በትውውቅ ከመሸጥ እስከ ወጪ ንግድ

ገና በልጅነቷ ለዲዛይን እና ፋሽን ላይ ልዩ ፍቅር የነበራት የዛሬ የስኬት ዓምድ እንግዳችን፤ ዲዛይነር ሊዲያ ሚሊዮን ትባላለች። በቆዳ ምርቶች ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ታዋቂነትን አትርፋለች፤ ‹‹ሊኖ ማኑፋክቸሪንግ ፒ ኤል ሲ›› የተሰኘው ድርጅቷ በዚህ ሥራ ላይ ከተሰማራ አሥራ ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል።

የድርጅቱ መሥራች፣ ባለቤት እና ሥራ አስኪያጅ ዲዛይነር ሊዲያ፤ በልጅነቷ የተገዙላትን ያለቀላቸውን ልብሶች በመቁረጥ ዲዛይን ታደርግ ነበር። ልብስ ሰፊዎችን ‹‹በዚህ መልክ ስፉ›› እያለች በራሷ መንገድ መዘነጥ እና መልበስ መለያዋ እንደነበርም ትናገራለች። አንዳንዴ ራሷም ልብሶችን በመቆራረጥ በመርፌ እየሰፋች የተለየ ዲዛይን እያወጣች ትለብስ ነበር።

በአያት እጅ ነው ያደገችው። የአያት ልጅ ቅምጥል እንደሚባለው፤ ልብስሽን ቀደድሽ ብሎ የሚከሳት አልነበረም። ቤተሰቦቿ ንፁህ መልበስ ብቻ ሳይሆን፤ ፋሽን እንደምትወድ ስለሚያውቁ ውጪ የሚኖሩት አክስቶቿ እና አሜሪካ ይመላለሱ የነበሩት አያቷ በተደጋጋሚ የተለያዩ ፋሽን ልብሶችን ያመጡላታል። አንዳንዴ ሀገር ውስጥ ያሉ አክስቶቿም ግብዣ ሲኖራቸው፤ ልብስ ከመምረጥ ጀምሮ ሲዘገጃጁ፤ ‹‹ ይህን ልበሱ፤ ይህን አታድርጉ›› ትል ስለነበር፤ የማሰማመሩን ዕድል ለእርሷ ይለቁላት እንደነበር ታስታውሳለች።

አዲስ አበባ ተወልዳ ሻሸመኔ አያቶቿ እጅ አድጋለች። ሻሸመኔ አብዮት ጮራ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ተከታትላለች። በመቀጠል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በዛ ጊዜ ደስታ ሻሸመኔ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማረች ሲሆን፤ 11ኛ ክፍል ስትደርስ ግን ሻሸመኔ ከተማን ለቃ ወጣች።

መምህር አባቷ እርሷን እና ወንድሟን ለብሔራዊ ማጠቃለያ ፈተና እንዲያዘጋጁ በሚል አዲስ አበባ ገቡ። የ11ኛ እና 12ኛ ክፍል ትምህርቷን ደጅአዝማች ወንድራድ ትምህርት ቤት ተከታተለች።

ጎበዝ ከሚባሉ ተማሪዎች መካከል ትመደብ እንደነበር ዲዛይነር ሊዲያ ገልጻለች። ለእዚህም ጎበዝ ተማሪዎች ብቻ በሚማሩበት ክፍል መማሯ አንድ ማስረጃ ይሆናል። ሀገር አቀፍ የማጠቃለያ ፈተናን ከወሰደች በኋላ፤ ያስመዘገበችው ውጤት ኮሌጅ የሚያስገባት ቢሆንም፣ የምትፈልገውን መስክ ማግኘት ሳትችል ትቀራለች። የእሷ ፍላጎት የቴክኖሎጂ ዘርፍ ነበርና በማይክሮሊንክ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በሶፍት ዌር ኢንጂነሪንግ ትምህርቷን አጠናቀቀች።

ዲዛይነር ሊዲያ እንደምታስታውሰው፤ የራሷን ሥራ ሠርታ ገንዘብ ማግኘትን መሻት የጀመረችው ገና በልጅነቷ ነበር። አያቷ በነበራቸው አነስተኛ ሱቅ ውስጥ እሷ እና ታናሽ ወንድሟ ሲሠሩ አያቶቿ የማያቀርቧቸውን፤ እሷ ልትሸጥ የምትችላቸውን ዕቃዎች ሱቁ ውስጥ በማስገባት የራሷን ገቢ ለማግኘት ጥያቄ አቅርባ ይሁንታ አግኝታለች።

በ12 ዓመቷ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ሆና፤ አባቷን ለመጠየቅ አዲስ አበባ ስትመጣ፤ በዚህ መንገድ ዕቃ እየሸጠች ያጠራቀመችውን የራሷን ገንዘብ ትጠቀም እንደነበር ታስታውሳለች። የኮሌጅ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች የሚያምናት አጥታ እንጂ በራሷ ሥራ ለመጀመር ፈልጋም ነበር።

እንደተመረቀች ወዲያው ትዳር መሰረተች፤ ይሁንና ጋብቻው አልተሳካም። አንዲት ልጅ ወልዳ ከአጋሯ ተለያየች። ልጇን ያለ አባት ለማሳደግ ተገደደች። ለብቻዋ ልጇን ማሳደግ ውስጥ መግባቷ ግን ከብዙ ውሳኔዎቿ ወደ ኋላ አላስቀራትም።

ዲዛይነር ሊዲያ ኢትዮ ቴሌኮም እና መብራት ኃይል በተለያዩ ጊዜያት ተቀጥራ ሠርታለች። በትርፍ ሰዓቷ ስለአፕልኬሽን ሶፍትዌር በጥሩ መልኩ አስተምራለች። በኋላም መንግሥታዊ ባልሆነ የበጎ አድራጎት ድርጅት ተቀጥራ ሠርታለች።

‹‹ሠው ትምህርቱን ጨርሶ ከኮሌጅ ሲወጣ ተቀጣሪ መሆኑ ጥሩ ነው፡፡›› የሚል እምነት እንዳላት የምትናገረው ዲዛይነር ሊዲያ፤ ተቀጥሮ በመሥራት የሥራ ላይ መልካም ስነምግባሮችን ለምሳሌ ታዛዥነትን እና ሰዓት ማክበርን የመሳሰሉትን ለመረዳት ምቹ መንገድ ይሆናል ትላለች።

ከስምንት እስከ አስር ዓመት ተቀጥራ በመሥራቷ ደስተኛ መሆኗን ገልፃ፤ የመንግሥት፣ የግል እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆነ የበጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ በመሥራቷ ብዙ ነገር መማር እንዳስቻላት እና ልምዶችን እንዳገኘች ትናገራች።

ተቀጣሪነት ለማሰብም ሆነ ለመንቀሳቀስ እንዲሁም ውሳኔዎችን ከማስተላለፍ በተጨማሪ የጊዜ እና የገንዘብ ገደብ አለበት ስትል ጠቅሳ፣ በሌሎች ወይም በሰዎች ውሳኔ እና ዕቅድ እስከ መጨረሻው መዝለቅ እንደሚከብድም አስታውቃለች፡፡

ዲዛይነር ሊዲያ፤ ‹‹እኔ ገደብ አልፈልግም። በተለይ ውሳኔ መስጠት ላይ ልክ ነኝ ብዬ የማምንበትን እንዳልወስን የሚያደርጉ ነገሮች አይመቹኝም፡፡›› ትላለች። በመጨረሻም መንግሥታዊ ያልሆነ የበጎ አድራጎት ድርጅት ተቋም መሥራቷ፤ የአሁኑን ከ42 ሰራተኞች በላይ ቀጥራ የምታሠራበትን ድርጅት ለመጀመር ምክንያት እንደሆናት ትገልጻለች።

እሷ እንዳለችው፤ መንግሥታዊ ያልሆነ የበጎ አድራጎት ድርጅት ስትሠራ ፕሮጀክታቸው አፋር ክልል ነበር። አንዳንዴ 48 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ድረስ የሚዘልቅ ከባድ ሙቀት ባለበት በዚህ አካባቢ ሙቀቱን ተቋቁማ ሠርታለች።

በተደጋጋሚ ፈታኙን የአየር ሁኔታ እና ርቀቱን ተቋቁማ እየቆየች ስትመጣ፤ ጥንካሬዋን በደንብ ተገነዘበች። ከባዱን ሁኔታ በሥራ መወጣት መቻሏ፤ በግል ሥራ ላይ የሚያጋጥም ማንኛውም ሊከብድ የሚችል ነገር ልትወጣው እንደምትችል እያረጋገጠላት መምጣቱን ገልጻለች። በእንደዛ ዓይነት አድካሚ ሁኔታ ውስጥ መሥራቷ፤ የራሷን ሥራ ለመሥራት እንድትወስን ትልቅ አቅም በመሆን አገልግሏታል።

ሥራ ለቅቃ የራሷን የግል ሥራ ስትጀምር፤ ‹‹ አንድ ልጄን ማሳደጊያ ባጣስ? ምን አደርጋታለሁ?›› የሚል ስጋት ነበረባት። ሆኖም ይህ ስጋቷ ከተስፋዋ የሚበልጥ አልነበረም። ኢትዮጵያ ውስጥ የትኛውም ችግረኛ የሚያድርበት ቢያጣ የሚጎርሰውን አያጣም በሚል እምነት፤ እሷ በዚህ ደረጃ እንደማትወርድ አስባ መልቀቂያ ወሰደች። የምትሠራውን ለመለየት ማጥናት ጀመረች።

ዲዛይነር ሊዲያ እንደምትናገረው፤ የሚወድቀው ሥራ የማይወድ ነው፤ ታታሪን ፈጣሪ አይጥልም ብላ በማመኗ ያለመቀጠር ውሳኔዋን አጸናች። ከሥራ ወጪ ሆና ሌላ ምንም ገቢ ሳይኖራት በቀጣይ የምትሠራውን ማጥናት ውስጥ ብትገባም፣ ልትሠራበት ያሰበችው ገንዘብ ቀስ በቀስ ከእጇ እየወጣ መሆኑ ታሰባት።

ወደ ሥራ ልትገባ በሰነችበት ወቅት እጇ ላይ ምንም ገንዘብ አልነበራትም። ይህንንም እጇ ላይ የነበሩትን ወርቆች በመሸጥ ለመሻገር ጥረት አድርጋለች። ለመኖሪያነት በተከራየችው ግቢ ውሰጥ ማሽኗን እና ጥሬ እቃውን እንዲሁም ለአንድ ሠራተኛ ለሁለት ወር ደሞዝ መክፈል የምትችልበትን ብር ይዛ ሙሉ ጊዜዋን ሥራዋ ላይ ማዋል ጀመረች፡፡

ዲዛይነሯ በቅጥር ሕይወቷ ከባድ ችግሮችን ስትቋቋም በመቆየቷ እና ፈጣሪዋን በማመኗ ሁሉንም ፈተናዎች አልፋ እንደተሳካላት ትናገራለች።

ከሥራዋ ጎን ለጎን የመንግሥትን ድጋፍ እየጠየቀች በቅድሚያ በዙሪያዋ የሚያውቋት ሰዎች እና ሥራዋን የሰሙ ሌሎች ሰዎች ምርቶቿን ይገዟት ጀመር ። ሱቅ ተከራይታ መሸጡን ተያያዘችው፤ ሥራው በዚህ አላቆመም፤ ወደ ወጪ ንግድ አደገ።

ብዙ ሠራተኞችን መቅጠር ጀመረች። 68 ሠራተኞችን ቀጥራ ስታሠራ፤ የኮረና 19 ወረርሽኝ ተከሰተ። ወረርሽኙ የተወሰኑ ሠራተኞች እንዲቀነሱ ምክንያት ሆነ፤ እሷ ግን እጇን አልሰጠችም፤ በድጋሚ አገገመች። የሠራተኞቿም ቁጥር እስከ 82 ደረሶም ነበር።

ሆኖም ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ላይ በደረሰ ጫና በተለይ ከአሜሪካ ጋር በተፈጠረው ክፍተት ብዙዎች እንደተዳከሙ ሁሉ፤ የእሷም ድርጅት አሉታዊ ተጽእኖ ደረሰበት። ድርጅቷ በተወሰነ መልኩ ተዳከመ። የደንበኞች ቁጥር ቀነሰ፡፡

አሁን ስድስት ወንዶችን እና 36 ሴት ሠራተኞች በአጠቃላይ 42 ሠራተኞችን ይዛ እየሰራች ትገኛለች። 80 በመቶ የሚሆኑ ምርቶቿ ለአሜሪካ ገበያ የሚቀርቡ ናቸው፤ ምርቶቿን ወደ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካም ትልካለች።

ዲዛይነር ሊዲያ እንደምትናገረው፤ ከአሜሪካ ጋር ተያይዞ ያጋጠማት ችግር ብቻ አልሆነም፤ መልካም አጋጣሚም ፈጠረላት፤ የሌሎች ሀገሮችንም ገበያ ለማየት ዕድል ከፈተላት። ስለዚህ ወደ ሌሎች ሀገሮችም ምርቷን ለመላክ እያጠናች ትገኛለች።

ብዙዎች ባለማወቅ ብዙ ዕድሎች እንደሚያመልጣቸው በመጠቆም፤ እሷ አስቀድማ ቴክኖሎጂ መማሯ ሥራዋ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ እንደረዳት ትናገራለች። ቴክኖሎጂው የመግባባት ችሎታዋን እንደጨመረው እንዲሁም በዘርፉ ላይ ሊረዱ እና ሊያግዙ የሚችሉ መንግሥታዊም ሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ለመፈለግ እና ብዙ ዕድሎችን ለመጠቀም እንዳገዛት ታብራራለች።

የውጪ ገዢዎች ሲመጡ እና በኢሜል መልዕክቶች ሲላኩ ወዲያው መመለስ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሳ፤ ለማደጓ ሌላኛው ምክንያት መማሯ መሆኑን ጠቅሳለች።

ማኑፋክቸሪንግ በባህሪው በጣም ዕልህ አስጨራሽ እና አድካሚ መሆኑን የምትናገረዋ ዲዛይነር ሊዲያ፤ አንድ ምርት ለማውጣት ምናልባት እስከ አስር ግብዓት ሊያስፈልግ ይችላል ስትል ትገልጻለች።

ይህም ሥራውን ከባድ እንደሚያደርገው በማመልከት፤ ቆዳ እዚህ ሀገር መገኘቱ መልካም ዕድል ቢሆንም፣ ሌሎች ግብአቶች ከውጪ እንደሚመጡ እና አልፎ አልፎ የጥራት ችግር እንደሚያጋጥም ጠቁማለች፡፡

እሷ እንደምትለው፤ በውጪ ምንዛሪ ችግር ምክንያት የዘርፉ ግብዓት አስመጪዎች የሉም ማለት ይቻላል። ገበያ ላይ አንድ አስመጪ ብቻ ነው ያለው፤ ግብዓት ለማግኘት ሽሚያ ነው። ይህ አንደኛው ፈተና ነው፤ በሌላ በኩል ሥራው ገንዘብ ይፈልጋል፤ ገንዘብ ማግኘት አስቸጋሪ ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሀገሪቱ የፋይናንስ አሠራር ምቹ አለመሆኑን ስታስረዳ፤ ‹‹ ወደ ተለያዩ ሀገራት ስሔድ፤ የምሠራቸውን ናሙናዎች ይወዷቸዋል። ሆኖም ‹10 ሺህ ወይም 50 ሺህ ሰርተሽ አምጪ› ሲሉ ምላሽ መስጠት አልችልም። ምክንያቱም 50 ሺህ ቦርሳ ለመሥራት ብፈራረም። የተፈራረምኩትን ውል አይቶ ገንዘብ የሚያበድረኝ ባንክ የለም›› ትላለች። ባንክ ማስያዣ ከመጠየቅ ውጪ ፕሮጀክት ወይም የውል ስምምነት አይቶ ብድር አይሰጥም ስትል አመልክታለች፡፡

ይሄ ኢንዱስትሪው በሚፈለገው መጠን እንዳያድግ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ መሆኑን ገልፃ፤ ከፋይናንስ እና ከግብዓት እጥረት ውጪ ያሉ የቦታ ችግሮችን በተመለከተ ገና ሥራውን ስትጀምር መጠየቅ የጀመረችው ዲዛይነር ሊዲያ፤ መንግሥት ከታች ጀምሮ ሥራዋን ባሰፋች ቁጥር የተሻሉ ቦታዎችን በመስጠት ድጋፍ እንዳደረገላት ገልፃለች፡፡

ሀገር በቆዳ ኢንዱስትሪም ሆነ በሌሎች ማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች የተሻለ ተጠቃሚ እንድትሆን፤ የፋይናንስ አቅርቦት በተለይ ፕሮጀክቶችን በማየት እና ውሎችን በማረጋገጥ ብድር በማመቻቸት ዙሪያ ሠፋፊ ሥራዎች መሠራት አለባቸው። ለምርት የሚያገለግሉ ግብዓቶችን በተመለከተ የውጭ ምንዛሪ ላይም ሆነ ሌሎች አማራጭ ግብዓት የሚገኙባቸው ሁኔታዎች ላይ መሠራት እንዳለበት አስገንዝባለች።

በምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You