
የዕለቱ የስኬት ዓምድ እንግዳችን ለአሥር ዓመታት በግለሰቦች ሱቅ እና ኩባንያ ተቀጥራ ሠርታለች። ዛሬ ላይ ከተቀጣሪነት ተላቃ ከራሷ አልፋ ለሌሎች ሥራ መፍጠር ችላለች:: እንግዳችን ትዕግስት መንበሩ ትባላለች።
ትዕግስት ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አየር ጤና ዓለም ባንክ አካባቢ ነው። የማነ ብርሃን የመጀመሪያ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጀመሪያና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ተከታትላለች። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በአየር ጤና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተከታተለችው። በትምህርቷ መካከለኛ ከሚባሉ ተማሪዎች ተርታ እንደምትሰለፍ ታስታውሳለች::
ለመንግሥት ሠራተኛ አባቷ እና ለቤት እመቤት እናቷ፤ የመጀመሪያ ልጅ የሆነችው ትዕግስት፣ ቤተሰቦቿ ከልጅነቷ ጀምሮ ተገቢውን እንክብካቤ ያደርጉላት እንደነበርም ትናገራለች። የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ውጤቷ ለዩኒቨርሲቲ የማያበቃ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲ አልገባችም፤ ቤተሰቦቿ የምትፈልገውን የሚያደርጉላት በመሆኑ በዚህም አልተከፋችም።
ትዕግስት የገቢ ችግር ባያስጨንቃትም፤ ሥራ የመሥራት ጽኑ ፍላጎት ግን ነበራት። በልጅነቷ ዝንባሌዋን ለይታ ለማወቅ ትቸገር ነበር፤ የተለያዩ ሥራዎችን ሞክራለች።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች፤ የኮምፒውተር ስልጠና መውሰድ ጀመረች። ሥልጠናውን እየወሰደች የሥራ ላይ ልምምዷን፤ ፒያሳ የድሮ አያሌው ሙዚቃ ቤት አካባቢ በአንድ የፅሁፍ አገልግሎት በሚሰጥ መለከት መፅሔት በሚታተምበት ሱቅ ታደርግ ነበር። በዚህም በወር ለአውቶቢስ ትራንስፖርት 50 ብር ብቻ እየተከፈላት ለሶስት ወር ልምምድ ስታደርግ ቆይታ የልምምድ ጊዜዋ ያበቃል። ከቤት መውጣት እና መሥራት ትፈልግ ነበርና ቤት ላለመዋል ስትል በወር የትራንስፖርት እየተባለ እንደ ደመወዝ እየተከፈላት መቆየቷን ትወደው እንደነበርም ትናገራለች።
ባለሱቆቹም ቅልጥፍናዋን ስለወደዱ ልምምዷን ብትጨርስም ሥራውን እንድትቀጥልበት ጋበዟት፤ በዚህም ገና በ17 ዓመቷ የሥራውን ዓለም ተቀላቀለች። ከተለማማጅነት ወደ ቋሚ ተቀጣሪነት አደገች። ደመወዟም 350 ብር አካባቢ ሆነ። የፅሁፍ እና የፎቶ ኮፒ አገልግሎት በሚሰጠው ሱቅ ተቀጥራ ስትሠራ፤ ተገልጋዮች በምትሰጣቸው አገልግሎት ይደሰቱ እንደነበር ታስታውሳለች። የዚህ ዋነኛው ምክንያትም ደንበኞች የተለያዩ ካርዶችን ሲያዙ፤ የምትሠራቸው ዲዛይኖች ያስደስታቸው ስለነበረ ነው።
በኋላ አባቷ ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን እዚያው ፒያሳ አካባቢ ኮምፒውተር ቤት ከፈቱ። የአባቷ ጓደኞች፤ ‹‹ ልጅህ ልምድ ስላላት እርሷ ትሥራ›› ሲሉ ጥያቄ አቀረቡ። ይህ ሁኔታ ሥራ ከጀመረችበት ሱቅ ለቅቃ ፣ አባቷ እና ጓደኞቻቸው በከፈቱት ሱቅ መሥራቱን ተያያዘችው።
ጎን ለጎንም የአድማስ ዩኒቨርሲቲ የማታው ክፍለ ጊዜ ተማሪ ሆነች። ትምህርቱ ከሱቅ ስትወጣ ወደ ቤቷ ሳይሆን ወደ ትምህርት ቤት እንድትሮጥ አረጋት። ከኮሌጁ በኦፊስ ማኔጅመንት ዲፕሎማ ተመረቀች።
በመቀጠል በአካባቢዋ ባለው ቤተሰብ አካዳሚ በተሰኘ ትምህርት ቤት ተቀጥራ መሥራት ጀመረች። ምንም እንኳ ከግለሰብ የሱቅ ቅጥር ከፍ ብላ ትምህርት ቤት ተቀጥራ በተሻለ ደመወዝ በፀሃፊነት ብትሠራም አልረካችም። በድጋሚ በማታው ክፍለ ጊዜ በዲግሪ ፕሮግራም ናሽናል ኮሌጅ አካውንቲንግ መማር ጀመረች።
ከሥራዋ ጎን ለጎን ትምህርቷን አጠናቃ ለመመረቅ በቃች። አሁንም ደመወዟ አደገ። የተቀጠረችበት ትምህርት ቤትም አደገ። ተስፋፍቶ ብዙ ቅርንጫፎችን ከፈተ፤ እሷም ደረጃዋ እያደገ የኩባንያው ምክትል አስተዳዳሪ እስከመሆን ደረሰች፤ አሁንም ፍላጎቷን ማርካት አልሆነላትም።
በአጠቃላይ አሥር ዓመት ያስቆጠረውን የቅጥር ሥራዋን ትታ በራሷ ሌላ ሥራ ለመሥራት አሠበች። ከድርጅት ተቀጣሪነት የራስ ድርጅት ወደ መክፈት አዘነበለች። በጉዳዩ ላይም ከእህቶቿ ጋር መከሩ፤ አወጡ አወረዱ። የሚሠሩትንም ለዩ።
ይሁንና ለዚህ የሚሆን መነሻ ገንዘብ ጠፋ። ለእዚህም አንደኛው አማራጭ ከአነስተኛ ቁጠባ እና ብድር ተቋም ገንዘብ ማፈላለግ ነበር። ከእህቶቿ ጋር ሆነው ከአዲስ ቁጠባ እና ብድር 250 ሺህ ብር ተበደሩ። አንደኛዋ እህቷ ቁርስ ቤት ከፈተች። እርሷ ደግሞ ከሌላኛዋ በቆዳ ኢንዱስትሪ ስልጠና ከተከታተለች እህቷ ጋር በአንድ ማሽን፣ በአንድ ክፍል ቤት ውስጥ ወደ ቆዳ ሥራ ገቡ። ኢንዱስትሪውን በይፋ ተቀላቀሉ።
በቆዳና የቆዳ ውጤቶች ዘርፍ የራሳቸውን ሥራ ፈጥረው ትልቅ ቦታ ለመድረስ እየሠሩ ባሉበት ወቅት ትዕግስት ለፋሽን እና ዲዛይን ልዩ ፍላጎት እንዳላት መረዳት ጀመረች:: ያለፈውን ስታስታውስ፤ ሰዎች ፋሽን እና የተለየ ዲዛይን ለብሰው በቴሌቪዥንም ሆነ በአካል ስታይ ትደሰት ነበርናም ዲዛይን እያወጣች መሥራት ውስጥ ገባች።
ትዕግስት፤ የውስጥ ፍላጎቷ ዲዛይን ላይ እንደሚያዘነብል ያወቀችበት ሌላኛው ምክንያት ወደ ቆዳ ኢንዱስትሪ ከገባች በኋላ ገንዘብ ሳታገኝ እንደውም ገንዘቧን እያወጣች ሳይቀር ደስተኛ ሆና እየሠራች መሆኑን ስትረዳ ነው። የውስጥ ፍላጎቷ ዲዛይን መሆኑን ስታረጋግጥ ለሊት እና ቀን መሥራትን ልማዷ አደረገችው። በኋላም ከእህቷ ጋር የነበረውን ሥራ ወደ ሁለት ድርጅት ከፈሉት፤ ሁለቱም በየራሳቸው መሥራት ጀመሩ።
ወደ ራሷ ሥራ ከመግባቷ በፊት ከእህቷ ጋር መሥራቷ አቅምና ልምድ ለማግኘት ምቹ ሁኔታ ፈጠረላት። ተቀጣሪ የነበረችው ትዕግስት በሂደት ብቻዋን ማሽኖችን በመግዛት ዘለበት የተሰኘ የቆዳ ፋብሪካ በመክፈት፤ ከራሷ አልፋ ሌሎችን ቀጠረች።
‹‹አንድ ሥራ ሲታሰብ ዋነኛው ጥሬ ዕቃ የሚገኘው ከየት ነው? የሚለው ትልቅ መልስ የሚሻ ጉዳይ ነው›› የምትለው ትዕግስት፤ በምን ያህል ጥራት? ለማን ማቅረብ ይቻላል? የሚለውን አስቦ መሥራት ስኬታማ ያደርጋል ባይ ናት።
የኢትዮጵያ ቆዳ ጠንካራ በመሆኑ እና ጥራት ስላለው በውጪ ገበያ በጣም ተፈላጊ ነው ስትል ትገልፃለች። የሥራው መሠረት ቆዳ ነው፤ ቆዳው በሀገር ውስጥ በስፋት የሚገኝ በመሆኑ ለማምረት ምቹ ነው የምትለዋ ትዕግስት፤ ሥራው ላይ እንድትቆይ ያደረጓት ዋነኛዎቹ ምክንያቶች ቆዳ የሚገኘው ከሀገር ውስጥ መሆኑ እና ለሙያው ትልቅ ፍቅር ስላላት እንደሆነ ትናገራለች።
ከቆዳው ውጪ ያሉ ቁልፍ፤ ዘለበት እና ዚፕን የመሳሰሉት ጥራት ያላቸው ግብአቶች ከውጪ የሚገቡ መሆናቸውን ጠቅሳ፣ እነዚህን ግብዓቶች ለማግኘት ያለው ፈተና እርሷንም ሆነ ጠቅላላውን የቆዳውን ኢንዱስትሪ እየፈተኑት እንደሚገኙ ትገልፃለች።
ትዕግስት ገበያው እና የሚገኘው ትርፍ አነስተኛ መሆን ያሳስባት እንደነበርም ታስታውሳለች። የፈለገውን ያህል ጥራት ያለው ምርት ቢመረት ከምርቱ የሚገኘው ጥቅም ዝቅተኛ ነው ትላለች። ቆዳ በሀገር ውስጥ በቀላሉ ይገኛል ተብሎ ስለሚታሰብ ለምርታቸው የሚሰጠው ዋጋ በጣም የወረደ ነው ስትል ታብራራለች። ምርቱን የሚጠቀሙት ጥቂቶች መሆናቸውንም ነው የተናገረችው።
ግለሰቦች የቆዳ ምርቶችን በየቤቱ በስፋት ቢያመርቱ፣ ምርቱ ቢጨምር፣ ውድድር እንደሚፈጠርና ጥራት ያለው ምርት የሚመረትበት ሁኔታም እንደሚፈጠር ጠቁማለች። ይህ ደግሞ ምርቱ ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ ያስችላል የሚል እምነትም አላት።
ሌላው የዘርፉ ችግር የግብዓቶች ዋጋ መወደድና እጥረት መሆኑን ጠቁማለች። ‹‹ከውጪ ከሚገቡት ግብዓቶች አንዳንዶቹ የጥራት ጉድለት አለባቸው። ጥራት ያላቸው ግብዓቶች ደግሞ ዋጋቸው ውድ ነው፤ በውድ ለመግዛትም ሲፈለጉ አይገኙም። ›› የምትለዋ ትዕግስት፤ ከውጪ የሚገቡት የዘርፉ ግብዓቶችን በጥራት፣ በተመጣጣኝ ዋጋ፤ በብዛት እና በስፋት በአማራጭ ማግኘት አዳጋች መሆኑንም አመልክታለች። ይህ የሆነበት ምክንያት የቆዳ ኢንዱስትሪ ከትልልቅ እስከ አነስተኛው አምራች የሚሳተፍበት ዘርፍ በመሆኑ ነው የሚል ግምት እንዳላት ታመለክታለች።
አጨራረሱ ላይ ችግር እያጋጠመ መሆኑ እንደሚጠቆም ጠቅሳ፣ ይህ የሚሆንበት አንዱ ምክንያት ግብዓቶች ባለመኖራቸው መሆኑን ጠቁማለች። ለማጠናቀቂያነት እና ለምርት ውበት የሚያገለግሉ ማሽኖች የማግኘት ችግሮችም እንዳሉም ነው ። ከውጪ የሚገቡ ጥራታቸው የተረጋገጡ ግብዓቶች ብቻ ሳይሆኑ ማሽኖችን መጠቀም ከተቻለ፤ ሙሉ ለሙሉ ከኢትዮጵያ ገበያ መውጣት እንደሚቻል አስታውቃ፣ ከዘርፉ በአግባቡ ለመጠቀም ዋነኛው መፍትሔ ምርቱን ወደ ውጪ መላክ መሆኑን ጠቁማለች።
‹‹በዘርፉ ላይ ያለው ሌላኛው ዋነኛው ፈታኝ ነገር የፋይናንስ ችግር ›› መሆኑን ትዕግስት ጠቁማለች። ሥራውን እየጀመሩ ያሉ ብዙ ሰዎች ማሽን ገዝተው በየጊዜው የሚጨምር የሱቅ እና የቤት ኪራይ ከፍለው መሥራት አቅቷቸው በፋይናንስ እጥረት ምክንያት ሙያውን ትተው ወደ ሌላ ሙያ የሚገቡ መሆናቸውን አመልክታ፣ የፋይናንስ እጥረት የእርሷም ችግር መሆኑን ትናገራለች። በእርሷ በኩል የመሥሪያ እና የመሸጫ ቦታዎች በኪራይ የምትሠራባቸው መሆናቸውን አስታውሳ፤
እሷ እንደምትለው፤ ኢትዮጵያ ካላት አቅም አንፃር የቆዳው ኢንዱስትሪ ዘርፍ በጣም ማደግ የሚችል፤ አቅም ያለው ዘርፍ ነው። ሆኖም መንግሥት ለዘርፉ እያደረገ ያለው ድጋፍ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ግብዓቶችን ከውጪ የሚያስገቡ ሰዎች ምቹ ሁኔታ ቢፈጠርላቸው እና በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያው በብዛት ቢያቀርቡ ችግሩ ይቃለላል። መንግሥት በዚህ በኩል መፍትሔ ካመጣ በተወሰነ መልኩ ኢንዱስትሪውን ማስፋት እና ለብዙዎች የሥራ ዕድል መፍጠር ይቻላል።
አምስት ቋሚ እና ከ10 በላይ ጊዜያዊ ሠራተኞችን ቀጥራ የምታሠራዋ ትዕግስት፤ በምርጥ ጥራት እና ዲዛይን ለመሥራት በዘርፉ ላይ ያሉት ብቁ ባለሙያዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑንም ጠቁማለች። ትዕግስት እንደምትገልፀው፤ እሷ ብቁ የቆዳ ባለሙያዎች በሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች ላይ በከፍተኛ ገንዘብ ቀጥራ ታሠራለች። አንዳንድ አስቸኳይ ያልሆኑ ሥራዎች ላይ ለማጆችን በማስገባት ሥራውን እንዲለማመዱ የማድረግ ኃላፊነቷን እየተወጣችም ናት።
በብዛት በማምረት፤ ከኢትዮጵያ ውጪ ምርቶቿን የመላክ ፍላጎት እንዳላትም ጠቁማለች። ምርቶቿን ወደ ጀርመን ለመላክ በሂደት ላይ ናት፣ ምርቶችን በሀገር ውስጥም ለሱቆች ለማከፋፈል ትፈልጋለች፤ ሆኖም ያንን ማድረግ አልቻለችም። ምክንያቷ ደግሞ ይህንን ማድረግ በብዛት ማምረትን የሚጠይቅ መሆኑ ነው። በብዛት ማምረት ደግሞ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚጠይቅ አስታውቃ፣ ለጊዜው በተወሰነ ብዛት በጨረታ ተወዳድራ መንግሥታዊ ላልሆኑ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ለባንኮች በትዕዛዝ በመሥራት እንዲሁም ሱቅ ከፍታ በመሸጥ ላይ ብቻ መገደቧን አስታውቃለች።
በዘርፉ ላይ ተሠማርታ አምስት ዓመታትን ያስቆጠረች ሲሆን፤ ከየት ተነስቶ መጀመር እንደሚቻል እርሷን እንደማሳያ መውሰድ እንደሚቻል ትናገራለች። ‹‹ ድርጅት መክፈትና ቀጣሪ መሆን የሚችሉ፤ ሆኖም ከተቀጣሪነት ለመውጣት የሚፈሩ በተለያዩ ድርጅቶች የሚሠሩ ሠራተኞች ብዙ ናቸው›› የምትለዋ ትዕግስት፤ እነዚህ ሠራተኞች የራሳቸው ሥራ ፈጣሪ ለመሆን ጥረት ቢያደርጉ ብቃታቸውን ማሳየት እንዲሁም ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚችሉ ትዕግስት መክራለች::
‹‹የትኛውም ስኬት ያለ ሥራ፣ ያለልፋት አይመጣም፤ አልጋ በአልጋ የሆነ መንገድ የለም›› የምትለው ትዕግስት፤ የትኛውም ሰው በየዕለቱ በትጋት ከሠራ ሁሉም የሚወደውን ማግኘት እና ማደግ እንደሚችል አስገንዝባለች::
አሁን ለደረሰችበት ደረጃ የባለቤቷ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳልተለያት ጠቅሳ፣ በየትኛውም የሥራ ዘርፍ ላይ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ቤተሰብ ሥራ ፈጣሪዎችን ማበረታታት እንዳለባቸው አስገንዝባለች። ይህ ሲሆን ትልቅ ውጤት ማግኘት እንደሚቻልም ጠቁማለች::
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 16 ቀን 2017 ዓ.ም