‹‹ያለ አገር ክብርና ነጻነት አለመኖሩን ተረድተው የጠላት መሳሪያ ከመሆን መከራና ስደትን መርጠው አምስት ዓመት ሙሉ ተስፋ ባለመቁረጥ ሲንገላቱና ሲንከራተቱ ለኖሩ ስድተኞች የቆመ መታሰቢያ›› ሲል በነጻነት ሐውልት በአንደኛው አምድ ላይ ተፅፏል:: በሌላኛው አምድ ላይ ደግሞ ‹‹ከጠላት ጋር ተስማምቶ ከመኖር ሞትን መርጦ በጦር ሜዳ ላይ የሚገባውን ሰርቶና ደሙን አፍስሶ፤ አምስት ዓመት ሙሉ ሲታገልና ሲሟገት በስደት ላይ ኖሮ እንደገና ከእግዚአብሄር ጋራ በድል አድራጊነት ጠላትን አባርሮ ሰንደቅ ዓላማችንን ለመለሰልን ለቀዳማዊ ኃይለስላሴ የዘላለም መታሰቢያ›› ይላል::
‹‹አምስት ዓመት ሙሉ በጠላት የጭቆና ቀንበር ውስጥ ተቀምጠው የሞት ጥላ በራሳቸው ላይ እያንዣበበ ሐሳባቸውን ከአርበኞችና ከስደተኞች ሳይለዩ አገራቸውን በስውር ላገለገሉ የውስጥ አርበኞች የቆመ መታሰቢያ›› ሲልም እንዲሁ በሌላኛው አምድ ላይ ተጽፎ የሚነበብ ሲሆን፣ ‹‹ለአገራውቸው ነጻነት አምስት ዓመት ሙሉ በዱር በገደል እየተንከራተቱ ደማቸውን ላፈሰሱና አጽማቸውን ለከሰከሱ ለስመ ጥሩ አርበኞች የቆመ የዘላለም መታሰቢያ›› ሲል ደግሞ በአራተኛው አምድ ላይ ሰፍሮ የሚነበብ ዘመን ተሻጋሪ ጽሁፍ ይስተዋላል::
ከእነዚህ ዘመን ተሻጋሪ ጽሁፎች ከፍ ብሎ ወጥ በሆነውና የሐውልቱ ዋና አምድ ዙሪያ ደግሞ የተጻፈው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ገብተው በቤተ
መንግስታቸው የተናገሩት ዲስኩር ሲሆን፣ የጽሁፉ ዋና ርዕስም ‹‹የአገሬ የኢትዮጵያ ህዝብ፤ በተለይም የታመናችሁ አርበኞች›› የሚል ነው::
ይህ በአራት ኪሎ አደባባይ በኩራት የቆመው የነፃነት ሐውልት የተሰራው ጣልያን ኢትዮጵያን ለአምስት ዓመታት ይዟት በነበረ ወቅት ህይወታቸውን ለገበሩ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ነው:: በየዓመቱ ሚያዝያ 27 የሚከበረው በዓል ዘንድሮ ለ79ኛ ጊዜ ሲሆን፣ ይህም በዓል ‹‹የአርበኞች የድል በዓል›› በሚል የሚታወቅ ነው::
ዛሬ በአራት ኪሎ አደባባይ በዓለም አቀፍ በተከሰተው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት መሰባሰብ ባይኖርም፤ እንደወትሮው ለበዓሉ ድምቀት ይሆን ዘንድ በዓሉን ሊዘክሩ የሚችሉ የተለያዩ ዝግጅቶችና ጀግኖችን የሚያወድሱ የጎዳና ላይ ትርዒቶች ባይዘጋጁም፤ ታላቅ መስዋዕት መክፈላቸውን ሁሌም የሚያሳይ፤ የፋሽስቶችን የወራሪነት እና የቅኝ ገዢነት፤ የቂምና የበቀል እርምጃ ያፈረሰ፣ የኢትዮጵያውያንን ጽናት፣ አይበገሬነትና አንድነት ዳግም ያረጋገጠ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ክስተት የሆነውን ታሪክ የሚያስታውስ ዘመን ተሻጋሪው የነጻነት ሐውልት ግን ዛሬም በቦታው ነው:: ጽሁፉን ከተለያዩ መረጃዎችና ከራሱ ከነጻነት ሐውልቱ አሰባስበን የተጠናቀረ ነው::
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 27/2012
አስቴር ኤልያስ