የዝግጅት ክፍላችን ባለፉት ተከታታይ ሳምንታት በወቅታዊው ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የኮቪድ 19 ቫይረስ ላይ ትኩረት አድርጓል። ጉዳዩ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ሊሰጠውና ግንዛቤ ሊፈጠርበት የሚገባ አንገብጋቢ መሆኑ ጥርጣሬ ውስጥ የሚገባ አልነበረም። ለዚህም ነው በሁሉም ዘርፍ ላይ ያሉት አምዶቻችን ይህን ወረርሽኝ ታሳቢ በማድረግ ርእሰ ጉዳዮችን ወደ አንድ አቅጣጫ እንዲያተኩሩ የተደረገው።
የኪነ ጥብብ አምድም በተመሳሳይ ለተከታታይ ሳምንታት በዚሁ ርእስ ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ የማህበረሰቡን ንቃተ ህሊና የሚያሳድጉ መረጃዎችን ሲያቀብል ሰንብቷል። በመጀመሪያዎቹ ሰሞንም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በጉዳዩ ዙሪያ የአንበሳውን ድርሻ መውሰድ ይኖርባቸዋል በሚል ሃሳብ ላይ አጠንጥነን ጥሪ ለማድረግም ሞክረናል። የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊነት ቀዳሚው ድርሻ ይሄ በመሆኑም በተከታታይ ይህን ከማድረግ አልቦዘንም።
የጥበብ (ኪነ ጥበብ፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ሥነ ጥበብ እና ሌሎችንም) ባለሙያውም የእኛን ጥሪ ጨምሮ የበርካታ መገናኛ ብዙኃንን ሃሳብ ከመቀበል አልፎ በራሳቸው ተነሳሽነትም ጭምር በርካታ ትርጉም ያላቸው ሥራዎችን ሰርተዋልም፤ አሁንም እየሰሩ ይገኛሉ። ጥበብ ለማህበረሰቡ ውግንና ከሚቆሙ ዘርፎች ውስጥ አንዱ ከመሆኑ አንፃር ይህ መሆኑ ብዙም የሚያስገርም አልነበረም። እውነቱን ለመናገርም እንደዚህ ዓይነት ፈታኝ ጊዜያት በሚከሰቱበት ወቅት ከዘርፉ ከዚህ የበለጠ እንጂ ያነሰ ተግባር ይፈፀማል ተብሎ አይጠበቅም።
ሆኖም ከብስል ባቄላ ውስጥ አንድ ጥሬ አይታጣም እንደሚባለው ብሂል ሰሞኑን በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ዙሪያ ከጥበብ ባለሙያዎች ግንዛቤ ለመፍጠር በሚሉ የሚሰሩ አግባብነት የጎደላቸው ዝግጅቶች አልጠፉም። በዚህ ምክንያት ነው የዛሬ ርእሰ ጉዳያችን እንዲያጠነጥን የፈለግነው። የጥበብ ባለሙያዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መጎትጎት፤ መልካም ሲሰሩ ማበረታታት እንዲሁም አላስፈላጊ ስህተቶች ሲፈፅሙ እንዲታረሙ ገንቢ ትችት መሰንዘር እንዳለብን እናምናለን።
ምን ተከሰተ?
የእጅ ጓንቶችም ሆኑ የአፍ መሸፈኛ ማስኮች ኮቪድ 19 በከፍተኛ ሁኔታ እያጠቃቸው በሚገኙ አገራት ተፈላጊነታቸው እጅግ ከፍተኛ ነው። አንዱ የሕክምና ቁስ ቢያንስ አንድን ሰው አክሞ ለማዳን በሚደረገው ሂደት ውስጥ እሚኖረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑንም የሕክምና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲገልፁ ይደመጣሉ። እነዚሁ ባለሙያዎች በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ማስኮቹንም ሆነ ጓንቶቹን በአግባቡ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ያሳስባሉ። ይህ ምክረ ሃሳባቸው ከስጋትም የዘለለ እውነታን ያዘለ ጭምር ነው።
ቁሳቁሶቹ በውጭ ምንዛሬ እየተገዙ ነው የሚገቡት። ከዚህ ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊነታቸው እጅግ ከፍተኛ ነው። ታዲያ እነዚህም የወቅቱን አንገብጋቢ ቁሶች እንዳይናችን ብሌን እየተመለከትን በአግባቡ የማንጠቀምባቸው ከሆነ ዳፋው እኛው ላይ ተመልሶ እንደሚመጣ ግልፅ ነው። አንድ ሰው ጓንት በማድረጉና የአፍ መሸፈኛ በማጥለቁ ከቫይረሱ ተጋላጭነት ከመጠበቁም ባለፈ ሌሎች ላይ በተመሳሳይ ሊከሰት የሚችለውን የመዛመት ፍጥነት መቅጨት ይችላል። በዚህ ምክንያት እነዚህን ቁሳቁስ ከምንም በላይ በጥንቃቄና ያለ ብክነት መገልገል አስፈላጊ ይሆናል።
ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምናየው ከዚህ በተቃራኒ የሆነውን ነው። በተለይ ጉዳዩን ይበልጥ አስደንጋጭ ያደረገው ግንዛቤያቸው ከፍ ያለ ነው ተብሎ ከሚታሰቡ ወገኖች መምጣቱ ነበር። ለዚያውም ግንዛቤ የመፍጠር አቅማቸው ከፍተኛ ነው በሚል ከመንግሥት ጋር በቅርበት ከሚሰሩ የጥበብ ባለሙያዎች ሲሆን ነገሩን የከፋ ያደርገዋል።
ነገሩ እንዲህ ነው። በትንሳኤ በዓል ላይ በሚተላለፍ የመዝናኛ ዝግጅት ላይ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተወዳጅና ተቀባይ ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ኮሜዲያን ያልታሰበና አስደንጋጭ ስህተት ሲሰሩ ተስተውለዋል። በዚህ ክፉ ጊዜ ከፍተኛ ገንዘብ ከመንግሥት ካዝና ወጥቶ የተገዛን የአፍ መሸፈኛ የበግ አፍ ለመሸፈንና ጓንቶቹን ደግሞ በአራቱም የበጎቹ እግሮች ውስጥ በማጥለቅ አሳፋሪ ሥራ ሲሰሩ ተመልክተናል።
ይህ ድርጊት በፍፁም ተገቢ ያልነበረና በቀጣይ ሥራዎች ላይም በፍፁም ሊደገም የማይገባ ስህተት ነው። ሥራዎች ሲሰሩ ስህተት አይፈጠርም ማለት አይቻልም። ነገር ግን በተለይ ከማንኛውም ጊዜ በላይ ጥንቃቄ በሚያስፈልግበት በአሁኑ ወቅት መሰል ስህተቶች እንዳይፈጠሩ መስራት ያስፈልጋል።
የችግሩ መንስኤ
ማንኛውም የጤና እክል በሰው ልጆች ላይ በሚከሰት ጊዜ ችግሩን ለመግታት ዋነኛው መሣሪያ መረጃ ወይም በጤና ባለሙያዎቹ እንደሚገለፀው ‹‹health communication›› ነው። መረጃ ከህክምናው በላይ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ሰዎች (በተለይ በአሁኑ ወቅት እንደተከሰተው ዓይነት ወረርሽኝ ሲያጋጥም) መረጃ ሳይዛባ በመለዋወጥ በሽታውን ለመግታትና እራስን ለመከላከል እንዲያስችላቸው ነው። ስለዚህ ማንኛውም መረጃ በህክምና ባለሙያውና ተቋሙ ተመዝኖ ተመርምሮ ለኅብረተሰቡ መሰራጨትን ይጠይቃል።
የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በተለይ ማህበረሰቡን ግንዛቤ ሰጥቶ በማንቃት፣ እያዝናኑ በማስተማር እንዲሁም ያላቸውን ተፅዕኖ የመፍጠር አቅም ተጠቅመው ማህበረሰቡ እራሱን እንዲጠብቅ ምሳሌ በመሆን ረገድ ሚናቸው ከፍተኛ ነው። ሆኖም ግን ይህን መሰል ሙያዊ የመረጃ ስርጭት የሚጠይቅ ሁኔታ ሲያጋጥም በቀጥታ ከህክምና ባለሙያዎች የሚሰጡ አቅጣጫዎችን መከተል ይኖርባቸዋል። ሰሞኑን የተመለከትነው ግን ከዚህ በተቃራኒ ያለውን ነው። ሙያውን ከመከተልና ወቅቱ የሚጠይቀውን ጥንቃቄ ከማድረግ ይልቅ መዘናጋት አስተውለናል። የእነሱ መዘናጋት ደግሞ የማህበረሰቡን ቸልተኝነት በከፍተኛ ደረጃ የሚጨምር ነው።
አርቲስቶቹ በቀልድ ማስተማር እንደሚቻል ሁሉ በቀልድ ዜጎችን ወደተሳሳተ አቅጣጫ መውሰድ ቀላል መሆኑን መገንዘብ የቻሉ አይመስሉም። ለዚህ ነው ከፍተኛ ውግዘት ሊያስከትል የሚችል ተግባር እንደቀልድ «በቀልድ» ለዚያውም በቀጥታ ስርጭት ለማህበረሰቡ ሲያሰራጩ የነበሩት። ለዚህ ዋነኛው ተጠያቂዎቹ ኮሜዲያኑ ቢሆንም ቅሉ ይህን መሰል መልዕክት ሲተላለፍ የጤና ሚኒስቴርና ዝግጅቱን ያስተላለፈው የቴሌቪዥን ጣቢያ ቅድመ ግምገማ ማድረግ ነበረባቸው። በተለይ የጤና ሚኒስቴር በጀት መድቦ በአርቲስቶች ለማህበረሰቡ መልዕክት እንዲተላለፍ ሲያደርግ ቀድሞ መገንዘብ የሚኖርበት ‹‹health communication›› መስፈርት የተከተሉ መረጃዎች ለኅብረተሰቡ እየተላለፉ ነው የሚለውን ነው።
የስህተት መካሻ
ከላይ እንደ ዋና ጉዳይ አንስተን ከተቸነው ስህተት ባለፈ ይህ አደገኛ ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ከታወቀ ጀምሮ ግለሰቦች በሽታው እንዳይዛመት የሚረዱ ድጋፎችን እያደረጉ ይገኛሉ። በተለይ ቫይረሱ እንዳይሰራጭ የሚያግዙ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ከመስራት ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችም ናቸው እየተደረጉ የሚገኙት። ከዚህ ውስጥ የጥበብ ቤተሰቡ ይገኝበታል። ዋናው የዝግጅት ክፍላችን ዓላማም ስህተቶችን እየነቀሱ መተቸት ብቻ አይደለምና ለአርአያነት እንዲጠቅሙ በሚል ከዚህ እንደሚከተለው ልናስታውሳቸው ወደናል።
ለምሳሌ በብዙኃን ዘንድ ተወዳጅ የሆነው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (በመድረክ ስሙ ቴዲ አፍሮ) 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር መለገስ ችሏል። ይህ ብቻ ሳይሆን በሚሊዮን ሕዝብ የሚቆጠር ተከታይ ባለው ማህበራዊ ድረገፁም የበሽታውን አስከፊነት በመግለፅ ዜጎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ አሳስቧል። በተመሳሳይ በተለያዩ የጥበብ ሥራዎቿ የምትታወቀው ባለቤቱ አምለሰት ሙጬም ለተከታዮቿ የተለያዩ የምስልና የጽሑፍ መልዕክቶችን በማስተላለፍ ግንዛቤ ስትፈጥር ተስተውላለች።
ሌላኛዋ ተወዳጅ የጥበብ ቤተሰብ አርቲስት ሃመልማል አባተ ነች። ይህቺ ታዋቂ ግለሰብ ወደፊት ቫይረሱ ቢስፋፋ በሚል ለህክምና አገልግሎት እንዲውል በማሰብ መኖሪያ ቤቷን ሰጥታ የክፉ ጊዜ አጋርነቷን ማሳየት ችላለች። አርቲስት ጎሳዬ ተስፋዬ ለጌሪጊሲኖን የንጽህና መጠበቂያ በማበርከት ለሌሎች ምሳሌ መሆን ችሏል።
እንዲሁ ጸጋዬ እሸቱ የ40 ሺህ ብር ምግብ በቫይረሱ ለተጎዱ ወገኖች ለግሷል። የተለያዩ ፊልምና ቴአትር ቡድኖች ግንዛቤ ማስጨበጫ ሲሰሩ ተስተውለዋል። የፊልም ባለሙያው እና የጉዞ አድዋ አስተባባሪው ያሬድ ሹመቴና ጓደኞቹ የበጎ ተግባር ሥራ ላይ ተሰማርተው በርካታ የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፎችን በማሰባሰብ ላይ ይገኛሉ።
ነገ ምን እንጠብቅ
ያለፈውን ስህተት ማረም የሚቻለው ተመሳሳይ የሆነ ድርጊት ከመፈፀም በመቆጠብ ነው። ለመዳሰስ እንደሞከርነው ተደጋጋሚም ባይሆን እጅግ አደገኛ የሆነ ስህተት አርቲስቶቻችን ሲሰሩ አስተውለናል። በቀላሉ ሊታለፍ የሚችል ባለመሆኑ ትኩረት ይደረግበት ስንል ድምፃችንን ለማሰማት ወደናል።
ይህ ማለት ግን በቀጣይ እነዚህ ተወዳጅ አርቲስቶች የሚሰሩትን ተግባር ይግቱ አይደለም። ከጤና ባለሙያዎች ጋር በቀጥታ በመገናኘት የሚሰጡትን መረጃ መለየት አለባቸው። የሚያደርጉት ተግባር የሚያስከትለውን ችግር በመለየት በጥንቃቄ የተለመደውን ተግባራቸውን መከወን ይጠበቅባቸዋል።
አልፎ አልፎ ከሚያጋጥሙ ስህተቶች ባሻገር የጥበብ ቤተሰቡ በፈጣን ምላሽ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል። ይህ ማለት ግን ከችግሩ አንፃር አሁን እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቂ ነው ማለት አይቻልም። ቫይረሱ በፍጥነት ከመዛመቱና የሚያደርሰው ማህበራዊ ቀውስ ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር ተደጋጋሚ ርብርብ የሚፈልግ ነው። በመሆኑም ከጤና ባለሙያዎች ጋር በቀጥታ በመቀናጀት በቀጣይ በኪነ ጥበብ፣ ሥነ ጥበብ እና አጠቃላይ የጥበብ ቤተሰቡ ኃላፊነት ተወስዶ ሊከወን ስለሚገባው ተግባር እናንሳ።
ግንዛቤ
በተለይ ስርጭቱ በቀላሉ በሰው ንክኪ የሚተላለፍ ከመሆኑ አንፃር እያንዳንዱ ሰው የመተላለፊያ መንገዶቹን አውቆ እንዲጠነቀቅ የግንዛቤ ማስጨበጥ ተግባር መሰራት አለበት። ለዚህ ደግሞ በቀዳሚነት የጥበብ ቤተሰቡ ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው። ፈጠራ የታከለባቸውና እያዝናኑ የሚያስተምሩ የተለያዩ ጥበባዊ ሥራዎችን ለዚህ ተግባር ማዋል ይቻላል። ይህ ማለት ግን በበግ አፍ ላይ መሸፈኛ፤ እግሮቹ ላይ ደግሞ ጓንት ማጥለቅን አያካትትም። ይሄ እያዝናኑ ማስተማር ሳይሆን። እያሳሳቁ ማሳሳት ነው።
ራስን መጠበቅ
ከዚህ ዓለም አቀፍ ተዛማጅ ቫይረስ ተወዳጅና ተፅዕኖ ፈጣሪ የጥበብ ቤተሰቦች ራሳቸውን ሊጠብቁና ምሳሌ ሊሆኑ ይገባል። ይህ ሲሆን ዜጎች የእነርሱን ፈለግ የመከተል ልምድ አዳብረው በቀላሉ ቫይረሱ በቁጥጥር ስር መዋል እንዲቻል ያግዛል። በዓለማችን ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ የጥበብ ቤተሰቦች በቫይረሱ እንደተያዙ አንዳንዶቹም ለህልፈተ ሕይወት እንደተዳረጉ ሰምተናል። ይህ በዚህ አገር ቢከሰት ተፅእኖው ከባድ እንደሚሆን ተረድተው ራሳቸውን ሊጠብቁና አርአያ ሊሆኑ ይገባል።
ድጋፍ ማሰባሰብ
ይሄ ለዛሬ በወቅታዊው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጉዳይ ላይ በጥበብ ቤተሰቡ መደረግ አለበት ብለን ያነሳነው ነጥብ ነው። በመሆኑም ከላይ እንዳነሳነው ችግሩ በተከሰተ ወቅት ድጋፋቸውን እንዳሳዩ ጥቂት ግለሰቦችና ስብስቦች በተጨማሪ በቅንጅትና በተደራጀ መልኩ ወጥ እንቅስቃሴ ሊደረግ ይገባል የሚል እምነት አለን።
በመሆኑም ለተጎጂዎች የሚሆን የህክምና መርጂያ መሣሪያ፣ ምግብ እና አልባሳትን ጨምሮ መሰል አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ማሰባሰብና ለሚመለከተው አካል ማስረከብ ትልቁ ድርሻቸው ይሆናል። ይህን ከተደረገ የማንወጣውና የማንደረምሰው የችግር ተራራ አይኖርም። ክፉውን ቀን ዛሬም እንደ ትናንቱ ተባብረን እንሻገረዋለን።
መቋጠሪያ
ዓለም ሁሌም በለውጥ ላይ ነች። ለውጥ ደግሞ ጥሩውንም መጥፎውንም በአንድ ላይ ይዞ ይመጣል። ይህን ሕግ ተከትሎ በምድራችን ላይ አዲስ ነገር ተከስቷል። ለጊዜው ለውጡ ጥሩውን ሳይሆን ክፉውን አጋጣሚ ነው ይዞ የመጣው። ምድር በአስጨናቂ ወረርሽኝ ተከባለች። ከሰው ወደ ሰው ተላልፎ የሞት መቅሰፍት የሚያመጣ በሽታ ገጥሟታል። ሥልጣኔ፣ የጦር መሣሪያ ብዛትና የገንዘብ አቅም ሊገድበው አልቻለም። አሁን ሁሉም በአንድነት ስለ አንድ ጉዳይ ብቻ የሚያስብበት ወቅት ላይ ደርሰናል። ተመራማሪውም ሆነ ተራው ዜጋ እኩል ወደየእምነቱ አንጋጦ ምህረት የሚለምንበት ወቅት ነው። ጊዜው እጅግ ከባድ ነው።
ይህ ጊዜ ከየትኛውም ወቅት በተለየ መተባበር፣ መደጋገፍ፣ መተሳሰብ በጥቅሉ አንድነትን የሚፈለግ ነው። ከላይ ለማንሳት እንደሞከርነው ይህን መሰል ማህበራዊ ቀውስ በሚከሰትበት ጊዜ ከፊት የሚሰለፈውም ሆነ መቅደም ያለበት የጥበብ ቤተሰቡ ነው ። ቀደም ባሉ ጊዜያት በተግባር ያየነውም ይሄንኑ ነው። ይህ ሲባል ግን ማህበረሰቡ ከሚያውቀው በታች ሆነን ተዘናግተን ማዘናጋት አይጨምርም።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18/2012
ዳግም ከበደ