ሕዝብ በኮሮና ቫይረስ ቀሳፊ በሽታና በሚያስከትለው የከፋ ጥፋትና አደጋ ተጨንቆ ያለበት ወቅት ላይ ነን:: ዓለም በእልቂት ዶፍ እየተመታች የሰው ልጅ የስልጣኔ ጣሪያና ጫፍ እራሱን መመከት አቅቶት ጣእረ ሞት ተንሰራፍቶ ያለበት ዘመን ነው:: ሁሉም እንደየእምነቱ እጆቹን ወደ ላይ አንስቶ ፈጣሪውን እየለመነ ሲሆን በእኛም የተለያዩ የእምነት አባቶች ቀን ከለሊት እግዚኦታ ላይ ናቸው::
በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የሞተው 3 ሰው ብቻ ስለሆነ ከታመሙት ብዙዎች ስላገገሙ እኛ የጻድቃን ሀገር ስለሆንን ኮሮና አይነካንም የለብንም የሚለው የድንቁርና ጥግ መንግስት ያወጣውን መመሪያና ደንብ እስከመጣስ ተሸጋግሮአል:: ሌሎቹ ደግሞ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ውስጥ ሀገር ወድቃ ምርጫ መደረግ አለበት ሽግግር መንግስት መመስረት አለበት የሚሉም እያየን ነው:: መጠየቅ መብታቸው ቢሆንም ጊዜውን እና ተጨባጭ እውነታውን ሊያጤኑት ይገባል:: ተው ሲሉት የሚብስበት የእኛ ሰው ኮሮና አይነካኝም በሚል አደባባዩን መንገዱን ሞልቶ እየተገማሸረ ነው:: ትርምሱ ግፊያው ሁካታው ጫጫታው ከድሮውም ብሶበታል::
መንግስት ከዚህ ገዳይ መቅሰፍት ሕዝብና ሀገርን ለመታደግ የሚችለውን ሁሉ አድርጎአል:: እራሳችሁን ፤ርቀታችሁን ጠብቁ፤ ደጋግማችሁ ታጠቡ፤ ሳልና ማስነጠስ ካለባቸው ሰዎች ራቁ የሚለውን ምክርና ማስጠንቀቂያ ደግሞ ደጋግሞ በየሚዲያው በየስልክ መስመሩ ሰጥቶአል:: እናሳ—-እምቢ—ሲልሳ አሉ ሰውየው:: ምከረው ምክረው እምቢ ካለ መከራ ይምከረው የሚለው የቆየ አባባል በተግባር የተመሰከረ ነው:: ከሕዝቡ ውስጥ ምክሩን የተቀበለ ያልተቀበለም አለ:: እንግዲህ ምን ይባላል የሚሆነውን ማየት ነው::
ዓለም አቀፉ ወረርሽኝ ባለው ተለዋዋጭ ባሕርይ በፍጥነት ዓለምን እያዳረሰ ይገኛል:: እስከአሁን ከ250 ሺ በላይ የዓለም ሕዝብ ሞቶአል:: ያገገሙትም ብዙ ናቸው:: በሙያተኞች የሚሰጥን ምክርና በመንግስት የወጡ ደንቦችን አለማክበር የሚጎዳው ሕዝቡን ነው:: መጠንቀቁ ራስን ቤተሰብን ጎረቤትን መንደርን ከፍ ብሎም ሀገርን
ከጥፋት ይታደጋል:: አጉል ድፍረት፤ መቅበዝበዝ ፤ ንቀት፤ ስደብና ማጣጣል ደግሞ መመለሻ የሌለው የሕይወት ዋጋ ያስከፍላል:: ለሁሉም መጠንቀቁ ይበጃል::
ሕዝብ በዚህ ጭንቀትና ስጋት ውስጥ ወድቆ ባለበት ሰአት የፖለቲካዊ ስክነት ያጡትን እያየን ነው:: ስለምርጫና ሽግግር መንግስት ሃሳብ አቅርበዋል:: መብታቸው ነው:: ኮሮኖ ገባ በተባለ ሰሞን የሁሉም ድምጽ ጠፍቶ መነጋገሪያ ሁነው ነበር:: ፖለቲከኞች ሳይፈጠሩም ይህቺ ሀገር ነበረች:: ከእነሱ በኋላም ወደፊትም ትኖራለች:: ፖለቲከኞች ለአፍታ እንኳን ሰክኖ ማሰብ አልሆነላቸውም:: በዚህ ጭንቅ ሰአት የትኛው ሕዝብ ነው የሚመርጣቸው የሚለውንም ለማየት አልቻሉም:: በሀገርና በህዝብ ላይ አደጋ አንዣቦ እያለ ለፖለቲካ ስልጣን መሮጡ ትርጉም የለውም:: አይደለም ውስብስብ የፖለቲካ ተቃርኖ ያለባትን ሀገር በቅጡ አሰባስቦ አቻችሎ ለመምራት ትእግስትና እርጋታን ይጠይቃል::
ሕዝብና ሀገር መቀለጃ መጫወቻ አይደሉም:: ሊሆኑም አይችሉም:: አንዳንድ የተሻለ የሚያስቡ መኖራቸው እውነት ነው:: አይካድም:: ከሁልም ይልቅ በዚህ ጊዜ ምርጫ ይደረግ የሽግግር መንግስት ይደረግ የሚሉት ግራ አጋቢ ናቸው ::
ይህ ክፉ ቀን እንደ ሀገር እስኪያልፍ ድረስ ቢታገሱስ ምን ነበረበት ? የሀገርና የሕዝብ ሰላም፤ ደህንነትና ጤና ከምርጫም ከምንም ነገር በፊት ይቀድማል:: ሕዝብ በጤናው ሲኖር ነው የሚመርጠው:: ደግሞስ ሕዝብን ወክለናል ይበሉ አንጂ የትኛው ሕዝብ መቼስ ነው የወከላቸው ? በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በቅርብ ዓመታት እንደታየው የፖለቲካ ፓርቲ መመስረት አንዱ የዘመናዊ ንግድ መንገድ ነው:: በሕዝብና በሀገር ስም ብር እየተለመነ የሚሰበሰብበት:: የግል ኑሮ የሚደረጅበት:: ሕዝብ ይሄን ሁሉ ያውቃል:: በአስተሳሰባቸው የላቁ ተቃዋሚዎች ያሉትን ያህል ሀገሬ ድንቅነሽ እንዲሉ ማንም ጩልሌ የፖለቲካ ሲራራ ነጋዴ እየተነሳ አስር ስም እያወጣ ፓርቲ ነኝ እያለ የወረደና የከሰረ አስተሳሰብ ይዞ በጥላቻ እየዳከረና እየተርመጠመጠ እንዴት ይሄን ታላቅ ሕዝብ እመራለሁ ብሎ እንደሚያስብ ሲታይ አካሄዳቸው ከሕዝብ ንቀት የመነጨ መሆኑን መረዳት ይቻላል:: የተማርነው እኛ ፤ የምናውቀው እኛ ምን ያመጣል ባይ ናቸው:: ይሄም ታላቅ አደጋ ነው::
ሕዝብ የሚበጀውንና የማይበጀውን ያውቃል :: ጥላቻ የሚሰብኩ አክራሪ ፖለቲከኞች በዘር ፖለቲካ የተበከሉ ኮቪዶች አያስፈልጉትም:: በፍቅር በሰላም በመቻቻል በአብሮነት በመከባበር እሳቤ ብቻ ነው ሀገርን ወደፊት ማራመድ የሚቻለው:: ሕዝብ ለከፋፋዮች ሊያባሉት ለሚጥሩ መርገምቶች በስሙ ለሚነግዱ ደላላዎች ቦታ የለውም:: አሁን ያለው አመራር ዓለም አቀፉ ወረርሽኝ እስኪገታም ሆነ መቆጣጠር እስኪቻል እንዲሁም የበለጠ ሀገራዊ ሰላምና መረጋጋት እስኪፈጠር ድረስ ምርጫውን ማራዘሙ በእጅጉ ይደገፋል::
የተመረጠበት ጊዜ መስከረም ላይ ያበቃል፤ ሕጋዊነት የለውም፤ ትርምስ እንፈጥራለን የሚለው ባዶ ቀረርቶ ወንዝ አያሻግርም:: በየትም ሀገር የተፈጥሮ አደጋ፤ በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ወረርሽኝ ሲከሰት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ (ስቴት ኦፍ ኢመርጀንሲ) ይታወጃል:: ምርጫ ካለ ይራዘማል::
እንደ ሌላው ዓለም ሁሉ የእኛም ሀገር በችግርና በስጋት ውስጥ መውደቋን ዓለም ያውቃል:: ስለዚህ መጀመሪያ ለሕዝቡ ጤንነት ቢያስቡ ነው የሚሻለው::
ዴሞክራሲ በሀገራቸው መገንባት ያልቻሉትና በሌላው ሀገር ጉዳይ እየገቡ ሲያቦኩ የነበሩት ኃያላኑ ዛሬ ስለምርጫም ሆነ ስለ ዴሞክራሲ ትንፍሽ አይሉም:: ጊዜ የላቸውም:: ክፉኛ ተመተው አንገታቸውን ደፍተዋል:: የኢትዮጵያን ችግርና ፈተና መክተው የሚወጡት ልጆቿ ብቻ ናቸው:: ምርጫ ይደረግ የሚሉት ሰዎች ራሳቸው ከበሽታው ባህርይ የተነሳ ስለነገ መናገር አይችሉም::
መጀመሪያ ሰው ይኑር:: ጤና እንሁን:: ሀገራችን የእኛ እንጂ የማንም አይደለችም:: ምርጫው የትም ሮጦ አያመልጥም:: ሰላም ሲሆን ይደረስበታል:: እስከዛው ግን አደብ መግዛት ግድ ይላል:: መቅበዝበዙ ሌላ መአት ሌላ ዙር ጥፋት ሊያስከትል ስለሚችል እየተናበቡ መሄዱ ይበጃል:: ሀገርና ሕዝብ ስክነት ማስተዋል እርጋታ ማመዛዘንን ይፈልጋሉ:: ዘመኑና ኮረና ቫይረስ ሁለት ምርጫ ነው ያስቀመጡት:: አንድ ፈተናውን ተጋፍጦ ማለፍና በህይወት መኖር አሊያም ማለፍ:: ኢትዮጵያ ትቀጥላለች እንጂ አታልፍም:: በማስተዋል መራመዱ ለሁሉም ይበጃል::
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 27/2012
ወንድወሰን መኮንን