ረቡዕ ሐምሌ 8 ቀን 1962 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን በምንጭነት ጠቅሶ የኤሌክትሪክ ምሰሶ ይዘው ህይወታቸው ስላለፈ እናት ተከታዩን ዘገባ አስነብቦ ነበር፡፡
እመት እናኑን ኮረንቲ ገደላቸው
በግምት 35 ዓመት ዕድሜ ያላቸው አንዲት ሴት ባለፈው ቅዳሜ ደሴ ከተማ ውስጥ በኤሌክትሪክ አደጋ ሞቱ፡፡ እመት እናኑ ረታ የተባሉት እኚሁ ሴት ሙጋድ ከተባለው ሥፍራ ውሃ ቀድተው ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲመለሱ በዕለቱ በዘነበው ዝናብ ምክንያት የረገጡት መሬት አዳልጧቸው ያገኙትን የኤሌክትሪክ ምሰሶ በእጃቸው ሲይዙት ኮንታክት አድርጎ ወዲያውኑ ገድሏቸዋል፡፡
አስክሬናቸው በፖሊስና በቤተ ዘመዶቻቸው ዕርዳታ ተነስቶ አስፋወሰን ኃይለሥላሴ ሆስፒታል ከተመረመረ በኋላ በዚያው ዕለት ደሴ ከተማ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ተቀብ ሯል፡፡
*
ሐሙስ ነሐሴ ሰባት ቀን 1962 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ደግሞ ቀበና ወንዝ ላይ ስለተከሰተ የመኪና አደጋ ተከታዩን ዘገባ አስነብቦ ነበር፡፡
ኦፔል ወይዘሮዋን ይዛ
ቀበና ወንዝ ገባች
ቁጥር 324404 የሆነችው ኦፔል አውቶሞቢል ነሐሴ 4 ቀን አጥቢያ አራት ሰዓት ሲሆን ዊንድ ሱዛ የተባለችዋን የ28 ዓመት እንግሊዛዊት ወይዘሪት እንደያዘች ቀበና ድልድይ ውስጥ ዘላ ገብታለች፡፡ ወይዘሪቷና መኪናዋ ከዋናው አውራ ጎዳና ጠርዝ ላይ ቁልቁል ዘለው አውቶሞቢሏ በጀርባዋ ስትዘረር አናቷ ተሰርጉዷል፡፡ በወይዘሪት ሱዛ ላይ ምንም ዓይነት አደጋ ሳይደርስ በሰላም ወጥታለች፡፡
ርዝመቱ 22 ሜትር ርቀት ባለው የቀበና አዘቅት ውስጥ የገቡት እንግሊዛዊቷ ወይዘሪትና ኦፔል አውቶሞቢል በአካባቢው ህዝብና በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የአደጋ መከላከያ አማካኝነት ወጥተው ወይዘሪቷ ወደ ሆስፒታል መኪናዋ ወደ ጋራዥ መወሰዳቸውን ምርመራውን የተከታተለው የትራፊክ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2012
የትናየት ፈሩ