መነሻውን በቻይናዋ ውሃን ግዛት ያደረገው የኮሮና ቫይረስ ወደ ሌሎች ሀገራት በፍጥነት መዛመቱን ተከትሎ የዓለምአቀፉ የጤና ድርጅት፤ ዓለምአቀፍ ወረርሽኝ እንደሆነና የዓለም የጤና ስጋትነቱን አምኖ ማወጁ ይታወቃል። በሀገራችንም ቫይረሱ ከመከሰቱ በፊት ሆነ ከተከሰተም በኋላ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ለማስቀረት ብዙ ተሠርቷል ፤ አሁንም እየተራ ነው። በአሁን ወቅት በህዝባችን ዘንድ ካለው መዘናጋትና መዘናጋቱ ሊያስከፍለን ከሚችለው መጠነ ሰፊ አደጋ ለመቀልበስ ያስችለን ዘንድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል። የአዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብም ወጥቶ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።
የተደነገገው አዋጅ ተግባራዊነቱ እንዴት እየሄደ እንደሆነ እና እያጋጠሙ ስላሉ የህግ ጥሰቶች ማብራሪያ እንዲሰጡን አዲስ ዘመን ከአገር አቀፍ ኮቪድ 19 ዋና ግብረ ኃይል ኮሚቴ አባልና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ከወይዘሮ አዳነች አቤቤ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ ይዞ ቀርቧል። እንዲህ አቅርበነዋል፦
አዲስ ዘመን፡- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅ ተቀባይነት ያለው ጉዳይ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ፤ ከኢትዮጵያውያን ባህልና የአኗኗር ስርዓት አኳያ የአዋጁ አፈጻጸም እንዴት እየተተገበረ ነው? ተግዳሮት አልገጠመውም?
ወይዘሮ አዳነች፡- አዋጁን ማወጅ ያስፈለገው ሰዎች በፈቃደኝነት በተባለው ልክ የተሰጠውን መመሪያና ዝርዝር የጥንቃቄ ህግ ባለማክበራቸው ነው። አስገዳጅ በምናደርግበት ጊዜ ደግሞ በማወጅ ብቻ ሳይሆን ተጠያቂነትንም ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው።
ሌሎች አገሮች ላይ ፖሊስ ሰዎችን እንዴት አድርጎ እየተቆጣጠረ እንዳለ ብዙዎቻችን የምናየው፣ የምንሰማው ነው። መንገድ ላይ የተገኘውን ሁሉ በዱላ እስከማባረር እና ሰብዓዊ መብቱን እና ክብሩን ጭምር በሚያዋርድ ደረጃ ህጉን ለማስከበር ሲንቀሳቀሱ ይስተዋለል። ይህ የፖሊሶቹ ድርጊት ወረርሽኙ አገር ውስጥ ገብቶ ህዝቡን ከሚጨርስ እየወሰዱ ያለው ዕርምጃ ሳይሻል አይቀርም የሚያስብል ዓይነት ነው።
ነገር ግን እኛ ኢትዮጵያውያን እንደማመጣለን ብዬ አምናለሁ። ስለዚህም ህጉን ማክበር አለብን ማለት ነው። አሁንም ሁሉም እንደሚያውቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወጥቷል። ህዝቡ ማወቅ ያለበት የህግ አስከባሪው አካል ዕርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ነው። ዕርምጃዎቹ ደግሞ በመደበኛው ህግ ከለመድነው አካሄድ ጠንከር ያሉ ናቸው። በ48 ሰዓት ፍርድ ቤት አቅርበኝ የሚል ክርክር የሌለበት ጊዜ ነው። የጊዜ ቀጠሮ ጠይቅልኝ የሚልም ክርክር የሌለበት፤ ምስክር ላቅርብ የሚልም መከራከሪያ የሌለበት አካሄድ ነው።
ህግ አስከባሪው አካል ህግ ተጥሶ ካገኘና ካመነበት ህግ የተላለፉትን ሰዎች መያዝ ይችላል። በፖሊስ ጣቢያዎች ውስጥ ማሰር ይችላል፤ በሌሎችም ቦታዎች ማሰር ይችላል። ምክንያቱም እንደዛ አድርገህ ህዝቡንና አገሪቱን ታደግ ነው የተባለው። እኛ ግን ከዚህም በላይ ይታደገናል ብለን ዛሬም የምናምነውና ህዝባችን እንዲያውቅ የምንፈልገው እያንዳንዳችን ፖሊስ እንሁን ነው። ይህንን የሚለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ነው። ለህግ አስከባሪው አካል መታዘዝ ግዴታ ነው። ህጎችንም ማክበር ግዴታ ነው። ህጎችን ካላከበረ ደግሞ ምን ሊቀጣ እንደሚችልና እንዴት ዓይነት ፈጣን የሆነ ችሎት እንደሚቋቋም እንዲሁም ውሳኔ እንደሚሰጥ ተቀምጧል። ይህ ሁሉ እያለ ግን የመጀመሪያው መርህ እያዳንዱ ሰው የራሱ፣ የሌላው ሰው እና የአካባቢው ፖሊስ ሆኖ ይንቀሳቀስ ነው የምንለው፤ እንደዚያ ካልሆነ በስተቀር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ ስላልን ብቻ ኮቪድ 19ን እንከላከላለን ማለት አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ሰዎች አሁንም ቢሆን የወጣውን አዋጅ እምብዛም ተግባራዊ ሲያደርጉት አይስተዋሉም፤ ለአብነት እንኳ የበዓል ገበያው ሲታይ ወትሮ እንደሚደረገው ሁሉ ግፊያ የበዛበት እንደሆነ መታዘብ ይቻላል። በዚህም አዋጁ ተጥሷል የሚሉ አሉና ከዚህ የበለጠ ራሳቸው ዜጎቹም ቢሆኑ ምን ማድረግ አለባቸው? የታሰበስ ጠንካራ ነገር ይኖር ይሆን ?
ወይዘሮ አዳነች፡- በእርግጥ ኢትዮጵያ ላይ ያወጅነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሙሉ ለሙሉ ሁሉንም ነገር ዝግ የማድረግ አካሄድ አይደለም። አብዛኛው የጥንቃቄ ህጎች ላይ ያተኮረ ነው። ለምንድን ነው ኮቪድ 19 ሳይገለን የኢኮኖሚው ችግር አስቀድሞ እንዳይገለን ጭምር ታሳቢ ያደረገ ነው። ስለዚህ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ፈጽሞ ማቆም የለባቸውም የተባሉ ተቋማት አሉ። በአዋጁም በደንቡም ላይ የተገለጸው፤ ሰዎች በየሰፈራቸው በቀላሉ እንደሌላው አገር በኦንላይን አዝዘው የሚፈልጉት ዓይነት ሸቀጥ በራቸው ድረስ የሚመጣበት አገር ውስጥ አይደለንም ያለነው።
ሸቀጡ ወዳለበት ድረስ ሄደው እጅ በእጅ ከፍለውና ተሸክመው ነው የሚመጡት። ካልሸመቱ ደግሞ የሚፈልጉትን ነገር ማግኘት አይችሉም፤ ስለዚህ ተገቢውን ጥንቃቄ አድርገው እንዲሁም ደግሞ የወጣን ህግ አክብረው እንዲገበያዩ ነው። በተለይ የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ ሥራ ኮቪድ 19ን ለመከላከል ግብዓት የሆኑ የምግብና የመከላከያ እቃዎች በብዛት እንዲመረቱ ይፈለጋል። ይህ ግድ ነው፤ ከውጭም በሚፈለገው ደረጃ ሊገኝ የሚችል አይደለም። የገቢና የወጪ ንግዱ ወደመገታት ደረጃ ላይ ደርሷል።
ስለዚህም እኛ ይህን የከፋ ወረርሽኝ ልንቋቋም የምንችለው ትናንት ባሉን ፋብሪካዎች መኪና እናመርት ከሆነ ምርት ቀይረን የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ አሊያም የንጽሕና መጠበቂያ ምርት በማምረት ነው። ከውጭ አስመጪ ድርጅቶች ያስገባሉ ብለን የምንለው ነገር አይደለም። ስለዚህ የምንደርጋቸው እንቅስቃሴዎች በሙሉ ተገቢውን ርቀት በመጠበቅና የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ በማድረግ እንዲሁም ንፅሕናችንን በአግባቡ በመጠበቅ ነው። ይህንን ለሰከንድም ቢሆን ብንስት ህይወታችን አደጋ ላይ ይወድቃል።
ይህን ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ አሠሪዎችና በየአካባቢው የሚገኙ ኃላፊዎች ግዴታቸውን የማይወጡ ከሆነ የመጀመሪያዎቹ ተጠያቂዎች እነርሱ ይሆናሉ። ስለዚህ ለህግ አስከባሪው አካል የወጣውን ህግ እንዲስያከብር ተጨማሪ ስልጣን ተሰጥቶታል። ስለሆነም የሚሠራው በሙሉ ኃይሉ ነው።
በኮቪድ 19 ምክንያት የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመተላለፍ እስር ቤቶቻችን እንዳይሞሉ ለዜጎቻችንም በማሰብ ቀለል ያሉ ጥፋቶችን በመለየት ህዝባችንን ይህ ወረርሽኝ ከሚጎዳው ወደፊት ይታረማሉ በሚልና ምህረትም ይቅርታም ማድረግን ዋጋ ይሰጡታል ብለን የግማሹን ክስ በማቋረጥ ግማሹን ደግሞ ለቀናል። ይህ ማለት ግን ህጉን የበለጠ እንዲያከብሩትና ኃላፊነት ይሰማቸዋል በሚል ነው እንጂ ያጠፋ ዛሬ አይታስርም ማለት አይደለም። አሁን ከምናየው አንጻር ብዙ ሰው ሊታሰር ይችላል። የህግ አስከባሪውን አካል በሙሉ ኃይልህ ሥራ የሚል መመሪያ ተሰጥቶታል። ብዙ ለማስተማር ጥረናል። በብዙ መንገድም ግንዛቤው እንዲኖር አድርገናል። ይህን ሁሉ እያደረግን ደግሞ ህይወትን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል አካል እንዲኖር ዕድል ፈጽሞ መስጠት አንፈልግም።
ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ በየደረጃው ያለ የህግ አስከባሪው አካል ይህንን ታሳቢ ያደረገ ወጥ የሆነ አፈጻጸም፣ አሠራሩም ጥብቅ የሆነ አካሄድን ተከትሎ ነው መሥራት ያለበት። እዚህ ላይ እንደሌሎቹ ዱላ ይዘው እየተከታተሉ ሰው ላይደበድቡ ይችላሉ፤ ነገር ግን በስነ ስርዓት ይዘው ማሰርና መቅጣት ግድ ይላል። ስለሆነም ህዝቡ ይህንን አውቆ መጀመሪያ ራሱን መግዛት ቢችል ጥሩ ነው። አለበለዚያ ህግ ይገዛዋል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከሰሞኑን ለበዓል በማለት የትራንስፖርት አገልግሎት መፈቀዱን ተከትሎ ብዙዎች ወደተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተጉዘዋል፤ መንግሥት ይህን አገልግሎት መፍቀዱ ቫይረሱን እንደማሰራጨት ይቆጠራል የሚሉ ወገኖች አሉና እዚህ ምላሽዎ ምንድን ነው?
ወይዘሮ አዳነች፡- እንቅስቃሴን በምንገታበት ሰዓት ያገኘነውን ዕርዳታ ለሚሊዮኖች ማድረስ የሚከብድ ነው። ሁሉን ነገር ቤት አስቀምጠን እና የሚያስፈልገውን አቅርበን የት ድረስ መዝለቅ እንችላለን? ለአሁኑ ያገኘነው ቀደም ሲል የጠቀስኩልሽን ያህል ከሆነ ነገሩ የሚባባስ ከሆነ ደግሞ (እግዚአብሄር አይደርገው እንጂ ወረርሽኙ በዓለም ደረጃ እየተነገረ ያለው ሊቆይ እንደሚችል ነው) ሥራና እንቅስቃሴን መቶ በመቶ ገድበን እስከየት እንደርሳለን። የኢኮኖሚውን እንቅስቃሴ መግታት ደግሞ ሌላ ያልጠበቅነው ትልቅ ቀውስ ውስጥ ሊከተን ይችላል። ሰዎች እኮ ‹‹ሞት እንኳ ከሆነ ተርበን ሳይሆን እየበላን ይሁን›› እያሉ ሲናገሩ እንሰማለን። ለዚህ ደግሞ ጆሮም ዋጋም መስጠት ግድ ነው የሚሆነው።
ስለዚህ የትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ ትራንስፖርት ባለስልጣንም እውስዳሁ ብሎ ግዴታ የገባባቸውና ህግም ግዴታ የጣለበት አሠራር አለ። ልክ ህግ በእነሱም ላይ ግዴታ ጥሎባቸዋል። አንደኛ ማንኛውም ተሽከርካሪ ከተፈቀደለት ከግማሽ በላይ አለመጫን፤ እንዲሁም መኪናው ውስጥ ተዋሲ እንዳይኖር አስፈላጊውን ሁሉ በመጠቀም ምቹ ማድረግም ይጠበቅበታል። ተሳፋሪው ወደውስጥ ከመዝለቁም በፊት በእጅ ንጽሕና መጠበቂያ እጁን መታጠብና እንደ አልኮል ዓይነት እንዲጠቀም ማድረግ አለባቸው። ጓንት እንዲሁም የፊት መሸፈኛ የማድረግም ግዴታዎች አሉ።
ሌላው ደግሞ ዋነኛ ግዴታ ነው ያልነው ተሳፋሪዎች ከመሳፈራቸው በፊት ሌላው ቢቀር ሙቀታቸው ይለካል። ሊያስተላልፍ የሚችል ዓይነት ሰው ከታየ እንዳይሳፈርም ይደረጋል። እነዚህ ሁሉ ተግባራዊ የማይደረጉ ከሆነ የመጀመሪያው ተጠያቂ የሚሆነው አጓጓዡ፣ መናኸሪያዎቻችንን የሚያተዳድርና እስከ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድረስ ያለው አካል ነው። ይህንን ጥንቃቄ ማድረግ እንችላለን፤ ዝግጅቱም አለን ስለተባለ ነው ህጉ የወጣው። ከዚህ በተጨማሪ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውም እንዳይሞት ለማድረግም ጭምር ነው። ነገር ግን አሁንም ቢሆን መርሁ አትንቀሳቀሱ ነው። መንቀሳቀስ ግድ ከሆነባችሁ ግን የተጠቀሱትን መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ ሁለት በሚይዘው ወንበር ላይ አንድ ሰው ብቻ በመቀመጥና የአንድ ሰው ሂሳብን ከትራንስፖርተሩ ጋር በመጋራት ጉዞውን የሚያካሂድ ሲሆን ተሳፋሪው 75 በመቶውን የሚሸፍን ይሆናል። ምናልባት የዋጋው መጨመር በራሱ የህዝቡን እንቅስቃሴ ይገድበዋል የሚል እምነት ይዘን ነው። ይህን ህጉ በሚለው ደረጃ ካስፈጸምን ችግር አይኖርም፤ ካላስፈጸምን ግን ምንም ጥያቄ የለውም ሙሉ ለሙሉ መዝጋትም ሊመጣ ይችላል።
በተለይ አሁን የችግሩ ሁኔታ ታይቶ የምርመራው ሁኔታ ሰፋ ተደርጎ ሊጀመር ነው። እሱ የሚያሳየንን መረጃ መነሻ አድርገን አዋጁ ለዚህ ክፍት አድርጓል። ጥብቅ ማዕቀፍ አስቀመጠናል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለሚያወጣው ደንብ እንደችግሩ ሁኔታ ስፋትና ጥበት ክልከላዎቹና ጥንቃቄዎቹ እንዲሁም ዕርምጃዎቹም ክልከላዎቹንም ሊያጠብቅ ወይም ሊያላላ እንደሚችል አስቀምጧል።
አሁን የምናገኘው ውጤትና የህዝቡ አተገባበር ወይ እንድናጠብቀው ያደርገናል፤ አሊያ በያዝነው ደረጃ ጥንቃቄያችንን እያጎለበትን እንድንሄድ የሚያደርገን ይሆናል። ይህ ለየዘርፉ የሥራ ስምሪት ተሰጥቷል፤ በጤና ሚኒስቴርም በጸጥታ ዘርፍ አስተባባሪም አማካይነት የሚሠራ ነው። የየራሳቸውን ክትትል አድርገው ሪፖርት የሚያቀርቡ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- በእስከአሁኑ ሂደት የተለያዩ የህግ ጥሰቶች ተስተውለዋልና የታሰሩ ግለሰቦችም የተቀጡም ተቋማት ምን ያህል ናቸው?
ወይዘሮ አዳነች፡- ብዙ ናቸው፤ በመጀመሪያ የሚነሱት የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡት ናቸው።በከተማ ውስጥ አገልግሎቱን የሚሰጡ ታክሲዎችና ትራንስፖርተሮች፣ በገበያው ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎች፣ ምርት ደባቂዎች እና ሌሎችም የሚጠቀሱ ሲሆን የተቀጡት ክልልን ጨምሮ ወደ 30 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ናቸው።
ራሱ ወረርሽኙና ችግሩ ህዝባችንን ወደስነ ልቦና ጫና ውስጥ አስገብቶታል። ስጋትና ፍርሐትም እየተፈራረቀበት ነው። በዚህ ላይ ደግሞ በማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ሐሰተኛ መረጃ በመልቀቅ በቋፍ ያለውን የህብረተሰቡን ስነ ልቦናዊ ቀውስ ለማባባስ ሲተጉ የነበሩ አሉና እነርሱንም ይዘን ውሳኔ የመስጠት ሂደት ላይ ነን። አሁን ደግሞ ሰሞኑን በጥግግት ህግና አትሰብሰቡ በተባለበት ቦታ ላይ በመሰብሰባቸው ምክንያት በርካታ ሰዎች ተይዘዋል።
አዲስ ዘመን፡- ለህግ ፈጻሚው ህብረተሰብና ህጉ እንዲፈጸም ለሚያደርገው የህግ አካል የሚያስተላልፉት መልዕክት ካልዎት?
ወይዘሮ አዳነች፡- ሁላችንም ህጉን የማክበርም የማስከበርም ግዴታ አለብን። ይህ ኃላፊነታችን ነው። ስለዚህ ከመቼውም ጊዜ በላይ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማውጣታችንም ምስጢር ህጉን የማስፈጸም አቅማችን እንዲጨመር በማሰብ ነው። ስለዚህ ተቀናጅተን በጋራ ኃላፊነታችንን እንድመንወጣ ይገባናል፤ በዚህ መንገድ ሁሉም ሰው ህጉን መተግበርና ማስተግበር አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ከልብ አመሰግናለሁ።
ወይዘሮ አዳነች፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16/2012
አስቴር ኤልያስ