አሊባባ – የዓለም የችርቻሮ ንግድ ሥርዓትን የቀየረ

ወዲህ ሀገራችን የችርቻሮም ሆነ የጅምላ ንግድን ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ማድረጓን ተከትሎ የቻይናው ግዙፉ የችርቻሮ ኩባንያ የጃክ ማው አሊባባ እህት ኩባንያ አሊኤክስፕረስ ወደ ሀገራችን ሊገባ እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል። አሊ ኤክስፕረስ ቻይናው አሊባባ የበይነ መረብ የሸቀጦች የጅምላ መገበያያ ኩባንያ በኢትዮጵያ ለመሠማራት ዝግጅት ላይ መኾኑን በዚያ ሰሞን አዲስ አበባ ላይ ባዘጋጀው የማብሰሪያ መድረክ ይፋ አድርጓል። በኢትዮጵያ ግብይት ለመጀመር ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ከስምምነት ላይ የደረሰው፣ የአሊባባ ኩባንያ አካል የኾነው አሊ-ኤክስፕረስ የተሰኘው ኩባንያ ነው።

ኩባንያው በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ መሠማራቱ፣ ለሸማቾችና ነጋዴዎች በዓለም ገበያ ምርቶችንና አገልግሎቶችን ለመገበያየትና ኢትዮጵያን ይበልጥ ወደ ዓለም አቀፍ ንግድ ለማስገባት እንደሚያስችል የተመለከተ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኩባንያው የበይነ መረብ መገበያያ አገልግሎት የሚሰጥበትን ማዕከል አዘጋጅቷል ተብሏል። ካለው ግዙፍ አቅምና ልምድ አንጻር በኢትዮጵያ የችርቻሮ ንግድ ላይ ማርሽ ቀያሪ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። የሀገራችን ቸርቻሪዎችም አቅማቸውን አስተባብረው ለመፎካከር ሊዘጋጁ ይገባል።

በነገራችን ላይ መስኩ ለውጭ ኩባንያዎችና ዜጎች ክፍት ከሆነ ወራት ያለፉ ቢሆንም አሊ ኤክስፕረስ ወደ ሀገራችን ለመግባት የወሰነው የውጭ ምንዛሬ በገበያ እንዲወሰን ከተደረገ በኋላ ነው። ይህ የገንዘብ ፖሊሲው ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ያለውን ሚና ያሳያል። እኔም ከቻይና ጋር የሚኖረን ወቅታዊ የኢኮኖሚ ግንኙነትን ለመቃኘት ቢያግዝ በሚል አሁናዊ የቻይናን ኢኮኖሚ የሚገመግም ጽሑፍ ላጋራችሁ ወደድሁ።

ወዲያ የቻይና የፋብሪካና የኢንዱስትሪ ምርቶችና ውጤቶች በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ገበያ ፈላጊ አጥተዋል። ረክሰዋል። ኧረ እንዲያውም ጥንባቸውን ጥለዋል እየተባለ በስፋት እየተለፈፈ ነው። የሀገራችን አስመጭዎች ግን ዋጋ እየቆለሉ እጥፍ ስንጥቅ እያተረፉ ሸማች እየገፈፉ ባለበት አሊባባ ሲገባ ምን እንደሚውጣቸው አብረን የምናየው ሆኖ፤ ቻይና የዓለም ገበያ ከሚፈልገው በላይ አምርታ ገበያ አጥታ እንዲያውም አንዳንዶች እንደሚሉት መጣያ አጥታ ባለችበት ነውና አሊባባ የሚመጣው ይሄን መልካም አጋጣሚ ሳያሳልፍ ብሔራዊና የሸማቹን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ መዋዋል ይገባል።

እንደ “ፎሪን አፊርስ” መጽሔት በአንድ ጊዜ የሲአይኤ፣ የኋይታወስ፣ የፔንታገን ቤተኛ የሆነ መጽሔት የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። እንዲሁም ዓለም አቀፍ ግንኙነት የሚቃኝበት፤ ጂኦፖለቲካ የሚተነተንበት፤ የምዕራባውያን ትኩረት የሚመላከትበት ከመጽሔት የተሻገረ ስትራቴጂያዊ ሰነድ ነው። የቻይና ኢኮኖሚ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነው። መጀመሪያ ይትበሀሉ ፈረንሳይ ስታስነጥስ የተቀረው ዓለም ጉንፋን ይይዘዋል ነበር። ከዛ አጎት ሳም ሲያስነጥስ አሜሪካ ለማለት ነው የተቀረው ዓለም ጉንፋን ይይዘዋል ነበር። አሁን ደግሞ ቻይና ጃፓንን ፈንቅላ ሁለተኛው የዓለማችን ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ መሆኗን ተከትሎ ይትበሀሉ ተከትሏታል።

ቻይና ካለፉት አስርት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ቀርፋፋ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ነው። በዓለም ላይ ካሉት ትላልቅ ኢኮኖሚዎች አንዷ ሆና ብትቀጥልም፣ ዓመታዊ የሀገር ውስጥ ምርቷ ቀንሷል። ትንበያዎች ቢለያዩም በአጠቃላይ ከ4 እስከ 5 በመቶ አካባቢ ሊቀንስ ይችላል እየተባለ ነው። ኢኮኖሚው ከኮቪድ-19 ተጽእኖዎች በማገገም ላይ ነው። እንደ አገልግሎት እና ማኑፋክቸሪንግ ያሉ ዘርፎች ቀስ በቀስ እያንሰራሩ ናቸው። ይሁን እንጂ በሌሎች ዘርፎች የወረርሽኙ አንጎቨር አለቀቃቸውም።

የቻይና ኢኮኖሚ ጉልህ አካል የሆነው የሪል ስቴት ሴክተር፣ በንብረት አልሚዎች ከመጠን ያለፈ ብድር ላይ የተወሰደ ባለ እርምጃ እና የቤት ዋጋ ማሽቆልቆሉን ጨምሮ በርካታ ተግዳሮቶች ገጥሟቸዋል። የሸማቾች መተማመን አሽቆልቁሏል። በዚህ የተነሳ ኢንቨስትመንት ተቀዛቅዟል። ቻይና የዓለም አቀፍ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ሆና ቆይታለች። ነገር ግን ከአሜሪካ እና ከሌሎች ሀገራት ጋር ባለው የንግድ ውጥረት የተነሳ ፈተና ገጥሟታል። የጂኦፖለቲካ ጉዳዮች እና የአቅርቦት ሰንሰለት መስተጓጎል የወጪ ንግድ ዕድገት ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ ቀጥሏል።

በሰው ሠራሽ አስተውሎት AI፣ ሴሚኮንዳክተር ምርት እና አረንጓዴ ቴክኖሎጂዎችን ጨምሮ በቴክኖሎጂ ዘርፎች ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ላይ ትገኛለች።እነዚህ ኢንቨስትመንቶች ተወዳዳሪ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ እና ፈጠራን ለማጎልበት ወሳኝ ተደርገው ቢወሰዱም ከገበያ ፍላጎት በላይ እየተመረቱ መሆናቸው መጋዘን እያጣበቡ ነው። ሌላው የኩባንያዎችና የአካባቢ አስተዳደሮች ዕዳ ቁልል አሳሳቢ ሆኖ ቀጥሏል። ይህንን ዕዳ ለመቆጣጠር እና ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት የተሳካ አይመስልም። ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት ተስኖታል።

ለዓመታት ትከተለው የነበረ የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ የአረጋውያንና የጡረተኞች ምድር አድርጓታል። ይህ ደግሞ የአምራች ኃይል እጥረት እንዲገጥሟት አድርጓል። ይሄን ክፍተት ለመሙላት አገዛዙ የወሊድ መጠንን ለማበረታታት የተቀናጀ ርብርብ እያደረገ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት የሚያመጣ አይመስልም ይላሉ ኢኮኖሚውን በቅርብ የሚከታተሉ ተንታኞች ሰሞኑን የአሜሪካው የውጭ ግንኙነቶች ምክር ቤት ተመራማሪ እና የ “Sovereign Funds: How the Communist Party of China Finances Its Global Ambitions.” መጽሐፍ ደራሲ ዞንግዩዋን ዞኢ ሊኡ፤ የቻይና ኢኮኖሚ ቅርቃር ውስጥ ነው ይሉናል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2022 መገባዳጃ ላይ ቻይና ከኮቪድ ሙሉ በሙሉ ነፃ የመሆን ወይም “zero COVID” ፖሊሲዋን እርግፍ ማድረጓን ስታውጅ የቻይና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያንሰራራል ብለው ገምተው ነበር። በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሳቢያ ለዓመታት ጥርቅም ተደርጎ ከውስጥ ተዘግቶበት የነበረው የአለማችን ሁለተኛው ኢኮኖሚ ሲከፋፈት ፈጥኖ ይነቃቃል ተብሎ ተጠብቆ የነበር ቢሆንም እየሆነ ያለው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው።

ኢኮኖሚው ከማገገም ይልቅ በአለበት መርገጥና መንሸራተት ጀመረ። ኢኮኖሚውን ያስፈነጥራሉ ተብለው ተጠብቀው የነበሩት እንደ ሪል ስቴት ያሉ ዘርፎች ማሽቆልቆሉን ተያያዙት። ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት GDP ዕድገት መንቀራፈፍ፤ የሸማች የሸመታ ፍላጎት ማጣት፤ ከምዕራባውያን ጋር የገባችበት እሰጥ አገባ መባባስ፤ የሪልስቴት ዋጋ መርከስ ትላልቅ ኩባንያዎችን ለኪሳራ መዳረጉ የቻይናን ዕድገት አቀዛቅዞታል። ለበርካታ አስርት ዓመታት ባለ ሁለት አኃዝ ተከታታይ ዕድገት እንዳላስመዘገበች አሁን በአምስት በመቶ እንኳ ለማደግ ተቸግራለች።

ለተከታታይ ዓመታት የሪል እስቴት ኢኮኖሚው ከገባበት ቀውስ መውጣት አለመቻሉ፤ የአረጋውያንና የተጧሪ ሀገር መሆኗ፤ ኢኮኖሚዋ በፕሬዝዳንት ዢ ጅንፒንግ መዳፍ ስር መውደቁ እና በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት ኢኮኖሚዋን ሙሉ በሙሉ ጥርቅም አድርጋ መዝጋቷ ኢኮኖሚዋን አሽመድምዶታል ይለናል ፎሪን አፊርስ።

ሌላው ለዛሬው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የዳረጋት ትከተለው የነበረው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከምንም በላይ ኢንዱስትሪው ላይ ያተኮረ መሆኑ ኢኮኖሚያዊ መዋቅሯን ከማጎበጡ ባሻገር እዳ በእዳ አድርጓታል ይሉናል ዞንግዩዋን ዞኢ ሊኡ።

በአጭሩ ይላሉ ጸሐፊው ቻይና የምታመርተው ገበያው ከሚፈልገው በላይ ነው። በዚህ የተነሳም ዋጋ ሲወረድ፣ እዳን መመለስ ፈተና ስለሚሆን ፋብሪካዎች መዘጋትና ሠራተኛ ወደ መበተን ይገባሉ። ይሄ ደግሞ ለአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ መቀዛቀዝ ዳርጓል። ከ2010 ዓ.ም ወዲህ ርካሽ የቻይና የኢንዱስትሪ ውጤት የዓለም ገበያን በማጥለቅለቁ ለዓለም ሳይቀር ስጋት እየሆነ ነው ይሉናል ጸሐፊው።

በአብነትም ባለፈው ዓመት በወርሀ ታኅሣሥ የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሶላ ቮን ደር ሌየን ርካሽ የሆነው የቻይና ምርት ቀጣይነት የሌለው የንግድ ጉድለት ከመፍጠሩ ባሻገር ገበያውን በማጥለቅለቁ ሌሎች ሀገራትን ከገበያ እያስወጣ ነው ሲሉ ይከሳሉ። የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር እነሱ የትሬዠሪ ሴክሬታሪ ይሏቸዋል ያኔት የለን ባለፈው ሚያዝያ እንዲሁ ቻይና ብረት፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪና ሌሎች ምርቶች ላይ ግዙፍ መዋዕል ንዋይ በማፍሰሷ ኢኮኖሚያዊ መፈናቀልን እያስከተለ ከመሆኑ ባሻገር ከገበያው የተትረፈረፈ ሸቀጥ እያቀረበች ነው ሲሉ አምርረው ይተቻሉ።

ቻይና ክሱን ደጋግማ ብታስተባብልም ሀቁ ግን ቻይና ዛሬም የዓለምን ገበያ እያጥለቀለቀች ነው። ለፖለቲካዊ አላማ ስትል ሸቀጦችን ከማምረቻ ዋጋቸው ባነሰ እየቸበቸበች ነው። ኮሚኒስት ፓርቲው ፋብሪካዎች ገበያው ከሚፈልገው በላይ እንዲያመርቱ ዛሬም ጫና ያደርጋል። ይህ በአጋጣሚ የተደረገ ሳይሆን የፓርቲው የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ራዕዩ አካል ነው ይለናል ፎሪን አፊርስ መጽሔት።

አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን ኢኮኖሚያቸውን ከቻይና የርካሽ ሸቀጥ ማራገፊያነት ለመከላከል አዳዲስ የንግድ ገደቦችን እየጣሉ ነው። ከዚህም በላይ ቻይናን ከዓለም አቀፍ ገበያው ለመነጠል ተቀናጅተው እየሰሩ ነው። ሆኖም ይህ ውሳኔያቸው የገዛ ኢኮኖሚያቸውን ሊጎዳ ይችላል ይሉናል ጸሐፊው ዞንግዩዋን ዞኢ ሊኡ።

ጸሐፊው በነገራችን ላይ ብለው ሰነድ ያገላብጣሉ። በነገራችን ላይ የቻይና ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ችግር የሚጀምረው የቻይና ዕድገት አባት በመባል የሚታወቁት ዴንግ ዣውፒንግ የስድስት ጊዜ የአምስት የአምስት ዓመት የኢኮኖሚ ዕቅዶችን በ1981 ዓ.ም ይፋ ካደረጉ ወዲህ ይሉናል። ይህ ከ100 ገጾች በላይ የያዘ ዕቅድ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ ስለ ቻይና ኢንዱስትሪ መስፋፋት፤ ስለ ዓለም አቀፍ ንግድን ማሳደግ፤ በቴክኖሎጂ ስለመዘመን ያወሳል እንጂ ስለ ዜጎች ገቢ መጨመርና ስለ ፍጆታ ግን በአንዲት አጭር አንቀጽ ነው የሚዘለው። የኢኮኖሚው ስብራት የሚጀምረው ከዚህ ነው ይለናል መጽሔቱ። በዓለማችን ቴክኖሎጂው እየዘመነና እየረቀቀ፤ ገበያው ከቀደመው ዘመን የተለወጠ ቢሆንም የቻይና የኢኮኖሚ ዕቅድ ግን ያው የተትረፈረፈ ምርት ማምረትና ገበያው ማጥለቅለቅና መቆጣጠር ላይ ያተኮረ ነው።

አሁን ሥራ ላይ ያለው 14ኛው የአምስት ዓመት ዕቅድ ወይም የ2021-2025 ኢኮኖሚያው ፕላን እንኳ ያው የተትረፈረፈ ምርት ላይና የውጭ ገበያ ላይ የተንጠለጠለ ነው ይሉናል ጸሐፊው። የሀገር ውስጥ ገበያውን የዘነጋና ትኩረት የነፈገ መሆኑ ለውጭ ገበያ ጥገኛ አድርጎታል። የውጭው ዓለም ደግሞ ቅድሚያ ለራሱ ኢንዱስትሪዎች ምርት መስጠት በመጀመሩ እንዲሁም በተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምክንያቶች ለቻይና ምርቶች ፍላጎት እየተቀዛቀዘ መምጣቱ ግዙፉ ኢኮኖሚ ለአደጋ ሊጋለጥ ችሏል።

የቻይና የብረት ምርት ከጀርመን፣ ከጃፓንና ከአሜሪካ አጠቃላይ ምርት ይበልጣል። እንዲሁም የድንጋይ ከሰል፣ የአልሙኒየም፣ የሮቦት ግብዓቶች፣ የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ ምርቷ ከእነዚሁ ሀገራት ይበልጣል። የዓለማችን ገበያ ከሚፈልገው የሶላር ፓናል ከእጥፍ በላይ አምርታለች። ገበያ ግን የላትም። ከ27 እስከ 32 በመቶ የቻይና መኪና አምራቾች ያለ ትርፍ ነው ሽያጭ የፈጸሙት። የምርት መትረፍረፍ ዋጋን እያረከሰው፤ የዋጋ ግሽበቱን ወደ ዜሮ እያወረደው፤ እዳ ጣራ እየነካ፤ የሸማቹ በራስ መተማመን እየቀነሰና ከሸመታ እየታቀበ ስለሆነ የሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንዳይወርድ ወይም ዲኢንፍሌሽን እንዳይከሰት ያሰጋል ይሉናል ጸሐፊው ዞንግዩዋን ዞኢ ሊኡ።

ከገበያው ፍላጎት በላይ ማምረቷ የዋጋ ግሽበቱን ወደ ዜሮ ከማውረዱ ባሻገር፤ በተቃራኒው የዕዳ ክፍያ ምጣኔው ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ይህ ክስተት ሸማቹ ከሸመታ እንዲቆጠብ ስለሚያደርግ አጠቃላይ ፍጆታ እንዲቀንስ በማስከተልም የሸቀጦች ዋጋ እንዲረክስ ያደርጋል።

የቻይና የበታች ሹማምንት በኮሚኒስት ፓርቲው ከፍተኛ አመራር ሞገስ የሚያገኙት የሚሸለሙትና የሚሾሙት በከተማቸው ወይም በክልላቸው የመንግሥትን የኢንዱስትሪ ፖሊሲ አቅጣጫ የተከተለ ኢንቨስትመንት በእነሱ የብድር ዋስትና ሲያስፋፉ እንጂ አዋጭ ኢንቨስትመንትን በማድረግ ስላልሆነ ከገበያውና ከሸማቹ ፍላጎት በላይ ምርት ሊከማች ችሏል። ባለፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች ደግሞ ለምርቶቻቸው ገበያ ባለማግኘታቸው እዳቸውን መክፈል አልቻሉም።

የአሜሪካው “ዘ ዎል ስትሬት ጆርናል” በሰራው የምርመራ ዘገባ የየአካባቢው አስተዳደሮች እዳ ከ7 እስከ 11 ትሪሊየን ዶላር ሲገመት ከዚህ ውስጥ 800 ቢሊየን ዶላሩ የተበላሸ ብድር ነው ይለናል። በነገራችን ላይ የአካባቢው አስተዳደሮች ዕድ የቻይና ጥቅል ሀገራዊ ምርት GDP ግማሽ ነው ማለት ይቻላል። የቻይና የአካባቢ አስተዳደሮች ከምዕራብ እስከ ምስራቅ ከዢንጂያንግ እስከ ሻንጋይ፤ ከሰሜን እስከ ደቡብ ሔሎንግጂያንግ እስከ ሀይናን የኮሚኒስት ፓርቲውን የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ለማስፈጸም እርስ በርስ ሲፎካከሩ ገበያውን በተመሳሳይ ምርት አጥለቅልቀውት አረፉ።

እንደ አብነት እናንስ ይላሉ የፎሪን አፊርስ ጸሐፊ ዞንግዩዋን ዞኢ ሊኡ፤ ቻይና በየዓመቱ ዓለማችን ከሚያስፈልገው የሶላር ፓናል በእጥፍ ታመርታለች። የቻይና መንግሥት ምክር ቤት 2010 ዓ.ም ላይ እስከ 2020 የጸሐይ ኃይል ወይም ሶላር ፓወር የGDP 15 በመቶ ድርሻ ሊኖረው እንደሚገባ መመሪያ አወረደ። በሁለት ዓመት ውስጥ ከሀገሪቱ 34 ግዛቶች 31ዱ የጸሐይ ኃይል ግብዓት ምርት መናኸሪያ ሆኑ። 100 የግብዓት ማምረቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገነቡ። ወዲያው ምርቱ ከሀገር ውስጥ ገበያው ፍላጎት በላይ ሆነ። በመቀጠል የአውሮፓንና የአሜሪካን ገበያ ማጥለቅለቅ ጀመሩ። በ2013 ዓ.ም አሜሪካና አውሮፓ ከቻይና በሚገቡ የሶላር ፓናሎችና ሌሎች የጸሐይ ኃይል ማምረቻ ግብዓት ላይ ከፍተኛ ታሪፍ ጣሉ።

ቻይናስ ምኗ ሞኝ ነው። ይሄን ታሪፍ ለማምለጥ ምርቷን ወደ ካምፓዲያ፣ ማሌዥያ፣ ታይላንድ፣ ቬትናምና ሌሎች ሀገራት አዛወረች። በነሐሴ 2023 የአሜሪካ ኮሜርስ ይሄን የቻይና ሸፍጥ ደረሰበትና አስቆመው። የፎሪን አፊርስ ጸሐፊ ቀጥለዋል። ቻይና በ”2025 ዓ.ም Made in China” በሚለው ስትራቴጂዋ ከ2015 ዓ.ም ለበሮቦቲክስ ትኩረት መስጠት ጀመረች። ይሄ ስትራቴጂዋ እውን እስኪሆን ከጃፓን በላይ የዓለማችንን የሮቦቲክስ ኢንዱስትሪ ሸማች ነበረች።

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን መስከረም 9/2017 ዓ.ም

Recommended For You