የመጨረሻ ክፍል
ጠና ደዎ(ፒ.ኤች.ዲ)
ባለፈው ሳምንት የፍልስፍና አምዳችን በአገራችን የፖለቲካ ስርኣቶች ውስጥ ላጋጠሙ ስብራቶች መፍትሄ ይሆናሉ ያልናቸውን ሃሳቦች በተለይ ከመደመር ፍልስፍና ጋር ተያይዞ ያለውን ሁኔታ መዳሰሳችን ይወሳል።ዛሬም ቀጣዩን ክፍል ይዘን ቀርበናል።
የሀገር አመራር ለተሰራው መልካም ነገር እውቅና መስጠት፤ ለተፈፀመ ስሕተትና ጥፋት ትምህርታዊ እርምት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሊኖረው ይገባል። ያገራችን የአገዛዝ ሥርዓቶች ባብዛኛው ያስለመዱን መካሰስንና መወነጃጀልን እንጂ መመሰጋገንና መሸላለምን አይደለም።ጥሩም ይሁን መጥፎ ሰዎች ታሪክ ይሰራሉ።ታሪክ ሠሪ በወሳኝነት ሕዝብ ቢሆንም የግለሰቦችም ሚና በቀላሉ የሚገመት አይደለም።ኢትዮጵያ ታሪክ የሰሩና ያላቸው ዜጎችና መሪዎች አፍርታለች።ዜጎች በመልካም ስራቸው መወደስ፤ በመጥፎ ስራቸው መኮነን አለባቸው።በመጥፎ የፖለቲካ ሥርዓቶች ምክንያት ግን በተሰራው ታሪክ ልክ ከመወዳደስ በላይ መወጋገዝ ገዝፎ ቆይቶአል።አዲሱ ትውልድ አሮጌውን የሚረዳው በብዛት በበጎ ገጽታው ሳይሆን በመጥፎ ባሕርይው ነው።እስቲ ሌላውን ትተን የኢትዮጵያ ዓፄዎችና መሪዎች በመጨረሻ ያተረፉት ነገር ምንድ ነው ብለን እንጠይቅ።ሀብት ነው? ዝና ነው? ታሪክ ነው? ፍቅርና ክብር ነው ወይስ ሐውልትና ምስጋና?
የብዙዎቹ ታሪክ አወዛጋቢ ነው።አብዛኛዎቹ ከሥልጣን ሲወርዱም ሆነ የሕይወት ዘመናቸው አልቆ ሲሞቱ እንኳ በክብር አልተሸኙም።አንዳንዶቹ የሚገባቸውን ክብር የተነፈጉ ብቻ አይደሉም፤ ተገድለው በሚዲያ የተቅራራባቸው ናቸው።በዚህ ታሪክ ኩራት የሚሰማው ዜጋ አለ ብሎ መገመት ያስቸግራል።አድልዎ የሌለበት ታሪክ ያለው መንግሥታዊ ሥርዓት በኢትዮጵያ አልነበረም።የየትኛውም ሥርዓት አስተዳደር አንዱን አስጠግቶ ሌሎችን የሚገፋ ነበር።የተጠጋው ሲያወድስ የተገፋው ያወግዛል።ማለት አንዱ የሚያወድሰውን ሌላው ያወግዘዋል።ስለዚህ በኢትዮጵያ ታሪክ አንድ መሪ ባንድ በኩል የሚመሰገን በሌላ በኩል የሚኮነን ነው፡፡
በእርግጥ መሪዎች በተለያዩ መንገዶች በሕዝብ መካከል የሚፈጠሩና የሚኖሩ ሰዎች እንጂ መላእክት አይደሉም።በሁሉም ነገር ፍጹም መሆን አይጠበቅባቸውም።ቁምነገሩ ለጽድቅ ወይም ለኩነኔ ከሚያበቃ ድርጊታቸው ሚዛን የሚደፋው የትኛው ነው? ለሀገር ነፃነትና ክብር ባሳዩት ቁርጠኝነት ዝና ወይም ክብር ያላቸው መሪዎች አንደነበሩ አይካድም።እነዚህም ቢሆኑ እንከንየለሾች ናቸው ማለት አይቻልም።ባንጻሩ ሀገርን ለጉዳት፤ ሕዝብን ለበደል ያጋለጡ መሪዎች ነበሩ።እነዚህም ቢሆኑ መልካም የሚባል ምንም ነገር አልሰሩም ብሎ መደምደም ያስቸግራል።አንዳንድ መሪዎች የተመሰገኑና በሐውልት እንዲታሰቡ ተደርገዋል።የትኛውም ሐውልት የውስን ወገኖች እንጂ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ይሁንታ የለውም።አንዳንዶቹ ደግሞ አይደለም ሐውልት ሊቆምላቸው ከነስማቸው እንዲረሱ ተደርገዋል – ባብዛኛው ችግር አድርሰው ሳይሆን አድልዎ ተፈጽሞባቸው; መመስገን ሳይኖርባቸው የተመሰገኑ የየሥርዓቱ ባለሟሎችና መመስገን ሲገባቸው ሳይመሰገኑ የቀሩ በርካታ የሀገር ባለውለታዎች አሉ።
የብዙዎቹ መሪዎቻችን ታሪክ የተደመደመው አሳዛኝ በሆነ መንገድ ነው።ሀገር የመሩ ሰዎች ክብርን ባጓደለ መንገድ የያዙትን ሥልጣን ሲነጠቁና ያለ ፍርድ ለሞት ሲዳረጉ ደጋግመን አይተናል።የችግሩ መነሻ የራሳቸው አገዛዝ ባሕርይና ብልሽት ቢሆንም እንዲህ ዓይነት ድርጊቶችን በመሪዎች ላይ መፈጸም ሀገርንም ሆነ ትውልድን፤ ሕዝብንም ሆነ ዜጋን የሚያኮሩ አይደለም።እነዚህ ድርጊቶች የተፈጸሙት ጠንካራ የእሴት ሥርዓትና ታሪክ፤ ሕግና ወግ በሌለው ሀገርና ሕዝብ ቢሆን ብዙ ላያሳዝን ይችላል።በኢትዮጵያና በዜጎችዋ መሆኑ ግን ቅስም የሚሰብር ነው።የጥንታዊ ታሪክና ሥልጣኔ ባለቤት ከሆኑት ሀገሮች አንዷ ናት ተብሎ የሚነገርላትና በቅዱሳን መጻሕፍት በተደጋጋሚ የተጠቀሰች ናት ተብሎ ከሚወሳላት ኢትዮጵያ ይሕ አይጠበቅም።ለዚህ ነው በፖለቲካ ሥልጣን ዙሪያ ያለን ታሪክ አሳፋሪ የሚሆነው። የኢትዮጵያን ታሪክ አወዛጋቢ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል አንዱ ይኸ ነው።
እዚህ ጋር አንድ አስቸጋሪ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል።የሀገራችን ታሪክ የትኛው ነው? የመሪዎች ታሪክ ነው ወይስ የሕዝብ? የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ አለው ከተባለ እንዴት ይገለጻል? ለዚህ ጥያቄ ቀላል መልስ መስጠት ያስቸግራል።አንድ የማይታበል ሀቅ ግን አለ።ኢትዮጵያም ሆነች ሕዝቧ ታሪክ አላቸው – ዥንጉርጉርና አወዛጋቢ ቢሆንም።ታሪኩ ባንድ በኩል የጭቆናና የበደል፤ የእርስ በእርስ ጦርነትና የትርምስ፤ የረሃብና የእርዛት፤ የድህነትና የውድቀት ነው።በሌላ በኩል በልጆችዋ ተጋድሎ ነፃነትዋንና ሉአላዊነትዋን አስከብራ የኖረች ሀገር፤ በጀግንነቱ ሀገሩንና ማንነቱ ያላስደፈረ የጨዋና ሰላማዊ ሕዝብ ታሪክ ነው።ይህ ታሪክ የተጻፈና ያልተጻፈ ነው።በሚገባ የተጻፉ ታሪኮች፤ ጭራሽ ያልተጻፉ ታሪኮች፤ ከልካቸው በላይና ከልካቸው በታች የተጻፈላቸው ገድሎች አሉ – በሀገራችን፤ ስለሀገራችን።
ተጨባጭ ማስረጃና ማረጋገጫ ላይ ተመስርቶ የተጻፈ ታሪክ ተአማኒነት አለው።በማስረጃ ያልተደገፈ ታሪክ ግን ያወዛግባል።በእኔ እምነት አወዛጋቢነቱ በራሱ ታሪክ ነው – ይበልጥ ለመማርና ለመመራመር ያነሳሳል።አወዛጋቢ የሚያደርገውን ምክንያት በአደባባይ አውጥቶ መነጋገርና መጻፍ የመረዳዳት፤ የመናበብና የመቻቻል ባሕልን የሚያዳብር እንጂ የሚጎዳ አይደለም።ብዙ ሀገሮች አሁን ካሉበት የተረጋጋ ዕድገት የደረሱት በእንዲህ ዓይነት ትርምስና ታሪክ ውስጥ አልፈው ነው።ኢትዮጵያም በውዝግብ የተነሳ ተጎሳቁሎ የቆየ ታሪኳን ለመታደግ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ እልባት ልታበጅለት ይገባል።መልካም ባልሆኑ የፖለቲካ ሥርዓቶች ምክንያት ባለታሪክ የሆኑ ዜጎችዋ በጥቁር መጋረጃ ተሸፍነው እንዲቀሩ መፍቀድ የለባትም።
ሀገርን የመገንባት ራዕይ ያለው የፖለቲካ ሥርዓት በሀገሩ ሕዝብ ብዛትና በሀገር የኢኮኖሚ አቅም መካከል ያለውን ጥምረት በቅርበት ይከታተላል።ዛሬ በሀገራችን ያለው ሕዝብ ብዛት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ መሸከም ከሚችለው በላይ መሆኑ በውል ይታወቃል።ሀገሪቱ በቆዳ ስፋት ትልቅ ብትሆንም ይህን የቆዳ ስፋት የሚመጥን ሀብት የላትም።የሕዝብ ብዛት በራሱ የሚወደድ ወይም የሚጠላ አይደለም።ጥቅም ወይም ጉዳት እንዲሆን የሚያደርገው የሀገር ኢኮኖሚያዊ አቅም ነው።ኢኮኖሚው ሕዝቡን በማምረትና በመፍጠር፤ በመሸጥና በመግዛት፤ አገልግሎት በመስጠትና በመቀበል፤ በመገንባትና በመጠገን ማንቀሳቀስ አለበት።ከሀገራችን ቆዳ ስፋትና ካላት ተፈጥሮአዊ ምቹነት አንጻር አሁን ያለው የሕዝብ ብዛት አንደ ችግር መታየት የሚገባው አይደለም።በተጨባጭ መሬት ላይ ያለው ነገር ግን በእጅጉ ያሳስባል።ሀብት መሆን የሚገባው የሰው ብዛት (ኃይል) ድህነትን በእጅጉ እያገዘፈ ነው።የብዙ ወገኖች ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ ነው።ከዚህ በታች የሆነ ኑሮ ያላቸው ሚሊዮኖች አሉ።እጅግ ብዙ ወገኖች ሥራ የላቸውም።
አንዳንድ ከተሞቻችን ዛሬ የሚሸከሙት የሕዝብ ቁጥር እጅግ ግዙፍ ነው።ዜጎች ከገጠር ወደ ከተሞች በብዛት እየፈለሱ ነው።የሚፈልሱት የተሻለ ኑሮና ሥራን ለመፈለግ ነው።አብዛኛው ወጣትና ያልሰለጠነ፤ ዘመናዊ ሙያ፤ ዕውቀት ወይም ክህሎት የሌለው ነው።ከተሞች ለዚህ ሁሉ ጉልበት በመጠንም ሆነ በዓይነት ሥራ ማቅረብ አይችሉም።በዚህ ምክንያት ጎዳናን ቤታቸው፤ ልመናን የገቢ ምንጫቸው፤ ቆሻሻን ዕጣ-ፋንታቸው ያደረጉ ወገኖች ብዙ ናቸው።ይህ እጅግ ከፍተኛ ትኩረት ይፈልጋል።የሕዝብ ብዛትን ከሀገሪቱ የመመገብ አቅም ጋር ማቀራረብና ማመጣጠን የሚያስችል ፖሊሲ አስፈላጊ ነው።ወደ ከተሞች የሚደረገው ፍልሰት ገደብ ሊኖረው ይገባል።ዜጎች መኖሪያቸውን ጎዳና፤ ሥራቸውን ልመና ሲያደርጉ ዝም ሊባሉ አይገባም።በጎዳና ላይ ተወልደው፤ እዚያው አድገው፤ እዚያው ወልደው፤ እዚያው አርጅተው እዚያው መሞት – ለምን? የመውለድ እንጂ የማሳደግ አቅም የሌላቸው ብዙ ዜጎች አሉ።ስላልፈለግነው ወይም ስላላሰብንበት እንጂ ይህ የማንፈታው ችግር ሆኖ ግን አይደለም።በተለይም በጎዳና ላይ የሚያድግ ሕፃን መኖር የለበትም።መሠረታዊ መፍትሔው ገጠሩን ማልማትና ለኑሮ ምቹ ማድረግ ነው።ያ እስኪሆን ችግሩ ቆሞ ስለማይጠብቀን አፋጣኝ መፍትሔ ያስፈልጋል።
በእስካሁን ታሪካችን የተቀናጀ ጉዞና ጥረት፤ የሚናበብ አስተሳሰብና ድርጊት አልነበረንም።ሀገርን አቅም ሲያሳጡ ከነበሩት ነገሮች መካከል አንዱ ይህ ነው።ፖለቲካውና ኢኮኖሚው፤ ግብርናውና ኢንዱስትሪው፤ አስተሳሰብና ተግባር፤ ማሕበራዊ ሕይወትና ፍላጎት፤ ትምህርትና ሥራ እምብዛም አይናበቡም።አንዱ ለሌላው ግብአት የሚሆነው በሚፈለገው መጠንና ዓይነት አይደለም።መሪም ሆነ ተመሪ የነገሮችን መስተጋብራዊና ጥምረታዊ ትስስር እምብዛም አያገናዝቡም። አንዱ ራሱን በሌላ ውስጥ አያይም።እያንዳንዱ ሰው፤ ተቋም ወይም አካል ጉዳዬ ብሎ የሚንቀሳቀሰው በራሱ መስክ ብቻ ነው።የሌላው እንቅስቃሴ ለራሱ ግብአት አንደሚሆን አይረዳም።
አጋዥ ወይም አጋር ከመሆን ይልቅ በማወቅ ወይም ባለማወቅ በተቃራኒ መቆምን ምርጫ የሚያደርግ አለ።አንዱ የገነባውን ሌላው ሲያፈርሰው ማየት አዲስ አይደለም።ይህን በቀላል ምሳሌ መረዳት ይቻላል።መብራት ኃይል የገነባውን የውኃ ልማት ያፈርሰዋል፤ ቴሌ የተከለውን የቤቶች ልማት ይነቅላል።የውኃ ልማት ያደራጀውን መብራት ኃይል ይበትናል።በሁሉም ባይሆንም በሌሎች ሴክተሮችም ተመሳሳይ ታሪክ አለ።ሁሉም የሚሰራው ለአንድ ሀገር መሆኑ እየታወቀ አንዱ የሚንቀሳቀሰው የሌላውን እንቅስቃሴ ባላገናዘበ መንገድ ነው።ችግሮች የገዘፉት ባለመስራታችን ብቻ አይደለም – የሰራናቸውና የምንሰራቸው ባብዛኛው በተበጣጠሱና ባልተቀናጁ መንገዶች በመሆናቸውም ነው።መናበብና መቀናጀት ከሌለ አንዱን ለማልማት ሌላውን ማጥፋት የግድ ሊሆን ይችላል።
ስለሀገራችን የፖለቲካ ሥርዓቶችና ለመፍትሔ ይረዳሉ ብለን ያቀርብናቸውን መንደርደሪያ ሐሳቦችን አሁን ባንድ ቁልፍ ጉዳይ መቆጨት አለብን – እርቅና ይቅርታ።አሮጌውን የጉግማንጉግ ታሪክ አብቅተን ወደ አዲስ ታሪክ ለመግባት የማይበጀን ነገር ከኛ ጋር እንዳይሻገርና የሚበጀን ነገር ደግሞ እንዳይቀርብን በሀገር-አቀፍ ደረጃ እርቅ ማውረድና ይቅርታን ማድረግ የግድ ይለናል።ይህ የአሮጌ ሥርዓቶች ክፋትና ጥፋት ማብቂያና የአዲስ ዘመን ልማት ማብሰሪያ መሆን አለበት።
ኢትዮጵያዊ ግለሰብ፤ ቤተሰብና ማሕበረሰብ መታከም የሚኖርባቸው ቁስሎች አሉአቸው።በርካቶች ውድ ልጆቻቸውን ወይም ወላጆቻቸውን፤ ባሎቻቸውን ወይም ሚስቶቻቸውን፤ እህቶቻቸውን ወይም ወንድሞቻቸውን በፖለቲካ ምክንያት አጥተዋል።ይህ በቀላሉ የሚረሳ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን የበደሉን ስሜት ከእያንዳንዱ ተበዳይ ሕይወት ነቅሎ ማውጣት የሚያስችል ስራ አልተሰራም።ትውልዱ ከሀገሪቱ፤ ከሕዝቡ፤ ከግል ተበዳዮችና ከራሱ ጋር አልታረቀም።ይህ ማንንም ያልጠቀመ ነገር ግን ሁሉንም የጎዳ ታሪክ ነው።የተፈፀመው የታቀደ የመጠፋፋት ፍላጎት ኖሮ ሳይሆን በአስተሳሰብ ድህነት ምክንያት በሀገር ፍቅር ስሜት የተቀሰቀሰው የለውጥ መንፈስ መንገዱን ስቶ ከድጡ ወደ ማጡ በመሄዱ ነው።ከዚህ ለመውጣት እርቅ ከማውረድና ይቅርታን ከማድረግ የተሻለ መንገድ የለም።
ሀገርና ትውልድ፤ ግለሰቦችና ሕዝብ የተሻለ ሥርዓት ለማምጣት በምንም የማይለካ ዋጋ ከፍለዋል።ታሪካችን የበደል፤ የበዳይና የተበዳይ ታሪክ ነው።በዚህ ምክንያት የተበዳይነት ስሜት በአእምሮና በልባቸው ውስጥ እየተመላለሰ እጅግ የሚያስቸግራቸው ብዙ ዜጎች ነበሩ፤ ዛሬም አሉ።በዚህ ምክንያት እርቅና ይቅርታ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ መሠረታዊ ጥያቄ ሆኖ ቆይቶአል።ስለዚህ ሀገርንና ትውልድን፤ ግለሰቦችንና ሕዝብን፤ በተለይ የበደሉ ገፈት ቀማሽ የሆኑ ግለሰቦችና ቤተሰቦችን ከልብ ይቅርታን መጠየቅ ትልቅ ፈውስ ነው።ይቅርታ ተጠያቂዎችም ለጠያቂዎች ከልብ ይቅርታ ሲያደርጉ ማየት ከፍ ያለ የሕሊና እረፍት ይፈጠራል።ይህ በወረቀት ላይ የሚጻፍ ታሪክ መስራት ሳይሆን በዋናነት በልብና በኅሊና ውስጥ የሚቀረጽ የግብረገብ ማሕተም ማኖር ነው።መልእክቱ የሕግና የፖለቲካ ጉዳይ ሳይሆን የደምና የነብስ፤ የክብርና የሰብአዊነት ጉዳይ ነው።በደል ፈጻሚዎች ትውልድ፤ ሕዝብ፤ ግለሰቦችና ቡድኖች ናቸው።ይቅርታ ጠያቂዎችም እነርሱ ናቸው።ተበዳዮች ሀገርና ሕዝብ፤ ትውልድ፤ ግለሰቦችና ቡድኖች ናቸው።እነርሱ ደግሞ ይቅርታ ሰጭዎች ናቸው።
ለይቅርታ ጠያቂነትም ሆነ ለይቅርታ ሰጭነት መብቃት ራሱ ትልቅ ፀጋ ነው።በነበሩ በደሎች ሕይወትና አካላቸውን፤ ሀብትና ንብረታቸውን፤ ቤትና ትዳራቸውን ያጡ፤ በዚህም ሰበብ ከመንገድ የተመለሱ ዜጎች ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው።ሀገርና ትውልድ፤ ሕዝብና ዜጎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የበደሉ ሰለባ ናቸውና ይቅርታ እንዲያደርጉልን ልንጠይቃቸው ይገባል።ባለማወቅና ባለማስተዋል እነዚህን በደሎች በወገኖች ላይ ያደረሱ ግለሰቦች፤ ቡድኖች፤ ተቋማት ወዘተ “አጥፍተናልና ይቅርታ ይደረግልን” ብለው መጠየቅ አለባቸው።ይቅርታ ሰጭዎች (አድራጊዎች) እና ጠያቂዎች በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ከልብ “ይቅር ብለናል” እንዲሉ፤ እንዲሁም ይቅርታ ጠያቂዎች በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም “የተደረገልንን ይቅርታ ከልብ ተቀብለናል” ማለት እንዲችሉ ሁኔታዎች ሊመቻቹላቸው ይገባል።
ይቅርታ መጠየቅና ይቅርታ ማድረግ ለኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያዊነት ከፍተኛ ክብር ያጎናጽፋል።ለሀገር ጉልበት ይሰጣል፤ ለዜጎች መደማመጥ፤ መተማመንና መፈቃቀድ በር ይከፍታል።እኛ መጣላት እንጂ መታረቅ የማንችል፤ መገፋፋት እንጂ መተቃቀፍ የማናውቅ፤ አመጽና ጦርነት እንጂ ሰላምንና ፍቅርን የማንረዳ አይደለንም።ይቅርታን መጠየቅ፤ ማድረግና መቀበል፤ እርቅን አውርዶ ሰላምና ፍቅርን መገንባት የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ነባር ባሕል ነው።በዜጎች መካከል ግጭቶች በተፈጠሩ ቁጥር ቀድሞ የሚደርሰው ሽምግልና ነበር።ባለመታደል ለገላጋይ የማይመቹ ፖለቲከኞች ማንኛውንም አለመግባባት በፖለቲካ ቋንቋ እያወሳሰቡና የማይታረቁ ችግሮች ያደርጉአቸዋል – የራሳቸውን የፖለቲካ ትርፍና ኪሳራ በማስላት።ይህ ታሪክ መቀየር አለበት። እርቅን ማውረድ፤ ይቅርታን መጠየቅና ማድረግ አስፈላጊ የሚያደርጉ ሕመሞችና ችግሮች በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ሕይወት ውስጥ ተንሰራፍተው መገኘታቸው እየታወቀ ይህን ከማድረግ መቆጠብ ትልቅ ግብረገባዊ ግድፈትን መፈጸም ነው።
ዛሬ በኢትዮጵያ የእርቅና ይቅርታ ጉዳይ በወሳኝነት የኢትዮጵያ ሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎት ነው።የግፍና የበደል መዳፍ በቀጥታ ሲያርፉባቸው የኖሩት ሀገርና ሕዝብ ናቸው።የዚህ የሕዝብ ድምፅ መደመጥ አለበት።የግፍ ቀንበር ሊነሳለት ይገባል።ኢትዮጵያዊ ከኢትዮጵያዊ፤ ኢትዮጵያዊያን ከኢትዮጵያ ጋር ተጣልተዋል።ኢትዮጵያዊ ከራሱ፤ ከዜግነቱ፤ ከታሪኩና ከበጎ እሴቶች ጋር ተጣልቶአል።በዚህ ምክንያት ሁላችንም በአካልም ሆነ በሐሳብ የምንገኘው ከማይገባን ቦታ ነው።ከዚህ ለመውጣት አንድ ብቸኛ ምርጫ ነው ያለን – ሕዝባዊ መሥመር የሚከተል ሥርዓት መመስረት።አዲስትዋን ኢትዮጵያ በአዲስ አንድነትና በአዲስ ኢትዮጰያዊነት መገንባት የግድ ይለናል።ካሁን በ|ላ ኢትዮጵያዊነት የሚገለጸው በመልካምነት ነው፤ እርቅ በማውረድና ይቅርታን በማድረግ ነው።
ሀገራችንና ሕዝባችንን ከአደጋ መታደግ የሚችለው የአዲስ ሕዝባዊ ዲሞክራሲዊ ሥርዓት መመስረት ነው።የሺህ ዘመናት ውድቀትና ዝቅጠት ዓይነተኛ ምክንያት አንድና አንድ ነው – የፖለቲካ ሥልጣን።“ማን ማንን ይመራል? ማን በማን ይመራል?” የሚለው ጥያቄ በአግባቡ ባለመመለሱ ምክንያት የሀገራችን ሕልውና አደጋ ላይ ወድቆ ቆይቶአል።ከዚህ አደጋ ለመዳን የተጠቀሰው ጥያቄ ዛሬ መመለስ የሚኖርበት በኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎትና ፍቃድ ልክ ነው።መፈጠር ላለበት የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ የፖለቲካ ሥልጣን ሉአላዊ ባለቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው።ከሕዝብ ይሁንታ ወይም ድምፅ መምጣት ያለበት እንጂ ከግለሰቦችና ቡድኖች በጎ ፈቃድ የሚፈጠር አይደለም።ይህ የሚሆነው እኛ ስለፈለግነው ሳይሆን በተፈጥሮ የሥልጣን መሠረትና ምንጭ ሕዝብ ራሱ በመሆኑ ነው።ግለሰብ መሪዎችና ሹመኞች ባለሥልጣን የሚሆኑት ሕዝብ በሚሰጣቸው አደራ ነው።አደራ የሚሰጣቸው ደግሞ ሕዝብን እንዲያገለግሉበት እንጂ ሕዝብን አገልጋይ እንዲያደርጉበት አይደለም። ሥልጣን በጉልበትና በሴራ የሚያዝበት ጊዜን ለታሪክ እንተው።
ሰላም
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2012