የሸማኔው ባለውለታ

ችግር ለመፍታት መፈጠራቸውን አምነው፤ የሰውን ልጅ አኗኗር ለማሻሻል በሚተጉ ሰዎች ዓለም በብዙ መልኩ ተቀይራለች። ጨለማን በመግፈፍ ብርሃን ለማጎናጸፍ አምፖልን በፈጠረው ቶማስ ኤድሰን፤ ስልክን በመፍጠር ዓለምን ባገናኘው ኢንጂነሩ አሌክሳንደር ግርሃም ቤል፣ ዓለምን በአዲስ መልክ እስከ መፍጠር ደረሱ የተባለላቸው አሜሪካውያኑ ወንድማማቾች የአውሮፕላን ፈጣሪዎች ዊልበር እና ኦልቪር ራይት ባበረከቱት ቴክኖሎጂ የሰው ልጅና ዓለም በብዙ መልኩ መለወጥ ችለዋል።

እነዚህ የድንቅ ፈጠራ ሥራዎች ባለቤቶች ቢያልፉም የፈጠራ ሥራዎቻቸው ትልቅ ትርጉም በማስገኘታቸው ስማቸው በወርቅ መዝገብ ተፅፎ፤ ሥራቸው ብቻ ሳይሆን ታሪካቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ ይገኛል።

አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እያበረከቱ የሰዎችን ሕይወት በማቃለል፤ የተፈጠሩበትን ዓላማ ግብ የመቱ ሰዎች በብዙ እየተመሰገኑ ሥራቸው እና ታሪካቸው ዘመናትን አልፎ የሰውን ልጆች እያገለገለ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገረው የፈጠራ ሥራውን የፈጠራ ባለቤቱ ብቻውን አንድ፣ ሁለት እያለ እያባዛ ወይም እያመረተ ለገበያ በሚያቀርብበት መንገድ አይደለም፤ በሌሎች አካላት በስፋት ተባዝተው በመላ ዓለም መሠራጨት ሲችሉ ነው።

የፈጠራ ሰዎችን ግኝት አባዝተው ለዓለም ለማበርከት አስበው በሚሠሩ አካላት፤ ከላይ የተጠቀሱት የድንቅ ፈጠራ ውጤት ባለቤቶች በተፈጠሩባቸው እንደነአሜሪካ እና ካናዳ የመሳሰሉ ሀገሮች ላይ የተወለደ ሰው ግኝቶችን መፍጠር ከቻለ፤ የፈጠራ ውጤቶችን በስፋት አምርቶ ለመላ ዓለም ማዳረስ እጅግ ቀላል ነው። ምክንያቱም የማባዛት ኃላፊነትን የሚወስደው ሌላ አካል ነው። የፈጠራ ባለሞያ የሥራው ባለመብት ሆኖ ማግኘት ያለበትን ገቢ ያገኛል፤ ግኝቱ ለዓለም ይበተናል።

አፍሪካ ውስጥ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ድሃ ሀገራት ተወልዶ የፈጠራ ባለሞያ ለመሆን በራሱ ትልቅ ትጋትን ይጠይቃል። ፈጥሮ መገኘት ደግሞ ትልቅ ስኬት ነው።

በልጅነቱ የወገኑን ድካም ለማቃለል እየተመኘ ያደገው ቻላቸው ሰጠኝ፤ ጎንደር ተወልዶ አዲስ አበባ ሲያድግ ነገሮችን የሚረዳበት መንገድ ከሌሎች ልጆች የተለየ እንደነበር ያስታውሳል። እንደ ጓደኞቹ ኳስ መጫወት ወይም ልቦለድ ማንበብ አልነበረም የእርሱ ትኩረት። ሥራዎች በቀላሉ የሚከወኑባቸው ሁኔታዎችን ማሰላሰል ላይ የተመሠረተ ነበር።

ነገሮች ያለብዙ ድካም እንዲሠሩ ቀላል ማሽኖች መሠራት አለባቸው የሚል ፅኑ እምነት ያለው ቻላቸው፤ ሕዝቡ እና ሀገር ምድሩ የእርሱ እንደሆነ አምኖ፤ ሰዎች ትንሽ ነገር ለመሥራት ረዥም ጊዜ ሲወስድባቸው እና ከፍተኛ ጉልበት ሲያባክኑ ይበሳጫል።

ሥራ በአነስተኛ ጉልበት በጥቂት ደቂቃ የሚሠራበት መንገድ እንዲኖር ይፈልጋል። ገና በልጅነቱ የመኖሩን ትርጉም በሚያሳይ መልኩ ሰዎች ለመሥራት የተቸገሩበትን ሁኔታ አይቶ፤ ‹‹ይህንን በዚህ በቀላሉ ብትሠሩት›› ይል ነበር። የሚሰሙት ይጠቀማሉ። አንዳንዶች ሃሳቡ አስደንግጧቸው እና ልጅነቱን አይተው ሲያገሉት በዝምታ ያልፋቸዋል።

ጎንደር ተወልዶ ለተወሰነ ጊዜ በለሳ የቆየው ቻላቸው፤ አዲስ አበባ ተምሮ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ነጥብ በማስመዝገብ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን ይቀላቀላል፤ ማሽን በመሥራት የወገኑን ችግር ለማቃለል በማሰቡ፤ መካኒካል ኢንጂነሪንግ መማርም ይጀምራል። የመጀመሪያ ዲግሪውን ለማግኘት ጥናት ሲያካሂድ፤ ለመመረቂያው ኅብረተሰቡን የሚጠቅም ነገር ለመሥራት ሲያስብ፤ በአጋጣሚ ባሕላዊ የሽመና ላብራቶሪን ተመለከተ።

ሸማኔዎቹ ያሉበት ቦታ በመሔድ ሁኔታዎችን አጠና። በእጃቸው እየፈተሉ፤ በአጥር ላይ ተመላልሰው እያዳወሩ፣ በእጃቸው እና በእግራቸው እያጠነጠኑ በብዙ ድካም እንደሚሠሩ አረጋገጠ። በእጅ እና በእግራቸው በብዙ ድካም ሲሠሩ ሲያይ፤ ድካማቸውን ለማቃለል ተመኘ። መመኘት ብቻ ሳይሆን የሸማኔውን ድካም ለማቃለል እስከ መጨረሻው ለመታገል ወሰነ።

‹‹በ1997 ዓ.ም የ3ኛ ዓመት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁ ስለመመረቂያ ፕሮጀክት እያሰብኩ ሸማኔዎችን የማገኝበት አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡›› ይላል። አንድ ቀሰም ላይ የሚፈጁትን ጊዜ ሲያይ በጣም መገረሙን አስታውሶ፤ በቀላሉ በአንድ ጊዜ በብዙ ቀሰም ላይ መሥራት የሚችሉበትን ሁኔታ በተመለከተ ማሰብ ይጀምራል። ለመመረቂያነት በቅድሚያ የክር ማጠንጠኛ ማሽን በመሥራት፤ በአንድ ቀሰም ይሠራ የነበረውን በአንድ ጊዜ ብዙ ቀሰም ላይ የሚሠራበት ሁኔታ ላይ ጥናት በማካሄድ ፕሮጀክቱን አጠናቆ ለመመረቅ መብቃቱንም ይገልጻል።

ሙሉ ጊዜውን ማሽን በመሥራት በምርምር ሥራ ላይ ማሳለፍ ቢፈልግም፤ ማሽን ለመሥራት መመራመር ብቻውን ገቢ አያስገኝምና ጎን ለጎን ሌሎች ገቢ የሚያስገኙ አማራጮችን ለማየት ይገደዳል።

ከባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ በመካኒካል ኢንጂነሪንግ በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀ በመሆኑ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በረዳት መምህርነት ተቀጠረ። ይህም የምርምር ሥራውን ለመቀጠል ምቹ ሁኔታ ፈጠረለት። በከፊል ክር ታጠነጥን የነበረችው ማሽን፤ ሙሉ ለሙሉ ያለ ሰው ማጠንጠን እንድትችል አሻሻላት። በ2005 ዓ.ም ይህንን እንደሠራ ለሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ። ማሽኑ ትክክለኛ መሆኑ ተረጋግጦ፤ በወቅቱ ጠቅላይ ሚንስትር በነበሩት ኃይለማሪያም ደሳለኝ በፈጠራ ሥራው ተሸላሚ ለመሆን በቃ።

ቻላቸው በዚህ ሽልማት ገንዘብ ባይሰጠውም የመሥሪያ ቦታ ብቻ ተበርክቶለታል፤ ሽልማቱ የበለጠ ጉልበት ሰጠው። በተወሰነ መልኩ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እየረዳው፤ ማሽኑን ማምረት ጀመረ።

በማሽኑ ክር በማጠንጠን የሸማኔዎችን የጥሬ ዕቃ ችግር ከማቃለል በተጨማሪ የብዙዎችን ጊዜ እና ጉልበት እንዲሁም የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛን ማስቀረት የሚችልበትን ሁኔታ ፈጠረ። ሸማኔዎች ሥራ ቀለለላቸው፤ ከእርሱ ላይ በከፊል የተዘጋጀ ግብዓት እየተጠቀሙ መሥራት ጀመሩ።

ከመሥሪያ ቦታ (work shop) የማይነጠለው ቻላቸው፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቀጥሮ ከመምህርነቱ ጎን ለጎን፤ አዲሱ ገበያ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 በተሰጠው መሬት ላይ የፈጠራ ሥራውን የበለጠ ለማጎልበት ጥረት ማድረጉን ቀጠለ።

በ2009 ዓ.ም የሥራ ፈጠራውን ከፍ ለማድረግ በፅናት እየታገለ፤ እንደተለመደው የተለያዩ ምርምሮችን ማድረጉን ቀጠለ። እያሻሻለ መጥቶም የሰው ጉልበት የማትፈልግ በኤሌክትሪክ የምታጠነጥን ማሽን ሠራ።

በሂደት በ2015 ፈጠራውን የበለጠ በማሻሻል አራቱንም የሽመና ሥራዎች ለመሥራት የሚያስችል ማለትም፤ በፍጥነት እና በብዛት ጨርቅ ለማምረት የሚያግዝ መፍተያ፣ ማጠንጠኛ፣ ማዳወሪያ እና መሸመኛ ማሽን በመሥራቱ፤ የአልጋ ልብስ፣ መጋረጃ፣ ሙሉ የወንድ እና የሴት ልብስ ለመሥራት እንዲያመች ብትን የፈትል ጨርቅ መስሪያ ማሽን አደረገው። በዚህም ትልቅ የፈጠራ ሥራ ማግኘት መቻሉን አረጋገጠ።

‹‹ማሽኑ ሥራ ላይ መዋሉ፤ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፤ የሥራ ጫና እና የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛን ያቃልላል፡፡›› የሚል እምነት እንዳለው የሚናገረው የፈጠራ ባለሞያው ቻላቸው፤ ማሽኑ በብዛት ቢመረት ከሀገር ውስጥ አልፎ ወደ ውጭ ልኮ መሸጥ እንደሚቻል ይናገራል፡፡

የፈጠራ ባለሞያን ግኝት ማባዛት፤ የፈጠራ ባለሞያን ተጠቃሚ ያደርጋል፤ የግለሰቡን አቅም ይጎለብታል ሲል ገልጾ፣ የፈጠራ ባለሙያው ማሽኑን ለማባዛት ከሚደክም ይልቅ ጊዜውን ሌሎች ፈጠራዎች ላይ ማሳለፍ ይጀምራል ይላል። የፈጠራ ሥራን ማብዛት ላይ ትኩረት ቢሰጥ ሀገር የምታድግበት ሁኔታ ቀላል ሊሆን እንደሚችል ያመላክታል።

‹‹የዩኒቨርሲቲ መምህር በመሆኔ ብዙ ዕድሎች ነበሩኝ። 3ኛ ዲግሪ ለመሥራት ውጭ መሔድ እችል ነበር። ሆኖም ፍላጎቴ ያ ባለመሆኑ ቀን እና ማታ አብዛኛውን ከማስተማር ውጭ ያለውን ጊዜዬን የመሥሪያ ቦታ (work shop) በማሳለፍ፤ ለ20 ዓመታት ጥረት በማድረጌ ማሽኑን ለእዚህ ደረጃ አድርሻለሁ፡፡›› የሚለው የፈጠራ ባለሞያው፤ መፍተያ፣ ማዳወሪያ፣ ማጠንጠኛ እና መሸመኛ ሠርቶ የሸማኔውን ድካም የሚቀንስ ትልቅ የፈጠራ ሥራን ቢያበረክትም እግሩን እየጎተቱ አላላውስ ያሉ ብዙ ፈተናዎች እንደገጠሙትም አመልክቷል።

‹‹ በ2005 ዓ.ም ሥራ ቢኖረኝም የፈጠራ ሥራዬን ለማሳደግ እና ማሽኑን ለማባዛት ለሥራ አጥ የተዘጋጀ ሼድ በሽልማት መልክ ተሰጠኝ፡፡›› ሲል አስታውሶ፣ ወረዳ አካባቢ የነበሩ ባለሞያዎችም ሆኑ የሥራ ኃላፊዎች በፋይናንስ እጥረት ምክንያት በሼዱ እንዳልተጠቀመ እንደሚያውቁ ጠቅሶ፣ አዋሽ የታታሪዎች ውድድርን በማሸነፍ የአንድ ሚሊየን ብር እና በተጨማሪ የ5 ሚሊየን ብር ብድር ሽልማትን ሲገኝ ሼዱን እንዳሸጉበት እና መሬቱን እንደነጠቁት ይናገራል።

‹‹መሥራት ልጀምር ስል አስተጓጎሉኝ። ይህ አንድ ቦታ ላይ ለመውሰድ ካሳፈሩ በኋላ ተሳፋሪው ያሰበበት ሳይደርስ ውረድ እንደማለት ይቆጠራል፡፡›› የሚለው የፈጠራ ባለሞያው ቻላቸው፤ እነርሱ እንቅፋት ቢሆኑበትም ሥራውን ለማስቀጠል ቆርጦ ተነስቶ እንደነበርም ያስታውሳል፤ ሆኖም በፋይናንስ እጥረት ሳቢያ ለመቀጠል መቸገሩን ይናገራል።

የፈጠራ ባለሞያው ቻላቸው እንደገለፀው፤ በፈተናው ተስፋ አልቆረጠም፤ ቦታ ለመከራየት አሰበ። ማሽኑን ለመሥራት የሚያስፈልገውን ሰፊ ቦታ አዲስ አበባ ላይ መከራየት በእርሱ አቅም የሚቻል አልሆነም። ስለዚህ ወደ ትውልድ አካባቢው ጎንደር አቀና።

ቻላቸው ጎንደር ከገባ በኋላ ሰዎችን አሰባስቦ አሰለጠነ፤ መሬት ተከራይቶ መሥራቱን ተያያዘው። እስከ አሁን አምስት ማሽኖችን ሠርቶ ሸጧል፤ በፈጠራ ሥራውም ሸማኔዎች እየተገለገሉበት ይገኛሉ። ለጊዜው 17 ሠራተኞችን ቀጥሮ ያሠራል፡፡

የማሽኖቹ ገዢዎች (ገበያው) አዲስ አበባ እንደሆኑ ጠቅሶ፣ ማሽኑን ከጎንደር አጓጉዘው አዲስ አበባ ለማድረስ ብቻ እስከ 80 ሺህ ብር እያወጡ መሆናቸውን አስታውቋል። ማሽኑን አዲስ አበባ ላይ ማምረት ቢችል ጥቅሙ ለእርሱ ብቻ ሳይሆን፤ ማሽኑን የሚገዙ ሸማኔዎችም በቀላሉ ማሽኑን የሚያገኙበት ሁኔታ በመፍጠር ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ይገልፃል።

‹‹የፋይናንስ ችግርን መቅረፍ በጣም ከባድ ነው፡፡›› የሚለው የፈጠራ ባለሞያው፤ ቢሮክራሲውም ውስብስብ መሆኑን ይናገራል፤ በዚህ ምክንያትም አዲስ አበባ ውስጥ ማሽኑን ለማባዛት ተቸግሯል።

ቀደም ሲል ምርምሩን ሲያካሔድ እና ግኝቶቹ እያደጉ ሲመጡ፤ ማሽኑን ከሀገር አልፎ ለአፍሪካም ይተርፋል የሚል ጉጉት ነበረው። ‹‹ለወገን ለውጥ፣ ለራስ ዕድገት እየጣሩ እንደገና በየወረዳው ለገንዘብ፣ ለቦታ፣ ለኃይል አቅርቦት መመላለስ ያድክማል፡፡›› ሲል ምርር ባለ አንደበት ይገልጻል።

ማሽኑ ውጤታማ መሆኑ ተረጋግጦ፤ የሥራ ጫናን ምን ያህል እንደሚቀንስ ታስቦ እንዲሁም የሸማኔውን ጉልበት ከመቀነስ ባሻገር ማሽኑን እና በማሽኑ የሚመረቱትን ባሕላዊ ልብሶችንም ጭምር ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪን ማግኘት እና የሥራ ዕድል መፍጠር እየተቻለ፤ ይህ ሳይሆን መቅረቱ እንደሚያሳዝነው ይናገራል።

‹‹ማሽኑ እንዴት በብዛት ይመረት?›› የሚለው ጥያቄ በአንድ ግለሰብ የሚመለስ አለመሆኑን በመጠቆም፤ የውጭ በተለይ ያደጉት ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው አንድ ቴክኖሎጂስት ወይም የፈጠራ ባለሞያ የሚጠበቅበት የሠራውን ማሳወቅ ብቻ መሆኑን ይገልጻል። የፈጠራ ሥራውን ማባዛት እና የፈጠራ ሥራውን መጠቀም የኢንቨስተሮች ሥራ ነው ሲል ተናግሯል። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ይሄ እንዳልተለመደ አመልክቷል።

‹‹የፈጠራ ባለሞያ ግኝቱን ከሠራ እና የፈጠራው ውጤት መሥራቱ ከተረጋገጠ በኋላ፤ የሚባዛበትን እና ተደራሽ የሚሆንበትን ሁኔታ አስበው የሚሠሩት እና የሚያሠራጩት መንግሥት እና ባለሀብቶች ወይም መንግሥታዊ ያልሆኑ የልማት ድርጅቶች መሆን አለባቸው፡፡›› ይላል።

በኢትዮጵያ እውነተኛ ለውጥ እንዲመጣ፤ ዜጎች ከድህነት እንዲወጡ እና ድካማቸው እንዲቃለል፤ ሰዎች ለተፈጠሩበት፤ ሁሉም ድርጅቶች ለተቋቋሙበት ዓላማ መሥራት እንዳለባቸው ያስገነዝባል። ‹‹በፈጠራ ባለሞያው እና በባለሀብቶች መካከል ትስስር ቢፈጠር ባለሀብቶች የተሻለ አቅም ስላላቸው ማሽኑን ወይም የፈጠራ ሥራውን በስፋት እያመረቱ በብዛት ማሰራጨት ይችላሉ›› ሲል ጠቁሟል። መንግሥት የፈጠራ ባለሞያውን ማበረታታት እና የፈጠራ ሥራውን ለባለሀብቶች በማሳወቅ ሚናውን ከተወጣ፤ በትክክልም በብዛት ለሸማኔው ማሠራጨት አዳጋች አይሆንም ብሏል።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You