እንደ መዳረሻ
የጋራ መኖሪያ ቤቶች እንደስማቸው ግብራቸውም ቢሆን መልካም በሆነ ነበር።የጋራ ጥፋት መስሪያዎች እየሆኑ መምጣታቸው የሚደመጥ ሆነ እንጂ።ይሁን እንጂ መኖሪያ ቤት የናፈቀው ስፍር ቁጥር ሌለው ሕዝብ በእጁ እንዲገቡለት ይቋምጥባቸዋል። የቤቶቹ ግንባታ ምስጢር ግን ነገሩ ወዲህ ነው።በሕብረተሰቡ በኩል ለቤት ናፍቆትና ላልጠነከረ የኢኮኖሚ አቅም መፍትሔ በመሆን ፈጥነው ይደርሳሉ።በመንግሥት በኩል ደግሞ ለመጠርነፍ ያመቻሉ ይባላል።
የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለአቅመ መኖሪያነት ሲደርሱ ከፍ ካለው ሕብረት ሥራ ማህበራት ዝቅ እስከሚለው ‹‹ብሎክ›› መሪና ‹‹ፍሎር››መሪ ይደራጃሉ።
ከፍ ያለው ውቅር ሕጋዊ ሰውነት ያለው ሲሆን፤ ዝቅ ያሉት ግን በተለይም ‹‹ፍሎር›› መሪዎች እውቅና አልባዎች እንደሆኑ ይወራል።በተለይም አገራዊ የለውጥ ንፋሱ ከመንፈሱ በፊት የ‹‹ፍሎሩ››ን ነዋሪ አረማመድና ምንጭ ጭምር ይከታተሉ እንደነበር ዛሬ ላይ እንደታሪክ ይወራል።
በለውጥ ሂደቱም ቢሆን ሁሉም ለሕብረተሰቡ እኩል ያስባል ተብሎ አይታሰብም።በየደረጃው የለውጥ ዘዋሪ ማሽኖች ጥቂት መሪዎች እንጂ ሺዎች ሆነው አያውቁም፤ ሚሊዮኖች ግን ተከታዮች ናቸው።ጥቂት የማይባሉት ለውጥን ያግዛሉ፤ አለያም ይገዘግዛሉ።
የጥሩ መሪዎች ጥበብ ከአድማጭ ጀሮዎች ይወለዳል ይላሉ የዘርፉ አጥኚዎች።ይነስም ይብዛ፣ይጥበብም ይስፋ በተዋዕረድ የሚገኙ የሕዝብ አገልጋዮች ለሚያገለግሉት ማህበረሰብ ጆሮ መስጠት አለባቸው።ለሚያስተዳድሩት አለያም ለሚመሩት የሕብረተሰብ ክፍል ከፊት ሆነው እንቅፋቱን እያነሱ፣አቧራውን እየጠረጉ፣ አሜካላውን እየነቀሉ፣የሻከረውን እያለሰለሱ፣እምባ ሚያፈሰውን እያበሱ ወደአገሪቱ መዳረሻ ይዞ መገስገስ የተሰየሙበት ዓላማ እንጂ በችሮታ የሚደረግ ተግባር አይደለም።
እንዳለፉት ጊዜያት ከመሪነት አውሪነት ወይም አደናጋሪነት፣አቤቱታን ከማፍታት ማምታታት ኣይነት ባህሪይን በመላበስ የማህበረሰቡን የቅሬታ ቀዳዳዎች ከመድፈን የኪሳቸውን ቀዳዳዎች የሚያስቀድሙ ብዙዎች ስለመኖራቸው ይነገራል። የቀላል ጉዳዮች መፍትሔ መልሳቸው ከሰማይ የራቀ ያህል ሲቸግር፣በጽሑፍ ለሚጠየቁት ጉዳዮች የአዎንታም ይሁን የአሉታ ምላሽ ሲርቃቸው በአንክሮ ለሚያስተውለው ራሳቸውን የቻሉ ቋንቋዎች ናቸው።ይናገራሉ፤ ያስረዳሉ፤ያብራራሉ፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያዊ ወግና ባህሎች እንደተጠበቁ ሆነው ‹‹ከፍትፍቱ ፊቱ›› እንዲሉ ማህበ ረሰቡ መውደዱንም መጥላቱንም ፣ማቅረቡንም ማራቁንም፣ መከፋቱንም መደሰቱንም፣ ማጥፋቱንም ማልማቱንም ቀርቦ አወያይቶ ከፊቱ ማንበብ የሚችል ብልህ መሪንም፣መካሪንም ይሻል።ፈጣን ምላሽንም ይፈልጋል።
በሥልጣኔ ጎዳና ሕዝብ መራመድ ሲጀምር እና ለዚህ ምቹ ሁኔታዎችን ከፊት ለፊቱ በርቀትም ቢሆን አሻግሮ ሲመለከት እንደ ትናንቱ እጅ አስጨብጦ አለያም አንገት ደፍቶ ጉዳዩን ለማስፈጸም አይከጅልም።ለዚያውም የማህበረሰቡና የሕዝቡ የሆነ ጥያቄን።
መሪዎች ከተመሪዎች ልቀውና መጥቀው ካልተገኙ ለውሳኔ ይቸገራሉ።ወሬ አቀባይ ይመለምላሉ፤ከብዙሃኑ ይልቅ ለግለሰቦች ጆሮ ይሰጣሉ።የጥያቄ ማዘግየትን ከመፍትሔ ይቆጥራሉ፤ቀላል ጥያቄዎች ጭምር ከባድ ቅሬታን አርግዘው እንዲወልዱ ዕድል ይሰጧቸዋል። የልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 መሪዎችም ከዚህ የተለዩ አለመሆናቸውን የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪዎቹ እያነጻጸሩ በምሬት ይናገራሉ፡፡
አቤቱታዎቹን ከማህበሩ አመራሮች አንደበትየአቤቱታው መዳረሻ ልደታ ነው። ልደታ የት? እንደምትሉኝ አልጠራጠርም።ምክንያቱም ሰዎች ስለልደታ ሲሰሙ በአዕምሯቸው ውስጥ ፈጥኖ የሚያቃጭለው ልደታ ፍርድ ቤት ነው አሉ? ልብ በሉ አሉ ነው ነገሩ።እንጂማ ‹‹ትዝታ ትዝ ሲል ትዝ የሚል ትዝ ይላል›› ነው ነገሩ።ከሰው ሰው ትዝታው መለያየቱ ባይቀርም።ወደ ቁምነገሩ ልመልሳችሁ፤ ቅሬታው ከልደታ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አንድ ማህበር የቀረበ ነው።
ቅሬታ አቅራቢው የልደታ ብርሃን ከብሎክ አንድ እስከ 14 የኮንዶሚኒየም የቤት ባለቤቶች ኃላ/የተ/የህ/ሥ/ማህበር ሲሆን፤ የነዋሪዎችን ሰላማዊ ኑሮ የሚያውኩ በርካታ ችግሮች በመጋረጣቸው እነዚህ ችግሮች እልባት እንዲሰጣቸው የማህበሩ አመራሮች ደብዳቤ ያልጻፉለት የመንግሥት ተቋም፣ በእግራቸው ያልረገጡት የኃላፊ ቢሮ አለመኖሩን ይናገራሉ።ዳሩ ምን ዋጋ አለው ለችግራቸው መፍትሔ ይዞ የደረሰላቸው ቀርቶ ለደብዳቤዎቻቸው ጆሮ የሰጣቸው አካል አለመኖሩን በምሬት ይገልጻሉ፡፡
በተለይም ብሎኮቹን እኩል ከፍሎ በሚያልፈው የኮብል ስቶን መንገድ የተነሳ አሳራቸውን እያዩ እንደሆነ ይገልጻሉ።የሚተላለፈው የሰው ቁጥር በርካታ በመሆኑ ከዚህ በፊት በመንገዱ ሰበብ ከሚደርስባቸው ችግሮች በበለጠ ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት መጋለጣቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ልደታ ብርሃን ከብሎክ አንድ እስከ 14 የኮንዶሚኒየም የቤት ባለቤቶች ኃላ/የተ/የህ/ሥ/ማህበር ሰብሳቢ አቶ በለጠ ተሾመ ማህበሩ በሥሩ 14 ብሎኮች፣ 385 ቤቶች እና ከሁለት ሺ በላይ ነዋሪዎችን ያቀፈ ነው።በመሆኑም ነዋሪዎችን ለዘርፈ ብዙ ችግር ያጋለጡ ጉዳዮችን በመለየት ለሚመለከታቸው የወረዳ መስሪያ ቤቶች ቢያቀርቡም ከወረዳው ሥራ አስፈጻሚ ጀምሮ የሚመለከታቸው መስሪያ ቤት ኃላፊዎች የሕብረተሰቡን ችግር ለመፍታት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ለነዋሪዎች ችግር ፈጥረዋል ብላችሁ የለያችኋቸው ጉዳዮች ምን ምን ናቸው? ቅሬታዎቹ የትኞቹን መስሪያ ቤቶች እገዛና ድጋፍ ጠይቃችሁ ነበር? ምን ምላሽስ ተሰጣችሁ? ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ አቶ በለጠ ሲመልሱ፡-
አሁን ለማንኛውም ችግር ምንጭ ሆኖ ያስቸገራቸው በብሎኮቹ መሀል ከፍሎ የሚያልፈውን መንገድ በር እንዲዘጋጅለት በማድረግ ወንጀልን መከላከል አለመቻላቸው እንደሆነ ተናግረዋል።የአጥር፣የበር እና የጋራ መገልገያዎች አለመሟላት(አለመኖር) ፈተና ሆነውብና ይላሉ አቶ በለጠ።በሕብረተሰቡ ተወካዮች በኩል የሚነሱ ቅሬታዎችን መጠየቅና ለወረዳ አስተዳደሩ ማቅረብ ከተጀመረ ቆይቷል።የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ተሠርተው ነዋሪዎች ሲረከቧቸው የጋራ የመጠቀሚያ ቦታዎች የተዘጋጁላቸው አልነበሩም።ከዚያ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ቅሬታዎች ቢኖሩም ማህበረሰቡን በማስተባበር ለችግሮቹ ጊዜያዊ መፍትሔዎች እየተሰጡ፤ በዘላቂነት መፍትሔዎች እንዲያገኙ ጥያቄዎችን በተደጋጋሚ ሲያቀርቡም መቆየታቸውን ተናግረዋል።በሂደትም ከእነዚህ የከፉ ችግሮች እየተፈጠሩ መጥተዋል። ግቢው ዙሪያውን እስኪታጠር ድረስ ነዎሪዎች በፈተና ውስጥ መኖራቸውን የገለጹት አቶ በለጠ፤ ችግሩን በዚያ ብቻ ማቃለልና መቅረፍ አልተቻለም ይላሉ።
ብሎኮቹን ከአንድ እስከ ሠባት እና ከብሎክ ሥምንት እስከ 14 ድረስ እኩል ከፍሎ የሚያልፍ በኮብል ስቶን የተሠራ የውስጥ ለውስጥ መንገድ አለ።በመሆኑም ቀደም ሲል ከባልቻ ልደታ ፣ከአብነት ፍርድ ቤት የሚሠራው የባቡርና የመኪና መንገድ በመኖሩ እና በቁፋሮ ላይ ስለነበር ከከተማው የተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመጣው ማህበረሰብ በብሎኮቹ መሐል ሰንጥቆ በሚያልፈው የኮብልስቶን መንገድ እንደማቋረጫ ሲገለገልበት ኖሯል።አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን፤ መንገዱ ለ24 ሰዓት ለአገልግሎት ክፍት ነው። የጋራ መኖሪያ ሠፈሩ በትላልቅ የድርጅት ሕንፃዎች ዙሪያውን የተከበበ በመሆኑ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በሞተርና በመኪና የተለያዩ የዝርፊያ ወንጀሎች የሚፈጽሙ አካላት ማቋረጫ፣መደበቂያና ማምለጫ አድርገውታል፤ በሰፈር መሐል በመሆኑም ነዋሪ መስለው ወደ ሕንፃዎቹ በመዝለቅ ያመልጣሉ፤ይደበቃሉ።ከዚህ በተጨማሪም በሰፈሮቹ መሐል አቋርጦ የሚሄደው የሰው ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ነዎሪዎቹን ከተላላፊዎቹ፣ ሌባዎቹን ከሠላማዊ ነዋሪውና ተላላፊው ለይቶ መቆጣጠርም ሆነ ለሕግ ለማቅረብ አዳጋች አድርጎታል።
መንገዱ ክፍት የሚያድር በመሆኑ የሰካራም መፈንጫ በመሆን የነዋሪዎች ሰላም ታውኳል።በቀንም ቢሆን በልመና የተሰማሩ በርካታ የኔ ቢጤዎች በመንገዱ ዳርና ዳር የሚቀመጡበት፣በአነስተኛ ሱቅ በደረቴ የተሰማሩ ሕገወጥ ነጋዴዎች የሚራኮቱበት እና በትርምስ ነዋሪው ለስርቆት የተጋለጠበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
በአጥር የተከለለና በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እንቅስቃሰው የታገደ ባለመሆኑ ችግሮቹን ለመቆጣጠር ድርጅቱ (ማህበሩ) የቀጠራቸው የጥበቃ ሠራተኞች ጭምር የተማረሩበትና ሕይወታቸውን ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ ውስጥ የወደቁበት ሁኔታ ተፈጥሯል።ሰፈሩን በሚያቋርጠው ኮብል ስቶን መንገድበምሽትም ሆነ በቀን ያለገደብ ከትላልቅ እስከ ትናንሽ መኪኖች የሚመላለሱበት ፣ ሞተር ሣይክሎች ያለገደብ በፍጥነት የሚሽከረከሩበት በመሆኑ በሌሊት ጊዜ በሥራ ሲለፋ የሚውለው ነዋሪ በሰላም የማይተኛበትና ዕረፍት የማያገኝበት በድምፅ የታወከ ሰፈር እንዲሆን አድርጎታል፡፡
በቀን የሰፈሩ ነዎሪዎች ልጆችና ቤተሰቦች በሰላም ልጆቻቸው ትምህርት ቤት ደርሰው ለመመለስ አስቸጋሪ ከመሆኑም በተጨማሪ ለአደጋ ተጋላጭ ሆነዋል።በጥቅሉ የመንገዱ በዚያ በመኖሪያ ሰፈር መሀል መገኘቱ የሰፈሩ ዋነኛ የችግር ምንጭ ሆኗል።
በመሆኑም ግቢውን የሚያካልለው አጥር በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ነዋሪዎች ርብርብ እያደረጉ ሲሆን፤ በሮች ተሠርተው የሚፈጠረው የጸጥታ ችግር መፍትሔ እንዲያገኝ ለሚመለከተው የልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት አስተዳደር እና ለሚመለከታቸው አካላት በደብዳቤ ለማሳወቅ ቦዝኖም ሰልችቶም አያውቅም።ነገር ግን ምላሽ የሚሰጥና ለማህበረሰቡ ሰላም የሚጨነቅ አካል አልተገኘም እንጂ።
ለኮንዶሚኒየም ነዋሪዎች ብቻ እንዲያገለግል ታስቦ ብሎኮቹን እኩል ከፍሎ የተሠራው የውስጥ ለውስጥ ኮብልስቶን መንገድ ቀደም ሲል ከሞላ ማሩ ልደታና ከአብነት ፍርድ ቤት የሚያስኬዱ መንገዶች በሥራና በቁፋሮ ላይ በነበሩት ጊዜ በማስተንፈሻነት አገልግሏል።አሁን ላይ ግን ሁሉም በሥራ ላይ የነበሩት መንገዶች ተጠናቅቀው በሥራ ላይ በመሆናቸው የጋራመኖሪያ ቤት ነዋሪዎች በችግር ውስጥ መውደቃቸው ከግንዛቤ ውስጥ ገብቶ መተላለፊያው የሚዘጋበት አለያም ለክትትልና ለቁጥጥር አመቺ እንዲሆን በበር የሚዘጋበት ሁኔታዎች እንዲፈጠሩላቸው በተደጋጋሚ ጠይቀዋል።
ለቁጥጥር አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ ነዋሪዎችን ከተላላፊዎች መለየት ባለመቻሉ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ከፍተኛ ወንጀሎች እንዲፈጸሙ ምቹ ሁኔታዎች ፈጥሯል።ከተፈጸሙ በርካታ ወንጀሎች ለማሳያነት ያህል የመኪና አካል ስርቆት የተለመደ ነው፤በአንድ ቀን ከ10 ጊዜ በላይ የመኪና አካል ስርቆቶች ተከናውነዋል።ብሎክ 11 የመስኮት ግሪል ተፈልቅቆ ቴሌቪዥንና ሌሎች ንብረቶች ተሰርቀዋል።በብሎክ ሰባት ቤት ቁጥር 303 በጠራራ ፀሐይ በር ተፈልቅቆ 32 ሺ ብር በጥሬ ገንዘብ ተሰርቋል።በብሎክ ሁለት፣አራት፣አምስት፣አስር የመኪና ግራና ቀኝ መስታወቶች ‹‹ስፖኪዮ›› ና ሌሎች ንብረቶች ተሰርቀዋል።የልብስና የቁሳቁስ ስርቆቶች የእለት ከእለት ተግባሮች ናቸው።ችግሩ ከነዋሪዎችም በላይ የሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ራስ ምታት ከሆነ ቆይቷል።የዚህ ሁሉ ችግሮች መንስኤ በር ተዘጋጅቶ ተገቢውን ቁጥጥር ለማድረግ አመቺ ሁኔታዎች አለመኖራቸው በመሆኑ በጋራ የማህበረሰቡን ሰላም እንጠብቅ፣አካባቢው በወንጀል እየታመሰ እስከ መቼ? በሚል ለወረዳው አካላት ማቅረባቸውን አቶ በለጠ አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል የሚቀርቡ ችግሮችን ለመፍታት የወረዳው አመራሮች የሚንቀሳቀሱበት መንገድ ችግሮች ያሉባቸው እንደሆኑ የተናገሩት አቶ በለጠ፣ የወረዳው አመራሮች ችግሮቹ እንዲፈቱ የማይተባበሩባቸው ሁኔታዎች የተለዩ ጥቅሞች በመፈለግ እንጂ ከባድ ሆነውባቸው እንዳልሆነ ያስረዳሉ። በቀን፣ በቁጥርና በማህተም በተደገፉ ደብዳቤዎች በሕጋዊ መንገድ የሚጠየቁ መፍትሔ የሚፈልጉ ችግሮችን በምንም ተዓምር ምላሽ አይሰጣቸውም፤ በቃል ብቻ እንደዚህ ነው የሚል ተጨባጭነት የሌላቸው ምላሾች ይሰጡናል።እናስተዳድረዋለን ለሚሉት ማህበረሰብ የሰጡትን ግምት ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ነው፡፡
አሁን በቃል የምትሉትን በሕጋዊ ደብዳቤ ስጡን በሚል ሲጠየቁ እሺ ነገ፣ዛሬ በሚል ያታልላሉ እንጂ ሕጋዊና ተቋማዊ ምላሽ ሊሰጡ ፈቃደኞች አይደሉም።አንድ አመራር በሚመለከተው ጉዳይ ይሆናል የሚለውን መልስ በሕጋዊ መንገድ እንዴት መስጠት ያቅተዋል? ሆን ተብሎ ካልሆነ በስተቀር።ስለዚህ ቅንነት የሌለበትና የመልካም አስተዳደር ችግር በሚፈጥር መንገድ የሚሠሩ ናቸው ይላሉ።
ረዥም ጊዜ የወሰደውን የግቢውን የዙሪያ አጥር ለማጠር ጥረት በሚደረግበት ጊዜ በአመራሮቹ በኩል በሕብረተሰብ ተሳትፎ እንዲሠራ በ‹‹ኤ›› የባንክ ሒሳብ ቁጥር ገንዘብ አስገቡ ተብለናል።በአካውንቱ እናስገባለን ነገር ግን ለአሠራር ያመቸን ዘንድ በሕብረተሰብ ተሳትፎ እንዲሠራ ከሚመለከተው አካል ትዕዛዝ የተቀበላችሁበትን ግልባጭ ስጡን የሚል ጥያቄ አነሳን።በዚህ ወቅት ትዕዛዝ የተሰጠን በቃል ስለሆነ ለእናንተም በቃል ነግረናችኋል አስገቡ አሉን።በዚህ መንገድ አንችልም በማለታችን ጥርስ ውስጥ አስገቡን።በዚህ ረገድ ማህበረሰቡን በማስተባበርና በዙሪያው ከሚገኙ ድርጅቶች በተገኘ እገዛ ባይጠቅም ከጭቅጭቅ ሙሉ ለሙሉ የተላቀቀ ባይሆንም የመንግሥትን ወጪ ለማዳን ረዥም ርቀት መሄዳቸውን አንስተዋል፡፡
ከለውጡ ወዲህ በተወሰኑ አመራሮች ዘንድ ቅንነት በተሞላበትና ሕጋዊ አሠራርን ተከትሎ ለመሥራት ጥረቶች ቢኖሩም በፊት በነበሩትና ሕዝብ እያስለቀሱ ኪሳቸውን ለመሙላት በሚያሰሉና በሚሯሯጡ አመራሮች እየተመረዙ መጥተዋል።የዚያ ችግር ውጤት አሁንም በር ተሠርቶ የነዋሪዎችን ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳይቃለሉ ማድረጉን አያይዘው አንስተዋል፡፡
መንግሥት ለማህበረሰቡ እነዚህን መኖሪያዎች ገንብቶ ሲሰጥ የማህበረሰቡን ችግሮች በማቃለል የመልካም አስተዳደር ችግሮችና የማህበራዊ ቀውሶች እንዳይፈጠሩ ነዉ።ነገር ግን ሕዝብና መንግሥት ተናብበውና ተስማምተው እንዳይሄዱ የሚያደርጉ አመራሮች አሁንም አሉ።ሕዝቡ በተለያዩ ችግሮች እንዲወጠርና እንዲሰቃይ በማድረግ በመንግሥት ላይ ማህበረሰቡ ጥርሱን እንዲነክስ ቀን ከሌት እየሠሩ ነው።የዚህ የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪዎች በርካታ ችግሮች አሉባቸው።
ያልተሟሉ ብዙ መሰረተ ልማቶች እንዳሉ ይታወቃል።ለምሳሌ የጋራ መጠቀሚያ ‹‹ኮሚናል›› ማህበረሰቡ በደስታውም ሆነ በኀዘኑ የሚሰባሰብባቸው፣በግ የሚያርድባቸው መገልገያዎች ባለመኖራቸው ሕብር በሆነው ወግና ባህሉ ላይ ቀላል የማይባል ተጽዕኖ አሳድሮበታል።ይሁን እንጂ እነዚህን ችግሮች ብቻ የተሸከመ ባለመሆኑ ማህበረሰቡ እንዲረጋጋ በማድረግ በማህበረሰቡ ጥረት የሚሟሉት እንዲሟሉና በመንግሥት በኩል መደረግ ያለባቸው እንዲሠሩ በጽሑፍ ብናመለክትም ማን ጆሮ ይስጠን! ሕዝብን የሚያዳምጡ አመራሮች የሉም፤በግልጽ ተነጋግረን በሐቅ ላይ ለመሥራት ተቸግረናል።በሌሎች አካባቢዎች እንደሞዴል ለመሆን የበቁት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግቢያቸውን አጥረው የነዋሪዎቻቸውን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቃቸው ነው፤ለዚህ የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ነው።የመኖሪያ የውስጥ ለውስጥ ጽዳቶችና ውበቶችን በማስጠበቅ በአትክልቶች ግቢያቸውን በማስዋባቸው ነው።ስለዚህ ይህን ለማድረግ ማህበረሰባቸውን ይዘው በመመካከርና በማሳመን በቁርጠኝነት መነሳታቸው ነውርነት እንደሌለው ያስረዳሉ፡፡
የነዋሪዎቹ ተወካዮች ከሕዝባቸው ይሁንታና ፈቃድ እንዲሁም እውቅና ውጪ አንዳች ነገር ለመሥራት ወይም ገንዘብ ወደ ሆነ አካል አካውንት ለማስገባት ባለመፍቀዳቸው በችግር ውስጥ እንድንወድቅ አድርገናል ባይ ናቸው።የሕዝቡን ሰላም የሚያስጠብቁ እና አገራዊ በሆኑ ተግባሮች ላይ ሕዝባቸውን አስተባብረው መሳተፍ እንዳይችሉ በወረዳው አመራር በኩል መታገዙ ቀርቶ በቅንነት እየታዩ እንዳልሆነ ተናረዋል።በመሆኑም ሥራዎችን እንድንሠራ እያገዙን ሳይሆን በችግር ውስጥ ሕዝቡ እንዲወድቅ፣እንዲማረር፣በትንሽ በትልቁ ከሕጋዊ አሠራሩ ውጪ በአሳቻ ሰዓትና በምሽት አመራሮች ጭምር እየመጡ እንደሚረብሿቸው እና ሕጸጽ በመፈለግ መጠመዳቸውን ገልጸዋል።
ኮንዶሚኒየሙ ለነዋሪዎች ከተሰጠበት ጊዜ እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ ወና ሆኖ የቆየ ነው።ለቁጥር የሚያታክቱ ደብዳቤዎች ችግሮች ተጠቅሰው ለወረዳው አስተዳደር ተጽፏል።ወና ሆኖ መኖሩን የሚፈልጉት አካላት አሉ።ጥያቄዎች በማህበሩ ሕጋዊ ማህተም ሲቀርቡ ኖረዋል፤ ለመመለስ ፈቃደኛ አይደሉም።
ከብዙ ዓመታት ጥረት በኋላ የግቢውን አጥር ለማጠር የግንባታ ፈቃድ፣የቴራዞ ንጣፍ፣የመኪና ማቆሚያ፣ጊዜያዊ የግንባታ እቃ ማስቀመጫ እንዲገነባ ፈቃድ መገኘቱን ያስረዳሉ፡፡
ከብሎክ አንድ እስከ 14 የልደታ ብርሃን የኮንዶሚኒየም የቤት ባለቤቶች ኃ/የተ/የህ/ሥ/ማህበር ለወረዳው አስተዳደር በተለያዩ ጊዜያት በሕጋዊ ደብዳቤ ሲጠይቃቸው ከኖሩት በርካታ ጥያቄዎች በጽሑፍ የተገኘ ምላሽ አንድ ብቻ ነው።ይዘቱንም በሚከተለው መልክ እንዳለ ሳይሻሻል ለማስቀመጥ ተሞክሯል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2012
ሙሐመድ ሁሴን