አቶ ፍቅሬ ኮይራ ይባላሉ። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ካጠናቀቁ በኋላ፤ ራሺያ በመሔድ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሰርተዋል። ወደ አገራቸው እንደተመለሱም በግብርና ሚኒስቴር በተለያዩ ቦታዎች ሃላፊ በመሆን አገልግለዋል። ቀደም ሲል በተማሪነት ጊዜያቸው ከወላይታ ሶዶ አዲስ አበባ በመግባት ዘመድ ቤት ይኖሩ የነበሩት አቶ ፍቅሬ፣ ከወንደላጤው አጎታቸው ጋር አራት ኪሎ ቤት ተከራይተው ከጥገኝት ተላቀቁ።
እነ አቶ ፍቅሬ ይኖሩበት የነበረው ቤት መንግስት ባወጀው መሰረት ባለቤትነቱ የቀበሌ ሆኖ እነርሱ በተከራይነት ቀጠሉ። ብዙም ሳይቆዩ አቶ ፍቅሬ ለትምህርት ወደ ራሺያ አመሩ። አብረዋቸው ይኖሩ የነበሩት አጎታቸው ደግሞ የእርሳቸውን ከአገር መውጣት ተከትለው ሚስት አገቡ። ሚስቲቱ ከቀደመ ባሏ ሁለት ልጆች ያሏት ሲሆን፣ ምንም እንኳ በኮተቤ እና በአየርጤና አካባቢ ከባሏ የወረሰችው የግል ቤቶች ቢኖሯትም፤ በእዚህም ቀበሌ እነ አቶ ፍቅሬ የተከራዩበት ቤት ቅጽ ውስጥ ስሟን ብቻ ሳይሆን የልጆቿን ስም አስገባች።
አቶ ፍቅሬ ከራሺያ መጥተው ወደ ቤት ሲመለሱ፤ ሙሉ ለመሉ የአጎታቸው ሚስት ቤቱን ተቆጣጥራዋለች። አጎትየው በመሞቱ ‹‹የራሴ ቤት ነው፤ አላውቅህም›› ብላ አባረረቻቸው። የግለሰብ ቤት ተከራይተው ትዳር መሰረቱ። ሆኖም በቤቱ ቅጽ ውስጥ የአቶ ፍቅሬ ስም በመኖሩ ተከራክረው በከፊል ረቱ። ሴትየዋ ግን የምትለቅላቸው አልነበረችም። አስቀድማ የልጆቿን ስም በማስገባቷ የእርሷ ልጆችም በቀበሌው ቤት መኖር እንዲችሉ ሆኖ ተወሰነ።
በብዙ ጭቅጭቅ እና አማላጅነት የሴትየዋ ወንድ ልጅ እና አቶ ፍቅሬ መሃል ሰላም ሰፍኖ የቀበሌ ቤቱን ለሁለት ሁለት ሁለት ክፍል ቤቱን ተካፈሉ። የአቶ
ፍቅሬ ህይወት በእዛው ቀጠለ። ሹመት መጣ፤ በየጊዜው ለስብሰባ በተለያዩ አገራት ወደ አውሮፓም ሆነ ወደ አፍሪካ ለስልጠናና ተሞክሮ ለመውሰድ ይጓዛሉ። የውሎ አበል ተብሎ የሚከፈላቸውንና ደመወዛቸውን ጨምረው ጠንክረው ገንዘብ ቢያጠራቅሙም፤ እንደሌሎቹ እኩዮቿቸው መሬት ገዝተው ቤት ሰርተው ልጆቻቸውን በፎቅ ቤት ለማሳደግ አልቻሉም። በተደጋጋሚ ቢሞክሩም ደፍረው ቤት ለመግዛት አልታደሉም።
‹‹አሁን ላይ ሳስበው ካጋጠሙኝ መልካም አጋጣሚዎች በሙሉ ከሁሉም ይልቅ የሚያበሳጨኝ፤ ከ16 ዓመት በፊት የተከሰተው ነው›› ይላሉ። ጉርድ ሾላ አካባቢ በአነስተኛ ብር በወቅቱ ሙሉ ወጪው ተችሎ ምናልባትም ከ200 ሺህ ብር ባልዘለለ ወጪ ቤት ለመግዛት ከደላሎችና ከሻጭ ጋር ተስማሙ። ገንዘቡን ሊከፍሉ ባለቤታቸውን እና የባለቤታቸውን ወንድም ይዘው ወደ ሚሸጠው ቤት አመሩ። ተነጋግረውና ተስማምተው ገዢና ሻጭ ውል አዘጋጅተው ቢገናኙም ሻጭ ‹‹በራሴ በተዘጋጀው ውል መሻሻጥ አለብን›› የሚል ሃሳብ ያቀርባሉ። ገዢው አቶ ፍቅሬ ተስማምተው ሊገዙ ‹‹እማኞች ይፈርሙ›› ሲባል አንደኛው ከጎረቤት የተጠራው እማኝ ወደ ቤት ሲገባ ሻጭን ‹‹ሻለቃ›› ብሎ ይጠራል። ቀድሞም የተጠራጠሩት አቶ ፍቅሬ ‹‹ውሉ ላይ የሻጭ ስም ለምን ‹አቶ› ተብሎ ተፃፈ? ለማታለል ነው›› ብለው ገንዘባቸውን ይዘው ውል መዋዋሉን አቋርጠው ወደ ቤታቸው ተመለሱ።
‹‹የስም ለወጥ አለው›› በሚል ሰበብ በተፈጠረ ስጋት ይህኛው ቤት አመለጠ። ሻጭ ቸግሯቸው ስለነበር ‹‹ውሉ ከፈለግክ ‹ሻለቃ› በሚል ይስተካከል›› ብለው ነበር። አቶ ፍቅሬ ግን ውስጣቸው ያደረው ፍርሃት ‹‹ለዘመናት ፍላጎቴን ገድቤ ያጠራቀምኩትን ገንዘብ ሜዳ ላይ አልበትንም›› በሚል ቤቱን ሳይገዙ ቀሩ። ይህ የይሆናል ፍርሃት በጉርድ ሾላ በተገኘው ቤት ላይ ብቻ አላበቃም።
ጊዜ ጊዜን እየወለደ ሲሄድ በእርሳቸው ገንዘብ ቤት
መግዛት አዳጋች መሆን ጀመረ፤ ትንሽ ራቅ ያለ ቦታ ቢሆንም፤ ‹‹ልግዛ›› ብለው እንደገና ማጠያየቅ ያዙ። ሃና ማሪያም አካባቢ በሚፈልጉት ዋጋ የሚሸጥ ቤት አገኙ። አሁን ያው ፍራቻ እና ጥርጣሬ አለቀቃቸውም። ከባለቤታቸው ጋር ሄደው ሲጎበኙ ቤቱ የሰው ጊቢን አልፎ የሚገባበት ነበር። ‹‹ከሰዎቹ ጋር አለመስማማት ቢፈጠር ማለፊያ ይጠፋል፤ ችግር ነው›› በሚል ፍራቻ እንደገና ለመግዛት ጫፍ ደርሰው መልሰው አፋረሱት።
አቶ ፍቅሬ አሁንም ገንዘብ ሲያንሳቸው ህጋዊ የሆነ ከሚታወቅ ሰው ላይ ቤት ለመግዛት ሲያጠያይቁ ገንዘቡ እንዲሁ ያለስራ ተቀምጦ ዋጋ እያጣ መጣ። አዲስ አበባ ላይ ቤት የመግዛት ተስፋቸው ሙሉ ለሙሉ ተሟጠጠ። ክፍለአገርም ቢሆን የሚያውቋቸው ሰዎች እና ዘመድ ባለበት አካባቢ ቢቻል የሚኖሩበት ካልሆነም የሚያከራዩትን ቤት ለመግዛት ማጠያየቅ ጀመሩ። በቅርብ በአዲስ አበባ ዙሪያ በኦሮሚያ ልዩ ዞኖች ባሉ ይዞታዎች መተማመን አቃታቸው። የቅርብ ዘመዳቸው ባሉበት በወላይታ ሶዶ ቆንጆ የሚባል የሚሸጥ ቤት መገኘቱ ተነገራቸው። የይዞታው ስፋት የሚማርክ፤ ዋና ቤት ብቻ ሳይሆን ሰርቪስ ቤት ያለው በደህና ዋጋ መከራየት የሚችል ቤት ቢያገኙም ሄደው ማየት አልቻሉም።
ባለቤታቸው ወደዛው አመሩ፤ ባለቤቲቱ ቤቱን አይተው ቢወዱትም የአቶ ፍቅሬ ቤቱን አይቶ አለመወሰን ስላሳሰባቸው ደፍረው ውል መዋዋል እና ቤቱን መግዛት አልቻሉም። አቶ ፍቅሬም ለአስቸኳይ የስራ ጉዳይ ከአገር ወጥተው ቶሎ ስላልተመለሱ የቤት መግዛት ጉዳዩ በይደር ሲቆይ በመሃል ትዕግስት ያጡት ሻጮች ቤቱን ለሌላ ሰው ዋጋውን ቀንሰው ሸጡት።
አቶ ፍቅሬ ቀድሞ በእርሳቸው ፍርሃት አሁን ደግሞ በሚስታቸው ፍርሃት ቤቱን ሳይገዙ ቀሩ። አራት ልጆች በዛችው በቀድሞ የቀበሌ ሁለት ክፍል ቤት ውስጥ ተወልደው አደጉ። አካባቢው ለመልሶ ማልማት ይፈለጋል ቢባልም፤ ቤቱ ሳይፈርስ ኑሯቸውን
ቀጠሉ። በ1997 ዓ.ም ‹‹የጋራ መኖሪያ ቤት ባገኝ›› ብለው ተመዘገቡ፤ ነገር ግን ዕድል አልቀናቻቸውም።
በ2005 ዓ.ም በዳግም የጋራ መኖሪያ ቤቶች ምዝገባ የ40/60 ቤት ተመዝግበው ቀድመው ቤት ለመግዛት ሲያፈላልጉበት የነበረውን ገንዘብ በሙሉ ለመንግስት አስገቡ። ሆኖም እንዳሰቡት አልሆነም። ዓመታት ተቆጠሩ፤ አሁን ምንም እንኳ ገንዘቡን ከከፈሉ ሰባት ዓመታትን ቢያስቆጥሩም ቤት ማግኘት አልቻሉም። በፍራቻ ሲፋረሱ የነበሩ የቤት ግዢዎች ምናልባት ተፈፅመው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ከነበረው ህይወታቸው የተሻለ መኖር በቻሉ ነበር። ነገር ግን አልሆነም።
ግለሰብን አምነው በመፍራታቸው ገንዘብ እያላቸው ቤት ሳይገዙ ዓመታትን በሁለት ክፍል ቤት ስድስት የቤተሰብ ዓባላትን ይዘው ባልተመቸ ሁኔታ የኖሩት አቶ ፍቅሬ፣ መንግስትን ማመናቸውም ዋጋ እያስከፈላቸው ይገኛል። አሁንም የልጆች ክፍል የለም። መመገቢያውም ማረፊያውም መተኛውም ያው ሳሎን ያለው ሶፋ ነው። በሌላኛው ክፍል ያለው የመኝታ ቤት አልጋ ለገሚሶቹ መተኛ ብቻ ሳይሆን ማጥኛም ጭምር ነው። ይህ የሆነው ዕውቀት አንሶ ወይም ገንዘብ ቸግሮ አይደለም። አቅም ኖሮ በተፈጠረ ፍራቻ ነው። ዛሬም አቶ ፍቅሬ የተመዘገቡትን ባለ 3 መኝታ የ40/60 ቤት አገኛለሁ ብለው ተስፋ አድርገዋል። ነገር ግን በሁለቱም ዙር የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች በወጡት እጣዎች ውስጥ የእርሳቸው ስም የለም። ያመኑት መንግስት መቼ የቤት ባለቤት ያደርጋቸው ይሆን? ለመገመት ያዳግታል።
አቶ ፍቅሬ ‹‹ሰላም ያቆየን፤ የግል ቤቴን ለማግኘት የፈለግኩትም ሆነ የጠበቅኩት አንድና ሁለት ዓመታትን ብቻ ሳይሆን፤ በአስር የሚቆጠሩ ዓመታትን ጠብቄያለሁ። ዛሬም ተስፋ አደርጋለሁ። አሁን ላለፈው ጊዜ አላማርርም፤ ጤና ይስጠን፤ ነገ የተሻለ ቀን ይሆናል ብዬ አስባለሁ›› በማለት ተስፋቸውን ገልፀውልናል። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20/2012
ምህረት ሞገስ
1996; 2 483 506 how to buy priligy im 16 years old