የፊታችን ማክሰኞ ሚያዝያ 27 ለ79ኛ ጊዜ የሚከበረው የአርበኞች ቀን ነው። ይህ የድል ቀን በየዓመቱ አራት ኪሎ በሚገኘው የድል ሀውልት አደባባይ በድምቀት ይከበር ነበር። በዚህ ዓመት ዓለም አቀፉ የኮሮና ወረርሽኝ አልፈቀደልንም። ሆኖም ግን በልባችን የአባቶችን ድል እናስታውሳለን። በአባቶች የድል ወኔ የኛን ጀግንነትም በኮሮና ወረርሽኝ ላይ እናሳያለን። ጀግንነት ማሸነፍ ነው። ማሸነፍ ደግሞ እንደ ጠላታችን ባህሪ ይለያያል። የኮሮና ማሸነፊያ የህክምና ባለሙያዎች የሚሉትን መተግበር ነው። ከታሪክ ድርሳናትና ከተለያዩ የበይነ መረብ ገጾች ባገኘናቸው መረጃዎች በየቤታችን ሆነን 79ኛውን የአርበኞች ቀን እንዲህ እናስታውሳለን።
ጀግንነት በኢትዮጵያ ውስጥ ልዩ ቦታ ያለው ይመስላል። ለዚህም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ባህሎችን ልብ ብንል በቂ ምስክር ናቸው። ከጥንታዊው የአደን ሕይወት ጀምሮ ዛሬ ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ጀግንነት ከባህልና ማንነት ጋር የተሳሰረ ነው። ከዘመን ዘመን የተለያየ ቢሆንም ዛሬም ድረስ ጀግንነት ትልቅ ዋጋ ያለው ነው። ለምሳሌ በቀድሞው ጊዜ ‹‹አንበሳ ገዳይ፣ ነብር ገዳይ›› እየተባለ ይሞገስ ነበር። አነጣጥሮ ዒላማውን የሚመታ ሰው ‹‹ተኳሽ›› እየተባለ ይጠራ ነበር።
እንደየዘመኑ የተለያየ መሆኑን የምናውቀው ደግሞ አሁን ላይ በምናየው የጀግንነት ትርጉም ነው። ለምሳሌ በገጠር አካባቢ አንድ አርሶ አደር ለእርሻ አስቸጋሪ የሆነን ማሳ አለሳልሶት ከታየ ‹‹እገሌ እኮ ጀግና ነው›› ይባላል። በዝናብ ሰብል ሲያርም የታየን ሰው ‹‹አይ ጀግንነት›› እየተባለ ሲሞገስ ይሰማል። በትምህርት ቤት እንኳን ብንሄድ አንደኛ የሚወጣ ተማሪ ‹‹የእገሌ ልጅ ጀግና እኮ ነው›› ይባላል፤ በጓደኞቹ ዘንድም ትልቅ ክብር ይሰጠዋል።
ሌላው ጀግንነት በኢትዮጵያ ውስጥ ባህል መሆኑን የምናውቀው በሰርግ እና በሌሎች የድግስ ጉዳዮች ላይ ሲጫወቱ የሚወዳደሱት ጀግንነትን መሰረት በማድረግ ነው። የድሮ አባቶችን ገድል መዘከር ብቻ ሳይሆን የአሁን ልጅም ጀግና መሆን እንዳለበት ይጠቁማሉ። አባቴ ጀግና ነበር ማለት ብቻ ሳይሆን ራሱ ሰርቶ ማሳየት እንዳለበት ለመጠቆም እንዲህ እየተባለም ይዘፈናል።
አርገው ሞቅ ሞቅ እንደ ደሬ ፍም
የአባት ጀግንነት ለልጅ አያልፍም!
ደሬ ማለት የዛፍ አይነት ነው፤ ሲደርቅ ማገዶ ይሆናል። የደሬ እንጨት ፍሙ ቶሎ አይጠፋም። ለዚህም ነው ደሬ የተባለውን እንጨት የመረጡት።
የእረኞችን ጨዋታ እንኳን ብናስተውል በማሸነፍና በመሸነፍ ላይ የተመሰረተ ነው። ድንጋይ በማቆም ዒላማ መጫወት ነው። ከርቀት ሆኖ የቆመውን ድንጋይ በተወርዋሪ ድንጋይ መምታት የጀግንነት ምልክት ነው። እረኞች ከኮባ ወይም ከሸንበቆ የተዘጋጀ ጠመንጃ መሰል ነገር መያዝ ይወዳሉ። ይሄ እንግዲህ ከአካባቢያቸው ሁኔታ ተነስተው የሚያደርጉትና የተለመደ ነው።
ጀግንነት ጥበብ ነው። በጦርነት ታሪክ ውስጥ በተለይም ኢትዮጵያውያን በጥበብ እንደሚያሸንፉ በብዙ የታሪክ ጸሐፍት ተጽፏል። ታላቁን የዓድዋ ድል እንኳን ብንወስድ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀው የጣሊያን ሰራዊት በጦር፣ በጎራዴና በኋላቀር መሳሪያ ነው ዓለም አቀፍ ውርደትን የተከናነበው። ለዚህም ኢትዮጵያውያን አርበኞች የተጠቀሙት ጥበብ ነው። በዚሁ አሁን በምናከብረው የአርበኞች ቀን ድል እንኳን ብዙ ጥበብ የተሞላባቸው አሸናፊነቶችን መጥቀስ እንችላለን። ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983›› በሚለው በታሪክ ተመራማሪው ባህሩ ዘውዴ መጽሐፍ ላይ ተጽፎ እንደምናገኘው ራስ አበባ አረጋይ ይህን ስልት ተጠቅመው ነበር።
በ1932 ዓ.ም ራስ አበባ አረጋይ ለጣሊያን ‹‹እጄን ሰጥቻለሁ›› በማለት አጃጅሏቸው ነበር። ይህ መጭበርበር የደረሰበትም ምክትል እንደራሴና የሸዋ ገዥ የነበረው ጄኔራል ናዚ ነበር። ራስ አበበ አረጋይ ለናዚ ‹‹እጄን ሰጥቻለሁ›› በማለት ለአርበኞች ጓደኞቹ ‹‹አይዟችሁ እንዲህ እያልኩ እያታለልኳቸው ነው›› እያለ ይልክባቸው ነበር። ናዚም ምንም ሳይጠረጥር እውነት መስሎት የሰላም ድርድሩን ተያያዘው። በኋላም ራስ አበበ አረጋይ ጦሩ ቀደም ሲል የደረሰበትን ጥቃት ማገገሙን ሲያረጋግጥ ጣሊያንን ‹‹ዞር በል!›› በማለት ትግሉን ቀጠለ።
ሌላኛው የጦርነት ስልታቸው ደግሞ በወቅቱ የማይጠረጠሩትን ሴቶችን ማሰለፍ ነበር። ለዚህም እነ ሸዋረገድ ገድሌና አርበኛ ከበደች ሥዩም ተጠቃሽ ናቸው። በዓድዋው ጦርነትም የእቴጌ ጣይቱን ጥበብ ተደጋግሞ መጠቀሱን ልብ ይሏል። የጣሊያን ምርኮኛ መስለው
የሰራዊቱን ጥንካሬና ድክመት ያጠኑ የነበሩ ሰላዮችም ነበሩ።
በሌላ በኩል ደግሞ በተለያየ መንገድ ያታልሏቸው ነበር። በወቅቱ ኢትዮጵያውን በባዶ እግራቸው የሚሄዱም ስለነበሩ የእግራችን ዳና እየተከተለ ጠላት ያጠቃናል ብለው የጠረጠሩ አርበኞች አንድ ዘዴ ፈጠሩ። ለምሳሌ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ መሄድ ፈልገው ከሆነ የእግር ዳና በመፍጠር ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ ይሄዳሉ። ከዚያም የእግር ዳና ሳይፈጥሩ ወደ ምዕራብ ይመለሳሉ። ጠላት ወደዚያ የሄዱ መስሎት ዳና ተከትሎ ሲሄድ ከኋላ ያጠቁት ነበር።
ይህ እንግዲህ ተጽፎ ያገኘነውና ሲባል የሰማነው ነው። ያልተጻፈና ሲባልም ያልሰማነው ደግሞ ብዙ ስልት ተጠቅመዋል። ለዚህም ምስክር የሚሆነው ሃያላን ከሚባሉ አገራት የመጣውንና ዘመናዊ መሳሪያ እስከአፍንጫው የታጠቀውን ወራሪ ድል ማድረጋቸው ነው። በዚህም ጥበባቸው ኢትዮጵያውያን አርበኞች አገሪቱን በቅኝ ግዛት ያልተገዛች ብቸኛ አገር ተብላ በታሪክ መዝገብ ላይ እንድትሰፍር አደረጓት።
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የጀግንነትን ነገር እናንሳ ከተባለ እያንዳንዷ ዕለት ጀብዱ የተፈጸመባት ትሆናለች። ዳሩ ግን ሦስት ቀኖች ደግሞ በተለየ መልኩ ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው ናቸው። የካቲት 12፣ የካቲት 23 እና ሚያዝያ 27 በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ አላቸው። የካቲት 12 ግፈኛው ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያውያንን የጨፈጨፈበት ሲሆን የካቲት 23 እና ሚያዝያ 27 ግን የድል ቀኖች ናቸው። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያላቸው እነዚህ ሦስት ቀናት ሁሉም ከጣሊያን ወራሪ ጋር መሆናቸው ነው።
ጣሊያን በ1888 ዓ.ም ዓድዋ ላይ ዓለም አቀፍ ውርደት ተቀበለ። ለ40 ዓመታት ያህል ውስጥ ውስጡን ሲከነክነው ኖረ። ከ40 ዓመት በኋላ ቂሙን ሊወጣ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ መጣ። በታሪካዊው ቀን የካቲት 12 1929 ዓ.ም የኔፕልስ ልዕልት በመወለዷ ግራዚያኒ የደስታ መግለጫ ገንዘብ እሰጣለሁ ብሎ ከዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከድሮው ቤተመንግስት ሰዎች እንዲሰበሰቡ አዘዘ። ታላላቅ የኢጣልያ ሹማምንት፣ የሜትሮፖሊታን ጳጳስ አቡነ ኪርልና ሌሎችም ነበሩ። ለእያንዳንዱ ድሀም ሁለት ማርትሬዛ ብር እንዲሰጥ ተወስኖ ነበር። ይህ ልኩን ያለፈ የጣሊያን አገዛዝ ያንገበገባቸው ሞገስ አስገዶምና አብርሃም ደቦጭ የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው ወደ አዳራሹ ገብተው ነበር። ጀግኖቹ ያሰቡትን አደረጉ። ግራዚያኒ ላይ ቦንብ ተወረወረ። ድግሱ ወደ ጦርነት ተቀየረ። በዚህ ሰበብም ጣሊያን የበርካታ ኢትዮጵያውያንን ህይወት ቀጠፈ።
ከዚያ በኋላ እንግዲህ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች በዱር በገደል ተሰደዱ። በከፍተኛ መስዋዕት ግፈኛውን የጣሊያን ወራሪ በተለያየ ስልት ሲዋጉ ቆይተው በ1933 ዓ.ም ሚያዝያ 27 የድል ቀን ሆነ።
በጣሊያን የወረራ ዘመን ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማዋ ከታጠፈ፣ ሉዓላዊነቷ ከተደፈረ 5 ዓመታት በኋላ ነፃነቷን ያስመለሰችው ከ79 ዓመት በፊት ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ በ11 ሰዓት ንጉሰ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በአርበኞች ብርታትና መስዋዕትነት የጣሊያን ባንዲራ አውርደው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በታላቁ ቤተ መንግሥት ሰቀሉ። የሚያዝያ 27 የንጉሰ ነገስቱ አዲስ አበባ ገብቶ ሰንደቅ ዓለማ መስቀል ሌላው ታሪካዊነቱ ከአምስት ዓመታት አስቀድሞ ሚያዝያ 27 ቀን 1928 በዚያው ቀን ወደ ኢትዮጵያ የዘመተው የጣልያኑ ጦር አዛዥ ጄኔራል ባዶሊዩ አዲስ አበባ ገብቶ በታላቁ ቤተ መንግሥት የጣሊያንን ባንዲራ የሰቀለበት ቀን መሆኑ ነው። ጣሊያን ከዓድዋ ሽንፈቷ 40 ዓመታት በኋላ በዘመናዊ የጦር መሣሪያና በወታደራዊ ኃይል ይበልጥ ደርጅታ ኢትዮጵያን ከሦስት አቅጣጫዎች ወረረች። ከአድዋው ዘመቻ ያልተሻለ የጦር ትጥቅ የነበራት ኢትዮጵያም የጣሊያንን ጦር በፅናት ተዋጋች።
የወቅቱ ኃያላን እንግሊዝና ፈረንሳይ የጦር መሣሪያ በግዢ እንዳታገኝ ለጣሊያን ተደርበው ስላሴሩባት ኢትዮጵያ ብቻዋን ጦርነቱን በመጋፈጧ ድል ማግኘት አልቻለችም።
የየግንባሮቹ የኢትዮጵያ የጦር አዛዦች ብዙዎቹ ሞተው ሠራዊቱም በመርዝ ጋዝና በአውሮኘላን ቦምብ ተደብድቦ ያለቀው አልቆ የቀረው ቀርቶ ጣልያን ጊዜያዊ ድል አግኝታ ዋና ዋና ከተሞችን ብትቆጣጠርም ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በገጠሩ ክፍል እምቢ ለነፃነቴ፣ እምቢ ለአገሬ ብለው የሽምቅ ውጊያ ጀመሩ። ንጉሰ ነገስቱም ስደት ሄደው በጊዜው ለነበረው የመንግሥታቱ ማህበር(ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) አቤቱታ አቀረቡ። የሚሰማቸውግን አላገኙም። አርበኞች ግን ከቀን ወደ ቀን ድል እየተቀናጁ የጣሊያን ወታደሮችን
መፈናፈኛ፤ መግቢያ መውጫ አሳጧቸው።ከጣሊያን ወታደሮች ይማርኳቸው በነበሩ መሣሪያዎች ራሳቸውን እያደራጁ አብዛኛውን የገጠር ክፍል ተቆጣጠሩት።
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መቀስቀስ ለኢትዮጵያ ትልቅ ቦታ ነበረው። የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲቀሰቀስ ጣሊያን የናዚ ጀርመን አጋር ሆነች። ያን ጊዜ እንግሊዞች የጣሊያን ጠላት ሆነው ኢትዮጵያን መደገፍ ጀመሩ። ስለዚህም ወታደራዊ ድጋፍ ሰጥተው፤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ረዷቸው። በጄኔራል ካኒንግሂም የሚመራው የእንግሊዝ ጦር ከኬንያ ተነስቶ ከደቡብ አቅጣጫ ወደ መሀል ኢትዮጵያ ሲገሰግስ፤ በጄኔራል ኘላት የሚመራው ጦር ከሱዳን ተነስቶ ወደ አሥመራ፤ ከዚያም ከሰሜን አቅጣጫ ወደ መሐል ኢትዮጵያ ተንቀሳቀሰ።
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሚመራውና የአርበኞችና የእንግሊዝ አማካሪዎች የሚገኙበት ጌዲዮን ተብሎ የተሰየመው ጦር ከሱዳን ተነስቶ በኦሜድላ አልፎ በጐጃም በኩል ወደ መሐል አገር ገሠገሠ።
በመካከለኛ ኢትዮጵያ አርበኞች በጣሊያን ወታደሮች ላይ ጥቃታቸውን አፋፋሙ።
ጣሊያኖች ክፉኛ ተሸነፉ። በየቦታው ድል የመሆናቸው ዜና ናኘ።
ዘመቻው ከተጀመረ ሁለት ወራት ሳይሞላው፤ ጣሊያኖች አዲስ አበባን ለቀው ፈረጠጡ።
መጋቢት 28 ቀን 1933 ዓ.ም የጄኔራል ካኒንግሃም ጦር አዲስ አበባን ተቆጣጠረ።
እንግሊዞች ኢትዮጵያውያን አርበኞች ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ስላልፈለጉ ቀዳማዊ ኃይል ሥላሴን በደብረ ማርቆስ ለአንድ ወር ያህል እንዲቆዩ አደረጓቸው። ይሁንና በአዲስ አበባ በአርበኞች ተፅዕኖና ቅሬታ የተነሳ አርበኞች ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ፈቀዱ።አፄ ኃይለ ሥላሴም ወደ አዲስ አበባ እንዲጓዙ ፈቀዱ። ንጉሰ ነገስቱም አዲስ አበባ በታላቁ ቤተ መንግሥት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ሰቀሉ።
አጼ ኃይለሥላሴ አዲስ አበባ ገብተው የሚከተለውን ንግግር አድርገው ነበር።
‹‹ይህ የምትሰሙት ድምጽ የኔ የንጉሳችሁ የቀዳማዊ ሀይለ ሥላሴ ነው። አባቶቻችን ደማቸውን አፍሰው አጥንታቸውን ከስክሰው በነፃነት ያቆዩልን አገራችንን ወደ ከፍተኛው የሥልጣኔ ደረጃ ለማራመድ የምንደክምበት ጊዜ ከጥንት ጀምሮ ስለሆነ ዳግመኛ ጠላታችን ኢጣሊያ ይህንን እይታ ወሰናችንን ጥሳ የግፍ ጦርነት እንዳደረገችብን ሁላችሁም የምታውቁት ነው። እኛም በተቻለን ከተከላከልን በኋላ ርዳታ ለመጠየቅ ወደ መንግስታት ማሕበር ወደ ወዳጆቻችን መንግስታቶች መጣን እዚህ ስንነጋገር በቆዬንበት ጊዜ የኢትዮጵያ አርበኞች ሰይፋችሁን ሳትከቱ ፊታችሁን ሳትመልሱ ሰንደቅ አላማችሁን ሳታጥፉ ለባዕድ አንገዛም በማለት በመሳሪያ ብዛት ከሚበልጣችሁ ጨካኝ ጠላት ጋር የባሕርይ የሆነውን ጀግንነታችሁን መሣሪያ አድርጋችሁ በኢትዮጵያ አምላክ ብቻ ተማምናችሁ በጀግንነት ቀንና ሌሊት በዱር በገደል ስትጋደሉ ቆይታችሁ ይኸው አሁን እንደምታዩት የማያቋርጥ የአምስት ዓመት ትግላችሁ የድካማችሁንና የመሥዕዋታችሁን ፍሬ ለማየት እንድትበቁ አደረጋችሁ።
የሀገሬ የኢትዮጵያ ህዝብ!
ዛሬ ኢትዮጵያ እጆቹዋን ወደ እግዚያብሔር ዘርግታ እልል እያለች ምስጋናዋን የምታቀርብበት ደስታዋንም ለልጆቹዋ የምትገልጽበት ቀን ነው። የኢትዮጵያ ልጆች ከባድ የመከራ ቀንበርና ከዘለአለም ባርነት ነፃ የወጡበት ቀንና እኛም አምስት ዓመት ሙሉ ተለይተነው ከነበረው ከምንወደውና ከምንናፍቀው ሕዝባችን ጋር ለመቀላለቀል የበቃንበት ቀን ስለሆነ ይህ ቀን የተከበረና የተቀደሰ በየዓመቱም ታላቁ የኢትዮጵያ በዓል የሚውልበት ነው። በዚህም ቀን ለሚዎዷት ለአገራቸው ነፃነት ለንጉሰ ነገስታቸውና ለሰንደቅ አላማቸወ ክብር አባቶቻቸው የተላለፈውን ጥብቅ አደራ አናስወስድም በማለት መስዕዋት ሆነው ደማቸውን ያፈሰሱትን አጥንታቸውን የከሰከሱትን ጀግኖቻችንን እናስታውሳለን። ለዚህም ለጀግኖቻችን የኢትዮጵያ ታሪክ ምስክር ይሆናል።
ባለፈው አምስት ዓመታት ውስጥ በዝርዝር ተነግረውና ተቆጥረው የማያልቁ ያገኘናቸው መከራና ስቃይ ትምህርት ሆነውን ሰራተኛነት አንድነት ህብረትና ፍቅር በልባችሁ ተጽፈዉ ለምናስበው ለኢትዮጵያ ጉዳይ ረዳቶች ለመሆን ዋና ትምህርት የሚሰጣችሁ ነው። በአዲሷ ኢትዮጵያ ከእንግድህ ወድያ የማትነጣጠሉ በሕግ ፊት ትክክልና ነፃነት ያላችሁ ሕዝቦች እንድትሆኑ እንፈልጋለን። አገር የሚለማበትን ሕዝብ የሚበለጽግበትን እርሻ፣ ንግድ፣ ትምህርትና ጥበብ የሚሰፋበትን የሕዝባችን ሕይወቱና ሀብቱ የሚጠበቅበትን የአገር አስተዳደርም በአዲሱ ስልጣኔ ተለውጦ ፍጹም የሚሆንበትን ይህን ለመሰለው ለምንደክምበት ስራ አብሮ ደካሚ መሆን አለባችሁ።
ይሄ የኢትዮጵያውያን የድል ብስራት የሆነው የአርበኞች ቀን ከፍተኛ ዋጋ የተከፈለበት ነው። በዚህ ጦርነት ውስጥ ምላጭ ስቦ ጥይት ከተኮሰው አርበኛ በተጨማሪ በየቤቱ ሆኖ የተባበረውም ቀላል አልነበረም። በትግሉ ጊዜ የአርበኞች ዋናው ችግር ቀለብ ነበር። ቀለባቸውን የሚያገኙትም ከአርሶ አደሩ ቤት ነው። ይሄ ነገር የሚሆነው ታዲያ በግድም በውድም ነበር። በተለይም ከጠላት ጋር የሚያብሩ ሰዎችን ደግሞ እህላቸው እንዲዘረፍና ለሰራዊቱ ቀለብ እንዲሆን ተደርጓል።
ሰራዊቱ ‹‹ደረቅ ጦር›› እና ‹‹መደዴ ጦር›› ተብሎ ለሁለት ተከፍሎም ነበር። ደረቅ ጦር የተባለው ሙሉ በሙሉ ውጊያ ላይ የሚያተኩር ሲሆን ‹‹መደዴ ጦር›› የተባለው ደግሞ እንደሁኔታው የእርሻ ሥራ ላይ እንዲሰማራ ይደረጋል። ነገሩ ሲከፋ ግን አርበኞች ፍራፍሬ፣ ቅጠላቅጠልና የዱር አውሬ ሁሉ እየበሉ ተዋግተዋል። እናቶች ከሰራዊቱ ጋር አብሮ በመዝመት ምግብና ውሃ ከማቀበል በተጨማሪ ባህላዊ ህክምና እየሰጡ ሰራዊቱን ታድገዋል። የወደቀውን በማንሳት የቆሰለውን በመጠገን ተሳትፈዋል። ይህ የአርበኞች ቀን የሁሉም ኢትዮጵያዊ የተጋድሎ ድል ነው ማለት ይቻላል።
በዚህ የአርበኞች የድል በዓል ላይ የሲልቪያ ፓንክረስት አስተዋፅዖም ሊጠቀስ ይገባል።
ሲልቪያ ፓንክረስት እንግሊዛዊት ናት። የኢትዮጵያ በፋሽስቶች መወረር ያንገበገባት ሴት ናት። ከኢትዮጵያ ንጉሥ ጎን በመቆም የኢትዮጵያ አርበኛ ሆነች። New Times and Ethiopian News የተሰኘ ጋዜጣ ማሳተም ጀመረች። ጋዜጣው በየሳምንቱ ለእንግሊዝ ፓርላማ አባላት የሚበተን ነው። ቀሪው ደግሞ ለሌሎች ታላላቅ ሰዎች የሚሰጥ ነው። ጋዜጣው ኢትዮጵያ ውስጥ ፋሽስቶች እየፈፀሙ ስላሉት አሰቃቂ ግፍ የሚገልጽ ነው። እንደ እንግሊዝ ያሉ ታላላቅ መንግሥታት ይህን ግፍ እንዲቃወሙ የሚቀሰቅስ ነው። በመጨረሻም የእንግሊዝ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጎን ቆሞ ፋሽስቶችን እንዲፋለም አደረገች። ሲልቪያ ፓንክረስት ኢትዮጵያን ታደገች ማለት ነው።
የአርበኞች ቀን ጣሊያንን የማሸነፍ ድል ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያ የምትባል አገር ማን እንደሆነች ዓለም ያወቀበት የታሪክ ክስተት ነው። በዓድዋው ታሪክ የተደመመ የዓለም ህዝብ የጣሊያን ዳግም ወረራም ከሽፎ ማየቱ የበለጠ አስገራሚ ያደርገዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የአባት አርበኞች ገድል ለልጆች የአሸናፊነት ተምሳሌት ነው። ይህን የአባቶቹን ድል የሚያነብና የሚሰማ ትውልድ መሸነፍን አይቀበልም። እዚህ ላይ አንድ ነገር እንበል። አንድ በተደጋጋሚ የምንሰማው ወቀሳ አለ። ይሄውም ወጣቱ ታሪኩን አያውቅም የሚል ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ ከወጣቱ የሚሰማው ወቀሳ መገናኛ ብዙኃንም ሆኑ ሌሎች አካላት ታሪክን ማሳወቅ ላይ ድክመት እንዳለባቸው ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህን ወቀሳ የሚያጠፉ ነገሮች እየታዩ ነው፤ ይሄውም ወጣቶች ለታሪክ ያላቸውን ትልቅ ትኩረት በተለያየ መድረክና በመገናኛ ብዙኃን እያየን እየሰማን ነው። መገናኛ ብዙኃንም ቢሆን ለእንዲህ አይነት ታሪካዊ ቀኖች በቀጥታ ሥርጭት ጨምሮ ሰፊ ሽፋን እየሰጡ ነው። ይሄ ነገር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። ከወጣቱ በኩልም ወቀሳ ብቻ ሳይሆን ትኩረት መስጠትም ያስፈልጋል። በመገናኛ ብዙኃን የሚሰጠው ሽፋን ቀላል አይደለም፤ ከዚህ በላይ ደግሞ ያሉት የታሪክ መጻሕፍትም ቀላል አይደሉም። ክብር አገሪቱን በነጻነት ላቆዩት ጀግኖች አባቶቻችን!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2012
ዋለልኝ አየለ