የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን እያስገነባቸው ከሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ ነው:: በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድና በከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የቅርብ ክትትል እየተደረገለትም ይገኛል:: ፕሮጀክቱ የመንግስትን ትኩረት አግኝቶ እየተሰራ በመሆኑና በተለይ ለእንጦጦ ፓርክ መዳረሻ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል:: የሽሮ ሜዳ -ቁስቋም የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት::
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬከተር አቶ ጥኡማይ ወልደገብርኤል እንደሚገልፁት፤ በ2011 ዓ.ም ባለስልጣኑ በይፋ ካስጀመራቸው በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ የሆነው የሽሮ ሜዳ -ቁስቋም የመንገድ ግንባታ ስራው በየካቲት ወር 2011 ዓ.ም ተጀምሯል:: 1 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር ርዝማኔና 20 ሜትር የጎን ስፋትም ይሸፍናል::
ፕሮጀክቱን ዮቴክ የተሰኘው የሀገር ውስጥ ኮንትራክተር እያከናወነው የሚገኝ ሲሆን፣ 160 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞለታል:: የማማከሩን ስራ ደግሞ ቤስት የተሰኘ አማካሪ ድርጅት እያከናወነ ይገኛል:: ፕሮጀክቱ በሁለት አቅጣጫ ከሽሮ ሜዳ እንጦጦ እና ከሽሮ ሜዳ እንጦጦ ሀመረኖህ ኪዳነምህረት ገዳም እየተከናወነ ነው:: በተለይ ከሽሮ ሜዳ እንጦጦ የሚወስደው የመንገድ ፕሮጀክት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አነሳሽነት ተጀምሮ ወደ መጠናቀቁ የተቃረበውን የእንጦጦ ፓርክ የሚያገናኝ በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው::
በተጠናቀቀው ዲዛይን መሰረት 600 ሜትር በመጨመሩ የመንገድ ፕሮጀክቱ 2 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ይኖረዋል:: በዚህም መነሻነት 200 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦለታል:: 1 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የሚሆነው የመንገዱ ክፍልም በዮቴክ እየተሰራ ሲሆን፣ ቀሪው 600 ሜትሩ ደግሞ በባለስልጣኑ እየተከናወነ ይገኛል::
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ የመንገድ ፕሮጀክቱ ከሌሎች ፕሮጀክቶች የተለየ ገፅታ ያለው ነው:: ኮንትራክተሩ ስራውን ሲረከብ በሁለት አመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ በማሰብ ነበር:: ይሁንና ከላይኛው የእንጦጦ ፓርክ ጋር ተያያዥነት ያለው
በመሆኑና በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይም የቅርብ ክትትል እየተደረገበት ያለ በመሆኑ በጊዜ ሰርቶ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገበት ይገኛል:: ባለስልጣኑም ከሌሎች የመንገድ ፕሮጀክቶች በተለየ ልዩ ትኩረት አድርጎበት እየሰራ ነው:: በመሆኑም በሶስት ፈረቃ ቀንና ማታ እያከናወነ ይገኛል:: ሌላ ቦታ ያለውን የሰውና የቁሳቁስ ሃብት በሙሉ በዚህ ፕሮጀክት ላይ በማፍሰስ የጥራት ችግር ሳያጋጥም በፍጥነት እየተሰራ ነው::
በኮንትራት ስምምነቱ መሰረት ፕሮጀክቱ በቀጣይ ዓመት መጋቢት ወር 2013 ዓ.ም የሚጠናቀቅ ቢሆንም፤ አብዛኛዎቹ ስራዎች በዚህ ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይታሰባል:: ከ 1 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትሩ ውስጥም የመንገዱ የግራ ክፍል ሙሉ
በሙሉ ተጠናቋል:: ባለስልጣኑ እየሰራው ያለው 600 ሜትሩም አስፓልት የማልበስ ስራ ተጀምሯል:: በመሆኑም ፕሮጀክቱ በዚህ አመት ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል::
ለዚህ ፕሮጀክት መቃናትም በተለይ በሽሮ ሜዳ አካባቢ የሚገኙ የንግድ ቤቶች በቶሎ መነሳትና የወሰን ማስከበር ስራዎች በቶሎ መከናወን ትልቁን ድርሻ የወሰዱ ሲሆን፣ የከተማ አስተዳደሩም በዚህ በኩል የራሱን ጥረት አድርጓል:: እስካሁንም በስራው ሂደት ምንም አይነት እንቅፋት ያጋጠመ ባለመሆኑ የመንገድ ፕሮጀክቱን እስከ ሰኔ 30 2012 ዓ.ም ድረስ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ይገኛል::
እስካሁን ባለው ሂደትም 600 ሜትሩ የመንገድ ክፍል የቀኝ ክፍሉ አስፓልት የለበሰ ሲሆን፣ የ1 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትሩ መንገድ ደግሞ 180 ሜትር የአስፓልት ማንጠፍ ስራ ተከናውኗል:: ከዚህ ውስጥ የመንገዱ አንደኛው ጎን ሙሉ በሙሉ አስፓልት ለብሷል:: በተቃራኒው ያለው የመንገዱ ክፍል ደግሞ የቁፋሮና የአፈር ስራዎች እየተጠናቀቁ ይገኛሉ:: በተለይ የመንገዱ አንደኛው ክፍል በሚጠናቀቅበት ጊዜ ለትራፊክ ክፍት በማድረግ ቀሪውን የመንገድ ክፍል ሰርቶ ማጠናቀቅ ይቻላል:: ይህም በቀሪ ሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ የሚጠናቀቅ ይሆናል:: የክረምት ወቅት ከመግባቱ በፊትም የአስፓልት ስራውን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል:: ጥቃቅን የሆኑ ስራዎችና የመንገድ መልክ የማስያዝ እንዲሁም የእግረኛ መንገድ ስራዎች በቀጣይ የሚከናወኑ ይሆናል:: በአጠቃላይም የመንገዱ አፈፃፀም 30 ከመቶ ደርሷል::
በኮንትራት ስምምነቱ መሰረት ግንባታው በቀጣዩ አመት መጋቢት ወር 2013 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ የተያዘው የሽሮ ሜዳ- ቁስቋም የመንገድ ፕሮጀክት ዋና ዋናዎቹ ስራዎች በቶሎ የሚከናወኑ ከሆነ ከተያዘለት የጊዜ ገደብ በፊት የሚጠናቀቅበት እድል ሰፊ መሆኑን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን እየገለፀ የሚገኝ ሲሆን፣ ለዚህም የክረምት ወር ከመግባቱ በፊት መንገዱን ሰርቶ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል::
የመንገድ ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሲሆን፣ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ሽሮ ሜዳ የሚመጣን የትራፊክ እንቅስቃሴ ተቀብሎ ወደ ቁስቋምና እንጦጦ ተራራ የሚደረገውን የትራፊክ እንቅስቃሴ ያሳልጣል ተብሎ ይጠበቃል:: በተጨማሪም መንገዱ ለአካባቢው ነዋሪዎችና በእንጦጦ አረንጓዴ ስፍራዎች እንዲሁም ወደ ፓርኩ ለመዝናናት ለሚመጡ የከተማዋ ነዋሪዎችና ቱሪስቶች ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል ተብሎም ይታሰባል::
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 27/2012
አስናቀ ፀጋዬ