በአሁን ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ከ110 ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን ይገመታል። የህዝብ ቁጥር በሚጨምርበት ወቅት ደግሞ ያንን ህዝብ መሸከም የሚያስችል ኢኮኖሚ ሊያድግ የግድ ይላል። ይሁን እንጂ እየመነጨ ያለው ኢኮኖሚም ሆነ ኢኮኖሚውን ይበልጥ ሊያሳድግ የሚችል ቴክኖሎጂ የሚፈለገውን ያህል ባለመስፋፋቱ ገጠር ያለው የህብረተሰብ ክፍል በአስገዳጅ ምክንያቶች ወደ ከተማ ሲፈልስ ይስተዋላል። በተለይ የገጠሩ ኢኮኖሚም ሆነ መሬት የገጠሩን ህዝብ መደገፍ እንዳቃተው ይነገራል።
ከተማ ራሱ ያለው የህዝብ ቁጥር በየጊዜው የሚጨምር መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ገጠር ያለው የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ አማራጭ ፍለጋ ወደከተማ ይፈልሳልና ለዚህ መፍትሄ ሊሆን የሚችለው ምን ይሆን? ስንል የጠየቅናቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአርክቴክቸር ቢውሊዲንግ ኮንስትራክሽንና የከተማ ልማት ትምህርት የሚያስተምሩት ዶክተር ህያው ተረፈ፤ በኢትዮጵያ ደረጃ የከተማ እድገት መጠን በየዓመቱ እስከ 5 ነጥብ 4 በመቶ እየጨመረ ይገኛል። ይህ የተወሰነ ያህሉ ከገጠር ወደ ከተማ በመምጣቱ ቢሆንም የከተማው ህዝብ በራሱ ቁጥሩ እየጨመረ መሄዱን የሚያሳይ ነው በማለት ለጠየቅናቸው ጥያቄ መል ስ መስጠት ይጀምራሉ።
ኢትዮጵያ እንደ አገር ከገጠር ወደ ከተማ እየተሸጋገረች መሆኗን የሚጠቅሱት ዶክተር ህያው፣ ይህ ሽግግርም ከተለኮሰ መቆየቱን ይገልጻሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እየተካሄደ ያለው በከፍተኛ ፍጥነት እንደሆነ መሆኑን ያስረዳሉ።
ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት የራሱ ምክንያት አለው የሚሉት ዶክተር ህያው፤ ይኸውም ገፊና እና ሳቢ የሆኑ ምክንያቶች በማለት ያብራራሉ። በተለምዶ የገጠር ግፊት (ገፊ) በመባል የሚታወቀው ምክንያት አለ። እንዲህም ሲባል ከገጠሩ የአገሪቱ ክፍል የኑሮ ሁኔታ ገፍቶ የሚያመጣው የህብረተሰብ ክፍል ነው። ያንን ሰው ወደ ከተማ ገፍቶ ሊያመጣው የሚችለው ለአብነት የእርሻ መሬት እጥረትን መጥቀስ ይቻላል። አሊያም ደግሞ የቤተሰብ ብዛትም እንደ ገፊ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል። ይህ ደግሞ ያለውን የእርሻ መሬት ለማከፋፈል በሚደረግ ሂደት ለአንድ ሰው ሊደርስ የሚችለው ኮታ ስለሚቀንስ ያለው አማራጭ ወደከተማ መፍለስ ላይ ነውና ትኩረት የሚደረግበት ሁኔታ አለ።
ዶክተር ህያው፣ ከገጠር ወደ ከተማ ለሚደረገው ፍልሰት ምክንያት ናቸው የተባሉትን አክለው ሲናገሩ፤ የገጠሩ አካባቢ ድርቅ ተከስቶ ሊሆን ይችላል። አሊያም ደግሞ ሊገፋ የሚችለው ምክንያት ሰላም በመጥፋቱ መረጋጋት አለመቻልን ተከትሎ ሊሆን ይችላል። እነዚህን መሰል የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና አንዳንዴም ደግሞ የአካባቢያዊ ገፊ ሁኔታዎች አሉ። ስለሆነም በእነዚህ ገፊ ምክንያቶች ወደ ከተማ የሚፈልስ ህዝብ አለ ማለት ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ የከተማ ስበት የሚባል ነገር አለ። ይህም ልክ እንደ ገፊ ምክንያት ሁሉ የገጠሩን ህዝብ ወደ ከተማ የሚያፈልስ ሁኔታ ነው። እንዲህ ሲባል ደግሞ ከተማ ውስጥ የተሻለ የገቢ ሁኔታ ያለ መስሎ በሚታይበት ጊዜ የገጠሩ ህብረተሰብ የሚያገኘውን መረጃ በመያዝ ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት ነው። ይህ አይነቱ ፍልሰት ጥሩ የሚባል አይነት ፍልሰት ነው ሊባል ይቻላል። ከገጠሩ አካባቢ በችግር ምክንያት ተገፍቶ ከመምጣት የተሻለ ገቢ እንዲኖር ታስቦ መምጣት የተሻለ ነው።
እንደ ዶክተር ህያው ገለጻ፤ ወደ ከተማ ተስቦ የሚመጣው የህብረተሰብ ክፍል የተሻለ ገቢ ለማግኘትና ኑሮውንም መልካም ለማድረግ የታሰበ በመሆኑ ተመራጭ ነው። ይህ አይነቱ አፈላለስ የሚጠበቅም ጭምር ነው። ከተማ አካባቢ የሰው ኃይል ይፈለጋል። በተለያዩ የሙያ አይነት የሰው ኃይል ስለሚፈለግ ያንን ፍላጎት መሰረት አድርጎ ወደ ከተማ መፍለስ ‹‹መልካም ፍልሰት ነው›› ተብሎ ሊወሰድ ይችላል።
ዶክተር ህያው እንደሚያብራሩት፤ ገጠር አካባቢ ባለው የሁኔታዎች አለመመቻቸት ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት ግን ከችግር ጋር የተያያዘ ስለሆነ የሚበጅ አይደለም። እንዲያም ሆኖ የህዝቡ ከገጠር ወደ ከተማ የመፍለሱ ጉዳይ የማይቀር ነው። አንዴ ጥቅሙን ማጣጣም ስለተቻለ በተወሰነ መልኩ ጉዳት ቢኖረውም ፍልሰቱ አይቀርም፤ የሌሎቹም አገሮች ልምድ የሚያሳየው ይኸው እንደሆነ ነው ።
‹‹በአሁኑ ወቅት እንደ እነአውሮፓ እና አሜሪካ አይነት አገሮችን ስንመለከት ወደ 80 በመቶና ከዚያ በላይ ያህሉ ወደ ከተማ ሽግግር አድርገዋል። በዚህም መሰረት ሰፊ ቁጥር ያለው ህዝባቸው የሚኖረው በከተማ ውስጥ ነው›› ያሉት ዶክተሩ፣ ‹‹ልክ እንደ እኛ ሁሉ ከዚህ ቀደም አብላጫ ህዝባቸው ይኖር የነበረው ገጠር ነው›› መሆኑን ያወሳሉ።
ስለዚህ ኢኮኖሚው ተሻሽሎና እድል ፈጥሮ ህዝቡን ከገጠር ወደ ከተማ መሳብ በመቻላቸው አሁን በገጠሩ ያለው የህዝባቸው ቁጥር ከ20 በመቶ ያነሰው ብቻ እንደሆነ ያስረዳሉ። በመሆኑም በኢትዮጵያም አብላጫ ቁጥርን የያዘው ህዝብ በገጠር ያለ ቢሆንም፤ በሂደት ወደዚህ ስርዓት መግባቱ የማይቀር መሆኑን ይገልፃሉ።
‹‹ነገር ግን›› ይላሉ ዶክተር ህያው፣ ይህን ለማሳካት በርካታ ስራዎች መሰራት እንዳለበት ይናገራሉ። (የአገልግሎት ዘርፉ) ፐብሊክ ሴክተሩ አቅም ያንሰዋልና የፋይናንስም ሆነ የቴክኒክ ድጋፍ ያሻዋል። በተለይ የተማረ የሰው ኃይልና ቴክኖሎጂ የመሳሰሉ ነገሮች የግድ ይለዋል። እነዚህ ነገሮች የሚሟሉ ከሆነ ግን ሸግግሩ እንደ መልካም ሁኔታ የሚቆጠር መሆኑን ይገልጻሉ። አለበለዚያ ግን በዚያው ልክ ችግር ሊኖር እንደሚችል ነው የጠቆሙት።
ዶክተር ህያው እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ ከሁለት ሺህ በላይ ህዝብ የሚኖርባቸው ከተሞች በአሁኑ ወቅት ሁለት ሺህ አምስት መቶ ደርሰዋል። ይህ የሚያሳየው ቁጥራቸው በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን ነው። ህዝቡ ከገጠር ወደ ከተማ ሲፈልስ ግማሹ ወደ ትልልቆቹ ከተሞች እንደሚገባ ሁሉ አብላጫ ቁጥር ያለው ደግሞ ወደ ትንንሾቹ ከተሞች እየገባ ነው። ከእዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ወደ ነባሮቹ ከተሞች እየገቡ እንዳሉት ሁሉ፤ በዚያው ልክ አዳዲስ ከተሞች እየተቆረቆሩ መሆናቸው የከተማዎቹን ቁጥር አሳድጓቸዋል። ይህ ሁሉ ሆኖ ግን በየዓመቱ እድገት ቢኖርም በኢትዮጵያ ደረጃ በከተማ የሚኖረው ህዝብ ቁጥር የደረሰ 20 በመቶ ብቻ በመሆኑ ሊጤን ይገባል።
‹‹80 በመቶ ያህሉ የህብረተሰብ ክፍል ኑሮውን ያደረገው በገጠሩ በመሆኑ አሁንም ገና ብዙ መስራት ይቀራል›› ሲሉ ጠቅሰው፤ እንደ አደጉት አገራት ከሆነ ከገጠር ወደ ከተማ 60 በመቶ ያህሉ የሕብረተሰብ ክፍል ገና መምጣት ያለበት እንደሆነ ይገልፃሉ። በተመሳሳይ መልኩ ‹‹ከተሞችም በቁጥር እየጨመሩ መሄድ ይጠበቅባቸዋል›› ይላሉ።
‹‹ይሁንና›› የሚሉት ዶክተር ህያው፣ ‹‹ይህ ሁሉ ሸግግር ግን ጥሩ እንዲሆን የአገልግሎት ዘርፉ (የፐብሊክ ሴክተሩ) በጣም ጠንካራ ሆኖ መዘጋጀት አለበት። ምክንያቱም ከከተማው ቁጥር በላይ የሆነ ሰው ወደ ከተማ ሊመጣ ይችላል። ለምሳሌ ከተማው ማኖር የሚችለው አምስት ሺህ ሰው ቢሆን ፍልሰት በማየሉ ከአቅም በላይ ሆኖ ወደ ሃምሳ ሺህ ሰው በከተማው ቢገኝ፤ ወደ 45 ሺህ ያህሉ ሰው መኖር በሚችልበት አይነት ደረጃ አይኖርም። ከዛ በጣም ዝቅ ባለ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ በመግባት ምናልባትም እስከ ጎዳና ላይ መውጣት ድረስ ሊቸገር ይችላል።›› ይላሉ።
‹‹ካፒታል ሰራተኛን ወደ ራሱ በሚስብበት ጊዜ ሁልጊዜ የሚስበው ከአቅሙ በላይ ነው የሚባል አባባል አለ›› የሚሉት ዶክተሩ፣ ለምሳሌ አንድ ሺህ ሰራተኛ ቢፈለግ የሚመጣው አስር ሺህ ተወዳዳሪ ነው። ካፒታሉ ከመጣው አስር ሺህ ውስጥ አንድ ሺውን ይመርጥና ይወስዳል። ሌላውን ሰራተኛ ወደመንግስት ይገፈተራል፤ መንግስት ደግሞ ለእነሱ መኖሪያም ሆነ አስፈላጊ አገልግሎት ለማቅረብ ብሎም የስራ እድል ለመፍጠር ውጥረት ውስጥ ይገባል›› ሲሉ ይገልፃሉ።
‹‹ስለዚህ እኛ ብዙ ጊዜ የምንለው ነገር ከገጠር አካባቢ ያሉ ገፊ ምክንያቶችን የከተማ ልማቱ አካል አድርጎ ለእነሱም ጊዜ ለመስጠት መሞከር ያስፈልጋል። እንዲህም ሲባል ገጠር አካባቢ የሚገፉ ነገሮችን ለምሳሌ ቀደም ሲል የጠቀስኩት የመሬት እጦት ሊሆን ይችላል፤ ወይ ደግሞ የድርቅ ችግር ገጠር ውስጥ ካለ ከተማ ላይ የምናደርገውን የኢንቨስትመንት ከተማ ሽግግር እዛም ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ ኢንቨስትመንት ከተማ ላይ ኢንቨስት እንደሚደርግ ተቆጥሮ መደረግ አለበት። ምክንያቱም እዛ ኢንቨስት ካደረግን ችግሩን እዛው ማቃለል እንጀምራለን ማለት ነው›› ይ ላሉ።
እንደ እርሳቸው አባባል፤ እዛው ገጠር አካባቢ ልክ ከተማ ውስጥ ኢንቨስት እንደሚደረግ ተቆጥሮ ኢንቨስት ካልተደረገ ሰው ወደ ከተማ ይፈልስና ኑሮውን በዛ ያደርጋል። ይህ ከሆነ ደግሞ የከተማውን እንጂ የገጠር ስራ አይሰራም። ከተማ ሲመጣ የመኖሪያ ቤት ፈላጊ ይሆናል፤ ገጠር እያለ ግን መኖሪያ ቤት ስለሚኖረው የቤት ሁኔታ ችግር አይሆንበትም።
ስለዚህም‹‹ በገጠር ያለው ችግር የከተማም ችግር ነው›› በሚል ሁለቱም አካባቢ አንድ ላይ በተቀናጀ መንገድ እቅድ ማውጣትና መፍትሄ ለማበጀት መሞከር ሂደቱን የተሻለ ያደርገዋል። ይህ አይነቱ አሰራር ቀደም ሲል ከነበረው የተለየ ነውና ትኩረት ይፈልጋል። ምክንያቱም የገጠሩ ህዝብ የወደፊት የከተማ ህዝብ መሆኑ ከግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል። ኢትዮጵያ ከገጠር ወደ ከተማ በሚደረገው ሽግግር ውስጥ እንደመሆኗ ይህ ጉዞ የሚቆም አይደለም።
‹‹ላለው ፍላጎት አቅርቦትን በመጨመር ፍላጎት ለማርካት ብቻ ከመሞከር ይልቅ ፍላጎቱን ራሱን ማስተዳደር ያስፈልጋል›› የሚባል አባባል መኖሩን የሚጠቅሱት ዶክተር ህያው፤ እንዲህ ሲባል ከገጠሩ ለመምጣት የሚፈልግ ህዝብ አለ፤ ከተማው ደግሞ የመቀበል አቅም የሚባል ነገር አለው። ስለዚህ የመቀበል አቅም ማስፋት አንድ ነገር ሆኖ ፍላጎታቸውን በመረዳት እዛው ባሉበት አካባቢ ማስተዳደር የሚቻል መሆኑን የሚያስረዳ እንደሆነ ያብራራሉ።
በመሆኑም ሁለቱን አንድ ላይ ማየቱ የተሻለ መሆኑን አመልክተው፤ ይህ ካልሆነ ግን የሚመጣን ሁሉ መቀበል ከከተሞች አቅም በላይ ይሆናልና ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ። ባሉበት ቦታ የሚገፏቸውን ምክንያቶች በማስተዋል ያንን ማስተካከል ተመራጭ እንደሆነ ጠቅሰው፤ እዛ ገጠር የሚሰራው ስራ በራሱ ጠቃሚነቱ ለከተማ ጭምር መሆኑም መታወቅ እንዳለበት አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20/2012
አስቴር ኤልያስ