
ቢሾፍቱ፡- ከምርመራ እስከ ክስ ሂደት በአግባቡ ለመከታተል የሚያስችል ግልጽ፣ በየደረጃው ተጠያቂነት ያለበትን ሥርዓት ለመገንባት የሚያግዝ አዲስ ሲስተም ለማበልጸግ በሂደት ላይ እንደሚገኝ ፍትህ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የፍትህ ሚኒስትሯ ሃና አርአያሥላሴ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በተለይ ከፖሊስ እና ወንጀል ከሚያጣሩ አካላት ጋር የተሻለ ቅንጅት እንዲኖር የጋራ እቅዶች እየወጡ ናቸው፣ የመለኪያ ሥርዓቶችም እየተስተካከሉ ይገኛሉ፡፡
የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ሥርዓቱ በቴክኖሎጂና በአሠራር ለመደገፍ በርካታ ሥራዎች እንደሚቀሩ ጠቁመው፤ ባለፉት ዓመታትም ሊተገበሩ የተሞከሩ ብዙ ሥርዓቶች (ሲስተሞች) መኖራቸውንና የወንጀል ምርመራ ሥርዓቱን ማዘመን አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የተጀመሩ መልካም ተግባራት ቢኖሩም በርካታ ሥራዎች ይቀሩናል ያሉት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሃና፤ በእንዲህ አይነት ተግባር ውጤታማ ሊሆን የሚቻለው አሠራሮች በአግባቡ ሲዘረጉ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
መረጃ ከሚሰጡ አካላት ጋር የበለጠ ግንኙነትን ማጠናከርና መሰል ተግባራት ተደምረው በክስ አመሰራረት፤ ፍርድ ቤት ሄዶም ክስ የሚመሰረትበትን ጊዜ በማሻሻል ውጤት ለማምጣት ትኩረት ተደርጎ መሥራት ይገባልም ነው ያሉት፡፡ በፍትህ ዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በፌዴራልም በክልልም ያሉ የተለያዩ የፍትህ ተቋማት በተቀናጀ መልኩ ሥራቸውን መሥራት የሚያስችል የሶስት ዓመት እቅድ ተቀርፆ የሁለት ዓመት ትግበራ እየተጠናቀቀ ይገኛልም ብለዋል፡፡
ከለውጥ ትግበራው ቁልፍ ጉዳዮች መካከል የመሰረተ ማህበረሰብ ፍትህ ተጠቃሽ መሆኑንም ገልጸው፤ ከመደበኛ የፍትህ ሥርዓቱ ትይዩ የሆኑ የፍትህ ሥርዓቶችን እውቅና በመስጠት የመሰረተ ማህበረሰብ ፍትህ እንዲስፋፋ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
እንደሀገር መደበኛው ወይም የመንግሥት የፍትህ ሥርዓት ከሌላ ሀገራት ልምድ ተወስዶ የተቀመረ ላለፉት 70 እና 80 ዓመታት በሥራ ላይ የዋለ መሆኑን አውስተው፤ ከእዚህ ትይዩ ማህበረሰቡ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ባህላዊ የግጭት መፍቻ ሥርዓቶችን ሕጋዊ ሥርዓት ለማላበስ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ለባህላዊ የፍትህ ሥርዓቶች እውቅና ሳይሰጥ ቢቆይም ማህበረሰቡ መደበኛ ባልሆነ መንገድ የግጭት መፍቻ ሥርዓቶችን እንደሚጠቀም አስታውሰዋል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት በለውጥ ጊዜው አንዱ በትኩረት እየተሠራ በነበረው የመሰረተ ማህበረሰብ ፍትህ ተግባር ከለውጡ በፊት ቀድመው ጀምረው እውቅና የሰጡ ክልሎች እንዳሉ አውስተው፤ ዘንድሮ አራት ክልሎች የባህላዊ ፍርድ ቤቶችን እውቅና የሚሰጡ ሕጎችን ማውጣታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በተግባሩ ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል ያሉት ወይዘሮ ሃና፤ የፍትህ ሥርዓቱ የሚለካበት ለህብረተሰቡ የሚፈጥረው አመኔታ አለ ብለዋል፡፡
ህብረተሰቡ በመደበኛ የፍትህ ሥርዓቱ በፍርድ ቤት የሚያገኘው ፍትህ እንዳለ ሆኖ፤ የለመዳቸው ባህላዊ ተቋማት ሕጋዊ እውቅና በመሰጠቱ አማራጭ የግጭት መፍቻ በመሆን ወደ ፍርድ ቤት ይሄድ የነበረውን ጫና እንደሚቀንስም ተናግረዋል፡፡
ለህብረተሰቡ የፍትህ ጥያቄ በስፋት ምላሽ እየሰጠ ይገኛል፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ያሉ የባህል ፍርድ ቤቶች ለብዙ ዓመታትም ሥራ ላይ የቆዩ በመሆናቸው ውጤቶች ተገኝተዋል፤ ለሌሎችም ልምዶች እየተወሰደ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
ሀገር አቀፍ የፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን (የለውጥ ሂደት) የሶስት ዓመታት ትግበራ፤ አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን፣ ቀልጣፋና ጥራቱ የተጠበቀ ማድረግን ጨምሮ 10 በዋና ዋና አምዶች ዙሪያ የሚተገበሩ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም