
በባለፈው ወር የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኢኒስቲትዩትና የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በጋራ ባዘጋጁት 4ኛው የክህሎት ውድድር ላይ በርካታ የፈጠራ ውጤቶች ቀርበዋል፡፡ ከእነዚህ መካካል በከፍተኛ ወጪ ከውጭ ሀገር የሚገቡ ማሽኖችን መተካት የሚችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ይገኙበታል፡፡
በዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዓምዳችን በውድድሩ የቀረቡ የእህል ወፍጮና የእንጨት ቅርጽ ማውጫና መሰንጠቂያ የፈጠራ ውጤቶችን ይዘን ቀርበናል፡፡
ይስማው ወያማ ሀዋሳ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የመካኒክ ክፍል ሰልጣኝ ነው፡፡ የተለያዩ የእህል ዓይነቶችን የሚፈጭና የሚከካ ማሽን ሰርቶ በመድረኩ ተገኝቷል፡፡ ማሽኑን እንዲሰራ መነሻ የሆነው በገጠር አካባቢ የሚኖሩ እናቶች እህል ለማስፈጨት ራቅ ወዳለ ቦታ የሚያደርጉት ጉዞ ነው፡፡ እነዚህ እናቶች እህሉን በጀርባቸው ተሸክመው ረጅም መንገድ መጓዛቸው የዕለት ተዕለት ኑሮአቸው አንድ አካል ስለመሆኑ ከልጅነቱ ጀምሮ ሲመለከተው ኖሯል፡፡
ይስማው እነዚህ እናቶች ችግሩ አብሮአቸው የኖረና አንዳንድ አካባቢዎች ላይ አሁንም የቀጠለ መሆኑ በእጅጉ አሳስቦት ለችግሩ መፍትሔ ለማምጣት ሲያስብና ሲያሰላስል ቆይቶ፤ ብዙ ችግሮችን በአንድ ሊፈታ የሚችል ማሽን ለመስራት ወስኖ ወደ ፈጠራ ስራው እንደገባ ይገልጻል፡፡
ሀሳቡን ለሌሎች ጓደኞቹና ለመምህሮቹ አማክሯል፤ ይሁንና እንዳሰበው ሥራውን ለመጀመር ቀላል አልሆነለትም፡፡ የዚህ ምክንያቱ በኮሌጁ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ መሆኑን በመጥቀስ ትንሽ ቆይ የሚል ምላሽ ማግኘቱ ነው፡ እሱ ግን ውስጡ ያለውን ሀሳብ እስካላወጣ ድረስ እንቅልፍ ሊወሰድው አልቻለም፤ ሀሳቡን ወደ ተግባር ለውጦ እውን ለማድረግ ትግልና ጥረቱን ተያያዘው፡፡ ያሰበውም ተሳካለት፤ ያለመውን ዓይነት ማሽን ሰርቶ አሳየ፡፡
ማሽኑን ለመሥራት ያደረገው ጥናት የእናቶችን ልፋት ከመቀነስ በተጨማሪ ማሽኑን አህሉ ጤንነቱ በተጠበቀ መልኩ እንዲፈጭ ማድረግ የሚያስችል አርጎ እንደሰራው ይገልጻል፡፡ በተለይ ከስድስት ዓመት በታች ያሉ ህጻናትን ምግቦች መፍጨትና መከካት እንዲችል አርጎ ማሽኑን መስራቱን ይናገራል፡፡
ማሽኑ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ጤፍና የመሳሳሉትን እህሎች መፍጨት ወይም መከካት እንደሚያስችል ያመላክታል፡፡ ማሽኑ በአንድ ሰዓት ተኩል ጊዜ ውስጥ ሁለት ኩንታል በቆሎ ይፈጫል፡፡ ሌሎችንም እንዲሁ ከዚህ ባነሰ ሰዓት መፍጨት ይችላል ሲለም አብራርቷል፡፡
ይስማው እንዳብራራው፤ ይህ ማሽን በገጠር የሚኖሩ እናቶችን ችግር የሚፈታ ብቻ ሳይሆን በተለምዶ አገልግሎት እየሰጠ ያለውን በድንጋይ ወፍጮ የሚሰራ ማሽን መቀየርንም ያለመ ነው፡፡ ማሽኑ የተሠራባቸው ቁሳቀስ በተለምዶ ከሚታወቀው ከድንጋይ ወፍጮው ይለያሉ፤ በጤና ላይም ምንም ዓይነት ጉዳት አያስከትሉም፡፡
የተሰራውም ከወዳደቁ ቁርጥራጭ ብረቶች ሲሆን፣ ዲናሞና የኢንዱስትሪ ሶኬት ለመግዛት ብቻ ወጪ ተደርጎበታል፡፡ አነስተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ይጠቀማል፡፡ ኤሌክትሪክ ባለባቸው ገጠራማ አካባቢዎች ለቤት ውስጥ ፍጆታ በሚውል ቀላል የኤሌክትሪክ ኃይል ማሽኑን ማሰራት ይቻላል፡፡ መብራት በሌለባቸው አካባቢዎች ደግሞ በጀነሬተርና በሶላር እንዲሰራ ተደርጓል፡፡
ከውጭ የሚገባው ማሽን መፍጫው ድንጋይ ከመሆኑም በላይ መፍጨትና መከካትን በአንድ ላይ እንደማይሰራ ተናግሮ፤ ሁሉንም ዓይነት እህሎች በአንድ ላይ የሚፈጭም እንዳልሆነም ይስማው ይገልጻል፡፡ ጥራቱን ጠብቆ የተሰራ በመሆኑም የሚፈጨውም ሆነ የሚከካው እህል ለህጻናት ምግብነት መዋል እንደሚችል ጠቁሟል፡፡
ዋጋውም 70 ሺ ብር መሆኑን ጠቁሞ፣ ተመጣጣኝ የሚባል ዋጋ መሆኑን ተናግሯል፡፡ በሀገር ውስጥ ከሚገኙ ቁሰቀስ መሰረቱ ዋጋው በጣም ተመጣጣኝ እንዲሆን እንዳደረገው ጠቅሷል፡፡
‹‹ማሽኑ ሁሉንም የእህል ዓይነቶች መፍጨትና መከካት የሚችል ስለመሆኑም በፍተሻ መረጋገጡን ተናግሯል›› የሚለው ሰልጣኝ ይስማው፤ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እያደረገ እንደሆነ አመልክቷል፡፡ በተለይ በገጠር አካባቢ ለሚኖሩ እናቶች ማሽኑ ተደራሽ ቢደረግ በተለይ እናቶችን ከብዙ ድካም እንደሚታደጋቸው ይገልጻል፡፡ ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ ቢያደርጉ መልካም መሆኑን ጠቁሟል፡፡
ወደፊትም ችግር ፊቺ የፈጠራ ሥራዎችን በመሥራት የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት ብዙ ማቀዱን የሚናገረው ሰልጣኙ፤ በመካኒክ ሙያ ክህሎት ውድድር ከክልሉ አንደኛ መውጣቱን አስታውቋል፡፡ ያለውን ክህሎት ተጠቅሞ ለሀገር የሚጠቅሙ ብዙ ፈጠራዎች እንዲሚስራም ጠቁሟል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሉ የሚዛን ቴፒ ኢንተርፕራይዝ ሌላው በመድረኩ ለውድድር የቀረበ ተቋም ነው፡፡ የኢንተርፕራይዙ ባለሙያ አቶ ነስረዲን አሕመድ እንደሚለው፤ ኢንተርፕራይዙ ‹‹ኮምቢኔሽን ኦፍ ውድ ሌዝ ማሽን›› ( ሁለት ሥራ የሚሰራ የእንጨት ማሽን) ሰርቷል፡፡ ማሽኑ የእንጨት ቶርኖ (የእንጨት ጌጥ) ለማውጣትና ለመሰንጠቅ ያስችላል፡፡
የእንጨት ቶርኖ፤ ለፎቅ ደረጃዎች ፣ ለወንበርና ለጠረጴዛ እግር፣ ለኮርነር ቴብል፣ አልጋ አናት ላይ ለሚቀመጡ ጌጦች እና ለመሳሳሉት እንጨቶች የተለያዩ ቅርጾችን የሚያወጣ ነው፡፡ ሙቀጫ ፣ ገበቴ፣ የቡና ማቅረቢያ የመሳሳሉትንም በተለያየ ውፍረትና ቅርጽ ለማምረትም ይጠቅማል፡፡
ማሽኑ ከሌሎች ተመሳሳይ ማሽኖች ለየት የሚደርጉት ብዙ ባህሪዎች እንዳሉትም ነስረዲን አመልክቷል፡፡ አንደኛው ልዩ የሚያደርገው የእንጨት መስንጠቂያ የተገጠመለት መሆኑ ነው ሲል ጠቅሶ፣ ሁለተኛው ደግሞ የሚጠቀመው ዲናሞ አራት የፈረስ ጉልበት መሆኑ ነው ይላል፡፡
2900 አርፒኤም ያለውና በጣም ፈጣን መሆኑ መሆኑን ተናግሮ፣ በፋብሪካዎች የሚመረቱት ማሽኖች 1400 አርፒኤም እንዳላቸው አስታውቋል፡፡ ፍጥነታቸውም መካለለኛ መሆኑን አመልከቷል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት መስንጠቂያው በቀጥታ እስከ 10 ሳንቲ ሜትር የሆነን እንጨት በቀላሉ መስንጠቅ እንዲችል ተደርጎ በመሰራቱ ነው ብሏል፡፡
እሱ እንዳብራራው ፤ በተጨማሪም ወፍራም እንጨት በሚሰነጥቅበት ጊዜ ማሽኑን በኮንክሪት መሬት ላይ መትከል ሳያስፈልግ በራሱ ሚዛኑን ጠብቆ መስራት ይችላል፡፡ የፋብሪካው ማሽን በኮንክሪት ተደርጎ መሬት ላይ ካልተተከለ በስተቀር በራሱ ቆሞ መስራት አይችልም፡፡ በተለይ እንጨቱ ወፋራም ሲሆን ይንቀጠቀጣል፡፡ የዚህ አንዱ ምክንያት የተሰራበት ብረት ጠንከራ ስላልሆነ ነው፡፡
ይህ ማሽን የተገጠመሉት ብረትና ዲናሞ በሚሰራበት ጊዜ ጉልበቱን የተመጣጣነ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ማሽኑ የትኛውም ቦታ ላይ ቢቀመጥ ያለምንም መንቀጥቀጥ በቀላሉ መስራትም ይችላል፡፡ መሰንጠቂያው አደጋ እንዳይፈጠር የራሱ ክዳን ተሰርቶለታል፡፡
ሌላው ማሽኑን ከሌሎቹ በጣም ለየት የሚያደርገው የፋብሪካው ማሽን 50 ሳንቲ ሜትር ቁመት ያለውንና አምስት ሳንቲ ሜትር ጎን ያለውን የወንበር እግር በሰዓት ስምንት ቢበዛ አስር ቢያመርት ነው፡፡
ይህ ማሽን ግን ዘገምተኛ ከሆነ በሰዓት 24 የወንበር እግሮች ፤ፈጣን ከሆነ 30 የወንበር እግሮችን ይሰራል፡፡ በሁለት ደቂቃ አንድ የወንበር እግር ያወጣል፤ የጠረጴዛ እግር ቁመቱ 80 ውፍረቱ 8 ሳንቲሜትር የሆነ የጠረጴዛ እግር በአንድ ሰዓት ውስጥ 18 ማምረት ይችላል፤ በጣም ፈጣን ነው፡፡
የቻይና ወይም የፋብሪካው ማሽን የጠረጴዛ እግር ለመስራት ይንቀጠቀጣል፤ ይቸገራል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የጤረጴዛ እግር ረጅምና ወፍራም ስለሆነ ነው ሲል አብራርቷል፡፡
ማሽኑ እስከ አንድ ሜትር ቁመት ያለውን ማንኛውንም እንጨት ቅርጽ በቀላሉ ማውጣት እንደሚችል አቶ ነስረዲን ተናግሯል፡፡ አስራ ስምንት ሳንቲ ሜትር ራዲየስ ወይም 36 ሳንቲሜትር ርዝመትና ወፍረት ያለውን እንጨት ሙቀጫ አድርጎ መስራት እንደሚችልም ያመላክታል፡፡
ኢንተርፕራይዙ በሌሎች ማሽኖች ላይ ከገጠሙ ችግሮች በመነሳት መፍትሔ ለመፈለግ በተደረገ ጥረት ይህ ማሽን መሰራቱን ይናገራል፡፡ ቀደም ሲሉ ከውጪ የሚገባውን ማሽን ገዝተው ይሰሩ እንደነበረ ጠቅሶ፣ የማሽኑ የዲናሞ መጠን 0ነጥብ 5 ኤችፒ እንደሆነና በስራ ላይ እያለ እየቆመ እንደሚያስቸግር አመልክቷል፡፡
በዚህ ዓይነቱ ማሽን አንድ ሥራ ለመሥራት በጣም ረጅም ጊዜ እንደሚወሰድ ተናግሮ፣ በፍጥነት አቀላልጥፎ ለመስራት እንደማያስችልና ትዕዛዞችን በወቅቱ ለማድረስም እንደሚያስቸግር አስታውቋል፡፡
‹‹ 200 የወንበር እግሮችን በሁለትና በሦስት ቀናት እንድናቀርብ ትዕዛዝ ተጠይቀን ከአምስት እስከ አስር ቀናት ባሉት ጊዜያት ሊፈጅብን ይችል ነበር፤ ይህ ማሽን ግን በስምንት ሰዓት 160 የወንበር እግሮች መስራት አስችሎናል›› ሲል አብራርቷል፡፡
ነስረዲን እንዳስታወቀው፤ የፋብሪካው ማሽን ወፍር ያለ እንጨት ሲሰጠው ይንቀጠቀጣል፡፡ በሚስማር ተወጥሮ ግርግዳ ላይ ተመትቶ ነው የሚሰራው፡፡
አዲሱ ማሽን ግን ለዚህ መፍትሔ ለማምጣት ታስቦ የተሰራ በመሆኑ ያለምንም ችግር ይሰራል፡፡ ይህንን ሁሉ ችግር ሊቀርፍ የሚችልና በብዙ መልኩ ከውጭ ከሚገባው የተሻለ ነው፤ ጊዜንም በጣም ይቆጥባል፡፡ በዚያኛው ማሽን የሚፈለገውን ያህል ሰርቶ መለወጥ ይከበዳል፡፡ በአዲሱ ማሽን ግን በአንድ ጊዜ ብዙ መስራት ከመቻሉም በላይ በከፍተኛ ሁኔታ በማምረት ጥሩ እንድንስራ አድርጎናል ይላል፡፡
አንድ ማሽን ከተሰራ ቀጥሎ ያለውን ማሽን መስራት በጣም ቀላል ነው የሚለው ነስረዲን፤ በመጀመሪያው ማሽን ላይ ያሉ ክፍተቶችን በመለየት በቀላሉ አሻሽሎ ሁለተኛውን ማሽን መስራት እንደሚቻል ጠቁሟል፡፡
ይህ ማሽን ወደ ገበያ ሳይወጣ ስድስት ወራት ስለቆየ የተለያዩ ማስተካከያዎች ስናድርግበት ቆይተናል የሚለው ነስረዲን፤ ይህም ሂደት ብዙ ሙከራ ውስጥ ስለሚያልፍ ሁለት ዓመታትን ፈጅታል ብሏል፡፡
እሱ እንዳለው፤ ማሽኑ ተፈትሾ ጥራቱ መረጋገጡን ተከትሎ ኢንተርፕራዙ ሦስት ማሽኖችን በመሰራት ለሌሎች ኢንተርፕራይዞች ሸጦ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ ይህን ማሽን ተጠቅመው በመስራት ሌሎች ማሽኖችን ለመግዛት ጥሩ ደረጃ ላይ የደረሱ አሉ፡፡ ኢንተርፕራይዙ አሁን ሉሎች ተጨማሪ ትዕዛዞች ተሰጥተውታል፡፡ በቀን እስከ 160 እግሮችን፣ ከተቻለም ከዚህ በላይ ውጤታማ ሥራዎችን ለመሥራት እንደሚቻል ጠቁሟል፡፡
የኢንተርፕራይዙ ባለሙያ አቶ ነስረዲን እንዳብራራው፤ ማሽኑ የሚሸጥበት 70 ሺ ብር የህብረተሰቡን የመግዛት አቅም ያማከለ ነው፣ የፋብሪካው ማሽን ዋጋ አነስተኛው 50ሺ ብር፤ ትልቁ ደግሞ 250ሺ ብር ነው፡፡ ትንሿ አትስራም ማለት ይቻላል፡፡ ከአዲሱ ማሽን ጋር ተመጣጣኝ ሥራ ሊሰራ የሚችለው ባለ250ሺ ብሩ ነው፡፡
ቶርኖ ማሽን ያለው የግድ መሰንጠቂያ ማሽን ያስፈልገዋል፡፡ ይህን መስንጠቂያ ማሽን ለመግዛት 140ሺ ብር ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን ሁለቱን ማሽኖች በአንድ ላይ የያዘው ማሽን ነው በዚህ ዋጋ ለገበያ የቀረበው፡፡
‹‹ የሀገር ውስጥ ምርቶች በአብዛኛው በጥራትና በአጨራረስ ላይ ችግር አለባቸው ሲባል እየሰማን ነው የመጣነው፤ ይሄ የተለመደ አነጋገር ነው›› የሚለው ነስረዲን፤ ሥራዎቹ በባለሙያ ከተሰሩ፣ ባለሙያው በትምህርት ያገኘውን እውቀት ተግባራዊ ስለሚያደርግ እምብዛም ችግር አይገጥምም ብሏል፡፡
ማሽኑ የተሰራው ጥራት ካላቸው ብረቶች እንደሆነ ገልጾ፣ ወደ አምራቾች የተላለፉት ማሽኖች ውጤታማ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡ ‹‹በማሽኑ እኛ እያመረትንም ማሽን እየሸጠን ነው፤ በብዙ መልኩ ተጠቃሚ ሆነናል፤ ይሄ ማሽን ብንሸጠውም ብንሰራበትም ካፒታላችን ነው›› ሲል ገልጸል፡፡
ኢንተርፕራይዙ በቀጣይም ይህንን ማሽን ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ማሽኖችን በስፋት ለመስራት ማቀዱን ናስረዲን ጠቁሟል፡፡ አሁንም ‹‹በአንድ ሰው›› የተሰኘ የግንድ መሰንጠቂያ ማሽን በጣም ጥራት ባለው መልኩ መስራት ጀምረናል ሲልም አመልክቷል፡፡ የዚህ ማሽን ዋጋ ገበያ ላይ ሁለት ሚሊዮን ሁለት መቶሺ ብር መሆኑንም ተረድተናል ይላል፡፡
የተሻለ ቁሳቁስ ተጠቅመን የምናመርው እንደመሆኑም የኛ ማሽን ከውጭ ከሚመጣው በብዙ መልኩ ይሻላል ሲል አብራርቶ፤ ይህንንም ማሽን በሀገር ውስጥ አምርተን ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ማዋል አለብን›› የሚል ጽኑ እምነት አለን ሲል አስታውቋል፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2017 ዓ.ም