ክፍል ሁለት
ባለፈው ሳምንት የፍልስፍና አምዳችን በአገራችን የፖለቲካ ሥርዓቶች ውስጥ ላጋጠሙ ስብራቶች መፍትሄ ይሆናሉ ያልናቸውን ሃሳቦች በመጠኑ መጠቆማችን ይወሳል። ዛሬም ቀጣዩን ክፍል ይዘን ቀርበናል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መደመር ሲሉ የሚሆነውንና የማይሆነውን ሁሉ አንድ ላይ በመሰብሰብ ወይም ጎን ለጎን በመደርደር ወይም አንዱን በሌላው ላይ በመከመር ወይም ነገሮችን በቁጥር በመጨመርና በመጨማመር ክምችት መፍጠር ማለታቸው አይደለም። በእንዲህ ዓይነት መደመር አንዱ ከሌላው ውጭ ይሆናል። በዚህ መልኩ ደግሞ ጉልበትና ሀብት፤ ውበትና ድምቀት፤ አንድነትና ፍቅር የማመንጨት አቅም አይኖረውም። በመሠረቱ መደመር የሚያስፈልገው አቅም ለመፍጠር ነው። ያለ አቅም መገንባትም ሆነ ማፍረስ፤ መፍጠርም ሆነ ማምረት፤ ማልማትም ሆነ ማፍራት፤ መውጣትም ሆነ መውረድ፤ ማቀናጀትም ሆነ ማደራጀት አይቻልም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እንደመር” ሲሉ ከፍተኛ ጉልበትና ልማት፤ ልዩነትና ዕውቀት ማምጣት የሚያስችል ኃይል እንፍጠር፤ የበለጸገች፤ የተከበረችና የታፈረች ኢትዮጵያን አንገንባ፤ ለማንምና ለምንም ጥቃትና ክፋት የማይበገር ኃይል እንሁን ማለታቸው ነው። ከዚህ አንጻር መደመር ለውጥ አማጪ፤ ለውጥ አራማጅና ኃይል መፍጠሪያ ነው።
መደመር የከፋፍለህ ግዛ ተቃራኒ ነው። የተበተነውን የሚሰበስብ ነው፤ ከፋፍሎ መግዛት የተሰበሰበውን/አንድ የሆነውን የሚበትን ነው። ቀደምት ሥርዓቶች ሀገርና ሕዝብን የመሩት በከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ነው። በሃይማኖቶችና እምነቶች፤ በርዕዮተ ዓለምና አስተሳሰቦች፤ በብሔር፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፤ በዘርና በቋንቋዎች መካከል ላሉት ልዩነቶች የሚያበላልጡ እሴቶችን በተለያዩ መንገዶች በማስረጽ አንድነታቸውን መረዙ። ሕዝቡን በመከፋፈል አቅም አሳጡት፤ ለራሳቸው ግን አቅም ሆናቸው። በዚህ ምክንያት የደረሰው ጉዳት በምንም ነገር መለካት የሚችል አይደለም። ጉዳቱ ትናንት የደረሰ ብቻ ሳይሆን ዛሬም በሽታ ሆኖ ቀጥሎአል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር ፍልስፍና የቀድሞ ሥርዓቶች የበታተኑትን የሕዝብ ኃይል መልሶ የመገንባት ዓላማ ያለው ይመስላል። ይህ ደግሞ መሆን የሚችለው ለክፍፍሉ ምክንያት የሆኑትን እኩይ ነገሮችን በማፅዳት ነው።
ሰዎች “ተደመረናል” ሲሉ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ “ለውጥ ፈላጊዎች፤ አራማጆች ወይም ኃይሎች ነን” ማለታቸው ነው። በራሱ ይህ ማለት ደግሞ እስካሁን ከነበሩብን መጥፎ አስተሳሰቦችና አምነቶች፤ አሠራሮችና አኗኗሮች ራሳችንን ነፃ አድርገናል፤ መልካም የሆኑ ነገሮችን ለመቀበልና መልካም ያልሆኑ ነገሮችን ለማስወገድ ተዘጋጅተናል ማለት ነው። ሲሰናሰል መደመር ችግሮችን መመከት የሚያስችል አቅም ይፈጥራል። አለመደመር ግን ለማንኛውም ችግር ተጋላጭ ያደርጋል። መደመር መደርደር ሳይሆን መቀናጀት ወይም መሰናሰል ነው። ይህ ማለት አንዱ በሌላ ውስጥ የሌላው አካል ወይም አስትንፋስ ይሆናል።
“እንደመር” ሲባል በአካልና በቁጥር የሚለካ ስብስብ እንስራ ማለት አይደለም። ሰዎች በርካታ አቅም አላቸው። ጉልበት፤ ዕውቀት፤ ውበት፤ ክህሎት፤ እሴት፤ ሀብት ወይም ንብረት፤ ፍቅር፤ ልምድ፤ መንፈሳዊና ምሁራዊ እሴቶች ሁሉ አቅም ናቸው። ሰዎች የሚደመሩት እነዚህ አቅሞቻቸውን ይዘው ነው። የሰዎች መደመር ውስጣዊ ተነሳሽነት ወይም ውጫዊ ግፊት ይፈልጋል። መደመር በሚፈለገው መጠን ውጤታማ የሚሆነው አንዱ በራሱ ምርጫና ፍቃድ ለሌላው አካል ሲሆን ነው። በውጫዊ ግፊት የሚፈጠር መደመር በቀላሉ ሊበተን ይችላል፤ በውስጣዊ ተነሳሽነት የሚሰራው ግን በምርጫና በፍቃድ የተጋመደ ነው። እውነተኛ መደመር መገፋፋት ማለት ሳይሆን መተቃቀፍ፤ በፍቅርና በእኩልነት መቀናጀት ማለት ነው። የመደመር ውስጣዊ ጉልበት ነፃ ፍላጎት፤ ፍቅርና እምነት ናቸው። በተለይ ፍቅር ዋናው አንቀሳቃሽ ኃይል ነው።
በፍቅርና በመስማማት፤ በመተሳሰብና በመፈላለግ በሚፈጠር መደመር ውስጥ ያንዱ ኢነርጂ ወደ ሌላው ይፈሳል። ያንዱ ሀብትና ጉልበት፤ ዕውቀትና ክህሎት ሌላውን ያገለግላል። ለዚህ ሁሉ ደግሞ ፍቅር የደም ስር ይሆናል – ምክንያቱም ሁሉንም እሴቶችና ስሜቶች ካንዱ ወደ ሌላው ማዘዋወር የሚያስችል ጉልበት አለው። ፍቅር አዎንታዊ በሆነ መንገድ ያስራል ወይም ያስተሳስራል፤ ይፈታል ወይም ያፋታል፤ ያዛል ወይም ይታዘዛል። ባጭሩ መተሳሰብንና መሳሳብን፤ መያያዝንና መፈላለግን፤ መመጋገብንና መጋራትን በመፍጠር በአንድነት ያጋምዳል። መፋቀር ማለት አንዱ ሌላውን በመፈለግ፤ አንዱ ሌላውን በመፍቀድና በመቀበል ያልነበረ ኢነርጂን መፍጠር ነው። “ሁለት ሰዎች ይፋቀራሉ” ስንል ያንዱ ወገን የፍቅር ስሜት የሌላውን ወገን የፍቅር ስሜት በማንቀሳቀስ ወይም በማነቃቃት አስተሳስሮአቸዋል ማለት ነው። ፍቅርን ራሱ ፍቅር የሚያደርገው ያንዱ ፍላጎትና ስሜት የሌላውን ፍላጎትና ስሜት እንደ ራሱ አድርጎ ማንቀሳቀስ መቻሉ ነው። ስለዚህ መደመር በዓይነትና በመጠን መቀናጀት ነው።
የመደመር ፍልስፍና ከሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ ባሕርይ ጋር የሚጣጣም ነው። ሰው ማህበራዊ እንስሳ ነው። አንዱ ያለሌላው መኖር የማይችል ብቻ ሳይሆን ሰብአዊ ፍጡር የመሆን አቅምም የለውም። አንድ ላይ መሆንና መኖር፤ መፈላለግና መተጋገዝ ችግርንም ሆነ ጥቅምን፤ መከራንም ሆነ ደስታን መጋራት የግድ ነው። ወደድንም ጠላንም ሰው ያለ አብሮነት ሰብአዊ ፍጡር ሆኖ መኖር አይችልም። ምርጫ የሚሆነው አብሮነትን መልካም ወይም መጥፎ ማድረጉ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ በየደረጃው እየተደማመረ ኖሮአል። ይህ መደመር ወይም አብሮነት በግለሰብና በቡድን፤ በጉርብትናና በሰፈር፤ በእድርና በመንደር፤ በእምነትና በአምልኮት፤ በብሔርና በብሔረሰብ ወዘተ ደረጃ የኖረና ያለ ነው። የሰው ልጅ አብሮነት የግድ ከሆነ ለምንድነው የሰው ልጅ ብቸኛ ምርጫ የሚበጅና የሚጠቅም፤ የሚገነባና የሚያለማ አብሮነት የማይሆነው? የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ የመደመር ፍልስፍና ከሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ ባሕርይ ጋር የሚጣጣም ከመሆኑ አንጻር ለእንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች ንድፈ-ሐሳባዊና ጽንሰ-ሐሳባዊ መሠረትና አቅም መቀመር ይኖርበታል።
በእኔ እምነት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር ፍልስፍና ትልቁ መልእክት ሀገራዊ ችግሮቻችንን ለመፍታት ሀገርኛ የሆነ ፍልስፍና ይኑረን የሚል ነው። ይኸ ደግሞ ከዚህ በፊት ያልሞከርነው ይመስለኛል። ለውጥ ለማምጣት በነበረን ፍላጎት በኛ ልክ ያልተቃኙ አስተሳሰቦችን ከምዕራቡም ሆነ ከምስራቁ ተበድረናል። ያተረፍነው ችግር እንጂ ጥቅም አይደለም። ባልገቡን የተውሶ አስተሳሰቦች ላይ ከመጯጯህና ከመገዳደል በሚገባን ቋንቋና ሐሳብ እየተነጋገርንና እየተደማመጥን ችግርን እንፍታ የሚል መልእክት ይዞአል። የዚህ ፍልስፍና ዕድገት ገና በመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ የሚገኝ እንጂ ተሰርቶ ያበቃለት እንዳልሆነ ይታወቃል። ተስፋ የምናደርገው ዲበ-አካላዊ ፍልስፍና ሳይሆን የተግባር ፍልስፍና እንደሚሆን ነው። በተግባር እየተገለጸና እየተፈተነ፤ በሐሳብ እየበለፀገና በልምድ እየዳበረ መሄድ ከቻለ አይደለም ለኢትዮጵያ ለአፍሪካና ለሌሎችም በረከት ሊሆን ይችላል።
ወደ ዋና ጉዳያችን እንመለስ። ከላይ እንደተገለጸው የርዕዮተዓለም ችግር አለብን። የምንመራበትን ርዕዮተዓለም በትክክል የምናውቅ አይመስልም። በመሠረቱ ርዕዮተዓለም የሚፈጠረው አፈ-ታሪክን፤ ሥነ-መለኮትን፤ ፍልስፍናን፤ ሥነ-ጥበብንና ልዩ ልዩ ምሁራዊና አእምሮአዊ ትውፊቶችን መሠረት በማድረግ ነው። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት በርዕዮተዓለም/በአስተሳሰብ ጥገኛ ሆኖ ቆይቶአል። ሀገሪቱ የሌሎች ሀገሮች አስተሳሰብ፤ ትምህርት፤ ሃይማኖት፤ ፍልስፍናና ርዕዮተዓለም ሰለባ ነች። የአንዱን አንስታ የሌላውን ስትጥል፤ ያነሳችውን ጥላ የጣለችውን ስታነሳ ከርማለች። የኔ ወይም የራሴ ነው የምትለው የፖለቲካ ርዕዮተዓለም የላትም። የንጉሳዊው አገዛዝ ርዕዮተዓለም ዋና ምሰሶ ሃይማኖት ነው። የደርግ ሥርዓት ማርክሳዊ-ሌንናዊ ፍልስፍና ሲሆን የኢህአዲግ ምንነቱ ያልለየለት “አብዮታዊ”፤ አንዳንዴም “ልማታዊ ዲሞክራሲ” በመባል ይገለጻል። ሶስቱም ከውጭ የገቡ እንጂ ከሀገር ውስጥ የበቀሉ አይደሉም። የትኛውም ርዕዮተዓለም የኢትዮጵያን ሕዝብ ሕይወት የሚገልጽ አልነበረም።
እነዚህ የተዋስናቸው አስተሳሰቦች ሊረዱን ያልቻሉት ከውጭ በመምጣታቸው ነው ብሎ ማመን ያስቸግራል። ሕዝቦች ዕውቀቶችን፤ አስተሳሰቦችን፤ እምነቶችን፤ ፍልስፍናዎችን ወዘተ ሲወራረሱ ኖረዋል። ስለዚህ ችግር የሚሆነው ከሀገሪቱና ከሕዝቡ የሩቅና የቅርብ ፍላጎት አንጻር ተፈትሸው የሚጠቅሙና የማይጠቅሙ፤ የሚያለሙና የሚያጠፉ መሆናቸው በውል አለመረጋገጡ ነው። ለምንም ነገር በአስተሳሰብ ረገድ ራሳችንን ሳንችል ኖረናል። እውነት ራሳችንን መምራት የሚያስችለን አስተሳሰብ የለንም ወይስ በተለያዩ ምክንያቶች የማይጠቅሙ ናቸው ብለን ጥለናቸው ነው? የኛ የሆነውን ሁሉ እንደ መጥፎ፤ ኋላቀርና ጎታች በመቁጠር የሌላ የሆነውን እንደ ተራማጅና ጠቃሚ በማሰብ ራሳችንን ስናሳንስ ቆይተናል።
እኛ ምንም መልካም ነገር የመፍጠርና የማመንጨት አቅም እንደሌለን አድርገን ራሳችንን ፈርጀናል። ለዚህ ድክመት ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት የሀገራችን ፖለቲካ ሥርዓቶች፤ እሴቶችና አመለካከቶች ናቸው። እኛ እኛን እንድንሆን ያደረጉን ሀገር በቀል የእሴት ሥርዓታችን፤ አመለካከታችንና ሥራችን በትክክል ለይተን አናውቅም። የራሳችን እሴቶችና አመለካከቶችን አስመልክተው የተሰሩ ምርምርና ጥናቶች እምብዛም የሉም። ስለ ራሳችን ማንነት ራሱ በሚገባ የተጠና፤ የተብላላ፤ በምክንያትና በማስረጃ የታገዘና የጠለቀ አስተሳሰብ የለንም።
በግልጽ መረዳት የሚቻለው ግን ነባር እሴቶቻችን የመጨቆኛ መሳሪያ ሆነው ማገልገላቸውን ነው። የነበሩንና ያሉን እሴቶች ዜጎችን የሚያጣሉና የሚያናቁሩ፤ የሚያናንቁና የሚያራርቁ፤ እንዳይተማመኑና እንዳይተጋገዙ የሚያደርጉ አሉታዊ እሴቶች ናቸው። በውስጣቸው በያዙአቸው እኩይ ነገሮች ምክንያት የሕዝብን ውስጣዊ ትስስርና አቅም አዳክመዋል። በተቃራኒ የሚያቀራርቡና የሚያሰባስቡ፤ የሚያከባብሩና የሚያስተሳስሩ፤ የሚያፋቅሩና የሚያፈላልጉ ሰናይ እሴቶችም ነበሩን፤ አሉን። ዋናው ጉዳይ ግን ለምንድነው የሰናይ እሴቶች ምክንያታዊ አቅም የእኩይ እሴቶች ኢ-ምክንያታዊ ተፅዕኖ መቋቋም ያልቻለው የሚለው ነው። መፍትሄው ሰናይ እሴቶቻችንን በሕዝብ ሕይወትና ግንኙነት ውስጥ በማበልፀግ እኩይ እሴቶችን አመንምኖ ማዳከምና ማስወገድ ነው። ይህ አዲስ ለሚፈጠረው የፖለቲካ ሥርዓት ቁልፍ ጉዳይ ነው።
እስካሁን የነበረን ፖለቲካ ‹አራዊታዊ› ባሕርይ አለው። ከአራዊቶች ደመ-ነፍሳዊ ፍትጊያ የሚለየው በትንሹ ነው ብንል አንሳሳትም። የአራዊት ፍትጊያና መጠፋፋት ተፈጥሮኣዊ ነው – ምርጫና ዕድገት የለውም፤ ስለዚህ ለውጥ አያሳይም። ለእነርሱ መጠፋፉት ባብዛኛው የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነው – የምርጫ አይደለም። ለምሳሌ አንበሳ ሌሎች እንስሳትን ገድሎ ካልበላ መኖር አይችልም። የሰው ልጅ ግን ሳይጠፋፋ መኖር የሚያስችሉ አማራጮች አሉት። ይሁን እንጂ መጠፋፋት ዓይነተኛ የሀገራችን ፖለቲካ ባሕርይ ሆኖ ቆይቶአል። ልክ እንደ አራዊቱ ፖለቲካችን የዓይነት ለውጥ ሳያስመዘግብ ኖሮአል። ሁሌም የሴራ ፖለቲካ ነው፤ ሁሌም የመጠላለፍ ፖለቲካ ነው፤ ሁሌም በስሜት የሚነዳ ፖለቲካ ነው፤ ሁሌም የፍጅትና የደም መቃባት ፖለቲከ ነው፤ ሁሌም የውሸትና የጉልበት ፖለቲካ ነው፤ ሁሌም መደፍጠጥና ማንበርከክ እንጂ ሌላ አማራጭ የማይታየው ፖለቲካ ነው።
ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን ፖለቲካ ከበቂ በላይ ኖረውታል። ፈልገውና ወድደው ሳይሆን ተገድደውና ተረግጠው ዘልቀውታል። አሁን ይህችን ሀገርና ይህን ሕዝብ መታደግ የሚችለው መሠረታዊና ታሪካዊ የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ ማድረግ ብቻ ነው። ፖለቲካ ለሥልጣን መታገልን፤ ሥልጣን መያዝን፤ በሥልጣን ሀገርና ሕዝብ ማገልገልን፤ ሥልጣን ማቆየትን፤ በሀገርና በሕዝብ ጉዳዮች ላይ መወሰንን ወዘተ ያጠቃልላል። በኢትዮጵያ ታሪክ ራሱን ለሕዝብ ፍላጎት ያስገዛ ሥርዓት ኖሮ እንደማያውቅ በተደጋጋሚ ተጠቅሶአል። ይህ ችግር የሚፈታው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎትና ይሁንታ፤ ድምፅና ውሳኔ ወደ ሥልጣን የሚያመጣው መንግሥት ሲፈጠር ነው።
ከፖለቲካ ሥርዓቶች ዋነኛ ተልዕኮ መካከል አንዱ ዜጎችን ማብቃት ነው። እያንዳንዱን ዜጋ ማነሳሳትና ማሰራት የሚያስችል ሥርዓት መገንባት አለበት። እስካሁን በሀገራችን የነበሩ የፖለቲካ ሥርዓቶች ባብዛኛው ዜጎችን የማሳነስ አንጂ የማንሳት አቅምም ሆነ ፍላጎት አልነበራቸውም። የሀገር ዕድገት ደግሞ የሕዝብ አስተዋጽኦ ድምር ውጤት ነው። የእያንዳንዱ ዜጋ ጉልበትና ዕውቀት፤ ሀብትና ንብረት ሳይባክን ለሀገር ዕድገትና ጥቅም እንዲውል ማድረግ የመንግሥታት ግዴታ ነው። የሀገራችን ገዢዎች በጠባብ ሥርዓቶቻቸውና ፍላጎቶቻቸው ምክንያት በሀገሪቱ ቁሳዊና አእምሮአዊ ሀብቶች ላይ ግዙፍ ብክነት አድርሰዋል።
እንደ ሀገር ዜጎቻችንን በተለይ ወጣቶቻችንን ለመጪው ዓለም ማዘጋጀት ያሁኑ ትውልድ ግዴታ ነው። አሁን በመሬት ላይ የሚታየው ዝግጅት ሰፊና ፈርጀ-ብዙ አይደለም። ከዚህ ጠባብ አስተሳሰብ መውጣት አለብን። ነገሮችን ማየት የሚኖርብን በአካባቢና በሀገር ደረጃ ላሉና ለሚኖሩ ጉዳዮች ብቻ መሆን የለበትም። ዓለማችን አንድ መንደር ሆናለች። ዕድልም ሆነ ተግዳሮቶች አሉባት። ተግዳሮቶችን መሸከም የግድ የሚለንን ያህል ዕድሎችን የመቋደስ መብትም አለን። ሀገር ዜጎችዋን ማዘጋጀት የሚኖርባት ዓለም ከምትፈጥረው ዕድል ለመቋደስና ተግዳሮቶችዋን መቋቋም የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ነው። ኢትዮጵያ የወጣቶች ሀገር ነች። ይህ ግዙፍ አቅምና ሀብት ነው። ዓለም ለእነዚህ ወጣቶች የሚሆን ብዙ መድረኮች አሉዋት። ወጣቶቻችንን ለእነዚህ መድረኮች ማብቃት የሚያስችሉ ዝግጅቶች መደረግ አለባቸው።
ለምሳሌ በጣም ብዙ የሆኑ የእስፖርት ዘርፎችና ዓይነቶች በዓለም ላይ አሉ። የኢትዮጵያ ወጣቶች በዓለም የእስፖርት መድረክ ላይ አንጸባራቂ ታሪክ አላቸው። ይህን መሠረትና መነሻ በማድረግ ተሳትፎአቸውን ማስፋት ያስፈልጋል። በሚታወቁበት መስክ ብቻ ሳይሆን በማይታወቁበት መስክም መታወቅ አለባቸው። በዓለምአቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ስመ-ጥር መሆን የሚያስላቸውን ዕውቀትና ክህሎት ማግኘት ይኖርባቸዋል። በብቃታቸው ተፈላጊ የሚሆኑ ምሁራንንና ሌሎች የተማሩ ዜጎችን ማፍራት እጅግ አስፈላጊ ነው። ሳንሰጥ መቀበል፤ ሳናካፍል መካፈል የማይቻልበት ዓለም ውስጥ ነን። መስጠትም ሆነ መቀበል፤ ማካፈልም ሆነ መካፈል አቅም ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ መማርና ማስተማር ወሳኝ ነው።
በእኔ እምነት እስካሁን የነበረን የትምህርት ሥርዓት ትውልድን ሚያባክን ነው። እውነትን ለማግኘትና ውጤታማ ግኝትን ለማስመዝገብ የሚቆፍሩ፤ የሚመራመሩ፤ የሚያጠኑ ወይም የሚፈትሹ ዜጎችን የሚያመርት ሳይሆን ሌሎች ያሉትን መልሰው እንዲሉ የሚያደርግ ነው። ከተግባር ጋር የሚያገናኛቸው ሳይሆን ባብዛኛው በመነባነብ ዓለም ውስጥ በመድፈቅ የሚያስቀራቸው ነው። የራሳችንን ፈልገን ከማግኘትና ከማበልጸግ ይልቅ የሌሎችን እንዳደነቅን እንድንኖር የሚፈቅድ ነው። ስለዚህ መሬት የነካ የትምህርት ሥርዓት ያስፈልገናል። ከአፈራችንና አካባቢያችን፤ ከማንነታችንና ከእሴቶቻችን መነሳት ይኖርበታል። የኢትዮጵያ ልጆች የሌሎችን ከማወቅ በፊት የራሳቸውን ማወቅ ይገባቸዋል። ከዓለም ጋር መተዋወቅ የሚኖርባቸው የራሳቸው በሆኑ ነገሮች አማካይነት መሆን አለበት። ለራስ ዋጋ መስጠት፤ ራስን ማድነቅና በራስ የመተማመን መንፈስ የሚጎለብተው ይህ ሲሆን ነው።
ለዜጎች የሚደረገው አያያዝ እስካሁን በነበረው መልክ መቀጠል የለበትም። በኃላፊነትና በሀገር ፍቅር ስሜት የታነፁ ዜጎችን መፍጠር ከታች መጀመር አለበት። የሕፃናትና የልጆች አስተዳደግና አቀራረጽ በፖሊሲ መታገዝ ይኖርበታል። እስካሁን የነበረው መንገድ ባብዛኛው የበዘፈቀደ ነው። አሁን ባለው ትውልድ ዘንድ የተቀዛቀዘ የሀገር ፍቅርና የኃላፊነት ስሜት የምናየው ለዚህ ነው። የመደማመጥ፤ የመናበብ፤ ለእርስ በእርስ የመታዘዝ፤ ከእርስ በእርስ የመማር፤ ሕግን የማክበር ወይም ለሕግ የመታዘዝ፤ አብሮ የመስራትና የማደግ ባሕላችን ከሚፈለገው በታች ነው። ስለዚህ መንግሥት የሕፃናትንና የልጆችን ጉዳይ ለወላጆች ብቻ መተው የለበትም። መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት ብቻ በቂ አይደለም።
ወላጅ ለሕፃናት የመጀመሪያ ፊደላቸው ናቸው። የመልካምም ሆነ የመጥፎ ነገር ”ሀ ሁ”ን በመጀመሪያ የሚማሩት ከወላጅ ነው። ከወላጅ ዘንድ የሌለውን ነገር ማግኘት የሚችሉት ከጊዜ በኋላ ነው። ስለዚህ ከመልካም ወላጅ የሚጠበቀው ለልጆቹ ምርጥ ምርጥ ምግቦችን ማብላትና አልባሳትን ማልበስ ብቻ አይደለም። ምርጥ ምርጥ ቃላትን፤ አባባሎችን፤ አስተሳሰቦችንና ግንዛቤዎች በአእምሮአቸው ማስረጽ ነው። መጥፎ መጥፎ የሆኑ ቃላትን፤ አባባሎችን ለሚወዱአቸው ልጆቻቸው አእምሮ የሚያቀብል መልካም ወላጅ ይኖራል ተብሎ አይታሰብም። ለዚህ ደግሞ ተቋማዊ ክትትልና ድጋፍ መኖር አለበት።
ይቀጥላል
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 16 ቀን 2012