ባላየ ባልሰማ የማይታለፍ ዐቢይ ጉዳይ

የቆዳ ስፋቷ 1.1 ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር የሆነው ኢትዮጵያ ከዓለማችን 27ኛ ደረጃ ላይ የምትቀመጥ ሰፊ ሀገር ናት። ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ለእርሻ ሥራ መዋል የሚችል 38.5 ሚሊዮን ሔክታር መሬት አላት። ኢትዮጵያ አላት ከሚባለው 120 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ አብላጫው ጠንካራ የሥራ ኃይል መሆን የሚችል ወጣት የኅብረተሰብ ክፍል ነው። ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ122 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ የዝናብ ውሃም ታገኛለች ይባላል። ሀገሪቱ 2.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የከርሰ ምድር ውሃም አላት። ከዚህ በተጨማሪ በየአቅጣጫው እየፈሰሱ ለጎረቤት ሀገሮች ጭምር የተረፉ ከ12 ያላነሱ ዋና ዋና ወንዞችና ተፋሰሶችም አሏት።

ኢትዮጵያ ከ22 ያላነሱ ዋና ዋና ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ሐይቆች ሲኖራት፣ በመስኖ ሊለማ የሚችል ከ5.3 እስከ አሥር ሚሊዮን ሔክታር መሬት እንዳላትም ይነገራል። ራሷን ‹‹የ13 ወር ፀጋ›› እያለች ስትጠራ የኖረችው ኢትዮጵያ ዓመቱን ሙሉ የፀሐይ ብርሃን የምታገኝ ሀገር ናት። ሀገሪቱ በዓመት አንዴ ብቻ ሳይሆን ሁለትም ሆነ ሦስቴ አርሶ ለመብላት የምትቸገር አይደለችም። ኢትዮጵያ ለመራብና ለመቸገር ብዙ ምክንያት የላትም ነው የሚባለው። ሀገሪቱ ለመቸገርና ለመደህየት ራሷን ሆን ብላ ካላመቻቸች በስተቀር ተፈጥሮ ያደላት ባለፀጋ ነች ነው የሚባለው።

ለምሳሌ ለግብርና ከሚሆነው 38 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ውስጥ 16 ሚሊዮን ያህሉ የሚታረስ ሲሆን፣ ቀሪው 20 ሚሊዮን ሔክታር ደግሞ ለእንስሳት ግጦሽ የሚውል መሆኑ ይነገራል። በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ጥንታዊ መሠረት ያለው ነው። የሀገሪቱን 40 በመቶ ጥቅል ምርት የሚሸፍነው ግብርና 80 በመቶ የወጪ ንግድ ምርቶች መሠረት ነው። ግብርና ከሀገሪቱ የሥራ ኃይል ውስጥ 75 በመቶውን ያሰማራ መስክ ሲሆን፣ በአጠቃላይ የሀገር ‹ዋልታና ማገር› የሚል ስም የወጣለት የእያንዳንዱን ሰው ሕይወት የሚነካ የኢኮኖሚ መስክ ነው።

በሌላ መረጃ ደግሞ ግብርና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሠረት ሲሆን፣ 65 በመቶ ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን እንደሚመሩ የአረንጓዴ ትብብር በአፍሪካ ወይም አግራ የተሰኘው ተቋም ባለፈው ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል። የግብርና ዘርፍ የሀገሪቱን አንድ ሦስተኛ ጠቅላላ ብሔራዊ ምርት (GDP) ይሸፍናል። ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ የሀገሪቱ የወጪ (Export) ምርትም እስካሁንም ድረስ በዚሁ ዘርፍ ላይ የተንጠለጠለ ነው። ይሁንና ግብርና በኢትዮጵያ ከእጅ ወደ አፍ ከሚባል ደረጃ የተሻገረ አይደለም በማለት የዘርፉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይሰማል።

ዘርፉ በተለያዩ ጊዜያት በተቀያየሩ መንግሥታት ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶታል ይባል እንጂ፣ የሀገሪቱን አቅም ያህል ፍሬ ያፈራል የሚባልበት ደረጃ ገና አልደረሰም የሚሉም አሉ። መሬት ላይ ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ ሰሞኑን የአማርኛው ሪፖርተር ጋዜጣ “እጅግ አነስተኛ በሆነ ወለድ ለግብርና ዘርፍ የተመቻቸውን ብድር የሚጠቀም መጥፋቱን የሚገልጽ መጣጥፍ ሳይ የተደበላለቀ ስሜት ፈጥሮብኛል። እውነት ለመናገር ግራ አጋብቶኛል። እንቆቅልሽም ሆኖብኛል። መደንገጤም አልቀረም። ለማንኛውም ዘገባውን እንመልከት።

ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ የብድር ወለድ ምጣኔን የተመለከተ ማስተካከያ ስለማድረጉ ገልጾ ነበር። ከሌሎች የቢዝነስ ዘርፎች በተለየ ለግብርና ዘርፍ ተሰጠ የተባለው ዕድል በአጭሩ ቀድሞ በ11 በመቶ ወለድ ይሰጥ የነበረው ብድር ወደ ሰባት በመቶ መደረጉን የሚያመለክት ነው። በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ የብድር ወለድ ምጣኔ በዚህን ያህል ደረጃ መቀነሱ ብዙም ያልተለመደ ነበርና ባንኩ የወሰደው ርምጃ ያልተጠበቀ ሊባል የሚችል ነው። ለግብርና የሚሰጡ ብድሮች የወለድ ምጣኔ በዚህን ያህል ደረጃ እንዲወርድ የተደረገበት ዋነኛ ምክንያት ባንኩ እንደ አንድ የፖሊሲ ባንክ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ነው ሊባል ይችላል። ስለዚህ እንዲህ ያሉ ማበረታቻዎች ማመቻቸቱ እንደ አንድ ሥራው የሚቆጠር ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በአስገዳጅነት የቦንድ ግዥ መመሪያ ከግል የፋይናንስ ተቋማት ወደ ባንኩ ፈሰስ የሚደረግለት ገንዘብ ነበረውና ይህንን ገንዘብ እንዲህ ያለውን ማበረታቻ በመስጠት ጥቅም ላይ ማዋሉ አይገርምም። ለግብርና የሚሰጡ ብድሮች የወለድ ምጣኔያቸው እንዲቀንሱ የተደረገው ዘርፉን ለማሳደግ ምርታማነትን ለመጨመርና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ከፍ ለማድረግ ነው። በዘርፉ ለመሰራማት የሚፈልጉ ሁሉ እንዲበረታቱ ታሳቢ ያደረገም ነው። በወቅቱ ከባንኩ የተሰጠው ተጨማሪ ማብራሪያ የሚያመለክተውም ባንኩ እንደ አንድ ፖሊሲ ባንክ ኃላፊነቱን ለመወጣት ብቻ ሳይሆን ይህንን ዘርፍ ሊያበረታቱ የሚችሉ ውሳኔዎች ሀገራዊ ጠቀሜታ ስላላቸው ነው። ስለዚህ የባንክ ርምጃ የሚደገፍ ነው።

እዚህ ላይ ባንኩ ባመቻቸው ዕድል ምን ያህሉ ተጠቀመ? ምን ያህል አዲስ ኢንቨስተርስ አስገኘ? የሚለው ጥያቄ ወሳኝ ይሆናል። በግል ማጣራት እንደቻልኩት ባንኩ በሰጠው ዕድል የታሰበውን ያህል ተበዳሪ አለመቅረቡን ነው። በዚህ ምክንያት እንደገና የብድር ወለድ ምጣኔውን ለማስተካከል ተገዷል። በሰባት በመቶ ወለድ ለግብርናው ዘርፍ ሊሰጥ ታስቦ የተዘጋጀውም ገንዘብ ለሌሎች የቢዝነስ ዘርፎች ተላልፏል ወይም አልተነካም ማለት ነው። ባንኩ መልካም ይሆናል ብሎ ያሰበው ባለመሳካቱ ድጋሚ የወለድ ብድር ምጣኔውን አስተካክሎ የግብርና ዘርፍ ብድር ወለድ 13 በመቶ እንዲሆን ወስኗልም ተብሏል። ባንኩ ውሳኔውን የከለሰው የጠበቀው ባለመሆኑ ነው።

ይህ ማለት ለግብርና የሚሰጥ ብድር ወለድ በዚህን ያህል ከወረደ በዚህ ዘርፍ ለመሰማራት የሚፈልጉ አዳዲስ ኢንቨስተሮች ሊገቡ ይችላሉ የሚለው ምልከታ ወይም እምነት አልሠራም ማለት ነው። ብድሩ በግብርና ላይ የተሰማሩ ነባር ኢንቨስተሮችም እንዲጠቀሙበት የታሰበ በመሆኑ እነዚህም በሀገሪቱ የመጨረሻው አነስተኛ የወለድ ምጣኔ የቀረበላቸውን ብድር ለመውሰድ እጃቸውን መሰብሰባቸውን ያመለክታል። ለምን በዕድሉ ለመጠቀም አልተቻለም? ለሚለው ጥያቄ የጠራ መልስ ለማግኘት ባይቻልም ሁኔታው ግን ማስገረሙ አይቀርም።

እንዲህ ያለው ብድር ለሌላ የቢዝነስ ዘርፍ ተመቻችቶ ቢሆን ኖሮ ሽሚያው ቀላል እንደማይሆን ይታመናል። ዛሬም ዘላቂ ሀገራዊ ጠቀሜታ ያለው የግብርና ዘርፍ ውስጥ ለመግባት ያለው ፍላጎት ቀዝቃዛ መሆኑን ያሳያል። ባለሀብቶቻችን ወዲያው ወዲያው ትርፍ የሚገኝባቸው ቢዝነሶች ላይ ተጣብቀው መቅረታቸውን ያመላክታል። የተመቻቸ ፋይናንስ እያለ ኢንቨስተሮች የግብርናውን ዘርፍ ለመቀላቀል ማፈግፈጋቸው ግራ ያጋባል።

ለግብርና ኢንቨስትመንት ሥራዎች በቂ ብድር ለዚያውም በዝቅተኛ ወለድ በተመቻቸበት በዚህ ወቅት በዕድሉ ለመጠቀም ፍላጎት ያሳዩ ኢንቨስተሮች በጣት የሚቆጠሩ መሆናቸው ሊያሳስበን ይገባል። እውነት ነው ሊያሳስበን ይገባል።

የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንታችን ስለሆነ ለዘርፉ በሰባት በመቶ ወለድ የቀረበው ብድር ወሳጅ ለምን አጣ!? የዘርፉ ማነቆ ከፋይናንስ የተሻገረ ከሆነ ቁጭ ብሎ መነጋገርን መወያየትን ይጠይቃል። ባላየ ባልሰማ የምናልፈው ጉዳይ አይደለም። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት ሌላ ማሳያ እንቃኝ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለግብርና ዘርፍ የሚቀርበው የብድር መጠን እጅግ አነስተኛ በመሆኑ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ሀገራዊ የግብርና ፋይናንስ ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ በዚያ ሰሞን በተከበረው የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ 20ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት የሀገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት ለሆነው የግብርና ዘርፍ የብድር አቅርቦት አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይህንን ነባራዊ ሁኔታ ለማረምና ለግብርና ዘርፍ የሚቀርበውን ፋይናንስ (ብድር) ለማሳደግ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የግብርናው ዘርፍ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ውስጥ 32 በመቶ ድርሻ መያዙን፣ የሥራ ስምሪት ድርሻውም 64 በመቶ እንደሆነ አቶ ማሞ ምህረቱ ተናግረዋል። አክለውም፣ ይኸው የግብርና ዘርፍ ከሀገሪቱ የወጪ ንግድ ውስጥ ወደ 79 በመቶ ድርሻ እንዳለው ጠቁመዋል። ነገር ግን ዘርፉ እያገኘ ያለው የፋይናንስ አቅርቦት (ብድር) እጅግ አነስተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በ2016 የሒሳብ ዓመት ለግብርና የተሰጠው ብድር መጠን ከጠቅላላው ብድር ከስምንት በመቶ እንደማይበልጥ የጠቀሱት አቶ ማሞ፣ በአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት በኩል ከቀረበው ጠቅላላ ብድር ውስጥ የግብርና ዘርፍ ድርሻ 18 በመቶ ብቻ እንደነበረም አስታውሰዋል። በመሆኑም ይህንን ለመፍታት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሀገራዊ የግብርና ፋይናንስ ትግበራ ፍኖተ ካርታ እያዘጋጀ መሆኑን አስታውቀዋል። ይህንን ፍኖተ ካርታ ከማሳካት አኳያ የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው የጠቆሙት አቶ ማሞ፣ ይህንንም ‹‹የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን በፋይናንስ በመደገፍ ክፍተቱን ለመቅረፍ በምናደርገው ጥረት አካል እንደሚሆን ሙሉ እምነት አለኝ›› ብለዋል። አቶ ማሞ ለኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክን ወቅታዊ የሥራ አፈጻጸም እውቅና ሰጥተዋል።

የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ የዛሬ 20 ዓመት ሲመሠረት መነሻ ያደረገው የኅብረት ሥራ ማኅበራትና አርሶ አደር ሲሆን አዳዲስና ማኅበረሰብ ተኮር የሆኑ አገልግሎቶችን በመጠቀም የአገልግሎት አድማሱን እያሰፋ የመጣ ባንክ ነው። በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ከሚገኙ የግል ባንኮች መካከል አንዱ መሆኑንም ጠቅሰው ባንኩ በጠቅላላ የሀብት መጠን፣ በተቀማጭ ሒሳቡና በካፒታሉ ከዓመት ዓመት እያደገ መምጣቱንም አስታውቀዋል። ስለባንኩ እንቅስቃሴዎች ማሳያዎችን በመጥቀስ የተናገሩት አቶ ማሞ፣ ‹‹ብሔራዊ ባንክ ካወጣቸው የጤናማነት መለኪያዎች አንጻር የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ሲመዘን በአሁኑ ጊዜ እጅግ ጤናማ ባንክ መሆኑ ተረጋግጧል፤›› ብለዋል።

የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ከጥቂት ዓመታት በፊት ችግሮች እንደነበሩበት ያስታወሱት የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ፣ ባንኩ የነበሩበትን ችግሮች ጊዜ ወስዶ በማረም አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ መድረሱ የባንኩን አመራሮችና ሠራተኞች ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ ባንክንም ጭምር እንዳስደሰተ ገልጸዋል። የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክን ልዩ ከሚያደርጉት መካከል በባንኩ ተልዕኮ ውስጥ የፋይናንስ አካታችነትን፣ የዲጂታል ኢኖቬሽን ተግባራትንና የግብርና ዘርፍን በፋይናንስ ለማገዝ ትኩረት መስጠቱ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ማሞ፣ ይህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ አካታችነትን ከማስፋፋትና የሥራ ዕድልን ከማበረታታት እንዲሁም፣ በ2025 መጨረሻ 70 በመቶ ጎልማሶችን የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ካስቀመጠው ስትራቴጂ ጋር የተዛመደ መሆኑን ገልጸዋል። የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ መሠረታዊ ችግሮችን ለመፍታትና የብድር አቅርቦቱን ትርጉም ባለው መልኩ ለማስፋት አዳዲስ መፍትሔዎችን በመፈላለግ ረገድ አርዓያነት ያለው ባንክ ስለመሆኑ ያነሱት አቶ ማሞ፣ ‹‹ከዚህ አኳያ በግሌ መግለጽ የምፈልገው ከሁሉ በላይ ማኔጅመንቱ ተራማጅ መሆኑን ነው፤›› በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። አያይዘውም በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ካሉ የግል ባንኮች ውስጥ አጠቃላይ የመንግሥትን የፖሊሲ አቅጣጫና የማክሮ ኢኮኖሚ አቅጣጫ በውል ከሚረዱና የመንግሥትን አቅጣጫና አካሄድ ከሚከተሉ የባንክ አመራሮች መካከል አንደኛው የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እፈልጋለሁ ብለዋል።

በዚህ ረገድ በተለይ የባንኩን ዋና ሥራ አስፈጻሚ (አቶ ድርቤ አስፋው) ያመሠገኑት ገዥው፣ ‹‹ከተለያዩ የባንክ አመራሮች ጋር ብዙ ውይይቶችን አድርጌያለሁ። ካየኋቸው ሥራ አስፈጻሚዎች መካከል አካሄዱን በውል ተረድተው ሥራቸውን ከሚሠሩት አንዱ ናቸው፤›› ብለዋል። ባንኩ ባሳለፋቸው 20 ዓመታት በሀገራችን ኢኮኖሚ ዕድገት የፋይናንስ አካታችነትና ተደራሽነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው ማሳያ ይሆናል ብለው የጠቀሱት በዓይነቱ ልዩ የሆነ ማኅበረሰቡን ያቀፈ በተለይም በታሪክም ለአርሶ አደር ማኅበራት ትኩረት የሰጠ የገጠር ተደራሽነትንና አካታችነትን መርሁ አድርጎ መሥራቱን ነው።

ከዚህ በተጨማሪ አዳዲስ የዲጂታል ባንክ አገልግሎቶችን ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ በማስተዋወቅ ረገድ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝና በተለይ ባንኩ በሀገራችን ፈር ቀዳጅ የሆነውን መረጃን መሠረት ያደረገ፣ ያለዋስትና የሚሰጥ ምቹ አገልግሎቶችን ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ይፋ በማድረጉ ለአብነት የሚጠቀስና ብሔራዊ ባንክም ከምንደግፋቸው ስኬቶች መካከል አንዱ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ይህ የብድር ሥርዓት በመረጃ ላይ የተመሠረተ የብድር ውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓትን የያዘና በዋስትና ያልተገደበ የዲጂታል ብድር አገልግሎት የሚቀርብበት መሆኑን የተናገሩት አቶ ማሞ፣ በኢትዮጵያ ከተለመደው መደበኛ (ኮንቬንሽናል) የባንክ አገልግሎት ዓይነቶች በመውጣት አድማሱን ያሰፋበት አዲስ ኢንሼቲቭ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህ የዲጂታል ብድር አገልግሎቱም 1.2 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ያሉት ሲሆን በሁለት ዓመታት ውስጥ ከ18 ቢሊዮን ብር በላይ ለጥቃቅንና ለአነስተኛ ኢንተፕራይዞች ዕገዛ ማድረጉን ተናግረዋል። በተመሳሳይ በሴቶች ለሚመሩ የንግድ ሥራዎች ብድር በማቅረብ ለምሳሌነት ይጠቀሳል። ይህ ኢንሼቲቭ የብድርና ብድር ሥርዓቱ በፊኒቴክ ኩባንያዎች በባንኮች መካከል ያለውን ፉክክር ብቻ ሳይሆን ትብብር የሚያሳይ ነው ያሉት ገዥው፣ የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ በማለፍ ፈተናዎችን በመቋቋም መሻገር መቻሉንም ከልብ አደንቃለሁ በማለት የባንኩን ክዋኔ አወድሰዋል።

ባንኩ ራዕዩንና ግቡን ለማሳካት እንዲሁም በፋይናንስ ዘርፉ ያለውን ድርሻ ለማጎልበት የአስተዳደርና የሪስክ ማኔጅመንት አሠራሩን በይበልጥ እንዲያጠናክር አዳዲስ ቴክኖሎጂ ውጤቶች ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመቅሰም በመተግበር ቀጣይነትና ደኅንነቱ የተጠበቀ ዕድገት እንዲያስመዘግብ አሳስባለሁ። ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው ከፍተኛ የዕይታም ሆነ የአሠራር እንዲሁም የምርት ለውጥ እና ዕድገት እያሳዩ ካሉ የኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል አንዱ አሁንም የግብርናው ዘርፍ ነው።

በዚህ ረገድ የአርሶ አደሮችንና የአርብቶ አደሮችን ውጤታማነት ማየት ጥሩ ማሳያ ይሆናል። ለግብርናው ዘርፍ የሰጠው ትኩረት እና ለምርት ማደግ፣ ለአርሶ እና አርብቶ አደሮች ተጠቃሚነት ማደግ እያደረገ ያለው ድጋፍ ከግብርናው ባሻገር በሌሎች ዘርፎችም እንድንሰማራ አቅም ፈጥሮልናል ሲሉም በዘርፉ የተሰማሩ አርሶ እና አርብቶ አደሮች ይናገራሉ።

እዚህ ላይ የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ለአርሶ አደሮች ወይም ለግብርናው ዘርፍ ብድር በማቅረብ ያስመዘገበው ውጤት ለልማት ባንክ ለምን የመንኮራኩር ሳይንስ ያህል ከበደው፤ ከሚመለከታቸውና ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሮና ዘክሮ ችግሩን መፍታት ሲገባው ለምን በቀላሉ እጅ ሰጠ፤ ተስፋ ቆረጠ፤ በእሱ አቅም የሚፈታውን ችግር ቀርፎ፤ ከአቅም በላይ የሆኑትን ደግሞ ከመንግሥት ጋር ተወያይቶ ብድሩን ማቅረብ መቀጠል ሲገባው ቃል የገባውን የሰባት በመቶ ወለድ ለምን ወደ 13 በመቶ አሳደገው የሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ ይሻሉ። አዎ መንግሥት በአንጻራዊነት ለግብርናው ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑም ለባንኩ መልካም አጋጣሚ ሆኖ ሊወሰድ ይገባ ነበር።

ኢትዮጵያ ለግብርና ክፍለ- ኢኮኖሚ ምቹ ስለመሆኗ ለዘመናት ሲነገር የቆየ እውነት ነው። ነገር ግን ዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል አድጎ ሀገራዊ ፍጆታን ሸፍኖና ለወጪ ንግድ በሚገባ ቀርቦ የውጭ ምንዛሪ ለመሸፈን አልቻለም። ለዚህ እንደምክንያት ከሚጠቀሱት ጉዳዮች መካከል ትክክለኛ የፖሊሲ አቅጣጫና በሀገራዊ ራዕይ የተቃኘ ቁርጠኛ አመራር ያለመኖር ተጠቃሽ ነበር።

ኢትዮጵያን በአዲስ የልማት እና የዕድገት ሀዲድ ላይ ለማሳፈር በቅድሚያ በአዲስ ፖለቲካዊ ዕይታ የተቃኘ፤ ቁርጠኝነትንና ሀገራዊ ርዕይን የሰነቀ ፖለቲካዊ አመራር የመፍጠር ጉዳይ አጠያያቂ አይደለም። ከስድስት ዓመታት በፊት ወደ ስልጣን የመጣው የለውጥ አመራር ከላይ የተጠቀሱትን ክፍተቶች ለመሙላት የሚያስችል አመራር ለመፍጠር ጥረት እያደረገ መሆኑ ይታወቃል። የፖለቲካዊ አመራሩን በአዲስ ዕይታ አስተሳሰቡ ብቻ ሳይሆን አሠራሩንም በዚህ መልኩ እንዲቃኝ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት “አጓጊ ውጤቶች” ተመዝግበዋል።

ቀደም ሲል በግብርናው ዘርፍ ትኩረት ተነፍጓቸው ለቆዩ አካባቢዎች የተለየ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት፣ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ልማት፣ በኢንዱስትሪው፣ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር፣ በመንገድና በግንኙነት መሠረተ-ልማት ዝርጋታ፣ በተቋማት ሪፎርም፣ በወጪ ንግድ እንቅስቃሴ ቀጣናዊ የንግድ ትስስር ለመፍጠር እና ለማጠናከር እንዲሁም የቱሪዝም ዘርፉን ከድባቴው ለማላቀቅ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማልማት የተሠሩ እና እየተሠሩ ባሉ ሥራዎች አዎንታዊ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆናቸውን በቅርቡ በተከናወነ መንግሥታዊ የግምገማ መድረክ ላይ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋና አንቀሳቃሽ የግብርናው ዘርፍ መሆኑን የተረጋገጠ እውነት ነው። ግብርናው የሀገር ኢኮኖሚ ራስ ሆኖ እንዲዘልቅ ምርታማነትን በሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎች ብቻ ሳይሆን በአዲስ አስተሳሰብ በተቃኘ አመራር እና ባለሙያ መደገፍ እንደሚገባ በዘርፉ ላይ ምርምር ያደረጉ አካላት ምክረ-ሃሳቦችን ያቀርባሉ። በዚህ በኩል አዲሱ አመራር በሁሉም ዘርፍ ውጤት ለማምጣት አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ ዕይታ (ኒው ፓራዳይም) እንደሚያስፈልግ በተደጋጋሚ ያሳውቃል።

የፖለቲካ አመራሩ በአዲስ አስተሳሰብ እና በአዲስ አተያይ ከተቃኘ እንዲሁም ሀገራዊ ርዕይን በዋና የልማት ስንቅነት ከያዘ ማሳካት የማይቻል ህልም እንደሌለ የአፋር እና የሶማሌ ክልሎች አመራር አባላት በግብርና ዘርፉ ላይ ያከናወኑት ጥሩ ማሳያ ነው። የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን የሀገርን ኢኮኖሚ እድገት ለማረጋገጥ እንደሚቻል አመላካች ሁኔታዎች አሉ። ይህን እውነታ ወደ ውጤት ለመቀየር ደግሞ ከፖለቲካ አመራሩ ቁርጠኝነት፣ አዲስ አስተሳሰብ እና ዕይታ ያስፈልጋል። ለዚህ መጣጥፍ ኢዜአንና ሪፖርተርን በምንጭነት ተጠቅሜያለሁ።

ሻሎም ! አሜን።

 ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን)

fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You