አሜሪካና ኢራን ወደ ድርድር ይመለሱ ይሆን?

ትናንት ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው ስድስተኛው ዙር የአሜሪካና የኢራን ውይይት ሳይካሄድ ቀርቷል። እስራኤል በኢራን የኒውክሌር ተቋማትና ወታደራዊ ጣቢዎች ላይ የፈፀመችውን ጥቃት እና ኢራን የሰጠችውን የአፀፋ ምላሽ ተከትሎ ሁለቱ ሀገራት ወደ ውጊያ በመግባታቸው ድርድሩ እንዳልተካሄደ አደራዳሪዋ ኦማን አስታውቃለች።

ኢራን በእስራኤል ከተፈፀመባት ጥቃት በኋላ ለድርድር መቀመጥ ኢፍትሃዊ የሆነና ተገቢ ያልሆነ ሃሳብ እንደሆነ አሳውቃለች። የኢራን መገናኛ ብዙኃን የሀገሪቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መሀመድ ባጌይን ጠቅሰው እንደዘገቡት ኢራን ከጥቃቱ በኋላ ከአሜሪካ ጋር የምታደርገው ድርድር ትርጉም የለሽና ምንም ለውጥ የማያመጣ እንደሚሆን ታምናለች ነው ያሉት። ቃል አቀባዩ ‹‹በዚያኛው በኩል ያለው ተደራዳሪ አካል ድርድሩ ትርጉም አልባ እንዲሆን ሲያደርግ ቆይቷል። ጽዮናዊው አገዛዝ በኢራን ላይ ጥቃት እንዲፈፅም እያደረጉ ስለድርድር ማሰብ አይቻልም›› ብለዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከኢራኑ አቻቸው መሱድ ፔዥሽኪያን ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት ኢራን ወደ ድርድሩ እንድትመለስ ቢጠይቋቸውም ፔዥሽኪያን ግን ሀገራቸው በእስራኤል ጥቃት እየተፈፀመባት ድርድር እንደማይታሰብ ነግረዋቸዋል።

አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን ስድስተኛው ዙር የኒውክሌር ድርድር እንደማይደረግ እና አሜሪካ ግን አሁንም ቢሆን ለድርድር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላትና ኢራንም ወደ ድርድሩ ትመለሳለች ብላ እንደምታስብ ለ ‹‹አሶሺየትድ ፕሬስ›› (The Associated Press) ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በድጋሚ ወደ ዋይት ሃውስ ከተመለሱ ወዲህ አሜሪካና ኢራን በኦማን አደራዳሪነት አምስት ዙር ውይይቶችን አካሂደዋል። ውይይቶቹ እስካሁን ድረስ ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ውጤት ባያስገኙም፣ ሁለቱ አካላት ለኢራን ጉዳይ ሰላማዊ አማራጭን በተግባር ያሳዩባቸው ርምጃዎች እንደሆኑ ተቆጥረው ተወድሰው ነበር። የአሜሪካ ዩራኒየም የማበልጸግ ሂደቱን የማቋረጥ ጥያቄና የኢራን ያለማቋረጥ አቋም የሁለቱ አካላት የክርክር ነጥብ ሆኖ ዘልቋል።

የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር በኢራን ላይ የተጣሉት ማዕቀቦች እንዲነሱ ኢራን ዩራኒየም ማበልፀጓን እንድታቆም አልያም በትንሽ መጠን ብቻ እንድታበለፅግ ይፈልጋል። የአሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የኢራንን ኑክሌር የማበልጸግ ተግባር እንደ ‹‹ቀይ መስመር›› እንደሚቆጥሩት እና ኢራን ይህን ተግባሯን እንድታቋርጥ እንደሚፈልጉ ሁለቱ ሀገራት ባደረጓቸው ውይይቶች ላይ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።

ኑክሌሩን የምጠቀመው ለሰላማዊ ግልጋሎት ነው የምትለው ኢራን ደግሞ ዩራኒየምን ለኃይል ማመንጫ ማበልፀግ ሉዓላዊ መብቷ እና በዓለም አቀፍ ስምምነቶችም ያልተከለከለ ተግባር እንደሆነ ትገልፃለች። ኢራን ከአሜሪካ ጋር በምታደርገው ድርድር ዩራኒየም የማበልፀግ ተግባሯን ለሦስት ዓመታት ያህል ልታቆም ትችላለች ተብሎ የተነገረውን መረጃም ‹‹ፍፁም ውሸት›› ማለቷ የሚታወስ ነው።

የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊኻሜኒ ኢራን ዩራኒየም የማበልፀግ ተግባሯን እንደማታቆም ቁርጥ አድርገው ተናግረዋል። ኻሜኒ ሀገራቸው ከአሜሪካ ጋር እያደረገችው ባለው የኑክሌር ውይይት አሜሪካ ያቀረበችውን ዩራኒየም የማብላላት ተግባርን የማቆም ጥያቄ ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል።

እንዲህም ሆኖ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚደረገው ውይይት በጎ ውጤት እንደሚኖረው በልበ ሙሉነት ደጋግመው ሲናገሩ ቆይተዋል። ለአብነት ያህል ከሁለት ሳምንታት በፊት ‹‹ከኢራን ጋር በጣም በጣም ጥሩ ውይይት እያደረግን ነው። በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት የምነግራችሁ ነገር ጥሩ ይሁን መጥፎ እርግጠኛ አይደለሁም። ግን ጥሩውን እንደምነግራችሁ ይሰማኛል›› ማለታቸው ይታወሳል።

ድርድሩ ያሰቡትን ውጤት እንደሚያመጣላቸው ተስፋ አድርገው የነበሩት ትራምፕ፣ የኢራንን የኑክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤትነት የህልውናዋ ዋና አደጋ አድርጋ የምትመለከተው እስራኤል በድርድሩ ላይ እክል እንዳትፈጥርባቸው ሰግተውም ነበር። ከሁለት ሳምንታት በፊት ሀገራቸው ከኢራን ጋር በምታደርገው የኑክሌር ድርድር ከእስራኤል ጋር ጠንካራ የሆነ የጋራ አቋም እንዲኖራቸው እንደሚፈልጉ ለእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ መልዕክት የላኩባቸውም ለዚህ ሳይሆን አይቀርም።

ትራምፕ የሀገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትራቸውን ክሪስቲ ኖምን ከኢራን ጋር በሚደረገው ድርድር እስራኤልና አሜሪካ የጋራ አቋም መያዝ እንዳለባቸው የሚገልፅ መልዕክት አስይዘው ወደ ቲል አቪቭ ልከዋቸው እንደነበር የሚታወስ ነው። ሚኒስትሯም መልዕክቱን ለኔታንያሁ አስረክበው፣ ድርድሮቹ በምን ደረጃ ላይ እንዳሉ እና አሜሪካና እስራኤል በአንድነት መቆማቸው እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተነጋግረው ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዚዳንት ትራምፕ እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት እንዳትሰነዝር አስጠንቅቀውም ነበር። ከሁለት ሳምንታት በፊት ትራምፕ ለኔታንያሁ ስልክ ደውለው ‹‹ከኢራን ጋር ለምናደርገው ድርድር ተጨማሪ ጊዜና እድል መስጠት አለብን። ወደ መፍትሄ እየተቃረብንም ስለሆነ አሁን በኢራን ላይ ጥቃት መፈፀም ተገቢ አይደለም›› ብለው ነግረዋቸዋል።

ኢራን ኒውክሌር የምትገነባው ለኃይል ማመንጫ አገልግሎት እንደሆነ ብትናገርም እስራኤል ግን ይህን ፈፅሞ አታምንም። እስራኤል የኢራንን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤትነት የህልውናዋ ዋና አደጋ አድርጋ ትቆጥረዋለች። የእስራኤል ባለሥልጣናትም በቀጣናው እስራኤልን የሚወጉ ታጣቂ ቡድኖችን ትደግፋለች ብለው የሚከሷትን ኢራንን እንደዋና አደጋ ይመለከቷታል። ስለሆነም ኢራን የኒውክሌር ቦምብ ልትታጠቅ ጫፍ ላይ እንደደረሰች ደጋግማ የገለፀችው እስራኤል፣ በኢራን ላይ ወታደራዊ

ርምጃ እንደምትወስድ ስትዝት እንደነበር ይታወሳል።

ከኢራን ጋር ስምምነት ላይ የመድረስ ተስፋ የነበራቸውና ‹‹ስምምነት ላይ ልንደርስ ነው›› ብለው እርግጠኛ ሆነው ሲናገሩ የነበሩት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ ከቅርብ ቀናት ወዲህ ግን በሀገራቸውና በኢራን መካከል የሚደረገው ውይይት ውጤት ያመጣል የሚለው ተስፋቸው እየተመናመነ እንደሆነ መግለጻቸው ይታወሳል። ትራምፕ ራሳቸው እንደተናገሩት፣ ስለኑክሌር ስምምነት ጉዳይ ከወራት በፊት የነበራቸው ተስፋና በራስ መተማመን አሁን የለም። ‹‹ስምምነት ላይ ለመድረስ እንደ እኛ ዓይነት የፍላጎት ደረጃ ላይ አይደሉም። ምን እንደሆኑ አላውቅም። አሁን ያለኝ ተስፋ ከወራት በፊት ከነበረኝ ያነሰ ነው። ከጦርነት ይልቅ በድርድር ቢሆን ይሻል ነበር›› ብለዋል።

‹‹ከኢራን ጋር ብዙ ንግግሮችን አድርገናል። አስቸጋሪ ተደራዳሪዎች ናቸው። በግልጽ ለመናገር፣ የኑክሌር ጦር መሣሪያ ሊኖራቸው አይችልም፤ ያ እንዲሆን አንፈቅድም›› በማለት እሳቸው የአሜሪካ መሪ ሆነው ኢራን የኑክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤት እንደማትሆንም በድጋሚ ተናግረዋል።

ስድስተኛው ዙር የአሜሪካና ኢራን ውይይት እሁድ ዕለት በኦማን ከመካሄዱ ቀድሞ እስራኤል ባለፈው አርብ ዕለት በኢራን ላይ ከባድ ጥቃት ፈፅማለች። ኢራንም የአጸፋ ርምጃ ወስዳለች። ይህም ኢራን አሜሪካ ላቀረበችው የመደራደሪያ ሃሳብ ምላሽ የሚሆን የራሷን አማራጭ ታቀርብበታለች ተብሎ የተጠበቀው ስድስተኛው ዙር ውይይት እንዳይካሄድ አድርጎታል።

እስራኤል የፈፀመችውን ጥቃት ተከትሎ ሁለቱ ሀገራት የገቡበት ውጊያ የአሜሪካና የኢራንን የኒውክሌር ድርድር ዋጋ አልባ ሊሆን እንደሚችል የብዙዎች እምነት ነው። በቴህራን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ሀሜድ ሙሳቪ፣ ‹‹በርካታ ኢራናውያን ሀገራቸው ጥቃት እየተፈፀመባት ከአሜሪካ ጋር የምታደርውን ድርድር መቀጠል ትርጉም እንደሌለው ያስባሉ›› ብለዋል።

‹‹እስራኤል ዲፕሎማሲያዊ አማራጩን አበላሽታዋለች፤ ከኢራን ጋር የምትደራደረው አሜሪካ ከእስራኤል ጋር እየተባበረች መሆኑ ያስገርማል። ስለሆነም ድርድሮቹ ይቀጥላሉ ብዬ አላምንም›› በማለት ያስረዳሉ።

በሌላ በኩል አሜሪካና ኢራን ወደ ድርድር ቢመለሱም ሁለቱም አካላት ከቀድሞው የበለጠ ጠንካራ የድርድ ሃሳቦችን ይዘው ሊመጡ እንደሚችሉ የሚገልጹ ወገኖች አሉ። የእስራኤል ጥቃት ኢራን ኒውክሌር በመገንባት አቋም የበለጠ እንድትፀና ሊያደርጋት እንደሚችልም ያስረዳሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ፣ እስራኤል በኢራን የኑክሌር ጣቢያዎች ላይ ጥቃት የምትሰነዝር ከሆነ

በቀጣናው ከሚፈጠረው ግጭት በተጨማሪ ርምጃው የኢራንን የኑክሌር መሣሪያ የመገንባት አቋሟን የበለጠ ሊያጠነክረው እንደሚችል ተናግረው ነበር።

ግሮሲ ‹‹የኢራን ባለሥልጣናት እስራኤል ጥቃት የምትሰነዝር ከሆነ ከባድ የአጸፋ ምላሽ እንደሚኖር ነግረውኛል። በእስራኤል የሚፈፀም ጥቃት የኢራንን አቋም የበለጠ ከባድ ሊያደርገው ይችላል። ኢራን ከኒውክሌር ስምምነት (Treaty On the Non-Proliferation of Nuclear Weapons) ልትወጣም ትችላለች›› በማለት ለእስራኤል መገናኛ ብዙኃን መግለፃቸው ይታወሳል።

ኢራን ድርድሩ በስምምነት ሳይቋጭ ቀርቶ አሜሪካ ጥቃት የምትሰነዝርባት ከሆነ በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ጣቢያዎችን እንደምትደበድብ ዝታለች። የሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር አዚዝ ናስርዛዴህ፣ አሜሪካ በኢራን ላይ ቀድማ ጥቃት የምትከፍት ከሆነ ኢራን በቀጣናው የሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮችን ኢላማ ያደረገ ምላሽ እንደምትሰጥ ተናግረው ነበር።

አሜሪካ እስራኤል በኢራን ላይ የፈፀመችው ጥቃት እስራኤል በተናጠል የወሰደችው ርምጃ እንደሆነና በጥቃቱ ተሳትፎ እንደሌላት ብትገልጽም ኢራን ግን እስራኤል ያለአሜሪካ ፈቃድና ይሁንታ ይህን ጥቃት እንዳልፈፀመችው ታምናለች። የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ እስራኤል ካለአሜሪካ ትብብርና ፈቃድ ይህን ጥቃት እንዳልፈፀመችውና ኢራን በጥቃቱ የተሳተፉትን ሁሉንም አካላት ኢላማ ያደረገ ምላሽ በመስጠት ቴህራን ለተፈፀመባት ጥቃት ምላሽ የመስጠት ሕጋዊና ተገቢ መብት እንዳላት ታሳያለች ብሏል።

የአሜሪካ ባለሥልጣናትም ኢራን አሜሪካን የሚጎዳ ማንኛውንም ድርጊት እንዳትፈፅም አስጠንቅቀዋል። ኢራን በአካባቢው በሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ሰፈሮች ላይ ጥቃት የምትሰነዝር ከሆነ ግን አሜሪካ በቀጥታ ጦርነቱን ተቀላቅላ ኢራንን ስለምታጠቃ ይህ ዓይነቱ አጋጣሚ ድርድሩን ሙሉ በሙሉ ያከሽፈዋል።

በኒውክሌር ጉዳይ ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ኢራን ወታደራዊ ርምጃ እንደሚወሰድባት በተደጋጋሚ ሲናገሩ የነበሩት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ግን አሁንም ኢራን ወደ ድርድሩ እንድትመለስ እያሳሰቡ ነው። ከአርብ ዕለቱ የእስራኤል ጥቃት በኋላ ባወጡት መግለጫ፣ ኢራን አሁንም የድርድር አማራጭን እንድትቀበል የሚያስችል እድል እንዳላት ገልጸዋል።

ትራምፕ የእስራኤልን ጥቃት ባወደሱበት መግለጫቸው፣ ኢራን በኒውክሌር ፕሮግራሟ ላይ ከስምምነት ላይ ካልደረሰች ከአሁኑ የከፋ ከባድ ጥቃት እንደሚገጥማት አስጠንቀቀዋል።

‹‹ኢራን ወደ ስምምነት እንድትመጣ በተደጋጋሚ ዕድል ሰጥቻታለሁ። ከሚያውቁት በእጅጉ መጥፎ የሆነ ነገር ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ነግሬያቸዋለሁ። አሜሪካ በዓለም ላይ ያሉ ዘመናዊ የሆኑ የጦር መሣሪያዎችን በሙሉ መሥራቷን፣ እስራኤል እነዚህ የጦር መሣሪያዎች በብዛት እንዳሏት እንዲሁም ሌሎች መሣሪያዎችን ገና እንደምትጨምር እና እስራኤሎቹ መሣሪያዎቹን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው እንደሚያውቁም ለኢራኖቹ ነግሬያቸው ነበር ነው ያሉት።

ከዚህ የከፋ ነገር ሊፈጠር ይችላል። ብዙ ውድመቶችንና ሞቶችን አይተናል፤ ወደ ስምምነት ለመምጣት ግን አሁንም አልረፈደም። ከመርፈዱ በፊትና የኢራን ግዛትን ለማዳን ኢራን ወደ ስምምነት በመምጣት ተጨማሪ ሞት እና ውድመት ታስቀር። ሁሉም ነገር ከመጥፋቱ በፊት ኢራን ስምምነት ማድረግ አለባት፤ ‹በአንድ ወቅት የኢራን ኢምፓየር ነበር› እንዳይባል ታድርግ›› ብለዋል።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You