
አዲስ አበባ፦ በ2017 በጀት ዓመት 378 ሺህ 500 ዩኒት ደም መሰብሰቡን የኢትዮጵያ ደምና ህብረህዋስ ባንክ አገልግሎት አስታወቀ። 525 ሰዎች የዓይን ብሌን ለመለገስ ቃል መግባታቸውም ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ ደምና ህብረህዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ 21ኛው ዓለም አቀፍ የደም ለጋሾች ቀን “የሕይወትና የብርሃን ስጦታ ደምዎን ይለግሱ! ብሌንዎን ቃል ይግቡ !” በሚል መሪ ቃል ሲከበር እንደገለፁት፤ በበጀት ዓመቱ 11 ወራት 378 ሺህ 500 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ተችሏል። በ11 ወራት የተሰበሰበው የደም መጠን ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፃር የ 60 ሺህ ዩኒት ደም ብልጫ አለው ብለዋል፡፡
የደም ባንኮች መስፋፋት፤ ሥራዎችን በማዘመን የተሠሩ ሥራዎች እንዲሁም፤ የግንዛቤ ሥራዎች ማደግ ለስኬቱ መገኘት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰው፤ በበጀት ዓመቱ 11 ወራት 525 ሰዎች የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል የገቡ ሲሆን፤ 315 የዓይን ብሌን ተሰብስቧል ብለዋል።
ከደም እና ከዓይን ብሌን አሰባሰብ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ያነሱት አቶ ሀብታሙ፤ የአቅርቦት እና የፍላጎት አለመመጣጠን፤ የዓይን ብሌን ልገሳ በተፈለገው ደረጃ የተለመደ አለመሆን፤ የሀብት እጥረት መኖሩን አመላክተዋል።
የደም ልገሳ በአንዳንድ ክልሎች የተሻለ በሚባል ደረጃ ቢሆንም በተወሰኑ ክልሎች ከሀብት ማንቀሳቀስ ጀምሮ የመዳከም ሁኔታ ይስተዋላል። ከዚህ አንፃር ብዙ ሥራ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ደም እና የዓይን ብሌን የማይሸጥ፣ የማይለወጥ የላቀ ውድ ስጦታ መሆኑን ቀድመው የተገነዘቡ ሰዎች የሚለግሱት ነገር ነው። ምክንያቱም ሌላ የሚተካቸው ምንም ነገር የለም ብለዋል።
ደምና የዓይን ብሌን ውድ የሕይወት ስጦታ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ፈቃደኞቹ የለገሱት ደም ለድንገተኛ ህክምና ታካሚዎች ፣ ለእናቶችና ጨቅላ ህፃናት እንዲሁም ለካንሰር ተጠቂዎች በከፍተኛ ሁኔታ ጠቃሚ እንደሆነ የሚገነዘቡት በሥራው ላይ የተሰማሩ የጤና ባለሙያዎች እና ከሁሉ በላይ ተጠቃሚዎቹ ናቸውና ለዚህም ለለጋሾች ምስጋና አቅርበዋል።
ዶክተር መቅደስ እንደተናገሩት፤ አገልግሎቱ ዓለም ከደረሰባቸው ዘመናዊ አሠራሮች ጋር እኩል እንዲራመድ ለማድረግ የታቀዱ ሥራዎችን ከአስር ዓመቱ የጤና ስትራቴጂ ጋር በማስተሳሰር እየተተገበረ ይገኛል።
በዚህም አሠራሩ ከዕቅድ ባለፈ እውን እንዲሆንም የጤና ሚኒስቴር በሁሉም አቅጣጫ የኢትዮጵያ ደምና ሕብረህዋስ ባንክ አገልግሎትን እና በበጎ ፍቃድ የደም ልገሳ ለሚሳተፉ አካላትን፣ ከህልፈት በኋላ የዓይን ብሌናቸውን ቃል ለሚገቡ ወገኖችን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ለመደገፍ የተቻለውን ሁሉ እያደረገ ይገኛል ሲሉ አመላክተዋል፡፡
በዝግጅቱ ከተለያዩ ክልሎች ለመጡ ደም ለጋሾች፤ ተቋማት እንዲሁም ለሃይማኖት ተቋማት ሽልማት እና እውቅና ተሰጥቷል።
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም