“የዓባይን አጋሩን ” እና ” የቀይ ባሕርን አትንኩ” ተቃርኖ

የዓባይ ወንዝ እና ቀይባሕር ምስራቅ አፍሪካ አካባቢዎች በሚገኙ ሀገራት መካከል ለሚነሱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥያቄዎች መነሻ የሚሆኑ የቀጣናው ስስ ክፍሎች ናቸው፡፡ የቀጣናው ሀገራት እነዚህን ሁለት የውሃ አካላት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ወይም በሰጥቶ መቀበል መርህ ቢጠቀሟቸው ተያይዞ የማደግ እና ቀጣናውን ከሌሎች የዓለም ሀገራት ጋር ተወዳዳሪ የማድረግ እድላቸው የሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝ መነሻ ሆና እንኳን ከተፋሰሱ አባል ሀገራት የተለየ ጥቅም ላግኝ ሳትል ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲሰፍን መፈለጓ ትብብር እና መደጋገፍ ለእድገቷ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ መሆኑን ምሁራን ይገልጻሉ።

በቀጣናው ያሉ የቀይ ባር ወሰንተኛ ሀገራት ግን ጎረቤቶቻቸው ካሉባቸው ችግሮች እና ከሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች በላይ የሚያሳስባቸውና የባሕር በር የሚፈቅዱት ከሌላ አህጉር መጥተው ለሚጠይቋቸው ሃያላን ሀገራት መሆኑ ሲታይ ግር ይላል። እንደ ፈረንሳይ፣ አሜሪካ ፣ ቻይናና መሰል ሀገራት በብዙ ማይልስ ከሚርቅ ስፍራ መጥተው በቀይ ባሕር ላይ ግዛት ሲኖራቸው፤ ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ያላትና በማደግ ላይ ያለችው ኢትዮጵያ ግን አጠገቧ ካለውና ታሪካዊ የባለቤትነት ድርሻ ከነበራት ቀይባሕር መተንፈሻ እንኳ ማግኘት አለመቻሏ የሚያስገርም፤ የሚያስቆጭም መሆኑን ምሁራኑ ያስገነዝባሉ።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት ለመሆን ምን መሥራት አለባት? አሁን እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችስ ምን አዎንታዊ አንድምታ አላቸው ? ስንል የታሪክ ተመራማሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ በከሪ ፣ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪ፣ አማረ ቀናው (ዶ/ር)ን እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩን ጠይቀናል።

የታሪክ ተመራማሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ በከሪ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መሆን የምትችለው የኢኮኖሚ አቅሟን ማሳደግ ስትችል ነው። ለዚህም ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ሀብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል አስፈላጊ ነው። በተለይ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅሟ ከፍተኛ ከሆነ የጎረቤት ሀገራት የኢነርጂው ተጠቃሚ መሆን ይፈልጋሉ።

ባሕርበር ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እንዳለ ሆኖ ወሳኙ ጉዳይ ግን የሀገርን ደህንነት ማስጠበቅ እንደሆነ የተናገሩት ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ፤ ከዚህ መነሻነትም ኢትዮጵያ ባሕር በር ለማግኘት ከምታደርገው ጥረት ጎን ለጎን ዓባይ ወንዝ ላይ ተጨማሪ ግድብ መገንባት ይኖርባታል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ካውንስል አባል አለመሆኗን ገልጸው ፤ የዚህ ካውንስል አባል ለመሆን ቀይ ባሕርን ከዓባይ ወንዝ ጋር አስተሳስራ መመልከት ይኖርባታል። በዚህም ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት የምትችልበትን ሰፊ እድል መፍጠር ትችላለች ነው ያሉት።

ግብጾች የቀይ ባሕር ካውንስልን ያቋቋሙት ለዓባይ ወንዝ ብለው ነው የሚሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፤ ይህም ኢትዮጵያ ከዓባይ ወንዝ ይልቅ ቀይ ባሕር ላይ ትኩረት እንድታደርግ ያለመ ነው። ይህንን ከታሪክ አንፃር መመልከትና መገንዘብ አስፈላጊ ነው። ይህም ኢትዮጵያን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ሌላው የሱዳን መንግሥትን በተቻለ አቅም ከኢትዮጵያ ጎን እንዲሆን የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት ይገባል። ሱዳን በዓባይ ወንዝ ግድብ መሙላት ብትችልም ግድቡ በደለል እየተሞላ በቂ ውሃ መያዝ አልቻለችም። የዚህ ደግሞ መንስኤው የገነቡት ግድብ በግብጽ የተሠራ በመሆኑ እንደሆነ ተናግረዋል።

ይህም ግብጽ ዓባይ ወንዝን ከሌሎች ሀገራት ጋር በፍትሐዊ መንገድ መጠቀም እንደማትፈልግ የሚያሳይ መሆኑን የገለጹት ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ፤ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የገነባችው ግድብ ደግሞ የተፋሰሱ ሀገራትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ነው። ይህንንም ለሱዳን ማስገንዘብ እንደሚገባ ገልጸዋል።

እነዚህ ሥራዎች ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት የምትሆንበትን እድል እንደሚያሰፉ ተናግረው፤ ሥራው እውን ከሆነ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚና በኃይል ጠንካራ እንደምትሆን ጠቁመዋል።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ በሦስተኛው የቀይባሕር እና ኤደን ባህረ ሰላጤ የውይይት መድረክ ላይ እንደተናገሩት፤ ሁለቱ ውሃዎች ማለትም ዓባይና ቀይ ባሕር የኢትዮጵያን ቀጣይ ዘላቂ መረጋጋትና ብልፅግና የሚበይኑ ናቸው ብለዋል።

እነዚህን ውሃዎች የመጠቀም ወይም በእነዚህ ውሃዎች ላይ ያለንን ስትራቴጂካዊ ጥቅም ማረጋገጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አጀንዳ ብቻ ሳይሆን፣ ብሔራዊ መግባባት መፍጠሪያም ጭምር ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህን ወሳኝ ጉዳይ በአካባቢው ያሉና የጎረቤት ሀገሮች እንዲገነዘቡት የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪና የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር ጀኔራል አማረ ቀናው (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በቀይ ባሕር፣ በኤደን ባህረ ሰላጤና በአካባቢው ያሉ አደረጃጀቶች ጉድለት አለባቸው። ይህም ኢፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ የሚታይ መሆኑን ገልጸዋል።

እነዚህ ነገሮች ተደማምረው በኢኮኖሚ ላይ ቀላል የማይባል አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ስለዚህ ሀገራቱ ይህንን ሁኔታ በንግግር መቀየር አለባቸው። የባሕር በር አልባ መሆን ከባድ ነው። በዚህም ኢትዮጵያ ማግኘት የሚገባትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማግኘት አልቻለችም፤ ህልውናዋም አደጋ ላይ ይወድቃል ብለዋል።

የባሕር በር አልባነት ጉዳይ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እና እድገቱን ከማቀላጠፍ አኳያ የራሱ የሆነ ተጽዕኖ ይኖረዋል። በመሆኑም የባሕር በር ለኢኮኖሚ እድገት፣ ለብሔራዊ ጥቅም እንዲሁም ለደህንነትም ጭምር አስፈላጊ መሆኑን አማረ (ዶ/ር)፤ ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩትም ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መሆን የምትችልበትን ሁኔታዎች የማፈላለግ ሥራ እየሠራ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላትና ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ምክክር እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። በዚህም ለፖሊሲና ለዲፕሎማሲ ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎችን የማፈላለግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ምሁራኑ በሰጡት ማብራሪያ የዓባይን ውሃ በፍትሃዊ መልኩ ተጠቃሚነቴ ይረጋገጥ ከማለት ባሻገር ብቻዬን ልጠቀም የምትለዋ ግብጽ ዓባይን አጋሩኝ ቀይ ባሕርን አትንኩ የሚለው ኢ ፍትሃዊ አካሄድ አያዋጣም። ይልቁንስ በሁለቱ የውሃ አካላት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ መሥራት ይኖርባታል ነው ያሉት። በአንጻሩ ኢትዮጵያ በዓባይና በቀይ ባሕር ፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ በጋራ መግባባትና በአብሮ ማደግ መርህ ሊቃኝ ይገባል ብላ እየሠራች መሆኑን ጠቁመዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You