” የሚባሉት ሀገራት ሕዝቦችም ሳይቀሩ እንደምን “በስመ ዴሞክራሲ” ልቅ እንደተለቀቁ እድሜ ለዘመነ ቴክኖሎጂ በነጋ በጠባ ቤታችን ቁጭ ብለን እያስተዋልን ነው።እርግጥ ነው ሥጋቸው በእህልና ውሃ ወፍሯል፤ ኑሯቸውም በቁሳቁስ ደምቋል።በነፍሳቸውና በመንፈሳቸው ግን ተርበው “ኤሎሄ! ኤሎሄ” እያሉ እንደሚቃትቱ እያስተዋልን ነው፡፡
በግሌ መንግሥታዊ ሥልጣናቸውን አደላድለው እየመሩን ባሉት ጎምቱና ፊትአውራሪ ሹማምንት የተስፋ ወገግታ እየታየኝ ለእቅዳቸውና ለትግበራቸው “አሜን!” የምለው ሥራቸውን እንጂ “ለዴሞክራሲ ገድል” በነጋ በጠባ እየዘመሩ ስለማያደነቁሩን ነው።በአንጻሩ የሥልጣን ወንበር ብቻ እየቃዡ በፖለቲካው መድረክ ላይ በህልም ሩጫ የሚደነባበሩትን “ቅድመ አያቶች” የምኮንነው ተግባርና ቃል አልባ ሆነው ተራቁተው ስለማስተውላቸው ነው።በዴሞክራሲ “ወይን ጠጅ” በሰከሩት ዘንድ ሀፍረት፤ በእኛ የችግር ውሃ ጥም ባሳረረን ድሆች ዘንድ ደግሞ “የዴሞክራሲ ብርቅነት” እያቃዠን እንድንኖር አዚም የሚነዙብንን “ምንትስ ፖለቲከኞች” ሀገሬና ሕዝቤ አንገዋለው የጣሉ ዕለት የሚዥጎደጎደው የስዕለት ዕልልታ የህልም ያህል እየታየኝ ልቤ ሲረሰርስ ይታወቀኛል፡፡
በቤተሰባችን ውስጥ ከልጅ ልጅ እየተወራረሰ የተላለፈ አንድ የውርስ ዕቃ ሁሌም ትዝ ይለኛል። ምናልባት “ለግራ ገቡ የሀገሬ ስመ ዴሞክራሲ” ማሳያ ይሆን ከሆነ ለአንባቢያን ብገልጸው አይከፋም።የሴት አያቴ እማማ ይርገዱ ብሩ “አዋሽ” እያሉ የሚጠሩት አንዳች የሚያህል የእንጨት በርሜል ነበራቸው።በግዝፈቱ ቢወዳደር ዓለም አቀፍ እውቅና የሚያገኝ ይመስለኛል።አያቴ በዚያ በርሜል የሚጠምቁት ጠጅ ብዙዎችን አሳክሮ ለድብድብ ሲዳርግ ደጋግሜ በዓይኔ በብረቱ ተመልክቻለሁ።አያቴ በኩራት
የሚመሰክሩለትን ያንን “አዋሽ” በርሜል ከእናታቸው (ከእኔ ቅድመ አያት) በውርስ እንዳገኙት ደጋግመው ይመሰክሩ ነበር፡፡
ያንኑ በርሜል ለልጃቸው ለእኔ እናት በውርስ አሸጋግረውላት ጠላ እየጠመቀችበት ጠጭው በሞቅታ ሲንዠባረርም አስተውያለሁ።ይህ ጎምቱና ዘመን ያሸበተው በርሜል ወደ ታላቅ እህቴ በውርስ ተላልፎ የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከር ሆኖ ሲያገልግል ኖሯል።ቀጥሎ ወደ ልጅ ልጆች ሲተላለፍ ለምን ዓይነት አገልግሎት እንደሚውል እርግጠኛ ሆኜ ለመናገር አልደፍርም።ወይ የሚያሰክር መጠጥ እንደለመደው ይጠመቅበታል፤ አለያም እንዳልባሌ ቁሳቁስ ወደ ስርቻ ይጣላል።
ዕድሜውን አድሎኝ ለልጅ ልጆችም ሲወርድ ሲወራረድ ካየሁ አንድ የኀዘን እንጉርጉሮ ግጥም እጽፍለት ይሆናል።በጣሙን ፈገግ የሚያስደርገኝ ሌላው ከዚያ በርሜል ጋር በቅብብሎሽ እየተሸጋገረ የመጣው ተጠቃሽ የቤተሰባችን ብሂል ነው።እንዲህ ይላል፤ “ግብዣ ለማያውቅ ሰው ጠጅህን አትጋብዘው፡፡”
የዴሞክራሲ ጉዳይም እንዲሁ ይመስለኛል። ጥንታውያኑ ግሪኮች ገብቷቸውም ይሁን ሳይገባቸው እራሳቸው ፀንሰውና ወልደው ያሳደጉት ዴሞክራሲ እርስ በእርስ በአደባባይ ክርክር፣ በአተረጓጎምና በአተገባበር እያናከሳቸውና እያሳከራቸው ከትውልድ ትውልድ በመሸጋገር የዛሬዎቹ አውሮፓውያን፣ አሜሪካውያንና አንዳንድ ሀገራት እጅ ሊወድቅ ግድ ሆኗል፡፡
ውርሱን የተቀበሉት አንዳንድ የዓለማችን ሀገራትና ፖለቲከኛ መሪዎች ለሕዝባቸው እንደ ልብ የመናገርና የመብላት መብትን ማጎናጸፋቸውን እንክድም። በሥነ ምግባር ድህነትና ጉስቁልና ከሰብዓዊነት እንዳጎደሏቸውም መካድ አይቻልም።“የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻና ድሪያ”፣ ከሰብዓዊ ፍጡር ይልቅ አብዝቶና አግዝፎ ለእንስሳት መብት መጮኽና መቆርቆር (ለእንስሳት መብት መከራከር በራሱ ችግር ባይኖርበትም)፣ የራስን ጣኦት መቅረጽና ለሰይጣናዊ አምልኮ በይፋና በግላጭ መገዛት፣ በፈጣሪ መልክና አምሳል የተፈጠረውን ሰው በላቦራቶሪ ውስጥ እስከማምረት መድረስ፤ “ለተጠቁ የዓለም ሕዝቦች እንቆማለን” በሚል “በዴሞክራሲያዊ መርህ በተቀባባ ሤራ” ሀገራትን በጦርነትና በኢኮኖሚ ማድቀቅና የራስን የበላይነት ማንገስ “ኦ ዴሞክራሲ! በስምህ ስንት ግፍ ተሰራ!” የሚለውን ጩኸት እውነታነት ያረጋግጣል፡፡
የዛሬዎቹ የእኛ የዴሞክራሲ ጠበቆች (የጠብ ዕቃዎች) ደግሞ የዴሞክራሲ መገለጫዎች የሚሏቸውን መርሆዎች በነጋ በጠባ እንደ የገደል ሚሚቶ እያስተጋቡ ሀገርን ሲያምሱ እያስተዋልን ነው።ሀገር እየተፈተነችበት ያለው ወረርሽኝ መያዢያ መጨበጫ አሳጥቶን ግራ በተጋባንበት ወቅት ዴሞክራሲያዊው ሀገራዊ ምርጫ በተያዘለት ቀጠሮ መሠረት ካልተካሄደና እኛ በትረ ሥልጣኑን ካልነጠቅን የዓለም ፍጻሜ ይሆናል።የፈለገ ስለ ኮቪድ 19 እያወራ ሊቀጥል ይችላል እኛ ግን “ከዴሞክራሲያዊ ምርጫ” ውጭ ለወረርሽኙ፣ ለህሙማንና ሕይወታቸውን ለሚነጠቁት ግድ የለንም እየተባለ ሲለፈፍ በግላጭ እየሰማንም እያስተዋልንም ነው።
ለመሆኑ የሀገራችን የዴሞክራሲ ጠበቆች (የጠብ ዕቃዎች) ፖለቲካዊ ስብዕና ምን ይመስላል? ለሚለው መሠረታዊ ጥያቄ የምሰጠውን መልስ በተመለከተ በቀጣዩ ጽሑፌ እንደምመለስበት ቃል እየገባሁ አንዳንድ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ወርውሬ ሃሳቤን ላጠቃልል።“በዴሞክራሲ ምርጫ” ሥልጣን ተይዟል እንበል ከዛስ? “በዴሞክራሲ ምርጫ” የፈላጭ ቆራጭነት በትር ተጨበጠ፣ ዝናና ሀብትም ተገኘ እንበል ከዛስ? ልጆች ሚስትና ዘመድ አዝማድ “በዴሞክራሲ ምርጫ” በተገኘ ሀብትና መንገድ አረብ ሀገራት፣ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ ለመንሸራሸር በቁ እንበል ከዛስ? “በዴሞክራሲ ምርጫ” በተገኘው ሥልጣን ምክንያት “ጌታዬ እና እሳቸው” የመባል ምኞት ተፈጸመ እንበል ከዛስ? እረ ብዙ ከዛስ ብለን የምንደረድራቸው ጥያቄዎች ነበሩን።በ“ላም እሳት ወለደች . . .” የተንደረደርኩባቸውን የእነዚህን መሰል “የዴሞክራሲ የጠብ ዕቃዎች” ፖለቲካዊ ስብዕና ምን እንደሚመስል እመለስበታለሁ።ሰላም ይሁን!!!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2012
(በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ)