አንድን ከተማ ከተማ ነው ሊያስብለው የሚችል የራሱ መስፈርት አለው:: መስፈርቱ ከአገር አገር ሊለያይ ይችላል:: አገሮች እንደ የሁኔታውና እንደህጋቸው መሰረት ከተማ ነው አይደለም የሚለውን ያስቀምጣሉ:: በዚህ መልኩ የሚሰጠው ውሳኔ የሚገለጸው በአገራቱ ማዕከላዊ ስታቲስቲክ ባለስልጣን አማካይነት ነው::
ሰዎች በከተማ መኖርን አብዝተው ይሻሉ:: ለዚህ ደግሞ ዋና ምክንያታቸው ኑሯቸውን ቀላል ሊያድርግ ላቸው የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች በመኖራቸው ሲሆን፣ የስራ አጥነት ችግር እንደማይገጥማቸውም ስለሚያስቡ ነው:: በኢትዮጵያም የሚስተዋለው ይኸው ሲሆን፣ ከዚህም የተነሳ ጥቂት የማይባሉ ዜጎች የገጠሩን ኑሮ እርግፍ አድርገው ወደከተማ መፍለስን ይመርጣሉ:: እንዲያም ሆኖ ግን በኢትዮጵያ በከተማ የሚኖረው የህዝብ ቁጥር በጣም አነስተኛ ነው:: የዓለም አቀፍ ተሞክሮ እንደሚያሳየው በርካታ ህዝብ ኑሮውን ያደረገው በከተማ እንደሆነ ነው:: በሂደትም ሰዎች ኑሯቸውን በከተማ እንዲያደርጉ ይመከራል::
በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝና በቀጣይ ሰዎች ኑሯቸውን በከተማ እንዲያደርጉ ምን መደረግ አለበት የሚለውን ጥያቄ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ አርክቴክቸር ህንጻ ግንባታና ከተማ ልማት ኢንስቲትዩት የከተማ ልማት ኃላፊ ለሆኑት ለረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ብርሃኑ ወልደትንሳኤ ባነሳንላቸው ጊዜ እንዳስረዱት፤ ከተሜነት ሂደት ነው:: በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታይ ከፍተኛ ህዝብ የሚኖረው በከተማ ነው:: ይህን ሂደት ተከትለው ደግሞ እነ አሜሪካንም ሆኑ ሌሎች የአውሮፓውያውን አገሮች በከፍተኛ ደረጃ ከተሜነት ደረጃ ላይ ደርሰዋል:: በገጠሩ ያለው ህዝባቸው ቁጥር ከ10 በመቶ በታች ወርዷል:: እንዲህም ሲባል አብዛኛው የየአገሮቹ ነዋሪዎች በከተማ መኖር ከጀመሩ በርካታ ዓመታን አስቆጥረዋል::
ይህ ቁጥር ግን ወደ አፍሪካ ሲመጣ የሚገኘው ዝቅተኛ ሆኖ ነው:: አፍሪካ ዝቅተኛው የከተማ ነዋሪ ያለው ክፍለ አህጉር ናት:: ከዚህ ውስጥ ደግሞ ሰብ ሰሃራ የሚባሉ አገሮች በከተማ የሚኖረው ህዝባቸው ቁጥር የበለጠ በጣም አነስተኛ ነው:: በኢትዮጵያም በከተማ የሚኖረው ህዝብ ቁጥር በጣም አነስተኛ ሲሆን፤ ከፍተኛ የከተማ ነዋሪ አለ የሚባለው በአዲስ አበባ ከተማ ነው::
‹‹በእርግጥ›› ይላሉ ዶክተር ብርሃኑ፣ በአንድ ከተማ አስፈላጊ የሆኑ በርካታ መሰረተ ልማትና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት መኖር አለባቸው:: እ.ኤ.አ በ1950 በዓለም አቀፍ ደረጃ ከዛሬ 70 ዓመት በፊት 70 በመቶ
የሚሆነው የዓለም ህዝብ ይኖር የነበረው በገጠር ነው:: 30 በመቶ ያህሉ ደግሞ ይኖር የነበረው በከተማ ነው:: ሂደቱ እየተፋጠነ በ2010 አካባቢ በዓለም የሚኖረው ህዝብ በከተማና በገጠር ተመጣጣኝ ነበር:: ከዚህ በኋላ ግን በከተማ የሚኖረው የዓለም ህዝብ ቁጥር እያገደ መምጣቱን ነው የሚገልጹት::
‹‹እናም በ2050 ከ30 ዓመት በኋላ በዓለም 68 በመቶ የዓለም ህዝብ በከተማ ይኖራል ተብሎ ይገመታል›› የሚሉት ዶክተሩ፣ ‹‹በ2018 የሚያሳየው ወቅታዊ መረጃ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ በከተማ የሚኖረው ህዝብ 55 በመቶ ነበር:: ይሁንና ይህንን መረጃ ወደተለያዩ ክፍለ አህጉራት ስንበትነው ደግሞ ከዚህ አንጻር ከፍተኛ ደረጃ የደረሱት ላቲን አሜሪካ፣ ካሪቢያንና አሜሪካ ነበሩ:: እነዚህ በ2018 ከጠቅላላ ህዝባቸው 80 በመቶ የሚኖረው በከተማ ነው:: እናም በዚህ አካሄዳቸው በከተማ የሚኖረው ህዝባቸው ቁጥር በ2050 ወደ 90 በመቶ ይደርሳል:: ስለዚህ በእነዚህ አህጉራት በገጠር የሚኖረው ከ20 በመቶ ያነሰው ህዝባቸው ነው›› ይላሉ::
ወደ አውሮፓ ሲመጣ በከተማ የሚኖረው ህዝብ በ2018 ዓ.ም 75 በመቶ ነበር:: በ2050 ወደ 85 በመቶ ይደርሳል ተብሎ ይገመታል:: ኦሽኒያ የሚባሉ እንደ አውስትራሊያ አካባቢ ያሉ አገራት ደግሞ በ2018 ወደ 70 በመቶ ያህል ሲሆኑ፣ በቀጣይም የሚገመተው የኸውም ቁጥር ነው::
ዶክተር ብርሃኑ እንደሚያስረዱት ከሆነ፤ አሁን ትልቅ ለውጥ ያለው አፍሪካና ኢስያ ላይ ነው:: አፍሪካ በ2018 አብዛኛው ህዝብ የሚኖረው በገጠር ነው::
በከተማ የሚኖረው 40 በመቶ ያህሉ ህዝብ ብቻ ነበር:: ይህ ቁጥር በ2050 ላይ 59 በመቶ ይደርሳል ተብሎ ይገመታል:: ወደ ኢሲያ ሲመጣ ደግሞ በ2018 50 በመቶ ነበር፤ ይህ ወደ 2050 ደግሞ በከተማ ሊኖር የሚችለው የህዝብ መጠን ከፍተኛ እድገት አሳይቶ ወደ 66 ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል:: አህጉሩ ካለው የህዝብ ቁጥር አኳያ ሲታይ በጣም ብዙ ነው::
በአጠቃላይ አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ ኦሺኒያ ከፍተኛ የሆነ የከተማ እድገት ስላላቸው ወደፊት የሚጠበቀው የከተማ እድገት በአፍሪካና በኢሲያ ይሆናል ማለት ነው:: ትልቁ ነገር ይህ ነው:: አፍሪካና ኢሲያ በቀጣዮች ዓመታት እድገት ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል::
ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ዶክተር ብርሃኑ የተለያዩ ዓመታት ስታቲስቲክስን መሰረት ያደረገ መረጃን ጠቅሰው እንደተናገሩት፤ በ1950 በኢትዮጵያ በከተማ የሚኖረው ህዝብ 6 ነጥብ 1 ሚሊዮን ህዝብ ነበር:: ይህ ማለት የሚያሳየው 13 በመቶ ያህሉ ብቻ እንደሆነ ነው:: በ2018 የቅርብ ጊዜ መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ በከተማ የሚኖረው 22 ነጥብ 3 ሚሊዮን አካባቢ ህዝብ ነው:: ይህ ማለት 21 በመቶ ያህል ህዝብ ማለት ነው:: ስለዚህም 79 በመቶ ያህል የኢትዮጵያ ህዝብ ኑሮውን ያደረገው በገጠር ነው::
በ2030 ደግሞ ከ10 ዓመት በኋላ የከተማው ህዝብ ብዛት 37 ነጥብ 5 ሚሊዮን ይደርሳል:: ይህ ማለት ኢትዮጵያ ካላት የህዝብ ብዛት 27 በመቶ ብቻ በከተማ የሚኖር ይሆናል:: አሁንም 73 በመቶው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚኖረው በገጠር ነው ማለት ነው:: በ2050 ላይ የከተማው ነዋሪው ቁጥር 74 ነጥብ 5 ሚሊዮን ይደርሳል:: እንዲያም ቢሆን አሁንም በከተማ የሚኖረው ህዝብ 39 በመቶ ብቻ ነው ማለት ነው:: ይህ ማለት እንግዲህ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ በከተማ ሊኖር የሚችለው ከ2050 በኋላ ነው እንደማለት ነው:: እስከዛ ድረስ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚኖረው በገጠር ይሆናል::
ስለዚህ ልክ ሌላው ዓለም እንደሆነው ሁሉ የኢትዮጵያም ህዝብ የከተማ ነዋሪው ቁጥር ከፍ እንዲል መደረግ ካለበት መካከል የገጠር ነዋሪ ፈልሶ ወደ ከተማ እንዲመጣ ማድረግ ላይ ሳይሆን የከተማም ነዋሪ ይወልዳል፤ ይዋለዳልና እድገቱ እያሻቀበ ይሄዳል:: ስለዚህ አንዱ አማራጭ የገጠር አካባቢን ወደ ከተማ መቀየር እንደሆነ ነው ዶክተር ብርሃኑ የሚናገሩት::
እርሳቸው እንደሚያስረዱት፤ 74 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህዝብ ከ20 ዓመት በኋላ ከተማ ውስጥ ይኖራል ማለት ምን ያህል ጫና እንደሚፈጥር ማሰብ ይቻላል:: ኢኮኖሚው መሸከም መቻል አለበት:: ከገጠር ፈልሶ
የመጣውንና በከተማው ውስጥ የተዋለደውን ህዝብ ኢኮኖሚው መሸከም መቻል አለበት:: የስራ እድሉም ይህንን ህዝብ ማስተናገድ መቻል አለበት:: ለከተማ የሚያስፈልገው መሰረተ ልማቱም መዘጋጀት አለበት:: ይህም ሲባል ትምህርት ቤቱ፣ ውሃው፣ ጤና ተቋማ ትራንስፖርቱ፣ ማህበራዊ አገልግሎቱና መሰል ነገሮች ሁሉ ዝግጁ መሆን አለባቸው::
‹‹አለበለዚያ ገጠር ያለው ዝም ብሎ ከተማ ቢፈልስ ስራ የሌለው ቁጥር ከፍ ይላል:: ስለዚህ የምንመጣው ወደ ድህነት ነው:: ይህ እንዳይሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋል:: ከተሜነትን በተመለከተ የሰለጠኑ አገሮችን ስንመለከት የቀደመው ኢንዱስትራላይዜሽኑ ነው:: ከዛም ኢንዱስትራላይዜሽኑን ተከትሎ ከፍተኛ የሰራተኛ ሃይል ፍላጎት ነበር:: ይህን የሰራተኛ ኃይል ኢንዱስትሪው ስቦታል::›› ይላሉ::
አክለውም፤ ‹‹ነገር ግን የአፍሪካ አገሮች የከተሞች እድገት እንዲህ አይደለም:: ኢንዱስትራላይዜሽን እየቀደመ አይደለም:: ስለዚህ ኢኮኖሚው ከሳበ ጥሩ ነው:: ከገጠር ወደከተማ ሲፈልስ በከተማ ያለው የህዝብ ቁጥር ይበልጥ እየጨመረ ይመጣል:: ተወደደም ተጠላ ከተሜነት ደግሞ የሚቀር ነገር አይደለም:: ስለዚህ የከተማው ኢኮኖሚ ወደ ከተማ የሚፈልሰውን ህዝብ መያዝ ከቻለ ወደፊት የሚታየው ጥሩ ነገር ነው ማለት ይቻላል›› ሲሉ ያመለክታሉ::
ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ የአገሪቱ ከተሞች ሲታዩ፤ አዲስ አበባም ሲታይ በጣም ከፍ ያለ ስራ አጥ የሚበዛበት ሆኖ ይስተዋላል:: ድህነቱም ደግሞ የዚያን ያህል ነው:: የተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችም አሉ:: ስለዚህ በከተማ የመኖሩ ነገር የማይቀር እስከሆነ ድረስ እንዴት ተደርጎ መስራት አለበት በሚለው ላይ ትኩረት መስጠትና መንቀሳቀስ እንደሚገባ ይጠቁማሉ:: ከወዲሁ ለዛ መዘጋጀትም የግድ እንደሆነ ነው የሚናገሩት:: ‹‹እያታችንም ሩቅ መሆን አለበት:: እንዴት መጓዝ እንዳለብን የሚያሳይ የ20 እና 30 ዓመት እቅድ መንደፍ ይገባል›› ይላሉ::
በአደጉ አገሮች ቀድሞ የመጣ እድገቱ ነው፤ ስለዚህ የሰው ሃይል ፍላጎቱ ሲመጣ በቀደመው እድገት መስተናገድ ይችላል:: በከተማ የነበረው ያደገ ኢኮኖሚ ከገጠር ፈልሶ የመጣውን ሁሉ ጥቅልል አድርጎ መውሰድ ይችላል:: ከዚህ ውስጥ አንዱ ኢንዱስትሪው ሲሆን፣ የአገልግሎት ዘርፉ ሌላው ነው:: ለዚህ ደግሞ ኢንቨስትመንትን መሳብ መቻል አለብን:: ለኢንቨስትመንቱ ማነቆ የሆነ ነገሮችን ማቃለል የግድ ይላል:: የግሉን ዘርፍ ማበረታታትና ምቹ ሁኔታንም መፍጠር መዘንጋ የማይገባው ዋና ጉዳይ እንደሆነም ይገልጻሉ::
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 27/2012
አስቴር ኤልያስ