ቢያንስ በፍልስፍናው ደረጃ ስንሰማው እንደኖርነው አመራር ሳይንስም ጥበብም ነው። በንድፈ ሀሳቡ ቀማሪዎች ዘንድ አንድም ጊዜ የጉልበተኞችና የመጨቆኛ መሣሪያ ሆኖ አያውቅም፤ እንዲሆንም አይፈለግም። እንደዛ ከሆነ ደግሞ ስያሜውም የሆነ ትርጓሜው፤ ምዳቤውም ሆነ ብያኔው ከሌላ ነውና:: እዚህ እያወራንለት የምንገኘው፤ እንዲሁም የዘመነ ኮሮና ቀውስ ይህንን ስለማያሳይ እንለፈው።
የባለቅኔ ሰይፈ መታፈረሪያ ፍሬውን ገላጭና መሳጭ አባባል – “ሙዝ ላጥ ዋጥ” – እንጠቀምና አመራርም ሆነ ህዝብን ያህል ነገር ማስተዳደር፤ አገርን ያህል ጉድ ከላይ ሆኖ መምራት ሙዝ ላጥ ዋጥ ሳይሆን ከፍተኛ አቅምን፣ ከራስ በላይ ላገርና ለህዝብ ማሰብና እራስን አሳልፎ መስጠትን ሁሉ የሚጠይቅ ከባድ ውሳኔ እንጂ ሙዝን ላጥ አድርጎ ዋጥ እንደማድረግ አይነት የቀለለ አይደለም። በመሆኑም ይመስላል አመራርን በ”ሙዝ ላጥ ዋጥ” ደረጃ የተመለከቱና የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ያልተረዱ አመራሮች ህዝባቸውን ለወረርሽኝ አሳልፈው በመስጠት የዘመናቸውን ትራጀዲ እያስመዘገቡ ያሉት። ገራሚው አሳልፈው የመስጠታቸው ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ ከሁሉም አስገራሚው ጉዳይ አለሁልህ፣ አይዞህ፣ እስከ መንግስተ ሰማያት ድረስ አብሬህ ነኝ ሲሉት የነበረን ህዝብ እያለቀ ሁሉ እነርሱ በኋላ፣ እጅግ ዘግይቶ በኋላ ሊደርስ በሚችል ጉዳይ ላይ ሲነታረኩ መስተዋላቸው ነው።
በድሮ በሬ ያረሰ የለም እንደሚባለው ሁሉ፤ የአሰቃቂው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት “ቀድሞ የነበሩና አንድን መሪ ያገነኑ አሠራሮች በአሁኑ ሰዓት ከምንም የማይቆጠሩ ተራ” እንዲሆኑ አድርጓቸዋል በማለት አስተያየታቸውን እንደሚጀምሩት ግሌይ ሊዮፕሲስ ከሆነ በቀድሞው ጊዜ መሪዎችን ጀግና፣ ቆራጥ፣ ፈላስፋ፣ የተማረ፣ ዲሞክራት፣ ህዝባዊ፤ አንድንም አገር ሃያል፣ የበለፀገ ያሰኙ የነበሩ መስፈርቶችና መለኪያዎች በአሁኑ ኮሮናቫይረስ ዘመን ምንም ብቻ ሳይሆኑ እጅግ ተራ፤ ጭራሽም እንደ መስፈርት ሊቆጠሩ የሚገባቸው እንኳን ሆነው የማይገኙ ሆነዋል። እነዚህ እና መሰል መስፈርቶች እንደ ድሮው ሊያስሞግሱና ሊያስመርጡ ቀርቶ “አመራር፣ መሪ፣ ፖለቲከኛ” ለማስባል እንኳን ከቁብ የሚገቡ አይደሉም።
ግሌይ “ቀውስ አዳዲስ መንገዶችን የማሳየት፣ እራስን ለማረምና ለማጠናከር፤ እንዲሁም አመራር ማለት በትክክል ምን ማለት እንደሆን ለመገንዘብ ዕድል የሚሰጥ መውጫ መንገድ አለው፤ አሳይቷልም።” እንዳሉት ኮቪድ ያመጣው ቀውስም የዚህኑ አይነት ዕድል እየሰጠ ይገኛል፤ በተለይ ለተተኪ አመራሮች። ጸሐፊው እንደሚሉት አለማችን ከዚህ በኋላ የሚያስፈልጓት ከፍተኛ የአመራር ብቃትና ችሎታ ያላቸውን አመራሮች እንጂ በተለያዩ ብልጣብልጥ ዘዴዎች ወደ ሥልጣን ምኩራብ ላይ የተንጠላጠሉና ህዝብን ለከፋ እልቂት የሚዳርጉ መሪዎችን አይደለም። “ተወደደም ተጠላ” የሚሉት የአመራርና ስትራተጂክ ዕቅድ አማካሪው ግሌይ “በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት፣ ተሰሚነትና ተወዳጅነት ያላቸውና ከፍተኛ ተጽዕኖ በመፍጠር ለውጥ ማምጣትና ህይወትን ከእንደዚህ አይነቱ የከፋ እልቂት ማዳን የሚችሉ የታችኛው እርከን መሪዎች፤ እነሱ በትክክልም የላይኛውን ቦታ ሊመጥኑ የሚችሉ መሪዎች ናቸው።”
ከዚህ በኋላ የሥልጣን የበላይነትን፣ የግል ብልጽግናንም ሆነ ረግጦ ለመግዛት ያለን ድብቅ ስሜት በልብ ቋጥሮ አገርም ሆነ ተቋም፤ ባጠቃላይ ህዝብ እመራለሁ ማለት ተሟጦ ያለቀለት መሆኑን ሁሉም “መሪ ነኝ፤ ወይም እሆናለሁ” ባይ ከወዲሁ ሊያውቀው ይገባል። ምክንያቱም ህዝብ በወሳኝ ጊዜ፣ በህይወትና ሞት ጊዜ፣ በመኖርና አለመኖር ድንበር ላይ በቆመበት ክፉ ጊዜ ትክክለኛ መሪ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለይቶ አውቋልና ከዚህ በኋላ ያለው የመሪነት ሚና ይህንን ሁሉ ታሳቢ ያደረገ መሆን እንደሚገባ ላፍታም ሊረሳው አይገባም። ባለፈው ማክሰኞ አንድ የዓለም ጤና ድርጅት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊም ያሉት ይህንኑ ነው። እንደሳቸው አገላለፅ “ከዚህ በኋላ በድሮው የአኗኗር ሥርዓት ለመኖርም ሆነ ለመምራት መሞከር የዋህነት ነው፤ ለአዲስ አይነት የአኗኗር ዘይቤ እራስን ማዘጋጅት ይገባል።”
በተለያዩ አገራት መሪዎች ጦርነት መሆኑ የተነገረለት ኮሮናቫይረስ ያመጣውን እልቂትና ህዝብን ለማዳን የተወሰደውን እርምጃ በቅርብ ሲከታተሉ የነበሩት ግሌይ ሁኔታው ውስጣቸውን እንደነካውና ሁኔታውንም በሙያዊ ዓይን በመመዘን ያዩትን “የቀድሞው የአመራር መለኪያ መስፈርት የነበረው እና በማዘዝና መቆጣጠር፤ በመዋቅርና ሚስጥራዊ አሠራር ላይ የተመሠረተው የአመራር ሰጪነት ሞዴል ሲገረሰስ እያየን ነው” ሲሉ የገለፁት ሲሆን ኮሮናቫይረስ ምን ያህል ነገሮችን ላዩን ታች፤ ታቹን ላይ አደረጎ እንደቀያየራቸው ይናገራሉ።
ግሌይ ከመንግሥት ለህዝብ የሚሰጠውን ትእዛዝና መመሪያ “standardization” ሲሉት ያ መመሪያ ከታች ወርዶ በቤት ደረጃ ተግባራዊ ሲደረግ ደግሞ “personalization” ይሉታል። ለምሳሌ “ከቤት አትውጡ” የሚለውን መመሪያ/ትእዛዝና ከቤት ባለመውጣት ያንን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግን፤ እንዲሁም እቤት ውስጥ ራሱን ለተሰጠው መመሪያ ተገዥ በማድረግ ከቤት የማይወጣውን፤ ነገር ግን የተለያዩ የግል ሐሳቦችን በተለያዩ የኢንተርኔት መረቦች የራሱን፣ ይሆናል ይበጃል የሚለውን አስተያየቱን የሚሰጠውን ደግሞ “individuality” በማለት ከፋፍለው ያዩት ሲሆን በግለሰብ(ቦች) በኩል ያለውን እንደ ግል አስተያየት በማየት ያልፉትና በመንግሥት በኩል ያለውን ግን በእጅጉ ይተቻሉ። ትችቱም በጥቅሉ “የአሜሪካ ህዝብ ከአሜሪካ መንግሥት ወቅቱ የሚፈልገውን አመራር አላገኘም” የሚል ሲሆን፤ “የአሜሪካ መንግሥት ስህተቶችን ለማረም ከዚህ በላይ ጥሩ አጋጣሚ የለምና ራሱን ይመርምር፤ ከነበረው ብልሹ አሠራርም ይውጣ፤ ህዝቡም ከመንግሥት ማግኘት ያለበትን አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግ ጊዜው አሁንና አሁን ብቻ ነው” ሲሉም አቋማቸውን በደማቁ ያሰምሩበታል።
ሌላውና በኮሮናቫይረስ ምክንያት የወቅቱ አመራር የተፈተነበትን ሁኔታ የቃኘው ደግሞ የዕለት ተዕለት ዜናና ዘገባዎቹን ሙሉ ለሙሉ በወቅቱ ገዳይ ወረርሽኝ ኮሮናቫይረስ ላይ ያደረገው ሲኤንኤን (CNN) ቴቪ ጣቢያ ሲሆን በየዕለቱ ከሚተነትነው የህዝብ አስተያየት መረዳት የሚቻል አቢይ ጉዳይ ቢኖር በአሁኑ ሰዓት አሜሪካ ውስጥ ብቃት ያለው አመራር አለ ለማለት የማይቻል መሆኑን ነው። ከ45 ሺህ በላይ ሟቾች ባሉበት አገር ምኑን ነው ጥሩ አመራር አለ የሚባለው?” በማለት ተስፋ በቆረጠ ስሜት ከሚናገሩ የፖለቲካ ተንታኞችና አስተያየት ሰጪዎች ጀምሮ ፕሬዚዳንት ትራምፕ “በጥሩ ሁኔታ እየተሠራ ነው” ያሉትን “ፍፁም ውሸት ነው፤ ምንም እየተሠራ አይደለም” እስከማለት የደረሱ የስቴት ገዥዎች መኖራቸውን ከጣቢያው ስንመለከት አመራር፣ አመራር ሰጪነትና የህዝብ ተጠቃሚ መሆን/ያለመሆን ጉዳይ ምን ያህል አጣብቂኝ ውስጥ እንደገቡና ኮሮናቫይረስም መሪዎችና ዝግጅታቸውን ምን አይነት ቅርቃር ውስጥ እንደከተታቸው ጥሩ ማሳያ ነው።
በዚህ በአንድ ወር ውስጥ ወረርሽኙን በተመለከተ በአመራር ሚናቸውና ባስመዘገቡት ውጤት የተወገዙ (በእንዝህላልነት ጣሊያን፣ አሜሪካ፣ ስፔን፣ ብራዚል ወዘተ) የመኖራቸውን ያህል፤ህዝባቸውን ከአሰቃቂው ቸነፈር የታደጉ (እንደታይዋን፣ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ወዘተ) አሉ።
“ODI” የተባለ ድርጅት (https://www.odi.org) በለቀቀው ጥናት (Ben Ramalingam, Leni Wild and Matt Ferrari በጋራ ያጠኑት) እንዳመለከተው በአሁኑ ሰዓት ኮሮናቫይረስ ያስተማረን ነገር ቢኖር በድሮው የአመራር ፈሊጥና ስልት መሄድ እንደማንችልና በፍጥነት መለወጥ የግድ መሆኑን ነው። ከዚህ በኋላ ያለው አመራር እንደድሮው በእኔ አውቅልሀለሁ ብቻ የሚኬድበት፣ አንድን አገር ከሌላው ባገለለ መልኩ ውሳኔ የሚሰጥበት፣ እኔ ነኝ የበላይ በሚል ትምክህት የሚዘባነኑበት ሳይሆን ሳይንሳዊ አሠራርን፣ ፖሊሲዎችን ባማከለና የሕብረተሰብ ተሳትፎን ባጣመረ መልኩ የሚሠራበት ነው። ይህ ደግሞ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የወቅቱ ጥያቄና የህዝቦች የህልውና ጉዳይ ነው።
ግርማ መንግሥቴ