‹‹የአማራ ሕዝብ ከወንድሞቹና ከጎረቤት ክልሎች፣ ከትግራይ ሕዝብ ጋር ሰላም መሆን ይፈልጋል፤ ለዚህ የሰላም አጀንዳችሁም አመሠግናለሁ፡፡ የምመራው ሕዝብም ሰላም ይፈልጋል፤ ለመሥራት፣ ለመኖር፣ ለመሻሻል… የሚፈልግ ነው፡፡ ይህንንም ስታወያዩት ነግሯችኋል፡፡ እኔም ዝግጁ ነኝ፡፡ ሰላምን የሚጠላው ሰይጣናዊ አስተሳሰብ የተጠናወተው ነው …
‹‹የአማራና ትግራይ ሕዝቦች ለሺህ ዘመናት የጋራ ሃይማኖት፣ ባሕልና እሴት ያላቸው አንዱ በአንዱ የሚሰጋ ሳይሆን የሚኮራ ሕዝቦች ናቸው፤ ይህ ግን ከጊዜ ጊዜ እየተሸረሸረ መጥቷል፡፡ ሕዝቡ ሰላማዊ ፍላጎቱ በሰላም እንዲፈታ እንጂ እንዲጋጭ በፍጹም አይፈልግም፡፡ ያሉ ጥያቄዎች በውይይት በሰላም የሚፈቱበትን ሁኔታ ነው የሚፈልገው፡፡››
-የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው
‹‹ግንኙነታችን ከወንድምነትም በላይ ነው፤ የፖለቲካ ጓዶች ነን፡፡ የሀገራችን እሴቶች ብቻ ሳይሆን የድርጅታችንም እሴት መሸርሸር ስላለ ነው እናንተንም ወደዚህ ጉዳይ የጋበዝናችሁ፡፡ ከዚህ ችግር ቶሎ መውጣት አለብን፤ መጨነቅ ብቻ ሳይሆን ብዙ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች አሉ …
‹‹ፖለቲካችን ውለን አድረን ማስተካከል አለብን፤ የሰላም ጉዳይ ግን ለነገ አይባልም፡፡ የፖለቲካ ልዩነት አስቀድመን ሰላማችንን ማጣት የለብንም፡፡ … የአማራና የትግራይ ሕዝብ ዘመድ ብቻም አይደለም፤ ከዚያ በላይ ነው ግንኙነቱ፡፡ ችግር ያለው ፖለቲከኞች ላይ ነው፡፡ ሕዝቡ ወደ ግጭት አታስገቡን ነው እያለ ያለው፡፡››
-የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል
እነዚህ ንግግሮች ከትናንት በስቲያ ምሽት የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በተለያዩ አካባቢዎች ሲያደርጉት የነበረውን የሰላም ጉዞ ማጠናቀቂያ በማስመልከት በአዲስ አበባ ከተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች በተገኙበት በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና በትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የተላለፉ ናቸው፡፡
ሁለቱም መሪዎች በመርሃ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር በክልሎቹ መካከል የተፈጠሩት እስጣ ገባዎች ተገቢ አለመሆናቸውን፤ ህዝቡ መቃቃርን እንደማይፈልግ የፖለቲካ አመራሮች ለችግሮቹ ምክንያት መሆናቸውንና ኃላፊነትም መውሰድ እንደሚገባቸው እንዲሁም የተፈጠሩትን ክፍተቶች እንደሚፈቱት ቃል ገብተዋል፡፡
የአገራችን ሰው ‹‹የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ›› በማለት የቃልን ክቡርነት አበክሮ ይዘክራል፡፡ የፖለቲካ መሪዎቹ እጅግ በተከበሩት የሃይማኖት መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም በኢትዮጵያ ህዝብ ፊት የተናገሩትን ቃል በማክበር በሀገራችን የተጀመረው ለውጥ ፍሬ እንዲያፈራ ማድረግ አለባቸው፡፡ ያለው ነባራዊ ችግር ከመናገር በላይ በወንድማማችነት መንፈስ የሚደረግ ንግግርና በጥብቅ ሥነሥርዓት የሚመራ ተግባራዊ እርምጃ ይፈልጋልና ህዝቡ ከእነርሱ የሚጠብቀውን መፍትሄ ማመላከት አለባቸው፡፡
ከንግግር ባሻገር ስለ ተግባራዊ እርምጃ ሲነሳ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አስተዋጽኦ በአመራሮቹ ጥረት ላይ መደመር አለበት፡፡ በተለይ ወትሮም ‹‹አብሮነታችንን አትፈታተኑት›› እያለ ድምጹን የሚያሰማው ህዝብ የሰላም ጠበቃነቱን ማረጋገጥ አለበት፡፡ እዚህም እዚያም ለሚስተጋባው አሉባልታ ጆሮ ሳይሰጥ እስከዛሬ የዘለቀውን ተከባብሮ የመኖር እሴቱን ማስቀጠል ይጠበቅበታል፡፡
የተፈጠረውን ትንሽ ጉዳይ በማጋነን ብሎም ያልተፈጠረውን እንደ ተፈጠረ በማድረግ በማህበራዊ ድረገጾች ‹‹ክተት ሰራዊት …›› በማለት ጦርነት የሚያውጁት አካላት ኋላ ከሚፈጠር ጸጸት የሚያወጣቸው ከድርጊታቸው መቆጠብ ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ እዚሁ ሆነው በድርጊቱ የሚሳተፉ ሰላሟ በደፈረሰ አገር የሚፈጠረው እሳት እነርሱንም ሊለበልብ የሚችል ሲሆን፤ በርቀት ሆነው ነገር የሚያቀጣጥሉም የኔ የሚሉት ወገን የችግሩ ሰለባ ስለሚሆን ወላፈኑ ሊደርሳቸው ይችላልና ግጭት የሚፈጠርበትን መንገድ ተጨንቆ ከማሰራጨት ሰላም የሚሰፍንበትን መንገድ አምጠው ቢወልዱ ይመከራል፡፡
በአገር ውስጥ በህጋዊ መንገድ ተመዝግበው የሚገኙ እንዲሁም ከውጭ ሰላማዊ ትግልን በብቸኛ አማራጭነት ተቀብለው የገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሃይማኖት አባቶችና በሀገር ሽማግሌዎች የተጀመረው ጥረት ላይ ትንሽ ጠብታ በማከል የሰላሙን መንገድ ማጠናከር አለባቸው፡፡ በምርጫ መወዳደር፣ ተወዳድሮም ማሸነፍና ህዝብና ሀገርን መምራት የሚቻለው ሰላም ሲሰፍን በመሆኑ በምርጫ መንበሩን የያዘው መንግሥት ቃሉን ወደ ተግባር ይለውጥ ዘንድ እገዛ ማድረግ አለባቸው፡፡
ወጣቶች የነገ ሀገር ተረካቢ በመሆናቸው ብዙ በጎደለባት ሀገር መብታቸውን ለማስጠበቅ የሚያደርጉትን ትግል ያክል ስለ ግዴታቸውም በመጨነቅ ሀገርን መታደግ አለባቸው፡፡ በተለይ የሁለቱ ክልሎች አመራሮች የገቡትን ቃል ተግባራዊ ያደርጉ ዘንድ የእነርሱ ተደማሪ ሃሳብና ተግባር ጉልህ ሚና እንዳለው በማወቅ በስሜት ከሚፈጸሙ ተግባራት እራሳቸውን መግታት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በመንፈስ የወለዷቸው የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም በእድሜ ጸጋ በተቸራቸው ምክር የሚለግሷቸውን የሀገር ሽማግሌዎች ድካም ላለማጥፋት የሰላም አጋርነታቸውን ማስመስከር አለባቸው፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 9/2011