የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በከተማዋ በተቋራጮች እያስገነባቸው ካሉ ከ80 በላይ የመንገድ ፕሮጀክት ውስጥ የራስ ደስታ – ቀጨኔ መድሃኒዓለም- ስምንት ቁጥር ማዞሪያ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አንዱ ነው። የግንባታ ፕሮጀክቱ በኮንትራት ስምምነቱ መሰረት ሁለት ዓመታትን ይፈጃል የተባለ ቢሆንም፤ አብዛኛዎቹ ስራዎች በተለይ የቅድመ አስፓልት ስራው የክረምቱ ወቅት ከመግባቱ በፊት ሊጠናቀቅ እንደሚችል ባለስልጣኑ አስታውቋል።
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጥዑማይ ወልደገብርኤል እንደሚገልፁት፤ የራስ ደስታ -ቀጨኔ መድሃኒዓለም- ስምንት ቁጥር ማዞሪያ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ሁለት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር ርዝማኔና የእግረኛ መንገድን ጨምሮ 20 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ነው። 204 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞለትም በታህሳስ ወር በ2011 ዓ.ም በከተማው ምክትል ከንቲባ በይፋ ተጀምሯል። የመንገድ ፕሮጀክቱ ማርካን ትሬዲንግ በተሰኘ ሀገር በቀል ስራ ተቋራጭ እየተከናወነ ሲሆን፣ የማማከርና የምህንድስና ቁጥጥር ስራውን ደግሞ ቤስት ኢንጂነሪን አማካሪ ድርጅት እያከናወነው ይገኛል። ይህ ፕሮጀክት ባለፈው ዓመት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ካስጀመሯቸው ሰባት የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ ሲሆን፣ ግንባታው ከተጀመረበት ቀን አንስቶ አንድም ቀን ሳይስተጓጎል በተሻለ የግንባታ እንቅስቃሴ ደረጃ ላይ ይገኛል። ከመጀመሪያውኑ በአካባቢው ህዝብ ጥያቄ የተጀመረ ፕሮጀክት ከመሆኑ አኳያና የከተማ አስተዳደሩም በቅርብ የሚከታተለው በመሆኑ የግንባታ አፈፃፀሙ ጥሩ ደረጃ ላይ የደረሰና በሞዴልነት የሚጠቀስ ነው። ከወቅታዊ የኮሮና ቫይረስ ጋር በተያዘ መጠነኛ መቀዛቀዝ ከማሳየቱ በስተቀር መንገዱ በጥሩ እንቅስቃሴ
እየተሰራ ይገኛል።
የመንገድ ፕሮጀክቱ በሁለት አመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እየተሰራ የሚገኝ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት አንድ አመት ከአራት ወራት ሆኖታል። ቀደም ሲልም ከራስ ደስታ ችሎት ድረስ ያለው የመንገዱ አካል በግራም በቀኝም የመጀመሪያ ደረጃ የአስፓልት ማልበስ ስራ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የመሰረተ ልማት ዝርጋታና የእግረኛ መንገድ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
መንገዱ መጠነኛ መቀዛቀዞች የታዩበት ቢሆንም፤ አፈፃፀሙ አሁንም ጥሩ በመሆኑ ቢያንስ የክረምቱ ወቅት ከመግባቱ በፊት የዋናው መንገድ የቅድመ አስፓልት ስራ ይጠናቀቃል ተብሎ ይታሰባል። ከክረምቱ ወቅት በኋላም የእግረኛ መንገድ፣ የትራፊክ ምልክትና የቀለም መቀባት ስራዎች ይከናወናሉ። እስካሁንም የመንገዱ አፈፃፀም 45 ከመቶ ደርሷል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ የመንገድ ፕሮጀክቱ በመሃል ከራስ ደስታ ዳምጠው መታሰቢያ ሆስፒታል ጋር በተያያዘ
የተወሰነ የወሰን ማስከበር ችግር አጋጥሞት የነበረ ቢሆንም፤ ከመንግስትና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በተደረጉ ውይይቶች ሊፈታ ችሏል። ሆኖም አሁንም ከቀጨኔ መድሃኒአለም ቤት ክርስቲያን አካባቢ ባለው አደባባይ ያላለቁ የወሰን ማስከበር ስራዎች አሉ። ይህም የክፍለ ከተሞች የመሬት ማኔጅመንት ፅህፈት ቤቶችን ትብብር ይጠይቃል። በጥቅሉ ግን ከ80 በመቶ በላይ የፕሮጀክቱ ጉዳዮች አልቀዋል።
በአሁኑ ወቅትም የመንገዱ የስትራክቸር፣ ቁፋሮና የውሃ ማስተላለፊያ ቦዮች 80 ከመቶ ስራዎቻቸው ተጠናቅዋል። የፕሮጀክቱ አንድ ኪሎ ሜትር የሚሆነው መንገድም አስፓልት ለብሷል። ቀሪውን የዋናው መንገድ ሴሌክት ማቴሪያል የማንጠፍ ሲሆን፣ የቅድመ አስፓልት ስራዎችም ተጠናቀዋል። ፕሮጀክቱ ከዚህ በጀት ዓመት ገና ሶስት ወራት የሚቀሩት ከመሆኑ አኳያም ቀሪ ስራዎችን በነዚህ ጊዜያት ውስጥ ሰርቶ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ተገልጽዋል።
ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ሙሉ በሙሉ የአስፓልት ስራውን ማከናወን ባይቻል እንኳን የቅድመ አስፓልት ስራ በመስራት ከህብረተሰቡ የሚመጣውን ቅሬታ ማስቆም ይቻላል። በዚህ ዓመት ብቻ ቢያንስ ከ75 በመቶ በላይ የሚሆነውን ስራ ማጠናቀቅ የሚቻል ከሆነ ከከኮንትራት ስምምነቱ በፊት መንገዱ ተጠናቆ ሙሉ በሙሉ ለትራፊክ ክፍት የሚሆንበት እድል ይኖራል።
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ ፕሮጀክቱ ሁለት አመታትን የሚፈጅ ቢሆንም፤ ዋናው የመንገዱ ስራዎች ከወዲሁ የሚጠናቀቁ ከሆነ ከተቀመጠው የኮንትራት ስምምነት በፊት ሊጠናቀቅ ይችላል። ይሁንና የእግረኛ መንገድ፣ የቀለም ቅብና የትራፊክ ምልክትና የመሳሰሉ ቀሪ የመንገዱ ስራዎችን የሚጨምር ከሆነ በመጪው ዓመት በታህሳስ ወር 2013 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ባለስልጣኑ የሚያስተዳድራቸው አብዛኛዎቹ የመንገድ ፕሮከጀክቶች ከፍተኛ ውጣ ውረድ የሚታይባቸውና በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ የሚጠናቀቁ አይደሉም። ለዚህም የወሰን ማስከበር ስራዎች ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ። ይሁን እንጂ የዚህ መንገድ ፕሮጀክት አፈፃፀም ከሌሎች ፕሮጀክቶች ጋር ሲነፃፀር በጥሩ አፈፃፀም ደረጃ ላይ ይገኛል። ለዚህም የከተማ አስተዳደሩ ትኩረትና ያልተቋረጠ ክትትል እንዲሁም ኮንትራክተሩ ስራዎችን ሳያቆራርጥ መስራት ከፍተኛውን ሚና ተጫውቷል።
የራስ ደስታ – ቀጨኔ መድሃኒዓለም – ስምንት ቁጥር ማዞሪያ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ሲሆን፣ ወደ አዲሱ ገበያ፣ ፒያሳ፣ መርካቶ፣ ቁስቋም፣ ሽሮ ሜዳ፣ ስድስት ኪሎና አካባቢው መሄድ ለሚፈልጉ ተሽከርካሪዎች በአቋራጭነት በመጠቀም ፈጣን የሆነ የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣንም የመንገድ ፕሮጀክቱ ክረምት ከመግባቱ በፊት ዋና ዋና የፕሮጀክቱን ክፍል ሰርቶ ለማጠናቀቅ ርብርብ እያደረገ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20/2012
አስናቀ ፀጋዬ