ለመሆኑ ትንቢት ምንድነው?
ከኮሮና ጋር ተያይዞ የሰው ልጅ አንዳንድ ሃሳቦችን ቆም ብሎ በጥልቀት የሚመረምርበት ዕድል አግኝቷል። እኔም በዚህ ዙሪያ ቀልቤን ከገዙኝ ጉዳዮች መካከል የመጀመሪያ ያልኩትን ባለፈው ጽሁፌ አቅርቤላችኋለሁ። ለዛሬ በይደር ያቆየሁትን ይዤ ቀርቤአለሁ። ቃል በገባሁት መሰረት ዛሬ የምንመረምረው ጉዳይ ትንቢትና ትንቢተኞችን የሚመለከት ይሆናል።
ስለ ትንቢትና ጓዞቹ ከመነጋገራችን በፊት ሃሳቦቹን ለመረዳት መሪ ሆኖ ያገለግለን ዘንድ እስኪ በመጀመሪያ ትንቢት ራሱ ምን ማለት ነው? ከሚለው እንነሳ። አለበለዚያ ስለ ትንቢት ምንነት ሳይረዱ በእርሱ ውስጥ ስላሉ ነገሮች ለማውራት መሞከር የሚጫወቱበትን ቅኝት ሳያውቁ እንደመዝፈን ይቆጠራልና።
ትንቢት የወደፊቱን ቀድሞ ማወቅና መናገር መቻል ነው። “Prophecy” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “Propheteia” ከሚል የግሪክ ሥርወ-ቃል የተገኘ ሲሆን፤ ይህም “የእግዚአብሔርን ፈቃድ ምን እንደሆነ የመተርጎም ስጦታ” የሚል ትርጉም ያለው መሆኑን የዊኪፒዲያ መረጃ ያመለክታል። የትንቢትን ምንነት አስመልክቶ ከሁለት ሺ ዓመታት በፊት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ የሰጠው ማብራሪያም በቀጥታ ከግሪኩ ትርጉም ጋር የሚመሳሰል ነው። “ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፤ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ” ይላል ሐዋርያው።
የ“ፍካሬ 666” መጽሃፍ ደራሲ መጋቢ ተኩ ከበደ በበኩላቸው በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ወደ 6ሺ 208 ትንቢቶች መኖራቸውን ጠቁመው ከእነዚህም ከ3ሺ300 በላይ የሚሆኑት የተፈጸሙ መሆናቸውንና ወደ 2ሺ908 የሚጠጉት ደግሞ ወደ ፊት የሚፈጸሙ መሆናቸውን አመላክተው “ከተፈጸሙት ውስጥም አንድም ቃል እንኳን አልተሳሳተም” ይላሉ። ይህም ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣም የሚለውን የሐዋርያው ቃል ምንጭ በትንቢቱ የማይሳሳተው ሑሉን አዋቂ የሆነው ጌታ መሆኑን ያሳየናል” በማለት ትንቢት እውነት መሆኑን በማስረጃ ያረጋግጣሉ።
በእስልምናውም እንደዚሁ ትንቢት የሚለው ቃል “ኑቡዋ” የሚል አቻ የአረብኛ ቃል ያለው ሲሆን፤ የቃሉ መሰረት ተደርጎ የሚወሰደውም “ነቢ” የሚለው የአረብኛ ቃል ነው። “ነቢ” የሚለው ቃል በበኩሉ “ንበ” ከሚል የአረብኛ ቃል የመጣና ትርጉሙም “የምስራች፣ መልዕክት፣ ከፈጣሪ የተላኩ ህጎችን ተቀብለው በሚገባቸው ቋንቋ መልዕክቱን ለእያንዳንዱ ሙስሊም የሚያደርሱ “የአላህ መልዕክተኞች” የሚል ነው። ትንቢት የሚለው ቃል በቅዱስ ቁርአን ውስጥ አምስት ጊዜ የተጠቀሰ ሲሆን፤ ከመፈጸማቸው ከብዙ ዓመታት በፊት ቀድመው የተነገሩ ሁነቶችን የሚያመላክቱ ትንቢቶችን የያዙ አንቀጾች ቁርአን በውስጡ አካቶ ይዟል። ይህም በአማኞች ዘንድ ቅዱስ ቁርኣን ራሱ ከአላህ ዘንድ የተገኘ ነው የሚለውን አባባል ማረጋገጫ ተደርጎ ይወሰዳል።
እነዚህ ሁሉ ትርጓሜዎች ተደማምረው ትንቢት ሁሉን አዋቂና ሁሉን ቻይ በሆነ አምላካዊ ባህርይ ለሰዎች የሚገለጽ መለኮታዊ መልዕክት ነው ወደሚለው እውነታ ያደርሱናል።
ትንቢት ለምን ዓላማ ይነገራል?
በዚህ መንገድ በእግዚአብሔር መንፈስ ቀስቃሽነት በሰው አንደበት የሚነገረው ትንቢት የተለያዩ ዓላማዎች አሉት። ከእነዚህም ጥቂቶቹ የተደበቁ ኃጢአቶችን ለመግለፅ፣ ለተግሳጽ እና ከቀደሙ ስህተቶች ለመመለስ፣ የሰው ልጅ በፈጣሪው ማዳን ተስፋ እንዲያደርግና በዚህም ምቾትና ደስታ እንዲሰማው ፀጋው በተሰጣቸው ሰዎች አማካኝነት ትንቢት ሊነገር እንደሚችል (Spritualgiftstest.com) ከተባለ ድረ ገጽ ላይ የተገኘ መረጃ ያመላክታል። ሐዋርያው ጳውሎስ በበኩሉ ወደ ቆሮንጦስ ሰዎች በላከው መልዕክቱ ላይ “ትንቢት የሚናገር ግን ለማነጽና ለመምከር፣ ለማጽናናትም ለሰው ይናገራል” በማለት ትንቢት ለምን ዓላማ እንደሚነገር ገልጿል። ከዚህ የምንረዳው በእርግጥ ትንቢት የሚነገረው የወደፊቱን ክስተት ቀድሞ ለመተንበይ ብቻ አለመሆኑን ነው። በመጽሃፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥም መጭውን ጊዜ ከመተንበይ ባሻገር ህዝቡን ከጥፋቱ ለመመለስ ያለመና ለተግሳጽና ለምክር የተነገሩ በርካታ ትንቢቶች መኖራቸውን እናስታውሳለን።
ነብይስ ማን ነው?
እንግዲህ የትንቢትን ምንነት ካየን የነብይን ማንነት
ማወቅ አያቅተንም። በአጭሩ ነብይ ማለት በትንቢት ትርጉም ላይ እንደተመለከት ነው “በራሱ ፈቃድ ሳይሆን በእግዚአብሔር መንፈስ ተመርቶ፣ በመንፈስ ቅዱስ ተነድቶ ትንቢት የሚናገር ቅዱስ ሰው”(2ኛጴጥ.1፡20) ማለት ይሆናል። አሁን በዚህ የትንቢትና የነብይ የትርጉም ሚዛን ላይ የዘመናችን ትንቢቶችና ነብዮች እናስቀምጣቸውና እንመዝናቸው።
በዚህም አብዛኞቹ የዘመናችን “ነብያት” አንዱንም የነብይነት መስፈርት አያሟሉም። በመጀመሪያ “ትንቢት” የሚሉትን ነገር የሚናገሩት በራሳቸው ፈቃድ ሲሆን፤ የነብይነትን ማዕረግ የሚሰጡትም ራሳቸው ናቸው። ሌላው በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ሳይሆን በራሳቸው ፈቃድ የመሰላቸውን ይናገራሉ። ለአብነት በድህረ ኮሮና ዘመን ያሉ ነብይ ነን ባዮች መካከል አንዳቸውም የኮሮና ወረርሽኝ ሊከሰት እንደሚችል ትንቢት አልተናገሩም። ሲቀጥል ነብይ ሊሆን የሚችለው በግልጽ በመጽሃፍ እንደተነገረው ቅዱስ ሰው መሆን አለበት። እነዚህ ቅዱስ በሚለው በዙሪያው ራሱ አይደርሱም፤ ቅዱስነት ዕምነትን ከምግባር ጋር አስተባብሮ፣ ፈጣሪን መስሎ መገኘትን ይጠይቃልና። ሲሰልስ የሚናገሩት ነገር ህዝብን ከስህተቱ የሚመልስ፣ የሚያንጽና የሚመክር የሚያጽናናም አይደለም። ይባስ ብለው ቀድመው ትንቢት ያልተናገሩትን የኮሮና ወረርሽኝ ችግሩ ከተከሰተ በኋላ የ“ትንቢት” መዓት እያዥጎደጎዱብን ይገኛሉ።
ህዝቡን ከስህተቱ ወይም ከኃጢአቱ ለመመለስ፣ ለመምከርና ለማጽናናትም ነው እንዳይባል “ትንቢት” ብለው የሚናገሩት ነገር እንኳንስ ከስህተት የሚመልስና የሚያጽናና ሊሆን ቀርቶ ህዝብን የሚያሳስትና ወደባሰ ጥፋት የሚከት ነው። በተጨባጭ ማስረጃ አስደግፈን እንመልከት።
ኢትዮጵያዊቷ ነብይት ወአርድዕት ኮሮና፡-
እዚሁ በሃገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ እህተማርያም የተባለች ራሷን ንግስተ ነገስታት እንዲሁም ነብይ አድርጋ የቀባች ግለሰብ “ኮሮና ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል፣ የሚባለው ውሸት ነው፣ ሰላም ተባባሉ፣ ተቃቀፉ፣ ተሳሳሙ” በማለት በአደባባይ ህዝብን አሳስታለች። ታዲያ የ “ነብይት” ስንዱ (እህተማርያም ለራሷ የሰጠችው የንግስና ስም ስለሆነ ራሷ ትጠቀምበት እኔ በዚህ አልጠራትም) “ትንቢት” ከየትኛው የትንቢት ዓላማ ነው የሚመደበው? ከስህተት መመለስ፣ ከማስተማር፣ ከማነጽ ወይስ ከማጽናናት? እንደ ሰደድ እሳት በፍጥነት እየተዛመተ ዓለምን እየለበለበ ያለውን ይህንን አደገኛ ወረርሽኝ “ከሰው ወደ ሰው አይተላለፍም፣ እንደ ልባችሁ ተጨባበጡ፤ ተሳሳሙ፤” የሚል የሚያሳስት፣ የሚያስተምር ሳይሆን የሚያደድብ፣ ከችግርና ከፍርሃት የሚያጽናና ሳይሆን ፍርሃትና ችግርን የሚያጸና፣ እንዲህ ዓይነት ትንቢት ከየትኛውም የትንቢት ዓላማ አይመደብም፣ ትንቢትም አይደለም፣ እርሷም ነብይ አይደለችም። ምናልባት “ነብይት” ስንዱ ከመከላከያው በተቃራኒ ቆማ ኮሮና እንዲተላለፍ የሚያግዝ “ትንቢት” የምትናገር ስለሆነች ነብይ ከተባለችም “ነብይት ወ አርድዕት ኮሮና” ማለትም ኮሮናን የምትረዳ ነብይት ብትባል የሚያሳምን ይሆናል።
ከኮሮናም የከፋው ደቡብ አፍሪካዊው ነብይ፡-
ይህ ደግሞ የኮሮና ቫይረስ የበርካቶችን ህይወት እየነጠቀ ዓለምን እያስጨነቀ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት “ነብይ ነኝ” በሚል አህጉራችን አፍሪካ ውስጥ ከኮሮናም በከፋ ሁኔታ በአንድ ቀን የሃምሳ ዘጠኝ ሰዎችን ህይወት የነጠቀ” ራማ ስፋና “ የተባለ ደቡብ አፍሪካዊ ሰውነት የሌለው “ታህተ ሰብዕ” ግለሰብ ነው። “ከእንጨት መርጦ ለታቦት – ከሰው መርጦ ለሹመት” እንዲል የሃገሬ ብሂል እንኳንስ ከሰው ተመርጠው ለተቀደሱ ሰዎች ብቻ የሚሰጠው ታላቁ የነብይነት ፀጋ ሊኖረው ይቅርና ለሁሉም ሰብዓዊ ፍጡር እኩል የታደለው አዕምሮ እንኳን የሌለው ራሱን ነብይ አድርጎ የሾመ ግብዝ ፓስተር ከቆሻሻው ራሱ አፍልቆ “የኮሮና መድሃኒት በራዕይ ተገልጦልኛል” አለ። ይህ ጭንቅላቱ ከቫይረስ የሚያንስ ሰው ለቫይረሱ መድሃኒት ነው ብሎ በመንፈስ ተገልጦልኛል ያለው ደግሞ ሽንት ቤቶችንና ሌሎች ለማጽዳት የሚያስቸግሩ ጠንካራ ቅባት ነክ ቆሻሻዎችን ለማጽጃነት የሚያገለግለውን አደገኛውን ‘ዲቶል ‘ ሳሙና ነበር።
ሰነፍና እውቀት አልባ ሁል ጊዜ አብዝቶ ይደፍራልና ነብይ ነኝ ባዩ አላዋቂም ያለምንም ፍርሃት በማናለብኝነት አደገኛውን ኬሚካል አምነውት ከተሰበሰቡት ተከታዮቹ መካከል ለስልሳ ሦስቱ በድፍረት አጠጣቸው። ሃምሳ ዘጠኙ ወዲያውኑ ህይወታቸው ሲያልፍ አራቱ በጽኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ሆነው ህይወታቸውን ለማትረፍ አሁንም ድረስ ህክምና እየተከታተሉ ይገኛሉ። ይህም ሃገሪቱን ከበሽታው በከፋ ሁኔታ በሰው ኮሮና ዜጎቿን እንድታጣ አድርጓታል።
ሌላው እንዲህ ዓይነት የሰው ኮሮናዎችን ከበሽታው የከፉ የሚያደርጋቸው ቫይረሱን በጥንቃቄ መከላከል የሚቻል ሲሆን፤ ሰዎቹ ግን ከቫይረሱ በላይ አዘናጊ በመሆናቸው በጥቃታቸው የመጋለጥ ዕድሉ የሰፋ መሆኑ ነው።
ከዚህ ቀደምም በአጭበርባሪነቱና በሃሰተኛ ትንቢቶች ተናጋሪነቱ፤ በትንቢት ስም እጅግ በርካታ የሆኑ ለጆሮ የሚከብዱ ወንጀሎችንና ጥፋችን በሰዎች ላይ ይፈጽማል በሚል በአደባባይ አያሌ ክሶች የሚቀርቡበት ባለ ቴሌቪዥን ጣቢያው “ነብይ” ፓስተር እስራኤል ዳንሳም የሰፋ አይሁን እንጂ ሰዎችን ለሞት ሊያጋልጥ የሚችል አደገኛ ድርጊት ፈጽሟል።
እስራኤል ዳንሳ አማኞች በተሰበሰቡበት የአደባባይና የአዳራሽ ስብከቱን በቴሌቪዥን በቀጥታ በማስተላለፍ “ጌታ ነግሮኛል፣ የኮሮና ቫይረስ በእጄ ላይ እንደ አቧራ ሲቦን ሲራገፍ አይቻለሁ፤ አሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ሄጄ እጎበኛለሁ ያኔም ፈውስን ያገኛሉ” በማለት “በትንቢቱ” ተመጻድቋል። እስራኤል ዳንሳ ያራግፍልኛል በሚል ወደ ኳራንቲን ሄዶ ህመምተኞቹን የጎበኘ፣ እጃቸውንም የጨበጠ ሰው ስለመኖሩ የተሰማ ነገር ባይኖርም በወቅቱ የ“ነብዩን” ትንቢት ለመታደም በአዳራሽ የተሰበሰበው ሰው በእልልታ ጮቤ ሲረግጥ ታይቷል። እናም የእስራኤል ዳንሳ “ትንቢት” እውነት መስሎት ቫይረሱን ለመከላከል በጤና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክር ከመተግበር ቸል ያለ ሰው ካለም በሂደት ራሱንና ወገኑን ለሞት አሳልፎ መስጠቱ የማይቀር ይሆናል።
በርካታ ተከታታዮችና ተከታዮች ያሉት የኢማ ኑኤል ቲቪ ባለቤትና መሪ “ነብይ” ጆሹዋ በበኩሉ፤ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር መጋቢት 23 ቀን 2020 በቀጥታ በቴሌቪዥን ባስተላለፈው “ትንቢቱ”፤ “እግዚአብሔር አሳይቶኛል፣ የኮሮና ወረርሽኝና ቫይረሱ በዓለም ዙሪያ የፈጠረው የፍርሃት መንፈስ እስከ መጋቢት 27 ቀን 2020 ድረስ ከምድረ ገጽ ይጠፋል። ከመጋቢት 27 ቀን በኋላ ኮሮና ታሪክ ሆኖ ይቀራል” ብሏል። ቀጠል አድርጎም፣ “አሁን ይሔን ትንቢት በምናገርበት ሰዓት በዓለም ዙሪያ ዝናብ ይዘንባል፣ ቫይረሱ በተነሳበት በቻይናዋ የሁዋን ከተማ ዝናብ እየዘነበ ነው፤ ከፈለጋችሁ ደውላችሁ መጠየቅ ትችላላችሁ” በማለት “በእግዚአብሔር መንፈስ” ተናግሮ ሳይጨርስ የትንቢቱ ምንጭ እግዚአብሔር ሳይሆን “በስልክ የተገኘ መረጃ” መሆኑን በራሱ አንደበት ተንፍሶት አረፈው። ትንቢቱ ይፈጸማል የተባለበት ቀን ከዋለ ወር አለፈው። ይጠፋል የተባለው ኮሮናም ሳይጠፋ ይኸው እያጠፋ ቀጥሏል።
በዓለማችን ላይ በተለይም በአህጉራችን አፍሪካ “ነብይ” ነን በሚል ሰዎችን እያጠቁ ያሉት የኮሮና ረዳቶች እንደ እህተማርያም፣ ኮሮናን እፈውሳለሁ ብሎ ወደ ቻይና የሄደውና በዚያው በኮሮና ተይዞ የነብይነቱን ዘመን አልጋ ላይ እየገፋ የሚገኘው ናይጄሪያዊው ፓስተር ኤልጅያ ሚካ፣ የኮሮና ቫይረስን የሚፈውስ ቅብአ ቅዱስ ከሰማይ ወርዶልኛል በሚል ዘይት በመቸርቸር ሚሊዬነር የሆነውና ሚሊዮኖችን ያደኸየው ጋናዊው የትንቢት ነጋዴ ፓስተር ዳንኤል ኦቢኒ ለአፍሪካ ተጨማሪ ኮሮና ሆነውባታል።
የ “ትንቢት ቃላቸው” የሚተላለፍበትን የቴሌቪዥን ስክሪን በማስዳሰስ ኮሮናን እንፈውሳለን የሚሉ እና በኦን ላይን ገንዘብ የሚሰበስቡ፣ የኮሮና መድሃኒት ነው በሚል አንድ ሊትር ያልታወቀ ፈሳሽ በሰማንያ ዶላር የሚሸጡ…ሌላም ሌላም የጥቅም፣ የሃሰትና የጥፋት ትንቢቶችን የሚያሰራጩ “ነብያት” መኖራቸው ገሃድ ወጥቷል።
ከሐሰተኞች ነብያት ተጠበቁ
እንግዲህ ከዚህ ሁሉ ክስተት የምንገነዘበው በዚህ ዘመን “ነብይ” ነን እያሉ ሃገር ምድሩን ሲያምሱ የኖሩ ሁሉ ነብይ አለመሆናቸውን ነው። ታዲያ ምንድናቸው ከተባለ “ሐሰተኛ ነብያት” ናቸው። ምክንያቱም ስለ እውነተኛ ነብያት የሚናገረው የመጽሃፍ ቃል ስለ ሐሰተኞችም ተናግሯልና! እናም እንዲህ ዓይነት የዘመኑ ነብያት ነን ባዮች በሕዝቡ መካከል ነበሩ፣ እንዲሁም በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ” በማለት በግልጽ ያስቀምጧቸዋል። ግብራቸውንም በሚመለከት “በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች” በማለት ከእውነተኞቹ ነብያት የሚለዩበትን ነጥብ በግልጽ ለይቶ አስቀምጧል።
እዚህ ጋ ልብ በሉ፤ እውነተኞቹ ነብያት “በራሳቸው ፈቃድ ሳይሆን ከእግዚአብሔር በተሰጠ መንፈስ የሚናገሩ ናቸው” እነዚህ ግን “እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች” ናቸው። ዘበታቸውስ ዘበት ያህላል እንዴ! ያለምንም መለኮታዊ ኃይል የሞተን ሰው አስነሳለሁ ብለው መቃብር የሚያስቆፍሩ፣ ተቃቀፉ ኮሮና አይዛችሁም የሚሉ፣ ኮሮናን እንደ አቧራ እናራግፋለን የሚሉ፣ በዲቶል ሳሙና ኮሮናን የሚፈውሱ፣ በአንድ ጀንበር ቱጃር የሚያደርጉ፣ ስልጣን የሚሾሙ፣ ከፈለጉ እንዲሻር የሚያደርጉ እንደነዚህ ዓይነት ዘባች(በነገራችን ላይ ዘባች የሚለው ቃል ትርጉም አዲስ የሆነባችሁ ካላችሁ ቀልደኛ፣ ፌዘኛ፣ ቧልተኛ ማለት ነው) ከወዴት ታይቶ ያውቃል?
እናም “ነብይ” ነን እያሉ ዓለምን በአንድ እግሯ ሲያስቆሟት የኖሩት እኚህ ባለ አምስት ኮከብ የዘመናችን ዘባቾች ወትሮም ቢሆን የሚያውቅ የሚያውቃቸው ቢሆንም አሁን ላይ በዘመነ ኮሮና ግን የሐሰት ጭንብላቸው ከመቼውም ጊዜ በላይ ሊገለጥና ትክክለኛው ማንነታቸው ሊታወቅባቸው ችሏል።
ከአሁኑ ሰዓት ጀምሮ ችግርህ ሁሉ ተወግቷል በሦስት ቀናት ውስጥ የናጠጠ ቱጃር ትሆናለህ፣ ከዛሬ ጀምሮ ከበሽታህ ተፈውሰሃል፣ በዚህ ወር ውስጥ የምትፈልጋትን ሴት ታገባለህ፣ የምትፈልገው ነገር ሁሉ ተሳክቷል እያሉ “እንደራሳቸው ምኞት ብቻ እየተመላለሱ” በፈጣሪያቸው ስም የማያልቀውን የራሳቸውን ምኞት በመዘርዘር ገንዘብ የሚሰበስቡ ጉዶች በጭንቁ ቀን ጉዳቸው ተጋልጧል።
በቅዱስ መንፈስ ሳይሆን በፍቅረ ንዋይ እየተነዱ የመሰላቸውን የሚናገሩ፣ ስተው የሚያስቱ፣ ጠፍተው የሚያጠፉ፣ የሳይንቲስቶችን መላ ምት እየተከተሉ ነብይ ሳይሆኑ ነን እያሉ “ትንቢት” የሚናገሩ አዕምሮ ቢሶች ጭንብል በሚያስለብሰው የኮሮና ዘመን ከመቼውም ጊዜ በላይ የሐሰት ጭንብላቸው ተገልጦ እርቃናቸውን ቀርተዋል።
ዓለም በተፈተነችበት በዚህ ወቅት ተፈትነው ሳይሆን ራሳቸውን ፈትነው ወድቀዋል። በመለኮታዊ ፀጋ የወደፊቱን ቀድመው አውቀው የሚያሳውቁ፣ ከአደጋ የሚያስጠነቅቁ፣ የሚመክሩ፣ የሚገስጹና የሚያጽናኑ ሳይሆኑ በራሳቸው ምኞት ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የማያውቁትን በድፍረት የሚናገሩ፣ ስተው የሚያስቱና ወደ ጥፋት የሚመሩ የሐሰት ነብያት መሆናቸውን በራሳቸው አስመስክረዋል። እናም በእነርሱ ሰበብ እኛም እንዳንጠፋ “ከሐሰተኛ ነብያቶች ተጠበቁ” በሚለው እውነተኛ ቃል ራሳችንን ልንጠብቅ ይገባል የዛሬውን የሀሳብ ምርመራዬን አጠናቀቅሁ። እግዚአብሔር አገራችንና ዓለማችንን በምህረቱ ይጎብኝ፣ ሁሉን የሚችል አምላክ ሰው ያልቻለውን የኮሮና ወረርሽኝ ከምድራችን ያስወግድ። አሜን!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 21/2012
ይበል ካሳ
ዘመን የገለጣቸው የነብይነት ጭንብሎች