ወዳጄ እስቲ አስበው!.. ..እንኳንስ 26 ኩባንያ አንድ አደርጎ ማስተዳደር ይቅርና አንድ ቤተሰብ (ሚስትና ልጆችህን) መምራት የቱን ያህል ከባድ እንደሆነ የምታውቀው ስትቀምሰው ነው። ዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ የቀድሞ ሲኢኦ ግን 26 ኩባንያዎችን ወልደው፣ ኮትኩተው አሳድገው ለፍሬ አብቅተዋል። ለዚህም ነው ከሰሞኑ የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸውን ስሰማ እምብዛም ያልከፋኝ። ምክንያቱም እስኪበቃቸው ሠርተዋላ! የሊደርሺፕ ጣሪያና ማገሩን አዋቅረዋላ! ደግሞ ያልከፋኝ ሌላ አይምሰልህ?!…በቅርብ ርቀት ስላወኳቸው ነው።
የሥራ ሰው፣ ደግሞም ንጹህ ሰው ታውቃለህ?… እኔን አንድ ሰው ጥራ ብትለኝ አንዴም ማሰብ ሳያስፈልገኝ እሳቸውን እጠራልሀለሁ። የሥራ ዲሲፒሊን፣ ሰው አክባሪነት፣ ጨዋነት፣ ለሥራና ለዓላማ ያላቸው ጠንካራ ታማኝነት ተነግሮ አያልቅም። በተለይ ማጭበርበርንና ሌብነትን በመጠየፍ ረገድ ያላቸው ጽናት ይገርመኛል። በቀጥታ የሚያዙበት ቢሊየን ብሮች ላይ ቁጭ ብለው ላመናቸው መታመን እንደምን ያለ ጸጋ ነው?
ያው አንተ እና እኔ በብዛት የምናውቀው አለቃ ቢሮ ቀጠሮ አስይዘህ፣ በጸሐፊው በኩል አልፈህ ስትገባ፤ አለቅዬ… ከተቀመጠበት ወንበር እምብዛም ሳይነቃነቅ “ምን ነበር?” የሚልህ ዓይነት ነው። ምናልባት ጨዋነት ያልነጠፈበት ከሆነ እንድትቀመጥ ይጋብዝህና ችግርህን ባይፈታም ያዳምጥህ ይሆናል። የዶ/ር አረጋ ግን የተለየ ነው። እንኳንስ ቢሮአቸው ዘልቀህ በኮሪደር ላይም የነገርካቸውን የማይረሱ ናቸው። በተለይ ለጠንካራ ሠራተኞቻቸውና ሥራ መሪዎች ያላቸውን አክብሮት ካስተዋልክ ልትደነግጥ ትችላለህ። በዚያው ልክ በንዴት አቅላቸውን የሚያስቱ ባልደረቦች ሲገጥሟቸው በስንት ጊዜ አንዴ ብልጭ የምትል ብስጭታቸውን መደበቅ ይሳናቸዋል።
ሁልጊዜም የተለየ አስገዳጅ ሁኔታ ካልገጠማቸው በስተቀር ጠዋት ማልደው ሥራ ይገባሉ። የመጀመሪያ ሥራቸው በሰርቪስ የሚገቡ ሠራተኞቻቸውን መቀበል ነው። በአለቃህ “እንደምን አደርክ” ተብለህ ወንበርህ ላይ መሰየም እንዴት ያለ መባረክ ነው። ማምሻውንም ቢሆን ሠራተኞች ወደ ሰርቪሳቸው ሲሄዱ በቅጥር ግቢው ተገኝተው ቆመው ካልሸኙ ወደ ቤታቸው መሄድ አይሞክሯትም። ቀን ላይ በግቢው ዘወር ዘወር ብለው በድንገት ሠራተኞችን ማነጋገር፣ እዚያው በቆሙበት ጥቃቅን ችግሮችን መፍታት ይችሉበታል።
እርሳቸው የሚመሩት የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ኦፊሰር (ሲኢኦ) ቢሮ በ1992 ዓ.ም ሲመሰረት አምስት ኩባንያዎችን በመያዝ ነበር። የኩባንያዎቹ ቁጥር በ20 ዓመታት ወደ 26 አድጓል። ሲጀመር 4 ሺ 136 የነበረው የሠራተኞች ቁጥር ዛሬ ላይ ከ9 ሺ 395 በላይ (የትረስት 2000 ኮንትራት ሠራተኞችን አያካትትም) የደረሰ ሲሆን፤ ዓመታዊ የሽያጭ መጠኑም ከ492 ሺ ብር ወደ 6 ቢሊየን በላይ ዕድገት ተመዝግቦበታል።
በነገራችን ላይ አንዳንዴም ቢሆን ምሽት ላይ እንደእኔ እና አንተ እንቅፋት ቤት ዶክተር አረጋን ማግኘት የማይታሰብ ነው። አልኮል አይጡም፣ መጠጥንም አያበረታቱም። ግን እርሳቸው ባሉበት የሚያስመሽ ሥራ ካለ ቢራ ወይንም አልኮል ስትጎነጭ ቢያዩ አይከፉም። እንዴት አለቃ ፊት የሚሉ ወገኛ አይደሉም።
ላለፉት 20 ዓመታት የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ኦፊሰር ብቻ አልነበሩም። በተጨማሪም
የሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ነበሩ። በትምህርታቸውም ቢሆን ሰቃይ ተማሪ ነበሩ። የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ፣ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኢንጂነሪንግ የትምህርት መስክ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል። በኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአሥር ዓመታት ሠርተዋል። በስኮላርሽፕ ወደ አሜሪካ ከሄዱ በኋላ እዚያ ለሃያ ዓመታት ቆይተዋል። የመጀመሪያ የፒኤችዲ ዲግሪ ሆኖሉሉ ሃዋይ ከሚገኘው ፓስፊክ ዌስተርን ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል። በዩኒቲ በፕሬዚዳንትነት ከተሾሙ በኋላ እንደገና ከፊልዲንግ ግራጁዌት ዩኒቨርሲቲ ሌላ ፒኤችዲ ዲግሪ ለመቀበል በቅተዋል። በሙያቸው መሐንዲስ የሆኑት ዶ/ር አረጋ ዘጠኝ ልጆችና አሥራ ሁለት የልጅ ልጆች አሏቸው።
በአንድ ወቅት ከሰጡኝ ቃለ ምልልስ ላይ የሚከተለውን ልጥቀስልህና ልሰናበትህ። አንተን ደህና ሰንብትልኝ ስል ዶ/ር አረጋን መልካም የሥራና የዕረፍት ጊዜ እመኝላቸዋለሁ።
- ታች ወርዶ ስለመሥራት፣
“….መጀመሪያ ማኔጀር ስትሆን የኩባንያውን የዕለት ተዕለት ሥራ በመመሪያ መሠረት መሥራት ነው። ይህ ደግሞ የራሱ የሆነ የሥራ መዘርዘር (ዲስክሪፕሽን) አለው። ዳይሬክተርም የራሱ አለው። ጀኔራል ማኔጀሩም በሥራ መዘርዝሩ መሠረት መሥራት የሚገባው አለ። በዚህ መሠረት መሥራት ከፈለክ ታች የሚሠራው ሥራ ያለ አንተ ጣልቃ ገብነት ራሱን ችሎ የሚሄድ መሆን መቻል አለበት። ኦፕሬሽን ላይ ያለ ሰው በሚገባ እየሠራ ከሆነ የእኔ ጣልቃ ገብነት አያስፈልግም፤ የምጨምረው ነገር የለኝምና። ጥቃቅን ጉዳዮች ላይ የምገባበት ምክንያት የለኝም። ነገር ግን በመንግስት ደረጃም ቢሆን ጠ/ሚኒስትሩ ከተቻለ ታች ወርደው ሰዎች ማናገራቸው አዲስ ነገር አይደለም። ይህን ሲያደርጉ እንመለከታለን።
‹‹ትንሽዬ ምሳሌ ልስጥህ። ኤምቢአይ የቀለም ፋብሪካ በቅርቡ የቃጠሎ አደጋ ደረሰበት። በዚህ ምክንያት ምርቱ ቆመ። እኔ ሲኢኦ ነኝ፣ እዚሁ ቁጭ ብዬ የሚያስፈልገውን ነገር ንገሩኝ፤ የምትፈልጉትን አፀድቃለሁ ማለት እችላለሁ። ግን ያደረኩት ምንድነው፤ ከረባቴን አወለኩኝ፤ ቱታዬን ለበስኩ። በየቦታው ያሉትን ባለሙያዎቻችንን ሰበሰብኩ። ቡድን አቋቋምኩ። በአሥር ቀናት ውስጥ በቃጠሎ ጉዳት የደረሰበትን ጠግነን ወደ ሥራ ማስገባት ቻልን። ይህ ክስተት ዝቅ ብሎ የመሥራትን ውጤታማነት በተግባር ያሳየ ይመስለኛል። በዚያ መልክ ሥራው ባይቀናጅ ኖሮ የወራት ጊዜን በወሰደ ነበር።
‹‹ወደታች ወርደህ የሠራተኛውን ሁኔታ ማየት ሳትችል፣ ችግሩን ሳትካፈል ብትቀር አለቃችን’ኮ የእኛን ሥራ የት ያውቃል ሊልህ ይችላል። ይህ ወደታች ወርዶ ማየት፣ መደገፍ፣ መመሪያ መስጠት፣ የተበላሹ ነገሮች ካሉ እንዲስተካከሉ ማድረግ፣ ጥሩውን ነገር ማበረታታት ለእኔ ጣልቃ ገብነት አይደለም። ፒራሚዱ ጫፍ ላይ ያሉ ሰዎች ፒራሚዱ ውስጥ ወደታች ወደ ላይ የሚወጡበትና የሚወርዱበት መሰላል ያስፈልጋቸዋል። የማያስፈልግ ከሆነ፣ መውጣትና መውረድ አያስፈልጋቸውም። የሚያስፈልግ ከሆነ ግን መውረድ ብቻ ሳይሆን አብረህ መሥራትም አለብህ። የቡድን ሥራ የሚባለው ለእኔ ይህ ነው።
‹‹አንዳንድ ጊዜ ለማንም ሳልነግር ድንገት ተነስቼ አንዱን ኩባንያ እጎበኛለሁ። ይህ ዓይነት ጉብኝቴ ኩባንያዎቹ ያሉበትን ደረጃ እንድፈትሽ ያግዘኛል። የአሠራር ስታንዳርድ እንዳይወርድ ይረዳኛል። ዝም ብትል ግን ወርዶ፣ አሽቆልቁሎ ሊሆን ይችላል። ኢትዮጵያ ውስጥ ውጤታማ ይሆናሉ ብዬ የማስባቸው ሥራ መሪዎች በተቻላቸው መጠን በፒራሚዱ ውስጥ ሆነው ወደላይ፣ ወደታች፣ ወደጎን የሚሄዱ አቅሙ ያላቸው ናቸው። ምክንያቱም ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ይህን ዓይነት ሊደርሺፕ የሚፈልግበት ጊዜ በመሆኑ ነው።
‹‹አርሶአደሮችን ተመልከት። ካላንደራቸው ከተፈጥሮ (ዝናብ፣ ፀሐይ) ጋር የተያያዘ ነው። የሚሠሩትን ያውቃሉ፣ መቼ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ያውቃሉ፣ መቼ እንደሚያርሱ፣ መቼ እንደሚኮተኩቱ፣ መቼ ምርቱን እንደሚሰበስቡ፣ መቼ እንደሚወቁና ወደጎተራ እንደሚያስገቡ፣ መቼ ለገበያ እንደሚያወጡ፣ ሁሉንም ያውቃሉ። አርሶአደሮቹ የራሳቸው የሥራ ባህል አላቸው። ይህ ባህል ወደ ፋብሪካ፣ ወደ ከተማ መምጣት አለበት። ሙስና፣ ተገቢ ያልሆነ ቢሮክራሲ የሚኖረው ይህ ዓይነት አሠራር ስላልመጣ ነው። እንደአርሶ አደሩ ሥራን በጊዜውና በትክክል መተግበር ባለመቻሉ ነው። ሥራን በጊዜው ጀምሮ በታቀደለት ጊዜ መፈጸምን ከአርሶ አደሩ መማር ያስፈልጋል። በተጨማሪ ከመርካቶም ብዙ ቁምነገር መማር ይቻላል።›› - በሥራቸው ረክተው ይሆን?
‹‹…በየዓመቱ ለሁሉም ሠራተኛ የሚደረግ የደመወዝ ጭማሪ አለ። በየዓመቱ ለራሴ የሥራ አፈፃፀም የምሰጠው ‹ቢ› ወይንም ‹ሲ ፕላስ› ነው። ምክንያቱም የማስበውና ያሳካሁት ነገር አልጣጣም ስለሚለኝ ነው። ረክቻለሁ የምላቸው ነገሮች አሉ። በተለይ ኩባንያዎቻችን ሰው ተኮር በመሆናቸው ብዙ ሰዎች የሥራ ዕድል በመከፈቱ፣ ሠራተኞቻችንም እፎይ ብለው፣ ተረጋግተው፣ ለሊቀመንበራችን ለሼህ ሙሐመድ በየሄዱበት ረጅም ዕድሜና ጤና እየተመኙ ሲሠሩ ማየት በጣም የምረካበት ትልቅ ነገር ነው። በተጨማሪም ከ90 በመቶ በላይ የሆኑ ሠራተኞቻችን በፎቶግራፍ ሣይሆን በአካል ያውቁኛል ብዬ አምናለሁ። ይሄ ግንኙነቴ ያረካኛል። ሌላው ሰዎች ያላቸውን ችሎታቸውን አሟጠው ለሥራ እንዲያውሉ፣ ይሄ እኮ የእኔ ጉዳይ አይደለም ብለው እንዳይዘናጉ፣ የተማርኩት ይህንን አይደለም የሚል ባህርይን እንዲተው፣ ቻሌንጅ አደርጋለሁ። አንዳንድ ጊዜ በቁጣም ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ አንድ አካውንታት ከሂሳብ በስተቀር አላውቅም ማለት የለበትም።
የመጀመሪያ ዲግሪ የተሰጠህ ብዙ ነገር ለመሥራት እንጂ የአካውንታት ትምህርት ስላለህ ሌላ ሥራ አትሠራም ማለት አይደለም። የሰው ልጅ ብዙ ችሎታ አለው ብዬ አስባለሁኝ። በዚህ አስተሳሰብ ሰዎችን በተለያየ ቦታ ላይ ችሎታቸውን እንዲያወጡና እንዲጠቀሙበት በማድረጌ በጣም ያረካኛል። እኔ የተማርኩት ሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ነው፣ ስፔስ ኢንጅነሪንግ ነው፣ ማኔጅመንት ነው፤ ግን ሲኢኦ ቢሮን፣ ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኩባንያን፣ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲን በተለይ እመራለሁ፣ በየኩባንዎቹ ሄጄ ስለስጋ፣ ስለእንቁላል፣ ስለቆርቆሮ ስናገር እገኛለሁ። እኔ ይህን ማድረግ ከቻልኩ ሌሎችም ይችላሉ። ሰዎች ችሎታቸውን መገደብ የለባቸውም። ራሳቸውን ቻሌንጅ ማድረግ አለባቸው ብዬ አምናለሁ።
‹‹በትዕዛዝ ጠዋት ስትገባ ፈርመህ ግባ፣ ስትወጣ ፈርመህ ውጣ በማለት ሠራተኛን ማስተዳደር ሳይሆን ሲነጋ ሠራተኛው መ/ቤቴ መሄድ አለብኝ ብሎ በፍቅር እንዲመጣ የማድረግ ሁናቴ መፍጠር ያስፈልጋል። ሠራተኞቼ ለሥራና ለኩባንያዎቻቸው ያላቸው ፍቅር እጅግ አርክቶኛል።
‹‹ሌላው ብዙ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን ወደአመራር ቦታ አውጥቻለሁ ብዬ አስባለሁ። አሁን ብዙ ዋና ሥራአስኪያጆች ወጣቶች ናቸው። ይሄን ማድረግ መቻሌ ያረካኛል። ቴክኖሎጂ ግሩፕ እንደስታዲየም ዓይነት ትልቅ ፕሮጀክት ወስዶ የቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች ተባብረው መሥራትና ውጤታማ እንዲሆን ማድረጋቸው በምሣሌነቱ ቆንጆ ነው ብዬ አምናለሁ። አርክቶኛልም። በኢትዮጵያናይዜሽን ፕሮግራሜ ኢትዮጵያውያን ፈረንጆችን ተክተው መሥራት በመቻላቸው ደስተኛ ነኝ።
‹‹ሌላው የቴክኖሎጂ ግሩፑ ጨዋነት፣ የሀገር ሕግ ማክበር ባህል ላይ ያለን ትኩረት በሰፊው እየታወቀ መሄዱ በጣም ደስ ይለኛል። በመጨረሻም አለቃዬ በመጠኑም ቢሆን የቴክኖሎጂ ግሩፕ መሀል እሴት ጨምሯል ብዬ ስለማምን ደስ ይለኛል። ሰዎችን መርዳት ማለት ቤተሰብን መርዳት ነው፣ ቤተሰብ መርዳት ማለት ሀገርን መርዳት ነው። በዚህ ረገድ ጥሩ ሥራ ሠርተናል ብዬ አምናለሁ።››
“ኤ” ን መነፈግ ለምን?
‹‹…መጀመሪያ ነገር የነበረኝን ራዕይ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ማሳካት አለመቻሌ ነው። መጀመሪያ የነበረኝ ራዕይ የሼህ ሙሐመድ በኢትዮጵያ የሚገኙ ኩባንያዎች በጠቅላላ አንድ አመራር ኖሯቸው፣ ከመንግሥት ቀጥሎ በጣም ግዙፍ ሆነው ማየት ነበር። አሁን ያለው የተለያዩ ኩባንያዎች አደረጃጀት መጥፎ ነው ማለቴ አይደለም። አሁን ያለው አሠራርም ሌላኛው አማራጭ መሆኑን እገነዘባለሁ። ነገር ግን አንድ ጠንካራ የሆነ ግሩፕ ተፈጥሮ፣ ጥንካሬው በአስተማማኝ መሠረት ላይ እንዲቀመጥ፣ የሼህ ሙሐመድ ራዕይና ሌጋሲ ለአሁን ብቻ ሣይሆን ለቀጣይ ትውልዶች እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ።
‹‹ለምሳሌ ከአንድ ሰው ዕድሜ በላይ በሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የተመሠረተውን ቦይንግ ኩባንያን ውሰድ። መሥራቹ ሚስተር ቦይንግ ካረፉ ብዙ ዓመታት አልፈዋል። አሁንም ግን ገናና እና ስመጥር ኩባንያ ሆኖ ቀጥሏል። በዚሁ መልክ የሼህ ሙሐመድ ሌጋሲ የዛሬ 100 እና 200 ዓመታትም የሚዘልቅ እንዲሆን ከማድረግ አኳያ ብዙ አልሠራንም ብዬ አምናለሁ።
‹‹ከዚህ ውጪ በጣም ደስተኛ ነኝ። በሥራ ብቻ ሣይሆን በሌሎች ማኅበራዊ ተሳትፎዎች በመንግስት አካባቢ፣ በሃይማኖት አካባቢ፣ ወዘተ… የምችለውን ሁሉ ማድረግ በመቻሌ ውጤታማ አድርጎኛል ብዬ አስባለሁኝ።
ወደፊትም ገና እንሠራለን፣ እናድጋለን፣ ለሀገራችንም ኢኮኖሚ ዕድገት የተሻለ ነገር እናደርጋለን በሚል አሁንም የአቅማችንን እያበረከትን እንገኛለን። ይህም ሆኖ ላደርግ የምችለውንና ያለኝን ችሎታ ከሠራሁትና አሁን ከምሠራው ጋር ሳነጻጽረው ብዙ ይቀረኛል። ስለዚህም ‘ኤ’ የማገኝበትን ጊዜ እናፍቃለሁ።››
በመጨረሻም
የክብር ዶ/ር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ተጠባባቂ ሲኢኦ አድርገው ሰሞኑን የሾሟቸው አቶ ጌታቸው ሐጎስ በዶ/ር አረጋ ሊደርሺፕ ውስጥ ጉልህ አሻራ የነበራቸው ናቸው። በመጨረሻም የምሰናበተው ለተሰናባቹ ዶ/ር አረጋ ይርዳው እና ለአዲሱ ተሿሚ መልካም የሥራ ዘመን (ጊዜ) በመመኘት ነው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 21/2012
ፍሬው አበበ