ለሰለጠነ መንገድ- የሰለጠነ አሽከርካሪ

“መንገድ” ማለት በተለምዶ ተሽከርካሪዎች የሚጠቀሙበት ማንኛውም መንገድ፤ የከተማ መንገድ፤ አውራ ጎዳና ወይም መተላለፊያ ሲሆን ድልድይንም ይጨምራል። እነዚህ መንገዶች ደግሞ ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ማንም የሚያውቀው ነው። ትናንት እንዲህ በስፋትና በጥራት መሠራት ባይችሉም አገልግሎታቸው ግን ብዙ ነበር። ወጣ ገባ ሆነው እንኳን ሰዎችን ከሰዎች አገናኝተው ያገበያዩናል፣ የፈለግነውን እንድናገኝም ያደርጉናል። ዛሬ ደግሞ በስፋት፣ በጥልቀት እንዲሁም በቴክኖሎጂ ታግዞ መሠራት ሲጀምር አገልግሎቱ የበለጠ አስተማማኝ፤ የተቀናጀ፤ ዘመናዊና ደህንነቱ የተረጋገጠ ሆኗል።

የመንገድ ትራንስፖርት አስተዳደር የመንግሥትን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ፖሊሲ በአግባቡ ለመተግበር፤ የመንገድ ትራንስፖርት እስከታችኛው የሀገራችን መዋቅር ድረስ ጠንካራ አፈጻጸምና የቁጥጥር ሥርዓት እንዲኖረው ለማድረግና የመንገድ ትራንስፖርት ዘርፉን በቴክኖሎጂ ተደግፎ ተደራሽና አስተማማኝ እንዲሆን ለማስቻል እንደ ሀገር በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። በአሁኑ ጊዜ የኮሪዶር ልማቱ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል እንዲተገበር እየተደረገ ነው። ውጤቱ ደግሞ በብዙ መልኩ እየታየና ብዙ ለውጦችን እያመላከተን ነው።

በኮሪዶር ልማቱ አካባቢው እጅጉን ተቀይሯል። አላፊ አግዳሚውም በየቀኑ እየመጣ ያለውን ለውጥ በአግራሞት መመልከት ከጀመረ ሰንብቷል። እግረኛው ደከም ሲለውም በየመንገድ ዳሩ በተሰናዱ መቀመጫዎች ላይ አረፍ በማለት መንፈሱን ያድሳል። የአካባቢው የማታም ሆነ የቀኑ ድባብ ለየት ያለ ሆኗል። ዜጎች የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የተቻለበት ይመስላል። ምክንያቱም ዛሬ በመንገዱ ጥበት ምክንያት መገፋፋት የለም። አሽከርካሪዎችም ቢሆኑ በአንድ መንገድ መሄዳቸውን ትተው አማራጮችን እንደ ልብ መጠቀም ጀምረዋል። በርካታ ዜጎችም የሥራ እድልን አግኝተዋል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ በደሳሳ ጎጆ ውስጥ፣ ተደጋግፈው ሊወድቁ በሚደርሱ ቤቶች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ዜጎች እፎይታን ማግኘታቸው ነው። በዚህ ቤት ውስጥ ሲኖሩ መጸዳጃ ቤት ለማስመጠጥ የሚገባ መኪና መንገድ የለም፣ ድንገተኛ አደጋ ሲፈጠርም የእሳት አደጋ መኪናም ሆነ አምቡላንሶችን ለማስገባት በእጅጉ ያዳግታል። ከዚያ በተጨማሪም ዘወትር ሕይወታቸው በበጋ በፀሐዩ ፣ በክረምት ደግሞ በዝናቡ በእጅጉ የሚፈተንበት ነበር።

አሁንስ ከተባለ በኮሪዶር ልማቱ የተነሳ ብዙዎች እፎይታን እንዳገኙ በአንደበታቸው ሲናገሩ የምንሰማው ጉዳይ ነው። አዎ ከዚህ እንደምንረዳው መንገድ የሁሉ ነገር መሠረት ነው። ያድናልም ይገላልም። አሁን እንደ ሀገር እየሄድንበት ያለው ርቀት ግን በብዙ መልኩ አወንታዊ አንድምታ ያለው ስለመሆኑ ነጋሪ አያሻንም። ለአብነት ከእግረኛ አንጻር እንኳን ብናነሳው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብቻ የተሠራውን ስናይ አብዛኛው በእግር ጉዞ የሚራመድበት ቅንጡ መንገድ ተሠርቶለታል።

ሙሉ ባይሆንም አካል ጉዳተኛውም በእግሩም ሆነ በሁለት እግር ተሽከርካሪ የራሱ የሆነ መስመር እንዲኖረው እድል ተሰጥቶታል። መኪና የመግዛት አቅሙ የሌለው እንዲሁም በሳይክል ዘና ማለት ለሚፈልግም ቢሆን ዛሬ ላይ በኮሪዶር ልማቱ ጥሩ የመንገድ ደህንነት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለው እድል ተመቻችቷል። ከዚያም ሻገር ስንል በአውቶቢሶች መንቀሳቀስ የሚፈልግ ካለ የራሳቸው መስመር እንዲኖራቸው ተደርጓልና ያንን እድል እንዲጠቀም ሆኗል።

ሀገራችን የመንገድ ደህንነትን ለማስጠበቅ ከዚህ አንጻር ታዲያ እስካሁን ባለው ጉዞዋ ምን ሠርታለች ከተባለ ጥቂት ሃሳቦችን ከተለያዩ መረጃ ምንጮች ያገኘናቸውን አብነት አድርገን እናንሳ። አዲስ ዘመን ጋዜጣ የኢትዮያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽንን ጠቅሶ በወጣው ዜና ያመላከተውን ስናስቀድም ባለፉት ስድስት ዓመታት የመንገድ ግንባታው ባለፉት 20 እና 30 ዓመታት ከተሠሩት ጋር ሲነጻጸር 550 በመቶ እድገት የታየበት ስለመሆኑ ተናግሯል።

የመንገድ ግንባታው ባለፈው ጊዜ ከነበረው 26ሺህ ኪሎ ሜትር ወደ 275 ሺህ ኪሎ ሜትር ከፍ ብሏል። ይህ ደግሞ የሚያሳየን ደህንነቱ የተጠበቀ መንገድ እንዲኖር የማድረግ ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ነው። ይሁንና መንገዶችን በጥራትና በብዛት መገንባቱ ብቻ ፋይዳው ዘላቂነት እንዲኖረው ለማድረግ ይቸግራል። ምክንያቱም መንገዱን የሚጠቀሙበት አካላት በአግባቡ ጥቅም ላይ ሊያውሉት ይገባል። ሕግን መሠረት ያደረጉ ተግባራትም ሊከወኑበት የግድ ነው። በተለይም አሽከርካሪና እግረኞች እያንዳንዱ መንገድ ለምን ዓላማ እንደሚውሉ መረዳት አለባቸው።

ከዚያም ባሻገር እንቅስቃሴያቸውን ሲያደርጉ በአግባቡ መናበብ ይኖርባቸዋል። ለዚህም እንደ አዲስ አበባ ከተማ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ መመሪያና አዋጆች ወጥተዋል። አንዱ እግረኛን የሚያስተምርና ሕጉን ተከትሎ እንዲሄድ የሚያደርገው ነው። እግረኛ በምንም መልኩ ያለ ዜብራ ማቋረጥ የለበትም። መብራትንም ተከትሎ ማቋረጥ የሕይወቱ ዋስትና እንደሆነ ማመን አለበት። በተመሳሳይ ድልድይ የሚያቋርጥበት ሁኔታ፣ መንገዶችን ሲያቋርጥ የሚያደርጋቸው አላግባብ የሆኑ ነገሮች (ስልክ ማውራት፣ ኤርፎን ማድረግ ወዘተ ዋጋ የሚያስከፍሉት እንደሆኑ መገንዘብ አለበት።

ወደ አሸከርካሪው ስንመጣ ደግሞ መጀመሪያ መውሰድ ያለበት ነገር ምን ያህል ለሥራው ብቁ ነኝ የሚለው ነው። ሙያውን ማወቅ ደግሞ ወደ ሕግ ማክበር ያራምዳል። ቸልታ ይሉት ነገርን ያጠፋል። ለሰው ሕይወት መጨነቅን ያመጣል። ከምንም በላይ ደግሞ የራስን ሕይወት ለመጠበቅ ያስችላል። በዚህም የቤተሰብ የመኖር ደህንነት ይጠበቃል፣ ያለአግባብ ወጪዎችንም ይቀንሳል።

ብዙ ጊዜ ከአሽከርካሪዎች ጋር በተያያዘ የሚነሳው ትዕግስት ማጣት ነው። ከዚህ አንጻርም ሕግ አለማክበር ብቻ ሳይሆን ከዚያም ያለፉ ተግባራት ሲፈጸሙ ይስተዋላል።

ለአብነት አንዳንድ መብራት በሌለባቸው አካባቢዎች አቅመ ደካሞች፣ አዛውንቶችና ሕጻናት እንዲሁም ነብሰጡር እናቶችን በአግባቡ ለማሳለፍ ሲቸገሩ ይታያል። በማንኛውም የዜብራ መንገድ ላይ ቅድሚያ ማግኘት ያለበት እግረኛ ቢሆንም አንዳንድ ትዕግስት የሌላቸው አሽከርካሪዎች ግን ከፍተኛ የሆነ አደጋ ሲከስቱና መመለስ የማይቻል ጥፋት ሲፈጽሙ ይታያል። በዚህ ደግሞ የብዙዎች ሕይወት ይቀጠፋል። አሁን ላይ በተለይ የምንሰማውና የምናዳምጠው ነገር በእጅጉ የሚዘገንን ነው።

አሽከርካሪው ጠጥቶ አለያም ሃሳብ ውስጥ ገብቶ ከዚያም ሲያልፍ ደግሞ አጠቃላይ የመኪናውን ደህንነት ሳያረጋግጥ በመነሳቱ ብዙ አደጋዎች እየተከሰቱ ይገኛሉ። የእኛ ጉዳይ ግን ‹‹የመንገድ ደህንነት ጉዳይ›› በመሆኑ ከአሽከርካሪ ጋር የምናነሳው በዋናነት ለእግረኛ ቦታ አለመስጠት፣ የተከለከሉ ቦታዎች ላይ አለማቆምና አለመጫን እንዲሁም ቅጣትን ለመዳን ሲባል አላግባብ መንዳትና መብራቶችን ሳይቀር ጥሶ መሄድ እንደሆነ በብዙ መልኩ የሚታይ ነው። እናም ይህ ሁሉ ተግባራቸው በሕግ የሚስተካከል ሳይሆን በአቅምና ሕግን ተረድቶ በመተርጎም ነውና ይህንን ማድረግ ይገባል ማለት እንፈልጋለን። በእርግጥ እነዚህ አይነት ስህተቶች ዝም ብለው የሚመጡ አይደሉም። በቂ እውቀት ካለመጨበጥ ጋርም ይያያዛሉ።

አንዳንድ አሽከርካሪዎች ዛሬ ላይ የመንጃ ፈቃድ ለማውጣት ብዙ አይቸገሩም። በማሰልጠኛ ተቋማት ውስጥ ለሚሠሩ አንዳንድ የዜጎች ደህንነት ለማያሳስባቸው አካላት ገንዘብ በመስጠት የመንጃ ፈቃዱ ቤታቸው ድረስ እንዲመጣላቸው ይሆናል። አሰለጣጠኑም ቢሆን ብዙ ችግሮች የሚስተዋሉበት ነው። በተለይም ከአሰልጣኞች ጋር ተያይዞ ብዙ የሚስተዋሉ ነገሮች አሉ። በስፋት እንደሚታየው ለወራት የሚፈጀውን የተግባር ልምምድ ትምህርት በሦስትና በአራት ቀናት ይጨርሱና ገንዘባቸውን ተቀብለው ይሸኙታል።

አንዳንዶች ደግሞ በአግባቡ ስልጠናውን ቢወስዱም በቂ እውቀት ሳያስጨብጡ ‹‹ ጨርሰሃል ነገር ግን ፈተናውን ለማለፍ ከእኛ ጋር መደራደር አለብህ›› ተብለው ገንዘባቸውን ይሰበስቡና ያሰናብቷቸዋል። ለዚህም የሚሰጣቸው ተማሪ ብዛትና ያላቸው ቀን በእጅጉ ወሳኝ ነው። ሁሉንም ተማሪ በአግባቡ ለማሰልጠን የሚፈልጉ እንዳሉ ሁሉ የሚገኘው ጉርሻና ከሚያሰለጥኑት ተማሪ የሚያገኙት ገንዘብ እንዳያንስባቸው ሲሉ የሰውን ሕይወት ከአደጋ የሚጥሉ ጥቂቶች አይደሉም።

እንደ ሕግ አንድ አሽከርካሪ ምን ያህል ሰዓት የንድፈ ሃሳብ ትምህርት መማር አለበት፣ ምን ያህሉን ሰዓት ደግሞ በልምምድ ወይም በተግባር ማሳለፍ አለበት የሚል ተቀምጦ ይሆናል። ምን አይነት ቦታ ላይ በምን አይነት መኪና መነዳትና እንዴት ይነዳ የሚለውም እንዲሁ የራሱ ገደብና የስልጠና ሥርዓት ይኖረዋል። ነገር ግን ከሁሉም በሚሸቀብ ሰዓት አማካኝነት በቂ ስልጠና ለማግኘት ያልቻሉ ብዙዎች ናቸው።

ይህ ደግሞ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ዜጋ ከፍተኛ አደጋን እየጋረጠ እንደሆነ ማንም ይረዳዋል። እና ምን ይሁን ከተባለ ከመንግሥት አካላት በኩል የመንገድ ደህንነቱ ጉዳይ በዚህ ልክ እየተሠራበት ከሆነ የአሽከርካሪና የእግረኛ እንዲሁም የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማትና አሰልጣኞች በአግባቡ የሚታዩበትን እድል በስፋት ማየት ይገባል። እነርሱም ተጠያቂ የሚሆኑበትን አሠራር መፍጠርም ያስፈልጋል። ከሙስና የሚጸዱበትን የቴክኖሎጂ አማራጮችን ማስፋትም ተገቢ ነው።

ሌላው የአሽከርካሪ ተቋማት ኃላፊነት ነው። በእነርሱ እጅ ላይ ከ130 ሚሊዮን ያላነሰ ሕዝብ አለ። እነርሱ በቀረጹት አሽከርካሪ አማካኝነት የሚድን አልያም የሚሞት ሰው እንዳለ መገንዘብ ይጠበቅባቸዋል። ለዛሬ ደስታቸው ተረካቢውን ዜጋ ማጥፋት የለባቸውም። የችግሩ ሰለባ የሚሆነው ሌላ ሰው ሳይሆን ወንድምና እህታቸው አለያም ዘመዳቸው እንደሆነ ማመን አለባቸው።

በስልጠና ሥራቸው ይህንን እያሰቡ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል። አሰልጣኞችም እንዲሁ የሚያሰለጥኑት ሰው የነገ የተሻለ ሕይወት መሪ እንዲሆን ማስቻል አለባቸው። ምክንያቱም ስልጡን አሽከርካሪን ስንፈጥር ስልጡን እግረኛን እናያለን። በሁሉም ዘርፍ ስልጡን ማህበረሰብን እንገነባለን። ስልጡን ማህበረሰብ ካለ ደግሞ የተገነባችና ያደገች ሀገርን እናያለን። ስለሆነም በየደረጃው ያለነው ሰዎች የመንገድ ደህንነታችን በሥራችን እንዲረጋገጥ እንሥራ በማለት የያዝነውን ሃሳብ ቋጨን። ሰላም!!

ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

ክብረ መንግሥት

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You