የክብር ቆንሲል ተስፋዬ ወንድሙ ከበደ የተወለዱትና ያደጉት በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ አካባቢ ነው:: መጀመሪያ ቄስ ትምህርት ቤት ቀጥሎ በኮልፌ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ /ኮምፕርሄንሲቭ/ ትምህርት ቤት ተምረው አጠናቀዋል::ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ኩባ ሪፐብሊክ በመሄድ በሆሴ ማሴዎ ወታደራዊ አካዳሚ ለ3 አመት ከ6 ወር በመካኒካል ኢንጂነሪንግና ፖለቲካል ሳይንስ ትምህርታቸውን ተከታትለው በመኮንንነት ተመርቀዋል::
ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ የአየር ወለድ ስልጠና ወስደዋል::በቀድሞው ሠራዊት የተለያዩ ክፍሎች የከባድ ተሸከርካሪዎች ታንኮችና ሚሳኤሎች ጥገና ላይ ሰርተዋል::ወደ ሶቭየት ሕብረት ተልከው 1 አመት የኢንተለጀንስ ትምህርት ተከታትለዋል:: ተመልሰው በታንከኛ ሻለቃ አዛዥነት ሰርተዋል፡፡
ደብረዘይት በሚገኘው ፕሮጀክት 40020 በሚባለው የተሸከርካሪዎችና የተለያዩ መሳሪያዎች ማምረቻና መጠገኛ ውስጥ ያገለገሉ ሲሆን በወታደራዊ ማእረግ ሻለቃ ደርሰዋል::የማስተርስ ዲግሪያቸውን በሂዩመን ሪሶርስ ማኔጅመንት ከአድማስ ዩኒቨርሲቲ በተልእኮ ትምህርት አጠናቀዋል::ቤተሰባቸው ወደ ሚኖርበት አውስትራሊያ በመሄድ የተለያዩ የሙያ ስልጠናዎችን በኮምፒዩተር ሳይንስ፤ በሴክዩሪቲና በክሊኒክ ማኔጅመንት ወስደዋል::
በኢንቨስትመንትና በሴኪዩሪቲ ካምፓኒ ባለቤትነት ይሰራሉ:: በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያ የኡራጓይ የክብር ቆንስልም ናቸው::በኢንቨስትመንት፤ በግል ሴኩሪቲ ካምፓኒ ባለቤትነት እንዲሁም ተዛማጅ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ አድርገዋል::ይከታተሉት
አዲስ ዘመን፡- አሁን የተሰማሩበት መስክ ኢንቨስትመንትና ሴክዩሪቲ ነው::እንዴት ጀመሩት፤ ኢንቨስትመንቱ ያተኮረው በምን ላይ ነው?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- ሚረር ትሬዲንግ ኤንድ ሰርቪስስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ካምፓኒ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ነኝ::ካምፓኒው የጽዳት፤ ጋርደንና፤ የግል ሴኪዩሪቲ (ጥበቃ) ስራዎችን ከተለየዩ የኢንቨስትመንት፤ ንግድና የኮንስትራክሽን ካምፓኒዎች ጋር ይሰራል::አውስትራሊያ እያለሁ በዚህ ስራ ተሰማርቼ ስሰራበት ነበር::በሀገሬ ውስጥ ይሄን ስራ አምጥቼ ብሰራ ውጤታማ እንደምሆን ለብዙ ወገኖቼም የስራ እድል እንደምፈጥር አምን ነበር::ይሄንን ድርጅት 2001 ዓ/ም አቋቁመን በርካታ ሰዎችን ቀጥረን በማሰልጠን በተለያዩ ድርጅቶች፤ ተቋማት፤ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች፤ በኢንቨስትመንት መስኮች፤ በተለይም በላቲን አሜሪካ ኤምባሲዎችና በሌሎችም አሰማርተን በማሰራት ላይ ነን::የዛሬ አራት አመት ገደማ የባቡሩ ስራና እንቅስቃሴ ከጀመረ ጀምሮ ከአውስትራሊያ ያየሁትን የባቡር ጽዳት ስራ ወደ እኛ ሀገር እንዲተላለፍ በማድረግ በጨረታ እየተሳተፍን እያሸነፍን በመስራት ላይ እንገኛለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ምን ያህል ሠራተኞች አለዎት ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- 500 ሠራተኞች አሉን::
አዲስ ዘመን፤—-ከአዲስ አበባ ውጭ ፕሮጀክቶች አሏችሁ ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፤ ድሬደዋ ፤ ናዝሬት ፤ በአማራ ክልልም አሉን፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኢንቨስትመንትና በኮንስት ራክሽን ዙሪያ ያለውን-ሴክዩሪቲ በምን መልኩ ማስፋፋት አስባችኋል ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- የሴክዩሪቲውን ስራ በተመለከተ ሳልጠቅስ የማላልፈው ነገር አለ:: በሕብረተሰባችን ውስጥ የተለመደና የተሳሳሳተ ግንዛቤ አለ:: የግል ሴኩሪቲውን ስራ እንደ ዝቅተኛ ስራ አድርጎ የመቁጠር ችግር:: ግን አይደለም::በአለም ላይ የተከበረ ዋነኛ ስራ ነው:: ሕይወትን ንብረትን ከአደጋ የሚጠብቅ ሕይወቱን አሳልፎ ሰጥቶ ሌላውን የሚያተርፍ ስራ ነው::በስራው ላይ ከሌሎች ጋር ስንወዳደር ጨረታም ሲያወጡ የሚያወጡት የደመወዝ ስኬል እጅግ በጣም አነስተኛ ነው::በጣም ከባዱና ትልቁ ስራ ጽዳትና የሴኪዩሪቲ
ስራ ነው::ሴፍቲ (ደህንነት) ካልተሰማው አንድ ሰራተኛም ሆነ ኢንቨስተር ስራውን መስራት አይችልም::ሁሉም ሰራተኞች ኢንሹራንስ አላቸው::ክፍያቸውም የተሻለ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ካምፓኒያችሁ በየቦታው ምን ሰራ ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- ኮቪድ 19 (ኮሮና) በተመለከተ የእኛ ድርጅት (ሚረር ካምፓኒ) የባቡር ጽዳት በተለይ “የዲስ ኢንፌክሽን” ስራውን ከምድር ባቡር ጋር ባለን የስራ ውል መሰረት እየሰራን ነው::በቅርቡ አርጀንቲና ሄጄ በነበረበት ሰአት ላቦራቶሪዎ “ፊያም” ከሚባል ድርጅት ጋር በመዋዋል “ሜዲ ክሊን” የሚባል አንድ ኬሚካል በሳምፕል መልክ ይዤ መጥቼ ነበረ::በአሁኑ ሰአት ለባቡሩ ጽዳት እሱን እየተጠቀመን “የዲስኢንፌክሽን” ስራውን እየሰራን ነው::ከሀያት እስከ ጦር ኃይሎች መስመር ያለው የእኔ ነው::በቀን 110 ሠራተኛ እናሰማራለን::በተለያዩ ስቴሽኖችና ግቢው ውስጥ እንሰራለን::በተለይ አሁን የምድር ባቡር ዋና ስራ አስኪያጅ እና የትራንስፖርት ሚኒስትሯ በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት የሰጡበት እንቅስቃሴ የባቡሩ እንቅስቃሴ ነው፡፡
የባቡሩ ዋና ስራ አስኪያጅ እና የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ሌሊት 11 ሰአት እየመጡ ይከታተላሉ:: በየስቴሽኑ በኋላም ማታ 4 ሰአት ባቡሩ ስራውን ሲያቆም ይጸዳል:: ባቡሩን ለሊት የእኛ ሰራተኞች ለነገው ስራ ዝግጁ እንዲሆን “በዲስኢንፌክታንት” ያጥቡታል:: ሲነጋ ደግሞ ሌሎች ሰራተኞች በየጣቢያው አሉ:: ሲነሳ በኬሚካል ይታጠባል::ጨርሶ ጦር ኃይሎች ሲደርስ እናጥበዋለን:: ሲመለስም እንደዚሁ:: የድርጅታችን ሠራተኞች ለበሽታው እንዳይጋለጡ ተገቢውን መከላከያ ያደርጋሉ:: ማስክ ከመገኘቱ በፊት ምናልባት ሌላ ተቀናቃኝ ከሌለኝ የመጀመሪያውን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰራ ማስክ መርካቶ ሄጄ የሰራሁት እኔ ነኝ፡፡
አቡጀዲ ገዛሁ::ተቆረጠ::ግራና ቀኝ ላስቲክ አሰርኩበት:: ለሁሉም ሰራተኞቼ አደልኩ:: አማራጭ ከሌለ አማራጭ ትፈጥራለህ ማለት ይሄ ነው::እስከአሁን ድረስ እግዚአብሄር ተጨምሮበት ከጤና ጥበቃ የተሰጡትን የጥንቃቄ ትግበራዎች እየተከተልን ሰራተኞቻችን በሙሉ ደህና ናቸው::ለድርጅታችን የጥበቃና የጽዳት ሰራተኞች ምናልባት ድንገተኛ ችግር ቢፈጠር፤ ስራ ላይ ቢቆዩና ወደቤት መሄድ ባይችሉ በሚል ድሮ በወታደርነቴ የማውቀውን ምግብ (ኮቸሮ) ከ25 ሺ ብር በላይ አውጥቼ በመግዛት በቢሮአችን በመጠባበቂያነት አስቀምጠናል::
አዲስ ዘመን፡- ወደኢንቨስትመንቱ እንግባ:: በአይነቱ የተለየና ትልቅ የሆነ ሆስፒታል ለመጀመር እንቅስቃሴ ላይ ነበራችሁ::ከምን ደረሰ ቢያስረዱን?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- እኔ፤ ዶክተር መብራቱ ጀምበርና ሻለቃ አለምሰገድ ከበደ፤ አቶ ግርማ ተክለማርያም ሆነን አንድ አክስዮን መሰረትን::ለሀሳቡ መጠንሰስ መነሻ አጋጣሚ ነበረው::በተለያየ ቦታ ቤተክርስትያንና በመስጊዶችም በኩል ስናልፍ ማይክሮፎኖች ተጠምደው የልብ ሕክምና የኩላሊት ሕክምና የተለያዩ በኢትዮጵያ ውስጥ ሕክምና የሌላቸውን በሽታዎች ለማሳከም እባካችሁ እርዱን የሚሉ ብዙ ድምጾችን እንሰማለን::ይሄን ችግር የአቅማችንን ያህል እንዴት ነው የምንቀርፈው ብለን ሶስታችንም በተደጋጋሚ ተነጋገርን::መከርንበት፡፡
ዶክተር መብራቱ ጀምበር እኔና ጓደኛዬ ሻለቃ አለምሰገድ ከበደ እንዲሁም አቶ ግርማ ተክለማርያም በተማርንበት ሀገር የተማረ የማሕጸን ስፔሻሊስት ነው::ከዚሁ ጀምረን አክስዮን በማቋቋምና የኩባ ዶክተሮችን ወደዚህ በማምጣት ሆስፒታሉንም ሙሉ በሙሉ በኩባ ዶክተሮችና ኩባ በተማሩ ኢትዮጵያውያን ዶክተሮች ብንመሰርተው የተሻለ ውጤት ያስገኛል ብለን መሰረትነው::
አዲስ ዘመን፡- ከተመሰረተ ምን ያህል ግዜ ሆነው ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- ከ5 አመት በላይ ሆነው።
አዲስ ዘመን፡- ከምን ደርሶአል ? ኢንቨስትመንቱ ለምን ወደስራ አልገባም ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- በኢንቨስትመንቱ ላይ ምንም ችግር አልነበረም::የአክስዮን ሽያጭ ተጀምሮ ነበር:: የመመስረቻና የመተዳደሪያ ደንቡን የተመለከቱት በተለያዩ ከፍተኛ ቦታዎች በግል ስራ፤ በንግዱ አለም በኢንቨስተርነት በሕክምናው ዘርፍ ያሉ ምሁራን፤ በአስመጪና ላኪነት በብዙ ዘርፍ ተሰማርተው የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ለሀገራችንና ለሕዝባችን አስፈላጊና ወሳኝ ነው በሚል ከፍተኛ ተሳትፎና ርብርብ እያደረጉ ነበሩ፡፡
በአጋጣሚ ያጋጠመን መሰናክል ሆስፒታሉን ልንመሰርተው ያሰብነው በአዲስ አበባና በዱከም አካባቢ ስለነበር ደንቡን አሟልተን መሬት እንዲሰጠን ጥያቄ አቅርበን እያለ ምላሹ ዘገየ:: እንደሚታወቀው በሀገራችን ባለፉት አመታት የተለያዩ የፖለቲካ ትግሎችና እንቅስቃሴዎች ነበሩ:: በተለይ በኦሮሚያ ሁሉም ባለስልጣኖች አምነውበት ለዚሁ ስራ በዱከም ከተማ መሬት እንድናገኝ ደብዳቤም ሰጥተውናል::ከኦሮሚያ የጤና ቢሮም የተሰጠን ደብዳቤ አለ:: የጠየቅነው ለዋናው ሆስፒታልና ማስፋፊያም ጭምር ነው:: አብሮ የሚሰራ የታካሚዎች መንደር አለ:: ለእኛ ብቻም ሳይሆን ለመላው አፍሪካም ይጠቅማል፡፡
ባንኮክና ሕንድ ሄደው ከሚታከሙ ኢትዮጵያ መጥተው ቢታከሙ ለሀገራችን ትልቅ ጥቅም ያስገኛል:: አዲስ አበባ የአፍሪካና የአለም መዲና ናት:: ለአውሮፓ ሕብረት ከኒውዮርክና ከቤልጅየም ብራስልስ ቀጥላ ሶስተኛ አለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ከተማ ናት:: ይህን ለመስራት የጠየቅነውን ትልቅ ሆስፒታል ፈጥነን እውን ብናደርግ ጠቀሜታው በብዙ መልኩ የጎላ ነው የሚሆነው::
አዲስ ዘመን፡- መነሻ ካፒታላችሁን ስንት ነበር ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- 11 ሚሊዮን አካባቢ ነው::በዝግ አካውንት ተቀምጦ ነው ያለው::አሁን ያሉት ከንቲባ ታከለ ኡማ ለሕዝባዊ አገልግሎት ለሚሰጡ ስራዎች ቅንነት ያላቸው መሆኑ ስለሚታይ ቀደም ሲል የጠየቅነውን ለሆስፒታሉ የሚሆነውን መሬት ጉዳይ እንደገና አቅርበን ለማስወሰን እየሰራን ነው::የእኛ ሀሳብ በብዙ በተጠኑ ምክንያቶች ከታካሚዎች ጸጥታና ንጹህ አየር ከማግኘትም አንጻር ቦታው ከተማ ዳርቻ ላይ እንዲሆን ነበር ስንጠይቅ የነበረው::ቦርዱ አሁን ሀገሪቱን እየመራ ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አመራር ለብልጽግናና ለእድገት የሚሰራ ለቅን ሕዝባዊ አስተሳሰቦች ድጋፍ የሚያደርግ ነው የሚል ጽኑ እምነት አለው::
የኮሮና ወረርሽኝ አለምአቀፍ አደጋ ወደሀገራችን መግባት በተለያዩ የመንግስትም ሆነ የግሉ ዘርፍ የኢንቨስትመንትና የኮንስትራክሽን የንግድ ፍሰትና ልውውጥ ስራዎች ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮአል::እኛም እየሄድንበት የነበረውን የሆስፒታል ግንባታ ስራ ለመጀመር መሬቱን የማስጨረሱን ጉዳይ ገታ ያደረግነው በዚሁ ምክንያት ነው::ያኔ እንደጀመርን ተሰጥቶን የሆስፒታሉ ግንባታ አልቆ ስራው ጀምሮ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ከመጣው በሽታ አንጻር ሰፊ ሕዝባዊ አገልግሎቶችን መስጠት ይችል ነበር::አሁንም ቢሆን ፈጥኖ ወደስራው መግባት ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- መሰናክሉ የተፈጠረው ምኑ ላይ ነው ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- ሁሉም ነገር መንገድ ይዞ እየሄደ ነበር:: መሰናክል የሆነብን መሬቱን ፈጥኖ የማግኘቱ ጉዳይ ነው:: መሬቱ ሲገኝ በአርክቴክቶችና ሲቪል መሀንዲሶች ባሰራነው የሆስፒታሉ ሞዴል ዲዛይን መሰረት አስተዳደሩ የሚያሻሽለውን አሻሽሎ ካጸደቀው በኋላ በቀጥታ ወደ ግንባታ ነው የሚገባው::
የሕክምና ባለሙያዎች አክስዮን ገዝተው ለመግባት ፍላጎታቸውን የገለጹ አሉ:: በዚህ ሆስፒታል ጉዳይ ውጭ ካሉ ኢንቨስተሮችም ጋር ተነጋግረናል::ሼር እንደሚገቡ አረጋግጠውልናል:: የሚገነባው ሆስፒታል ሀገራዊና ሕዝባዊ አገልግሎቱ ከፍተኛ ነው::በሀገራችን ካለው 110 ሚሊዮን የሕዝብ ብዛት አንጻር ሲታይ ብዙ ሆስፒታል የለንም:: ቢኖሩንም ውስንና ዋና ከተሞች ውስጥ ያሉ ናቸው:: እኛ ከጀመርነው በኋላ ወደ ክልሎችም የማስፋት እቅድ አለን:: ወደፊት በጣም ብዙ ሆስፒታሎች ያስፈልጋሉ::መሬቱን ካገኘን ከአምስት አመት በፊት በባለሙያ ያስጠናነው የግንባታው አጠቃላይ ወጪ አሁን ከተፈጠረው አለም አቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስና መዳከም አንጻር ወጪው እጥፍ ስለሚጨምር እንደገና ተከልሶ ነው የሚሰራው::,ካፒታል በጀቱን ለማሳደግ አክስዮን ሽያጩን ለሕዝብ ክፍት ማድረግ አንዱ መንገድ ነው::በዚህ ገቢውን ማሳደግ እንችላለን::የሕብረተሰብ ጤና ጉዳይ ስለሆነ መንግስት እገዛ ሊያደርግ ሊሳተፍ ይችላል::ይህም ፈጥነን የምንጀምረውን ግንባታና ውስጣዊ ድርጅቱን ለማሟላት ይረዳናል::ሆስፒታሉ ሰፊ ኮምፕሌክስ ነው የሚሆነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለሆስፒታሉ ስራ መጀመር በዝግ አካውንታችሁ ካለው 11 ሚሊዮን ብር ውጭ ሌሎች ቃል የገቡላችሁ ነበሩ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- በአውሮፓና አሜሪካ ያሉ ኢትዮጵያውያን በአክስዮን ግዢው እንደሚሳተፉ ገልጸውልናል::ሆስፒታሉን እውንና ዘመናዊ ለማድረግ አለም አቀፍ አስተባባሪ “ቻፕተር” አቋቁመናል::በተለይ ከእኛው ጋር የተማሩ ዛሬ በአውሮፓና አሜሪካ የሚኖሩ ከፍተኛ ባለሀብት የሆኑ አሉ::እነሱ በብዙ መልኩ ያግዙናል:: በውጭ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያ ገብተው በሕክምና ስራ ላይ ለመስራት የሚፈልጉ ድርጅቶች አሉ::40 ፐርሰንቱን ያህል እንደሚገዙ ቃል ገብተዋል::
አዲስ ዘመን፡- በእቅዳችሁ መሰረት ሆስፒታሉ ተሰርቶ ሲጠናቀቅና ስራ ሲጀምር በቀን ምን ያህል ኢትዮጵያውያንን ሊያስተናግድ ይችላል ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- አክስዮኑን ስንመሰርት በመጀመሪያ ቃል የተገባባነው ሀሳቡም የተጸነሰው በየቤተክርስቲያኑና በየመስጊዱ የወደቁና ረዳት የሌላቸውን በገንዘባቸው ውጭ ወጥተው መታከም የማይችሉትን በተለያዩ በሽታዎች የሚሰቃዩ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ከያሉበት አምጥተን በነጻ እንዲታከሙ ማድረግ ነው::ሆስፒታሉ መጠለያ ይኖረዋል የሚለውን ታሳቢ አድርገን የያዝነው እነዚህ ህሙማን ታክመው ድነው ወይንም ተሽሎአቸው ወደቤታቸው እስኪሄዱ ድረስ የሚያርፉበት ነው::ከእነሱ ውጭ ያለው ዜጋ ተመጣጣኝ ዋጋ ከፍሎ የሚታከም ይሆናል::ሆስፒታሉ ሙሉ አገልግሎቱን ሲጀምር በቀን ከ1000 እስከ 2000 ታማሚ ተቀብሎ ማስተናገድ ከቻለ ትልቅ ስኬት ነው::ሆስፒታሉ የሕጻናት፤ የአረጋውያን፤ የሴቶች፤ የአንገት በላይና የቆዳ ሕክምና፤ የልብና የኩላሊት ሕክምና፤ የካንሰርና የለምጥ ሕክምና፤ ኦፕሬሽን ሩም፤ የሕሙማን መተኛ ክፍሎች፤ የራሱ ፋርማሲ፤ የበሽታዎችና የመድሀኒቶች የምርምር ማእከል፤ የራሱ ክበብና የህሙማን መዝናኛ ቦታዎች፤ የትራንስፖርት አገልግሎትና አምቡላንሶች በስፋት ይኖረዋል:: በሀሳብ ደረጃ ግዙፍ ነው:: ሰፊ አለም አቀፍ እርዳታም ከመንግስታትና ከድርጅቶች ያገኛል ብለን እናምናለን::ቀስ በቀስ ይሟላል::የሙያተኛ እጥረት ቢከሰት ከውጭ እናስመጣለን:: በተለይም ከኩባ:: እነዚህን በስፋት አካተው የሚይዙ የተለያዩ ፎቆች ይኖረዋል::ፈረንጆቹ ኦል ኢን ዋን (ሁሉንም በአንድ ቦታ ማግኘት) ይቻላል የሚሉት አይነት እንዲሆን ነው አቅደን እየሰራን ያለነው:: ሆስፒታሉ እያደገ ሲሄድ ማሕበራዊ አገልግሎቶችን የማገዝ ደካሞችና አረጋውያንን በነጻ የማከምና የመርዳት ሰፊ አላማ አለው::
አዲስ ዘመን፡-,ኩባ በአለም ላይ የለምጽና የካንሰር መድሀኒት ያገኘች ብቸኛ ሀገር ነች:: የሕክምና ምርምራቸውን ወደ ሀገራችን ለማስገባት ከኤምባሲው ጋር አልተነጋገራችሁም ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- አዲስ አበባ ከሚገኘው የኩባ ኤምባሲ ጋር በቅርበት እንገናኛለን:: እንሰራለን:: የተማሪዎች ማሕበርም አለን:: ኩባ ተምረው ተመርቀው የመጡ ምርጥ የሕክምና ዶክተሮች ዛሬ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን እያገለገሉ ነው::ኩባ በብዙ መስክ አስተምራ ለኢትዮጵያ ምሁራንን ያፈራች ሀገር ነች::የኩባ ም/ፕሬዚደንት ከሁለት አመት በፊት አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት ብዙ ተነጋግረናል:: የኩባን የሕክምና ምርምር
እውቀትና ልምድ በምንከፍተው ሆስፒታል ውስጥ ራሱን የቻለ አካዳሚ ከፍተው የእውቀት ሽግግር በማድረግ እንደሚያግዙን ቃል ገብተዋል፡፡
በወቅቱ ባደረጉት ንግግር እኛ ሁልግዜ የኩባ ዶክተሮችን ወደ ኢትዮጵያ መላክ ሳይሆን የኩባን የሕክምና ጥበብና እውቀት ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስቀረት የሕክምና ኮሌጅ (አካዳሚ) መክፈት እንፈልጋለን ነው ያሉት;::
እኔም በቅርቡ በኩባና በተለያዩ የላቲን አሜሪካ ሀገራት ከሆስፒታሉ ስራ ጋር በተያያዘ ልምድ ለመውሰድ ጉብኝት አድርጌለሁ::አንደኛ ለኢትዮጵያ ያላቸው አመለካከት እጅግ በጣም ቀና ነው::በስልጠና በልምድ ልውውጥና በእውቀት ሽግግር ሊያግዙን እንደሚፈልጉ ገልጸውልኛል::በተለይ ኩባዎች በየግዜው የሆስፒታል ግንባታውን ስራ የመጀመሩን ነገር ከምን አደረሳችሁት ብለው በተደጋጋሚ ጠይቀውኛል::ይሄ ትልቅ ነገር ነው:: ሆስፒታሉ ከተገነባ በኋላ በእርግጠኝነት የኩባ መንግስት አስፈላጊ የሆኑትን ሙያተኞች በካንሰር በለምጥ ,(መድሀኒት ስላገኙ) በመሳሰሉት እንደሚልኩ ነግረውናል፡፡
ኩባዎች ለኢትዮጵያ ያላቸው ፍቅር የተለየ ስለሆነ በአለም በታወቁበት የሕክምናው ዘርፍ ብዙ ያደግፉናል ብዬ አስባለሁ::ሌላ በትልቁ ያስተሳሰረን ጉዳይ አለ::ኩባውያን ኢትዮጵያ በሶማሌ ስትወረር በቀጥታ ለእርዳታ ገብተው ለኢትዮጵያ ሲሉ የደም መስዋእትነት የከፈሉ በዚህም በሀገራችን ታሪክ ላይ ደማቅ አሻራቸውን ያስቀመጡ ናቸው::መቸም ቢሆን ኢትዮጵያ እንድትነካ አይፈልጉም:: ትልቅ ሆና ማየት ይፈልጋሉ::
አዲስ ዘመን፡- እነሱ ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልጉት በተለይ በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እውቅና ባገኙበት በሕክምናው ዘርፍ እውቀትን ማስተላለፍ ነው ብለውኛል:: ቢያስረዱን ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- አለም አቀፍ ትብብራቸውን በተለይ በዚህ ዘርፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ማድረግ ይፈልጋሉ::ኩባዎች ብቻ አይደሉም::ሌሎች የአለም መንግስታትም ጭምር ኢትዮጵያ ላይ ኢንቨስት የማድረግ ብርቱ ፍላጎት አላቸው::ለዚህ ነው በርካታ የታላላቅ ሀገራት የኢንቨስትመንት ካምፓኒዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት እያደረጉ ያሉት:: የምንገነባውና የምንከፍተው ሆስፒታል “ኢስተርን ስታር ተርሸሪ ሆስፒታል” የሚባል
መታደግ ከቻልን አቅም የሌለውን ከረዳን ለእኛ ትልቁ እርካታችን የሚሆነው እሱ ነው::ለመንግስትም ቢሆን በሕክምናው ዘርፍ የሚያደርገውን ስራ ያግዛል::ያለምከው ነገር ሲሳካ ማየት ደስታው ትልቅ ነው::ተግባራዊ ሁኖ ማየት እንፈልጋለን::በተለይ ቀደም ብለን ከአምስት አመት በፊት በጠየቅነው መሰረት ተሰርቶ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ለተከሰተው ወረርሽኝና የሕክምና መጨናነቅ ምን ያህል እገዛ ማድረግ ይችል እንደነበር ስናስብ መጸጸታችን አልቀረም::
አዲስ ዘመን፡- ዘመናዊ ሕክምናን ከባሕል ሕክምና የማቀናጀቱስ ሀሳብ አላችሁ ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- ሁሉም የአደጉና የበለጸጉ ሀገራት በየሀገራቸው ለዘመናት የኖረውን ባሕላዊ ሕክምና ከዘመናዊ ሕክምና ጋር እያስተሳሰሩ ነው ለተለያዩ በሽታዎች መድሀኒት የሚያገኙት::ኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊ ሕክምና ከመግባቱ በፊት ስትጠቀምበት የኖረችው የራሷ ባሕላዊ ሕክምና አላት::ለባሕላዊ ሕክምናዎቻችንና መድሀኒቶቻችን ትልቅ እውቅና እንሰጣለን:: የውጭዎቹ ከጥንታዊ የኢትዮጵያ የመድሀኒት ጥበቦች ወስደው በለው ዘርፈው ይጠቀሙበታል::እኛ ደግሞ የራሳችንን እናጣጥላላን:: ይሄ መሆን የለበትም::በጣም በርካታ በሆኑ የአለም ሀገራት የመዘዋወር እድሉ ገጥሞኛል:: ከቀደሙት አባቶቻቸው በትውልድ ተራ የተላለፈላቸውን የየሐገራቸውን ባሕላዊ መድሀኒት አክብረው ይይዛሉ::ይጠቀሙበታል::በዘመናዊ መልክ እንዲለወጥ ይሰራሉ::ኢትዮጰያ በዚህ ረገድ ሀብታም ነች:: በሆስፒታላችን ውስጥ በርካታ ዶክተሮችና የባሕላዊ ሕክምና እውቀት ያላቸው ዜጎች እየተማከሩ የሚሳተፉበት ዘመናዊ ላብራቶሪ ይኖረናል::የምርምር ስራዎችና ለተለያዩ በሽታዎች አዳዲስ የመድሀኒት ፍለጋ ስራዎች ይሰራሉ::ቻይና፤ ኩባ፤ ሕንድ፤ ኮርያ፤ ጃፓን ሌሎችም ለዘመናዊው ሕክምና መነሻቸው ባሕላዊ ሕክምና ነው::በስፋት ይጠቀሙበታል፡፡ይሄን ሁሉ አጥንተናል::
በእኛ ሀገር ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ ትልቅ የባሕላዊ ሕክምና መድሀኒቶችና የተከማቸ እውቀት አለ::በሀገር ደረጃ ብዙ የባሕላዊ ሕክምና እውቀት አለ::እነሱን አቀናጅተን እውቅና አግኝተው እንዲሰሩ እውቀቱ ጠፍቶ እንዳይቀር ደግሞ አሰባስበን በመጽሀፍ መልክ ታትሞ እንዲቀመጥ ለትውልድ እንዲተላለፍ
ነው ፡፡
ሆስፒታሉ የተሟላ ስለሚሆን በተለይ ከላቲን አሜሪካ አምባሳደሮች ጋር ባደረግነው የተናጠል እና የወል ንግግር ሆስፒታሉ ተገንብቶ ስራ ሲጀምር በዚሁ በኩል የሕክምና አገልግሎት ማግኘት ይፈልጋሉ::
የቦርድ አባላቱም ሆኑ ሌሎቹ የአክስዮን አባላት ዋናው ፍላጎታችን ይሄን ሆስፒታል ብንገነባው ለሕዝብ በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቅም ስራ በመስራት ታሪክ ጥለን እናልፋለን የሚል ነው:: ማንም ጥቅም አይጠላም::እኛ ግን አሁን ባለው ደረጃ ጥቅም አይደለም እያሰብን ያለነው:: እሱ ወደፊት ይደረስበታል:: ብዙ ሰው ሆቴል መዝናኛ ሪል ስቴት ነው የሚገነባው:: እኛ ሕይወት አድን የሆነ ሆስፒታል ለመገንባት ነው የተነሳነው::
የሆስፒታል ጉዳይ የሕይወት ማዳንና ማትረፍ ስለሆነ በርካታ ወገኖቻችንን ከበሽታና ከሞት
መታደግ ከቻልን አቅም የሌለውን ከረዳን ለእኛ ትልቁ እርካታችን የሚሆነው እሱ ነው::ለመንግስትም ቢሆን በሕክምናው ዘርፍ የሚያደርገውን ስራ ያግዛል::ያለምከው ነገር ሲሳካ ማየት ደስታው ትልቅ ነው::ተግባራዊ ሁኖ ማየት እንፈልጋለን::በተለይ ቀደም ብለን ከአምስት አመት በፊት በጠየቅነው መሰረት ተሰርቶ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ለተከሰተው ወረርሽኝና የሕክምና መጨናነቅ ምን ያህል እገዛ ማድረግ ይችል እንደነበር ስናስብ መጸጸታችን አልቀረም::
አዲስ ዘመን፡- ዘመናዊ ሕክምናን ከባሕል ሕክምና የማቀናጀቱስ ሀሳብ አላችሁ ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- ሁሉም የአደጉና የበለጸጉ ሀገራት በየሀገራቸው ለዘመናት የኖረውን ባሕላዊ ሕክምና ከዘመናዊ ሕክምና ጋር እያስተሳሰሩ ነው ለተለያዩ በሽታዎች መድሀኒት የሚያገኙት::ኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊ ሕክምና ከመግባቱ በፊት ስትጠቀምበት የኖረችው የራሷ ባሕላዊ ሕክምና አላት::ለባሕላዊ ሕክምናዎቻችንና መድሀኒቶቻችን ትልቅ እውቅና እንሰጣለን:: የውጭዎቹ ከጥንታዊ የኢትዮጵያ የመድሀኒት ጥበቦች ወስደው በለው ዘርፈው ይጠቀሙበታል::እኛ ደግሞ የራሳችንን እናጣጥላላን:: ይሄ መሆን የለበትም::በጣም በርካታ በሆኑ የአለም ሀገራት የመዘዋወር እድሉ ገጥሞኛል:: ከቀደሙት አባቶቻቸው በትውልድ ተራ የተላለፈላቸውን የየሐገራቸውን ባሕላዊ መድሀኒት አክብረው ይይዛሉ::ይጠቀሙበታል::በዘመናዊ መልክ እንዲለወጥ ይሰራሉ::ኢትዮጰያ በዚህ ረገድ ሀብታም ነች:: በሆስፒታላችን ውስጥ በርካታ ዶክተሮችና የባሕላዊ ሕክምና እውቀት ያላቸው ዜጎች እየተማከሩ የሚሳተፉበት ዘመናዊ ላብራቶሪ ይኖረናል::የምርምር ስራዎችና ለተለያዩ በሽታዎች አዳዲስ የመድሀኒት ፍለጋ ስራዎች ይሰራሉ::ቻይና፤ ኩባ፤ ሕንድ፤ ኮርያ፤ ጃፓን ሌሎችም ለዘመናዊው ሕክምና መነሻቸው ባሕላዊ ሕክምና ነው::በስፋት ይጠቀሙበታል፡፡ይሄን ሁሉ አጥንተናል::
በእኛ ሀገር ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ ትልቅ የባሕላዊ ሕክምና መድሀኒቶችና የተከማቸ እውቀት አለ::በሀገር ደረጃ ብዙ የባሕላዊ ሕክምና እውቀት አለ::እነሱን አቀናጅተን እውቅና አግኝተው እንዲሰሩ እውቀቱ ጠፍቶ እንዳይቀር ደግሞ አሰባስበን በመጽሀፍ መልክ ታትሞ እንዲቀመጥ ለትውልድ እንዲተላለፍ
የማድረጉ ሰፊ ሀሳብ አለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- መንግስት መሬቱን ቢሰጥ ስራውን ጀምሮ ለመጨረስ ምን ያህል ግዜ ይፈጃል ይላሉ ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- መሬቱ እንደተገኘ ግንባታውን ባለን ፋይናንስ እንጀምረዋለን::የአክስዮኑን ሽያጭ ለመግዛት የሚጠብቁ እልፍ ኢትዮጵያውያን አሉ:: ቀደም ብለው በጠየቁን መሰረት 40 በመቶ የውጭ የሕክምና ሰዎችን በሼር እናሳትፋለን::የላቲን አሜሪካ ሀገራት አምባሳደሮች የገቡት ቃል አለ::እነዚህ ሁሉ ከእውቀት ልምድና ፋይናንስ ጋር ተቀናጅተው ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ ብለን እናምናለን::
ዘመናዊ የሕክምና መርጃ መሳሪያዎችን በተመለከተ ቃል የገቡልን የውጭ ድርጅቶች አሉ::ከዚህ ውስጥ “ሂዩመን ብሪጅ” የተባለ የስዊድን መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የምስራቅ አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር አቶ አዳሙ አንለይ ይገኙበታል::ሁሉም የመሬቱን መገኘትና ወደ ስራ መግባት ነው የሚጠብቁት::ዩኔስኮና የአለም የጤና ድርጅትም ይረዱናል የሚል እምነት አለን::የኩባ መንግስት በዋነኛነት አለ::ለሀገራችንና ለሕዝባችን የሚበጅ ትልቅ ስራ ስለሆነ የኢትዮጵያ መንግስትም እገዛ እንደሚያደርግ እርግጠኞች ነን::ዋናው ነገር ይሄንን ትልቅ ሀገራዊ ራእይ ያለውን ቀና ሀሳብ ለማሳካት መንግስታዊ አካላት የበኩላቸውን ትልቅ ድጋፍ እንደሚያደርጉ እንጠብቃለን::
እኛ ቢራና አረቄ ፋብሪካ መዝናኛ ሆቴል እንገንባ አላልንም:: ይሄም ትልቅ ገቢ የሚያስገኝ ኢንቨስትመንት ነው::የእኛ ምርጫ ደግሞ ለሕዝብ አገልግሎት የሚውል ትልቅ ሆስፒታል መገንባት ሆነ:: በሀገራችን አሁን ያለው የኮሮና ወረርሽኝ ስጋት ጋብ ካለ በኋላ ጉዳዩ እንዳይዘገይብን አፋጣኝ ውሳኔ እንዲያገኝ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጽ/ቤት፤ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን፤ የአዲስ አበባን ከንቲባ ክቡር ታከለ ኡማን ለማነጋገር ተዘጋጅተናል::አብሮ በመስራት ትልቅ እገዛ እንደሚያደርጉ እናምናለን::
አዲስ ዘመን፡- ከኢንቨስትመንት ከብዙ ሀገራዊ ጉዳዮች አንጻር አሁን ያለውን የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን አመራር እንዴት ያዩታል ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በቅንነት በመልካም እሳቤና በሰብአዊነት ሀገራዊ ብልጽግናን በመመኘት የሚሰሩ ናቸው::ይሄ የመጣው የኮሮና በሽታ አለም አቀፍ ወረርሽኝ ስለሆነ የሀገራት መሪዎችን ሌሎች የስራ ግዜዎች ተሻምቶአል::እኛም ጋ የሆነው ይሄ ነው::በሽታው እንዳይዛመት እንዳይስፋፋ የወሰዱት እርምጃ ሕዝቡን ያስተባበሩበትን መንገድ የሰጡትን አመራር አደንቃለሁ::እኔ የሠራዊቱ ከፍተኛ መኮንን የነበርኩ ነኝ::ጥልቅ የወገን ፍቅር ያለበት በሀገር ሰላምና አንድነት ጉዳይ ምንም አይነት ድርድር የማያደርጉ ቁርጠኛ ሰዎች የሚፈልቁበት ነው::በዚህ እኮራለሁ::በሁሉም መስክ ከጎናቸው ልንቆም ሊታገዙ የሚገባቸው መሪ ናቸው ብዬ አምናለሁ::ፈጣሪ ይርዳቸው ነው የምለው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደ አንድ ኢንቨስተር፤ ከፍተኛ መኮንን፤ የአስተዳደርና አመራር ሰው ሀገራችን በብዙ ችግሮች ተወጥራ ባለችበትና ቀሳፊ በሽታ ሀገራዊ ስጋት በሆነበት ሕዝብ ተጨንቆ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ምርጫና የሽግግር መንግስት የሚለውን የፖለቲከኞች ሀሳብ እንዴት ያዩታል ?
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፡- እኛ የወጣትነት እድሜያችንን በሙሉ ለዚህች ታላቅ ሀገር ሕልውናና መኖር ታላቅ መስዋእትነት የከፈልን ሰዎች ነን::ሀገር ለድርድርም ሆነ ለጨረታ አትቀርብም::ይህን ጥያቄ ለመመለስ ብዙ የፖለቲካ ምሁር መሆን አይጠበቅብንም፡፡ለሁሉም ነገር ለኢንቨስትመንቱ፤ ለልማቱ፤ ለምርጫውም ቢሆን የሀገር የሕዝብ ሰላምና ደህንነት ይቀድማል::
በዚህ ሰአት ሀገርና ሕዝብ በወረርሽኝ አደጋ ተጨንቀው መግቢያ መውጫ በጠፋበት፤ ስራው፤ ኢኮኖሚው በቀዘቀዘበት፤ ሁሉም በፍርሀት በተዋጠበት ሁኔታ ውስጥ ምርጫ ይደረግ ለማለት የሚከብድ ይመስለኛል::ሕዝብ የሀገሩን ሰላም በሰላም ወጥቶ ሰርቶ መግባቱን ነው የሚፈልገው::የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለያየ እምነት ቢኖረውም በአምላኩ ጽናት ያለው፤ ሩህሩህ፤ ቸር፤ አብሮ በመኖር የሚደሰትና በአለም ላይ ትሁት የሆነ ሕዝብ ስለሆነ ፈጣሪ ከምንም አይነት ችግር እንዲጠብቀውና ኢትዮጵያም ለዘለአለም ትኖር ዘንድ ታላቅ ጸሎቴና ምኞቴ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ሰፊ ቃለ ምልልስ እናመሰግናለን፡፡
የተከበሩ አቶ ተስፋዬ ወንድሙ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 27/2012
ወንድወሰን መኮንን