“የቤት የአደባባይ፤ የማን ማንነቱ፣
ሰው ቁምነገሩ እንጂ፤ ገላጭ መስታወቱ፣
በወል ስም መጠራት፤ ወይ አንተ ወይ አንቱ፣
አይሆንም መለኪያ ለሰው ሰውነቱ።”
የዚህ ግጥም ደራሲ በብዕሩ የአገጣጠም ስልትና በሚያነሳቸው የመጻሕፍቱ ሀገራዊ ይዘቶች (የእኔ ጋሻ፣ አንድ ቀን እና ምሥጢሯን ያልገለጠልን) አንቱታን ያተረፈውና የአንባቢያን ጎሽታ ሲዥጎደጎድለት የኖረው ወዳጄ ሻለቃ ክፍሌ አቦቸር ነው። ከስደት ኑሮው ወደ ሀገሩ ተመልሶ አራተኛ መጽሐፉን እንደሚያስነብበን ቃል ገብቶልኛል። የሻለቃ ክፍሌ የተለየ መለያው በ1969 ዓ.ም የሀገራችን የሚሊሺያ ሠራዊት የምሥራቁን የሶማሊያ ወረራ ለመመከት፤
“ይህ ነው ምኞቴ፤ እኔስ በሕይወቴ፣
ከራሴ በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ።
እያለ የተመመበትን መዝሙር ከብዙዎቹ ስራዎቹ መካከል በአይረሴነቱ ማስታወስ ይቻላል። የመንደርደሪያውን ግጥም ከዜማ ጋር አዋህዶ ለሕዝብ ያቀረበው ነፍሰ ሄር ጥላሁን ገሠሠ ነበር።
እንደ ግጥሙ ሁሉ እያንዳንዱ ግለሰብ ስለ ሕይወት ያለው ፍልስፍና ከሰው ሰው መለየቱ እርግጥ ነው። እውነታው ዓለም አቀፍ ስለሆነ እዚያና እዚህ፣ ወዲያና ወዲህ ብሎ ለመፈረጅ ያዳግታል። በየትኛው የዓለም ክፍል፣ በየትኛውም የባህል ዐውድ፣ በየትኛውም የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሰው የራሴ የሚለው ፍልስፍና ቢኖረው አያስገርምም። እንዴት ቢሉ፤ ማንም ሰው ራሱን ይጠላል ባይባልም አንዳንዱ የባሰበት ማዕከል የሚያደርገው ራሱንና ነፍሱን ብቻ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ለራሱ ጣኦት ቀርጾ ራሱን እስከ ማምለክ የሚደርስ ስለሆነ “ስግብግብ” የሚለው ቃል በምልዓት ላይገልጸው ይቻላል። “ራስ ተኮርነትን” ፍልስፍናቸው ያደረጉ እኒህን መሰል ግለሰቦች ተረታ ተረታቸው ሁሉ “ከራስ በላይ ነፋስ”፣ “ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” ወዘተ… የሚል ዓይነት ነው።
አንዳንድ ሰው ደግሞ አለ በተሻለ አንጻራዊነት ለምሳሌነት በሚበቃ አብነት ለሌሎች መኖርን የሕይወቱ ፍልስፍና ያደረገ። እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች አዘውትረው የሚያንጎራጉሩት፤
ለሀዘን፣ ለፍቅር፣ ለደስታ፣ ለችግር፣
ማነው የሚመረጥ ከሰው ወዲያ በምድር።” የሚሉትን ዓይነት ዜማዎች ነው። የሕይወታቸው መርህ በአፍቅሮተ ሰው የተቃኘው እነዚህን መሰል ሰዎች በዓለማችን ላይ መሳ ለመሳ ባይኖሩ ኖሮ የሕይወት ትርጉሙ ምን ሊመስል እንደሚችል መገመቱ አይከብድም። መለገስ ለሰጭው በረከት ሲሆን፤ የመስገብገብ ትርፉ ደግሞ ኩነኔና እርግማን ነው።
ልግስና የግድ ከቁስ ሀብት ጋር ብቻ የሚቆራኝ አይደለም። የመንፈስ ልዕልናም ብዙ ያልተነገረለት ከልግስና መገለጫዎች መካከል አንዱ ነው። እንዲያውም ከቁሳቁስ ልግስና በፊት የሚቀድመው የመንፈስ ልዕልና ነው። እርግጥ ነው የለገሰውን ሀብት ወይንም ቁስ በቀንና በመዓልት በአድናቆት እንዲዘከርለት የሚፈልግ ሰው ይጠፋል ተብሎ ላይታሰብ ይቻላል። በአንጻሩም እንደ ቅዱስ መጽሐፉ ቃል “ቀኝ እጁ የሚፈጽመውን መልካም ተግባር የግራ እጁ እንዳያውቅ” የሚጠነቀቅ አርአያ ሰብም የዚያኑ ያህል ማግኘቱ አይከብድም። የጠቢባኑን የዜማ ግጥም ለመንደርደሪያነት ለመጠቀም የፈለግሁት በዚሁ ምክንያት ነው።
ጉዳዩን በሌላ ምልከታ ጫን አድርገን እንመልከተው።
አንዳንዱ ሰው እየኖረ ያለው የትናንቱን ልግስናውን ዛሬም እየመነዘረ ሲሆን “እንዲህ ያደረጉት!” እየተባለ የሚሞካሸውም ትናንት ከትናንት ወዲያ የዋለው ለጋስነት ወደ ዛሬ እንዲሸጋገር አጥብቆ በመሥራቱና በማሠራቱ ሊሆን ይችላል። አንዳንዱ ሰውም ፍልስፍናው “ዛሬ” ብቻ ነው። “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል!” የሚለው ግለ ነፍስ መርሁ መገለጫው ነው። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ዛሬን ብቻ የሙጥኝ ብሎ አጥብቆ መያዙ ብቻ ሳይሆን ለትናንት መልካም ተግባሮችም ቁብ የለውም፤ ክብርም አይሰጥም። ጠንከር እንበል ካልንም “ዛሬን ብቻ” እያለ ከራሱ ጋር እሽኮለሌ የሚያበዛ ሰው ለነገው አዲስ ቀንም ጉጉት አንደሌለው በርግጠኝነት መናገር አይከብድም።
ትናንት፣ ዛሬንና ነገን ሦስት የጊዜ ቀለበቶች በመሸረብ ለሰው ልጆች በጎነት ለመዋል የሚጥር ሰው በፍጹም ማግኘት ያዳግታል ተብሎ አይታሰብም። ዓይነ ስውሩ ግሪካዊ ፈላስፋ ዲዮጋን እንዳደረገው ቁጥሩ ቢያንስም በጠራራ ፀሐይ ፋኖስ አብርተን እንዲህ ዓይነቱን ሰው በሕይወት ገበያ መካከል ብንፈልግ አይታጣም። ከእነዚህ ዓይነት በጎ ሰዎች የምንማረው እኔነት በእኛነት፣ እኛነት በእነርሱነት ካልተሸመነ በስተቀር “እኔነት” ብቻውን ፋይዳ የሌለው አጋባሽነት መሆኑን ነው።
በተለይም እንዳሁኑ ዘመነ ፍዳ በሀገርና በሕዝብ ላይ ክፉ ቀን ሲደርስ እኔነት ተሸንፎ ለእኛነት ካልተጨበጨበለት በስተቀር መከራው አይገፋም፤ አሳሩም ፈጥኖ አይወገድም። ይህ ዙሪያ ጥምጥም የንፍገትና የበጎነት ፍልስፍና በራሳችን ቀኤና ሕዝብ ውስጥ ሰሞኑን እንደምን ተግባር ላይ እየዋለ ብንወያይበት አይከፋም።
የሰሞኑ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስተማረን ትልቁ ቁምነገር እውቀት፣ ብርታትና ሀብት መትረፍረፉ ብቻ ለሕይወት ትርጉም እንደማይሰጥ ነው። በጸሐፊው የግል ምልከታ እንደየእምነታችን የምናመልከው ፈጣሪ የዓለምን ሕዝቦች በሙሉ እንቦቀቅላ ጨቅላዎችን በአንድ መዋዕለ ሕጻናት ማቆያ ውስጥ አስቀምጦ የሥነ ምግባር ትምህርቶችን እንደሚያስተምር መምህር እያስተማረን ያለ ይመስለኛል።
“ለሕጻናቱ የሚሰጠው ትምህርት ይዘቱ ምንድን ነው?” ከተባለ ከዋና ዋናዎቹ መካከል ሕጻናቱ ንጽህናቸውን በሚገባ እንዲጠብቁ፣ እጆቻቸውን በሳሙናና በውሃ እሽት አድርገው አዘውትረው እንዲታጠቡ፣ ጉንፋን ወይንም ሣል ከያዛቸው ጓደኞቻቸው ጋር ተራርቀው እንዲጫወቱና እንዲቀመጡ፣ ንክኪያቸውንም እንዲቀንሱና በየግላቸው መጫዎቻዎች ብቻ እንዲጫወቱ እንጂ እንዳይዋዋሱ መምከር ነው። የሕጻናቱ መሠረታዊ ትምህርት ይዘት ከዚህን መሰሉ የጥንቃቄ ምክር እጅግም የሚዘል አይደለም። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ለሕጻናት ባዘጋጀው ስድስት ያህል መጻሕፍት ውስጥ ደመቅ አድርጎ ያስተላለፋቸው ትምህርቶች በይዘታቸው ከዚህ የተለዩ አይደሉም፡
ይሄም ቢሆን ግን ሕጻናቱ ሙሉ ለሙሉ የመምህራኖቻቸውን ምክርና ትምህርት በተግባር ያውላሉ ማለት አይደለም። ለአፋቸው “እሺ” በተግባራቸው ግን ምክሩን በመጣስ አዘውትረው በተጋቦሽ በሽታ እንደሚጠቁ ወላጆች በሚገባ ይረዱታል።
ፈጣሪም ኮሮናን ምክንያት አድርጎ እያስተማረን ያለው ይህንን የመሰል ትምህርት ነው። የዓለም ሕዝቦችን በሙሉ እውቀታቸውን አስጥሎ፣ የጉልበት ብርታታቸውን አሽመድምዶ፣ የሀብት ቀረርቷቸውን ፉርሽ አድርጎ በኮቪድ-19 እየገሰጸን ያለው ሕጻናቱ በሚማሩበት ስልትና ሥነ ምግባር ዓይነት ነው። የመምህርነቱን ሙሉ ሥልጣን የሰጠው ደግሞ በዋነኛነት ለጤና ባለሙያዎች ነው። ለዚህም ነው የጤና ባለሙያዎቹ እጃችንን አዘውትረን በሳሙናና በውሃ እንድንታጠብ፣ ከጥግግት እንድንራራቅ (ያውም በሜትር ተሰፍሮ)፣ ስንስልና ስናስነጥስ አፋችንንና አፍንጫችንን በክንዳችን መታጠፊያ እንድንሸፍን፣ በወረርሽኙ ከተጠቃ ሰው እንድንርቅ ወዘተ. እየመከሩ ባለመሰልቸት የሚያስተምሩን። በአተገባበሩ ላይ የሚታየው የሕዝቡ መዘናጋትና ቸልተኝነት ግን ልክ እንደ ሕጻናቱ ሁሉ አሳሳቢነቱ የጎላ ነው።
ትምህርቱ በተግባር እንዲተረጎም የእድሜ ልዩነት ሳይደረግ፣ የድህነትና የሀብት መለኪያ ሳይኖረው፣ ድንበርና ዘር ሳይበላለጥ፣ ቋንቋና ብሔር ሳይለይ ለሁሉም የሰው ዘር የተሰጠ እኩል ትዕዛዝ ነው። ወይንም እንደ ጥንታዊው የግሪክ ጸሐፊ ተውኔት እንደ ሶፍክሊስ ትዕዛዙ የእድሜ ገደብ አልተበጀለትም።
ጠዋት ላይ በአራት እግራቸው ለሚሄዱ፣
ቀትር ላይ በሁለት እግራቸው ለሚሮጡ፣
ምሽት ላይ በሦስት እግራቸው ለሚውተረተሩ
ሕዝበ አዳም በሙሉ የተሰጠ የጋራ ትዕዛዝ ነው። በሶፍክሊስ የፍልስፍና ገለጻ መሠረት በጠዋት የዕድሜ ጀንበር ላይ የሚገኙና በአራት እግራቸው የሚሄዱበት የተባለው ዳዴ የሚሉ ሕጻናትን ለማመልከት ነው። በሁለት እግር ሯጮች የተመሰሉት ደግሞ “የነብር ጣቶቹ” ወጣቶች ናቸው። የሦስት እግር ተፍገምጋሚዎች የሚወክሉት ዕድሜያቸው አሽቆልቁሎ የማታ ማታ ከዘራ ወይንም በትር የያዙትን ጎልማሶችና አዛውንቶች የሚያመለክት ነው። በየትኛውም የእድሜ እርከን ላይ የሚገኝ ሰው ወረርሽኙን ለመከላከል የጤና ባለሙያዎችን ምክር መስማቱ አማራጭ ሳይሆን ግዴታና የመኖር ወይንም ያለመኖር ጥያቄ ነው።
“ሰሞኑን . . .” ብዬ በእንጥልጥል ወዳቆየሁት ጉዳይ ላቅና። ዘመን አመጣሹና ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ፍጡራንን ያተራመሰው ወረርሽኝ “አንተ፣ አንቺ፣ እርሶ” የሚባሉትን ተውላጠስሞች ደፍጥጦ የዓለምን ሕዝቦች በሙሉ የፈተነ ክስተት ስለመሆኑ ተደጋግሞ ተገልጧል። ይሄው ወረርሽኝ የሀገራችንን ምድር ከረገጠበት ካለፉት ሃምሳ ቀናት ወዲህና ከዚያም ቀደም ብሎ የጤና ባለሙያዎቻችን እየፈጸሙ ያለው ጀግንነትና ታሪክ በእኛ ትውልድ ብቻ ተወስኖ የሚወሳ ሳይሆን ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገር የሚያስጨበጭብ ተግባር ስለመሆኑ አንጠራጠርም። “አሹ!” የጤና ባለሙያዎቻችን ከክፉ ሁሉ ይጠብቃችሁ ብለን እንመርቃችኋለን።
ቁጥራቸው ውስን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በሀገራቸው ላይ ሀብት ያፈሩ ባለሀገሮችም ከሀብታቸው ቆንጥረው ቼካቸውን ሲመዠርጡ፣ የገንዘብ ኖታቸውን ሆጨጭ እያደረጉ ሲለግሱ እያየን ስለሆነ ዕድሜና ክብረት ብንለምንላቸው ለነገው ክፉ ቀንም ፈጥነው እንዲደርሱ ስንቅ ይሆናቸዋል። ሕንጻዎቻቸውንና አዳራሾቻቸውን
ለጊዜያዊ ማገገሚያነት የለገሱትም ቢሆኑ ከአሁን ቀደም አይተንም ሆነ ሰምተን የማናውቀው ተሞክሮ ስለሆነ አድናቆታችንን ብንለግሳቸው ለወደፊቱ ልማዱን ባህል ስለሚያደረጉት ፈጠናችሁ አሰኝቶ አያስተችም።
በተለይ በከተሞች አካባቢ የሚገኙ በርካታ ወጣቶቻችን ሕዝባቸውን አስተባብረው ምስኪኖችን ለመድረስ ያሳዩት ተነሳሽነት በአኩሪነቱ ቢታወስ ለተሻለ በጎነት ያነቃቃቸዋል። ወጣትነት በውበት ፈላጊነት ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን ለቁም ነገር ውበት መዋሉንም አስተውለናል። ፈቃደኞች ከሆኑና ምርቃታችንን በአሜንታ የሚቀበሉን ከሆነ የማቱሳላን እድሜ ተመኝተንላቸዋል።
በኪነ ጥበባት ዘርፉ ውስጥ የሚርመሰመሱትና በጥበቡ ዙሪያ ማዕዳቸውን ከዘረጉት ሙያተኞች መካከል ወረርሽኙን በተመለከተ ጥቂቶቹ ብቻ የጥበባቸውን ጠብታ አቃምሰውናልና ብናመሰግናቸው አይከፋም። ብዙ ጠብቀን እስካሁን የደረሰን ጥቂት መሆኑን ልብ ይሏል። ብዙኃኑ ደራስያን ጓዶቼ፣ ሠዓሊያንና ቀራፂያን ወገኖቼ፣ ተዋናዮቹና ድምጻዊያኑ ባለተሰጥኦዎች ምነው በዚህ ክፉ ቀን አልተባበር አሉ ብለን ብናጉተመትም ከሃሜት ሊቆጠር አይገባውም።
ቁጥራቸው እዚህ ግባ ባይባልም ጥቂት የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ከጊዜያዊ ትርፋቸው ይልቅ ሕዝባቸውን አስቀድመው በግርግሩ ገበያ መካከል በሥነ ምግባራቸው ፀንተው በመቆማቸው ልናከብራቸው ይገባል። ቁጥራቸው በርከት እንዲልም እንመኛለን። በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ተሰልፈው ለኮሮናው ጥቃት ሕዝባዊ ምላሽ የሰጡት በሙሉ ባይዘረዘሩም በልባችን ውስጥ የከበረ ቦታ እንዳላቸው ግን ሳንመሰክር አናልፍም።
የሀገራችንን ቤተእምነቶችና አራቱን መንግሥታዊ የቴሌቪዥን ተቋሞቻችንን (ኢቢሲ፣ ፋና፣ ዋልታና አዲስ ሚዲያ ኔት ወርክ) የምናመሰግነው ባልተለመደ አድናቆትና ገለጻ ነው። ምሽት ላይ ከሦስት ሰዓት ጀምሮ በሚያስተላልፏቸው መንፈሳዊ መነቃቂያዎች በጎ ትሩፋታቸውና ፍሬያቸው በቅርቡ እንደሚገለጥ ተስፋ እናደርጋለን። ለየእምነቱ መሪዎች አድናቆታችንን የምንገልጸው እነርሱው ባስተማሩን ቡራኬ “ቃለ ሕይወት ያሰማልን!” እና “ጄዛካላህ!” ወይንም “ምንዳችሁን አላህ ይክፈላችሁ!” በማለት ነው። (የእስልምና ሃይማኖት መሪዎች በምን ቃል እንደሚመረቁ በስልክ ጠይቄ የነገረኝ ወዳጄ ዑስታዝ አቡበከር ነው። መልእክቱን ስቀበል ቃሉን አጎልድፌው ከሆነ ይቅርታ እጠይቃለሁ።) ሙስሊም ወገኖቼን በሙሉ ጾማቸውን የበረከት ጾም እንዲያደርግላቸው ጭምር እግረ መንገዴን ምኞቴን እገልጻለሁ።
በየምሽቱ የሚተላለፉት መንፈሳዊ ትምህርቶች ሕዝቡ ወደ ፈጣሪው እንዲመለስና ራሱን እንዲፈትሽ የሚያግዙ ስለሆነ በረከቱ በቀላል የሚታይ አይደለም። የሰው ልጅ ወደ ፈጣሪው በተጠጋ ቁጥር “ሰዎች ሊያድርጉልን የምንፈልገውን ያህል እኛም ለሌላው እንዲሁ ለማድረግ ስለምንበረታታ” መንፈሳዊ ትምህርቶቹ በእጅጉ የሚያንፁ ናቸው።
በተረፈ በዚህ ፈታኝ ወቅት ሕዝቡን አረጋግቶ በመምራትና ኃላፊነቱን በትጋት ለመፈጸም የሚተጋውን መንግሥት ብናመሰግን ፈጠናችሁ አያሰኝም። በተለይም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩና አንዳንድ የአስፈጻሚ ተቋማት ሹመኞች (ሁሉም ባይሆኑም) በውጤታማነት እየተንቀሳቀሱ ስለሆነ ለጭብጨባ ባንቸኩልም ለምሥጋና ግን መዘግየት የሚገባን አይመስለኝም።
ኖሯቸው ላለማካፈል ንፍገት የተጠናወታቸውና “ግርግር ለሌባ ይመቻል” ይትባህልን መርሃቸው አድርገው ከሕዝብ ስቃይ ርካሽ ትርፍ ለማግኘት በሁሉም ዘርፍ ስለሚቃዡት ተኮናኞች ግን ብዙ ለማለት አልወደድኩም። አበው “ከሰደበኝ መልሶ የነገረኝ ገደለኝ” እንዲሉ ሆኖብኝ ነው። ስለ እነዚህ የክፉ ቀን የክፋት ሤረኞች አጽንኦት ሰጥቶ ማግነኑ አይበጅም። ይልቅስ በክፉ ቀን የተገጠመን አንድ ሀገራዊና ጥንታዊ ግጥም አስታውሶ ማለፉ ይበጅ ይመስለኛል።
“ያገኘም ያጣና ያጣም ያገኝና፣
ያስተዛዝበናል ይሄ ቀን ያልፍና።” አዎን ይሄው ነው። ሰላም ይሁን!!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 21/2012
በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ)
የልግስና በረከት፤ የማጋበስ እርግማን