ይህ ጽሁፍ ባለፉት አመታት ከቅድመ እና ከድህረ የዶ/ር አቢይ የለውጥ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከአጠቃላይ የለውጥ ሽግግር ንድፈ ሃሳብ አንጻር የቀረበ እንጂ አንድ የምርምር ጽሁፍ ሊከተል የሚገባውን የምርምር ስነ ዘዴ (Methodology) እንዲሁም መረጃውን ለመተንተን በሚያስችል ንድፈሃሳብና ስነ እውቀት (Epistomology) ያልተደገፈ በመሆኑ ብዙ ህጸጾች ቢኖሩበትም የግል ምልከታዬ እንደ ሆነ አንባቢያን ከወዲሁ እንዲረዱልኝ ማስገንዘብ እወዳለሁ። እንዲሁም ጹሁፉ የማንኛውንም የፖለቲካ ድርጅትም ይሁን የምመራውን ተቋም አይወክልም።
መጋቢት 10/2010 ዶ/ር አቢይ የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የሀገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የመጨረሻው የስልጣን ጫፍ (The axis of the power) ከወጡ በኋላ ባለፉት 27 አመታት የተጓዝንበትን መንገድ በመቀየር የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ራሳቸው አብዮተኛ ሳይሆኑ ሪፎርሜሽኒስት እንደሆኑና በመደመር የፖለቲካ አስተሳሰብ ወይም ፍልስፍና (Political thought) ነገ የተሻለች ኢትዮጵያን መፍጠር ይቻላል የሚል መላ ምት (Hypothesis) ይዘው በቆዩበት ሁለት አመታት በዘለቀ ጊዜ ውስጥ ሊነኩና ሊተገበሩ ይችላሉ ብለን የማናስባቸውን በርካታ ኩነቶች ሲፈጸሙ፣ በአንጻሩ በእኛ እድሜ አይተን የማናውቀው የህዝብ መፈናቀል እና በመንጋ ፍርድ ዜጎች በማንነታቸው እና በሀይማኖታቸው ምክንያት ብቻ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለውና ተሰቅለዋል።
የዚህ ጹሁፍ ጭብጥ ይህንን እውነታ መዘርዘር አይደለም፤ ከዚህ አለፍ ብሎ መንግስት ወይም አንድ የግሌ ወይም የመንግስት ተቋም ማንኛውንም አይነት ለውጥ ለመተግበር ሲነሳ የለውጡን ምንነት በለውጡ ሽግግር ወቅት ምን ምቹ ሁኔታ እና ፈታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥም ይችላሉ፤ ከለውጡ የሚጠበቅ ውጤትና የለውጡ ሂደት ተጠናቆ ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ (Satus quo) የሚመለስበትን ጊዜ በግልጽ አስቀምጦ፣ በየእለቱ እየተጓዘ ለውጡ ያለበትን ሁኔታ እየገመገሙ ከሁኔታዎች ጋር የሚጣጣሙ አቅጣጫዎችን እያስቀመጡ ለውጡን መምራትን ይጠይቃል። ስለዚህ ከዚህ አንጻር ላለፉት የለውጥ አመታት የነበሩ ጎዶሎዎችንና ስኬቶችን በግልብ (At a glance) እና ከለውጥ የሽግግር ኡደቶች አንጻር ለማመላከት ነው።
ለውጡ ሪፎርም፣ አብዮት ወይስ ነውጥ
አሁን ባለንበት ሁኔታ በእርግጥም ሪፎረም ወይስ አብዮት ወይስ ነውጥ ነው የሚሉትን ጉዳዮች መዳሰስ ተገቢ ነው። የሪፎርም ባህሪ አለው ስንል የአብዮት ባህሪያቶችን እንመለከታለን። አብዮት ነው እንዳንል ቅልጥ ያለ አብዮት አይደለም። እነዚህን ጉዳዮች መረዳት ይቻል ዘንድ በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ምንድናቸው የሚለውን ጉዳይ መመልከት ተገቢ ነው።
አብዮት የሚለው ቃል የተወሰደው ከስነ ፈለግ (Astronomy) ሲሆን ትርጉሙም ሙሻዙር (Turning Around) ማለት ነው። የፖለቲካ ትርጉሙን መነሻ ያደረገው ከጣሊያን ህዳሴ (Renaissace Italy Revoluziones) ከሚለው ነው። አንድን ስርዓት በሌላ ስርዓት መተካት የሚል ሃሳብ ይይዛል። በአለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ሀገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ ልዩ ልዩ አብዮቶች ተካሂደዋል። ለምሳሌ የአሜሪካን አብዮት እ.አ.አ (1776)፣ የፈረንሳይ (1789) የሜክሲኮ (1910) የራሺያ (1917) የቻይና (1949) የኢራን (1979) የኢትዮጵያ (1974) የሚጠቀሱ አብዮቶች ናቸው።
በፖለቲካ ንድፈ ሃሳብ ረገድ በራዲካሊስት አስተሳሰብ አብዮት ማለት መሠረታዊ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ለውጥ በአጠቃላይ ፖለቲካዊ ስርአቱን በአዲስ የፖለቲካ ስርዓት መተካትን (radical change) የያዘ ፅንሰ ሀሳብ ነው። ከዚህ አንፃር የ1966ቱ (በፈረንጆች 1974) የአጼ ኃይለ ስላሴ ስርዓት ወድቆ በደርግ ስርዓት ሲተካ የፖለቲካ ስርዓቱ ከፊውዲሊዝም ወደ ሶሻሊዝም የመንግስት ስርዓት የተሸጋገረበት ከንጉሳዊያን ወደ ተወሰኑ ቡድኖች ወይም ወደ ኦልጋርኪ (from monarchical to Olgarchial) የተደረጉትን
ለውጦች እንደ አብነት ማንሳት ይቻላል።
በአጠቃላይ አብዮት የሚለው ቃል ከሶሻሊስት ርዕዮት ከነውጥና ከኢኮኖሚ አለመረጋጋት ጋር ይያ ያዛል፡፡ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ አብዮት ሶስት በህሪያቶች ያሉት ሲሆን፣ እነሱም የነበረውን ስርዓት ማፍረስና በአዲስ መተካት የስልጣን ትግል (power struggle) አዳዲስ ተቋማትን ማቋቋምን ያጠቃለለ ጽንሰ ሃሳብ ነው። በዚህ ንድፈ ሃሳብ ማእቀፍ ውስጥ የ1966ቱን የኢትዮጵያን የመንግሰት ለውጥ በምናይበት ሰአት ሁሉም እንደሚገነዘበው ስርአቱ ከፊውዳሊዝም በቀጥታ ወደ ሶሻሊዝም የተሸጋገረበትና ስርአቱ የተወገደው በአመጽ መሆኑ እንዲሁም በደርግ አባላት መካከል የነበረው የስልጣን ትግል (Power sruggle) የጀነራል አማን አንዶምና የጀነራል ተፈሪ ባንቲ መገደል ከዚያም በኋላ የነበሩት የስልጣን ሽኩቻዎችን በምናይበት ሰአት በእርግጥም አብዮት ስለመሆኑ ማረጋገጥ እንችላለን።
ሁለተኛው ፅንጸ ሀሳብ ሪፎርም ሲሆን ትርጉሙም በፅንሰ ሀሳብ ደረጃ የነበረው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ መሰረቱን ሳይለቅ የሚታዩ ችግሮችን (mal-practices) የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ ማለት ነው። ቃሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ስራ ላይ የዋለው በ18ኛ ክ/ዘመን ክሪስቶፈር ዋይቪሌ (Wyuill) የነበረውን ፓርላማ ለማሻሻል (parliamentary reform) የተጠቀመበት ሀሳብ እንደሆነ ይገለጻል። በይዘት ደረጃ መሠረታዊ
ለውጥ ማምጣትን ሳይሆን ያሉትን ችግሮች ማከም ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ከፖለቲካው አስተሳሰብ አንጻር ሲታይ አለም በሁለት ካምፕ በተከፈለችበት ወቅት የሶሻሊዝምን ርዕዮተ አለም የሚከተሉ ሀገሮች በሶሻሊዝም ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው ሪቪዥኒስት እና ሪፎርሚስት በማለት ራሳቸውን ከፍለው በሁለቱም መንገድ ከካፒታሊዝም ወደ ሶሻሊዝም እንደርሳለን ወይም በካፒታሊዝም ስርአት ማህበር ውስጥ የሰራተኛውን መደብ ወደ ማህበራዊ ደህንነት ወይም ስርአቱን ወደ ሁሉን አቀፍ ብልጽግና (Social welfare) መለስተኛ ለውጥ ወይም ሪፎረም በማድረግ የነበረውን ማህበራዊና አኮኖሚያዊ መሰረቶችን ሳይቀይር (Within bourgeoisie democracy) የሚካሄድ ለውጥ ወይም ሪፎርም ነው ብለው የያዙት የፖለቲካ አስተሳሰብ ነው።
በአለም አቀፍ ደረጃ በርካታ በምሳሌነት የሚጠቀሱ ሪፎርሞች ተከናውነዋል። ለአብነት በ1500 በአውሮፓ የተከናወነውን የፕሮቴስታንት ሪፎረምን መጥቀስ ይቻላል። ይህ ሪፎረም ቤተ ክርስቲያንና መንግስት ግንኙነታቸው የተቋረጠበት ወይም ሴኪውላሪዝም (የሀይማኖት ነፃነት) የታወጀበት ነው። በቅርብ በቻይና (ከ1976-1978) እና በቀድሞ ሶቭየት ህብረት (ከ1983- 1985) የተከናወኑት ኩነቶች በኢኮኖሚው ረገድ የሚጠቀሱ የሪፎረም ምሳሌዎች ናቸው።
በሀገራችንም በተለያዩ መንግስታትና ጊዜያቶች የሪፎረም ስራዎች በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚውና በማህበራዊ መስኩ የተደረጉ ቢሆንም በውጤታማነት ደረጃ የተመዘገበ የለም። ሆኖም ግን በፖለቲካው ረገድ ከተደረጉ ሪፎርሞች ለምሳሌ አጼ ሀይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት የህዝቡን የፍትሀዊነትና የዴሞክራሲ ጥያቄ ለመመለስ በማሰብ የ1931ዓ.ም ህገ መንግስት፣ በ1955ቱ የህገ መንግስት ማሻሻያዎችን እንደ ሪፎርም ልንወስድ እንችላለን። ሆኖም ግን የተደረገው ማሻሻያ ወይም ሪፎርም ሁሉንም ህዝብ በእኩልነት ያሳተፈና የተረጋጋ መንግስት መመሰረት አላስቻላቸውም። በተመሳሳይ የደርግ ስርአትም በ1990 እንደ ፈረንጆች ከዕዝ ኢኮኖሚ ወደ ቅይጥ ኢኮኖሚ ያደረገው ለውጥ የኢኮኖሚ ሪፎርም ቢሆንም ስርአቱን ከመውደቅ አላዳነውም። በተመሳሳይ በዘመነ ኢህአዴግም ጥልቅ፣ የጥልቅ ጥልቅ ተሀድሶ እየተባለ በተለያዪ ጊዚያቶች የተደረጉ ሪፎርሞች ቢኖሩም ባለፉት 27 አመታት ጠብ ያለ ዴሞክራሲያዊ ስርአት መገንባት አላስቻለም።
ከሪፎረምና ከአብዮት ጽንሰ ሃሳቦች ጋር መታየት ያለበት ጽንሰ ሃሳብ ነውጥ (ወይም በእንግሊዘኛው Rebellion) ሲሆን ጥሬ ትርጉሙም አንድን መንግስት ለመጣል አመፅን እንደ አንድ የትግል አማራጭ ማየትን ሲሆን፤ አንድ ሰርዓትን በግልጽ መቃወምና የመንግስትን ህግ እምቢ በማለት በግለሰብም ይሁን በጋራ የሚካሄድ አመፅ ነው።
አንድም ለውጥ ለማምጣት አልያም ለውጡን በመቃወም የሚካሄድ ነውጦች ናቸው። የኢትዮጵያ አብዛኛውን የታሪክ ክፍል የሚሸፍነው የአመጽ ታሪክ ነው። ምንም እንኳን ደካሞች የጋራ ታሪክ የለንም ቢሉም በዚህ ረገድ የጎጃም፣ የጌዴኦ እና የትግራይ አርሶ አደሮች አመጽ፤ የ1966ቱ የተማሪዎች፣ የታክሲ ሾፌሮች እና የልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አመጽ እንዲሁም በኢህአዴግ ዘመነ መንግስትም ባልተደራጀ መልኩም ቢሆን በ1985 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ፣ ከ1997 ምርጫ በኋላ በአዲስ አበባና በዋና ዋና የሀገሪቱ ከተሞች፤ የባለፉት ሶስትና አራት አመታት የነበሩትን የኢትዮጵያን ሁኔታዎች በምናይበት ሰአት በመላ ሀገሪቱ በሚባልበት ደረጃ ህብረተሰቡ ውስጥ የለውጥ ፍላጎት ስለነበረው በመንግስት ላይ መልካቸውን የቀያየሩ የህዝብ አመጾች ወይም ነውጦች ተካሂደዋል።
ከለውጡ በኋላ ለውጡን በመቃወምም ይሁን የተለየ ፍላጎት በነበራቸው የህብረሰብ ክፍሎች ነውጦች ተከስተዋል። በእኔ እምነት አሁን ያለው ለውጥ ከሪፎርም ከፍ ያለ ከአብዮት አነስ ያለ በጥቅሉ የሪፎርምና የአብዮት ባህሪያቶችን የያዘ የለውጥ አይነት ነው ማለት ይቻላል። ምክንያቱም በኢህአዴግ በራሱ ውስጥ የስልጣን ትግል (power struggle) በመኖሩ የ27 አመታት የህወሀት የሀይል (power) የበላይነት አሁን ወደ ተፈጠረው የለውጥ ሀይል (Reformer or a select set of actors) ተሸጋግሯል። በበርካታ ቦታዎች አሁን ያለውን ለውጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ በመቃወም መንግስት ወደ እልህ ውስጥ (Aggresive) የሚያስገቡ፣
በመንግስት እውቅና በተሰጣቸው ቡድኖች ኢሰብአዊ ድርጊቶች ተፈጽመዋል። ስለዚህ ለውጡ ሪፎርም ብቻ ነው ብሎ መደምደም አይቻልም። ወጣም ወረደም ተወደደ ተጠላም በለውጥ ሂደት ወይም ሽግግር ውስጥ መሆናችን ጥርጥር የለውም። ስለዚህ ያሉ ስኬቶችንና ተግዳሮቶችን እንዲሁም የቀጣይ አቅጣጫዎችን ከሽግግር ንድፈ ሃሳብ አንጻር ከዚህ እንደ ሚከተለው ቀርቧል።
የለውጥ የሽግግር ኡደቶች
የዶ/ር አብይን ለውጥ እንደ አንድ የመተንተኛ አውድ (unit of analysis) ስንወስደው ከለውጡ በፊት የነበሩ ሁኔታዎች (Old state) የለውጡ ሽግግር (Transition) አዲስ የለውጥ ሁኔታዎች (New State) ይኖሩታል። ከዚህ አንጻር ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት የነበሩ ሁኔታዎችን ወይም ለለውጡ ገፊ ምክንያቶችን ለመለየት የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከታህሳስ 4-20/2010 የጥልቅ ተሃድሶና የሀገራችን የህልውና ስጋት በሚል ርእስ በወቅቱ የለያቸው ችግሮች ውሃ የሚቋጥሩ በመሆናቸው ለለውጡ ገፊ ምክንያቶች ነበሩ ማለት ይቻላል። ስለዚህ በወቅቱ ለሀገሪቷ ህልውና ስጋት ተብለው የተቀመጡት፦
- የውስጠ ድርጅት የዴሞክራሲ ችግር
- ሙስናና ብልሹ አሰራር
- የፌደራል ስርአታችንና ዴሞክራሲያዊ አንድ ነታችን ተግባራዊ አተረጓጓም ላይ ያለ ጉድለት (የመተግበር ችግር..በእኔ የተጨመረ)
- ለድርጅት የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆን (የድርጅትና የመንግስት ሚና የተደበላለቀ ነበር….በእኔ የተጨመረ)
- የህግ የበላይነትና የህግ ልእልና አለማስከበር
- የህዝቡን አንገብጋቢ የልማትና የመልካም አስተ ዳደር ጥያቄዎች አለመፍታት ወዘተ… የሚሉ ሁኔታዎች ነበሩ ብሎ የገመገመ ሲሆን፤ እነዚህ ሁኔታዎች ሲጨመቁ መንግስቱ አምባገነናዊ ወይም ዴሞክራት አልነበረም ብሎ መደምደም ይቻላል። ስለዚህ የለውጡ መሪዎች ሚና የለውጡ አላማና እነዚህን ችግሮች መፍታት እና መለወጥ ይሆናል።
የለውጡ ግብ በረጅም ጊዜ በህዝቦች ይሁንታ የተገነባች ፌዴራሊዊ ዴሞክራሲያዊ ሀገር መገንባት፤ በአጭር ጊዜ የህግ የበላይነት የተረጋገጠባት ፍትሀዊ ነጻ እና ምልአተ ህዝቡ የተሳተፈበት ምርጫ በማካሄድ የለውጡን የአጭር ጊዜ አላማ ማሳካት ሊሆን ይገባል። ስለዚህ የሀገራችንን የለውጥ ሁኔታ ከሽግግር ንድፈ ሀሳብ አንጻር ሲታይ፦
የሽግግር ሂደት (Transition State)
ከላይ እንደተመለከተው የዶ/ር አቢይን ዘመን (The era of Abiy) እንደ የሽግግር ወቅት ከወሰድን ይህን የሽግግር ወቅት ከሽግግር ንድፈ ሃሳብ (Transitional theory) አንጻር ማየት አስፈሊጊ ነው። በንድፈ ሃሳብ አንድ ስኬታማ ሽግግር ሶስት መሰረታዊ ኡደቶችን አስተሳስሮ መፈጸም ግድ ይላል። እነሱም የተዘጉ በርና መስኮቶችን መክፈት (Liberalization) ዴሞክራሲያዊነትና (democratization) ዴሞክራሲያዊ አንድነትን መፍጠር (democratic Consolidation) ናቸው።
በመጀመሪያ ተዘግተው የነበሩ በሮችን ነጻ ማድረግ ወይም ሊበራሊይዝ ሲባል መጀመሪያ ውሳኔ ላይ መድረስ ያለበት ፖለቲካዊ ሊበራሊይዜሽን ወይስ ኢኮኖሚያዊ ሊብራይዜሽን ወይንም ሁለቱንም ነው ብሎ ውሳኔ ላይ መድረስ ይኖርበታል። የፖለቲካ ሊበራላይዜሽን ሲባል የፖለቲካ ምህዳሩን ለሲቪክ ማህበረሰቡና ለፖለቲከኞች ማስፋት ሲሆን፤ የመናገርና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ማክበር የመሰብሰብና የመደራጀት ነጻነትን ተግባራዊ ማድረግና ማህበራዊ መሰረቱን የማስፋት ስራ መስራትን ያጠቃልላል።
በኢትዮጵያም ሁኔታ ባለፈው አንድ አመት ተኩል በፖለቲካዊ አመለካከታቸው ምክንያት ታስረው የነበሩ የፖለቲካ እስረኞችን፣ መልቀቅ በውጭ ሀገር በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሀገር እንዲገቡ ማድረግ፤ የመገናኛ ብዙሀንና ጋዜጠኞች አንጻራዊ በሆነ መልኩ ነጻ መሆናቸው ወዘተ… እንደ አብነት የተከናወኑትን እውነታዎችን (Realities) ማንሳት ይቻላል።
በአንጻሩ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ተዘግተው የነበሩ በሮችና መስኮቶች ሲከፈቱ ዶ/ር አቢይ እንዳሉት
የሚወጣው ትንፋግ ነው። ለትንፋጉ ዋና ዋና ምክንያት የሚሆኑት ለውጥ በሚፈልገው አካልና በለውጡ ተቃዋሚዎች በሚኖረው ትግል (Struggle between hardliners and liberalizers within authoritarian regime), ውጫዊ ግፊት (External Reform Pressure) የኢኮኖሚ ቀውስ (Economic Crisis), የህዝብ ተቃውሞ (Mass Protest) ሲሆኑ፤ በተግባር እንደታየውም ለውጡን በሚመራው በራሱ በፖለቲካ ስርአቱ ውስጥ ባሉ ቡድኖችም መካከል በሚኖር የስልጣን ሽኩቻ፤ (factional struggles within the core elite between proponents and opponents of reforms) አንድም በለውጡ ውጤት የተሳሳተ ግምት በመስጠት ወይም ስልጣኔን አጣለሁ በሚል አሰተሳሰብ (Mistaken assumption or Miscalculation) የሚከሰት ሁኔታ ይኖራል።
ለምሳሌ የአዴፓ ከፍተኛ አመራሮችን ህይወት የቀጠፈውን ክስተት እና ህወሀት በለውጡ ላይ ያለው የተዘበራረቀ ሁኔታ (Paradox) ከዚህ በተጨማሪም የፖለቲካው ምህዳር ነጻ በመደረጉ የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም ወደ ስልጣን በአቋራጭ ለመምጣት ባለ ፍላጎት (Multiple cross cutting cleavages) የራስን ብሄር (Ethnic groups) ሀይማኖትን ወይም ቋንቋን የልዩነት መፍጠሪያ በማድረግ የሚከሰቱ ፖለቲካዊ ቀውሶች የለውጡን ሂደት ውስብስብ ከማድረጋቸውም በላይ ለበርካታ ማህበራዊ ቀውሶች ምክንያት ሆነዋል።
ለምሳሌ በለውጥ ሽግግሩ ውስጥ የህግ የበላይነት የላላበትና ቀላል የማይባል እንዲያውም በተፈጥሮ አደጋ ወይም በጦርነት ምክንያት ከሚፈናቀል የህዝብ ብዛት ያልተናነሰ በርካታ ህዝብ የተፈናቀለበት፤ የሰላም ጉዳይም በጥያቄ ምልክት ውስጥ የወደቀበትን ሁኔታ ነበር። የአማራውን እና የኦሮሞ ህዝቦችን ለማጋጨት 24 ሰአት የተሰራውን አሁንም እየተሰራ ያለው ስራ ፤ለብዙ ሺህ አመታት አብሮና ተከባብሮ በኖሩ የክርስትናና እስልምና ሀይማኖቶች መካከል ግጭት ለመፍጠር የተደረጉ ሙከራዎች፤ መንግስት እውቅና ከሰጣቸው ቡድኖች አንዳንዶቹ አቢይን የሚደግፉ፣ ካልፈለጉ አቢይን መቀየር እንደሚችሉ በማሰብ የፈጠሩት ትርምስ ከዛም በላይ በእነርሱ ምክንያት የተፈጠሩ ኢሰብኣዊ ድርጊቶችን እንደ ጀብዱ የመቁጠር ዝንባሌዎች ወዘተ… የተከሰቱ ችግሮች ጥቂቶቹ ናቸው።
ይህ ሁኔታ መከሰቱ በለውጥ ወቅት የሚጠበቅ ቢሆንም የለውጡ መሪ ይህ ሁኔታ ቀድሞ ሊከሰት እንደሚችል ገምግሞ እንዴት ማቆም እንደሚችል የቤት ስራውን ማከናወን ይጠበቅበት ነበር። በርግጥ ባለፉት 27 አመታት የነበረው የተቋማት ግንባታ በራሱ ትልቁ የለውጡ የተግዳሮት ምንጭ ሊሆን እንደሚችል ቢገመትም ነገሩ አልጋ በአልጋ እንደማይሆን ይታመናል።
ለባለፉት 27 አመታት ለሀገር ግንባታ (Nation Building) የተከተልነው መንገድ (Approch)፣ ኢትዮጵያዊነትን የገደለና ጎሰኛና ጎጠኛ ማህበረሰብ የተፈጠረበት ሁኔታ መኖሩ፣ የሀይማኖት አክራሪነትና ጽንፈኝነት ኢትዮጵያን ለባለፉት አስርት አመታት መዳረሻቸው ማድረግ ብዙ የሰሩበት መሆኑ፣ አልሸባብም ይሁን አይሲስ ኢትዮጵያን በግራ አይናቸው እንደሚያዩዋት ለለውጥ ሀይሉ የተደበቁ ተግዳሮቶች አልነበሩም።
እነዚህ ችግሮች ለውጡን ወደፊት ለማራመድ እንቅፋት እንደሚሆኑ ታውቆ እነዚህን መከላከል የሚያስችል ስትራቴጂ መነደፍ ነበረበት። ይህም ብቻ አልነበረም የለውጡ መሪዎች በለውጡ መጀመሪያ የነበሩ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች የሚያድሱ ለምሳሌ በኦሮሞና
በአማራ (ኦሮማራ)፣ በአማራና በትግራይ፣ በትግራይና በኦሮሞ፣ በሲዲማና በወላይታ ወዘተ… ቀጣይነት አልነበራቸውም። ይህም ብቻ አይደለም የአዴፓና የኦዴፓ አንዳንድ አመራሮች ለለውጡ ቁርጠኛ ሆነው አዲስ ታሪክ ለመስራት 24 ሰአት ከመልፋት ይልቅ ለውጡን ወደ ኋላ የሚያንሸራትት ታሪካዊ ስህተት ሲፈጽሙም ተስተውሏል።
የፖለቲካውን ምህዳር እናስፋ ወይም ሊብራሊይዝ እናድርግ ሲባል መሰረታዊ እውነታዎች ታሳቢ ማድረግም ያስፈልጋል። ለምሳሌ አንድ አይነት ቋንቋ በመናገር አንድ ሀገርን አይፈጥርም፣ የተለያዩ ቋንቋዎች መኖራቸውም አንድ ሀገር ከመሆንም አያግዳቸውም። ይህ መርህ ቢሰራማ ትግራይና ኤርትራ ትግርኛ፤ ካናዳና ሰሜን አሜሪካ እንግሊዝኛ ላቲን አሜሪካና ስፔይን ስፓኒሽ በመናገራቸው አንድ ሀገር በሆኑ ነበር። በአንጻሩ ህንድ ከ179 እስከ 188 ቋንቋ መናገራቸው 179 ወይም 188 ሀገር አላደረጋቸውም። ስለዚህ የቋንቋ የሀይማኖትና የባህል ብዝሀነት አንድ ለመሆን ወይም ለመለያየት ምክንያት አይሆንም። ስለዚህ ኢትዮጵያ የተለያዩ ቋንቋዎች ባህሎች እና እምነቶች መኖራቸው አንድ ሀገር መሆኗን ተቀብለን ሁሉን በእኩል የሚያስተናግድ ዴሞክራሲያዊ ስርአት በመመስረት ሀገር መገንባት ይኖርብናል።
ይህንን ማድረግ ካልቻልን ግን በሽግግር ውስጥ እና የነጻነትን የመጀመሪያውን ሂደት (First Phase) እንደሚለማመድ የህብረተሰብ ክፍል እንደ መሆናችን መጠን በመደመር እሳቤ ቋጠሮውን ካላላነው አቶ ለማ እንዳሉት” ነጻነትን መሸከም የሚያቅተን ሁኔታ ይፈጠራል” ኦሾ እንደሚለው “ነጻነት ማለት እሺ ወይም እንቢ (Yes or No) ማለትን በምንፈለግበት ሰአት ማለት መቻል ነው፤ የሰው ልጆች እንደ እንስሳት ሁሉ ከተፈጥሮ እኩል ነጻነት ተሰጥቶናል ሆኖም ግን እንስሳቶች ነጻነታቸውን በአግባቡ ስለሚጠቀሙበት በነጻነት ሲኖሩ የሰው ልጆች ግን አሁንም ድረስ ነጻነታቸውን በአግባቡ ስለማይጠቀሙበት መንግስት ፍርድ ቤቶች ፖሊስ ወታደር ህግ አስፈልጓቸዋል ይላል፡፡
በእርግጥም ባለፉት ሁለት አመታት የታዩ ሁኔታዎች የሚያመላክቱን በተሠጠን ነጻነት ልክ ሃላፊነት ከመውሰድ ይልቅ የደቦ ፍርድ (Mob Justice) የታየበት ነው። ልናጣቸው የማይገቡ ውድ መሪዎቻችንን
ያጣንበት፤ መርህን ባልተከተለ ሁኔታ የመንግስትን ውሳኔ በዱላና በገጀራ ለማስቀየር የመፈለግ ዝንባሌን የተስተዋለበት፤ የፖለቲካ አክቲቪስት ፖሊሲ አውጪ፣ ፖሊስ ተንታኝ፣ ስልጣን ሰጪ፣ ስልጣን ነሺ ወዘተ… የሆንበትን ክስተት አይተናል። ይህ ደግሞ ኦሾ እንዳለው “ነጻነትን በመለማመድ ረገድ እንስሶች ይሻላሉ” የሚለውን ሃሳብ (Proposition) አቅም እንዲያገኝ እድል ይሰጠዋል።
ሁለተኛው የሽግግር ሂደት (Phase) ዴሞክራታይዜሽን ሲሆን፤ ዋንኛ ባህሪያቶቹም የህዝቡንና የፖለቲካ ተዋናያኖቹን ተሳትፎ የሚገድቡ ህግና የፖለቲካ ተቋማትን የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ ነው። በኢትዮጵያም ሁኔታ የምርጫ ቦርድ፣ የፕሬስ፣ የበጎ አድራጎትና ሲቪክ ማህበረሰብ ህጎች ማሻሻያ መደረጋቸውና የፍትህና የዳሞክራሲ ተቋማት ነጻና ገለልተኛ ሆነው ሊሰሩ የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠርን ያካትታል። በዚህ ረገድ በመንግስት በኩል የተደረገውን ጥረት የዚሁ አካል አድርጎ መውሰድ ይቻላል። ሆኖም ግን ህግን ማሻሻል በራሱ ዴሞክራሲያዊ ስርአትን አይገነባም። ይልቁንም ህጉን የሚመጥን ፖለቲከኛና ህብረሰተብ ያስፈልጋል። ስለዚህ ዴሞክራሲያዊ ስርአት መገንባት ብዙ ኪሎ ሜትሮችን መንገድ እንደ መስራት አይቀልም፤ ዛሬን ሳይሆን ነገን አሻግሮ ስልጣንን ሳይሆን የህዝብን ጥቅም፤ 24 ሰአት መተኛትን ሳይሆን 24 ሰአት መስራትን፤ በማህበራዊ የትስስር ሚዲያ እንደምንለቀው ዘለፋን ሳይሆን በምክንያት የሚያሳምንና የሚያምን ትውልድ ይጠይቃል።
ሶስተኛው የሽግግር ሂደት ለዴሞክራሲ በአንድነት መተባበርን (Consolidated Democracy) ነው። ሁሉም በፖለቲካው ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ ያላቸው አካላት (politically significant actors) የህግ የበላይነት የመገዛትና ከለውጡ በፊት የነበሩ ሁኔታዎች ተመልሰው እንዳይመጡ ወይም በእኛ አባባል ለውጡ እንዳይቀለበስ በጋራና በትብብር መንፈስን የመስራት ሁኔታን ያጠቃልላል። ከዚህ አንጻር አመርቂ ስራዎች ተሰርተዋል ባይባልም በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በትብብር ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸው እንደ አንድ ማሳያ የሚታይ ነው። እንዲሁም ቀደም ባለው ወቅት አጋር በመባል የሚታወቁ ድርጅቶች በብልጽግና
ፓርቲ አባል የመሆናቸው እውነታ ሌላው ማሳያ ነው። የብልጽግና ፓርቲ ከየትኛውም ተፎካካሪ ፓርቲ ጋር በጋራ ለመስራት ያሳየው ፈቃደኝነትም በዚህ መልኩ ሊታይ የሚችል ነው።
የተፎካካሪ ፓርቲዎች በሃሳብ ዙሪያ መፎካከርና (Contestation) የፖለቲካ ርእዮትን ወይም በሚታገሉለት ማህበራዊ መሰረቶች ዙሪያ በመሰባሰብ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ የድርሻቸውን ሊያበረክቱ ይገባል። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተዋናዮችን ስንመለከት ከአንድ መቶ ሰባት በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸው ባያስገርምም አሁን በርእዮተ አለምና በሚታገሉለት ማህበራዊ መሰረት ዙሪያ ለመሰባሰብ እያደረጉ ያሉት ጥረት ይበል የሚያሰኝ ነው።
በግዙፍ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ሴክተር የማዛወር ፍላጎትና ተግባር በየትኛውም መመዘኛ ከአብዮታዊ ዳሞክራሲ ይልቅ ለሊበራል የፖለቲካ ርእዮተ አለም ይወግናል። ስለዚህ በእኔ ምልከታ የፖለቲካ ማሻሻያው (political Reforms) እንደ ኢህአዴግ ከርእዮተ አለም ለውጥ እስከ ተቋማት ግንባታ ከመንግስት አወቃቀር እሰከ ሀገር ግንባታ (State or Nation building) የትኩረት መስኮች ሊሆኑ ይገባል። ምክንያቱም ከላይ እንደገለጽኩት አብዮታዊ ዴሞክራሲም ይሁን ልማታዊ መንግስት የፖለቲካ ርእዮተ አለም ሊሆኑ አይችሉም። ባለፉት 27 አመታት በተግባርም የታየው በስም አብዮታዊ ዴሞክራሲ ቢሆንም የሶሻል ዴሞክራሲ ባህሪያቶቹ ጎልተው የታዩ ነበር።
አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታም የአብዮታዊ ዴሞክራሲም ይሁን የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ርዕዮተ አለምና የፖለቲካ አስተሳሰብ (political tought) አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ይበልጥ ወጣቱን የህብረተሰብ ክፍል በሰፊ አንቀሳቅሶ (Mobilize) የሚያታግል አስተሳሰብ አይደለም። ምክንያቱም አብዮታዊ ዲሞክራሲ እንደ ርዕዮተ ዓለም በዓለም ደረጃ ያሰባሰበው የህብረተሰብ ክፍል ካለመኖሩም ባሻገር ባለፉት 27 ዓመታት አብዮታዊ ዴሞክራሲን እንደ ርዕዮት አለም አድርገን ብንወስድ እንኳን የተመራበት የኢኮኖሚ መርህ ጋር እርስ በርሱ የሚቃረን ነበር።
ለምሳሌ በአንድ ወቅት አቶ መለስ ዜናዊ የምንከተለው ስርዓት ነጭ ካፒታሊዝም ነው ብለዋል። ይህ ማለት ደግሞ ነጭ ካፒታሊዝም ማለት ነጭ የነፃ የገበያ ስርዓትና በጣም ጥቂት የመንግስት በኢኮኖሚው ላይ ጣልቃ መግባትን የሚፈቅድ ነው
የለውጥ ሀይሉ በአሁን ወቅት እያዜመው ያለው የመደመር ፖለቲካዊ አስተሳሰብ በምድራዊውም ይሁን በላይኛው አለም የተቀደሰ ሃሳብ ነው። ሰዎች ወደ መሀል ያሰባስባል፤ ያቀራርባል። አስተሳሰቡ ከሰዎች ተፈጥሮአዊ የሰው ልጆችን ተደማሪ ፍላጎቶችና አቅማቸውን እንደ መነሻ ይወስዳል። የሰው ልጅ በተፈጥሮው የሚያውቀውን ብቻ የሚፈልግ ሳይሆን የማያውቀውንም ይመኛል። ይህን ምኞትና ፍላጎት ለማርካት የአንዱ ፍላጎት ከሌላው ሰው ፍላጎት ጋር መደመር ከተቻለ የሰው ልጆችን ፍላጎት ማርካት ይቻላል ብሎ ይነሳል።
የትኛውን የሰው ልጆች ፍላጎት ነው የሚለው ግልጽ ነው። አሁን ስላለነው የኢትዮጵያ ህዝቦች ፍላጎታቸውን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ አቅርቦት ያስፈልጋል። የመደመር ፍልስፍና መሰረታቸው ሰላም፤ ይቅርታና ፍቅር ነው። ዶ/ር አቢይ ሲያንቆለጳጵሳቸውም ‹‹ሰይፍ›› ይሏቸዋል። እነዚህ ጉዳዮች ለአንድ ግለሰብ ወይም ማህበረሰብ ብሎም ሀይማኖት የማእዘን ድንጋዮች ናቸው። ሆኖም ግን በተፈጥሮ ወይም በማህበራዊ ሳይንስ መስኩ ሁልጊዜ
ሁለት ተጻራሪ ነገሮች እንዳሉ መዘንጋት የለበትም፡፡
ለምሳሌ አምላክ እንዳለ ሁሉ ሰይጣንም አለ፤ መሬት እንዳለ ሁሉ ሰማይም አለ፤ ወዳጅ የመኖሩን ያህል ጠላት አለ፤ ነፍስ እንዳለ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ አለ፤ በአጠቃላይ ለሰናይ ተግባራት እኩይ ምግባሮች አሉ። ስለዚህ በመደመር ፍልስፍና ዘይትና ውሃ እንደማይደባለቁ ሁሉ ሁለት ሊደመሩ የማይችሉ ነገሮችም ብንደምራቸው የሚፈጥሩት ውጤት አዎንታዊ (Positive) ምንም (Neutral) ወይም አሉታዊ (Negative) ሊሆኑ እንደሚችሉ ጥርጥር የለውም። ስለዚህ መደመርን ራሱ መቀነስ ይቃረነዋል። ለዚህም ነው ዶ/ር አቢይ በተለያዩ መድረኮች ዋልታ ረገጥ መኖራቸውን ሳይናገሩ የማያልፉት።
ዶ/ር አቢይ የሀይማኖት መሪ ሳይሆኑ የፖለቲካ መሪ እንደ መሆናቸው መጠን መደመር ነገ ለምርጫ ሲወዳደሩ እንደ ፖለቲካ አስተሳሰብም ይሁን ርእዮተ አለም በአባሎቻቸውም ይሁን በመራጩ ህብረተሰብ መስረጽ ይኖርበታል።
በአጠቃላይ ስለ ሪፎርም በምናወራበት ሰአት ማጠንጠኛችን ፖለቲካውና ኢኮኖሚው ሊሆኑ ይገባል። በዚህ ረገድ ስኬታማ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሪፎርም ካደረጉ ሀገሮች መካከል ቻይናና ራሺያ ተጠቃሽ ናቸው። የእነዚህን ሀገራት ተሞክሮ አይቶ እንደ ሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ ተገቢ ነው። ለምሳሌ በቻይና ከ1976-1978 እንዲሁም በቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት ከ1983-1985 ሪፎርሞች የተካሄዱ ሲሆን፤ ቻይና በኢኮኖሚው መስክ ስኬታማ ስትሆን የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት ጠንካራ መንግስት መመስረት አስችሏታል።
ቻይና ወደ ሪፎርም ከመግባቷ በፊት የኢኮኖሚ መሠረቷ ግብርና ሲሆን፤ የከተማነት ምጣኔዋም በ1979 እ.አ.አ. 18 ፐርሰንት ሲሆን፤ ሶቭየት ህብረት ግን የኢኮኖሚ መሠረቷ እንደስትሪ የነበረና የከተማ ምጣኔዋም 65.7% ነበር፡፡ ከብሄረሰብ ስብጥርም ሲታይ ቻይና በጣም ተመሳሳይ (higher ethnic homogniety) 87 % የ 43 ጎሳ አባላት ሲሆኑ፤ በUSSR ሁኔታ ግን 50% በላይ ከራሺያ ውጭ የሆኑ ጎሳዎች /ብሄሮች ነበሩ/ ቻይና ሪፎርም ማድረግ የጀመረችው ኢኮኖሚውን በማሳደግ ሲሆን፤ ሶቭየት ህብረት ግን ፖለቲካውን ነበር (Liberalized) ቅድሚያ የሰጠችው፡፡ ስለዚህ በእኛ ሁኔታ የትኛው መቅደም አለበት የሚለውን ጉዳይ ወይንም ሁለቱንም ነጻ (Liberalized) በማድረግ ሪፎርም ማካሄድ ይኖርብናል የሚለውን ጉዳይ ፖለቲከኞቻችን ሊያጤኑት ይገባል።
ቻይናዎች ከፖለቲካው ይልቅ ኢኮኖሚው ላይ ትኩረት ሲያደርጉ ምክንያ ታቸው የዴሞክራሲ ባህል ደካማ በሆነበት ሀገር እና እጅግ ብዙ የህዝብ ቁጥር እና የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ባሉበት ሁኔታ እንደ አውሮፓውያን ባለ ሁለት ም/ቤት እና ብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊኖሩ የሚችሉበትን ሁኔታ ከመፍጠር ይልቅ እንደ ማዕከላዊ መንግስት በአንድ ፓርቲ የሚመራ የፖለቲካ ስርአት በመገንባት ነገር ግን ኢኮኖሚውን ነጻ ማድረግ አለብን የሚል አቋም በመያዝ አሁን ታላቋን ቻይና መገንባት ችለዋል። ስለዚህ የቻይና ተሞክሮ የሚያሳየን ዴሞክራሲው ማደግ ያለበት በኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ ነው (Democratization is now essentially directed at the economic domain)። እኛም አስር ያባረረ አንድ አይዝም እንዳይሆን ማሰብ ይኖርብናል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2012 እንዳለ ሀይሌ (ፒ.ኤች. ዲ በፐብሊክ
ማኔጅመንትና ፖሊሲ)