የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ለአምስት ዓመታት በዱር በገደል ባደረጉት ተጋድሎ ፋሺስት ጣሊያን ተሸንፋ ባንዲራዋ ከታላቁ ቤተ-መንግሥት ወርዶ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የተሰቀለው ከ79 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ነበር።
ሚያዝያ 27 ሁለት ተያያዥ ጉልህ ታሪካዊ ክስተቶች የተስተናገዱበት ዕለት ነው። ኢትዮጵያ ላይ ወረራ የፈፀመው የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር አዲስ አበባ የገባው ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም ነው። ሚያዝያ 27 1933 ዓ.ም ደግሞ ከአምስት ዓመታት የአርበኞች ተጋድሎ በኋላ ኢትዮጵያ ፋሺስት ጣሊያንን ያሸነፈችበት የድል ቀን ነው።
ጣሊያን ከዓድዋ ሽንፈቷ 40 ዓመታት በኋላ በዘመናዊ የጦር መሣሪያና በወታደራዊ ኃይል ይበልጥ ደርጅታ ዳግም ኢትዮጵያን ወረረች። ኢትዮጵያም ከጣሊያን ጦር ጋር ለብዙ ወራት በፅናት ስትዋጋ ቆይታ የመጨረሻውን ጦርነት ማይጨው ላይ አደረገች። ነገር ግን እንግሊዝና ፈረንሳይ የጦር መሣሪያ ግዢ እንዳትፈጽም ለጣሊያን ወግነው ስላሴሩባት ኢትዮጵያ በጦርነቱ ድል ማድረግ አልቻለችም። የኢትዮጵያ ጦር በአውሮፕላን በሚጣልበት ቦምብና በሚርከፈከፍበት የመርዝ ጋዝ ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰበት የጣሊያን ጦር ዋና ዋና የሚባሉ ከተሞችን እየተቆጣጠረ ወደ ማዕከል መገስገስ ቀጠለ። በኋላም ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ገባ።
የማይጨው ሽንፈት ለጣሊያን አንገብርም ያሉ ጀግኖች በየጫካውና ሸንተረሩ ለአርበኝነት ሥራ እንዲነሳሱ አደረጋቸው። ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በዱር በገደሉ እምቢ ለአገሬ ብለው የሽምቅ ውጊያ ጀመሩ። ንጉሰነገስቱም ወደ አውሮፓ ተጉዘው በጊዜው ለነበረው የመንግሥታቱ ማኅበር አቤቱታ አቀረቡ ፤ የሚሰማቸው ግን አላገኙም።
ጣሊያን ኢትዮጵያ ውስጥ የቆየባቸው አምስት ዓመታት የዛፍ ላይ እንቅልፍ ሆነውበት ነበር። የኢትዮጵያ አርበኞች በቅንጅት በሚጥሉት ውጊያ የጣሊያን ወታደሮችን መፈናፈኛና መግቢያ መውጫ አሳጧቸው። በሂደትም ከጣሊያን ወታደሮች በሚ ማርኩት መሣሪያ ራሳቸውን እያደራጁ አብዛኛውን የገጠር ክፍል ተቆጣጠሩ።
በሌላ በኩል የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲቀጣጠል ጣሊያን የናዚ ጀርመን አጋር ስለሆነች እንግሊዞች ኢትዮጵያን መደገፍ ጀመሩ። ወታደራዊ ድጋፍ በማድረግ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ረዷቸው።
ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ “የኢትዮጵያ ታሪክ” በተሰኘ መጽሐፋቸው ሁኔታውን ሲተርኩ “የአርነት ትግሉ የመጨረሻውን ምዕራፍ የያዘው አርበኞቹ በጉጉት ሲጠብቁ እንደነበሩት ጦርነቱ ዓለም አቀፋዊ ስፋት ሲያገኝ ነው። በሰኔ 1932 ሙሶሊኒ ምናልባትም በህይወቱ ዐቢይ ሊባል የሚችለውን ስህተት ፈጸመ።
ይኸውም የሂትለር አጋር በመሆን ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ውስጥ መግባቱ ነው። በዚህ ዕርምጃው የኢትዮጵያ ወረራውን ያሳካለትን የእንግሊዝንና የፈረንሳይን አይዞህ ባይነት ከመቀጽበት አጣ። በተለይም እንግሊዞች በፊት እንደዋዛ ያልተመለከቱትን ያህል አሁን በምሥራቅ አፍሪካ ቀኝ ግዛቶቻቸው ላይ እንደሚያንዣብብ አደገኛ መቅሰፍት አዩት። በዚህም አኳኋን ከ19ኛው መቶ ዓመት መገባደጃ ጀምሮ የኢጣሊያ ወዳጅ የነበረችው እንግሊዝ ወደ ቀንደኛ ጠላትነት ተለወጠች። በአንጻሩ የአጼ ኃይለስላሴ የፖለቲካ ጠቀሜታ ገዝፎ መታየት ጀመረ። ኢትዮጵያውያንን በሙሉ ሊያስተባብራቸው የሚችል ዓይነተኛ መሳሪያ ሆኖ ስላገኙት እንግሊዞች በገጠር ከነበረበት የገጠር ከተማ አውጥተው ወደ ጦር ግንባሩ አሸጋገሩት” ይላሉ።
በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሚመራውና የአርበኞችና የእንግሊዝ አማካሪዎች የሚገኙበት ጌዲዮን ተብሎ የተሰየመው ጦር ከሱዳን ተነስቶ በኦሜድላ አልፎ በጐጃም በኩል ወደ መሐል አገር ገሠገሠ። በጄኔራል ካኒንግሃም የሚመራው የእንግሊዝ ጦር ከኬንያ ተነስቶ ከደቡብ አቅጣጫ ወደ መሀል ኢትዮጵያ ሲገሰግስ፤ በጄኔራል ፕላት የሚመራው ጦር ደግሞ ከሱዳን ተነስቶ ወደ አሥመራ፤ ከዚያም ከሰሜን አቅጣጫ ወደ መሐል ኢትዮጵያ ተንቀሳቀሰ። የኢትዮጵያ አርበኞች በጣሊያን ወታደሮች ላይ ጥቃትቸውን አፋፋሙ። ጣሊያኖች ክፉኛ ተሸነፉ። በየቦታው ድል የመሆናቸው ዜና ተነገረ ፤ ዘመቻው ከተጀመረ ሁለት ወራት ሳይሞላው፤ ጣሊያኖች አዲስ አበባን ለቀው ወጡ።
መጋቢት 28 ቀን 1933 ዓ.ም የጄኔራል ካኒንግሃም ጦር አዲስ አበባን ተቆጣጠረ። እንግሊዞች ኢትዮጵያውያን አርበኞች ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ስላልፈለጉ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን በደብረ ማርቆስ ለአንድ ወር ያህል እንዲቆዩ አደረጓቸው። በኋላ የአርበኞች ተቃውሞ ስለበረታ ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ፈቀዱ። ማርሻል ባዶሊዮ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማን አወርዶ፣ የጣሊያንን ባንዲራ በሰቀለበት አምስተኛ ዓመት ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥቱ በከፍተኛ አጀብ በታላቁ ቤተ መንግሥት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ መልሰው ሰቀሉ። ጀግኖች አርበኞች የጣልያንን ጦር ለአምስት ዓመታት ተጋድለው የአገር ነፃነትን ያስከበሩበት አኩሪ ድል ፣ኢትዮጵያ ከተቀሩት የአፍሪካ አገራት በተለየ መልኩ የድል ቀንን እንድታከብር አድርጓታል።
ይህ ታሪካዊ ቀን ለ20 ዓመታት እንደ ተራ ቀን የመታየት ዕጣ ፋንታ ገጥሞት ነበር። በ1967 ዓ.ም 34ተኛው የድል በዓል የተከበረው ሚያዝያ 27 ቀን ሳይሆን መጋቢት 28 ቀን ነበር። ይህም የሆነው በደርግ ቀጭን ትዕዛዝ ነው። መጋቢት 28 ቀን 1967 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ቀኑ የተቀየረበትን ምክንያት አስመልክቶ ተከታዩን አስነብቦ ነበር። “ይህ 34ተኛው የድል በዓል ወደ መጋቢት 28 ቀን የተዛወረው፣ እንደቀድሞው የንጉሡን ታሪክ
ለማሞካሸት ሳይሆን፣ የድሉ ባለታሪክ የሆነውን ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በመሆኑ፣ እውነተኛው የታሪክ ቀን ስፍራውን እንዲይዝና ሕዝቡም በራሱ ደም የገነባውን ታሪክ በእጁ መልሶ እንዲጨብጥ ለማድረግ ነው።”
መጋቢት 28 ቀን ጄኔራል ካኒንግሃም አዲስ አበባን ተቆጣጥሮ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በከተማዋ የሰቀለበት ቀን ነው። በእርግጥ በዚሁ ዕለት አጼ ኃይለሥላሴ በደብረማርቆስ ከተማ ንጉሥ ተክለሃይማኖት ዓደባባይ ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማ ሰቅለዋል። ንጉሠነገስቱ አዲስ አበባ ገብተው በታላቁ ቤተ- መንግሥት የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማ የሰቀሉት ሚያዝያ 27 ቀን ነው። በዚህ ምክንያት በዓሉ መጋቢት 28 ቀን እየተከበረ 55ተኛው የድል በዓል እስከተከበረበት እስከ 1988 ዓ.ም ድረስ ለሃያ ዓመታት ከዘለቀ በኋላ ወደ ቀደመ ቀኑ እንዲመለስ ተደርጓል።
ሚያዝያ 26 ቀን 1945 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ይዞት የወጣው መርሐግብር በወቅቱ የበዓሉ አከባበር ምን መልክ እንደነበረው ያስረዳል። ‹‹ልክ ከጠዋቱ 12፡00 የክብርዘበኛና የፖሊስ ማርሽ ቡድኖች ሰልፋቸውን ከአራት ኪሎ እስከ ምስካየ ኅዙናን መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ድረስ ይይዛሉ። ልክ ከጠዋቱ 12፡15 ሲሆን መኳንንቱ ፣ መሳፍንቱ፣ ሚኒስትሮችና ወይዛዝርት በምስካየ ኅዙናን መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ቦታ ቦታቸውን ይይዛሉ። ከጠዋቱ 1፡00 ሲሆንም፣ ጃንሆይ ከኢዮቤልዩ ቤተመንግሥታቸው (ከውጭ ጉዳይ ዝቅ ብሎ ከሚገኘው) ተነስተው ወደ ምስካየኅዙናን መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን በሞተረኛ ታጅበው ይሄዳሉ።
ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት ሲሆን የክብርዘበኛ ፣ የጦር ሠራዊት፣ የፖሊስና የሀገርፍቅር የሙዚቃ ተጫዋቾች በአዲስ አበባ ሬዲዮ ጣቢያ ተገኝተው ልዩ ልዩ ሙዚቃዎችን ያሰማሉ። ከጠዋቱ 2፡45 እስከ 3፡00 ደግሞ ከምስካየኅዙናን መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን እስከ ኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት ድረስ ያለው መንገድ ለትራፊክ ዝግ ሆኖ፣ ንጉሠነገሥቱ በሞተረኛ ታጅበው ከቅዳሴ የሚመለሱበት ሰዓት ይሆናል። ከ 3፡00 እስከ 3፡05 ባሉት አምስት ደቂቃዎች ውስጥ ዕለቱን በማሰብ የአዲስ አበባ አብያተ-ክርስቲያናት ደስታቸውን ያለማቋረጥ ደወላቸውን በመደወል ይገልጻሉ። ከረፋዱ ላይም የውጭ አገር መንግሥታት ወኪሎችና ታላላቅ የአዲስ አበባ ከተማ ኗሪዎች በተዘጋጀላቸው የክብር መዝገብ ላይ ፊርማቸውን ያኖራሉ። ልክ 5፡00 ሲሆንም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ፣ በከተማው ሕዝብ ሥም በድል ሐውልት ላይ የአበባ ጉንጉን ያስቀምጣሉ።››
የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች የድል ቀን መታሰቢያ ትናንት ለ79ኛ ጊዜ ታስቦ ውሏል። የአራት ኪሎ ግርማ ሞገስ የሆነው የድል ሐውልት ሚያዝያ 27 ቀን 1935 ዓ.ም የመሠረት ድንጋዩ ተቀምጦ በዓመቱ ሚያዝያ 27 ቀን 1936 ዓ.ም ተጠናቆ ተመርቋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2012
የትናየት ፈሩ