የሀገር ልጅ ውጤቱ የብረት ማቅለጫ ማሽን

መንግሥት ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በሀገር ውስጥ ምርቶች አስፈላጊነት ላይ በትኩረት እየሠራ ይገኛል:: በተለይ ‹‹በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ›› ከውጪ የሚመጡ ምርቶችን የሚተኩ ምርቶች (ተኪ ምርቶች) እንዲመረቱ ለማድረግ ለሚያስችል ተግባር ትኩረት መሰጠቱ አምራች ኢንዱስትሪውም እንዲነቃቃ እያደረገው ነው:: በሀገር ውስጥ ከሚመረቱ ምግብና አልባሳት ባለፈ ማሽነሪዎችን በሀገር ውስጥ ማምረት እየተቻለ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃም አመላክቷል:: ባለፉት ሶስት ዓመታት ለተኪ ምርት በተሰጠው ትኩረት ተኪ ምርቶችን የማምረቱ ሥራ ተጠናክሯል:: በ2017 በጀት ዓመት ብቻ ከሶስት ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ተኪ ምርቶችን ማምረታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ጠቁሟል::

እነዚህ ማሽነሪዎች በሀገር ውስጥ መመረታቸው ሀገሪቱ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ የምታስገባቸውን ማሽነሪዎች መተካት እያስቻላት ይገኛል:: ተኪ ማሽነሪዎችን በሀገር ውስጥ የሚያምርቱ በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎችና ግለሰቦች እየተፈጠሩ ስለመሆናቸውም መረጃዎች ይጠቁማሉ::

ማሽነሪዎች የህብረተሰቡን ችግር እንዲፈቱ ታስበው የሚሠሩ ከመሆናቸው ባሻገር ሀገሪቱ ቴክኖሎጂዎችን ከውጭ ለማምጣት የሚያስፈልጋትን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማዳን እያስቻለም ይገኛል::

በእነዚህ ማሽነሪዎች በመሠራት ተጠቃሽ ከሆኑት መካከል ኢንተርፕራይዞች ማንሳት ይቻላል:: ኢንተርፕራይዞች በተለይ የህብረተሰቡን ችግር ላይ መሠረት አድርገው መፍትሔ መስጠት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን በመሥራትም ሆነ በሌሎች የተሠሩትን በማባዛት ለብህረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ ያደርጋሉ::

ኢንተርፕራይዞች የሚሠሯቸውና የሚያባዙቸው ቴክኖሎጂዎች የህብረተሰቡን ችግር መቅረፍ የሚችሉ መሆን አለባቸው:: ችግርን ለመፍታት በሚል የሚያፈልቋቸው የፈጠራ ሥራዎች በከፍተኛ ወጪ ከውጭ የሚገቡትን ማሸነሪዎች በሀገር ውስጥ መተካት የሚያስችሉ ናቸው::

እነዚህ ማሽነሪዎች በውድ ዋጋ ከውጭ የሚመጡ ሲሆኑ፣ አብዛኛዎቹ ሀገር ውስጥ ሊሠሩ የማይደፈሩ የሚመስሉ አይነትም ናቸው:: እነዚህን ደፍሮ በመሥራት ከሚታወቁ ጥቂት ኢንተርፕራይዞች መካከል ገረመው አሕመድ አልሙኒየም ማቅለጫና የብረታብረት ሥራ ኢንተርፕራይዝ ይጠቀሳል::

ኢንተርፕራይዙ የተመሠረተው በ2007 ዓ.ም ነው:: ‹‹ገረመው አሕመድ አልሙኒየም ማቅለጫና የብረታብረት ሥራ ኢንተርፕራይዝ›› የተሰኘው ይህ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ተሰማርቶ የሚሠራ ኢንተርፕራይዝ፣ የብረታ ብረት ተረፈ ምርቶችን (ቁርጥራጭ አልሙኒየም፣ ነሀስና ካስታየረን የመሳሰሉት) መልሰው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ያደርጋል:: አገልግሎት የጨረሱትን ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች በማቅለጥም ከውጭ የሚገቡ የመኪና መለዋወጫ እና ሞልዶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ለመተካት ይሠራል:: እነዚህን ግብዓቶች ተጠቅሞ የማሽን መለዋወጫና የመኪና እቃዎችንም ያመርታል::

የኢንተርፕራይዙ ባለቤትና መስራች አቶ ገረመው አሕመድ እንዳሉት፤ ኢንተርፕራይዙ የሚያስፈልጉትን ማሽነሪዎች አሟልቶ ሥራውን ጀምሯል:: የማሽን መለዋወጫና የመኪና እቃዎችን በተሻለ ጥራት እያመረተ ለተጠቃሚ ያቀርባል፤ በዚህም ከውጭ የሚመጡትን ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርት እየተካ ይገኛል::

ለሥራቸው አስፈላጊ የሆነውን ብረት ማቅለጫ ማሽን በሀገር ውስጥ ቢፈልጉ ማግኘት ያልቻሉት አቶ ገረመው፣ ይህም ሥራውን በሚፈልጉት ልክ እንዳይፈጽሙ እንቅፋት ሆኖባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ::

ኢንተርፕራይዙ በተለይ የብረት ማቅለጫ ማሽን ለሥራዎቹ በጣም ያስፈልገው እንደነበር ጠቅሰው፣ ማሽኑን ለመግዛት ገበያዎች ቢያስሱም ዋጋው እጅግ ውድ በመሆኑ መግዛት ሳይችሉ መቆየታቸውን ተናግረዋል:: ለዚህ መፍትሔ ለማፈላለግ በማሰብ ከውጭ የሚመጣውን ማሽን ምንነት በደንብ እንዲጠና መደረጉን አስታውቀዋል::

አቶ ገረመው እንዳሉት፤ እሳቸው ለችግሩ መፍትሔ ለመፈለግ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ቀን ከሌሊት ጥረት አድርገዋል:: ከውጭ የሚገባውን ማሽን እንዴት በሀገር ውስጥ ካለ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ባገናዘበ መልኩ የራሳቸውን ፈጠራ በመጠቀም መተካት እንደሚችሉ ለመረዳት ሲሉ ብዙ አውጥተዋል፤ አውርደዋል:: ማሽኑን ለራሳቸው በሚሆን መልኩ ለመሥራት በማሰብም ጥናት አድርገዋል፤ በዚህም ብዙ መረጃዎችን ተመልክተዋል:: ሃሳባቸው ተሳክቶም ብረት ማቅለጫ ማሽኑን ሠርተዋል::

ኢንተርፕራይዙ በ2016 ዓ.ም በሀገሪቱ ምናልባትም የመጀመሪያ የሆነውን 500 ኪሎ ግራም ብረት ማቅለጥ የሚችል የብረት ማቅለጫ ማሽን የፈጠራ ሥራ አውጥተውና ፈጠራውንም አልምተው አገልግሎት ላይ እንዲውል አድርገዋል:: ማሽኑም ለመንገድ ልማት የሚሆኑ ዲሽከበሮችን፣ ከውጭ የሚመጡ በካስተየረን የሚሠሩ ከባድ ብረቶችን ያቀልጣል::

የብረት ማቅለጫው ከባድ የሚባሉ ብረቶችን እንደሚያቀልጥ ጠቅሰው፣ ከ1700 እስከ 2000 ዲግሪ ሴንቲግሬድ አካባቢ በሚደርስ ሃይል ነው ብረቱን የሚያቀልጠው:: አቶ ገረመው ይህ የፈጠራ ሥራ ሦስት ዓመታት ወስዶባቸዋል::

ከውጭ የሚገባው ለእዚህ አገልግሎት የሚውል ማሽን ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የሚገዛ ነው:: እሳቸው በሀገር ውስጥ የሠሩት ማሽን ግን ሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ዋጋ እንዳለው አስታውቀዋል::

የብረት ማቅለጫውን ለመሥራት ረጅም ጊዜ ከመወሰዱም ባሻገር ከፍተኛ ገንዘብ መጠየቁን የተናገሩት አቶ ገረመው፣ በወቅቱ ማሽኑን በመሥራት ሂደት ተስፋ አስቆራጭ ተግዳሮቶች ገጥመዋቸው እንደነበርም አስታውሰዋል::

የማሽኑን የብረት አወቃቀር (ሜታል ስትራክቸር) በአንድ ዓመት ውስጥ እንዳለቀ ተናግረው፣ ብረት ማቅለጥ የሚያስችለውን ሳይንስ ማግኘቱ በጣም ፈታኝ ሆኖባቸው እንደነበርም አጫውተውናል:: ለሦስት ዓመታት ባደረጉት ሙከራና ጥረት የብረት ማቅለጫ ማሽኑን መሥራት መቻላቸውን አስታውቀዋል::

‹‹ማሽኑን ሠርተን ከጨረስን በኋላ ሁለት ሦስት ጊዜ ያህል ሙከራ አድርገን ብረቱን አላቀልጥ ብሎን ነበር፤ በዚህ ጉዳይ ላይም ብዙ የውጭ ሀገር ዜጎችን አማክረናል፤ መጥተውም አይተውታል›› የሚሉት አቶ ገረመው፤ ይህንን አይነት ማሽን በእኛ አቅም መሥራት መጀመሩ ብቻ ሳይሆን መታሰቡ በራሱ አናዷቸዋል›› ሲሉ አብራርተዋል፤ ‹‹ይህን ማሽን በሀገር ውስጥ በፍጹም መሥራት አይቻልም፤ ከሌላ ቦታ ነው የመጣችሁት እስከ ማለት ደርሰውም ነበር ብለዋል::

‹‹የውጭ ዜጎች ሳይንሱንም በቀላሉ ስለሚረዱና ልምዱ ስላላቸው እኛን እምቢ ያለንን ሥራ እነርሱ በቀላሉ ሊሠሩት ይችላሉ በሚል እምነት ነበረን›› የሚሉት አቶ ገረመው፤ ነገሩ ግን የተገላቢጦሽ ሆኖ እንዳገኙት ነው የተናገሩት::

‹‹ማሽኑን እኛ መሥራታችን መገረምና መደንቅ ፈጥሮባቸዋል፤ የውጭ ዜጎቹ እውቀታቸውን ማጋራት እንደማይፈልጉ ተረድተናል›› ሲሉ ጠቅሰው፣ ‹‹የእነርሱ ሁኔታ ይበልጥ ገፍቼ ሥራውን እንዳልቀጥል ተስፋ እንድቆርጥ የሚያደርግ ቢሆንም በድጋሚ ተስፋ ሰንቄ ከብዙ ጥረትና ትግል በኋላ ለማቅለጥ ያደረጉት ሙከራ ተሳክቶልኝ ማሽኑ ብረት እንዲያቀልጥ ማድረግ ችያለሁ›› ሲሉ አብራርተዋል::

ማሽኑ አሁን የብረት ማቅለጥ አገልግሎት ለሚፈልጉ ሁሉ አገልግሎት እየሰጠ ነው:: አቶ ገረመው ማሽኑን ሠርተው ካጠናቀቁ በኋላ ሲያስቸግሯቸው ለነበሩ ሰዎች አሳይተዋል:: አሁንም ማሽኑን እይተው ከህንድ ወይም ከሌላ ሀገር አስመጥታቸሁ ይሆናል እንጂ ሀገር ውስጥ አልተሠራም በማለት እንደተከራከሯቸውም ገልጸዋል::

አቶ ገረመው እንዳብራሩት፤ ማሽኑ የተሠራው ከወዳደቁና ፋብሪካዎች ከጣሏቸው የብረታ ብረት ተረፈ ምርቶች ነው:: እንደ ላሜራ፣ ዲኖሞ ፣ ጌር ቦክስ፣ የመሳሰሉትንም እንዲሁ በፋብሪካዎች የሚወገዱ ብረቶችን በመጠቀምም ነው የተሠሩት:: እነዚህን ብረቶች በመሰብሰብ መቅለጥ የሚችሉትን በማቅለጥ፣ መቅለጥ የማይችሉትን ደግሞ በመሰብሰብ ለሚፈልጉ አካላት እንዲሸጡ ይደረጋል::

የብረቶቹ ዋጋም ቢሆን ከአዲሱ ሃምሳ በመቶ ያህል ለውጥ አለው ሲሉ ጠቅሰው፣ እነዚህን የሚወገዱ የብረት ቁርጥራጮች መልሰን ጥቅም ላይ ማዋል መቻላችን በራሱ ትልቅ ሥራ ነው ሲሉ ገልጸዋል:: ማሽኑን ለመሥራት በጣም ትልልቅና ወፋፍራም ብረቶች ጥቅም ላይ ማዋላቸውን አመልክተው፣ ወጪውም ቢሆን ቀላል እንደማይባል ተናግረዋል::

አቶ ገረመው እንዳስታወቁት፤ ማሽኑ በሁለት ሠዓት ከአስራ አምስት ደቂቃ 500 ኪሎ ግራም ብረት ማቅለጥ ይችላል:: ከውጭ የሚገባው ማሽን ሊያቀልጥ የሚችለውን የብረት መጠን ማቅለጥ የሚችል ከመሆኑም በላይ በሁሉም መልኩ በሚባል ደረጃ በጣም እንዲሻሻል ተደርጎ የተሠራው ነው::

አዲሱን ማሽን ከውጭ ከሚገባው በብዙ መልኩ አሻሽለነዋል ሲሉ አብራርተው፣ ለአብነት ከፓኪስታን የሚመጣው የብረት ማቅለጫ ማሽን 500 ኪሎ ግራም ብረት ለማቅለጥ በትንሹ ከሁለት ሰዓት ተኩል በላይ እንደሚፈጅበት ጠቁመዋል::

እንደ አሳቸው ገለጻ፤ ይህ ማሽን ግን ቢያንስ የግማሽ ሰዓት ያህል ጊዜን በመቀነስ በፍጥነት ብረት በማቅለጥ የፓኪስታኑ ብረትን ለማቅለጥ የሚወስደውን ጊዜ አሻሽሎታል፣ ስለዚህ ከውጭ የሚመጣውን ማሽን በሀገር ውስጥ በመተካት የሚወጣው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪም ማስቀረት ችሏል:: ‹‹ማሽኑን በመሥራታችን በሀገር ውስጥ ተኪ ማሽን ከመሥራት በዘለለ ሀገራችን ተጠቃሚ እንድትሆን በማድረጋችን ደስተኞች ነን ›› ብለዋል::

‹‹ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም የያሁትንና ያነበበኩትን ወደ ወርክሾፕ በመውሰድ ወደ ተግባር መቀየር መቻሌ ማሽኑን እንዲሠራ አድርጎኛል›› የሚሉት አቶ ገረመው፣ ማሽኑን ለመሥራት በኢንተርፕራይዙ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች በሙሉ እንደየሙያቸው መሳተፋቸውንና በትብብር የተሠራ መሆኑን ገልጸዋል:: ቴክኖሎጂው የሚፈልገውን አይነት ሥራ ለመሥራት የሚያስፈልጋቸውን መረጃ በቀላሉ ማግኘት እድሉ እንዳመቻቸላቸው ጠይቀዋል::

እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ የማሽኑ ምርቶች ከህንድ፣ ከፓኪስታን፣ ከሩሲያ እና ከቻይና የሚመጡ መለዋወጫዎችን የሚተኩ፣ ጥራታቸውን የጠበቁና የተሻሉ ምርቶች ናቸው:: ከባድ ማሽነሪዎች ሊረግጧቸው የሚችሉና በቀላሉ የማይሰበሩ የመንገድ ላይ ዲሽከበሮች፣ መሸጋገሪያዎች፣ ውሃ ፍሳሽ ማስወገጃዎች ላይ የሚገጠሙ ምርቶች እያመረተ ነው:: ለማኑፋክቸሪንግ አገልግሎት የሚውሉ ማሽነሪዎች፣ ለመለዋወጫ የሚውሉ ምርቶችንም ያመርታል::

ማሽኑ ብረት በማቅለጥ ለኢንተርፕራይዙም ሆነ ለሌሎች አገልግሎት ፈላጊዎች አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ የሚገልጹት አቶ ገረመው፤ ማሽኑን የመሸጥ ሃሳብ እንደሌላቸው ተናግረዋል:: ቴክኖሎጂውን ለቴክኒክና ሙያ ተቋማት በማሸጋገር በተሻለ መልኩ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል::

እንደ አቶ ገረመው ገለጻ፤ ኢንተርፕራይዙ ማምረት ከጀመረ ዘጠኝ ዓመት ገደማ ይሆነዋል፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ምርቶቹን በአይነትም ሆነ ጥራት እያሻሽለና እያሳደገ መጥቷል:: ምርቶቹ በጥራት ደረጃቸው ላቅ ያሉ ናቸው:: ይህም የገበያ ትስስር በመፍጠር ብዙ ደንበኞች ማፍራት እንዲችሉ አድርጓቸዋል::

‹‹እኛ በደንብ ከሠራንና ካመረትን ሰዎች እነዚሁኑ ምርቶች ከውጭ የማምጣት ሱስ የለባቸውም›› ሲሉ አስታውቀው፣ ባለሀብቱ ከድሮ አሁን ላይ በተሻለ መልኩ ለሀገር ውስጥ ምርቶች ትኩረት ሰጥቶ የመግዛት ፍላጎት አለው›› ብለዋል::

ኢንተርፕራይዙ ሥራውን ለማስፋት እየሠራ ይገኛል:: በብዛት የሚያመረተውም በትዕዛዝ ነው:: የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ከዚህ ለተሻለ ለውጥ ለማምጣት ይሠራል:: በቀጣይም ለሆስፒታል፣ ለመኖሪያ ቤት፣ ለሆቴል፣ የማይዝጉ የአልሙኒየም ድስቶችንና የኬሚካል እቃዎች ለማምረት ከአከንባሎ ጀምሮ ያሉ እንደ ድስት፣ መጥበሻ እና የመሳሳሉትን መገልገያ እቃዎች፤ የሆስፒታል የኬሚካል ማስቀመጫዎች፣ ለኪችን ካቢኒት ማሠሪያ የሚሆኑ ምርቶችን ለማምረት አቅዷል::

ለዚህም ፕሮጀክት ቀርጾን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስገብተናል ሲሉ ጠቁመው፣ ከተማ አስተዳደሩ የመሥሪያ ቦታ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው እየጠየቁ መሆናቸውንና ከዚህም በጎ ምላሽ እንደሚጠብቁ ተናግረዋል::

ይህን አሟልተን ወደሥራ ከገባን ደግሞ ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ በመግባት በከፍተኛ ሁኔታ ኢንቨስት ማድረግ እንፈልጋለን ብለዋል:: የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባዘጋጀው ዓውደ ርዕይ ላይ በመሳተፋችን ይህንኑ የሚያረጋግጡን ዕድሎችን አግኝተናል ሲሉም አስታውቀዋል:: ከንቲባዋና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ኃላፊዎች ዓውደ ርዕዩን በጎበኙበት ወቅት የኢንተርፕራይዙን ሥራም አይተዋል፤ በተለይ ብረት የሚያቀልጠው ማሽኑን በተግባር ማሳየታቸውን ገልጸው፣ ድጋፍ እንደሚያደርጉል ቃል ገብተውልናል፤ የሥራ ትስስር እንደሚፈጠሩልንም ተስፋ ሰጥተውናዋል›› ብለዋል:: በኮሪደሩ ልማቱ ለመሳተፍ የምንችልበትን አቅጣጫም አመላክተውናል ያሉት አቶ ገረመው፣ እነዚህን ዕድሎች በመጠቀምና አጠናክሮ በመሥራት ወደተሻለ ኢንዱስትሪ ለማደግ ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል::

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You