እንደ መግቢያ
ዓለም እየተጨነቀች ባለበት በአሁኑ ወቅት ፈፅሞ የማይታመኑ ነገሮች እየተሰሙ ነው። አንዳንዶቹ ጉዳዮች የሰው ልጅ መልካምነት ይህን ያክል ስለመግዘፉ ሰብዓዊነት ከመስፈሪያው አልፎ ከአፍ እስከ ገደፉ የተሸከሙ የዋሆች ስለመኖራቸው ያሳብቃል።
በሌላ ጎኑ ደግሞ የሰዎች ልጆች የጭካኔ ልክ መጠኑ አልፎ ለልኬት ሲያስቸግር እና ‹‹ይህማ ሲያንሰው ነው›› የሚያስብሉ ሁኔታዎች ይስተዋላሉ። በሌላ ጎኑ ደግሞ ሰዎች ራሳቸውን ምንኛ ይወዳሉ ብለን ለመጠየቅ ያስገድደናል። የዓለም ህዝቦች የኑሮ ደረጃ መበላለጥን ፍንትው አድርጎ ለመረዳትም ያግዛል። በእነዚህ ዳገት እና ቁልቁለት ከበዛባቻው ሁኔታዎች ውስጥ እንዲህም ይኖራል ወይ የሚያስብሉ አያሌ ክስተቶችን በአጭሩ ለመዳሰስ እንሞክራለን።
የተፈቱ እጆች
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ እያለ ሁለት ቁልፍ ፈተናዎች ነበሩበት። ሆኖም ሁለቱንም ወደቀ። የመካከለኛ ደረጃ ተማሪ እያለም ፈተና ከመውደቅ አልዳነም። ይህ ሰው ስኬት ለእርሱ ያልተፈጠረች ይመስል ለውድቀት ሦስት ጊዜ እጁን ሰጠው። ኮሌጅ ለመግባት ፅኑ ፍላጎት ቢኖረውም መግቢያ ፈተናዎቹን ሁለቴ ወስዶ በሽንፈት ተመለሰ። ከምንም በላይ የሚገርመው ደግሞ ያመጣው ውጤት አሳዛኝ ነበር። በተለመደው መንገድ መውደቅ አንድ ነገር ቢሆንም በሂሳብ ትምህርት ከ120 ነጥብ እጅግ በጣም ዝቅተኛ የተባለውንና ለጆሮ እንግዳ የሆነ አንድ ማምጣት ግን በርግጥም ከባድና አሳፋሪም ነበር ትምህርት ቤት ውስጥ ደብተር በቦርሳ አንጠልጥሎ ለሚሄድ ሰው። ውድቀቱ በዚህ አላበቃም እንደ ጅረታ ተያይዞ ይቀጥላል። ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ 10 ጊዜ አመልክቶ ውድቅ ተደርጎበታል ይህ ሰው።
በውጣ ውረዶች ውስጥ ከኮሌጅ ተመርቆ ከወጣ በኋላ ደግሞ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስራ የመቀጠር ፅኑ ፍላጎት የነበረው ቢሆንም ሰላሳ ስራ እድሎች በተከታታይ ቢሞክርም አልተሳካለትም። በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ ግን ተስፋ አልቆረጠም በመጨረሻ አንድ ስኬት ይኖራል አሊያም ደግሞ አልሸነፍም ብሎ ለራሱ ተናግሯል።
ኬ ኤፍ ሲ የተሰኘ ድርጅት ስራ አወጣ። በዚህም ደስተኛ ሆነ። በዚህኛው ዙር ግን በለስ ቀንቶት ሥራ ለማግኘት የሚያደርገው ጥረት በድል እንደሚደመደም አስቦ ወደፊት ተራመደ። ብዙ ፈተናዎችን አልፈው ለስራ የመጡት 24 ነበሩ። 23 ሰው አለፈ በሚደንቅ ሁኔታ የወደቀው አንዱ ሰው ይህ ታሪኩ ከላይ ሲተረክ የመጣ ሰው ነው። አሁንም ግን ተስፋ አልቆረጥንም።
‹‹ዛሬ ከባድ ነው…ነገም የከፋ ሊሆን ይችላል… ከነገወዲያ ግን መልካም ይሆናል›› አለ። ይህ ሰው በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ረብጣ ዶላሮችን በመቁጠር የሚታወቀውና ለተቸገሩት ቀድሞ በመድረስ የሚታወቀው ቻይናዊው ጃክ ማ ነው። ይህ ሰው ከዚህ ሁሉ ውድቀት በኋላ ቻይናን የቀየረ አማዝኦንን መሰል የአሜሪካ ካምፓኒዎችን የሚገዳዳረውን አሊባባን የመሰረተ እና እዚህ ደረጃ ያደረሰ ነው።
በመስጠት የበለጠ ማግኘት አንዳለ የሚያምነው አሊባባ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ለተለያዩ ሀገራት በተለይ ለአፍሪካ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጓል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአፍሪካ አገራት ቀዳሚው የክፉ ጊዜ ደራሽ ሆኗል። ከንክኪ መከላከያ ልብሶች፣ የመተንፈሻ መሳሪያዎች (ቬንትሌተሮች)፣ የሙቀት መለኪያዎች፣ የሕክምና ጓንቶች እና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች ለአፍሪካውያን በሦስት ዙር እንዲከፋፈል ልኳል።
በዚህ ረገድ ሰዎች ስለ ሰብዓዊነት ምንኛ እንደሚጨነቁ አንዱ ማሳያ ሲሆን፤ አፍሪካም የምንጊዜም
ባለውለታዋን ያገኘች ይመስላል። ወትሮም የአፍሪካን ሀብት ለመቀራመት የሚቀድማቸው የማይገኙ አገራት ደግሞ ለልገሳው እጃቸውን አጣጥፈው ራሳቸውን ብቻ ለማዳን ሲታትሩ ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ ፍንትው አድርጎ ለመረዳት ያግዛል። በዚያው ልክ ደግሞ የእነዚህ አገራት ባለሀብቶች ከአፍሪካ ሀብት መቀራመት እንጂ የአፍሪካ ጤና ደንታ እንደማይሰጣቸው የማንቂያ ደውል ይመስላል።
ከሞት ሽሽት
አሜሪካ አያሌ ዜጎቿን covid 19 መንጠቁን ተከትሎ የሀገሪቱ ቱባ ቱባ ባለፀጋዎች መጠጊያ መሸሸጊያ በመላው ዓለም እያሰሱ መሆኑ ደግሞ አግራሞት ፈጥሯል። ባለፀጋዎቹ መሸሻ ያሉትም በኒውዝላንድ በሚገኝ ቄንጠኛ እና እጅግ በውድ የተገነባ የመሬት ውስጥ ምሽግ ሲሆን ከሞት ለማምለጥ ወደር የለሽ ቦታ እንደሆነ በዓዕምሯቸው የታሳለ ስ ፍራ ሆኗል።
ታዲያ ጉደኛዋ ኒውዝላንድ እንኳን አይደለም ለመጤው የኮረና ወረርሽኝ ቀርቶ ለሚፈራው እና ለዓለም ፍፃሜ ወቅት ‹‹Doomsday› የፍርድ ቀን መሸሸጊያ የሚሆን ስፍራ በሰውኛ መጠን መገንባቷንና ይህም መነጋገሪያ መሆኑ የሰው ልጅ ምንኛ ራሱን አንደሚወድና ፈጣሪን አንዴት እንደሚገዳደር የሚያሳይ ነው።
ይህው ቄንጠኛ እና የሰው ልጅ ከዚህ በኋላ ወዴት ይመጥቃል የተባለው መኖርያ በትንሹ 720 ሚሊየን ዩሮ በልመና እና በወረፋ መግዣው ነው። ይህው በከፍተኛ ጥሪት የተገነባው መሸሸጊያ ባለፀጋ አሜሪካውያኖቹ ዓለምን የሚፈትነውን COVID 19 እና ሞትን ለማምለጥ መርጠውታል። መርጠው ብቻ አልቀሩም ያላቸውን ዶላር መዠረጥ አድርገው የኒውዝላንድን ኪስ ለመሙላት ተገደዋል። ብቻ ከዚህ ክፉ ወረርሽኝ ለመዳን የትም ይሁን የትም ለመሄድ ወስነው ጓዛቸውን ሸክፈው ኒውዝላንድ ከትመዋል።
በኒውዝላንድ የሚገኝው በቱጃሮቹ እና ቅምጥል ባለሀብቶች ፍላጎት የጨመረለት ምሽግ በውስጡ፤ የተጣራ ንፁህ አየር፤ ለዘመናት፤ የሚያስፈልጉ ቅንጡ ቁሳቁሶች፤ የስፖርት መንቀሳቀሻ፤ ለአንድ ሰውም ከተፈቀደው በላይ ዕድሜ የሚበቃ የማይነቅዝ እህል እና ሌላም ሌላም ውድ ይሆኑ ነገሮችን ይዟል።
የተለየ የተባለው ይህ ስፍራ እና መጠለያ በዓለም እጅግ ውድ ቅንጡ እና የኑሮን የመጨረሻውን ደረጃ ያልነቀነቀ ቦታ መሆኑን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን እየተቀባበሉ ሰው ለመኖርና ራሱን ለማዳን ምን ያክል ርቀት አንደሚጓጓና ፍላጎቱም ህልቆቢስ መሆኑን ያሳያል።
”ቀድሞ ነበር እንጂ…›‘
‹‹ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ወጪት ጥዶ ማልቀስ›› የሚለው አገርኛ ብሂል አሁን እያየነው ነው። የዓለም ጤና ድርጅትን ምክር የዘነጉ ሀገራት ኮቪዲ 19 ስርጭትን ለመግታት አምብዛም የተሳካ ሥራ አልሰሩም ሲሉ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ሰሞኑን ለመገኛኘ ብዙሃን ተናግረዋል።
ኮቪዲ 19ኝን እንደፈንጆቹ አቆጣጠር በጃንዋሪ 30 ቀን 2020 ዓለም አቀፍ አደጋ ነው ብሎ ሲያውጅ አለም በትኩረት ሊሰማ ይገባው እንደነበር በመግለፅ ቀድሞ ያልተጠነቀቁ እየተጎዱ መሆኑን ይናገራሉ።
‹‹ዓለም አቀፍ ስጋት ነው ብለን ስንናገር ከቻይና ውጪ 81 ሰው ብቻ ነበር ቫይረሱ የተገኘበት። አፍሪካና ላቲን አሜሪካ አልገባም ነበር። አውሮፓም ቢሆን 10 ሰው ነበር የተገኘበት›› በማለት ድርጅታቸው አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ እንደሰጠ ይነጋራሉ።
ይሁንና ግን በርካታ ግለሰቦችና ስመ ገናና መንግስታት የዓለም ጤና ድርጅት በወቅቱ በቂ መረጃን አልሰጠንም ሲሉ ይወቅሳሉ። በተለይ ደግሞ አሜሪካ እና ታይዋን በአንድ ጎራ ተሰልፈው የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ጭምር አስከማንፀባረቅ ደርሰዋል። የሆነው ሆኖ ግን ቀደም ሲል መወሰድ የነበረበት ጥንቃቄ ባለመወሰዱ አሜሪካ በአሁኑ ወቅት እጅግ ፈተና ውስጥ ገብታለች። የዓለም ጤና ድርጅትን መረጃ የሰሙት ደግሞ በመጠኑም ቢሆን ዜጎቻቸውን ታድገዋል።
ምን እናድርግ?
በምጣኔ ሀብት የደቀቀች አህጉር ብሎም አገር ላይ ሆኖ ከሞት ለመሸሽ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ረብጣ ዶላር መዥረጥ አድርገን ራሳችን እንታደጋለን የሚለው ነገር ከቶውንም አያስኬድም። ዓለም ላይ ከመጣው ወረርሽ እንድናለን በሚል ብሂል መዘናጋትም የማያባራ ለቅሶ ውስጥ ከተናል። ሙሉ ለሙሉ በራችን ዘግተን ከቤት እንዋል ማለትም ጉድጓዷ ተደፍኖ ውሃ የተለቀቀባት ዓይጥ እንሆንና አማራጫችን ሞትና ሞት ብቻ ይሆናል። በመሆኑም መንግስት ዜጎን ለመታደግ ሲል እያደረገው ያለውን ዘርፈ ብዙ ጥረት ለማገዝ መዘጋጀት እና ተባባሪ መሆን ግድ ይላል። በተለይ ደግሞ የጤና ባለሙያዎችን ምክር ሃሳብ መስማትና መተግበር የምንጊዜም ወሳኝ መፍትሄ ነው።
በአገራችን ብሂል ‹‹ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ወጭት ጥዶ ማልቀስ›› የሚለው ብሂል ተረቱ በእኛ ላይ ተፈፃሚ እንዳይሆን የተቻለንን ሁሉ ማድረግ ግድ ይላል። ቁልቁለት ከዳገት በበዛባት ዓለም፤ ቀድሞ ከመጠንቀቅ የተሻለ የለም። በአጭሩ ለአፍሪካ ሃገሮች ብቸኛው የcovid 19 ተህዋሲ መከላከያው እጅን በተደጋጋሚ መታጠብ አስፈላጊ ካልሆነ ከቤት አለመውጣትና መቆጠብ ብቸኛው መፍትሄ ነው። እንዲሁም ‹‹ከፈጣሪ መታረቅ ወደር የሌለው›› መፍትሄ ነው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር