አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ ግርማይ ይባላል:: የኪነ ሕንጻ (አርክቴክት) የስነቁፋሮ (አርኪዮሎጂ) ባለሙያ ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ / ከቀድሞው ሕንጻ ኮሌጅ/የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአርክቴክቸር ፤የማስተርስ ዲግሪያቸውን ደግሞ ስድስት ኪሎ ከሚገኘው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በአርኪዮሎጂ አግኝተዋል፡፡
በስራ አለም ኢቲጂ ዲዛይነር የሚባል የዲዛይን አማካሪ ድርጅት ውስጥ እንዲሁም አሶሽየት ኢንጂነሪንግ ኮንሰልታንት በሚባል አማካሪ ድርጅት ውስጥ በተለያዩ አመታት ሰርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተለምዶ ሕንጻ ኮሌጅ ተብሎ በሚጠራው የኢትዮጵያ የኪነ ሕንጻ ግንባታና የከተማ ዲዛይን ኢንስቲትዩት ከ10 አመት በላይ በመምህርነት በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ዙሪያም ያማክራሉ፡፡ በከተሞች ልማትና በኮንስትራክሽን ስራው መቀዛቀዝ፤ ተጀምረው ስለቆሙ ሕንጻዎች፤ ስለጥንታዊ ከተሞች ቁፋሮና ግኝት /የአርኪዮሎጂ ስራን/ በተመለከተ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ እንዲህ አቅርበነዋል ፦
አዲስ ዘመን፡- በአዲስ አበባና በሌሎችም ከተሞች ግንባታዎች ይካሄዳሉ፡፡ ግንባታዎቹ ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው ወይንስ አይደሉም የሚለው ጉዳይ ላይ ክርክር እየተደረገ ነው ። እርሶ በዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡- ታዳጊ ሀገር እንደመሆናችን መጠን ብዙ አይነት እጥረቶች ይኖራሉ፤ አሉብን፡፡ የሀሳብና የገንዘብ ችግር ብቻ አይደለም፡፡የተማረ የሰው ኃይል እጥረት አለብን:: ከአጠቃላይ ማሕበረሰባችን ስንት ፐርሰንት ነው የተማረው ብለን ስናስብ እሱም ራሱን የቻለ ምላሽ የሚፈልግ ጥያቄ ነው:: አብዛኛው ሰው ባለሙያ የሚባለውን ነገር በትክክል ተረድቶታል ብይ አላስብም፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ እውነታ የዲዛይንም ሆነ የግንባታ ስራዎች ሙሉ በሙሉ በባለሙያዎች እየተሰሩ ነው ማለት አይቻልም ፡፡ ሰዎች ተነስተው እንደፈለጉት ነው የሚሰሩት፡፡
መንግስት ሕግና ተቆጣጣሪ አስቀምጦ ይሰራል፡፡ ሁሉንም ቦታ ሙሉ በሙሉ ሸፍኖ ለመወጣት ይከብደዋል፡፡ ሕግ አውጪው አለ፡፡ ከግንባታና ክትትል አንጻር ሕግ አስፈጻሚው አካል በቂ ኃይል አለው ለማለት ይከብዳል፡፡ ሁላችንም ሕጉን ተከትለን የመስራት ባሕላችን አላደገም ፡፡ ግንባታዎችን ከሕግና ከስርአት ውጪ በዘፈቀደ የሚሰሩት ይበዛሉ፡፡ ሕንጻ ግንባታዎች ላይ ጥንቃቄ ብዙ የለም፡፡ ይሄ ከፍተኛ ችግር ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡-ሕንጻ ግንባታዎች ላይ ምን አይነት ጥንቃቄ መኖር አለበት ይላሉ ?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡- ከሕንጻው ዲዛይን እንነሳ፡፡ ዲዛይኑን በትክክል አንብቦ ተረድቶ መስራት አንድ ነገር ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ባለቤቱ ኃላፊነቱን እንዴት ይወጣል ? እሱ በፈለገው መንገድ ነው የሚሰራው ወይስ ባለሙያው የሚለውን ይቀበላል? የሚሉትን ጥያቄዎች ስናነሳ ምላሾቻቸው ላይ ሰፊ ክፍተቶች አሉ፡፡ የግንባታ ስራውን የሚሰሩ አብዛኛዎቹን ባለሙያዎች፤ የቀን ውሎ ሰራተኞችን ሁኔታ ስናይ የሚከፈላቸው ገንዘብ ትንሽ ከመሆኑም በላይ ለእነሱ የሚሆን የደህንነት መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ስንቱ ኮንትራክተር ያሟላል ስንል የአቅም ውስንነት ስላለ መልሱ አያሟላም ወደሚለው ይሄዳል፡፡ ይሄ ምን ያሳየናል ባለሙያዎች ብቻ እንዲሰሩ የሚል ሕግ ቢኖርም ተፈጻሚነቱ በትክክል ስለሌለ ማንኛውም ሰው እንደፈለገው የመስራት እድል ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለግንባታ ጨረታዎች አነስተኛ ዋጋ ለሚያቀርቡት በር ይከፍታል፡፡
በኮንስትራክሽንም ሆነ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ለስራዎች በሚወጣው ጨረታ ዝቅተኛ ዋጋ ያቀረበ ስራውን መስራት አለበት የሚል ነው ፡፡ ለአንድ ግንባታ የሚያስፈልገውን ወጪ በተመለከተ የግንባታ ወጪ ግምት / Engineering Cost Estimating / የሚባል አለ፡፡ በባለሙያ ተመዝኖ ተለክቶ ግንባታው ይጨርሳል የሚባለውን የገንዘብ መጠን የማስላት ስራ ነው ፡፡
ስሌቱ
ከአምስት እስከ አስር ፐርሰንት ልዩነት ቢኖረው እንጂ ግንባታው ሲሰራ ያን ያህል ገንዘብ ይጨርሳል ተብሎ አይታሰብም ፡፡ አነስተኛ የጨረታ ገንዘብ አቅርበው የሚወዳደሩ ተቋራጮች ለምሳሌ 20 እና 30 ፐርሰንት ከግምቱ ዝቅ አድርገው ካስገቡና ካሸነፉ ያንን ስራ በአግባቡ በጥራትና በብቃት ይሰሩታል ብሎ መገመት በፍጹም አይቻልም፡፡
ትክክለኛ አካሄድም አይደለም፡፡ ከስሮ መስራት እንደማለት ነው፡፡ ለጽድቅ የሚሰራ ሰው የለም፡፡ ከዚህ አንጻር ከግምቱ ከተወሰነ ፐርሰንት በታች ያስገባ ተቋራጭ ያንን ስራ በጥራት እንደማይሰራው በደምብ ይታወቃል፡፡ ከኢንጂነሪንግ ኢስቲሜቱ (ግምት) በላይ ያስገባ ደግሞ ተጨማሪ ሂሳብ ይጠይቃል፡፡ ሆኖም መቶ ፐርሰንት የተሻለ አድርጎ ይሰራዋል ማለት ደግሞ አንችልም፡፡ እንደዛ ከተከፈለው ቢያንስ በተሻለ ጥራት ይሰራዋል ብሎ ተስፋ ማድረግ ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዲዛይን የሚሰሩትና የሚገነቡት ብዙዎቹ ሕንጻዎች የአደጋ ግዜ መከላከያ አላቸው ?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡- ሁሉም ሕንጻዎች ዲዛይን ሲደረጉ በተቀመጠው ሕግ መሰረት ነው የሚሰሩት፡፡ መጀመሪያም ቢሆን በሕጉ መሰረት ካልተሰሩ አይጸድቁም፡፡ ስለዚህ ሁሉም ሕንጻዎች እንደአስፈላጊነቱ ሕጉ በሚያዘው መሰረት የእሳት አደጋ ግዜ መውጫ ከአንድም ሁለት በተቃራኒ ቦታዎች ያስፈልጋቸዋል የሚል ሕግ ካለ እሱ ተሟልቶ ዲዛይኑ ላይ ካልተሰራ አይጸድቅም ማለት ነው፡፡ የእሳት አደጋ መውጫ የማያስፈልጋቸው እንደ መኖሪያ ቤት
አይነት ሕንጻዎች ከሆኑ ደግሞ ባለው ሕግ መሰረት ይሰራል::
ከዲዛይን አንጻር በትክክል ነው የሚሰራው:: ዲዛይን ደግሞ ወረቀት ላይ የሚያርፍ ስለሆነ የተለያዩ ባለሙያዎች ተቀናጅተው ይሰሩታል፡፡ ትልቁ ችግር የሚኖረው አፈጻጸም ላይ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ፡- አፈጻጸም ላይ የሚታዩት ችግሮች ምንድናቸው ?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡- አፈጻጸም ላይ ሁሌም ችግር ይኖራል፡፡ እንደ ታዳጊ ሀገር በመንግስት አቅም በቂ የሆነ የክትትል ባለሙያ አይኖርም፡፡ ለምሳሌ ማዘጋጃ ቤትን ብንወስድ ለክትትል ብቻ 10 ባለሙያ ቢኖር በየክፍለ ከተማዎቹ ደግሞ በዛ ቢባል 10 አለ ብንል በብዜቱ 110 አካባቢ የግንባታ ክትትል ሙያተኛ ብቻ አለ ማለት ነው፡፡ 110 ባለሙያ ይዘህ በቀን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚካሄደውን ስንትና ስንት ሺ የሕንጻ ግንባታዎች በክትትል መሸፈን አይቻልም፡፡
እነዚህ 110 የግንባታ ክትትል ሙያተኞች ይሄንን ትልቅና ሰፊ ከተማ ለመሸፈን ይችላሉ ወይ የሚለውን ማየት ነው፡፡ በምክንያታዊነት ስናስብ ያንን ሁሉ ይቆጣጠራሉ ለማለት ይከብዳል፡፡ ከዚህ አንጻር ትልቁ ክፍተት አፈጻጸም ላይ ያለ ችግር ነው ማለት ነው::
አዲስ ዘመን፡- በተለያዩ ግዜያት የታዩትን የአፈጻጸም ችግሮች ለማረምና ለማስተካከል የተወሰዱ የሚታዩ እርምጃዎች የሉም ?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡- በተለያየ ግዜ የሚመለከታቸው መንግስታዊ አካላት እናስተካክላለን በዚህ መንገድ ይሻሻላል ይላሉ፡፡ ሕጉ ላይ ሁሉም ነገር አለ፡፡ ሕጉ ላይ ስህተት የለም ማለት ይቻላል፡፡ በአንድ መልኩ አፈጻጸሙ ላይ ችግር አለ የምለው የሀገራችን የኢኮኖሚ አቅም ውስን በመሆኑ ነው፡፡
በሌላው መልኩ ደግሞ ችግሩን ለመቅረፍ ወይንም ለመፍታት መንግስት አስፈላጊነቱን በደምብ ተረድቶ ቁርጠኛ የሆነ ውሳኔ የመወሰንና የሚያስፈልጉ ባለሙያዎችን በቦታው ቀጥሮ ያለማሰራት ነገር ይታይበታል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ይሄን ማድረግ ያልተቻለው ለምንድነው ብለው ያስባሉ ?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡- እኔ ግምቴን ነው የምናገረው፡፡ መንግስት እንደ መንግስት በአንድ ሀገር የሚካሄዱ ማናቸውም ነገሮች በአግባቡና በስርአቱ ሕጉን ተከትለው እንዲሰሩ ይፈልጋል፡፡ አይፈልግም አልልም፡፡ ቢፈልግስ የፈለገውን ለማድረግ በቂ የፋይናንስ ጉልበትና አቅም አለው ወይ የሚለው ጥያቄ ወሳኝ ነው ?
በምሳሌነት ይሄንን ጉዳይ ካለን ብዙ የስራ አጥ ቁጥር ጋር ማያያዝ እንችላለን፡፡ ለምንድነው እንደዚህ የሆነው ብለን ስንጠይቅ ይሄን ግዙፍ የስራ አጥ ኃይል ተሸክሞ ሊያሰራ የሚችል የመንግስትም ሆነ የግለሰብ የኢኮኖሚ አቅም ስለሌለ ነው፡፡ አፈጻጸሙ ከእነዚህ ችግሮች የሚወጣ አይሆንም፡፡
ሀገሪቷ አቅም ከሌላት ያላትን የሰው ኃይል በአግባቡ መጠቀም አትችልም፡፡
በሀገራችን በቂ የወጣት ኃይል አለ፡፡ ዝቅተኛ በሆነ ዋጋ ብዙ የሰው ኃይል ማግኘት ይቻላል፡፡ ለዛም ነው ኑና ኢንቨስት አድርጉ ብለን የውጭ ሰዎችን የምንጋብዘው፡፡ ይሄ የሚያሳየው እኛ ያለንን ሰፊ የሰው ጉልበት ማሰራት አልቻልንም ማለት ነው፡፡ የማንችልበት ምክንያት ደግሞ በቂ የኢኮኖሚ አቅም ስለሌለን ነው፡፡
እንደ ታዳጊ ሀገር በጣም ድሀ ከሚባሉት ሀገሮች ተርታ የምንሰለፍ በመሆናችን አቅም ስለሌለን ነው ይሄ ክፍተት ሊፈጠር የሚችለው፡፡ይህም ቢሆን መንግስት ችግሩን ተቋቁሞ በተወሰነ ፐርሰንት ማሻሻል ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- መንግስት ችግሩን ለመፍታት ምን ማድረግ አለበት ይላሉ ?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡- ከግንባታና ክትትሉ አንጻር መንግስት ማድረግ የሚችለው በአለው አቅም የቀጠራቸውን ባለሙያዎች የሚከፍላቸውን ክፍያ ግምት ውስጥ አስገብቶ የተመደበላቸውን በቀን የ8 ሰአት ግዜ በአግባቡ መጠቀማቸውን መቆጣጠር ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ ይሄን ማድረግ ከቻለ ቢያንስ በተወሰነ ፐርሰንት መሻሻል ይታያል ብዬ አስባለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡-አቅም ከሌለ ከአቅም በላይ ማቀዱ፤ ወደ ሕንጻ ግንባታና የመሳሰሉት መግባቱ ምንድነው የሚፈይደው ? ውጤት ያስገኛል ?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ:- ግንባታውን ስንወስድ መንግስት ብቻ አይደለም የሚገነባው፡፡ የሚበዛው የግሉ ሴክተር ነው፡፡ የግሉ ሴክተር የቻለውን ያህል ያለማል፡፡ በአንድ በኩል አቅም የምንለው ይሄ ነው ብለን ስናስብ በሌላ በኩል ደግሞ ለመስራት ያሰባቸውን ነገሮች በጥራት ተከታትሎ ለማስፈጸም እጥረት አለው ማለት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሕንጻ ግንባታ ዲዛይኖች ላይ የባለሀብቶች ፉክክር አለ ይባላል፡፡የተቀመጠውን የከተማ ስታንዳርድ ያለመጠበቅ፤ ሕንጻዎችን በሙሉ መስታወት ማድረግና የመሳሰሉት ውሎ አድሮ ችግር ይፈጥራል የሚሉ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ይሄንስ እንዴት ያዩታል ?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡- ይሄ መሰረታዊና ትልቅ እውነት ነው፡፡ ሕንጻና ፎቆችን በመስተዋት መስራቱ ችግር አለው፡፡ ኢትዮጵያ በትሮፒካል የአየር ንብረት ወስጥ የምትገኝ ሀገር ነች ። በዚህ የአየር ንብረት አካባቢ ሕንጻዎችን በመስተዋት መስራት አይመከርም ፡፡ ሕንጻና ፎቆቻቸው ላይ መስታወት የሚጠቀሙት ቀዝቃዛ የአየር ንብረት ወስጥ ያሉ ወደ ሰሜን አውሮፓ አካባቢ የሚገኙ የስካንዲኔቪያን ሀገሮች ናቸው ።
አብዛኛው ወራቸው ጨለማ ነው፡፡የጸሀይ እጥረት አለባቸው፡፡ በእንደዛ አይነት ቦታ ያሉ ሀገሮች መስታወት በሕንጻዎቻቸው ላይ በማድረግ በጨለማው ግዜ ብርሀን ያገኛሉ፡፡ ሞቃትና መካከለኛ ቦታ ያሉ ሀገሮች ደግሞ በሕንጻዎቻቸው ላይ መስታወት
አስገቡ ማለት ሙቀት በብዛት ተጨማሪ ሙቀት ፈጠሩ ማለት ነው፡፡ አስፈላጊ አይደለም፡፡
በህንጻና ፎቆቹ ላይ መስኮቶች አነስ ብለው በቂ በሆነ ሁኔታ ለንፋስ (አየር ለማስገባት) ቢሰሩ ብርሀን ለማስገባት በቂ ናቸው:: ሕንጻዎችና እና ፎቆችን በአብዛኛው በመስታወት መሸፈናቸውን በተመለከተ ምክንያቱ ምንድነው ካልን አብዛኛው ባለሀብት ከቅርብ ግዜ ወዲህ ቻይና ዱባይ ሌላም ሌላም ብዙ ሀገራት ይሄዳል፡፡
በነዚህ አካባቢ ያሉ ሀገራት የተሰሩ ሕንጻዎችንና ዲዛይኖችን ያያል፡፡ እነዛ ህንጻዎች ለየት ያለ መስታወት ነው የሚጠቀሙት፡፡ በጣም ውድ ናቸው፡፡ ሙቀት አያስገቡም፡፡ ብርሀን ብቻ ያስገባሉ፡፡ ከባቢ አየሩ ወይ ሞቃት ወይ ቀዝቃዛ ስለሚሆን በአብዛኛው ያንን ለመቋቋም ኤሲ (Air Conditioner) ይኖራቸዋል፡፡ የተለያየ ምቾትን ማምጫ መንገድ ተጠቅመው ይሰራሉ:: ሀብትም አቅምም ስላላቸው ማለት ነው፡፡ እኛ ሀገር ደግሞ ውጭ ያዩትን ሀሳብ በጥሬው ያመጡና ሲሰሩ የሚጠቀሙት ቁሳቁስ ደረጃውን የጠበቀ አይደለም፡፡ ችግሩ ይሄ ነው፡፡
በእኛ ሀገር በተገነቡት ሕንጻዎች ላይ በስፋት የተገጠሙትን መስታወቶች ስናይ በአጋጣሚ እሳት ቢነሳ ደረጃቸውን የጠበቁ ካለመሆናቸው የተነሳ የሚቀልጡበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል ማለት ነው፡፡ ችግሩ ያልተከሰተው መጥፎ ነገር አጋጥሞን ስለማያውቅ ብቻ ነው፡፡ ችግር ሳያጋጥመን ሲቀር መፍትሄ ማዘጋጀት ላይ እንድንሰንፍ ያደርገናል ማለት ነው፡፡ ብዙ ሀገሮች ችግር ሲያጋጥማቸው ነው መፍትሄ የፈጠሩት፡፡
በረዶ ሲሆን ለበረዶ ፤ሙቀት ሲሆን ለሙቀት የሚሆን መፍትሄ ይኖራል፡፡ የእኛ የአየር ንብረት ከሞላ ጎደል ጥሩ የሚባል ስለሆነ ሰነፍ እንድንሆን መፍትሄ እንዳናስብ አድርጎናል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ሰአት ከተከሰተው የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ጋር በተያያዘ የግንባታና ኮንስትራክሽን ስራዎች ተቀዛቅዘዋል:: የኢኮኖሚው መዳከም አለ፡፡ ችግሩ በኛ ሀገር እንዴት ይገለጻል ?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡- ኮሮና ቫይረስ በአለም ላይ ትልቅ ጫና አሳድሮአል፡፡ እንደ
ኢትዮጵያ ያሉ ሀገሮች ደግሞ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ከውጭ ስለሚያስገቡ ችግርን የከፋ ያደርገዋል፡፡ ምርቶችን ከውጭ ሀገራት በማስገባት ላይ የተመረኮዘ ኢኮኖሚ ነው ያለን፡፡ የአሁኑ አይነት አለም አቀፍ ወረርሽኝ ሲከሰት የምንፈልጋቸውን ነገሮች ከውጭ ሀገራት በቀላሉ ማግኘት የማንችልባቸው ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፡፡
ማንኛውም እንቅስቃሴ የተወሰነ ነው:: በአብዛኛው ተዘግቶአል ማለት ነው፡፡ እንቅስቃሴና ዝውውር ከተዘጋ ምንም አይነት ስራ መስራት አይቻልም፡፡ እንደዚህ ሲሆን ምንም የማያመርቱና ውጭ ሀገራት ካመረቱት የሚያስገቡ ሀገሮች ይቅርና ዋናዎቹ አምራች ሀገራትም የራሳቸውን ምርት በደምብ መቀጠል አይችሉም፡፡ ለራሳቸው ካልቻሉ ለሌላው የሚልኩት ነገር አይኖርም:: ጫናው እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአብዛኛው የግንባታ ስራዎች ቆመዋል፡፡ በቅርቡ ስራቸው ከቆመው ውጭ ቀደም ብለው መሀል አዲስ አበባ ላይ ተጀምረው የቆሙ ግንባታዎችም አሉ፡፡ የእርስዎ እይታ ምንድነው ?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡- በተለያየ ምክንያት የቆሙ የሕንጻ ግንባታዎች አሉ፡፡ የቆሙበት ጉዳይ መቋጫ ሲያገኝ ነው መፍትሄ የሚገኘው:: አቅም አንሶአቸው የቆሙት አቅም ሲያገኙ ነው የሚቀጥሉት:: አቅም ሲያገኙ ግንባታቸውን ይቀጥላሉ ብለን መደምደም የማንችልባቸው ምክንያቶችም አሉ::
ለምሳሌ በሊዝ የተወሰዱ መሬቶች ከሆኑ የሊዝ ግዜ ይቃጠላል፡፡ አሳማኝ ምክንያት ሲቀርብ ኢኮኖሚውን የሚያግዙ ነገሮች ናቸው ብሎ መንግስት ስለሚያምን ሙሉ በሙሉ አይዘጋቸውም፡፡ ሊያድሰው ይችላል፡፡ ባለሀብቱ ደግሞ በተሰጠው እድል መጠቀም ካልቻለ ሕጉ ያመክነዋል ወይ ደግሞ የሊዙ ውል ይቋረጣል ነው የሚለው፡፡
አዲስ ዘመን፡-የተሰራው ግንባታ በቦታው ላይ የፈሰሰው ሀብትስ ምን ይሆናል ?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡- እነዚህን ነገሮች በዝርዝር የሕግ ባለሙያዎች ሊያውቁት ይችላሉ:: ቦታው ላይ የፈሰሱት ንብረቶች በግለሰቡ ወይም በድርጅቱ ስም ይሁኑ እንጂ በተዘዋዋሪ የሀገር ሀብቶችና ንብረቶች ናቸው፡፡ መንግስት በማንኛውም መንገድተነሳሽነቱ እንዲኖር አድርጎ ስራውን እንዲጨርስና ወደ አገልግሎት እንዲገባ የማድረግ ፍላጎት አለው ብዬ ነው የማስበው፡፡
ይህንን ማድረግ ሳይቻል ሲቀር በተለያየ መንገድ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠና ጫና እየተደረገ ግለሰቡ በተለያየ መንገድ ከባንክ ብድርም በመውሰድ ሊሆን ይችላል የሚጨርስበት ሁኔታ ሊመቻች ይችላል:: ባንኮች ከወቅታዊ ችግሩ አኳያ ታይቶ የወለድ የእፎይታ ግዜ እንዲሰጡ እንዲቀንሱ የሚለውን ነገር መንግስት እያዘጋጀና እየተናገረ ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ሊያነቃቁት ይችላሉ የሚል እሳቤ አለኝ፡፡
አንድ ሕንጻ በዲዛይኑ መሰረት ተሰርቶ ሲጠናቀቅ ለመጠቀም ዝግጁና ብቁ ነው የሚል የመጠቀሚያ ፈቃድ ከድሮ ጀምሮ በሀገራችን አለ፡፡ ፈቃዱ ሳይሰጥ ስራ መጀመር አይችልም፡፡ የመጠቀሚያ ፈቃድ ሲባል በመጀመሪያ ደረጃ የሚሰራውን ሕንጻ ዲዛይን መንግስት አይቶት አውቆት ነው የሚጸድቀው፡፡
ግንባታው ተሰርቶ መጨረሻ ካለቀ በኋላ ተጠቃሚው ሰው ምቾቱ ወይንም ደህንነቱ መታወቅ ስላለበት ታይቶ ሕንጻው ሁሉንም ነገር አሟልቷል ለአገልግሎት ክፍት ይሁን የሚለው ከድሮ ጀምሮ የነበረ ሕግ ነው፡፡ ቀደም ሲል እንዳነሳነው ሁልግዜም ችግር የሚኖረው አፈጻጸም ላይ ነው፡፡ በአቅም ማነስ ወይንም የሕግ አለመጥበቅ እነዚህ ነገሮች እየያዙት ሊጓተት ይችላል እንጂ ሕጉ ድሮም ነበረ፡፡ አሁንም አለ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ወደሌላው ሙያዎት አርኪዮሎጂስትነቱ እንሂድ፡፡ ሀገራችን ብዙ ጥንታዊ ከተሞች ነበሯት፡፡ በተለያየ ምክንያት በመሬት መንቀጥቀጥ፤ በናዳ፤ በእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ወዘተ የጠፉ ጥንታዊ ከተሞች እንደነበሩ ይነገራል፡፡ በዚህ በኩል ምን እየተሰራ ነው ?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ – ከአርኪዮሎጂ (ስነ ቁፋሮ) ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ በመጀመሪያ የ13 ወር ጸጋ ነበር የምትባለው፡፡ የብዙ ነገሮች መነሻና መጀመሪያ ስለሆነች ነው፡፡ በዚህም በቱሪዝም የሁሉም ነገር መነሻ (ዘ ላንድ ኦፍ ኦሪጅን ) ተብላለች፡፡ ይሄ እንዲሆን ያደረገው በአርኪዮሎጂና ፓሊዮንቶሎጂ ከሰው ዘር ጋር የተያያዙ ነገሮችና የሰው ልጅ በሺዎች አመታት ሲኖር ይጠቀምባቸው የነበሩትን መሳሪያዎችን ለማየት ምርምርና ጥናቶች እየሰፉ በመሄዳቸው ነው፡፡
ከነዚህ ጥናቶች በመነሳት የተለያዩ ነገሮች ሲመጡ እነዛ ግኝቶች የገነኑ ሆነው ሲገኙ በአለማችን በተነባቢነቱ ቁጥር አንድ በሆነው “ኔቸር መጽሄት” /Nature Maga¬zine/ ላይ ታትመው ይወጣሉ፡፡ አንድ ግኝት በዚህ መጽሄት የፊት ገጽ ላይ ወጣ ማለት በአለም አቀፍ ደረጃ በጣም ጠቃሚ ግኝት ነው ማለት ነው::
ብዙ ኢትዮጵያውያን ሳይንቲስቶች ከሌሎች አለም አቀፍ ተመራማሪዎች ጋር በመሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ አዳዲስ ግኝቶችን አግኝተዋል፡፡ ለምሳሌ ከ1974 ዓ/ም ጀምረን ስንነሳ አፋር ሉሲ የምትባለው ቅሪተ አካል ከዛም በኋላ ሰላም ተገኝታለች፡፡ ሌሎች ሳይንሳዊ ስማቸው ሰፋ ያለ ብዙ ቅርሶች፤የሰው ቅሪቶች፤ የሰው ልጅ ሲጠቀምባቸው የነበሩ የተለያዩ ቁሳቁሶች፤ እስከ 3000 አመትና እዛው አካባቢ እድሜ ያላቸው ጥንታዊ ከተሞችና ሕንጻዎች ተገኝተዋል፡፡ ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ እየተሰሩም ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- አንዱ ጠፍቶ የነበረና ተቆፍሮ የተገኘው ጥንታዊ ከተማ ትግራይ ውስጥ ነው፡፡ ከዛ ውጭ የተገኙ አሉ ?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡- ከጥንታዊ ከተሞች ጋር የተያያዙት የተገኙት ብዙዎቹ ትግራይ ውስጥ ናቸው፡፡ ከሰው ዘር ጋር ተያይዞ ደግሞ አፋር አካባቢ ነው፡፡
እንደገና የሰው ልጅ የተጠቀማቸውን የጥበብ ውጤቶች በተመለከተ ድሬዳዋ አካባቢ እንደ ለጋ ኦዳ አካባቢ ያሉ አሉ፡፡ ትግራይ ጉሎ መከዳ የሚባለው አካባቢ ወደዛላአምበሳ ስትሄድ እዛም አለ፡፡ ሀረርንም ስትወስድ 1000 ዘመን እድሜ ያስቆጠሩ ቅርሶች አሉ፡፡ በአጠቃላይ ብዙ ናቸው፡፡ አርኪዮሎጂካል የሆነ ነገርም አላቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ጥንታዊ ከተማ ተፈልጎ ተገኘ ሲባል ለጥናቱ መነሻው ምንድነው ?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡- ለጥናቶቹ መነሻ ብዙ አይነት ነገሮች ይኖራሉ፡፡ አንደኛው በአካባቢ ሰዎች ከረዥም ግዜ ጀምሮ በአፈ ታሪክ በስነ ቃል ሲነገሩ የኖሩ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ የተወሰኑ መነሻ ምልክቶች ይታያሉ፡፡ ማንም ሰው ሊያያቸው ይችላል:: በዚህ መነሻነት ሳይንሳዊ ምርምሮችን የሚሰሩ አካላት ይኖራሉ፡፡ በእኛ ሀገር እንደዚህ አይነት አርኪዮሎጂያዊ ጥናት ለማድረግ የምርምር ቡድኑን የሚመራው ሰው የፒኤችዲ ዲግሪ (ዶክትሬት) ሊኖረው ይገባል፡፡
በቡድኑ ውስጥ አርኪዮሎጂስት፤ ፓሎንቶ ሎጂስት፤ጂኦሎጂስት፤ አርክቴክት፤ ኢንጂነር ሌሎችም ሙያተኞች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ከተለያዩ የሙያ መስኮች ብዙ ሰዎች ተቀናጅተው ነው ምርምሩ የሚሰራው:: ምን ጥቅም አለው ካልን አርኪዮሎጂስቱ የሆነ ነገር ፍንጭ ሲያገኝ ያንን አካባቢ ይወስድና የቁፋሮ ናሙናዎች ያዘጋጃል፡፡
በዛ መሰረት የተወሰነችውን ቦታ በጥንቃቄ ይቃኛል፡፡ መጀመሪያ በአይን ይቃኛል፡፡የተጻፉ ነገሮችን ይፈላለጋሉ፡፡ በቃል የሚነገሩ ባህሎችን ይደመጣሉ:: ቀጥሎ የሙከራ ቁፋሮ ያደርጋል ማለት ነው፡፡ ትንሽ ሲቆፍር የሚያገኛቸውን ነገሮች በሙሉ ይዘቱ እንዳይታወክ በጥንቃቄ በመያዝ ነባራዊ ሁኔታው እንዳይቃወስ አድርጎ ሳይነካካ የሚወስዳቸው ፎቶዎች፤ የጂፒኤስ ንባቦች ፤ ልኬቶች ይኖራሉ፡፡
የተለያዩ ባለሙያዎች እንደ ጂኦሎጂስት ያሉት ደግሞ በመሬት ስራ ውስጥ ያሉ አፈር ደረጃዎች / stratum/ አሉ ፡፡ መሬቱ ወደ ውስጥ ሲቆፈር የሚኖረው የተለያየ የአፈሩ ደረጃዎች የተደመደመበት ከእድሜ ብዛት የተለያየ መስመር ይኖረዋል፡፡ የተለያየ ሚሊዮን አመት እድሜ ያለው የአፈር ክፍል ይኖራል ማለት ነው፡፡ እነሱን በማየት መተርጎም ስራዎች ይከናወናሉ:: በዚህም የተለያዩ ባለሙያዎች ይሳተፋሉ፡፡
በጥንታዊ ከተሞች ጥናት ምርምር ፍለጋና ክትትል ዙሪያ አንድ አርክቴክት ሲሳተፍ የሚያገኛቸው የተለያዩ ፍንጭዎች አሉ፡፡ እሳት፤ የተቃጠለ ነገር ወይንም አመድ ካየ ያ አካባቢ ምናልባት በአብዛኛው ከማብሰል ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ይወስዳል:: ያንን ደግሞ የሚያረጋግጠው ከዚሁ ጋር የሚያያዙ ቀጣይ ፍለጋዎችን በመስራት ነው፡፡ ቁፋሮውን ሲቀጥል ተያይዘው ያሉት ነገሮች ምን ሊሆኑ ይችላሉ የሚለው ይከተላል፡፡ ለምሳሌ አጠገቡ መኝታ ቤት ካለ መታጠቢያ ቤትም ሊኖር ይችላል ብሎ መገመት ፤እንደ ሳሎን ነገር አጠገቡ ካለ ማብሰያ ሊኖር ይችላል እያለ ይቀጥላል፡፡
ደረጃዎች ካሉ መግቢያ ሊሆን እንደሚችል፤ የፍሳሽ መስመር ካለ ከፍሳሽ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ሊገምት ይችላል፡፡ እነዚህን ሁሉ ያሰባስብና አንድ ሊጨበጥ የሚችል ሀሳቡ ላይ ይደርሳል ፡፡ ከዛ የህንጻው መሰረት፤ ግድግዳ፤ መሬት፤ ወለል፤ ጣራ፤ ክፍተቶች፤ መስኮቶች የምንላቸው የተለያዩ ነገሮችና ልኬታቸው ከሰው ልጅ ምጣኔ ፤ ከቁመት ከስፋት አንጻር ምን ምን ሊያክሉ ይችላሉ የሚለው ደረጃ (ስታንዳርድ) ይሰራሉ፡፡ ጥናቶቹና ምርምሮቹ ተያይዘው አንድ ሊጨበጡ የሚችል ሀሳቦችን ሊሰጡ ይችላሉ፡፡
እነዚህ ከላይ የገለጽኩልህ በሙሉ ተቀናብረው አንድ ስእል ይሰራሉ፡፡ በስትራክቸራል መሀንዲስነት ያለው ባለሙያ ደግሞ ጣሪያው የተደመደመ ወይንስ ጠፍጣፋ ነው ? ወይንስ እንደ ጎጆ ቅርጽ ያለው ነው? ወይንስ እንደ አሞራ ክንፍ ያለ ነው ? የሚለውን ያጠናል፡፡ ከኢንጂነሪንግ አንጻር መሸከም ይችላል ወይንስ አይችልም ? የት ጠፋ? እንዴት ሊጠፋ ቻለ? ወዘተ የሚሉትን ሀሳቦች ሲያቀርብ የእነዚህ ድምር ውጤትና እያንዳንዱ ባለሙያ የሚሰጠው አስተያየት ጥናቱና ግኝቱ ሙሉ ሀሳብ / ሙሉ አረፍተ ነገር / እንዲሆን ይረዳል ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ጥንት የነበሩና የጠፉ ብዙ ከተሞች እንደነበሩን ይታመናል፡፡ የጥናትና ፍለጋ ስራውን ለመስራት በሀገር ደረጃ ያለን የአርኪዮሎጂስቶች አቅም ምን ያህል ነው ?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡- እኔ በተማርኩበት ግዜ በአርኪዮሎጂ የሙያ መስክ ትምህርቱ የሚሰጠው በማስትሬት ዲግሪ ደረጃ ብቻ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነበር፡፡ አሁን ሁለተኛው፤ ሶስተኛው፤ አራተኛው ትውልድ የሚባሉት ዩኒቨርስቲዎች ከመጡ ወዲህ በእያንዳንዱ ወይንም በአብዛኛው ዩኒቨርስቲ ማለት ይቻላል የአርኪዮሎጂ ትምህርት መስክ እየተስፋፋ ነው፡፡ በተለይም ለአርኪዮሎጂ ዲሲፕሊን ወይንም ትምህርት ስልጠና ምቹ የሚባሉ እንደ አክሱም ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች ጥሩ የሆነ ባለሙያም እያፈሩ አዳዲስ ግኝቶችንም እያገኙ ነው፡፡ብዙዎቹ አክሱም ዩኒቨርስቲ የነበሩ አስተማሪዎችና ተመራማሪዎች ወደ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ የገቡ አሉ፡፡ እነሱም የተለያዩ ግኝቶችን እያገኙ ነው:: መንግስት ባደረገው ረዥም ጥረት ማለት ይቻላል ሙያው እየተስፋፋ በመምጣት ላይ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን፤—- ስለሰጡን ቃለ ምልልስ እናመሰግናለን፡፡
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ ግርማይ:-እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20/2012
ወንድወሰን መኮንን