ዘግይቶም ቢሆን ወደ መሬት ሊወርድ የተቃረበው ፋብሪካ

ሰሞኑን አንድ በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት በስፋት እየተንሸራሸረና በርካታ አስተያየቶችን (በአብዛኛው ድጋፍ) እያስተናገደ ያለ አንድ መሠረታዊ ጉዳይ ያለ ሲሆን እሱም የማዳበሪያ ፋብሪካ መገንባቱ ነገር ነው።

ዓለም እንደሚያውቀን ገበሬዎች ነን፤ ኢኮኖሚያችንም ግብርና መር ሲሆን፤ አጠቃላይ ሕይወታችንም የተንጠለጠለው ግብርና ላይ ነው።

በእዚህ ጉዳይ ላይ መጻፋችን ለቅንጦት ሳይሆን ስለሚመለከተን ነው። የሚመለከተን ደግሞ በሩቁ ሳይሆን በቅርበት – ባለ ድርሻ አካል ስለሆንን፣ ባለድርሻነታችንም ፕሮፌሰር ፍሬው መክብብ እንደሚሉት “እህል የሚበላ ሁሉ የግብርና ባለ ድርሻ አካል” ስለሆነ ነው።

ስለማዳበሪያ ስናነሳ ከሁሉም በፊት ወደ አእምሯችን ጓዳ ከተፍ የሚለው አርሶ አደሩ ስለ መሆኑ መጠራጠር አይቻልም። ለእዚህ ደግሞ ከበቂ በላይ ምክንያቶች ያሉ ሲሆን፤ ዋናውና ቀዳሚው ሰኔ ግም ሲል ገበሬን ለስቃይ የሚዳርገው ማዳበሪያ እየናረ የሚመጣው ዋጋ ነው።

ስለእውነት ለመናገር የዘርፉ ምሁራን ያላቸውን ያልወረወሩበት፣ ምክረ-ሃሳባቸውን ያልሰነዘሩበት ወቅት የለም። ግብአቶች (አንዱ ማዳበሪያ ነው) ይሟሉና ግብርናው ይዘምን ዘንድ ወዘተ ያልተመከረበት ጊዜ ስለመኖሩ መረጃ የለም። ይህ ሁሉ ይሁን እንጂ ለግብርናው ዘርፍ ቁልፍ የሆነው ማዳበሪያን በተመለከተ ሰኔ ሲመጣ ርዕሰ ጉዳይ ከማድረግ ያለፈ ተግባር ሲፈጸም አልታየም።

ከምክረ ሃሳቦቹ መካከል በቅርቡ በጀርመን በግብርና ሙያ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የዶክትሬት ዲግሪውን የተቀበለው ደረጀ ታምሩ የሰጠው ሲሆን፣ “ኢትዮጵያ በምግብ ራስዋን እንድትችል ግብርና ሪፎርም ወይም መንግሥት በግብርና ላይ ያለውን ፖሊሲ ትኩረት ሊያደርግበት ይገባል። አሁንም ለግብርና ትኩረት መሰጠት አለበት። መንግሥት ትኩረት ቢሰጥ ነገሮች ይሻሻላሉ። ምሁራኑ ፖሊሲው አመቺ ስላልሆነላቸው ተግባራዊ ማድረግ አልቻሉም። ገበሬው ማለዳ በሬዎቹን ይዞ፣ ሞፈር ቀንበሩን ተሸክሞ ወደ ግብርና ሲሰማራ ማየት በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚያሳፍር ነው፤ ያማል። ይህንን ከግብርና ምሁራን፣ በተለይም ከውጭ ሀገር ምሁራን ጋር በጉዳዩ ላይ ማውራት የሚያሳፍር ነው።” የሚለው ለጥቅስ የሚበቃ ሲሆን፤ የእዚህ የማዳበሪያ ፋብሪካ መገንባት የአስተያየቱን ተገቢነትና ገንቢነት ያረጋግጣልና ይበል የሚያሰኝ ነው።

ከተለያዩ መረጃዎች መገንዘብ እንደተቻለው በአዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ መሠረት በ2030 ዓ.ም የግብርናውን መዋቅራዊ ሽግግር በማረጋገጥ በገጠር መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣትና ለሀገር ብልፅግና ጉልህ ሚና የሚጫወት ሆኖ የማየት ርዕይ ሰፍሯል። ይህ ሰነድ ያለምንም ጥርጥር ማዳበሪያንና ተያያዥ ጉዳዮችን ትኩረት ሳይሰጣቸው ሊያልፋቸው የሚችል ሰነድ አይሆንም። በመሆኑም አሁን ሊገነባ አጓጊ፣ እጅግ ዘመናዊ የሆነው ዲዛይን ሥራው ያለቀው የማዳበሪያ ፋብሪካ የእዚህ ከ20 ዓመታት በላይ በሥራ ላይ ቆይቶ ሚያዝያ 17/2016 ዓ.ም የተሻሻለው ሰነድ ድጋፍ አለው ማለት ይቻላል።

ፖሊሲውን አስመልክተው ሲወጡ በነበሩ ጽሑፎች ላይ እንደተብራራው፤ አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ መዘጋጀቱ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የግብርና ምርትና ምርታማነት እድገትን በማረጋገጥ፣ ለሀገራዊ ሥርዓተ ምግብ መሻሻል እንዲሁም የምግብ ዋስትናና የምግብ ሉዓላዊነት እንዲረጋገጥ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል። የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ዘላቂ አጠቃቀም ለማሳደግ፣ ፖሊሲው ከውጭ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ፣ አርሶ አደሩ መሬቱን ተጠቅሞ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኝና የገጠሩን ሕዝብ የአኗኗር ዘይቤ ለማሻሻል መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑ በስፋት እየተገለጸ ይገኛል።

በአዲስ መልክ የተሻሻለው ይህ ፖሊሲ እነዚህን ሁሉ ችግሮች እንደሚፈታ የታመነበት ከሆነ፤ በጉዳዩ ላይ ያዋራኋት የሥራ ባልደረባዬ መሬት ያለ ማዳበሪያ ማለት ምጣድ ያለ ማሰሻ ማለት ነው እንዳለችው ሁሉ፤ ሳይወድ በግድ ማዳበሪያን እንዲለምድ የተገደደው መሬት ያለማዳበሪያ ምርት አምጣ ቢሉት ሊሆን የሚችል አይደለምና የፋብሪካው መገንባት የዘገየ እንጂ ከእዚህ በኋላ ለደቂቃም ሊጓተት የሚገባው ተግባር አይደለም።

ይህ በመንግሥትና አፍሪካዊው ባለ ሀብት ዳንጎቴ አማካኝነት በሦስት ቢሊዮን ዶላር ወጪ ሊገነባ የታሰበው፤ ከሕዳሴ ግድባችን ቀጥሎ በሁሉም ነገሩ 2ኛ መሆኑ እየተነገረለት ያለው የማዳበሪያ ፋብሪካ መገንባት የሚፈታው ችግር የአንድ የአርሶ አደሩን (ከአጠቃላይ ሕዝቡ 85 በመቶ የሆነውን) ዘመናትን የፈጀ ስቃይ ብቻ አይደለም፤ ፋብሪካው የሁላችንንም ችግር ከመፍታትም ባለፈ በየዓመቱ ለማዳበሪያ ማስገቢያ ወጪ ሲደረግ የነበረውን ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪንም ነው የሚያስቀረው።

ፋብሪካው ከእኛም ባለፈ ምርቱን ለአፍሪካዊያን ወንድም እህቶቻችን ተደራሽ በማድረግ የውጭ ምንዛሪ የሚያሳፍሰን ብቻ ሳይሆን የእነሱንም ችግር ከመፍታት አኳያ የሚጫወተው አህጉራዊ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከእዚህ በመለስ የሚባል አይደለም። በመሆኑም፤ የፋብሪካው መገንባት ከእኛም ባለፈ በመላ አፍሪካ የሚጠበቅና ሲናፈቅም የነበረ ስለመሆኑ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል።

ያለ ማዳበሪያ ግብአት ስለምርትና ምርታማነት ማውራት ጉንጭ ማልፋት ስለሚሆን፤ አርሶ አደሩ ሰኔ በመጣ ቁጥር ጥሪቱን የሚያሟጥጠው ለእዚሁ ለማዳበሪያ ግዥ በመሆኑ (ለእዛውም በስንትና ስንት ስቃይ)፤ የሥራ እድል ከመፍጠር ባለፈ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን አስገኚ በመሆኑና በሌሎች በርካታ ምክንያቶች የማዳበሪያ ፋብሪካው መገንባት ፅድቅ እንጂ ኩነኔ ሊሆን አይችልምና መንግሥት በእዚህ በኩል ለወሰደው ተነሳሽነት ሊመሰገን ይገባል።

በግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You